በዚህ አገር የሥራ አጥ ቁጥር ለመብዛቱ ዋናው እና ትልቁ ምክንያት ወጣቱ ሥራ ፈጣሪ ለመሆን የሚያደርገው ጥረት ደካማ መሆኑ ነው:: አብዛኛው ወጣት የሚማረው በአንድ ተቋም ውስጥ ተቀጣሪ ለመሆን ነው:: አነስተኛ ቢዝነስ ብጀምር ትልቅ ቦታ እደርሳለሁ የሚለው አስተሳሰብ በአገራችን በአብዛኛው ወጣት ዘንድ እምብዛም አይስተዋልም:: በዚህ ረገድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መጠነኛ ለውጦች መኖራቸው ባይካድም አሁንም በጣም ብዙ ይቀረናል:: ወጣቶች ሁለት እና ሦስት ሆነው የራሳቸውን ቢዝነስ የመፍጠር አስተሳሰብ እዚህ አገር ላይ ገና አልዳበረም:: እርግጥ አጠቃላይ ፖለቲካ ኢኮኖሚውም ጥሮ-ግሮ በማደግ ላይ ሳይሆን በአጭር ጊዜ በአቋራጭ መንገድን ሲያበረታታ የቆየ ነው:: የአስተሳሰብና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ ያስፈልጋል:: በላቡና በወዝ ጥሮ- ግሮ ማደግ መለመድና መበረታታት አለበት:: በመንግሥት በኩልም የግሉን ዘርፍ የሚያይበት መነፀር መስተካከል አለበት:: ያለ ግሉ ዘርፍ ዕድገት አገር ዕድገት ብሎ ነገር የማይታሰብ ነው::
መንግሥት ያለውን ሀብት ከገበያው ጋር በማገናኘት የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማድረግ ላይ ብዙ ሥራ መሥራት እንዳለበት ይሰማኛል:: አሁን ላይ ብድር በማመቻቸት እና ወጣቶች የራሳቸውን የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ የማድረጉ ሁኔታ ብልጭ ድርግም በሚል በልኩ አልፎ አልፎ ይታያል:: እነዚህ እንቅስቃሴዎች መጎልበትና ተጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል::
በአገራችን ከፍተኛ የሆነ የምርት እጥረት እንዳለ ይታወቃል:: በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ ናት:: ከእንዲህ ዓይነቱ ጥገኝነት ነጻ መውጣትና ራስን መቻል ያስፈልጋል:: ከውጭ ምርት ጥገኝነት ነጻ መሆን የሚቻለው ወጣቶች ከውጭ የሚገባውን ምርት እዚሁ በአገር ውስጥ ምርት መተካት ሲችሉ እና አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ሲፈጠሩ ብቻ ነው::
መንግሥት እንደ መንግሥት የክህሎት ግንባታ ላይ እና የብድር አቅርቦት ላይ ጠንክሮ መሥራት ይገባዋል:: እንደ ቻይና ባሉ አገሮች ላይ የሚታየው አዲስ ሥራ የመፍጠር ባህል እና ልምድ እዚህም አገር በስፋት መለመድ መቻል አለበት:: ሥራ የመፍጠር ባህል እንዲኖር በትውልዱ ላይ በደንብ መሠራት አለበት:: ከትንሽ ቦታ ተነስቶ ትልቅ ቦታ መድረስ ይቻላል የሚለው አስተሳሰብ በወጣቱ ላይ መኖር አለበት:: ይህን አስተሳሰብ መፍጠር ካልቻልን ለዚህ ሁሉ ወጣት መንግሥት የሥራ ዕድል እየከፈተ ይሰጣል ማለት አይችልም:: አቅምም የለውም:: የመንግሥት ድርሻ ምቹ ሜዳ ማመቻቸት ነው:: በተሰጠው ሜዳ ላይ የመጫወት እና ያለመጫወት ጉዳይ የወጣቱ ነው የሚሆነው::
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መሠረታዊ ችግር በአንድ በተለመደ ሽክርክሪቱ ውስጥ ለረጅም ዘመናት መቆየት ነው:: ይህ አዙሪት በጣም የተለመደ እና ባህላዊ አካሄድን የተከተለ ነው:: የእኛ አገር ቢዝነስ እንቅስቃሴ ዕድገት ላይ መስፋት ላይ የተመሠረተ አይደለም:: የእኛ አገር ተቋማት ቅርንጫፍ መክፈትና ማደግ ላይ ትኩረት ያደረጉ አይደሉም:: የተለመደችውን ትርፍ እያገኙ በዚያው ሲንከባለሉ መቆየትን አጥብቀው ይወዳሉ:: በኢትዮጵያ ትልልቅ የሚባሉት ተቋማት ሳይቀር ተመሳሳይ መጠን ባለው የሥራ ዘርፍ ላይ ለአምስት ዓመት እና ከዚያ በላይ ቆመው ነው የሚታዩት:: አዳዲስ ነገሮችን መሞከር አዳዲስ የቢዝነስ አጋር (ፓርትነር) መፍጠር ላይ ሰፊ ችግር አለባቸው::
የኩባንያዎች ዕድገት ድምር ውጤት ነው አገር እንዲያድግ የሚያደርገው:: አሁን ላነሳነው ርእሰ-ጉዳይ ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችለው የኖኪያ ሞባይል ምርት ነው:: በአገራችን ገበያ ላይ ከሁሉም ቀድሞ በስፋት የተዋወቀው የሞባይል ምርት ኖኪያ እንደነበር ይታወቃል:: ነገር ግን ተቋሙ ራሱን በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪና ተመራጭ ማድረግ ስላልቻለ ከገበያው ተገፍቶ እንዲወጣ ተደርጓል:: በሒደት ሌላ የአሜሪካ ኩባንያ ጠቅልሎት ስያሜውም በሌላ ተተክቷል:: ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቢዝነስ ተቋም ሁኔታ እንደ ኖኪያ ሞባይል አምራች ኩባንያ ዓይነት ነው:: ራሱን ለውድድር የሚያዘጋጅ አዲስ ነገር ፈጥሮ ገበያው ለመምራት የሚጥር ዓይነት አይደለም:: ከውጭ ትንሽ ነገር ለወጥ አድርገው የሚያመርቱ ተቋማት ሲመጡ በቀላሉ ከገበያው ተገፍተው ይወጣሉ::
ሌላው ምክንያት በእኛ አገር ለጥናትና ምርምር የሚሰጠው ትኩረት በጣም ደካማ መሆኑ ነው:: ኩባንያዎች በተጠና መልኩ ሲሄዱ ነው ገበያውን መቆጣጠር የሚችሉት:: ስለሆነም ለጥናት እና ምርምር ሥራ በጀት መመደብና ገንዘብ ማውጣት ይገባቸዋል:: ጥናትና ምርምር በአንድ ተቋም የሥራ ሂደት ውስጥ መቋረጥ የሌለበት መሠረታዊ ነገር ነው:: ኩባንያው ለጊዜው ውጤታማ እና ጠንካራ ትርፍ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም ጥናት ማድረግ እና የገበያውን ሁኔታ ማየት መቆም የሌለበት ተግባር ነው:: የቢዝነስ ተቋማት ሁልጊዜ ነገን እና ከነገ ወዲያን አሻግረው ማየት መቻል አለባቸው:: የሥራ መስመራቸውን ማስፋት፤ እይታቸው እንዲሰፋ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት አለብን:: የእኛ አገር ቢዝነስ አለማደግ መሠረታዊ ችግር እነዚህ ጉዳዮች በትኩረት አለመታየታቸው ነው:: መኪና ነዳጅ ሲሰጥ ፍጥነት እንደሚጨምር ሁሉ የሥራ እንቅስቃሴም አዳዲስ ሐሳብ ሲታከልበት ነው በሚፈለገው ፍጥነት መብረር የሚችለው:: የሥራ እንቅስቃሴው በአግባቡ ሲቀጣጠል ነው የአገር ኢኮኖሚ የሚያድገው እና የሥራ ዕድል የሚፈጠረው:: አሁን ላይ በአገሪቱ ለበዛው የሥራ አጥ ቁጥር አንዱ ምክንያት በሥራ ላይ ያሉት አምራቾቻች ባሉበት መርገጣቸው ነው::
Leave a Reply