የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስንብት
Uncategorized

የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስንብት

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል::

ፕሮፌሰር መስፍን በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለ10 ቀናት የሕክምና ክትትል ሲደረግላቸው እንደቆየና ባለፉት ጥቂት ቀናት ሕመማቸው እንደበረታ ከቤተሰቦቻቸው የተገነው መረጃ ያመለክታል:: ፕሮፌሰር መስፍን ከአባታቸው አቶ ወልደማርያም እንዳለ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ይመኙሻል ዘውዴ በሚያዚያ ወር 1922 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ተወለዱ::

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን የተከታተሉ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአብነት ትምህርት ተከታትለው ዲቁና አግኝተዋል:: ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደ አውሮፓዊያን የዘመን አቆጣጠር በ1951 በፑንጃብና ቻንዲጋር ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል:: በኢትዮጵያ የገጠር ክፍል የሚኖሩ ዜጎች የረኀብ ተጋላጭነት በተመለከተ ባቀረቡት የመመረቂያ ጽሑፍ የማስተርስ ዲግሪ አሜሪካ፣ ቦስተን ከሚገኘው ክላርክ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል:: ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ሲመለሱም በቀድሞው ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ከ1965 ጀምሮ በጆኦግራፊ የትምህርት ክፍል በመምህርነትና በትምህርት ክፍሉ ሊቀመንበርነት አገልግለዋል:: በ1970ዎቹ መጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዳግም በመመለስ በጡረታ እስከተገለሉበት ጊዜ ድረስ በዩኒቨርሲቲው በመምህርነት አግልግለዋል:: በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ መንግሥት የመጨረሻዎቹ ዘመናት ላይ የአውራጃ ገዥ ሆነው ተሹመው እንደነበርም ታውቋል::

የረዥም ዘመን የአካዳሚክ ሕይወት የነበራቸው ፕሮፌሰር መስፍን በኢኮኖሚ፣ በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ በጅኦግራፊ፣ በሰብአዊ መብቶች፣ በችጋር፣ ረኀብና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችንና መጻሕፍትን አበርክተዋል:: በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ መድረኮች ላይ በመገኘት በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ባገኟቸው መድረኮች ሁሉ ያላቸውን ዕውቀት፣ ልምድና ምልከታ በስፋት አካፍለዋል::

በልዩ ልዩ የምርምር መጽሔቶች (ጆርናሎች) ያሳተሟቸው ጥናታዊ ጽሑፎች እና በየጋዜጣውና መጽሔቱ ያወጧቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጽሑፎች እንደተጠበቁ ሆነው ከታተሙ መጽሐፎቻቸው መካከል በአማርኛ “ዛሬም እንደትናንት”፣ “አድማጭ ያጣ ጩኸት (ቅጽ 1)”፣ “እንዘጭ እንቦጭ የኢትዮጵያ ጉዞ”፣ “አዳፍኔ – ፍርሃት እና መክሸፍ”፣ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ”፣ “ዛሬም እንጉርጉሮ? (ግጥምና ቅኔ)”፣ “ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?” “አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ”፣ “የክህደት ቁልቁለት”፣ “ሥልጣን፤ ባህል እና አገዛዝ”፣ “ፖለቲካ እና ምርጫ”፣ “አገቱኒ ተምረን ወጣን”፣ “እንጉርጉሮ (ግጥምና ቅኔ)”፣ “ልማት፤ ኢትዮጵያዊነት በኅብረት”፤ እንዲሁም በእንግሊዝኛ ቋንቋ “The Horn of Africa: Conflict and Poverty”፣ “Suffering under God’s environment: A vertical study of the predicament of peas­ants in North-Central Ethiopia”፣ “Rural vulnerability of Famine in Ethiopia 1958- 77”፣ “Somalia: The Problem child of Afri­ca”፣ “An atlas of Ethiopia” የተሰኙ መጻሕፍት ይገኙበታል::

 

October 4, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *