የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለንዋይ ፍሰት በኢትዮጵያ | ሳሙኤል ተክለየሱስ
Uncategorized, ኢኮኖሚ

የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለንዋይ ፍሰት በኢትዮጵያ | ሳሙኤል ተክለየሱስ

ሁለተኛውን የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከወራት በፊት ያገባደደችው ኢትዮጵያ፣ በዓለም ባንክ እና ሌሎች መሰል ተቋማት የተመሰከረ ፈጣን የሚባል የኢኮኖሚያ ዕድገት ከሚያስመዘግቡ ጥቂት የአፍሪካ አገሮች መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡ ለረጅም ዓመታት በኋላ ቀር የግብርና ምርት ላይ እና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ተመርኩዞ ሲዘወር የነበረው ኢኮኖሚዋ በሂደት በአገር በቀል አገልግሎት ሰጪ ኢንቨስትመንት እና ከውጭ በሚገኝ የመዋዕለንዋይ ፍሰት ላይ መመርኮዝ እንዳለበት አንዳንድ ምሁራን አጥብቀው ሲሞግቱ ይደመጣል፡፡

የመዋዕለንዋይ ፍሰት በአገር ውስጥ ካሉ ሀብቶች በተሻለ መልኩ ማመንጨት ቢቻል ተመራጭነት እንዳለው እና ጠንካራም የሆነ የኢኮኖሚ መዋቅር ለመፍጠር እንደሚረዳ ጥርጥር የለውም፡፡ ይሁን እንጂ የውጭ ቀጥተኛ የመዋዕለንዋይ ፍሰት አዲስ የሥራ ዕድልን ከመፍጠር እና ለተፈጠረውም ጠንካራ የኢኮኖሚ ድጋፍ ከመስጠት አኳያ የሚኖረው ጉልህ ሚና መዘንጋት የለበትም፡፡ አገራችን ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ በዋነኝነት ተጠቃሽ የሆነው ምክንያት ዘመናዊ የግብርና ዘዴ መተግበር መጀመሩ እና የአምራች ክፍሉ በተደራጀ መልኩ መንቀሳቀስ መጀመሩ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ረገድ የውጭ ኢንቨስትመንት እና የመንግሥት የመሠረተ ልማት ግንባታ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ አገሮች ትልቅ የውጭ ኢንቨስትመንት በመውሰድ በቀዳሚነት ትቀመጣለች፡፡ በአገራችን እንደ አውሮፓዎች አቆጣጠር 2019 ከተፈጠረው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 60 በመቶ ገደማ የሚጠጋውን በማቅረብ ቻይና ቀዳሚ ስትሆን፣ የሳውዲ ዐረብያ፣ የአሜሪካ፣ ሕንድ እና ቱርክ ባለሀብቶች ከቻይና ይከተላሉ፡፡

ግብርና በተለይም አበባ እርሻዎች፣ የጨርቃ ጨርቅ እና ሌጦ ማምረቻዎች ከዚሁ ጋር ተያይዘው የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን አብዛኛውን የመዋዕለንዋይ ፍሰት በመሳብ የአንበሳውን ድርሻ የያዙ የኢኮኖሚ ዘርፎች ናቸው፡፡

የአገራችን የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለንዋይ ፍሰት በደንብ ከመተንተናችን በፊት በዓለም ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንደሚከተለው እንመልከት፡፡ የ2020 የዓለም የመዋዕለንዋይ ፍሰት ሪፖርት  አብዛኛውን በአምራች ዘርፍ ላይ የተፈጠረ የውጭ ኢንቨስትመንትን  በመሳብ የእስያ ቀዳሚ ነች፡፡ ይህንንም ለማሳየት ከ2017 አስከ 2019  የአውሮፓዎች የቀን ቀመር አቆጣጠር በዓለማችን ላይ የነበረውን የውጭ ቀጥተኛ  የመዋዕለንዋይ ፍሰት እንደሚከተለው እንመለከት፡፡

(በዚህ ጽሑፍ ላይ የተቀመጡ ሁሉም አሃዞች በዶላር ሲሆን ዓመተ ምሕረቶቹም በአውሮፓዎቹ የቀን አቆጣጠር ስሌት መሠረት ነው)

2012 2018 2019
ዓለም 1.7 ትሪሊዮን 1.49 ትሪሊዮን 1.54 ትሪሊዮን
እስያ 502 ቢሊዮን 499 ቢሊዮን 474 ቢሊዮን
ሰሜን  አሜሪካ 304 ቢሊዮን 297 ቢሊዮን 297 ቢሊዮን
አፍሪካ 42 ቢሊዮን 51 ቢሊዮን 45 ቢሊዮን
ኢትዮጵያ 4  ቢሊዮን 3.3 ቢሊዮን 2.5 ቢሊዮን
አውሮፓ 507 ቢሊዮን 364 ቢሊዮን 429   ቢሊዮን

ምንጭ፡- የዓለም የመዋዕለንዋይ ፍሰት ሪፖርት 2020 እ.ኤ.አ

ከሰሐራ በታች ያሉ አገሮች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ስንመለከት እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ2019 ወደ 32 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የመዋዕለንዋይ ፍሰት መሳብ ችለዋል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት የ10 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ አብዛኛው ፍሰት የሚቀበሉት እንደ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ላይ የነበረው የአንቨስትመንት መቀነስ ለዚህ ዋነኛ አስተዋጽዖ እንዳደረገ ይገመታል፡፡ ከዚሁም ውስጥ በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ አገሮች ወደ 7.8 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ አገራችን ከባለፈው ዓመት የ2.5 ቢሊዮን ዶላር የቀጥታ መዋዕለንዋይ ፍሰት ከውጭ አገሮች የሳበች ሲሆን፣ ይህም ከዚህ ዓመት በፊት ከነበረው የ24 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ስንመለከት፡-

 

 

        ዓመት ኢንቨስትመንት በቢሊዮን ዶላር ከለፉት ዓመታት አንጻር ያለው ጭማሪ በመቶኛ
2014 1.855 0
2015 2.627 42
2016 4.147 58
2017 4.017 -3
2018 3.310 -18
2019 2.516 -24

 

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚኖረው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በተለይም ኢኮኖሚያቸው በማደግ ላይ ባለ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች የሚኖረው ጉልህ ሚና መገመት አያዳግትም፡፡ ስለዚህም ኢንቨስትመንትን ከአገር ውስጥ እና ከውጭ መሳብ ለተፈጠረው አመርቂ ኢኮኖሚ የዕድገት ጉዞ ወሳኝ ነበር፡፡ በቀላሉ ሰልጥኖ ውጤታማ ከሚሆን ብቁ የሰው ኅይል ለሚገቡ ማሽነሪዎች የቀረጥ ነጻ አገልግሎቶች በመስጠት መንግሥት ባለሀብቶችን ለማማለል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለንዋይ ፍሰት በአንድ አገር  ኢኮኖሚ ላይ  አሉታዊ እና አውንታዊ ተጽዕኖን አለው፡፡ የአዳዲስ ቴክኖሎጂ  ልውውጥ፣  ሥራ ዕድል  ፈጠራ ዋነኞቹ  አውንታዊ ተጽዕኖዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አብዛኛው የውጭ ኢንቨስትመንት  በአምራች አርፍ ላይ ነው፡፡  የሚለው በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የተገነቡትን እና በመገንባት ላይ ያሉትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለዚህ ዋነኛው ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ፓርኮች በተለይ አገራችን ከጥሬ እቃ ይልቅ ዕሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ወደ ውጭ መላክ እንዳትችል ረድቷታል፡፡

በአገራችን በአብዛኛው ከውጭ በሚገባ ምርት ላይ የተመረኮዘ ፍጆታ ነው ያለው፡፡ ይህም ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዳርጎናል፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ይህንን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና አለው፤ በተጨማሪም የአገራችን ምርቶች በውጭ አገሮች በገበያ ላይ ተወዳዳሪነታቸው እንዲጨምርም ያግዛል፤ እንደ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚነሳው የአገር ውስጥ የካፒታል ፍሰት መቀጨጭ ነው፡፡

እንደ ማጠቃለያ በቅርቡ ከተደረገው የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ለውጥ ጋር ተያይዞ አገራችን  ለውጭ አገሮች ኢንቨስተሮች ምቹ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ይታያል፡፡ በሂደት ላይ ያለው በመንግሥት የተያዙ ተቋማት ወደ ግል ባለሀብቶች የማስተላለፍ ሂደት እንዲሁ የተቀዛቀዘውን እና በመቀነስ ላይ ያለውን የመዋዕለንዋይ ፍሰት እንደገና እንዲያንሰራራ ይረዳዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ መንግሥት የፖሊሲ ማነቆዎችን መፍታት፣ ጠንካራና ዘመናዊ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎች ማዘጋጀት እና መተግባር ይገባዋል፡፡ በአገር ደረጃ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር እና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ እንዲፈጠር ጠንካራ ሥራ መሥራትም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

October 21, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *