Uncategorized

የብሔር ግጭቶች ቀጣይነት | ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር)

የብሔር ግጭቶቹ ምንጭ ከፖለቲካ ሥርዓቱ ባሕርይ የሚቀዳ ነው፡፡ ለ27 ዓመት የተፈተለ ዘውግን መሠረት ያደረገ፣ ዘውግን መሠረት ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን አነጣጥሮ ሲቀጠቅጥ የኖረው ሥርዓት ነው ትልቁ የአገሪቱ ፈተና፡፡ የዘውገኝነት መሠረታዊ የሆነው አጥፊ ባሕርይው እንደተጠበቀ ሆኖ ጤነኛ በሆነ መልኩ ሊስተናገድ የሚችልበት ዕድል ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊ ውስጥ በተራመደበት ሁኔታ ማራመድ አስፈላጊ የማይሆንበት ሁኔታ ነበር፡፡ ዘውገኝነትን ለመኳል ኢትዮጵያዊነትን ማጠልሸትና ማሰይጠን ሳያስፈልግ የዘውጌ ማኅበረሰቦችን ማንነት ማስጠብቅና መብታቸውን ማስከበር ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የተተከለው ዘውግ አስተሳሰብና ሥርዓት የህልውናው መሠረት ኢትዮጰጵያዊነት የሚባለውንና የኢትዮጵያዊነትን አስተሳሰብ ማጥላላትና ማክፋፋት ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ዘውገኝነት ዘር-አጥፊ (genocidal) በሆነ ድምጸት ነው ከጅምሩ እንዲቀኝ የተደረገው፡፡ ዘውገኝነት በዚህ ዓይነት አጥፊ ባሕርይው ለ27 ዓመታት ተሠርቶበታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሥራ በመሥራት እንጀራቸውን የሚያበስሉና ሕይወታቸውን የሚመሩ ሚሊዮኖች አሉ፡፡ በዚህ ትረካና ሒደት ውስጥ ተወልደው ያደጉ፣ በዘውግ ፖለቲካው ከመናወዛቸው የተነሳ ለ27 ዓመታት በሕወሓት/ኢሕአዴግ ጥይት የሚገደሉ ወንድሞቻቸው ሳያሳዝኗቸው በዐፄ ምኒልክ ዘመን የሞቱት ምንዥላቶቻቸው አሟሟት የሚያንፈቀፍቃቸው ሚሊዮኖች ተወልደዋል፡፡ ጽንፈኛ የሆነው የዘውግ ፖለቲካ አደገኛ ፍሬ አፍርቷል፡፡ በዚህ ደረጃ ነው መርዙ የተተከለው፡፡ ለ27 ዓመታት ሲታዩ የቆዩትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ የመጡት የብሔር ግጭቶች ምንጭ ይህ ነው፡፡

በዘውግ ፖለቲካ የከበሩ፣ ወደፊትም ደግሞ ትናንሽ ሥረወ-መንግሥታትን መሥርተው ለመንገሥ የቋመጡ ነገር ግን ሊመጣ ባለው የዜግነት ፖለቲካ ምክንያት የነጋባቸው የፖለቲካ ኤሊቶችም አሉ፡፡ እነኝህ ኀይሎች ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትንና የዜግነት ፖለቲካን እንደ ጦር ነው የሚፈሩት፡፡ ስለሆነም ባለ በሌለ አቅማቸው ይዋጉታል፡፡ እንጀራቸው ከአገራዊ ቀውስ ጋር የተያያዘ ነው፤ ሰላም ሲጠፋ፣ በየአካባቢው ቀውስ ሲነሳና ሕዝብ ሲሰቃይ ነው ፖለቲካቸው የሚደራው፡፡ ጽንፈኛ የዘውግ ፖለቲከኞች እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ ስሜታዊ በሆነ መልኩ በመቀስቀስ፣ ሕዝቡን ነጻ ትወጣለህ ብቻ ሳይሆን ጠላትህን ትገድላለህ፣ የቀድሞ ገዥዎችህን ትበቀላለህ እያሉ ነው የሚቀሰቅሱት፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በዚህች አገር ያለማቋረጥ ፍፁም ኀላፊነት በማይሰማው መልኩ የተሠራበት አጀንዳ ይህ ነው፡፡ ይህን መሰሉን የጥፋት አጀንዳ በፊታውራሪነት ሲያራምድ የቆየው የፖለቲካ ኀይል በፖለቲካ መድረክ ቢሸነፍም አሁንም ከፍተኛ አቅም ይዞ እንደቀጠለ ነው፡፡ ገዳይ ኀይሉ፣ እስከ መንደር ድረስ የተዘረጋው ስለላና አፈና መዋቅሩ አሁንም ከእጁ ሙሉ በሙሉ አልወጣም፡፡

ግልጽ ሊባል በሚል ሁኔታ ለሌውጥ ኀይሉ የመታዘዝ ችግር ያለበትን የፖሊስና የደህንነት መዋቅርም እንደያዘ ነው ያለው፡፡ ይህን ለ27 ዓመታት ፍፁም አጥፊ በሆነ የዘረኝነት ቅኝት የተዘረጋ መዋቅር እንዲገለል ሳይደረግ አንድ ሁለት ሦስት የሚባሉ ኀላፊዎችንና ዋና ተዋናይ የሚባሉትን አካላት ዘወር በማድረግ መሬት ላይ ያለውን የኀይል ሚዛን መቀየር አይቻልም፡፡ ማን ምን ያደርጋል የሚለው የተወሰነ ሚና ቢኖረውም ማሠሪያው ማን ምን ማድረግ ይችላል የሚለው ነው፡፡ ሐቁን እንነጋገር ከተባለ አሁን ያለው የፌደራልም ሆነ የክልል የፖሊስ፣ ፀጥታና የደህንነት መዋቅር (እንደ ተቋም ነው የማወራው) የለውጥ ኀይሉን እንደመንግሥት የሚቀበልና የሚያከብር አይደለም፡፡ ለውጡን ለማስፈፀም ፈቃደኛ ነው ማለትም አይቻልም፡፡ ሁኔታውን በምሳሌ ለመግለጽ ሦስት አብነቶችን ላንሳ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር በቅርቡ ቡራዩ ላይ በተከሰተው አሰቃቂና ዘረኛ የሆነ የግፍ ድርጊት ላይ የሰጡትን አስተያየት እንመልከት፡፡ በጊዜው የፖሊስ ኮሚሽነሩ ያን ኢሰብአዊና አስነዋሪ ድርጊት ማስቆም ያልተቻለው መሬቱ ወጣ-ገባና አስቸጋሪ ስለሆነ ነው የሚል መልስ ነበር የሰጡት፡፡ የሚደንቀው ኮሚሽነሩ ይህንን ብለውም እስካሁን በኀላፊነታቸው ቀጥለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር የሠራዊት ሜጀር ጀኔራል ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ይኼ ራስ የሚያስይዝ ዜና ነው፡፡ እንዴት ነው የመከላከያ ሠራዊት ሜጀር ጀኔራል የፖሊስ ኮሚሽነር ሊሆን የሚችለው? በየትኛው ሎጅክ? ጀኔራሉ በሺሕ የሚቆጠሩ የአዲስ የአዲስ አበባ ወጣቶች ለምን እየታፈሱ ወደ እስር ቤትና ማሰልጠኛ ጣቢያዎች እንደሚጋዙ ሲገልጹ ወጣቶቹ የሚያዙት ሽሻ ሲያጨሱና ጫት ሲቅሙ ስለተገኙ ነው ነበር ያሉት፡፡ ሳት ብሏቸው “ሲጋራ ሲያጨሱ…” የሚል ነገር ከተናገሩ በኋላ መልሰው ተወት አደረጉት፡፡ እኝህ ሰው መሠረታዊ ሕግ የማያውቁ ሳይሆን ሕግ በሚወራበት ሰፈር ያለፉበት መሆኑን እጠራጠራለሁ፡፡ አዲስ አበባን የሚያህል የአፍሪካ መዲናና ሜትሮፖሊታን ከተማ እንዲህ ዓይነት ሕግ በዞረበት ያልዞረ የፖሊስ ኮሚሽነር ነው ያላት፡፡ ያሳፍራል፤ ያንገበግባል!

ሌላው ቁጣ ሊቀሰቅስና ለሌላ ግጭት ምንጭ ሊሆን የሚችል ነገርም አለ፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ይል የነበረውን በደንብ እናውቃለን፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተው ሕዝብን በሚገስጽ የፊት ገጽታ ፍርጥም ብሎ “የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝና ሕጋዊ ነው፤ እርምጃው ባይወሰድ ኖሮ ሁላችንም ለአደጋ እንጋለጥ ነበር፤” ይለን እንደነበር እናውቃለን፡፡ እንዲህ ሲለን የኖረው ያው ግለሰብ ቡራዩ ላይ ምን እንደተከሰተ አጣርቼ እነግራችኋለሁ ማለት ነው፡፡

በዚህ ደረጃ ያሉትን የለውጥ ሒደቱን የሚያጠለሹ አካሄዶች ባልተቻለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የብሔር ግጭቶች በየቦታው ቦነሱ፣ አሁን ከተከሰቱት አደጋዎች የባሱ አደጋዎች ቢመጡ ሊገርመን አይችልም፡፡ ፀረ-ለውጥ ኀይሉና የእኛ ተራ ነው ብሎ የጥፋት እርምጃ የሚወስደው ግብዝ ቡድን ሃይ ካልተባለ የሚመጣው ጊዜ በጣም አስከፊ ነው፡፡

 

November 9, 2018

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *