ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከጤና ሚኒስቴር በሚወጡ ዕለታዊ የኮሮና ቫይረስ ሪፖርት ላይ የተጠቂ ቁጥር ላይ መቀነስ እየተመለከትን ነው:: ነገር ግን ይህ የቁጥር መቀነስ ከምን የመጣ ነው ብለን ስንጠይቅ፣ የምናገኘው መልስ ከምርመራ ቁጥር አብሮ መቀነስ ጋር ተያይዞ እናገኛዋለን:: መጀመሪያ በነበረው ሁኔታ የምርመራው አቅም አነስተኛ ቢሆንም በዚያው ልክ በቫይረሱ የሚጠቃውም ሰው ቁጥር በጣም ጥቂት የሚባል ነበር:: ከሚመረመረው ሰው ቁጥር አንጻር በቫይረሱ የሚያዘው ቁጥር ከ10 በመቶ በታች ነበር::
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር ከምርመራው ቁጥር አንጻር እስከ 15 በመቶ እየደረሰ ነው:: 4 ሺሕ ሰው ተመርምሮ 700 ሰው ቫይረሱ እየተገኘበት ነው:: ይህ የሚያሳየው ምን ያህል ቫይረሱ ወደ ማኅበረሰቡ ውስጥ እንደ ገባ ነው:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን መንግሥት የምርመራውን አቅም መቀነሱ ለብዙዎቻችን ድንጋጤም ብዥታም ፈጥሮብናል:: በዚህ ሰዓት የአገሪቱ በቀን የመመርመር አቅም 30 ሺሕ እና 40 ሺሕ መድረስ ሲገባው ቀድሞ ከደረሰበት 20 ሺሕ ወርዶ 6 እና 7 ሺሕ መድረሱ በየትኛውም መንገድ አግባብ ነው የሚል እምነት የለኝም:: የዓለም ጤና ድርጅት ከሚመክረው ፍፁም በተቃራኒ የቆመ ተግባር ነው::
በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ (ኬዝ) የምርመራው አቅም ቢቀነስም፤ በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር ግን እየጨመረ ነው:: ትንሽ ተመርምሮ ብዙ ሰው በቫይረሱ ተጠቅቶ ከተገኘ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው:: ለዚህም በየቀኑ የሚወጡት የቁጥር ሪፖርቶች ማሳያ ናቸው:: የምርመራው ቁጥር በዚህ ሰዓት ቢጨምር ቀድሞ ከሰማናቸው ቁጥሮች በላይ ሰዎች ለቫይረሱ ተጋልጠው እንደማይገኙ የሚያደርግ ምንም ዓይነት ምክንያት የለም::
አሁን የሚወጣው የዕለት ሪፖርት ቁጥር መቀነስ የመጣው የቫይረሱ የስርጭት መጠን በመቀነሱ ሳይሆን በምርመራ አቅም መቀነስ ነው:: ይኼ ደግሞ አርቴፊሻል የሽውዳ ቅነሳ ነው እንጂ ነባራዊ ሁኔታውን የሚያሳይ አልመሆኑን ሁሉም ሰው ሊገነዘበው ይገባል::
መንግሥት የምርመራ አቅም ለመቀነሱ በርካታ ምክንያቶችን ቢያስቀምጥም እንደ ጤና ባለሙያ ግን ምክንያቶቹ አሳማኝ እና በቂ ናቸው የሚል እምነት የለኝም:: መንግሥት እንደ መንግሥት የሕዝብን ደኅንነት ከመጠበቅ በላይ የሆነ ጉዳይ ሊኖረው አይችልም:: ሕዝብ ሰላም ሲሆን ነው የትኛውንም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥራ መሥራት የሚቻለው::
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከመቶ ሚሊዮን በላይ ነው:: ይህን ለሚያክል ሕዝብ የምርመራ አቅሙ ቢያንስ 30 ሺሕ እና 40 ሺሕ የየቀን ምርመራ መደረግ መቻል ነበረበት:: የምርመራ አቅምን በመቀነስ በቫይረሱ የሚያዘውን ሰው ቁጥር መቀነስ አይቻልም:: የተጠቂውን ቁጥር መቀነስ የሚቻለው ዜጎች ለቫይረሱ ያላቸውን ተጋላጭነት መቀነስ ስንችል ብቻ ነው:: አሁን እየሆነ ያለው ከዚህ የራቀ ነው:: ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ ነው:: የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንደቀደመው ሰው በሰው ላይ ደርበው እንዲጭኑ እየተደረገ ነው:: ይህ እንደ ጤና ባለሙያ የሚመከር አይደለም:: ውሳኔዎቹ በአብዛኛው የፖለቲካ ውሳኔዎች ናቸው:: በዚህ ጉዳይ ላይ ብንጮህም የሚሰማን አካል አላገኘንም:: ቫይረሱ እንደፈለገ እንዲሰራጭ የሚያግዙ ውሳኔዎች ከመንግሥት ተቋማት ሲወጡ እየተመለከትን ነው:: ዛሬ የምንወስናቸው ውሳኔዎች ለነገ ትልቅ መዘዝ ማምጣታቸው የማይቀር እውነታ ነው::
ዛሬም ቢሆን የዓለም ጤና ድርጅት ሰዎች በ2 ሜትር እንዲራራቁ፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ ነው እየመከረን ያለው:: ሁሉም ሰው የፊትና የአፍንጫ ጭምብል (ማስክ) ማድረግ ቢችል በቫይረሱ ምክንያት የሚሞተውን ሰው በ50 በመቶ መቀነስ ይቻላል:: አሁን ላይ እየተከናወኑ ያሉ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ ባዕላት ላይ ጭምብል የመጠቀሙ እና በሁለት ሜትር የመራራቁ ጉዳይ እየተረሳ ነው ያለው:: ይህ መዘናጋት እየመጣ ያለው ከላይ ያሉ አካላት በሚያወጡት ፖሊሲ እና መመሪያ ምክንያት ነው::
ዛሬ ላይ ከታካሚ ባለፈ በርካታ የጤና ባለሙያዎች ሕሙማንን ለማዳን በሚያደርጉት ጥረት የራሳቸው ሕይወት አደጋ ውስጥ እየገባ ነው:: እስካሁን ከ1 ሺሕ 300 በላይ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል:: ሕይወታቸውንም እያጡ ነው:: በመንግሥት እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው መዘናጋት የጤና ባለሙያዎች ስጋት ውስጥ ከቶናል::
Leave a Reply