የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ከሥርወ መንግሥታዊ ወደ አብዮታዊ ከዚያም ወደ ዘውጋዊነት ባደረገው ታሪካዊ ጉዞ ምክንያት የጥንታዊነትና ዘመናዊነት፣ ዜግነታዊነትና ዘውጋዊነት፣ ባህላዊነትና ፖለቲካዊነት፣ ወዘተ… መንትያነቶች በአገሪቱ ብሔራዊ ማንነት ግንዛቤ፣ የብሔርተኝነት ፖለቲካና ጥናት ውስጥ በሰፊው ይንጸባረቃሉ፡፡
ስለዚህም ተቀዳሚው እርምጃ እነዚህን ጉራማይሌዎች የሚያስተናግድ ለአገር ግንባታው መሠረት የሚሆን ግልጽና አካታች ርዕዮተ ዓለም መንደፍ ይሆናል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ሕዝብን ከመንግሥት፣ እንዲሁም የመንግሥትን አካላት በአዎንታዊነት የሚያቀራርብ መሆን አለበት፡፡ የአገሪቱን የታሪክና ባህል ቀጣይነት የሚያረጋግጥና መጻኢ እጣፈንታዋንም በግልጽ የሚያስቀምጥ መሆን አለበት፡፡
ከዚህም አልፎ አገራዊነት/ብሔራዊነትና ዘውጌነት የሚደጋገፉበትን መንገዶች መተለም ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ለብሔራዊው መንግሥት የሚኖር ውዴታና ታማኝነት መገለጫ እንደየማኅበረሰባዊና ወቅታዊ ጭብጦች ቢወሰንም፣ አገራዊነት ከዘውጌነት ንቃተ ኅሊና ጋር አብሮ ተባብሮ ሊኖር ይችላል፡፡ ኢትዮጵያና ብሔረሰቦቿ በተቃርኖ የቆሙ ሳይሆኑ፣ ተደጋጋፊዎችና አንዱ ያለሌላው የተሟላ ትርጉም የማይሰጡ ናቸው፡፡
ከታሪካችን እንደምንገነዘበው የአገሪቱ ህልውና ምርጫ በአሐዳዊነትና በመበታተን መካከል አይደለም፡፡ ሁለቱም ተሞክረው ያላዋጡ መንገዶች ናቸው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የአገር ግንባታ ሥርዓት ብዝሃነትና አሐዳዊነትን በዴሞክራሲ አማካይነት የሚያቻችል ነው፡፡ ፌዴራሊዝም ለብዝሃነት ባለው ትኩረትና ዴሞክራሲ ለእኩልነት ባለው ትኩረት መካከል አለመጣጣም የለም፡፡ ብዝሃዊ መንግሥታት በመገንባት ረገድ ቀንደኛው ተግዳሮት ሕዝቡ መንታ ዘውጋዊና ብሔራዊ ማንነት እንዲላበስ ማስቻል ነው፡፡ ለዚህም ማንነት ንብርብራዊ ተፈጥሮ እንዳለውና በደመነፍሳዊ ጥጎች ብቻ እንደማይገደብ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ያለንበት ፌዴራላዊ ሥርዓት በዋነኝነት በቋንቋ መሥፈርት የተሠራ መሆኑ መሠረታዊ ግድፈቱ ነው፡፡ በተጨማሪ አብዛኞቹ የፌዴራል ሥርዓታችን ግዛታዊ አሐዶች ታሪካዊ መሠረት የላቸውም፡፡ ይህም የክልሎችን ተቀባይነት አሳንሶታል፡፡ ስለዚህም ተመራጩ የአገር ግንባታው ርዕዮት የባህል ነጻነትን ወይም ራስ ገዝነትን ኢግዛታዊ (consociational democracy) ተመራጩ የሚያደርግ ሊሆን ይገባል፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱን ከዘውጋዊነት ወደ አስተዳደራዊነት አሐዶች መቀየር ብቻ አይበቃም፡፡ አሁን እንደሚታየው ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ከአገር ዐቀፋዊ ትብብር ይልቅ የክልሎች ፉክክር ማዕቀፍ እንዳይሆን፣ በክልሎችም ሆኑ ክፍለ ሀገራት መካከል ጠንካራ ድንበር ተሻጋሪ ትብብሮችና ትስስሮችን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
የአገር ግንባታ ዕቅዶች የዜጎችን ባህላዊ አድማስ በድምር በሚያሰፉ እርስ በርሳቸው በሚሰናሰሉና በሚመጋገቡ ለውጦች መተለም አለበት፡፡ ከርዕዮታዊና ባህላዊ ጉዳዮች በተጨማሪ መሠረቱ ሰፊ የሆነ ማኅበረ – ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎችንም ማካተት አለበት፡፡
አገር ግንባታ ነባሩን የሚያጠናክር፣ የሚያሻሽልና አዲስ የሚፈጥር ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስልቶችን ያቀናጀ መሆን አለበት፡፡ ማንኛውም አዎንታዊ የግንባታ ጥረት ታሪካዊና ባህላዊ ቀጣይነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል፡፡ በአዲሱ የብሔርተኝነት እሳቤ ውስጥ ነባሩን ማንነት ችላ ማለት ፅኑ ግድፈት ነው፡፡ በተጨማሪም የአገር ግንባታውን በአገር በቀልና በማኅበረሰቦች የጋራ እሴቶች ላይ መመሥረትም የማይታለፍ ቁም ነገር ነው፡፡
የአገር ግንባታ በሁለት መልኩ በላዕላዊና ታኅታዊ መዋቅሮችና ሂደቶች የተቀናጀ መሆን አለበት፡፡ መንግሥት በግንባታው ሂደት ማዕከላዊ ቦታ ቢኖረውም፣ በተጓዳኝ ከታች በሰፊው ሕዝብ ፈቃዳዊ ጥረት የሚደገፍ መሆን አለበት፡፡ በኢትዮጵያ እንደታየው መንግሥታዊ ብሔርተኝነት ራሱ በታሪክና በፖለቲካዊ ኀይል አሰላለፍ ተጽዕኖዎችና በፖለቲካዊ ብልጠት የተነሳ አገራዊነቱ ወይም ዘውጋዊነቱ ሊጎላ ይችላል፡፡ ለዚህ ሚዛን የሚያስይዝ ዘላቂ ሕዝባዊ ብሔርተኝነት ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ የአገር ግንባታው በልሂቃዊ መደቦች ተንጠልጥሎ እንዳይቀር በስፋትና በጥልቀት ከሕዝባዊነት ጋር ማጣጣም ተገቢ ነው፡፡
በአጠቃላይ በአገር ግንባታው ሂደት ማን፣ ምን፣ እንዴት ይሥራ? የሚለው ፍኖተ ካርታን በጥንቃቄ ማዘጋጀት ታላቅ ትኩረት የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ የፖለቲካ ተዋናዮች፣ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት የሕዝባቸውን ብሔራዊ ማንነት በመቅረጽ ጥረት ላይ ሊሠሩ የሚፈቀድላቸው፣ የሚበረታቱት፣ የሚፈለግባቸው ወይም የሚከለከሉት ተለይቶ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የአገር ግንባታው ባህላዊ ዘርፍ ሕዝባዊ ትዕምርቶችን በየትኞቹ የጋራ እሴቶች ላይ ይገንባ፤ ከታሪካችን የጋራ ብሔራዊ ትውስታን በመገንባቱ ጥረት የቱ ይፈቀድ? የትኛው ይበረታታ ወይም ይከልከል? የሚሉትን በቅጡ የሚለይ ሊሆን ይገባል፡፡
Leave a Reply