የጎረቤቶቿ ቸልተኝነት ኢትዮጵያን ለተደጋጋሚ የአንበጣ መንጋ ጉዳት አጋልጧታል ተባለ
ዜና

የጎረቤቶቿ ቸልተኝነት ኢትዮጵያን ለተደጋጋሚ የአንበጣ መንጋ ጉዳት አጋልጧታል ተባለ

የጎረቤት አገራት ሰብል አምራች አለመሆናቸው እና ለአንበጣ መንጋ መከላከል አመርቂ ምላሽ አለመስጠታቸው ኢትዮጵያን ለተደጋጋሚ የአንበጣ መንጋ ጉዳት ተጋላጭ አድርጓታል ተባለ፡፡

ሶማሊያ እና ጅቡቲ የሰብል ምርት አምራች አለመሆናቸው እና በአገራቱ ለሚፈለፈለው የአንበጣ መንጋ ስርጭት ትኩረት አለመስጠታቸው ኢትዮጵያን ለተደጋጋሚ የአንበጣ መንጋ ጉዳት እያጋለጣት መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ከሲራራ ጋዜጣ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ታምሩ ከበደ በአሁኑ ሰዓት የአንበጣ መንጋ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ከዚህ ቀደም በአፋር ደባቃ ቦታዎች የተፈለፈለው የአንበጣ መንጋ መብረር በመጀመሩ በሰሜን አማራ፣ በደቡብ ትግራይ እና በአፋር አከባቢዎች በጥቅሉ 26 ወረዳዎች ላይ ጉዳት ማድረስ ጀምሯል” ብለዋል። የአንበጣ መንጋው ገና በመፈልፈሉ ሂደት ላይ ሳለ ለመከላከል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ያነሱት አቶ ታምሩ ” ለኬሚካል ርጭት አመቺ ባልሆኑ እና መኪና መግባት በማይችልባቸው አከባቢዎች እንዲሁም ሰው በማይኖርበት መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ አንበጣውን ባለበት ማምከን ሳይቻል ቆይቷል ብለዋል፡፡ በቦታዎቹ ላይ የተፈለፈለው የአንበጣ መንጋ እድገቱን ጨርሶ ወደ መብረር ደረጃ በመሸጋገሩ፤ መንጋው ወደ ተለያዩ አከባቢዎች በመንቀሳቀስ ጉዳት ማድረስ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

” ወደ ሰሜን ወሎ ፣ደቡብ ወሎ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ ደቡብ ትግራይ የአንበጣ መንጋው በመጠጋት ላይ ይገኛል፤ የመከላከል ሥራውም በተቻለ መጠን የሰው ኃይልን በማደራጀት እየተሠራ ይገኛል” ያሉት አቶ ታምሩ በአፋር፣ በሰሜን ወሎ ፣ ደቡብ ወሎ እና ደቡብ ትግራይ አከባቢ የአንበጣ መንጋው ሰብል ላይ ጉዳት ማድረስ መጀመሩን ጨምረው ገልፀዋል ፡፡

በቀጣይ የአንበጣ መንጋው በደረሰ የማሽላ ምርት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መንግሥት በማይደርስባቸው አከባቢዎች፤ አርሶአደሩ የነፍስ ወከፍ ኬሚካል መርጫ እንዲያገኝ በማድረግ መንጋውን እንዲከላከሉ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአፋር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና ደቡብ ትግራይ አከባቢ ጉዳት እያደረሰ ያለው የአንበጣ መንጋ በአገር ውስጥ የተፈለፈለ መሆኑን ያነሱት ተወካዩ ከሶማሌ ላንድ የሚገባው የአንበጣ መንጋ በምሥራቅ ሀረርጌ፣ ምዕራብ ሐረርጌ እና ድሬደዋ በማሽላ ምርት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ” ብለዋል፡፡

ከሶማሌ፣ ጅቡቲ፣ የመን እና ኦማን ከፍተኛ መጠን ያለው የአንበጣ መንጋ እየተፈለፈለ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ መቆየቱን ያነሱት አቶ ታምሩ እነዚህ አገራት በከብት እርባታ እና በነዳጅ ሽያጭ ኢኮኖሚያቸውን የሚያንቀሳቅሱ በመሆናቸው እና የሰብል ምርት አብቃይ ባለመሆናቸው ምክንያት ለአንበጣው መራባት ትኩረት እንደማይሰጡ ገልፀው ፤ ይህም ከአገራቱ የሚነሳው የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቀድሞ በኬንያ በኩል ወደ ደቡብ ክልል የገባውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከኬንያ መንግሥት ጋር በርብርብ ሲሠራ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ታምሩ አሁን ላይ ለመንጋው መነሻ የሆኑት ጅቡቲ ፣ ሶማሊያ ፣የመን ፣ ኦማን ለአንበጣ መንጋ የሚያሠጋ የሰብል ምርት ስለሌላቸው የመንጋውን ስርጭት የመከላከል ሥራው ላይ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ አለመቻላቸውን አንስተዋል፡፡

“ባለፉት ሳምንታት ሁለት የኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖች በደቡብ ወሎ እና ሀረርጌ አከባቢዎች ላይ መከስከሳቸው የአንበጣ መከላከል ሥራውን አዳጋች አድርጎታል ፡፡ በዚህ ሰዓት በዛ ያለ የኬሚካል መርጫ አውሮፕላን ያስፈልጋል፤ ለዛም የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት አውሮፕላኖቹን ለማግኘት ከተለያዩ አገራት ጋር ግንኙነት እያደረጉ ነው፡፡” ያሉት አቶ ታምሩ አሁን ላይ ከቀሩት አውሮፕላኖች አንዱ በብልሽት ምክንያት ሥራ ስላቆመ በአንድ አውሮፕላን ብቻ የኬሚካል እርጭት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በብልሽት ምክንያት ሥራ ያቆመው አውሮፕላን በቅርቡ ተጠግኖ ወደ ሥራ እንደሚገባ ጨምረው አስረድተዋል።

October 13, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *