ኢትዮጵያዊያን በርካታ መልካም ታሪካዊ አጋጣሚዎች አምልጠውናል፡፡ አሁን የሚታየው ለዴሞክራሲ ሽግግር ሊያግዝ የሚችል ታሪካዊ ዕድልም እንዳያመልጠን በእጅጉ ያሰጋል፡፡ ከአፈና አገዛዝ ተላቀን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ልንመሠርት ወደምንችልበት የሽግግር ዘመን ገባን ብለን ደስ ሲለን፣ ለውጡ መልኩን እንዲቀይርና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዲሄድ ከየአቅጣጫው መጠላለፍ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ባለፈው የአፈና ዘመን እንኳ ባልታየ መልኩ በሺሕዎች የሚቆተሩ ኢትዮጵያዊያን እንደመጤና ባይተዋር እየተቆጠሩ እየተፈናቀሉ ይገኛሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ባህል ባፈነገጠና ብሔራዊ ክብርን በሚያዋርድ መልኩ ንጹሐን ተዘቅዝቀው እየተሰቀሉ፣ በገዛ ወገኖቻቸው በገጀራ እየተገደሉ ነው፡፡ ችግሩ በዚህ ሳይወሰን አሁንም በየአካባቢው በመንግሥት ላይ መንግሥት የሆነ አካሄድ ይስተዋላል፤ የታጠቁ ቡድኖችና ድርጅቶች በአደባባይ ትጥቅ አንፈታም እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ነገሮች በዚህ መልኩ የሚቀጥሉ ከሆነ የአገራችን ሁኔታ በጣም አስቸጋሪና አስፈሪ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡
በዚህ የዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባትና እንደልባቸው ተዘዋውረው የመኖርና የመሥራት መብት አደጋ ላይ በወደቀበት ሁኔታ ምን ዓይነት የዴሞክራሲ ሽግግር ነው ሊመጣ የሚችለው? ይህ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ትግልና መስዋዕትነት የተገኘ የለውጥ ዕድል እንዳይኮላሽ ምን መደረግ አለበት?
የ50 ዓመት አጀንዳ
***
በቡድን መብት ላይ የሚያተኩረው ትርክት በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ማዕከላዊ ስፍራ ይዞ ቆይቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ጊዜ ጀምሮ ስለ ቡድን መብት በስፋት ተነግሯል፤ ተጽፏልም፡፡ ይህ የሕዝቦችንና የሃይማኖቶችን እኩልነት ለማስከበር በበጎ ዓላማ የተነሳ አጀንዳ ውሎ አድሮ ይበልጥ እየከረረና ጽንፍ እየረገጠ መጥቶ ለዘመናት በክፉውም በደጉም አብረን የኖርን፣ በጣም በርካታ የጋራ ዕሴቶችን ያዳብረን እና እጣ-ፈንታችን የተሳሰረ ሕዝቦች መሆናችን ተዘንግቶ ብዙ ጥፋት ደረሷል፤ እየደረሰም ነው፡፡
ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ ማግስት በሽግግሩ ወቅትና ከዚያም በኋላ የተዘረጋው ዘውጋዊ ማንነትን መሠረት ያደረገው ፌደራላዊ ሥርዓት የመለሳቸው ጥያቄዎች ቢኖሩም በአገር አንድነትና በሕዝቦች አብሮነት ላይ ያስከተላቸው መዘዞች በጣም በርካታ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ፌደራላዊ ሥርዓቱ የተዘረጋው ሕዝብ በነጻነት ሳይመክርበትና ሳይዘክርበት በተወሰኑ በትጥቅ ትግል አሸንፈናል ባሉ ልኂቃን ፊታውራሪነት በመሆኑ ከፍተኛ የቅቡልነት ጣጣ ውስጥ ግብቶ ቆይቷል፡፡ አሁንም ያለፍላጎታችን ተጨፍልቀን ወደማንፈልገው ክልል እንድንካተተ ተደርጓል የሚሉ ሕዝቦች የማንነት ጥያቄ እያነሱ በዚህም ሳቢያ ብዙ ሕይወት እየጠፋ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የተዘረጋው ፌደራላዊ አወቃቀር አንዳንድ ሕዝቦችን የክልሉ ዋና ባለቤቶች ሲያደርግ ሌሎችን እንደሁለተኛ ዜጋ እንዲቆጠሩ እድል ከፍቷል፤ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው “መጤ” እየተባሉ በገፍ እየተፈናቀሉ ይገኛሉ፤ በነጻነት ተንቀሳቅሰው ሠርተውና ሀብት አፍርተው መኖር አልቻሉም፤ ሁልጊዜም በፍርሃትና ሰቀቀን ውስጥ እንዲኖሩ ሆነዋል፡፡
ይህ ያለቅጥ በዘውጋዊ ማንነት ላይ ያተኮረ የፖለቲካ አካሄድ አገሪቱንና ሕዝቦቿን ውድ ዋጋ እያስከፈሏቸው ይገኛሉ፡፡ በየክልሉ ለሚገኙ አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ሕዝቦች የተሰጠው ትኩረት ከክልል ክልል ቢለያይም በጥቅሉ ግን በጣም ደካማ ነው፡፡ አንዱ ዋና ባለቤትና አድራጊ ፈጣሪ፣ ሌላው መጤና መብት የሌለው የሆነበት አስከፊ ሥርዓት ነው የተፈጠረው፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜግነትና ማንነት ከዘውጋዊ ማንነት በእጅጉ ያነሰ ደረጃ ነው የተሰጠው፡፡
የፌደራል አወቃቀሩ በራሱ የፈጠረው ትልቅ አደጋ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት የጋራ እሴቶቻችን የሚጎለብቱበትን መንገድ ከመፈለግና አብሮነታችንን የሚያጎለብቱ እሴቶችን ከመኮትኮት ይልቅ በልዩነቶቻችን ላይ አተኩሮ ሲሠራ ነው የኖረው፡፡ በዚህ ምክንያት ወጣቶቻችን እርስ በርሳቸው የማይተዋወቁ ብቻ ሳይሆን እርስ በርሳቸው የሚጠራጠሩና በጠላትነት የሚተያዩ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡
አሁን የሚታዩትም ሆነ ወደፊት ሊመጡ የሚችሉት ግጭቶች ዋነኛ ምንጭ ይኼ በኢትዮጵያዊያን መካከል የተዘራው የጥላቻና የጥርጣሬ ግንብ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ መካከል የተኮተኮተውና ሥር የሰደደው የልዩነትና የጥርጣሬ ዘር ከአገሪቱ ድህነት ጋር እየተመጋገበ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ ይገኛል፡፡
የዳበረ ኢኮኖሚና ጠንካራ ሥርዓት የገነቡ አገሮች ብዝሃነት ቢኖራቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታየው ሕዝቡ አውዳሚ በሆነ መልኩ እርስ በርሱ አይጠፋፋም፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ ሕግና ሥርዓትን ተከትለው መፍትሔ ያገኛሉ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምናየው ዓይነት የመንጋ ፍርድ ብሎ ነገር የለም፤ አንድ ኀይል/አቅም ያለው አካል (መንግሥት ወዘተ.) እንፈለገ የሚፈነጭበት ዕድልም የለም፡፡
የልኂቃኑ ሚና
***
በትምህርትና በምርምር የዳበረ ዕውቀት ያላቸው፣ በንግዱ ዓለም የተሳካላቸው፣ በመንግሥትና ሕዝባዊ ተቋማት አመራር ክህሎታቸው የታወቁ ልኂቃን ለአገርና ኅብረተሰብ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በዚያው መጠን በአገርና በሕዝብ ላይ ጉዳት የማድረስ አቅማቸውም ቀላል አይደለም፡፡
የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ እንዲዘምን፣ የአገራችንና የሕዝባችን ሁኔታ እንዲሻሻል፣ ሁሉንም በፍትሐዊነት የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ከአገራችን ልኂቃን የሚጠበቀው ብዙ ነበር፤ ነውም፡፡ ሆኖም በግልጽ እንደሚታየው ከፍተኛ የሆነ የክፍፍል አጀንዳ የሚራመደው ከማንም በላይ በልኂቃኑ አማካይነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ልኂቃን የሚገባቸውንና የሚጠበቅባቸውን በጎ ሚና ከመጫወት ይልቅ አክራሪ የሆነ የዘውግ ፖለቲካ በአገሪቱ ሥር እንዲሰድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በአመዛኙ በሚባል ደረጃ አገራችን የፖለቲካ ችግር ምንጩ አገሪቱ ልኂቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሕዝቦች መካከል እምበዛም ችግር የለም፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ሥር እየሰደደና ለአገሪቱ ህልውናም አስጊ እየሆነ የመጣው በልኂቃኑ መካከል የሚታየው ክፍፍል ነው፡፡ እያንዳንዱ ልኂቅ የእኔ የሚለውን ዘውጌ ማኅበረሰብ ስሜታዊ በሆነ መልኩ እየቀሰቀሰ የሥልጣን መወጣጫ፣ የሥራና ጥቅማጥቅም ማግኛ ሲያደርገው ነው የሚታየው፡፡ ትልቁ መከራ ይህ ነው፡፡ መወያየት ያለብንም በአገሪቱ ልኂቃን መካከል የሚታየው ክፍፍልና የተካረረ ልዩነት በምን መልኩ ይስተናገድ በሚለው መሠረታዊ ነጥብ ላይ ነው፡፡
ልኂቃኑ፣ በተለይም ምሁራን እንደ ኅብረተሰብ ህሊናነታቸው አገርና ሕዝብ ሊጠቅሙ በሚችሉ ተግባራት ላይ መሰማራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አገራችን እንዲህ ባለው አረንቋ ውስጥ እንዴት ልትገባ እንደቻለች፣ ለዘመናት ሊለቃት ካልቻለው ድህነትና ኋላቀርነት እንዴት ልትወጣ እንደምትችል፣ ዜጎችን በፍትሐዊነትና በእኩልነት ሊያስተናገዱ የሚችሉ ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማትን እንዴት መፍጠር እንደሚቻል ወዘተ. ጥልቀት ባለው መልኩ ማጥናትና የመፍትሔ ምክረ-ሐሳቦችን መሰንዘር ከምሁራን የሚጠበቅ ትልቅ ተግባር ነው፡፡
አገራችን ምሁራን በችግር ላይ ችግር ከሚቀፈቅፍና የግጭት ምንጭ ከሆነ አካሄዳቸው ታቅበው ወደሚጠበቅባቸው ምሁራዊ ተልዕኮ መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን የሚታየው ትልቅ አገራዊ ዕድል እንዳያመልጥ፣ ጉዟችንም ከግጭት ወደ ግጭት እንዳይሆን ከአገራችን ልኂቃን ብዙ ይጠበቃል፡፡
ሥራ አጥነትና ግጭት
***
ኢትዮጵያዊያን 102 ሚሊዮን ገደማ ሆነናል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ባላደረገበት ሁኔታ የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር በዚህ ደረጃ ማደጉ መልካም ዜና አይደለም፡፡ መንግሥትና ሌሎች የፖለቲካ ተዋናዮች ትልቅ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ አጀንዳ ነው የሥነ-ሕዝብ ጉዳይ፡፡
በአገራችን ሁለተኛ ደረጃ፣ ቴክኒክና ሙያ እና ኮሌጅ ጨርሰው ያለ ሥራ የተቀመጡ በጣም በርካታ ወጣቶች እንደሉ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ኢኮኖሚው አድጓል፣ አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ልትሰለፍ ነው እየተባለ ሲነገር ቢከርምም፣ ምሩቃኑንን ለመቀበል የሚያስችል ቁመና እንደሌለው በግልጽ ታይቷል፡፡ በዚህ ምክንያት በወጣቶቻችን ላይ ከፍ ያለ የተስፋ ማጣት ስሜት ነግሷል፡፡ በየእለቱ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ለተቃውሞም ሆነ ለድጋፍ ግልብጥ ብሎ የሚወጣው በአመዛኙ ይህ ለውጡን ተስፋ ያደረገ ወጣት ነው፡፡ ወጣቱ የጠበቀውን ነገር እንደማያገኝ ሲረዳም በየአካባቢው የሚገኙትን መሠረተልማቶቸና ኢንቨስትመንቶች ወደማውደሙ እያዘነበለ መጥቷል፡፡ በዚህ ሳይወሰን “መሬታችን ወሰዳችሁ፤ ሥራችንን ተሸማችሁ፤” ወዘተ. በሚልም በየአካባቢው “ከክልሉ ውጪ የመጡ” በተባሉት ኢትዮጵያዊያን ላይ ጥቃት ይፈፀማል፡፡
ወጣቱ ሥራ በማጣቱ ምክንያት በአገሩ ተስፋ መቁረጡ ሳያንሰው፣ አክራሪ በሆነ የዘውግ ፖለቲካ ተኮትኩቶ በማደጉ ምክንያት የእኔ ከሚላቸው ውጪ ለሆኑት ኢትዮጵያዊያን የሚያሳየው የጥላቻ ስሜት ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ወጣት ተቀጣጣይ የሆነ ኀይል ነው፤ ጉዳት ለማድረስ ጥቂት ሰበብ ብቻ ነው የሚበቃው፡፡
ስለሆነም መንግሥት በአንድ በኩል የቡድን መብቶች እንደተጠበቁ ሆነው በዜግነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነት ስለሚገነባበት እና ኢትዮጵያዊያንን ለዘመናት ገምደውና አንድ አድርገው የያዙን የጋራ እሴቶች በሚጠናከሩበት ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ሥራ መሥራት ይገባዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሁሉም ነገር በላይ የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶት በሥራ አጥነትና ተስፋ መጣት ውስጥ የሚገኙትን ወጣቶቻችንን ወደሥራ በማስገባት ላይ ትልቅ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡
እኛ፣ ስለእኛ፣ በእኛ
***
ኢትዮጵያዊያን በፊትም ሆነ አሁን ከሩዋንዳ ጋር ሊወዳደር የሚችል ችግር አልገጠመንም፡፡ ሩዋንዳ ውስጥ ቅኝ ገዥዎችና የእነሱ አስተሳሰብ ተሸካሚ የሆነው የሩዋንዳ ልኂቅ በመፈጠረው የጎሳ ልዩነት ምክንያት በቱቲሲዎችና በሁቱዎች መካከል በተደረገ ፍጅት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ800,000 በላይ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች አልቀዋል፡፡ ያን እጅግ ዘግናኝ ትራጀዲ ያሳለፈችው ሩዋንዳ “ገቻቻ” የተሰኘውን ባህልዊ የችግር መፍቻ በመጠቀም አጥፊዎች ያጠፉትን በግልጽ ለሕዝብ አሳውቀው ሕዝቡም ይቅር ብሏቸው ዛሬ ሩዋንዳ የተሻለ ሰላም ያላትና ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ግስጋሴ እያደረገች ያለች አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ሩዋንዳ ውስጥ እኔ ቱትሲ ነኝ፣ እኔ ሁቱ ነኝ የሚል ሰው የለም፤ ማለትም በሕግ ያስቀጣል፡፡ “ሩዋንዳዊ ነኝ” ነው የሚሉት፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ደቡብ አፍሪካ በከፋፋዩና ዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት የተፈፀሙትን በደሎች በዝርዝር በዳዮች ቀርበው የፈፀሙትን ወንጀል እያወጡና ሕዝብ እያወቀው፣ እውነቱ ከወጣ በኋላ በይቅርታና ምሕረት እንዲታለፍ የተደረገበት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ምሳሌ ሊሆን የሚችል እርምጃ ተወስዷል፡፡
የእኛ ችግር ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ ከደረሱት ችግሮች ጋር በምንም ዓይነት መልኩ የሚወዳደር አይደለም፡፡ ሆኖም አካሄዳችን መልካም ስላልሆነ ከወዲሁ እንዲስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዘመናዊው የሕግና ሥርዓት ማስከበሪያ መንገድ በተጨማሪ ነባሮቹን የግጭት መፍቻ መንገዶችም በሚገባ መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ግልጽ መሆን ያለበት የሚበዛው አገራችን ሕዝብ በሰላም ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር ያደረጉት በየአካባቢው ያሉት ነባር የግጭት መፍቻ መንገዶች ናቸው፡፡ ስለሆነም እነኝህን ነባር የግጭት መፍቻ መንገዶች ሥርዓት ባለውና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ መጠቀምም ያስፈልጋል፡፡
Leave a Reply