ኢትዮ ቴሌኮም 25.57 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ
ኢኮኖሚ, ዜና

ኢትዮ ቴሌኮም 25.57 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 ዓ.ም. የመጀመሪያው ስድስት ወራት 25.57 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮምን የስድስት ወራት የሥራ አስፈጻጸም በተመለከተ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ሐሙስ፣ ጥር 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙሃኑ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ኢትዮ ቴሌኮም ከጊዜ ወደ ጊዜ አሠራሩን እና አገልግሎቱን እያሰፋ መምጣቱን ያነሱ ሲሆን፣ የኩባንያውን የመሠረተ ልማቶች ለማስፋት፣ ለማጠናከር፣ የኔትዎርክ ሽፋንን ለማሳደግ እንዲሁም መሠረተ ልማቶችን በማከራየት ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት የሚችሉ 137 የፕሮጀክት ሥራዎችን በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው በ2013 ዓ.ም. የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት 25.57 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከዕቅዱ 95 በመቶ ማሳካቱን  የሚያሳይ  ነው ተብሏል፡፡ የዘንድሮ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ገቢ ካላፈው ተመሳሳይ ወቅት ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ12.3 በመቶ ዕድገት እንዳለው ሥራ አስፈጻሚዋ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በአገሪቱን የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ግቡን እንዳይመታ እንዳደገውም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ከተገኘው ገቢ ውስጥ ከሞባይል የድምጽ አገልግሎት 49 በመቶ፣ ዳታንና ኢንተርኔት 26.3 መቶ፣ ከዓለም ዐቀፍ ጥሪ 10.3 በመቶ፣ ዕሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች የ11 በመቶ እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች 3.4 በመቶ መሆኑን ወይዘሪት ፍሬሕይወት ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 80.21 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ያስታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም ይህ ገቢ መገኘት የቻለው ሕገ-ወጥ የቴሌኮም ማጭበርበሮችን መከላከል በመቻሉ መሆኑ ተነስቷል፡፡

በዚህ ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞች ብዛት 50.7 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ11.2 በመቶ ጭማሪ መታየቱን በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

እስካሁን ባለው የሞባይል የድምጽ ደንበኞች 48.9 ሚሊዮን፤ የመደበኛ ብሮድባንድ ደንበኞች 309.4 ሺሕ፣ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 981 ሺሕ፣ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 23.54 ሚሊዮን ደንበኞች አሉ የተባለ ሲሆን፤ አጠቃላይ የሞባይል አገልግሎት በቆዳ ስፋት ሽፋኑ 85.4 በመቶ መድረሱን ኩባንያው አስታውቋል፡፡

January 22, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *