በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በመተከል ዞን ንጹሐን እንዲገደሉ በማስተባበርና በመምራት የተጠረጠሩ 504 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነገረ፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን በመተከል ዞን ንጽሑን እንዲገደሉ በማስተባበርና በመምራት የተጠረጠሩ 504 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
ትናንትና ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሳነ መስተዳድሮች በጉዳዩ ዙሪያ በጋራ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ በመግለጫቸው በተደጋጋሚ በክልሉ መተከል ዞን በንጹሐን ላይ የሚፈፀመው ጥቃት መንስኤው ብዙ መሆኑን ጠቅሰው የመሬት ይዞታ እና ለውጡን ተከትለው ያኮረፉ አካላት የሚፈጥሩት የፀረ ሰላም ኀይሎች እንቅስቃሴ ዋናዎቹ ናቸው ያሉት አቶ አሻድሊ፣ ከንጹሐን ዜጎች ግድያ በስተጀርባም የሕወሓት እጅ እንዳለበት ደርሰንበታል ብለዋል፡፡
ይህን ድርጊት ለማስፈፀም ወጣቶችን በመመልመልና አንዳንድ በኢንቨስትመንት የገቡ ባለሀብቶችን በመጠቀም ችግሮቹ እንዲባባስ ሕወሓት ሲሠራ መክረሙን የተናገሩት አቶ አሻድሊ፣ የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በክልሉ ተዋቅሮ ያለውን የኮማንድ ፖስት አፈጻጸም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በመሆን መገምገማቸውን ገልጸዋል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት በአካባቢው የመሸጉ ታጣቂ ቡድኖችንና ሽፍቶችን የመደምሰስ ሥራ እንደቀጠለ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ነዋሪነታቸው በቤኒሻንጉል ክልል በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ደኅንነታቸውን ማስጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ሁለቱ ርእሳነ መስተዳደሮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የኮማንድ ፖስቱን ሥራ ከገመገሙ በኋላ መግለጫ የሰጡት ርእሳነ መስተዳድሮች ከየአካባቢው የተውጣጣ የሰላም ምክር ቤት እንደሚቋቋም አስታውቀዋል፡፡ ጥቃት አድራሾችን ትጥቅ ለማስፈታት እንደሚሠራና ኮማንድ ፖስቱ ለሚዲያዎች በቀጣይ የሠራውን አስመልክቶ በየጊዜው መግለጫ እንደሚሰጥ፣ አካባበው ብዙ የፖለቲካ ፍላጎት ያለበት በመሆኑ በዘላቂነት በኢኮኖሚ በማጠናከርና ሁለቱን ክልሎች በማስተሳሰር በየደረጃው መሪዎች ከየብሔሩ የተወጣጡ እንዲሆኑ እንደሚሠራም ተገልጿል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ በንጹሐን ዜጎች ላይ የተደራጀ ማንነት ተኮር ጥቃት እየተፈፀመ በርካታ የአማራና አገው ተወላጆች ሰለባ ሲሆኑ ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ቡድን ወደስፍራው አቅንቶ ውይይት ያደረገ ቢሆንም ሳምንት ሳይቆይ ጥቃቱ አገርሽቶ በርካታ ንጹሐን ዜጎች በታጠቁ ኀይሎች መገደላቸው አይዘነጋም፡፡
Leave a Reply