“ግብርና ውስጥ ለውጥ አለ” | ደምስ ጫንያለው  (ዶ/ር)
እንግዳ

“ግብርና ውስጥ ለውጥ አለ” | ደምስ ጫንያለው  (ዶ/ር)

እንግዳችን ዶ/ር ደምስ ጫንያለው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ በተለይም በኢትዮጵያ ግብርና ዙሪያ በርካታ የምርምርና የማማከር ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ በሕትመትና ብሮድካስት ሚዲያዎች እየቀረቡ በርካታ ገለጻዎችን በመስጠትም ይታወቃሉ፡፡ ስለ አገራችን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮች አወያይተናቸዋል፡፡

ሲራራ፡-  የግብርናው ዘርፍ በኢትዮጵያ ኦኮኖሚ ላይ ያለው አስተዋጽዖ ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ደምስ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ  ከአገሪቱ  ጥቅል ምርት  ከ33-35 በመቶ ድረሻ ይሸፍናል ሲባል እሰማለሁ፡፡ ሆኖም እኔ ባደረኩት ጥናትና ምልከታ ግብርናው የአገሪቱን ጥቅል ምርት 54 በመቶ ድረስ እንደሚሸፍን አረጋግጫለሁ፡፡ ለዚህም በቂ ማስረጃዎች አሉኝ፡፡ በብሔራዊ ባንክም ሆነ በሌሎች ተቋማት የሚገለጹት አሐዛዊ መረጃዎች ትክክል አለመሆናቸውን አይቻለሁ፡፡ ይህንንም በቅርቡ ባወጣሁት መጽሐፌ ላይም ከነማስረጃው አስቀምጨዋለሁ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን የምግብ ፖሊሲ አውጪዎች ባወጧቸው ጽሑፎችም ያረጋገጡት እውነታ ነው፡፡

እዚህ ላይ መጠንቀቅ ያለብን፤ ብዙ ሰዎችም የሚስቱት ነገር ‹ግብርና ሲባል ምንድን ነው?› የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ብዙ ሰው ግብርናን ከእርሻ፣ ከሰብል ምርት ጋር ብቻ አያይዞ ሲወራ ይታያል፡፡ ግብርና እና እርሻ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እርሻ አንዱ የግብርና ዘርፍ ወይም አካል ነው፡፡ እርሻ ሲባል ደግሞ ብዙ ባለሙያዎችም  ሆኑ ፖሊሲ አውጭዎች የሚያገናኙት ከዓመታዊ የሰብል ምርት ጋር ነው፡፡ የእንስሳት እርባታ በእርሻ ውስጥ የሚካተት አንዱ ዘርፍ ነው፡፡ ያህንን የሚረዳው ሰው በጣም ጥቂት ነው፡፡

ሌላው በመንግሥት ደረጃም የሚነገር አንድ የተሳተ ነገር አለ፡፡ በአገራችን የግብርናው ዘርፍ 80 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ እንደያዘ ነው የሚገለጸው፡፡ ይህም ትክክል ያልሆነ አሃዛዊ መረጃ ነው፡፡ በግብርናው ሥር ተቀጥሮ የሚሠራው የሰው ኀይል ዛሬም ወደ 85 በመቶ ገደማ ነው፡፡ በግብርና ዘርፍ የሚሰበሰበው ግብር ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስ ጨምሮ ከ75-80 በመቶ የሚደርስ ነው፡፡ ወደኋላ ቀርቷል ብለን የምናወራለት ግብርና ዛሬም ቢሆን የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረት  ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ይህን ያህል ኢኮኖሚ ተሸክሞ የሚገኘውን የግብርና ዘርፍ ከመንግሥት ጀምሮ በአግባቡ ያወቀውና የተረዳው አካል የለም፡፡ የግብርናው ችግር የሚጀምረው ግብርና ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቀው የፖለቲካ እና የፖሊሲ አውጪ  ጥቂት ከመሆኑ ነው፡፡ ሀኪም የበሽታ ምልክቶች ካልተነገረው በሽታውን መጠርጠር አይችልም፡፡ ሆድ ለቆረጠው ሁሉ አንድ ዓይነት መድሃኒት አይታዘዝለትም፡፡ ግብርናም ከዚያ የተለየ አይደለም፡፡ የግብርናውን ችግር ለማወቅም ሆነ ፖሊሲ ለማዘጋጀት ቅድሚያ ግብርናውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

ሲራራ፡- በእርስዎ ግምገማ የግብርናው ዘርፍ ምን ያህል በብቃትና በሚገባው ደረጃ እየተመራ ነው?

ዶ/ር ደምስ፡- እውነት ለመነጋገር ባለፉት 20 ዓመታት ግብርናው በጣም ትልቅ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ ይህ የማይካድ እውነታ ነው፡፡ ግብርና ውስጥ ለውጥ አለ፡፡ እኛ እየጠየቅን ያለነው ዕድገቱ በቂ ነው ወይ? ከዚህ በላይ ማደግ መለወጥ አንችልም ወይ? ከዚህ በላይ ግብርናው ውጤታማ ሆኖ ኢንዱስትሪውን መምራት ወይም የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ዕድገት ማቀጣጠል አይችልም ነበር ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ነው የምናነሳው፡፡ ለነዚህ ጥያቄዎች መልሱ ማደግ ባለብን ልክ አላደግንም የሚል ነው፡፡ ትንሽ ዕድገት አስመዝግበን መዝናናትን ከመረጥን ግን አዎ ዕድገት አስመዝግበናል፡፡ ከ1996 -1997 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ግብርና ከዜሮ በታች ዕድገት አስመዘግቦ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ዘርፉ ከዜሮ በታች የሆነ ዕድገት አስመዝግቦ አያውቅም።

የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በግራፍ ብናስቀመጥ፣ ዕድገቱም ቁልቁለቱም የሚወሰነው ግብርናው ከሚያሳየው እመርታ አንጻር ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየወደቀም እየተነሳም ቢሆን 7 በመቶ አካባቢ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ የዚህ ምስጢር ከመረመርነው ዕድገቱ የመጣው በግብርናው ምክንያት ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ኢንዱስትሪውም፣ አገልግሎት ዘርፉም የዕድገት ምጣኔያቸው ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ ላላፉት ዐሥራ አምስት እና ዐሥራ ስድስት ዓመታት ግብርናው እስከ 7 በመቶ አድጓል፡፡ ከዚህ ቀደም ነበሩ ዓመታትም እስከ ዐሥራ አምስት በመቶ ድረስ ያደገበት ጊዜ ነበረ፡፡  በሌላ በኩል ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት በኤልኒኖ ምክንያት በ3.5 በመቶ የወረደበት ጊዜም  ነበር፡፡

በጥቅሉ ግን የግብርናው ዘርፍ ዕድገት እያስመዘገበ ቢሆንም ዕድገቱ በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ ብዙዎቻችን የሚያስማማ ሐቅ ነው፡፡ ለምንድን ነው የሚጠበቀው ውጤት ከግብርና ያልተገኘው? ከተባለ የአመራር ሂደቱ ምን ይመስል ነበር? የሚለውን ዘወር ብለን እንድንፈትሽ ያደረጋል፡፡ እዚህ ላይ ብዙ አሻሚ ነገሮች አሉ፡፡ የአገሪቱ ግብርና የሚመራበት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ተቋም/ሥርዓት፣ ፕሮግራም ወዘተ… የሚሉ ነገሮች በደንብ መታየት አለባቸው፡፡ የነዚህ ቅንጅት ነው አውንታዊ ለውጥ አስተዋጽዖ የሚያበረክተው፡፡ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ብቻውን የትም አያደርስም፡፡

እዚህ ላይ የግብርናውን ዕድገት ከእርምጃ ጋር አያይዘን እንየው፡፡ አንድ ሰው ሦስት እርምጃ የመራመድ አቅም እያለው አንድ እርምጃ ቢራመድ፤ አንዱን እርምጃ የምናየው በአወንታ (positive) ነው፡፡ ምክንያቱም ሰውየው አንድም ብትሆን እርምጃ ተራምዷልና ነው፡፡ ግብርናውም እንዲሁ ነው፡፡ በዘርፉ ዕድገት ቢኖርም ዕድገቱ ግን ከአቅም በታች የሆነ አፈጻጸም ነው ያለው፡፡

ዘርፉ ማደግ ባለበት መጠን አላደገም ስንል አንዱ ማሳያችን የምርት መጠን ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የቦቆሎ ምርትን ብናይ፣ የበቆሎ ዓመታዊ አማካኝ  ምርት በሔክታር 22 ኩንታል ገደማ ነበር፡፡ ዛሬ ወደ 60-70 ኩንታል ድረስ ማሳደግ ተችሏል፡፡ አንዳንድ ሞዴል የሚባሉ ገበሬዎች 80-100 ኩንታል ድረስ ያመርታሉ፡፡ ባለፉት ኹለት ዓመታት ከ22 ኩንታል ብዙም ሳንሄድ 30 ኩንታል ላይ ቆመን ነው የቆየነው፡፡ ስንት ግርግር ተፈጥሮ፣ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር ተጠቀመን ተብሎ ነው ይህም ውጤት የተገኘው፡፡ ነገሮችን ጠለቅ ብለን ስንመረምር፣ ራሳችን ከዓለም  አገሮች ጋር ስናወዳድር፤ ከጎረቤቶቻችን ከሰሐራ በታች ከሉ አገሮች ጋር ብናነጻጽር አሁን እኛ አስመዘገብን የምንለው የዕድገት መጠን በጣም የወደቀ ነው፡፡

ኹለተኛ ማሳያ በማዳበሪያ፣ በምርጥ ዘር ስርጭት ወዘተ… ያለውን ሁኔታ መመልከት ነው፡፡ በጣም ዝቅተኛ ስርጭት ነው ያለው፡፡ አሁን ማዳበሪያ የሚጠቀመው የአርሶ አደር ብዛት 30 በመቶም በአግባቡ የሚሞላ አይደለም፡፡ ዛሬ ስለግብርና ይህ ሁሉ እየተወራ ምርጥ ዘር የሚጠቀመው አርሶ አደር ከ10 በመቶ አይበልጥም፡፡ በአብዛኛም ምርጥ ዘር የምንጠቀመው ለቦቆሎ እና ለስንዴ ነው፡፡ ገና ብዙ ይቀረናል፤ ሠራነው ከምንለው ያልሠራነው ገና ብዙ ነው፡፡ ዛሬ እኮ ነው በትራክተር ትንሽም ቢሆን መንቀሳቀስ የጀመርነው፡፡ ዛሬም እኮ በሬ ሞፈር ጎትቶ ነው ምርት የምናመርተው፡፡

የግብርናው ዘርፍ ከአመራር ስልት መነፅርም ብንመለከተው ከፍተኛ ከፍተት እንዳለበት ነው ማየት የሚቻለው፡፡ እ.ኤ.አ 2016 ዓ.ም. የግብርናው ዘርፍ ላይ ያለውን የአመራር ብቃት የሚቃኝ አንድ ጥናት አጥንተን ነበር፡፡ በጊዜው በርካታ የገጠር ቀበሌዎችን ዞረን ለማየት ሞክረናል፡፡ ግብርና የሚሠራው አስፓልት ላይ አይደለም፤ በከተሞችም አይደለም፡፡ ግብርና የሚሠራው በገጠር መሬት ላይ ነው፡፡ መሬቱ ያለበትን ቦታ የሚያስተዳድረው ወረዳ አስተዳዳሪም ሆነ ከዚያ በታች ያለው የግብርናውን ዘርፍ የሚመራው አመራር ወሳኝነት አለው፡፡ አመራሩ ዕውቀትና ክህሎት ከሌለው እና በፖለቲካ ሆይሆይታ ብቻ የሚሾም ከሆነ የሚሠራው ነገር ሁሉ ዜሮ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ በጥናት ያረጋገጥነው ነው፡፡ በተግባርም ያየነው ያንኑ ነበር፡፡ አብዛኛው የገጠር ቀበሌ የግብርና ዘርፍ አመራር ሙያዊ ክህሎት የሌለው ልምድም የሌለው ነው፡፡ አሁን መጠነኛ ለውጦች እንዳሉ እየታዘብን ነው፡፡ ሆኖም አሁንም ብዙ ይቀራል፡፡

አንድ ወረዳ ሲቋቋም ለአስተዳደር ሥራ እንዲመች ብቻ አይደለም የሚቋቋመው፡፡ በቦታው ሊገኝ የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እሳቤ ውስጥ ገብቶ ነው፡፡  ወረዳው የተቋቋመው ግብርናን መሠረት አድርጎ ከሆነ የሚመደብለት አመራርም ያንን የሚረዳ መሆን አለበት፡፡ ክህሎት የሌለውን አመራር አስቀምጦ፤ ግብርናውን ይደግፋል የተባለው ባለሙያውም ክህሎት የሌለው ከሆነ ዘርፉን ለመደገፍ ትራክተር ቢመደብ፣ መኪና ቢመደብ፣ ሞተር ሳይክል ቢመደብ ለውጥ አያመጣም፤ ትርፉ ብክነት ነው፡፡ ያ የተመደበው መኪናና ሞተር-ሳይክል ለፖለቲካ ሥራ ሲውል ነው የሚገኘው፡፡ ለግብርና ዘርፍ ውጤት ማጣት ምክንያቶቹ ጠለቅ ተብሎ ከተመረመረ ሥር የሰደደ ተቋማዊ ብለሽት አለ፡፡ ተቋማቱን በብቃት መምራት አለመቻል፣ የቅንጅት ችግር፣ ለግብርና የተመደበውን ሀብት ለሌላ ሥራ ማዋል በስፋት የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡

ሲራራ፡- በምርምር ሂደት ከአንድ አካባቢ አፈር እና አየር ሁኔታ ጋር የሚስማማ ዘር አበልጽጎ ለገበሬው ከማዳረስ አንጻር ምን ያህል ርቀት ተሂዷል?

ዶ/ር ደምስ፡- እኔ ከሃያ ዓመት በላይ ሥራዬን በግብርና ምርምር ውስጥ ነው ያሳለፍኩት፡፡ በግብርና ሥራ ውስጥ ሦስት ወሳኝ ሥራዎች አሉ፡፡ አንደኛው ምርምሩ ነው በዚህ ውስጥ የአፈር ምርምር፣ የተሻሻሉ የዘር ዓይነቶችን ማውጣት የመሳሳሉ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ኹለተኛው ደግሞ ምርምሩን የሚሞክረው እና አርሶ አደሩን የሚያለማምደው ነው፡፡ ሦስተኛው አርሶ አደሩን ካላመደ በኋላ የሚያስፈልገውን ግብዓት የሚያቀርበው አካል ነው፡፡ በነዚህ ቅንጅት ነው ሥራዎችን የሚያካሂዱት፡፡

ከዓመታት በፊት በርካታ የምርምር ሥራዎች ተሠርተው ነበር፡፡ በነዚህ ምርምሮች ውስጥ ተሳትፌም ስለነበር በደንብ ነው የማውቃቸው፡፡ ምርምሮቹ ግን ዛሬም ደረስ መሬት መውረድ አልቻሉም፡፡

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የመሬት ካርታ እናዘጋጃለን ተባለ፡፡ እንደሰለጠኑት አገሮች እያንዳንዱን የአፈር ዓይነት እየለየን በዚያ መሠረት አስፈላጊውን የአፈር ማዕድን እናቀርባለን ተባለ፤ ግርግር ተፈጠረ፤ ግን ዛሬም መሬት የወረደ ነገር የለም፡፡ አንዳንዱ ፕሮጀክት ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት ነው ድምጹ እንዲጠፋ የተደረገው፡፡

እንደ አቅማችን የምርምር ሥራ የሚሠራ ተቋም ከተቋቋመ ዛሬ ከ50 ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ተቋሙ ብዙ የምርምር ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ነገር ግን አቀናጅቶ ወደ መሬት ከማውረድ አንጻር ከፍተኛ ችግር ነው ያለው፡፡

በግብርና ውስጥ አንድ ያልተረዳነው ክፍል አለ፤ ያም ገበሬው ነው፡፡ በዚህ አገር በግብርና ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ገበሬው ነጻ መሆን አለበት፡፡ አሁንም ቢሆን ገበሬው ነጻ አይደለም፡፡ በብዙ ነገሮች ተተብትቦ ነው ያለው፡፡

ገበሬ ሞኝ አይደለም፡፡ ሳይንቲስት ኖረም አልኖረ በአንድ አካባቢ ምን እንደሚበቅል እና መቼ እንደሚበቅል ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ መሬቱ ላይ ምን መብቀል እንደሚችል ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ችግሩ አሁንም ቢሆን በምርምር የዳበረውን ሥራ ዛሬም እያገኘ አይደለም፡፡

እንዳንድ ጥናቶች የሚያሳዩት ለገበሬ ብድር ብቻ እንኳን ቢመቻችለት የማዳበሪያ ተጠቃሚነቱ ከ30 በመቶ በላይ ከፍ ይላል፡፡

ሲራራ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት በአገራችን የምግብ ዋስትና መረጋገጡን ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ በአንጻሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ምሁራን የምግብ ዋስትና ገና እንዳልተረጋገጠ ይሞግታሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

ዶ/ር ደምስ፡- የምግብ ዋስትና መረጋገጥ አለመረጋገጡን ለመለካት የሚያስችሉ በርካታ መንገዶች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ፤ አንድ አገር የምግብ ዋስትናውን አረጋግጧል ለማለት እያንዳንዱ ግለሰብ ቢያንስ በቀን 2100 ኪሎ ካሎሪ ማግኘት አለበት፡፡ ያን ለማግኘት ደግሞ በእህል ምርቶች ይሰላል፡፡ መስፈርቱን ለሟሟላት አንድ አገር ቢያንስ በዓመት በነፍስ ወከፍ 2.16 ኩንታል ምርት መኖር መቻል አለበት፡፡

በኢትዮጵያ ቀድሞ በነበረው ሆኔታ 1.66 ኩንታል ላይ ነበርን፡፡ አሁን በአገሪቱ በተከናወነው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቀድ ሥራ 3 ኩንታል በነፍስ ወከፍ ላይ ደርሰናል፡፡ የምግብ ዋስትና መለኪያ መሥፈርቱንም አልፈናል፡፡ እንደ ዓለም ዐቀፉ የምግብ ድርጅት መለኪያ መስፈርትን ካለፍን ቆይተናል፡፡ መንግሥትም ይህንኑ ሲነግረን ነው የቆየው፡፡ ያ ግን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የምግብ ሚዛንን (ባልንስን) እንደ መሥፈርት መጠቀም ያለብንም ይመስለኛል፡፡ 3 ኩንታል የሚለው ስሌት አጠቃላይ ምርቱ ለአገሪቱ ሕዝብ ተካፍሎ የሚመጣ የቁጥር ጉዳይ እንጅ በእያንዳንዱ ቤት ይህን ያህል ምርት ይገባል ማለት አይደለም፡፡ በአገር ደረጃ የምግብ ዋስትና ተረጋግጧል ቢባልም በቤተሰብ ደረጃ ግን አሁንም ገና አልተረጋገጠም፡፡ የምግብ ዋስታናን ለማረጋገጥ ማምረት ግዴታ ላይሆን ይችላል፡፡ ኤልኒኖ በተከሰተበት ጊዜ የማንንም እርዳታ ሳንጠይቅ በዓመት 20 ቢሊዮን ብር ድረስ አውጥተን ስንዴ ማስገባት ችለናል፡፡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ  ያም አንዱ መንገድ ነው፡፡

አሁን ለውጦች ቢኖሩም ጨርሶ በቂ አይደሉም፡፡ በቁጥር አይደለም መነጋገር ያለበን፡፡ መሬት ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ነው መነጋገር ያለብን፡፡ ቁጥሮቹ የሚሉን ትክክል አይደለም፡፡ ቁጥሮቹ የሚሉት የዛሬ ሃያ ዓመት የአገሪቱ የድህነት ምጣኔ 40 በመቶ ገደማ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ  23 በመቶ እንደወረደ ነው የሚነግሩን፡፡ በየጥጋጥጉ የወደቀው የድሃ ቁጥር ግን ከዚያ በላይ ነው፡፡ ሳይበላ የሚያድረውን የኢትዮጵያዊ ቁጥር ካየነው ዛሬም ስላለው ድህነት ቁጭ ብለን መነጋገር እንዳለብን ነው የሚገልጸው፡፡ ዓለም የሚጠቀምበትን የሰብአዊ ልማት መመዘኛን ብንመለከት ኢትዮጵያ ባለችበት እየረገጠች መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡ በዓለም ደረጃ ብትወስድ ኢትዮጵያ 173-174 ላይ ነው የነበረች፤ አሁንም እዚያው ላይ ነች፡፡

ሲራራ፡- የእርሻው ዘርፍ  የመሬት አጠቃቀም ብዙ ሲተች ይሰማል፡፡ አብዛኛው አርሶ አደር በብጣሽ መሬት ነው የሚያርሰው፤ ይህም ገበሬውንም አገርንም እየጎዳ ነው የሚሉ ትችቶች ይሰማሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

ዶ/ር ደምስ፡-  በዚህ ጉዳይ ላይ ሲጮሁ ከነበሩ ባለሙያዎች መካከል አንደኛው እኔ ነኝ፡፡ ወደ መካከለኛ እና ትልልቅ እርሻዎች ማደግ ካልተቻለ ዘርፉ የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ የትኛውም ግብርና ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚቻለው ሰፋ ያለ የእርሻ ቦታ ሲኖር ነው፡፡ ለምሳሌ በሰብል ልማት ላይ አንድ ትራክተርን ወደሥራ ለማስገባት ራሱ የሚፈልገው የማሳ ስፋት አለ፡፡ የበሬ ግንባር በምታክል መሬት ላይ ትራክተር ይዞ መግባት አይቻልም፡፡ አዋጭም አይደለም፡፡ በአርብቶ አደርም ደረጃ የማለቢያ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም በዛ ያለ የከብት ቁጥር ሊኖር ይገባል፡፡ ለአንድ ከብት ቴክኖሎጂ መጠቀም ያን ያህል አዋጭ ላይሆን ይችላል፡፡

አሁን ጩኸታችን ከሞላ ጎደል እየተሰማ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም፤ ማዳበሪያ እንዲያገኝ የታክስ ቅነሳ እየተደረገ ነው፡፡ በደጋማው የአገሪቱ ክፍል የተበጣጠሰውን የመሬት ክፍል ወደ አንድ ለማምጣት ጉን ለጎን ያለው አርሶ አደር በፍቃደኝነት ወደ አንድ እርሻ እንዲመጣ መሥራት መቻል አለብን፡፡ ያን ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡ ከባድ ቢሆንም የማይቻል ግን አይደለም፡፡ ግን መንግሥት መሬታቸውን ሰፍተው ለሚሠሩ አርሶ አደሮች ማበረታቻዎችን መስጠት መጀመር አለበት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የአንድ አርሶ አደር አንድ ሔክታር የማይሞላ መሬት ሦስት ቦታ ተከፋፍሎ በተለያየቦታ ነው ያለው፡፡ ይህን ወደ አንድ ለማምጣት አርሶ አደሩ በፍቃደኝነት አንዱ ወደ ሌላው ሲሄድ፣ ሌላው ወደ አንዱ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል፡፡ ምናልባት የአፈር ለምነት ልዩነት የሚያመጣ ከሆነ ድጎማ መድረግን በአማራጭነት መያዝ ይቻላል፡፡ መንግሥትም እንዚህ ዓይነት ሐሳቦች እንዳሉት ሲገልጽ እየሰማን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመረተው የሰብል ምርት 99 በመቶ የሚሆነው ከዐሥር ሔክታር በማይሞላ መሬት ባለቸው አርሶ አሮች የሚመረት  ነው፡፡ ከዚያ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው ምርት የሚያመርተው ከሁለት ሔክታር በታች በሆነ መሬት ባለው አርሶ አደር  ነው፡፡ አሁን የሚፈለገው አርሷ አደሩ 25 ሔክታር መሬት እንዲያርሱ አይደለም፡፡ ሁለት ሔክታር ያለው ወደ አምስት፣ አንድ ያለው ወደ ኹለት እንዲያሳድግ ነው፡፡ ይህ  ሲሆን የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙም አብሮ የሚያድግ ነው የሚሆነው፡፡

 

April 5, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *