“የፍትሕ ሥርዓቱ አሁንም ችግር ላይ ነው” አቶ ተክሌ በቀለ
እንግዳ

“የፍትሕ ሥርዓቱ አሁንም ችግር ላይ ነው” አቶ ተክሌ በቀለ

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በአገራችን በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተላልፎ የነበረውን ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛው አገራዊ ምርጫ በዚህ ዓመት እንዲካሄድ ወስኗል:: ሆኖም የአገሪቱ የጽጥታ ባልተረጋጋበት፣ በርካታ ፖለቲከኞች በእስር ቤት ውስጥ በሚገኙበት እና በቂ ዝግጅት ባልተደረገበት ሁኔታ እንደምን ያለ ነጻና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ይቻላል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው:: በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከኢዜማ የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተክሌ በቀለ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል:: ውይይቱን እነሆ፡-

ሲራራ፡- በአገራችን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የሕገ መንግሥት ትርጉም እስከማድረግ ተሂዶ ምርጫው እንዲራዘም ተደርጎ ነበር። ሆኖም በቅርቡ የጤና ሚኒስቴር ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ማለቱን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ዓመት ምርጫ እንደሚካሄድ ገልጿል። ወረርሽኙ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንዳልሆነ እየታወቀ የጤና ሚኒስቴር ይህን ማቅረቡና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መወሰኑ ምን ያህል አሳማኝ ነው?

አቶ ተክሌ፡- እንደተባለው በአገራችን በኮቪድ-19 የሚያዘው ዜጋ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ያለው:: በአፍሪካ ደረጃም እንደ አገር ከፍተኛውን ቁጥር እያስመዘገብን ነው ያለው:: ነገር ግን ነገሮችን መመዘን ያለብን በተከናወኑበት ወቅት ባለው እውነታ ነው የሚል እምነት አለኝ:: በወቅቱ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማድረግ እንደማይችል የጤና ሚኒስቴርን ምክረ ሐሳብ በመቀበል መናገሩ የሚታወስ ነው:: በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የነበርንበትን ሁኔታ በትኩረት ማጤን እንዳለብን ነው የሚሰማኝ:: ምክንያቱም በሰዓቱ ኮቪድ-19 በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ያደርስ ነበር:: ወደ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ቫይረሱ በስፋት እየተሰራጨ የነበረበት ጊዜ ነበር:: በወቅቱ እንደ መንግሥት፣ እንደ ሕዝብ፣ እንደ ግለሰብም ከፍተኛ የሆነ መደናገጥ ውስጥ ነበር የገባነው:: በወቅቱ ከ50 በላይ አገሮች ምርጫ ሰርዘዋል:: የተፈጠሩት መደናገሮች በመንግሥታት ውሳኔ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረው እንደነበር መገንዘብ ያስፈልጋል::

የኢትዮጵያ ሕዝብ ተውካዮች ምክር ቤት ምርጫውን ለማራዘም ሲወስን፣ የዓለም ጤና ድርጅት እና የጤና ሚኒስቴር የሚሰጡትን የሐሳብ ግብዓት ተከትሎ ምርጫው ይከናወናል የሚል ሐሳብ አቅርቦ ነበር:: በጊዜ ሂደት የዓለም ጤና ድርጅትም በተደጋጋሚ በሚሰጣቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች ከበሽታው ጋር እየተላመድን ጥንቃቄ እያደረግን መኖር እንዳለብን ነው እየመከረ ያለው:: የእኛም የጤና ሚኒስቴር ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚዛመድ ምክር ነው እየሰጠ ያለው:: ሚኒስቴሩ ምርጫ ብቻ ሳይሆነ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ትምህርት ቤቶችም ይከፈቱ የሚል ምክረ ሐሳብ አቅርቧል:: በዚህ ሰዓት የዓለም ሁኔታ ከምክር ቤቱ ውሳኔ ብዙም የማይለይ ነው:: በጥቅሉ ቀደም ሲል የተላለፈው ውሳኔ፤ ለውሳኔም ምክንያት የነበረው ሁኔታ እና አሁን እኛም ዓለምም ያለንበት ሁኔታ በሚገባ መታየት አለበት:: ከዚህ አንጻር ከታየ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል መባሉ አግባብነት ያለው ነው::

ሲራራ፡- ከወረርሽኙ ወጣ ብለን ስለ ፖለቲካ ምኅዳሩ ስንነጋገር፣ በአገራችን ነጻና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለ? በርካቶች ምርጫው ቢደረግ እንኳ ካለው የጸጥታ ሁኔታ አንጻር ሰላማዊ በሆነ መልኩ ይጠናቀቃል የሚል እምነት የላቸውም:: በዚህ  ላይ እርስዎ ሐሳብ ምንድን ነው?

አቶ ተክሌ፡- ምክር ቤቱ ምርጫው እንዲራዘም ሲወስን ያስቀመጠው ነገር የኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ስጋት አለመሆኑ በሚመለተው አካል ከተረጋገጠ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ [ምርጫ] ሊደረግ እንደሚችል ነው:: ከዚያ አኳያ አሁን የተወሰነው ውሳኔ አግባብነት ያለው ነው:: ይሁን እንጅ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ውሳኔዎች ሳይወሰኑና እና ሳይሠሩ ቀርተዋል:: አሁንም እነዚያ ሥራዎች እየተሠሩ አይደለም:: እንዲያውም አገሪቱ ምርጫ የምታከናውንም አትመስልም::

የጸጥታው ሁኔታ በመላው አገሪቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው:: በየጊዜው በየቦታው ግጭት እየተቀሰቀሰ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን እየተነጠቅን ነው ያለነው:: የጸጥታው ሁኔታ እንኳን ለምርጫ የእለት ተለት እንቅስቃሴንም ለማድረግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል:: ከአዲስ አበባ ወጣ ሲባል ያለው ነገር እጅግ የሚያሳዝን ነው:: በበኩሌ መንግሥት ይህን ችግር ለመፍታት አቅም አንሶት ነው የሚል እምነት የለኝም:: ጉዳዩ ከፍላጎት ማጣት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑን እየተመለከትን ያለነው:: በአንዳንድ ቦታዎች የራሱ የመንግሥት አካላት የግጭቱ አርክቴክቶችና ተዋናዮች ሲሆኑም ተስተውሏል::

የፖለቲካ ፓርቲዎችም የመቀራረብ እና የመነጋገር ሁኔታውን በስፋት አልሄዱበትም:: እነዚህ እስካሁን መሠራት የነበረባቸው እና መጀመር የነበረባቸው ጉዳዮች ነበሩ:: ነገር ግን በውዝፍ ሥራነት እስካሁን እየተንከባለሉ ዛሬ ላይ ደርሰዋል:: ፓርቲዎች እንዲነጋገሩ መድረክ የማመቻቸት እና ዕድሎችን የመፍጠሩ ሁኔታ በመንግሥት አቅም መከወን የሚችል ቢሆንም በመንግሥት ቁርጠኝነት ማጣት እስካሁን ይህን ማድረግ አልተቻለም:: በጥቅሉ ሲታይ ያለንበት ሁኔታ የምርጫ ዝግጅት ለማድረግ የ9 ወር ጊዜ ብቻ የቀረን አይመስልም:: ይህ አደገኛ ነው:: ምርጫው ተዓማኒነት እንዳይኖረው፣ የሚመሠረተው መንግሥትም የቅቡልነት አደጋ የተጋረጠበት እንዲሆን፤ ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ጥሩ መደላድል መፍጠር ሲቻል ተመልሰን ወደ ግጭት አዙሪት ልንገባ የምንችልበትን ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል:: መጪው ምርጫ በብዙ መልኩ የአገሪቱን መጻዒ ዕድል የሚወስን ነው:: በብስለትና በአርቆ አሳቢነት መንፈስ ከተራመድን ኢትዮጵያ ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር የምታደርግበት ዕድል ይፈጠራል:: እንደተለመደው ገዥው ፓርቲ በብልጣብልጥነት እና በአፈና መንገድ ለመቀጠል የሚሞክር ከሆነ ግን ጉዟችን ከመቼውም ጊዜ በላይ አደገኛ ነው:: ከጊዜያዊ የቡድን ጥቅም ባሻገር ማሰብ ያስፈልጋል:: መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር እየተናበበ ከሠራ የጸጥታውንም ሁኔታ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ማስተካከል ይቻላል፤ ተዓማኒነት እና ቅቡልነት ያለው ምርጫም ማደረግ ይቻላል::

ሲራራ፡- በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እስር ቤት እንደሆኑ ይታወቃል:: በዚህ ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ምን ያህል የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሽግግር ያግዛል? ምን ያህልስ ቅቡልነትስ ይኖረዋል?

አቶ ተክሌ፡- በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ ምንም ማለት አልፈልግም:: ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች በእስር ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መኖራቸው እውነት ነው:: የአመራሮች መታሰር ደግሞ በፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ ላይ ችግር መፍጠሩ ሳይታለም የተፈታ ነው:: ስለዚህ ይህ ሁኔታ በአጠቃላይ የፖለቲካ ምኅዳሩም ሆነ በምርጫው ላይ የራሱን ጥላ እንደሚያጠላ የሚያከራክር አይደለም::

የፖለቲካ እስረኛ የወንጀል ድርጊት ከፈፀመ እስረኛ ተለይቶ የሚታይበት አሠራር መኖር እንዳለበት አምናለሁ:: ይህን የምለው የወንጀል እስረኞች እና የፖለቲካ አስረኞችን አግበስብሶ የሚሄድ ሥርዓት በስፋት ስለማይ ነው:: ይህ አካሄድ መጥራት እንዳለበት ይሰማኛል:: በሕግ መጣራት ያለበት በሕግ፣ የፖለቲካው ጉዳይ ደግሞ በፖለቲካ ዐይን መታየት አለበት:: በወንጀል ድርጊት ላይ የተሳተፈ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አይጠየቅ የሚል አካል የለም፤ ካለም በጣም ስህተት ነው:: ሆኖም በአገራችን ዛሬም እንደ ትናንቱ የፍትሕ ሥርዓቱ የፖለቲካ መሣሪያ መሆን የለበትም ነው እየተባለ ያለው:: የዚህች አገር ትልቁ መከራ እና ፖለቲካችንም ፈቀቅ ማለት ያልቻለው የፍትሕ ሥርዓቱ በነጻነት እና በገለልተኛነት ፍትሕን ለማስከበር አለመቻሉ ነው:: ከፖለቲካ መሣሪያነት ራሱን ነጻ ያወጣ የፍትሕ ሥርዓት ካልገነባን ዛሬም ነገም ባለንበት መሄዳችን አይቀሬ ነው:: ያለ ጥርጥር የፍትሕ ሥርዓቱ አሁንም ችግር ላይ ነው:: ብዙ መጥራትና መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ::

ሲራራ፡- የተለያዩ አካላት በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ሲሰጣቸው ፖሊስ ትዕዛዙን አክብሮ ያለመፈፀም ሁኔታዎች እየታዩ ነው:: እንዲህ ዓይነቱ በተደጋጋሚ የሚታይ አካሄድ ሕግና ሥርዓትን ከማስከበር አኳያ፤ በተለይም በፍትሕ ተቋማት ላይ መተማመን እንዲኖር ከማድረግ አንጻር የሚኖረውን አንድምታ እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ተክሌ፡- ፍርድ ቤት ነጻ ያለውን ወይም የዋስ መብቱ ተከብሮለት ከእስር ቤት ውጭ ሆኑ ይህ እንዲከራከር የፈቀደለትን ተጠርጣሪ ፖሊስ አስሮ የሚያቆየው ከሆነ፣ በፍትሕ ተቋማት መካከል ከፍተኛ የመናበብ ችግር እንዳለ የሚያሳይ ነው:: በአስፈሪ ሁኔታ እየተደጋገመ የመጣ እጅግ አደገኛ አዝማሚያ ነው:: ይህ ለውጥ እንዲመጣ ገፊ ምክንያት ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ እና ዋነኛው የፍትሕ ሥርዓቱ መዝቀጥ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው:: በለውጡ ማግስት ስለ ፍትሕ ተቋማት ዝቅጠት በስፋት ሲዘገብ እንደነበርም እናስታውሳለን:: ይህን አሳፋሪ ሁኔታ ተሻገርነው ስንል አሁንም እዚያው ላይ መገኘታችን የሚያንገበግብ ነው::

ፍርድ ቤት የወሰነውን ጉዳይ ፖሊስ አልለቅም የሚልበት ሁኔታ በምንም ተዓምር መኖር የለበትም፤ አልነበረበትምም:: በዚህ ጊዜ የቀደመውን ኢሕአዴግ ተግባር ማየት እና መስማት ያለብን አይመስለኝም:: ፍርድ ቤት የለቀቀውን አካል ፖሊስ የሚይዝበት ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም:: ይህን ተግባር በፓርቲ ደረጃ አውግዘናል:: መወገዝም ያለበት ነገር ነው:: እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ሕዝብ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለው ተስፋ ጨርሶ እንዲሞት የሚያደርግ ነው:: እንደዚያ ያለ ስሜት ምን ሊፈጥር እንደሚችል ደግሞ ከሁለት ሦስት ዓመት በፊት በሚገባ አይተነዋል:: መታረም ያስፈልጋል::

በጥቅሉ እያየን ያለነው አካሄድ መንግሥት የሕግ እና ሥርዓት የበላይነትን ለመገንባት በሚያካሂደው እንቅስቃሴ ላይ ጥቁር ጥላሸትን የሚቀባ ተግባር ነው:: መንግሥት አሁንም የፍትሕ ሥርዓቱን በአግባቡ መፈተሽ እና የእርማት እርምጃዎችን መውሰድ አለበት:: እንዳልኩት እንዲህ ዓይነት ተግባራት በተደጋገሙ ቁጥር ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያላቸው እምነት እየተናደ ነው የሚሄደው::

ሲራራ፡- ለውጡ ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ለማድረግ ያግዛል በሚል ብዙ ኢትዮጵያዊያን ተስፋ አድርገው እንደነበር ይታወቃል። በእርስዎ ግምገማ የለውጡ ሒደት የገጠሙት ችግሮች ምንድን ናቸው? መፍትሔዎችስ?

አቶ ተክሌ፡- አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ በርካታ ኢትዮጵያውያን በለውጥ አመራሩ ላይ ተስፋ ጥለው ነበር:: አሁንም ቢሆን ዜጎች በለውጥ አመራሩ ላይ ያላቸው ተስፋ ተሟጦ አልቆ መዝገቡ ተዘግቷል የሚል እምነት የለኝም:: የመንግሥት ቁርጠኝነት ካለ አሁንም ተስፋው የሚለመልምበት ዕድል አለ:: ችግሩ የመንግሥት አካላት አካሄዳቸውን ቆም ብለው መገምገምና ማስተካከል አለመቻላቸው ነው::

ለውጡ ከፍተኛ ፈተና እንደገጠመው ለሁሉም ሰው የሚታይ እውነታ ነው:: በበኩሌ ለዚህ ሁሉ መንስኤው በብልጽግና በኩል ያለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት አነስተኛ መሆኑ እንደሆነ ይሰማኛል:: በፓርቲው ውስጥ ውስን አመራሮች የለውጥ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል:: ይህንንም በተለያዩ መድረኮች እና ጽሑፎች መመልከት ይቻላል:: ነገር ግን በጥቅሉ ብልጽግና ከኢሕአዴግ የተለየ እሳቤ ያለው መስሎ አይታየኝም:: ሙስናው እና ዘረፋው ተባብሶ የቀጠለ መሆኑንም ማንም የሚመሰክረው እውነታ ነው::

ብዙም ሩቅ ሳንሄድ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች እየተዘረፈ ያለው መሬት እና የሕዝብ ሀብት ለተመለከተ በሥልጣን ላይ ያለው አካል የገባውን ቃል በልቷል የሚያስብል ነው:: አድልዎ እና ብልሹ አሠራሩን ሁሉም ሰው የሚያወራው ጉዳይ ነው:: ብልጽግና ከኢሕአዴግ የዘረፋ ባህል ያልተላቀቀ ባሕርይ ያለው መሆኑ አንዱ እና ትልቁ ፈተና እንደሆነ ይሰማኛል:: ትልቁ አደጋ ይህ ነው:: ኢሕአዴግ 30 ዓመታትን የቆየ ፓርቲ ነው:: 30 ዓመታት የቆየ ባህል ደግሞ በ2 እና 3 ዓመታት ይለቃል ማለት አይቻልም:: በሥርዓቱ ላይ የተለጠጠ ተስፋ ጥለው የነበሩ አካላትም እንደተሳሳቱ ነው የሚሰማኝ::

ሌላው ችግር የተቃዋሚው ጎራ መበታተን ነው:: በፓርቲዎች መሃል ያለው መደማመጥ ማጣት እና አንዳንድ ፓርቲዎችም የሰላም ጠንቅ መሆናቸው ሂደቱ እንዳይጠራ እና ለውጡም እንቅፋት እንዲገጥመው ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል የሚል እምነት አለኝ:: በገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በተፎካካሪውም ጎራ ችግር አለ:: በጣም ጥቂት ፓርቲዎች ናቸው ሽግግሩ ዴሞክራሲን በሚያዋልድ መልኩ ወደፊት እንዲሄድ እየታገሉ ያሉት::

ሲራራ፡- ብልጽግና ፓርቲም እንደ ቀድሞው ኢሕአዴግ ተጠያቂነትን ከማስፈን ይልቅ ጥፋት የሠሩ አመራሮችን ቦታ እያቀያየረ ሲሾም ይስተዋላል:: በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ሽግግር ሊደረግ የሚችለው?

አቶ ተክሌ፡- ከፍ ብየ እንደገለጽኩት ኢሕአዴግ 30 ዓመት የቆየ ድርጅት ነው:: ምንም እንኳን ስሙን ቢቀይርም አዲስ የፖለቲካ ባህል እና ልምድ ይኖረዋል ብዬ አላስብም:: ለምሳሌ በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ ችግር የፈጠረን ግለሰብ ምናልባትም ጉዳዩ የሕግ አግባብ መታየት ሲኖርበት እና ለሕግ መቅረብ ሲገባው እንደ ገና የአገሪቱ ሀብት ወዳለበት አካባቢ ላይ መላኩ እጅግ የሚያሳዝን ነው:: ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ብልጽግና ኢሕአዴጋዊ ባሕርይው ብዙም ያልተቀየረ መሆኑን ነው:: አሁን ከላይ እስከታች የምናው ጉዳይ 30 ዓመታት በሕወሓት/ኢሕአዴግ ላይ የነበረውን አካሄድ ነው:: ፓርቲዎች በተለያዩ የክልል ወረዳዎች ጽሕፈት ቤት ሲከፍቱ ጥቃት የሚደርስባቸው ከኅብረተሰቡ አይደለም፤ ከመንግሥት መዋቅር ነው:: ይህም የሚያሳየው ብልጽግና ከቀደመው ኢሕአዴግ እምብዛም አለመለየቱን ነው::

የተቃዋሚው ወገን በአስተሳሰብም ሆነ በመተባበር ደካማ መሆኑ እንጂ ብልጽግና በሥልጣን ላይ መቆየት የማይገባው በሐሳብ ድርቀት የተመታ ወይም ሐሳቡን የጨረሰ ፓርቲ ነው:: ጽንፍ በያዙ ሰዎች መሃል በመገኘቱ ብቻ ነው ኅብረተሰቡ ብልጽግና በሥልጣን ላይ እንዲቆይ ዕድል የሰጠው እንጂ ጥሩ አማራጭ ቢያገኝ እስካሁን በሥልጣን ላይ አያስቀምጠውም ነበር::

ሲራራ፡- እንደገለጹት በተቃውሞው ጎራ ያለው ያለመቀናጀትና አብሮ ያለመሥራት ችግር አሁንም እንደቀጠለ ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሁን ባሉበት በተበታተነ ሁኔታ እንዴት ነው ጠንካራ አማራጭ ሆነው መውጣት የሚቻሉት?

አቶ ተክሌ፡- ራስን ለማጠናከር ወደ ወስጥ ማየት በጣም አንገብጋቢ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ:: በተቃውሞ ጎራ ያለው ኀይል ቆም ብሎ ማሰብ እና ራሱን መፈተሸ አለበት:: አገራችን ትልቅ ፈተና ውስጥ እንዳለች ሁላችንም እያየን ነው:: ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ አደጋ ላይ ነው ያለው:: አንዳንዶቹ ገዥውን ፓርቲ እንደ ሕፃን ልጅ ዳዴ ሊያስብሉት ሲሞክሮ አያለሁ:: እኛም እንደ ፓርቲ አንድ ጠንካራ ፓርቲ እንዲኖር ስንደክም ከርመናል:: ሆኖም እኛ ስንጥር የነበረው ጠንካራ መንግሥት እንዲኖር ነበር:: በእርግጥም ጠንካራ መንግሥት እንዲኖር ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረግ ይገባዋል:: እኛ አሁንም ቢሆን ጠንካራ መንግሥት እንዲኖረን እንፈልጋለን:: ጠንካራ የአገር መከላከያ፣ ጠንካራ የደህንነት ተቋም፣ ጠንካራ ፍርድ ቤት፣ ጠንካራ ምርጫ ቦርድ፣ ጠንካራ የሰብአዊ መብት ድርጅት ወዘተ… እንዲኖረን እንፈልጋለን:: ለዚህም በምንችለው መንገድ ሁሉ እንታገላለን::

አንዳንድ ወገኖች ጠንካራ መንግሥት እንዲኖር እንፈልጋለን ስንል ጠንካራ ብልጽግና የምንፈልግ ይመስላቸዋል:: ብዙ የመረረ ትችት ሲሰነዘርብንም እናያለን:: እውነታው ግን እሱ አይደለም:: ብልጽግና የእኛ ተፎካካሪ ፓርቲ ነው:: የምናየውም እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ነው:: መንግሥት ግን መጠናከርና መዘመን አለበት:: ተቋማት ጠንካራ ከሆኑ የፈለገው ፓርቲ ቢፈርስ እና ቢፈራርስ ሕዝብ ሳይጎዳ ክፉን ጊዜ ማሻገር ይቻላል:: ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን መገንባት እና ጠንካራ መንግሥት መፍጠር በጣም ቁልፍ ነገር ነው::

በግሌ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅንጅት፣ በግንባር፣ አልያም በውሕደት ጠንካራ እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን መፍጠር መቻል አለባቸው የሚል እምነት አለኝ:: ይህ ካልሆነ ደግሞ ፓርቲዎች ተከባብረው፣ አንዱ አንዱን ኂስ እያደረገ ግን ደግሞ ሳይጠፋፉ መሥራት መቻል አለባቸው:: ፓርቲዎችን የሚመርጠው ሕዝብ ነው:: ለዚህ ሕዝብ ሰላማዊ መሆናቸውን ማሳየት መቻል አለባቸው::

ሲራራ፡- በትግራይ ክልል መንግሥት እና በፌዴራል መንግሥቱ መሃል ያለው ልዩነት እየሰፋ መጥቷል:: የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ቀጣዩ ምርጫ በትግራይ ክልልም ይካሄዳል ማለቱን ተከትሎ ውዝግቡ እንደገና አገርሽቷል:: ይህ በሁለቱ አካላት መሀከል ያለው ፍጥጫ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ሊፈጥር የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

አቶ ተክሌ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ እንደ ፓርቲ የያዝነው አቋም የለም:: ነገር ግን አንደ አንድ ፖለቲከኛ እና አገር ወዳድ የምሰጠው አስተያየት በሁለቱም ወገኖች መሃል አንዱ ለአንዱ ቦታ እና ዕውቅና ሰጥተው መነጋገር መቻል አለባቸው:: በሁለቱ መሃል ያለውን ችግር የሚፈታው በውይይት ብቻ ነው:: አንዱ ለሌላው ዕውቅና ያለመስጠት ነገር ነው ጉዳዩን እያወሳሰበው የሚገኘው:: በማንኛውም መንገድ ወደ ግጭት የሚገቡበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም:: ግጭትም ካለ ግጭቱ መሆን ያለበት በሕወሓት እና በብልጽግና መሃል እንጂ በትግራይ ሕዝብ እና በፌዴራሉ መንግሥት መሀከል አይደለም መሆን ያለበት:: በመሠረቱ ግጭት ለማንም የሚጠቅም አይደለም:: አገር በእልህ አይመራም:: አንዱ ለአንዱ ዕውቅና ተሰጣጥቶ መወያየት ሲችሉ ነው ወደ መፍትሔ የሚሄዱት:: ግጭታቸው በአገራችን ካለው የሽምግልና ባህል እና የእርቅ እሴት በላይ ነው የሚል እምነት የለኝም:: እነዚህ ሰዎች እውነት ለሕዝብ ነው የቆምነው የሚል እምነት ካላቸው ሰከን ብለው መነጋገር መቻል አለባቸው::

የሁለቱ አካላት ግጭት አገሪቱን ወዳላስፈላጊ አደጋ ውስጥ እንዳያስገባት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል:: ለዘመናት አንድ ላይ ሲሠሩ የነበሩ፤ አንድ ላይ ሆነው ሕዝብ የበደሉ አካላት ዛሬ ደግም ተለያይተው አገርና ሕዝብ ሊበድሉ አይገባም:: እነሱ ችግራቸውን መፍታት ያቃታቸው እንደሆነ አገር ልትተራመስ አይገባም:: ሕዝቡም፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችም ግፊት ማድረግ ይገባቸዋል:: ኢትዮጵያ ግጭት እና የእርስ በርስ ጦርነት የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም::

 

 

 

October 4, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *