“የጥሬ ገንዘብ እጥረት የለም” | አቶ ፍቃዱ ደግፌ (የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እና ዋና ኢኮኖሚስት)
እንወያይ, እንግዳ

“የጥሬ ገንዘብ እጥረት የለም” | አቶ ፍቃዱ ደግፌ (የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እና ዋና ኢኮኖሚስት)

ሲራራ፡- ከሰሞኑ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው በመግለጽ ወጪ የሚፈልጉ ደንበኞችን   የሚመልሱ የግል እና የመንግሥት ባንክ ቅርንጫፎች ተበራክተዋል፡፡ የዚህ ችግር መሠረታዊ ምክንያቱ ምንድን ነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ስለዚህ ጉዳይ በእኛ በኩል የምናውቀው ነገር የለም፡፡ በእኛ መረጃ ጥሬ ገንዘብ የለም ወይም እጥረት ገጥሟል የሚል መረጃ የለንም፡፡ እኛ ያለን መረጃ ከአምናው የተሻለ ጥሬ ገንዘብ በገበያ ውስጥም ሆነ በባንክ ቤቶች እንዳለ ነው የሚያሳየው፡፡ ምናልባት ይህን ጉዳይ ባንኮች ሆነ ብለው ደንበኞቻቸውን የኤሌክትሮኒክስ የገንዘብ ልውውጥ ለማለማመድ የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል፡፡ እንጂ በባንኮች ላይ የጥሬ ገንዘብ እጥረት አልገጠመም፡፡ በቂ ጥሬ ገንዘብ ለባንኮችም ተሰራጭቷል፡፡

ሲራራ፡- ብሔራዊ ባንክ በዋናነት ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ የገንዘብ ፖሊሲን በማስተካከል የዋጋ ንረትን መከላከል ነው፡፡ ነገር ግን ያለፈውን የመጋቢት ወር የዋጋ ንረት መጠን  ካየን ከ20 በመቶ በላይ ነው፡፡ የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ ብሔራዊ ባንክ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ፍቃዱ፡- ቀደም ብለህ አንተም ለማንሳት እንደሞከርከው የገንዘብ ፖሊሲ በዋጋ ንረት መባባስ ላይ ሚና አለው፡፡ ለዋጋ ንረት መባባስ ገንዘብ ምክንያት የሚሆነው በገበያው ላይ ኢኮኖሚው ከሚሸከመው በላይ ገንዘብ ሲኖር ነው፡፡ በገንዘብ ፖሊሲ ላይ የሚወጡ የመመሪያ ማሻሻያዎች ዛሬ ወጥተው ነገ ውጤት የሚያመጡ አይደሉም፡፡ የገንዘብ ፖሊሲን ማስተካከል በገበያው ላይ በአንድ ቀን አዳር ውጤት የምታገኝበት መፍትሔ አይደለም፡፡ ገንዘብ ወደ ዋጋ ንረት የሚለወጥበት የራሱ የሆኑ ሂደቶች አሉ፡፡ በተመሳሳይ የሚወጡ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻዎችም በተመሳሳይ ገበያውን ለማረጋጋት የሚወስዱት ጊዜ አለ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከባለፈው ዓመት ወዲህ የገንዘብ ልቀቱ በጣም ጥብቅ  አድርጎታል፡፡  አዲስ ወደ ገበያ እያስገባ ያለ ገንዘብ የለም፡፡ ባንኩ አሁን እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን ውጤት ለማየት ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡

በተጨማሪም በገበያው ላይ የተፈጠረው የዋጋ ንረት በገንዘብ መብዛት ብቻ የተፈጠረ  አይደለም፡፡ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ የምርት እጥረት፣ የገበያው ሰንሰለት መርዘም እና የመሳሰሉ መሠረታዊ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከገንዘብ  አንጻር እኛ ፖሊሲዎቹን ጥብቅ አድርገናል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ጥብቅ ያደረግ ነው መመሪያ ዛሬውን ውጤት ስለማያመጣ ትንሽ ጊዜ መታገስ እና የዋጋ ንረቱ እያባባሱ ያሉ  ሌሎች ችግሮች ላይ መፍትሔ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ገበያው ቀደም ሲል የገባው ገንዘብ መጠን ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተደማምሮ የዋጋ ንረቱ ላይ ለጊዜው ውጤት እንዳይኖር አድርጓል፡፡ በጊዜ ሂደት ግን ይስተካከላል የሚል እምነት አለን፡፡

ሲራራ፡- ለዋጋ ንረቱ መባባስ ትልቁን አስተዋጽዖ እያደረገ ያለው ብሔራዊ ባንክ በየቀኑ የሚያደርገው የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስተካከያ ነው በሚል ለዋጋ ንረቱ የመጀመሪያ ተጠያቂ የሚያደርጓችህ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎ?

አቶ ፍቃዱ፡- በቅድሚያ የምንዛሪ ፖሊሲ (exchange rate policy) ምንድን ነው? የሚለውን በሚገባ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ምንዛሪ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንዱ ‹ኖሚናል ኤክስቼንጅ› የሚባለው ነው፡፡ ይህ ማለት ዶላር ከብር አንጻር ያለውን የተመን ልዩነትን የሚያሳይ ነው፤ በቀላሉ የብር ዋጋ የሚባለው ነው፡፡ ሁለተኛው ‹ሪል ኤክስቼንጅ ሬት› የሚባል ነው፡፡ ይህ ማለት ከኢትዮጵያ እቃ እና ከኬንያ እቃ በዓለም ገበያ ላይ የትኛው እርካሽ ነው የሚለውን የምንለካበት መስፈርት ነው፡፡

በየትኛውም መስፈርት ወስደን ብናየው የኢትዮጵያ ብር በጣም ውድ ነው (ብር ከዶላር አንጻር  ማግኘት ከሚገባው በላይ ጉልበት አግኝቷል)፡፡ ይህም የእኛ አገር እቃ ከሌላው አገር እቃ አንጻር በጣም ውድ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ተወዳድራ የመሸጥ ዕድሏ በጣም አነስተኛ ይሆናል፡፡ የተለያዩ ሰዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ብር ጉልበት የሌለው ገንዘብ አይደለም፡፡ በተቃራኒ  ጎልበቱ የበዛበት (overvalued) ገንዘብ ነው ያለን፡፡ የብር አቅም አሁን ካለውም በላይ መውረድ እና መዳከም ነበረበት፡፡  ነገር ግን አገሪቱ ምርት በብዛት ከውጭ የምታስገባ በመሆኑ ዋጋውን ለማስተካከል አልተቻለም፡፡

የብርን አቅም ከዚህ በላይ ብናዳክም ምርት ወደ ውጪ የሚልኩ አምራቾች ብዙ ምርት አምርተው ወደ ውጭ አገር ለመላክ ይበረታታሉ የሚል እምነት አለን፡፡ ብዙ ምርት በተላከ ቁጥር የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የዋጋ ንረት ስላለ በሚል እንዲለዝብ ተደረገ እንጂ ብር ከዶላር አንጻር ያለው የመግዛት አቅም መዳከም ባለበት ልክ አልተዳከመም፡፡ ከዚህ በላይም መዳከም አለበት፡፡ አሁን አንድ ዶላር 42 ኣካባቢ እየተሸጠ ነው፡፡ ትክክለኛ ዋጋው ይኼ አይደለም፣ ትክክለኛ ዋጋው ከ40 ብርም በላይ ነው፡፡

ሲራራ፡- ኢትዮጵያ የማምረት አቅሟ በሚፈለገው ልክ ባለደገበት እና በቂ  መጠን ያለው ምርት ማምረት ሳትችል ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ለማበረታታ ተብሎ የሚወሰደው እርምጃ  ምን ያህል አግባብ ነው? ከትርፉ ጉዳቱ እየበዛ አልመጣም?

አቶ ፍቃዱ፡- ይህን እኛም የምንቀበለው ሐሳብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት በጣም አነስተኛ መሆኑ ለማንም የሚያሻማ አይደለም፡፡ ነገር ግን ያለችውን ወደ ውጭ የምትላክ አነስተኛ ምርት ለማበረታታት የብርን አቅም ከዶላር አንጻር ማዳከሙ ግድ ነው፡፡ እኛ ብዙ ምርት ከውጭ ገዝተን የምናስገባ በመሆናችን የብርን አቅም ማዳከማችን  በዋጋ ንረት ላይ ተጽዕኖ እያደረገ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን  አሁን ያለን የውጭ ምንዛሪ ጎልበቱ እንደበዛ (overvalued) መያዙ ከምንም አያድንም፣ ዓለም ዐቀፍ ተወዳዳሪነትን አይጨምርም፣ የምርት መጠንም እንዲጨምር አያደርግም፡፡ ይልቁንም ያለችንን ወደ ውጭ የምንልካትን ምርት በማዳከም የበለጠ ችግር ውስጥ ይከተናል፡፡

ፖለሲ ሲወጣ ብዙ ነገሮች ከብዙ አቅጣጫ እንዲያይ ይደረጋል፡፡ የዋጋ ንረት፣ የወጪ ንግድን ማበረታታት፣ ዓለም ዐቀፍ ተወዳዳሪነትን እያመጣጠን የምንሄድበት ፖሊሲ ከሌለን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡  የሚወጣው ፖሊሲው ይህን ማመጣጠን ካቃተው በአንዱ አትራፊ ብንሆን እንኳን በሌላው እንከስራለን፡፡ ካለፈው ዓመት ወዲህ ወደ ውጭ የሚላከው ምርት መጠን እየጨመረ መጥቷል፡፡ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገር ቤት ላሉት ዘመዶቻቸው የሚልኩት ዶላር (ሬሚታንስ)  እየጨመረ  መጥቷል፡፡ ከትይዩ (ጥቁር) ገበያው እና  በባንኮች  መካከል ያለው የምንዛሪ ተመን ልዩነት እየጠበበ መጥቷል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በዶላር ተመን ላይ በተደረገው ማሻሻያ ነው፡፡

ምርት ወደ ውጭ መላክ ሲቻል ብዙ ዶላር ማግኘት ይቻላል፡፡  የዶላር  ግኝታችን ሲጨምር ለፋብሪካ ግብዓት የሚሆን ግብዓት በብዛት ማስገባት ይቻላል፡፡ ግብዓት በብዛት ማግኘት ከተቻለ ብዙ ምርት ማምረት ይቻላል፡፡ ምርት በብዛት መመረት ከቻለ የዋጋ ንረት እየተረጋጋ  ይሄዳል፡፡ አሁን የዶለር ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ  ቢሆንም አቅርቦቱ ግን በጣም ዝቅተኛ  ነው፡፡ ይኼ በሂደት የእየተጣጣመ ይሄዳል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃ  አንዱ ግብ በዶላር የአቅርቦት እና ፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ነው፡፡

ሲራራ፡- የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ገና ያልፋፋ ነው፤ በዚህ ሁኔታ የብርን የመግዛት አቅም  ከዶላር አንጻር ማዳከሙ የአገር ውስጥ ጀመሪ አልሚን ማዳከም ነው፤ ዶላር በተወደደ ቁጥር አልሚዎች ማሽን ለማስገባት፣ ጥሬ እቃ ለማስገባት የሚያወጡት ወጪ እየናረ ነው፤ ይህም  የአገር ውስጥ አልሚ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ተሳትፎ እየገደበው ነው፤  የኢንዱስትሪውም ዘርፍ እንደ ዘርፍ እንዳያድግ መሰናክል እየገጠመው ነው በሚል ቅሬታ የሚያቀርቡ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎ?

አቶ ፍቃዱ፡- ሐሳቡ ትክክል ነው፡፡ ግን መፍትሔው ምንድን ነው? የሚለውም መታየት  አለበት፡፡ የብርን አቅም ከሚገባው በላይ ጉልበት በመስጠት መፍትሔ ማግኘት አይቻልም፡፡ ማሽነሪ እና  ጥሬ እቃ ውድ የሚሆነው በቂ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ስለሌለም ጭምር ነው፡፡ መንግሥት የብርን አቅም ማዳከሙን ሥራ ቢያቆም እንኳ ዶላር ስለሌለ ማሽነሪ እና ጥሬ እቃ ውድ መሆኑ አይቀርም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚያድገው ደግሞ በርካታ ምርት ወደ ውጭ መላክ ሲቻል  ነው፡፡

አሁን ያነሳኸው ችግር እንዳለ እናውቃለን፡፡  የብርን የመግዛት አቅም እያዳከምን ምርት ላኪው እንዲበረታታ ጥረት ብናደርግም በቂ ምርት ግን እየተመረተ አይደለም፡፡ አሁን ችግር እየሆነ ያለው እሱ ነው፡፡  በሂደት ምርት እያደገ ሲሄድ ዋጋ ንረቱም የቀዘቀዘ የሚሄድበት ዕድል አለ፡፡ በተጨማሪም በቂ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ዕድል ይኖራል፡፡ በቂ የውጭ ምንዛሪ ካለ ደግሞ ኢንዱስትሪዎች በቀላሉ ጥሬ እቃ እና ማሽነሪ የሚያገኙበት ዕድል ይፈጠራል፡፡

 

 

 

 

April 19, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published.