በተመሠረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከብልጽግናና ኢዜማ ቀጥሎ በርካታ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በማቅረብ ብዙዎችን ያስገረመው እናት ፓርቲ እንዴት ተመሠረተ? የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው? ከመንግሥት አወቃቀር አኳያስ የፓርቲው አቋም ምን ይመስላል? በእነዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከፓርቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሰይፈሥላሴ አያሌው (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
ሲራራ፡- ፓርቲያችሁ ከብልጽግና እና ከኢዜማ ቀጥሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው የምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ማቅረቡ በብዙ ሰዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ከተመሠረታችሁ አጭር ጊዜ ነው፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን በመገናኛ ብዙሃን አካባቢ ስማችሁ እምብዛም የታወቀ አይደለም፡፡ እንዴት ይህን ያህል ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ማቅረብ ቻላችሁ?
ሰይፈሥላሴ (ዶ/ር)፡- ብዙ ጊዜ ስማቸው የሚነሳው ፓርቲዎች ባለፉት 25 ዓመታት የነበሩ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ በዋናነት ኢሕአዴግ ነበር፡፡ በመቀጠል ኢሕአዴግ የሚፈለፍላቸው ድርጅቶች ነበሩ፡፡ በዚያ ወቅት አልነበርንም፡፡ አዲስ ፓርቲ ነን፡፡ ፓርቲውን የመፍጠር ሐሳብ የመጣው በ2011 ዓ.ም. ሲሆን፣ ፓርቲውን የመመሥረቻ ጉባኤ አድርገን በግልጽ ያቋቋምነው ግን በ2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ከምርጫ ቦርድ የዕውቅና ሰርተፍኬት የወሰድነው ደግሞ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ምርጫ ቦርድ የዕውቅና ሰርተፍኬት ሰጠን ማለት ጥር 10 2013 ዓ.ም. ተወለድን ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ ጊዜ በፊት አገራችን ያሳለፈችው በኮሮና ወረርሽን ጋር ተያይዞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ብትሆንም የተለያዩ ሥራዎችን ስንሠራ ቆይተናል፡፡ አሁን በርካታ ዕጩዎችን ለምርጫ የማቅረባችን ዋነኛ ምስጢርም ይኼ ነው፡፡
ምናልባት አሁን ያለንን ዕውቅና ከጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. አስቀድመን አግኝተን ቢሆን አሁን ከሠራነው በላይ ሥራዎችን ሠርተን እጩ በማቅረብ አንደኛም ወይም ሁለተኛም ልንሆን እንችል ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ ብዛት ያለው ዕጩ ማቅረብ አንድ ነገር ነው፡፡ በራሱ ግብ ግን አይደለም፡፡ ዋናው ነገር አማራጭ አገርና ሕዝብን ሊያሻግር የሚችል ሐሳብ ይዞ መቅረብ ነው፡፡
ሲራራ፡- ፓርቲያችሁ እስካሁን በአግባቡ አለመታወቁ ለምርጫው የቀረው አጭር ጊዜ በመሆኑ በምርጫው ውጤት ላይ ተጽዕኖ አይፈጥርባችሁም? በቀሩት ጥቂት ጊዜያት ሐሳባችንን ሸጠን ለአሸናፊነት እንበቃለን ብላችሁ ታስባላችሁ?
ሰይፈሥላሴ (ዶ/ር)፡- ትልቅ ዕድል አለን ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም እስከ ዛሬ ያሉትን ፓርቲዎች ሕዝብ በሚገባ ያውቃቸዋል፡፡ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ብዙዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሕዝብ የተለየ ነገር ይዘው አልመጡም፡፡ ገዥው ፓርቲ ባለፉት 30 ዓመታት ሕዝብ መለወጥ የሚችል ምንም ዓይነት አሠራር አልነበረውም፡፡ 30 ዓመት መሥራት ያልቻለ ፓርቲ በ5 ዓመታት ሁኔታዎችን መለወጥ ይችላል የሚል እምነት የለንም፡፡ ሕዝባችን አዲስ ፊት፣ አዲስ የፖለቲካ አማራጭ ማየት ይፈልጋል፡፡ እኛ የመጣነው ይህን የሕዝብ ፍላጎት ለመሙላት ነው፡፡ እኛ በመጠላለፍ እና በሴራ ፖለቲካ አናምንም፡፡ እንዲያውም እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ በምንችለው ሁሉ እንዋጋዋለን፡፡ በሐሳብ ልዕልና፣ በፖሊሲ አማራጭ የማሸንፍን ሐሳብ ይዘን ነው የመጣነው፡፡ በሐሳብ ላይ ተከራክሮ መሸነፍ እና ማሸነፍ ነው በአገራችን መለመድ ያለበት፡፡ እኛ ቦታ መያዝ የምንፈልገው ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሆነ ገዥው ፓርቲን በማጠልሸት አይደለም፡፡ ከእነሱ በሐሳብ ልቀን የምንገኘው የተሻለ ሐሳብ ለሕዝብ በማቅረብ ነው፡፡ እርግጥ ይህን ለማድረግ የቀረው ጊዜ አጭር ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን የሕዝብ ልብ ውስጥ የምንገባበትን መንገድ እየሠራን ነው፡፡
ሲራራ፡- ምርጫውን በበላይነት እናሸንፋለን ብላችሁ ታስባላችሁ፤ ከወዲሁ ያላችሁ ግምገማ ምንድ ነው፡፡ ማሸነፍ ወይስ በምክር ቤት ወንበር ማግኘት?
ሰይፈሥላሴ (ዶ/ር)፡- ገዥው ፓርቲ ይኼን ምርጫ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻ እና ፍትሐዊ እናደርገዋለን የሚል ቃል በተደጋጋሚ ሲገባ ሰምተናል፡፡ ይህን ቃል ለአገራችን ሌላ አማራጭ ስለሌለ ልንጥለው አንፈልግም፡፡ በጠመንጃ፣ በዱላ እና በማስፈራሪያ ይህን ሕዝብ መግዛት አይቻልም፡፡ ብቸኛው መንገድ በሕዝብ ድምጽ በፍትሐዊነት በቀጥታ በሕዝብ ድምጽ የተመረጠ መንግሥት መመሥረት ነው፡፡ መንግሥት ቃሉን ይፈፅማል የሚል እምነት አለን፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ ከተከናወነ አንድም ፓርቲ ከዚህ ቀደም ሲደረግ እንደነበረው 90 በመቶ አይደለም ሐምሳ ሲደመር አንድ የፓርላማ ወንበር ድምፅ አግኝቶ አያሸንፍም፡፡ ይኼ እኛንም ይጨምራል፡፡ የአሸናፊ (ትልልቅ ድምጽ ያላቸው) ፓርቲዎች ጥምረት መንግሥት ይመሠርታል ብለን እናምናለን፡፡ እኛም ትልልቅ ድምጽ ካላቸው ፓርቲዎች መካከል ግንባር ቀደም ሆነን ጥምር መንግሥት እንመሠርታል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚያም ራሳችንን እያዘጋጀን ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ከፍተኛ ችግር እና በጣም የተራራቀ የፖለቲካ አመለካከት ባለበት አገር ውስጥ አንድ ፓርቲ ብቻውን መንግሥት ለመመሥረት የሚያበቃውን ድምጽ ሊያገኝ አይችልም፡፡ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ካለ ማለቴ ነው፡፡
ሲራራ፡- እናት ፓርቲ ወግ-ጠባቂ ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር ‹ኮንሰርቫቲቭ› የሆነ አስተሳሰብን እንደሚያራምድ ይነገራል፡፡ ወግ-ጠባቂ ነን ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? እስኪ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካና ከማኅበራዊ ጉዳዮች አኳያ የምትመሩበትን ርዕዮተ ዓለም ይግለጹልን?
ሰይፈሥላሴ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ቤተ ሙከራ ሆና ቆይታለች፡፡ ዓለም ዐቀፍ ርዕዮት ዓለምን አገራት ለእነሱ እንዲመች አድርገው የሠሯቸው ናቸው፡፡ ርዕዮት ዓለምን ከአሜሪካ ወስደህ ኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር ለኢትዮጵያ ያልተሰፋ ካባን ለማልበስ እንደመሞከር የሚቆጠር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጠልፎ ይጥላል፡፡ የእኛ ችግር ሆኖ የኖረውም እሱ ነው፡፡ ይህ ማለት ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ የምናገኘው ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡ በደንብ አለ፡፡ ብዙዎቹ የአውሮፓ አገሮችና እነ አሜሪካ ከሮማን ሪፐብሊክ ብዙ ነገር ወስደዋል፡፡ አንዱ አገር ከሌላው የሚማረው ብዙ ነገር አለ፡፡ ሆኖም ከውጭ የሚመጣው ሐሳብ ስር ሊይዝ የሚችለው ከአገሩ ነባር ባህልና ዕሴት ጋር በሚጋበ ሲዋሐድ ብቻ ነው፡፡
እኛ ወግ-ጠባቂ ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር ‹ኮንሰርቫቲቭ› የሆነ ርዕዮትን እንከተላለን ስንል፣ ልንጠብቃቸው፣ ልንንከባከባቸውና በእነሱ ላይ እየጨመርን ወደፊት ልንጓዝ እንችላለን የምንላቸው በርካታ የጋራ ዕሴቶች አሉን ማለታችን ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን በረዥም ዘመን አብሮነታችን ያዳበርናቸው በጣም በርካታ ብርቅ የሆኑ የጋራ ዕሴቶች አሉን፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ባህል፣ ማንነት እና ዕሴት ያላት ጥንታዊት አገር ነች፡፡ በእምነት ደረጃም የራሷ አካሄድ ያላት አገር ነች፡፡ የዓለማችን ታላላቅ እምነቶች ከመነሻቸው ጅምሮ ያሉባት አገር ነች፡፡ የአይሁድ፣ የክርስትና፣ የእስልምና ሃይማኖቶችን ቀድማ የተቀበላች አገር ነች፡፡ ሃይማኖቶችን አቻችላ የኖረችው ከራሷ ባህል እና አኗኗር ጋር አያይዛ በመሄዷ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ የተፈጠረች አይደለችም፡፡ ትልቁ ችግር እየተፈጠረ ያለው አገር ፈጣሪ ለመሆን ጥረት ስናደርግ ነው፡፡ ከነችግሯም ቢሆን ያህን ያህል ዘመን በአገረ መንግሥትነት ጸንታ የቆየችው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ጠንካራ ዕሴት ስላላት ነው፡፡
የራሳችን የሆነውን ባህላችንን እና ዕሴታችንን ጠብቀን፣ ሉላዊ ወደ ሆነው ዓለም ስንገባ ማንነታችንን ሳይዋጥ መሄድ የምንችልበትን ርዕዮት ዓለም ማጠቀም አለብን ብለን እናምናለን፡፡ ወግ-ጠባቂት የቀደመ ማንነትን፣ የጋራ ዕሴትን ማስጠበቅ የሚቻልበትን ሁኔታ የሚመለከት ነው፡፡ ዛሬ የዳበረ ዴሞክራሲ አላቸው የምንላቸው አገራት ሳይፈጠሩ ቀድሞ ኢትዮጵያ የራሷ ሥርዓተ መንግሥት የነበራት አገር ናት፡፡ አገሪቱ የራሷ ወጥ የሆነ ታሪክ የነበራት አገር ነበረች፡፡ ታሪኳ ሸለቆ ውስጥ የነበረበት ጊዜ ነበረ በከፍታም የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ዛሬ ባህሏን ዕሴቷን ጠብቀን ለነገ ትውልድ ለማሻገር እና ለማስተላለፍ ስንል ነው ወግ-ጠባቂነት አስፈላጊ ነው የምንለው፡፡ ይህ ማለት ግን የነበረው ሁሉ ባለበት ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ የሚሻሻሉ እና ከዘመኑ ጋር አብሮው የሚዘምኑም ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም በነባሩ ላይ እየተገነቡ እንጅ ነባሩን በመንቀልና አፍርሶ በመገንባት አይደለም፡፡
ወግ-ጠባቂነትን ከኢኮኖሚ አኳያ ያየነው እንደሆነ ደግሞ ቢዝነስን የሚደግፍ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ነጻነቱን ጠብቆ ፍትሐዊ በሆነ ውድድር እንዲያድግ ለዚህም ጠንካራ የሆነ ሁሉም የሚተማመንበትና ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ የኢኮኖሚ ከባቢ እና የፍትሕ ሥርዓት እንዲኖር እንሠራለን፡፡
ሲራራ፡- ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ የእናንተን ድርጅት ስያሜ የያዘ ደብዳቤ ሲሰራጭ ነበር፡፡ አንደኛ በአጭር ጊዜ ብዙ ተወዳዳሪ በማቅረባችሁ እና ሁለተኛ በዚህ በማኅበራዊ ሚዲያው በሚሰራጩት ደብዳቤዎች ምክንያት ከብልጽግና ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ፓርቲ ነው የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ እስኪ በዚህ አስተያየት ላይ ያለዎትን ምልከታ ይንገሩን?
ሰይፈ ሥላሴ( ዶ/ር)፡- ጥያቄውን በአጭሩ ለመመለስ በማኅበራዊ ሚዲያው ሲዘዋወር ያየኸው ደብዳቤ የእኛ አይደለም፡፡ የእናት ፓርቲ አባላት ወደ ፖለቲካ የመጣነው ኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነውን የሴራ እና የመጠላለፍ ፖለቲካ እናስወግዳለን ብለን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ትግል ሐሳብ ተይዞ የሚከናወን አይደለም፡፡ ፓርቲዎች ሐሳባቸውን ለሕዝብ ከመሸጥ ይልቅ አንዱ አንዱን በማጠልሸት የራስን ጥቅም ከፍ ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ያለው፡፡ ይህ ዓይነቱ ልፊያ ከኢትዮጵያ ውስጥ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማብቃት አለበት፡፡ በአገራችን የፖለቲካ ፉክክር በሐሳብ ላይ የተመሠረተ መሆን ይገባዋል፡፡
እንዳልኩት ደብዳቤው የእኛ አይደለም፡፡ ደብዳቤውን ለምን ማሰራጨት እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም፡፡ እርግጥ የእናት ፓርቲ አመጣጥ ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ ድንጋጤ የፈጠረባቸው ወገኖች እናት ፓርቲን ለመጣል ወጥመድ አስቀምጠው ጥላሸት ቀብተው በሕዝብ እንዲጠላ ሊያደርጉ እንደሚችሉ እንገምታለን፡፡ ነገር ግን የእናት ፓርቲ አባላት ባላቸው ባሕርይ በአርአያነት የሚነሱ በርካሽ ተግባር ውስጥ የማይገኙ አይደሉም፡፡ እናት ፓርቲ ደብዳቤ ላይ የተጠቀሰውን 5 ሚሊዮን ብር ለማግኘት የሚቸገሩ ዓይነት ሰዎች ስብስብ ያለበት ፓርቲ አይደለንም፡፡ ስማችን በ5 ሚሊዮን ከሚነሳ በተሻለ ገንዘብ ቢነሳ እንኳን የተሻለ ነበር፡፡
ይህ ደብዳቤ የተሠራጨው ቅዳሜ ነበር፡፡ ቅድሚያ የተሰራጨው ደብዳቤ ማሕተም የሌለው ነበር፡፡ ፓርቲያችን ይህን አይቶ ደብዳቤው የእኛ አለመሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ በማግስቱ ደግሞ ማሕተም ያለው ደብደቀቤ ተለቀቀ፡፡ ይህ የሚያሳየው ፓርቲው ላይ ጥላሸት የመቀባት እንቅስቃሴ መኖሩን ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ማኅበራዊ ሚዲያ ብዙ አገርና ወገን የሚጠቅሙ ነገሮች የሚስተናገዱበት መድረክ የመሆኑን ያህል በጣም በርካታ አጥፊ የሆኑ አጀንዳች የሚፈበረኩበት መድረክም ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ሥራችንን መሥራት እና እንዲህ ዓይነት ውዥንብር የሚፈጥሩ ጉዳዮች ሲከሰቱ እየተከታተሉ ለሕዝባችን ግልጽ ማድረግ ነው፡፡
ሲራራ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር ተኮር ግድያዎችና መፈናቀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መጥተዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ አገሪቱ የምትከተለው ብሔርን መሠረት ያደረገ የፌዴራሊዝም አወቃቀር ነው የሚሉ አካላት ነው፡፡ የሚሉ አሉ በሌላ ወገን የፌዴራል ሥርዓቱ በአግባቡ ስላልተገበረ እንጅ የዚህ አገር ፍቱን መድሃኒት ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ነው የሚሉ አካለትም አሉ፡፡ ፓርቲያችሁ በዚህ ላይ ምን አቋም አለው?
ሰይፈሥላሴ (ዶ/ር)፡- ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በአግባቡ ሥራ ላይ አልዋለም በተባለበት በኢሕአዴግ ዘመን የነበርንበትን ሁኔታ እናውቀዋለን፡፡ ሥርዓቱ በአግባቡ ሥራ ላይ ሲውል ደግሞ ምን ሊፈጥር እንደሚችል እያየነው ነው፡፡ ራሱ ተግባሩ ይመሰክራል፡፡ ኢትዮጵያ በተከተለችው የጎሳ ፖለቲካ ምክንያት ብዙ ሺሕ ውድ ሕይወት አጥታለች፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ዜጎቿን ከመኖሪያቸው አፈናቅላለች፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠር ንብረት ወድሟል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ከ80 በላይ ብሔረሰብ ባለበት አገር ላይ ቋንቋን መሠረት አድርጎ አገርን መከፋፈሉ ለማንም የሚበጅ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በየቀኑ ዋጋ እየከፈለች ነው፡፡ ዋጋ እየከፈከለች ያለችው ደግሞ በገንዘብ አይደለም፡፡ በልጆች ሕይወት እና ደም ነው፡፡ ዛሬ አሁን እያወራን ስንቶች በማንነታቸው ምክንያት እየታረዱ ነው? ስንቶቹ ከሞቀ ጎጇቸው ወጥተው በመጠለያ እየተሰቃዩ ነው? ይህን ሁሉ እልቂት እያየን ያለው በጎሳ ተኮር አደረጃጀት ምክንያት ነው፡፡ ምንም ያህል ልናሽሞነሙነው ብንሞክር ይህ አደረጃጀት ሊሠራ የሚችል አይደለም፡፡ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የጎሳ ተኮር ፖለቲካን በቃ ማለት አለብን፡፡
ዕድገት መምጣት የሚችለው ሐብት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በነጻነት መንቀሳቀስ ሲችል ነው፡፡ ትልቁ ሀብት ደግሞ ሰው ነው፡፡ እንደ እናት ፓርቲ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጎሳ ፖለቲካ ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማብቃት አለበት ብለን እንሠራለን፡፡ መንግሥት ሆነን የመጀመሪያ ሥራችን የሚሆነው የጎሳ ፖለቲካን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ቆፍረን መቅበር ነው፡፡ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ቋንቋውንና ባህሉን እንዲንከባከብና እንዲያበለጽግ የግድ በጎሳ መደራጀት የለበትም፡፡ የጎሳ ክልልም አያስፈልገውም፡፡
ሲራራ፡- አማራጭ መፍትሔያችሁ ምንድን ነው?
ሰይፈሥላሴ (ዶ/ር)፡- በዓለም ላይ የአሐዳዊ ሥርዓትን የሚከተሉ አገራት አሉ፡፡ ፌዴራሊዝምን የሚከተሉ አገሮችም አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ካላት 110 ሚሊዮን ሕዝብ እና ካለት የቆዳ ስፋት አንጻር በአሐዳዊ ሥርዓት ከአዲስ አበባ እስከ ሞያሌ፣ ቀብሪ ደሃር፣ ቶጎ ውጫሌ፣ መተማ፣ ኮሞክ ድረስ ኢትዮጵያን ማስተዳደር፣ ልማትና ዕድገት ማምጣት ፈታኝ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የፌዴራል ሥርዓት አሁንም ቢሆን ለኢትዮጵያ የሚሻለው የአስተዳደር ሥርዓት ነው ብለን እናምናለን፡፡ የምንከተለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ግን መልከዓምድራዊ እና ለአስተዳደር የሚያመች ፌዴራሊዝም ሥርዓትን መሆን ይገባዋል፡፡ እያንዳንዱ ጎሳ የራሱ ክልል፣ ልዩ ዞንና ወረዳ ከሌለው ባህሉንና ቋንቋውን ሊያሳድግ አይችልም የሚለው መከራከሪያ ውኃ የሚቋጥር አይደለም፣ ታሪካዊ መሠረትም የለውም፡፡
ዛሬ አማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር ብለን ከምንጃር ጫፍ ተነስቶ የክልሉን መንግሥት መፍትሔ የሚፈልግ ጉዳይ ቢገጥም ብዙ ኪሎ ሜትር ታልፎ ባሕር ዳር ነው የሚመጣው፡፡ የኦሮሚያን ዋና ከተማ ስንፈልግ ከሞያሌ ተነስተን አዲስ አበባ መምጣት ግድ ነው፡፡ ከደንቢዶሎ አዲስ አበባ ለመምጣት 700 ኪሎ ሜትር ታልፎ ሁለት ቀን መንገድ ላይ ታድሮ ነው የሚመጣው፡፡ ይህ ዓይነቱ የፌዴራል ሥርዓት አሐዳዊ ከሚባለውም በላይ የከፋ ሥርዓት ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሐዳዊ ሥርዓት በነበራት ጊዜ በክፍላተ አገራት ትመራ ነበር፡፡ ወለጋ አንድ ጉዳይ ሲኖር እዛው ነቀምት ባለ ገዥ እልባት ያገኛል፡፡ የጎጃም ደብረ ማርቆስ ላይ ጉዳዩ ያልቃል፡፡ አሁን ያለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት በርካታ ነገር አብሮ ገድሏል፡፡ በስመ አማራ ሥርዓቱ ወሎን፣ ሸዋን፣ ደብረ ማርቆስን በልቷል፡፡ በስመ ኦሮሚያ ከምዕራብ ኢትዮጵያ እስከ ሶማሌያ ጫፍ ያለውን ቦታ ገድሎታል፡፡ በዚያ ውስጥ ወለጋ፣ ኤሊባቡር፣ ከፋ፣ ባሌ፣ ሐረርጌን በልቶታል፡፡ እስኪ ኦሮሚያ ክልልን ነጥለን እንየው፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ አባል ክልል ነው፡፡ ሆኖም እንደ ክልል ሲታይ ፍፁም አሐዳዊ ክልል ነው፡፡ ስለ ጎሳ መብት እንታገላለን፣ እንቆረቆራለን እየተባለ በተግባር ያለው ግን አሐዳዊነት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር በሌሎችም ክልሎች ይታያል፡፡
በዚህ እና በሌሎችም ምክንየት እናት ፓርቲ ለኢትዮጵያ የሚበጀው የፌዴራል ሥርዓት መልከዓምድራዊ አቀማመጥን የተከተለ የፌዴራል ሥርዓት ነው ብሎ ያምናል፡፡
ሲራራ፡- በኢትዮጵያ የመሬት ጥያቄ ትልቅ የፖለቲካ ነው፡፡ መሬትን በሚመለከት የድርጅታችሁ አቋም ምንድን ነው?
ሰይፈሥላሴ (ዶ/ር)፡- መሬት እንደ ኢተዮጵያ በግብርና የሚተዳደር ማኅበረሰብ ላለው አገር ቁልፍ የሆነ ሀብት ነው፡፡ እንደ ሲንጋፖር ያሉ የከተማ መሠረት ያላቸው አገራት፣ ሀብታቸውን የሚያመነጩት ከመሬት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ኢኮኖሚው በግብርና ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ብቸኛው ሀብት መሬት ነው፡፡
እንደ እናት ፓርቲ አሁን ያለው የመሬት ስሪታችን በመሠረታዊነት መለወጥ አለበት ብለን እናምናለን፤ መሬት እንደ አንድ የምርት አካል ነው መታየት አለበት፡፡ የምርት ኣካል የሆኑ ነገሮች ደግሞ ምርታማ እንዲሆኑ ሀብት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወር መፈቀድ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ መሬትም እንደ ልብ መልማት እንዲችል የባለቤትነት መብት መለወጥ መቻል አለበት፡፡ በቀደሙት ዓመታት መንግሥት እንደ መከራከሪያ የሚያቀርበው መሬት የግለሰብ ቢሆን አርሶ አደሩ መሬቱን እየሸጠ ይጠጣበትና በኋላ ይቸገራል የሚል ነው፡፡ ይህ ገበሬውን ምንም እንደማያስብ አድርጎ አሳንሶ ማየት ነው፡፡ ገበሬው ትምህርት ቤት ባይሄድም በሕይወት የተማረው ትምህርት አለ፡፡ ይህ ዕውቀት በዩኒቨርሲቲ ካለው ትምህርት የተሻለ በተግባር የተፈተሸ ዕውቀት ነው፡፡ ይህን ማኅበረሰብ አንተ ለራስህ አታውቅም እኔ አውቅልሃለሁ ልንለው አይገባም፡፡ መሸጥ መለወጥ ከሚለው ጉዳይ ቀድሞ የመሬት ባለቤቱ ማነው የሚለው በግልፅ መቀመጥ አለበት፡፡
መሬትን በተመለከተ ሦስት ዓይነት ስሪት እንዲኖረው እናደርጋለን፡፡ በግል የሚያዝ፣ በመንግሥት የሚያዝ፣ በወል የሚያዝ የመሬት ስሪቶችን እንፈጥራለን፡፡
ሲራራ፡- እንደሚያውቁት መጪው ምርጫ በብዙ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት በሌለበት እንዲሁም አንዳንድ የሕዝብ ድጋፍ አላቸው የሚባሉ እንደ ኦነግና ኦፌኮ ያሉ ፓርቲዎች በማይሳተፉበት የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚካሄድ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በምርጫው ፍትሐዊነት ላይ የሚፈጥረው ችግር ምንድን ነው? ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለመመሥረትና ከምርጫው በኋላ አመጽ እንዳይቀሰቀስስ ምን ቢደረግ ይሻላል ይላሉ?
ሰይፈሥላሴ (ዶ/ር)፡- ምርጫ ማድረግ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ባለፈው መስከረም ሥልጣን ዘመኑ ማብቃት ቢኖርበትም በዓለም ላይ በተከሰው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የሥራ ዘመኑ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣበት ምርጫ በራሱ ብዙ መጭበርበር እና ብዙ ሸፍጥ የበዛበት ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም ግን መንግሥት ነው፡፡ አሁን ላይ ምርጫው እንዲራዘም የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት የለም፡፡ ምርጫ በተራዘ ቁጥር አገር ያለችበትን ችግር እየበዛ፣ አገር ወደ ባሰ ቅርቃር ውስጥ እየገባች እንሄዳለን፡፡
በትክከለኛ መንገድ ሕዝብ የመረጣቸው ተወካዮች ተሰባስበው አገሪቱ ከገባችበት ችግር የምትወጣበትን ዕድል መፍጠር አለባቸው፡፡ ቢቻል ቢቻል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ የምርጫ ሂደት ቢሳተፉ ምርጫውን ይበልጥ ተቀባይ እና የተሻሉ መፍትሔዎች ወደ እኛ ያመጣሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተለያየ መንገድ ከምርጫው የወጡ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ለምን በምርጫው አልተሳተፉም ብዬ ብዙ የምለው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሐሳብ አለኝ የሚል ፓርቲ በምርጫው ቢወዳደር የሕዝባችንን የመከራ ዘመን ማሳጠር እንችላለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያም መሆን ካልቻለ ምርጫው ግን መደረግ አለበት፡፡ ለኢትዮጵያ ሕጋዊ መንግሥት መመረጥ አለበት፡፡ ሕጋዊነት የሌለው መንግሥት በኢትዮጵያ ከዚህ በላይ መኖር የለበትም፡፡
ይህ ማለት ግን ከምርጫው በኋላም ሁሉም ፓርቲዎችና የፖለቲካ ተዋናዮች የሚሳተፉበት ውይይት መደረግ የለበትም ማለት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች ለረዥም ጊዜያት ሲንከባለሉ የመጡና በየጊዜው እየተወሳሰቡ የሄዱ በመሆናቸው ከምርጫው በኋላም ቀጣይነት ያላቸው ውይይቶችና ድርድሮች ያስፈልጋሉ፡፡
Leave a Reply