“የባንክ ጥራት እንጂ ብዛት ጥቅም የለውም” | በላይነህ ካሳ (ዶ/ር)
እንግዳ

“የባንክ ጥራት እንጂ ብዛት ጥቅም የለውም” | በላይነህ ካሳ (ዶ/ር)

ከደቡብ ኮሪያ ደቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት የዛሬው እንግዳችን በላይነህ ካሳ (ዶ/ር)፤ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በረዳት ፕሮፈሰርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ:: በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ወቅታዊ ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ባልደረባችን ይስሐቅ አበበ አወያይቷቸዋል:: ውይይቱን እነሆ፡-

ሲራራ፡- ለኢኮኖሚው ዕድገት የደም ስር እንደሆኑ የሚነገርላቸው የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ ገና እንጭጭ ላይ የሚገኙ ናቸው:: በኢትዮጵያ ያለውን የፋይናንስ ዘርፍ እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል?

በላይነህ (ዶ/ር)፡- በአገራችን መሠረታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመጣ የተቋማት እና የዘርፎች ትስስር ትልቅ ሚና አለው:: በአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የፋይናንስ (የገንዘብ ተቋማት) ድርሻ ከፍተኛ ነው:: የዚህ አገር የዕድገት ማነቆዎች ከሚባሉት መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ በቂ የሆነ የገንዘብ አቅርቦት በተቋማት በኩል አለመኖሩ ነው::

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ፣ በተለይ በኢትዮጵያ የመጣውን የአስተዳደር ለውጥ ተከትሎ በዘርፉ ላይ የሚሰማሩ ተቋማት ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል:: ይሁን እንጂ ምንም ያህል ቁጥራቸው ቢጨምርም የሚሰጡት አገልግሎት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በጣም ኋላቀር ነው:: ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንጻር ከጎረቤት አገር ኬንያ ጋር እንኳ የምንወዳደር አይደለንም፤ ርቀታችንም ሰፊ ነው:: በአጠቃላይ የአገራችን የባንክ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ኋላቀር ነው::

በፋይናንስ ዘርፍ ዕድገት ውስጥ ሁለት ዓይነት አካሄዶች አሉ:: አንዱ የፋይናንስ ዘርፉ ዕድገት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲያመጣ ሲያደርግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ የፋይናንስ ዘርፉን [እንዲያድግ] ሲያነቃቃው ነው:: አሁን በእኛ አገር ያለውን ሁኔታ ስንመለከተው በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት የወለደው መጠነ ሰፊ የፋይናንስ ተቋማትን የመጠቀም ፍላጎት አለ:: ይህም በባንክ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ዳጎስ ያለ ሀብት እና ትርፍ እንዲያጋብሱ አድርጓቸዋል:: በዚህ ምክንያት ነው በእኛ አገር የባንክ ተቋማት እየተበራከቱ የሚገኙት:: ስለዚህ በጥቅሉ የእኛን አገር የፋይናንስ ተቋማት ውስን ዕድገት ያመጣው በአገሪቱ ባለው የኢኮኖሚ ዕድገት ግፊት ነው ማለት ይቻላል::

የባንኮቹ ቀጥር መጨመር የራሱ ጥሩ ጎኖች ቢኖሩትም የባንኮቹ ቁጥር ከዚህም በላይ እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ግን በርካታ ችግሮችን ማስከተሉ አይቀሬ ነው:: ለአብነት ብንወስድ አሁን ባለው የቁጠባ ልምድ እና የአገሪቱ ካፒታል አቅም የባንኮች ቁጥር እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ሀብት የመከፋፈል ዕድሉ በጣም ሰፊ ነው:: ይህ ደግሞ በርካታ ግን ልፍስፍስ የሆኑ ባንኮች እንዲበራከቱ ያደርጋል:: በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት ለትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ማበደር የሚችሉ እና ጠንካራ አቅም ያላቸው ባንኮች ናቸው:: ሀብት ሲበተን ትናንሽ ባንኮች ናቸው የሚፈጠሩት:: ይህ ደግሞ ለኢንቨስትመንትም ሆነ የግብርናውን ዘርፍ የሚያበረታታ እና የሚደግፍ አይደለም:: ባንኮቹ መብዛታቸው ተደራሽነት በማስፋት በኩል ጠቀሜታ ቢኖረውም፤ በዚህ ጊዜ የሚያስፈልገው ኀይልም መከፋፈል ሳይሆን ያላችውን ኀይል በአግባቡ አሰባስቦ መጠቀም መቻል ነው:: ባንኮች የሚሰጡት አገልግሎት ዘመናዊነትና ጥራት እንጂ ብዛታቸው ጥቅም የለውም::

በግሌ በዚህ ሰዓት ማተኮር አለብን ብዬ የማስበው አዳዲስ ባንኮችን ወደ ሥራ ማስገባት ላይ ሳይሆን ያሉት ባንኮች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲያድግ፣ አዳዲስ ቅርንጫፎችን እንዲከፈቱ፣ የማበደር አቅማቸውን ጠንካራ ማድረግ፤ በጥቅሉ ከዘመኑ ጋር እንዲዘምኑ ማድረግ ላይ ትኩረት ቢደረግ መልካም ነው::

የእኛ አገር ባንኮች አብዛኛው ቅርንጫፋቸው የሚገኘው በከተሞች፣ ከከተሞችም አዲስ አበባ ውስጥ ነው:: የገጠሩ ሰፊ ሕዝብ አሁን ድረስ የባንክ ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም:: ይህም የባንኮችን የቁጠባ አቅምም ሆነ የማበደር አቅም ፈተና ውስጥ የሚከት ጉዳይ ነው:: ብሔራዊ ባንክ ይህን ችግር መፍታት የሚችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ይገባዋል::

እንደሚተታወቀው ኮቪድ-19 ወረርሽን በአገራችን በመከሰቱ ባንኮች ተጎድተዋል:: ለመጎዳታቸው አንዱ ምክንያት ደግሞ ባንኮቹ ይከተሉት የነበረው ባህላዊ አሠራር እና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አለመሆናቸው ነው:: ተክኖሎጂን ማዕከል የላደረገ የገንዘብ ዝውውር እና የግብይት ሥርዓት ነው ያለን:: እንዲህ ዓይነቱ ገበያ የኮቪድ-19 ዓይነት ወረርሽኝ ሲከሰት በአንዴ ነው የሚጎዳው:: የፋይናንስ ተቋማቶቻችን ለቴክኖሎጂ ቅድሚያ ሲሰጡ ይገባል የሚባለው ለዚህ ነው::

ሌላው ለፋይናንስ ዘርፉ ዕድገት መሰናክል የሆነው ችግር ከተቋማቱ ጋር አብረው መሥራት የሚችሉ ሌሎች ተቋማት አለመኖራቸው ነው:: የኢትዮጵያ ባንኮች ቴክኖሎጂውንም የገንዘብ አስተዳደሩንም አብረው ከሚመሩ፣ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታውን ለሌሎች አጋር ተቋማት ቢሰጡ የተሻለ ይሆን ነበር:: መንግሥትም እንደዚህ ዓይነት ተቋማት እንዲያድጉ ድጋፍ ማድረግ መቻል አለበት:: ከዚያ ባለፈ የሚወሰዱ ብድሮች ለታለመላቸው ዓለማ እየዋሉ መሆኑን ማረጋገጥ የሚችሉ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጋሉ:: የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሁን ባለው መጠን የተበላሸ ብድር ውስጥ የገባው እንደዚህ ዓይነት ተቋማት ባለመኖራቸው ነው:: ባለሀብቶች ገንዘብ እየተበደሩ ሥራ ላይ ሳያውሉ ገንዘቡን ይዘው የጠፉት እንዲህ ዓይነት ተቋማት ባለመኖራቸው ነው::

ስለዚህ መንግሥት ተቆጣጣሪ ተቋማት እንዲኖሩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት መቻል አለበት:: በአበደሪ እና ተበዳሪ መካከል ያሉ ግንኙነቶችን መቆጣጠር የሚችሉ ተቋማት መኖር አለባቸው:: እንደዚህ ዓይነት ተቋማት አሁን ባለው ሁኔታ በአገራችን የሉም:: እነዚህ ተቋማት የመንግሥትን እንቅስቃሴ ገለልተኛ ሆነው የሚቆጣጠሩ መሆን መቻል አለባቸው:: እንደ አብነት ብንጠቅስ በባሕር ዳር ዙሪያ በኢንቨስትመንት ስም በርካታ መሬት እና ብድር ወስደው ከመጋዘን እና በረንዳ የዘለለ ነገር ሳይገነቡ ዓመታት የሚያሳልፉ ተቋማት በርካታ ናቸው:: ብድር የሚወስዱበት የሥራ ዕቅድ በራሱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወዴትም የማያራምድ ዓይነት ነው:: እንዲህ ባሉ አሠራሮች ላይ ክትትል እያደረገ ከስር ከስር የቁጥጥር እና የእርማት ሥራ የሚሠራ ተቋም መፈጠር አለበት:: ብድር ሲቀር አይደለም እዬዬ መባል ያለበት:: ቀድሞ የቁጥጥር ሥርዓቱን መዘርጋት ያስፈልጋል::

ሲራራ፡- ብዙሃኑ የአገራችን ሕዝብ በገጠር የሚኖር ነው:: ብዙ ሕዝብ ማለት ደግሞ ብዙ ደንበኛ ማለት ነው:: እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የኢትዮጵያ [ንግድ] ባንኮች ብዙ ሕዝብ ወደሚኖርበት የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ክፍል ትኩረት የማያደርጉበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?

በላይነህ (ዶ/ር)፡- ያለ ጥርጥር አርሶ አደርን መደገፍ አገርን መደገፍ ነው:: በሚያሳዝን መልኩ አብዛኛዎች ባንኮች ግን ይህን ትልቅ እምቅ አቅም ያለውን ኀይል ያገለሉ ናቸው:: እስካሁን ባለው ሁኔታ አብዛኛው የባንኮች እንቅስቃሴ ተያዥን መሠረት ያደረገ ነው:: ቤትን ወይም መኪናን ተያዥ አድርገው ነው ብድር የሚሰጡት:: የአብዛኛው አርሶ አደር ቤት ባንኮች ለመያዣነት የሚያቀርቡትን መስፈርት የሚያሟላ አይደለም፤ መሬቱም በመንግሥት በወጣው መመሪያ መሠረት ለባንክ አስይዞ መበደር አይችልም:: መሬት የመንግሥት ነው የሚል የመንግሥት ፖሊሲ በመኖሩ ምክንያት አርሶ አደሩ በመሬቱ መሥራት እንጂ አስይዞ መበደር የሚያስችል የባለቤትነት መብት አልተሰጠውም:: ይህም አርሶ አደሩን የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳይሆን እያደረገው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር ላይ ትልቅ እንቅፋት የፈጠረ ነገር ነው::

የኢትዮጵያ ሕግ በጣም አስገራሚ ነው:: አንድ ሰው መሬት በሊዝ ተከራይቶ እስከ 25 ዓመት ድረስ መጠቀምን ይፈቅዳል:: የሚከራየውን መሬት አስይዞ ብድር እንዲወስድ የሚፈቅድ ሕግ ነው ያለው:: ይህ መብት ለባለ መሬቱ አርሶ አደር የተሰጠው አይደለም::

እንደ እኔ እምነት አርሶ አደሮች መሬታቸውን ሙሉ በሙሉ ማስያዝ እንኳን ባይፈቀድላቸው ለተወሰነ ዓመት ያላቸውን መብት እንደማስያዣ እየተጠቀሙ የፋይናንስ አቅርቦት የሚያገኙበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ነው:: የኢትዮጵያ የንግድ ባንኮች ወደ ክፍለ አገር የሚሄዱት ቅርንጫፍ የሚከፍቱት ቁጠባ ለመሰብሰብ እንጂ ለማበደር አይደለም:: ይህ ከተማ ላይ ላለው ማኅበረሰብ የሚያግዝ ቢሆንም የገጠሩን ዜጋ ግን በጣም ያገለለ ነው:: አርሶ አደሩ ብድር ይወስዳል የሚባለው ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ነበር:: የእነሱ የማበደሪያ የወለድ መጠን እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው:: የእኛ አርሶ አደር ስለ ገንዘብ አጠቃቀም በቂ ግንዛቤ ሳይሰጠው የሚወሰደው ብድር እዳ ነው ይዞበት እየመጣ ያለው::

ባንኮች ገበሬውን እንዴት ማገልገል አለብን ብለው በጥናት ላይ የተመሠረቱ እንቅስቃሴዎችን ሊያደርጉ ይገባል:: ባንኮች ከራሳቸው ትርፍ እና ጥቅም ባሻገር ስለ አገር ጥቅም ማሰብ መቻል አለባቸው:: ከተሞች ላይ ቤት እና መኪና ለመሸለም የሚያወጡት ገንዘብ ሰብሰብ አድርገው ለአርሶ አደሩ ብድር ቢሰጡ በአገሪቱ ዕድገት ላይ የሚኖረው አስተዋጽዖ ቀላል የሚባል አይደለም::

ሲራራ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም በማይክሮ ፋይናንስ ደረጃ ይሠሩ የነበሩ ተቋማት ወደ ባንክ ደረጃ እንዲያድጉ ፈቃድ ሰጥቷቸዋል:: በዚህ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?

በላይነህ (ዶ/ር)፡- ከሁሉ አስቀድሞ በአገር ውስጥ ያሉት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተቋቋሙበትን ዓላማ የዘነጉ ናቸው:: ተቋማቱ ሲቋቋሙ በዝቅተኛ እና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉትን ዜጎች ለማገልገል በማሰብ የተቋቋሙ ናቸው:: ተቋማቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ ዘንግተው በትርፍ ማጋበስ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ:: እንደሰማነው በቅርቡ እነዚህ ተቋማት ወደ ባንክነት እንዲያድጉ ፍቃድ ሰጥቷቸዋል:: በእኔ እምነት ተቋማቱን ወደ ባንክነት ማሳደጉ ትርፍ ለማጋበስ ካለቸው ፍላጎት አንጻር የተወሰነ ውሳኔ እንደሆነ ነው የምረዳው:: ተቋማቱ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ ያለውን አርሶ አደር ቢደግፍ የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ:: የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክነት ሲያድጉ ተቋማቱን በአዳዲስ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት መተካት ቢቻል የተሻለ ይሆን ነበር:: የማይክሮ ፋይናንስ ሥራውንም ደርበው ይሥሩት ተብሎ ከሆነ ግን በጣም አሳዛኝ ነው:: አርሶ አደሩን ይበልጥ መበደልም ነው::

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግሥት በየፋይናንስ ዘርፉ ላይ የእይታ ለውጦች እየተመለከትን ነው:: ፋይናንስ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ላይ ነዳጅ ሆኖ ነው የሚያገለግለው:: ፋይናንስ በሚሰጠው የብድር መጠን ልክ ምርት እያደገ ይመጣል:: በመንግሥት በኩል እየተሰጠው ያለው ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ ነው:: በዕውቀት የተደራጀ የፋይናንስ ዘርፍ ለኢኮኖሚው እጅግ በጣም መሠረታዊ ነው:: መንግሥትም ሆነ ተቋማቱ ለባለሙያዎቹ ክህሎት ዕድገት በትኩረት መሥራት መቻል አለባቸው:: የፋይናንስ ተቋማቶቻችን ከትርፍ ይልቅ እንዴት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽዖ ማበርከት እንዳለባቸው ማሰብ ይገባቸዋል:: ለትርፍ የተቋቋሙ ተቋማት እንደመሆናቸው ለትርፍ ትኩረት አይስጡ እያልኩ አይደለም:: ልልም አልችልም:: ሁሉንም ነገር በትርፍ መነፀር ብቻ ማየት የለባቸውም ነው እያልኩ ያለሁት:: አገር ማደግ ሲችል ኢኮኖሚው ሲደረጅ እነሱም የተሻለ ትርፍ ማግኘት እንደሚችሉ ማመን አለባቸው:: ሁሉም ዘርፍ ለምርት ዕድገት ትኩረት ሰጥቶ በትብብር መሥራት አለበት:: ባንኮቻችን ረጅም ርቀት አሳቢ መሆን ይገባቸዋል:: ሕጋዊ ሥርዓት መዘርጋት እና የቁጥጥር ሥራውን አጠንክሮ በመሥራት ባንኮች የረጅም ጊዜ ብድር መስጠትን መለማመድ አለባቸው::

በዚህ አገር አዳዲሶቹን እንኳን ትተን 40 እና 50 ዓመት የቆየው ባንክ ከሌሎች ባንኮች የተለየ አገልግሎት ሲሰጥ አናይም:: ባንኮች አሠራራቸውን ማዘመን እና ማደርጀት ላይ እጅግ በጣም በርካታ የቤት ሥራ ይጠበቅባቸዋል የቤት ሥራቸውን በአግባቡ ሊሠሩ ይገባል::

ሲራራ፡- በቅርቡ በመንግሥት እየተደረጉ ባሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነት በስፋት አለ የሚል ድምጽ ከተለያዩ ወገኖች ይሰማል:: የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

በላይነህ (ዶ/ር)፡- እንኳን ከተቋማት ጋር የሚደረግ ግንኙነት ይቅርና አገሮች ከአገሮች ጋር በሚያደርጉት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንኳን አንዱ ባንዱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር መሞከሩ የማይቀር ነው:: የተለያዩ አገሮች ለኢትዮጵያ በሚሰጡት ብድር እና እርዳታ ምትክ ይብዛም ይነስም ማግኘት የሚፈልጉት ጥቅም አለ:: ዓለም ባንክም ይሁን የዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለሚሰጡት ብድር እና እርዳታ እንዲሟሉ የሚጠይቋቸው በርካታ ቅድመ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ:: ባንኩ ብድር ለመንግሥታት ሲሰጥ ከፖሊሲ አንጻር ማስፈፀም የሚፈልጋቸው ተልዕኮዎች አሉት:: በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ብድር እና እርዳታዎች በተለይ አሁን ባለው መንግሥት እየወሰደች ነው:: በምን መደራደሪያ ይህን ብድር እና እርዳታ እያገኘች እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሪቱ እየተወሰኑ ባሉ ውሳኔዎች ላይ ከዚህ ቀደም አድርጉ ከሚሉት ምክረ-ሐሳብ ጋር በጣም ተቀራራቢ የሆኑ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እያየን ነው:: ይህ ለእጅ ጥምዘዛው አንድ ጠቋሚ ማሳያ መሆን የሚችል ነው::

የምናገኛቸው ብድሮች እና እርዳታዎች ለጀመርናቸው ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ እጅግ በጣም ወሳኝ መሆን ይችሉ ይሆናል:: ነገር ግን የሚመጡ ብድሮች እና እርዳታዎች የአገሪቱን ቀጣይ እጣ-ፋንታ እና የፖሊሲ ሉዓላዊነት ችግር ውስጥ የሚከቱ መሆን የለባቸውም:: ከምናያቸው እና ከምንሰማቸው ጉዳዮች አንጻር ከሉዓላዊነት ጋር ችግር የሚፈጥሩ አካሄዶች አሉ:: በተለይ ተቋማት ወደ ግል ይዞታነት እንዲቀየር ከማድረግ፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን ከማድረግ አንጻር ወዘተ… በእኔ እምነት መንግሥት በምንም ዓይነት የቀጣይ ትውልድን ህልውና የሚፈትኑ ስምምነቶችን ከማድረግ ሊቆጠብ ይገባል:: በእንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎች ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጣም ጠንካራ አቋም ነበራቸው:: አሁን ያለው መንግሥት በዚህ ደረጃ አቋሙን በጣም ወጥ ሊያደርግ ይገባል:: ራሳችንን ሊመጡ ከሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ልንከላከል የምንችልበትን አቅም መፍጠር ይገባል::

ሲራራ፡- በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያም በርካታ ዘርፎች ላይ ጫና አሳድሯል:: በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ያሳደረውን ጫና እርስዎ እንዴት ይመለከቱታል?

በላይነህ (ዶ/ር)፡- ይህ ጥልቅ ጥናትን የሚፈልግ ጉዳይ ነው:: ነገር ግን ከሚታዩ እውነታዎች በመነሳት የተወሰኑ ሐሳቦችን መሰንዘር ይቻላል:: በአገራችን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከገባ ጀምሮ ያልነካው የኢኮኖሚ ዘርፍ የለም:: የባንክ ዘርፉም በተለያዩ መንገዶች የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል:: በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እንደ ሆቴል እና ቱሪዝም ያሉ ዘርፎች ክፉኛ ተጎድተዋል:: ሆቴሎች ከዚህ ቀደም ከባንኮች የወሰዱት ገንዘብ በተባለው ጊዜ ለባንኮች ገቢ ማድረግ አልቻሉም:: በዚህም ምክንያት ባንኮች የብድር መመለሻ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ተደርጓል:: ይህ ለባንኮች ጉዳት ነው የሰበሰቡትን ገንዘብ በወቅቱ መሰብሰብ አቅቷቸዋል:: ባለው ደካማ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ምክንያት እንደ ቀደመ ከባንኮች የሚበደሩ ተቋማት አልነበሩም:: ይህም የባንኮች ዓመታዊ ትርፍ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው::

በወረርሽኙ ምክንያት አንዳንድ ዘርፎች ሙሉ በሙሉ ሥራ እስከማቆም ደርሰዋል:: ሰዎች ካላመረቱ እና የወር ገቢያቸው እየቀነሰ ሲሄድ ከዚህ ቀደም ያስቀመጡትን ገንዘብ ከባንክ አውጥተው እንዲጠቀሙ ይገደዳሉ:: እንዲህ ዓይነት ልምዶች በተራዘሙ ቁጥር የባንኮች ተቀማጭ እየተመናመነ መምጣቱ የማይቀር ነው:: በእነዚህ ምክንያቶች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በባንኮች ላይ ጠንከር ያለ ተጽዕኖዎችን መፍጠሩ አይቀሬ ነው:: ምናልባት የጉዳት መጠኑ እንደየ ሁኔታው ምን ያህል ነው የሚለው ጉዳይ በዝርዝር ጥናት መመለስ ያለበት ይመስለኛል:: በባንኮቹ ላይ እየደረሰ ያለው ተጽዕኖ ምናልባት በዘንድሮ ዓመት ላይ ማየት አይቻል ይሆናል:: ተጽዕኖውን በቀጣይ ዓመት ላይ በስፋት እንደሚታይ ግን ጥርጥር የለኝም::

 

October 4, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *