ሲራራ፡- ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን የአገረ መንግሥትነት ያላት አገር ሆና ሳለ ከታሪኳ ጋር አብሮ የሚሄድ ዘመናዊ እና/ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ያልቻለችው ለምንድን ነው?
ፕሮፌሰር መሳይ፡- ብዙ የጻፍኩበት ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ባደረግሁት ምርምር የደረስኩበት መደምደሚያ ኢትዮጵያዊያን የረዥም ዘመናት የአገረ መንግሥትነት ታሪክ ያለን መሆኑ የሚያኮራ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የተደረገው የአገረ መንግሥት ግንባታም አይደለም አሁን ለምንገኝበት አገራዊ ሁኔታ የዳረገን፡፡ እሱማ በበጎ መታየት ያለበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምሥረታ ፕሮጀክት ከሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ እንዲያውም በጭካኔው የምዕራብ አውሮፓው እጅግ አስከፊ ነበር፡፡ እሱ አይደለም የዝመና (modernity) እንቅፋት የሆነብን፡፡
አሁን ለምንገኝበት ሁኔታ የዳረጉን ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም፣ ትልቁ ችግር በፋሽስት ኢጣሊያ መሸነፋችን፣ ያን ሽንፈት በበቂ ሁኔታ አለመገምገማችን ወይም አልተሸነፍንም ብለን መኮፈሳችን ይልቁንም ከኢጣሊያ በኋላ በእንግሊዝ፣ ከዚያም በኋላ በአሜሪካና ሩሲያ ተጽዕኖ ስር መቆየታችን ነው መከራው፡፡ ቅኝ አልተገዛንም የሚለው ስህተት ነው፡፡ በተለይ በተለይ ዘመናዊ ትምህርት የተጀመረበት መንገድ፣ የትምህርት ፍልስፍናችን መሠረት ያደረገው የውጭውን እንጅ አገራዊ ዕሴታችንን አለመሆኑ እስካሁንም አደጋ እንደደቀነብን ይገኛል፡፡ ከአእምሮ ቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት ይገባናል፡፡ ከአእምሮ ቅኝ ግዛት ነጻ እስካልወጣን ድረስ አንዲትም ጋት ወደፊት መራምድ አንችልም፡፡
በራሱ እሴት ላይ ሳይመሠረት እና በራሱ ቋንቋ ሳያስተምር ያደገ አንድም የዓለም አገር የለም፡፡ ሁሉም የአውሮፓ አገሮች እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በራሳቸው ቋንቋ ያስተምራሉ፡፡ እነ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን፣ ቻይና ወዘተ… ብትልም በራሳቸው ቋንቋ ነው የሚያስተምሩት፡፡ የትምህርት ፍልስፍናውም አገራዊ እሴትን በሚገባ የያዘ ነው፡፡ የእኛ ትልቁ ችግር እሱ ነው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱም፣ ሕጉም፣ የተቋማት አደረጃጀትም ሁሉም ከወጭ የተገለበጠ ነው፡፡ ስር የለውም፡፡
አሁንም ቢሆን ጊዜ ወስደን ጠንካራ ውይይት አድርገን ወደ ቀልባችን ካልተመለስን አደጋ ነው፡፡ ልብ ብለን ካየን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸው ከፕሮግራም ጀምሮ ከውጭ ነው የሚገለብጡት፡፡ ያው ንድፈ-ሐሳቡም የሚገለበጠው ከውጭ ነው፡፡ ከውጭ በተገለበጠ ንድፈ-ሐሳብ ነው እርስ በርሳችን የምንጠፋፋው፡፡ በራሳችን ቋንቋ ለመገልገል ታግለናል የሚሉት የዘውግ ኢሊቶችም የውጪውን የላቲን ፊደል ነው የመረጡት፡፡ ነጻ መውጣት ሳይሆን በፈቃደኝነት ባርነትን መምረጥ ነው የሆነው፡፡ ትልቅ እንቆቅልሽ ነው፡፡
እና በዚህ ሁኔታ ዘመናዊ መሆን አይቻልም፡፡ በዚህ መንገድ ዕድገትና ብልጽግና አይታሰብም፡፡ የዓለም ተሞክሮም ይህን አያሳይም፡፡ መጀመሪያ በጥናትን ምርምር ላይ ተመሥርቶ የሕዝቡን ቱባ ባህልና እሴት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ታሪኩን መመርመር ይጠይቃል፡፡ ከዚያ በኋላ ዓለም የደረሰበትን የዘመና ሁኔታ መመርመር፤ ከዚያ ከራሳችን የምንወስደው የቱን ነው? ከውጭ የምናመጣውስ ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅና በዚያ ላይ ተመሥርቶ ፖሊሲ ማዘጋጀት ይገባል፡፡ ይህ ሁሉ ድካም ያለው ሥራ ይጠይቃል፡፡ መድከም ያስፈልጋል፡፡ እንደመገልበጥ ቀላል አይሆንም፡፡
ሲራራ፡- በጻፏቸው መጻሕፍትና ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ስለ ትምህርት ብዙ ጽፈዋል፡፡ በእርስዎ እይታ የትምህርት ዓላማ መሆን ያለበት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር መሳይ፡- ብዙ ጊዜ የሦስተኛው ዓለም አገራት መንግሥታት የትምህርት ግብ ዘመናዊነትን (modernization) እውን ማድረግ እንደሆነ አድርገው ሲያስቀምጡት ይስተዋላል፡፡ ዘመናዊነት ሲሉም በአብዛኛው ኢኮኖሚያዊ ልማት ማለታቸው ነው። የዚህ ዓይነቱ ትምህርት ድህነትን ለመቀነስና የልማት ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ መሣሪያ ነው ብለውም ያስባሉ። የኢኮኖሚ ልማት የሰው ኃይል ልማትን በቅድሚያ ከግምት የሚያስገባ መሆኑ ግን የታወቀ ነው።
እዚህ ላይ መነሳት ያለበት አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ይኸውም “የሰው ኀይል ልማት ማለት ምን ማለት ነው?” የሚለው ነው። ወደዘመናዊነት ሽግግር እያደረገ ባለ ማኅበረሰብ ውስጥ የሰው ኀይል ልማት ሲባል የዕውቀትና የክህሎት ባለቤት መሆንን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ዕውቀትንና ክህሎትን በአመርቂ መልኩ ለመጠቀም አጋዥ ዕሴቶችን ማልማትን ያካትታል። መሣሪያዎቹን የሚገለገለው ኃይል ትጥቁን በአግባቡ ካላሟላ መሣሪያዎቹ በራሳቸው በቂ ሊሆኑ አይችሉም። ጉዳዩ ከዜጎች የሞራል ትምህርት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ማለትም በሥርዓት የሚታነጹበት፣ ሙያዊ ኀላፊነታቸውን የሚያስገነዝብ፤ መብትና ግዴታቸውን የሚያውቁበት፤ እንዲሁም ታታሪ እንዲሆኑ ከሚያደረጋቸው የሞራል ትምህርት ጋር የተያያዘ ነው። የዚህ ትምህርት ግብ ሰዎችን ማስቻል ነው። ሰዎችን ማስቻል ግን ምቹ ማኅበራዊናና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ጉዳዩ ከብሔራዊ የትምህርት ዓላማ ጋር የተቆራኘ ነው ማለት ነው። የትምህርት ብሔራዊ ዓላማ ዜጎች የጋራ ማንነታቸውን የሚፈጥሩ መሠረታዊ ዕሴቶችንና የባህል ውርሶችን የሚጋሩበት ማኅበረሰብ አባላት እንዲሆኑ በሚያስችላቸው መንገድ ማስተማር ነው።
ዘመናዊ ዕውቀትና ክህሎት የግለሰቦቸን ብቃትና ብሔራዊ ኅብረት በሚያጎለብት መሠረት ላይ ሲጣሉ ነው የዘመናዊ ትምህርት እምቅ ኀይል ግቡን ሊመታ የሚችለው። ትክክለኛ የርዕዮተ-ዓለምና ባህል ሁኔታዎች ሳይደላደሉ፣ የኢኮኖሚ እመርታን ዒላማው ያደረገ የትምህርት ፖሊሲ፣ የኋላ ኋላ ዒላማውን መሳቱ የማይቀር ነው። እንደዚህ ዓይነቱን ሁኔታ ብዙ ምሁራን ‹አንደርደቨሎፕመንት› (underdevelopment) ብለው ይጠሩታል።
ሲራራ፡- የኢትዮጵያ ትምህርት ፍልስፍና ዐቢይ ችግሮች ምን ምን ናቸው?
ፕሮፌሰር መሳይ፡- የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓትና ፖሊሲ እጅግ አስከፊ ጉድለቶች እንዳሉበት ጥርጥር የለውም፡፡ ጉድለቶቹም በአንድ በኩል ከገንዘብ፣ ከሰው ኀይልና ከመገልገያ መሣሪያዎች ወይም ግብዓቶች እጥረት ጋር የተያያዙ ናቸው። እነዚህ ጉድለቶች በዘመናዊ ትምህርት መስፋፋትና ጥራት ላይ የተደቀኑ እንቅፋቶች ናቸው። ከአገራችን መሪዎችና ‘ኤሊቶች’ የተሳሳተ የዘመናዊነት ግንዛቤ የሚመነጩ መሰናክሎች መኖራቸውም የታወቀ ነው።
ኢትዮጵያ ለአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች መሆኗ ግልጽ ቢሆንም ቅኝ አገዛዝ ከፈጠራቸው ችግሮች ራሷን መከላከል ግን አልቻለችም። ዐለቃ አስረስ የኔሰው፣ “ጠቃሚ ምክር” በሚለው መጽሐፋቸው በግልጽ እንዳብራሩት፣ የኢጣሊያ ሠራዊት ከአገሪቱ ተባርሮ ቢወጣም፣ ፖለቲካው ግን እንደገባ ነው የቀረው። ምዕራባውያን ኀይሎች አገሮችን በቀጥታ ሳይቆጣጠሩ ፖሊሲያቸውን እንዲተገብሩ መሣሪያ የሆናቸው የምዕራቡ የትምህርት ዘይቤ ተግባራዊ መደረጉ ነው። ባህላዊውን ከዘመናዊው የትምህርት አሰጣጥ እንዲገለል ያደረገው በአግባቡ ያልታሰበበት፣ ሂስና ትችት ያልቀረበበት ወይም በቂ ክርክርና ወይይት ያልተደረገበት የምዕራቡ ካሪኩለም ተግባራዊ መሆኑ ዐለቃ አስረስ እንዳሉት፣ አስተዋጿቸው ከጠላት የመነጨውን ወስዶ ማስፋፋትና ለወጣቱ ማስተላለፍ የሆነ የኢትዮጵያ ምሁራን እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። በአጭሩ፣ የአገሪቱ ኤሊቶች የቅኝ ገዥዎችን ተልዕኮ የሚያገለግሉ “ቅጥረኞች” ሆነዋል ለማለት ይቻላል። “የኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ጊዜ ያለፈበት ወይም ያረጀ ያፈጀና ኋላቀር በመሆኑ የአገራችን ዘመናዊ ትምህርት ከነባሩ ባህልና የትምህርት ዘይቤ የሚወስደው ነገር የለም፤ ስለሆነም ከዜሮ መነሳት ይኖርብናል” የሚል አመለካከት ተይዞ ሲሠራ ቆይቷል።
ውጤቱ ደግሞ እንደታየው በአስተሳሰብ ደረጃ ቅኝ የተገዛና የምዕራብ የተባለን ነገር የሚናፍቅና የሚኮርጅ፤ ከበቀለበት ሕዝብ ጋር የተቆራረጠና በፈጠራ ታግዞ የተማረውን ዕውቀትና ክህሎት ከኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነታ ጋር ማጣጣም የተሳነውን ኤሊት መቀፍቀፍ ብቻ ነው የሆነው። ይኸው ኀይል “ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሚበጀውን የማወቀው እኔ ብቻ ነኝ›› በሚል ግትር እምነት የተጠፈረ በመሆኑ የሐሳብና የአመለካከት ብዝሃነትን መቀበል የሚችል አልሆነም፡፡ በዚህ ምክንያት “ኢትዮጵያ ድህነትንና ድንቁርናን ማስወገድና ኢኮኖሚ ልማት ማስመዝገብ የምትችለው ፍጹማዊ የሆነ ሥልጣን ያለው መንግሥት ሲኖር ነው” የሚል ሐሳብ አራመደ። በዚህ ምክንያት፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት የአለቃና ምንዝር ዓይነት ግንኙነት ሆነ፡፡ መንግሥት የሕዝቡ አገልጋይና ተጠያቂ መሆኑ ቀረ። ተራው ሕዝብ ከተማረው ኀይል የሚወርደውን ትዕዛዝ – ትዕዛዙ ለሕዝቡ ጥቅም ተብሎ መሆኑ ይነገረዋል – አሜን ብሎ የሚያስፈጽም ሆኖ ሁሉም ነገር ከላይ ወደ ታች እንዲወርድ ሆኖ ተዋቀረ።
አገዛዞች ዜጎች የሚበጃቸውን የመወሰን መሠረታዊ ችሎታ እንዳላቸው አይቀበሉም፡፡ ዘመናዊነት የሚባለው ፕሮጀክት ለምን በአገራችን ምንም ዓይነት መነቃቃት እንደማይፈጥር ይህ ማኅበራዊ በድንነት ያብራራል፡፡ ዜጎችን የራሳቸውን እጣ-ፈንታ ወሳኞች አድርጎ ስለማይመለከታቸው፣ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ‹‹ማስቻል›› የሚለውን ነጥብ ከግቦቹ መካከል አንዱ አድርጎት አያውቅም።
ሲራራ፡- ሦስቱም መንግሥታት ትምህርትን ለዜጎች ለማዳረስ ያደረጉት ጥረት እንዳለ ሆኖ፣ እስካሁንም ምሁራኑ ለኢትዮጵያ ችግሮች መሠረታዊ መፍትሔዎች ማምጣት አልቻሉም። የኢትዮጵያ ምሁራን አገራዊም የሆነ ርዕዮተ ዓለም ማመንጨት ያልቻሉት ለምንድን ነው? ይኼ ችግር ከትምህርት ሥርዓታችን የመነጨ ነው ወይንስ ሌላ ምክንያት አለው?
ፕሮፌሰር መሳይ፡- አገሪቱን የማዘመን ኀላፊነት የተቀባበሉትን ሦስቱን የኢትዮጵያ አገዛዞች ስናጤን፣ በአብዛኛው ከተከተሉት ዘዴ እና ከጊዜ አኳያ ከሚመነጩ መጠነኛ ልዩነቶች ውጪ ብዙ ባሕርያትን ተጋርተው እናገኛቸዋለን። የዐፄ ኀይለ ሥላሴ፣ የደርግና የኢሕአዴግ አገዛዞች ከሚጋሯቸው ባሕርያት የመጀመሪያውና መሠረታዊው የፖለቲካ ሥልጣንን የተማከለ ቅርጽ እንዲይዝ ማድረጋቸው ነው። የዚህ ሥልጣንን የተማከለ የማድረግ ዘይቤ ርዕዮተ-ዓለማዊ መሠረቱ ደግሞ የተሳሳተ የዘመናዊነት እሳቤ ነው። አስተሳሰቡ “ሕዝቡ ጊዜ ባለፈበትና ከዘመናዊ አስተሳሰቦችና ዘዴዎች ጋር በማይጣጣም ኋላቀር ባህል ስለታሰረ ዘመናዊነት ከላይ ወደታች መውረድ አለበት” የሚል ነው።
ሥልጣንን የተማከለ የማድረጉ መሠረታዊ ምክንያት አገሪቱ ያላትን ውሱን ኢኮኖሚያዊ ሀብት በብቸኝነት ለመቆጣጠር በሚያስችል መልኩ ተፎካካሪ ኤሊቶችን (ክልላዊ፣ የብሔረሰብ፣ የሃይማኖት) ከዚኸው ውሱን ሀብት ተካፋይ እንዳይሆኑ ለማገድ ነው። ይሁን እንጂ ሥልጣንና ሀብት የተማከሉ እንዲሆኑ መደረጉ የኢኮኖሚ እድገትን አቀበ፡፡ በዚህ ምክንያት በኤሊቶች መካከል ፉክክሩ ተጧጧፈ፡፡ ወደዳር በተገፉ ኤሊቶች መካከል ደግሞ አክራሪ ርዕዮተ-ዓለም ተስፋፋ፡፡ የትጥቅ ትግልም እዚህም እዚያም ይካሄድ ጀመር። በዚህ ሥልጣንንና ኢኮኖሚያዊ ሀብትን በብቸኝነት ለመቆጣጠር በሚደረገው የከረረ ፉክክር የተፈጠሩት የኢትዮጵያ ምሁራን አገሪቱ የዴሞክራሲ ጎዳናን እንድትከተል መንገዱን ማሳየት ቀርቶ ብሔራዊ ጥቅምንና ኅብረትን ማራመድ የተቻላቸው አልነበሩም። ከዚያ ይልቅ ጽንፍ የያዘ አብዮታዊነት አሊያም ጎሰኛ የሆነ አስተሳሰብ ሰለባ ሆኑ።
የዚህ ለተለያዩ ከአገራችን ሁኔታ ጋር ያልተዋሐዱ ርዕዮተ-ዓለሞች የመጋለጣችን ምንጩ በቂ ውይይትና ክርክር ሳይደረግበት እንዳለ ተገልብጦ የተወሰደው የምዕራቡ የትምህርት ዘይቤ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይኸው የትምህርት ሥርዓት መሠረቱ የተነቀለና ቀፎው ብቻ የቀረ፤ ምንም የሌለው ነገር ግን በድንቁርና እብሪት ራሱን የምሁር ቁንጮ አድርጎ የሚመለከት ቡድንን አዋለደ። ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታውም ሆነ የትምህርት ይዞታችን ብሔራዊ ምሁራንን ለመፍጠርና ለማጠናከር ምቹ ሁኔታን አልፈጠረም፡፡ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተስማሙና አገር በቀልነት ያላቸውን ጠቃሚ መፍትሔዎች ለማቅረብ የሚችሉ ምሁራንን መፍጠር ባለመቻሉም ምሁራኑ በነበሩት ችግሮች ላይ የባሰ ጋዝ አርከፈከፉ እንጂ መፍትሔ ሊያመጡ አልቻሉም። እኔም እራሴ ብሆን ከእነኝህ ምሁራን የምመደብ መሆኔን መግለጽ ይኖርብኛል። ከአፄ ኃይለሥላሴ አገዛዝ መውደቅ በኋላ አያሌ የኢትዮጵያ ምሁራንን ያነቃነቁት ሌኒን፣ ስታሊንና ማኦ እንደነበሩ እናስታውሳለን። ኢትዮጵያን የማዘመኑ ኀላፊነት ለእነዚህ ባዕዳን ተላልፎ መሰጠቱ በራሱ እጅግ የሚደንቅና የሚያስተዛዝብ ነው።
ሲራራ፡- እስኪ ደግሞ ብዛትና ጥራት በሚሉት ነጥቦች ላይ እንወያይ። አንዳንድ ወገኖች ጥራት ከብዛት ይገኛል ይላሉ። የእርሰዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር መሳይ፡- የብዛትና የጥራት ጉዳዮች ሁሉም ወደዘመናዊነት የሚራመዱ አገሮች የተጋፈጧቸው ችግሮች መሆናቸው ግልጽ ነው። የትምህርት ጥራትና ብዛት ጉዳይ ትልቅ ችግር ሲሆን ችግሩም በአመዛኙ በታዳጊ አገራት ውስጥ ካለው የሀብት እጥረት የሚመነጭ ነው። የውጭ ዕርዳታ በተፈጥሮው የሚያስከትላቸው ውስንነቶች እንዳሉ ሆኖ መጠነኛ ድጋፍ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ችግሩን ግን በጭራሽ የሚቀርፍ አይሆንም። ግልጽ መሆን ያለበት ችግሮቹን ለመቅረፍ ሊረዳ የሚችል ምትሃታዊ ቀመር የለም፡፡ ከሂደት ጋር የተያያዘ ነገር ነው። ኢኮኖሚው እመርታ ሲታይና የበለጠ አቅም ሲፈጠር የትምህርት ጥራት ቅድሚያ ያገኛል። አንዱ እሱ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ችግሩ አንዱን ከሌላኛው ከማስቀደም አንጻር መታየት የለበትም። ማለትም “ጥራት ወይስ ብዛት?” በሚል ስሌት መቅረብ የለበትም። ወደ ዘመናዊነት ሽግግር ለማድረግ የምታልም አገር በጥቂቶች ላይ ብቻ አተኩራ አብላጫ ዜጎቿን ችላ ማለት አይቻላትም። በማንኛውም መንገድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ለብዙሃኑ ዜጋ እንዲዳረስ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ማለት ግን ጥራት ትኩረት ይነፈገው ማለት አይደለም። ጥራት ከብዛት ይከተላል ማለትም አግባብ አይሆንም። ኢትዮጵያ በሁሉም ዋና ዋና የትምህርት ዘርፎች – ሥነ-ጽሑፍ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ወዘተ… ሊሆን ይችላል – ጥቂት ግን በከፍተኛ ደረጃ የተማሩና የሠለጠኑ ሰዎች ማፍራት ይጠበቅባታል። እነዚህ ሰዎች የአገሪቱን የሰው ኃይልና የማቴሪያል ልማት መሠረት ለመጣልና ለአገሪቱ ብሔራዊ ግቦችን ለመንደፍ እጅግ አስፈላጊ ናቸው። የኢትዮጵያን ዘመናዊነት የሚወክሉ ግንባር-ቀደም መሪ የሆኑ ኀይሎችም እነዚህ ናቸው።
ስለሆነም ጥራትና ብዛትን በተመለከተ እኔ ይበጃል የምለው መፍትሔ፣ ሁሉም ነገሮች ያልተሟሉለትም ቢሆን ዘመናዊ ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ በከፍተኛ ደረጃ የሠለጠኑ ጥቂት ኤክስፐርቶችን ማፍራት ግቡ ካደረገ ፖሊሲ ጋር የተቀናጀ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል የሚለውን ነው። ይህንንም ለማሳካት በከፍተኛ ፉክክር የሚታነጹ፣ የአእምሮ ብቃታቸው የላቀ ሳይንቲስቶች፣ ኢንጂነሮች፣ የሕክምና ዶክተሮች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ አስተማሪዎች፣ ማኅበራዊ ሳይንቲስቶችና የሥነ-መለኮት ሊቃውንት ለመሆን የሚስችሏቸው አስፈላጊ ግብዓቶች የተሟሉላቸው ጥቂት የሁለተኛ ደረጃ ምርጥ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆችን ማቋቋምን ይጠይቃል።
በእነኝህ ኤሊት ወይም ልዩ ተቋማት ውስጥ በሚሠለጥኑት ዝርዝር ውስጥ የሥነ-መለኮት ሊቃውንት የመካተታቸው ነገር ሊያስገርም ይችላል። ግን በምንም መልኩ ብዥታን ሊፈጥር አይገባም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሃይማኖት ቡራኬ ሳይታከልበት ኢትዮጵያን በስኬታማ መልኩ ማዘመን ስለማይቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከዘመናዊነት ጋር አብሮ የማይሄድ የሃይማኖት አስተምህሮ ታዛዥ ሆነው መቀጠል አይቻላቸውም። በመሆኑም፣ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሻሻል ዘዴዎችን መቀየስ አስፈላጊ እንደሆነው ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትናን ማሻሻልና ማዘመን ለዘመናዊነት ግብ በጣም አስፈላጊ ነው። ደርግና ሲቪሉ ግራ-ዘመም ኃይል የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተሳሰብ ከሶሻሊዝም ጋር ለማጣጣም ሲሉ ሃይማኖትን የማግለል ስትራቴጂ መከተላቸው ያመጣው ውጤት ምን እንደነበር የምናውቀው ነው፡፡ ግለኝነት ሰፈነ፤ የባህል መደበላለቅና ምስቅልቅል ተፈጠረ፤ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት አሽቆለቆለ፡፡
ከላይ እንገለጽኩት ከብዛት ጥራትን ማምጣት ይቻላል ብሎ መጠበቅ ስህተት ነው። የአሉታዊ ነገሮች መከማቸት ወደአዎንታዊነት አይለወጥም። ከዚህ ይልቅ ሁለት የተለያዩ ነገር ግን ተጣማሪ ፖሊሲዎችን መተግበር የተሻለ ነው፡፡ ትምህርት መስፋፋቱን መቀጠልና በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ኤክስፐርቶችን ለማፍራት የኤሊት ተቋማትን አብሮ ማቋቋም ያስፈልጋል። በእነኝህ ኤክስፐርቶች አስተዋጽዖ ኢኮኖሚው እየተሻሻለ ሲሄድ የትምህርት ጥራቱን ጎን ለጎን ማሻሻል የሚቻል ይሆናል።
ጥራትን ለማሻሻል ብቃት ያላቸውና ለሥራው ታማኝ የሆኑ መምህራንን ማፍራት አንዱ ቁልፍ ነገር መሆኑንም በሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። ካለው የገንዘብ ውሱንነት በተጨማሪ፣ ብቃት ያላቸው መምህራን እጥረት አንዱና ዋነኛው የኢትዮጵያ ትምህርት ችግር መሆኑን ሁሉም የሚያውቀው ነው። ለዚህ ችግር መፍትሔው ችሎታ ያላቸው ዜጎች መምህር ለመሆን ተነሳሽነቱ እንዲኖራቸው ማበረታቻዎችን መፍጠር፤ ለዚህ ደግሞ ከሁሉ አስቀድሞ የመምህራንን ደመወዝና የሕይወት ሁኔታዎች ማሻሻል የግድ ይላል። የመምህርነት ሙያ የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅም ሳይሻሻል የትምህርትን ጥራት ማሻሻል የማይታሰብ ነው። የተጠላውን የመምህርነት ሙያ ገጽታ ለመለወጥ መንግሥት ብዙ ማድረግ አለበት፤ ማድረግም ይችላል ብየ አምናለሁ።
ሌላው አስፈላጊና መጤን ያለበት ነጥብ የቋንቋ ጉዳይ ነው። ለመማር ማስተማሩ ሂደት እንግሊዝኛ ተናጋሪ መምህራንን መቅጠርና ማሰልጠን አለብን ወይንስ የአገሪቱ ብሔራዊ የሥራ ቋንቋ የሆነውንና አብዛኛው ኤሊት የሚገለገልበትን የአማርኛ ቋንቋን መጠቀም አለብን? አማርኛን መጠቀም የሚያስገኘው ጥቅም ብዙ ነው፡፡ አማርኛ ቋንቋ በኮሌጅ ደረጃ ማስተማሪያነት የሚውል ከሆነ ኢትዮጵያ በአነስተኛ ወጪ ዕውቀትን በቀላሉ ለማዳረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው ብሔራዊ ቋንቋ ይኖራታል ማለት ሲሆን፣ ይህም የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆልን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ ምክንያቱም መምህራንና ተማሪዎች በሚያውቁት ቋንቋ መግባባት ይቻላቸዋልና ነው። አማርኛን በማስተማሪያነት እንገልገልበት በሚባልበት ጊዜ በአንድ በኩል ዕውቀታቸውን በአገራቸው ቋንቋ ለማጋራት ከማይፈቅዱ መምህራን ፈተና ይገጥመናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቋንቋው በኮሌጅ ደረጃ ለማስተማሪያነት ከፍ ማለቱን የሚቃወሙ ጎሰኛ ዜጎችም እንቅፋት ይፈጥራሉ። ሌላው ፈተና በርካታ መጻሕፍትንና የማስተማሪያ ግብዓቶችን የመተርጎሙ ከባድና ትብብርን የሚጠይቀው ሥራ ነው። የግብዓትና የአደረጃጀት ችግሮች በቀላሉ ሊቀረፉ ይችላሉ። በጣም ከባዱ የፖለቲካው ጉዳይ ነው። እሱም ቢሆን ይቀረፋል፡፡ ያ የሚሆነው ኢትዮጵያውያን ሚዛናዊ ሆነው ማለትም ምርጫዎች መስዋዕትነት እንደሚያስከትሉ ተረድተውና ስሜታዊነታቸውን አሸንፈው ከሁሉም የተሻለውንና የሚበጀውን ምርጫ መምረጥ የቻሉ እንደሆነ ነው።
ሌላው የትምህርት ጥራት እንቅፋት በኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነታዎች ላይ የሚያጠነጥኑ ጥልቀት ያላቸው ጥናትና ምርምሮች እጥረት ነው። የትምህርት ተቋማቱ ዋና ርእሰ-ጉዳይ ኢትዮጵያና ሕዝቧ መሆን ይገባዋል። በምዕራባውያኑ የተሠሩት የተወሰኑት ጥናትና ምርምሮች ለማስተማሪያነት የሚበቃ ጥራት የሚጎድላቸው ባይሆኑም አብዛኞቹ ወገንተኝነት የሚንጻባረቅባቸውና ድምዳሜያቸውን ለማስደገፍ ሚዛናዊ ማስረጃ የማያቀርቡ ናቸው።
በአገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የአካዳሚ ነጻነት ባለመኖሩ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ምሁራን እንደልባቸው ጥናትና ምርምሮችን በመሥራት አስተዋጽዖ ማድረግ አልቻሉም፡፡ የዐፄ ኀይለ ሥላሴ ሥርዓት ከተቀሩት ሁለት አገዛዞች የተሻለ እንደነበር የማይካድ ቢሆንም ሦስቱም አገዛዞች መገለጫቸው በሆነው ኢዴሞክራሲያዊ ባሕርይ ምክንያት ለአካዳሚያዊ ነጻነት ቦታ የላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ተመራማሪዎች ያለውን መንግሥት በመቃወም ራሳቸውን ለእስር ባስ ሲልም ሞትን ለመቀበል መዘጋጀት፤ ምርምር የተባለን ነገር እርግፍ አድርገው መተው፤ ወይም ሳያምኑበት እንዲሁ መንግሥት የሚፈቅደውን ብቻ እንደበቀቀን መድገም በሚሉ አስቸጋሪ ምርጫዎች ውስጥ ወድቀው ይኖራሉ፡፡ አብዛኞቹ ምሁራን ከጥናትና ምርምር ጋር ተራርቀዋል፡፡ ሠሩ ከተባለም አካዳሚያዊ ነጻነት ባለመኖሩ ምክንያት የጥናትና ምርምሮቹ ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ባለው ችግር ምክንያት ምሁራኑ የኢትዮጵያን ችግሮች በሚመለከቱ ተግባራት ላይ ከመሥራት ይልቅ በሌሎች አገሮች ወይም መሠረታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩም ተገድደዋል፡፡
የአገራችን የትምህርት ይዞታ የቆመው በመሠረታዊ ቅራኔ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከሳይንስና ከዘመናዊ አስተሳሰቦች የሚጠበቀው ነገሮችን በጥልቀት የሚመረምርና ኂስና ትችት የሚያቀርብ አዕምሮን ማጎልበት ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ የትምህርት ሁኔታ ኂስና ትችት የራቀው፤ ክርክርና ውይይት የሌለበት ነው፡፡ በእርግጥ ሦስቱ አገዛዞች ትችትና ኂስ የሚያቀርብ ምሁር እንዳይፈጠር እግድ መጣላቸው በተዘዋዋሪ መንገድ የትምህርት ተቋማቱ የተቋቋሙት ሕዝቡን ሳይሆን እነርሱን ለማገልገል መሆኑን መናገራቸው ነው። እውነታው እንደሱ ከሆነ ታዲያ ቀድሞውኑ ስለትምህርት ጥራት እንጨነቃለን ማለትን ምን አመጣው?
የትምህርት ጥራት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ነው ሩቅ አሳቢና ብቃት ያለው አመራርም ማፍራት የሚቻለው። በአገራችን በ1960ዎቹና 70ዎቹ ዓመታት የሚጠይቅ አዕምሮ ያላቸው ሰዎች በመታፈናቸው ምክንያት በንጉሣዊው አገዛዝ ላይ የነበራቸውን ተቃውሞ የሚገልጹበት ሌላ መንገድ አልነበራቸውምና በጽንፈኞችና በፀረ-ኢትዮጵያውያን የሚሰራጩ ሴረኛ የሥነ-ጽሑፍ ውጤቶች ሰለባ ሆኑ። በመጨረሻም የስታሊን አስተሳሰብ የሰው ልጅ የመጨረሻው ጥበብ ነው ብለው አምነው አረፉት። ትምህርት ጥራት ሲጎድለው ቂሎችን ይፈጥራል – “አወቅሽ አወቅሽ ሲሏት የባሏን መጽሐፍ አጠበች” – እንደሚባለው ነው። አፈና ደግሞ ከዚህም የከፋ ነው፡፡
ሲራራ፡- በትምህርት ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ልትቀስመው የምትችለውና የሚገባት ልምድ ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር መሳይ፡- ኢትዮጵያ ከጃፓን፣ ከሕንድና ከተወሰኑ የምሥራቅ እስያ አገሮች ጠቃሚ ልምድ መቅሰም የምትችል ይመስለኛል። እዚህ ላይ ሊያጋጥም የሚችለው አደጋ የኩረጃው ነገር ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ከኢትዮጵያ የሚለዩ የመሆናቸው እውነታ በጭራሽ ሊሰወርብን አይገባም፡፡ በእነኝህ አገሮች ስኬታማ የሆነው ስትራቴጂ በእኛ ላይሠራ ይችላል። ስለሆነም ጥበበኞች መሆን አለብን፡፡ የእነዚህን አገሮች ተመክሮ መቅሰማችን እንደተጠበቀ ሆኖ እኛም የራሳችን የሆነውን መላ መቀየስ ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ ግን መረዳት ያለብን የትምህርት ሥርዓትን ማሻሻል ብሔራዊ መግባባትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ብሔራዊ መግባባት የሚገኘው ደግሞ መቋጫ ላልተገኘላቸው አንኳር አገራዊ ችግሮች የዴሞክራሲ ምህዳሩን ክፍት በማድረግ መፍትሔ መፈለግ ሲቻል ነው።
Leave a Reply