በኢትዮጵያ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ኀላፊዎች በዕውቀትም በልምድም ከእነሱ ያነሱ ሰዎችን የመመደብ የተለመደ አሠራር አለ፡፡ ይህ አሠራር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን የማይጠየቁና የማይደፈሩ፣ ብቸኛ አድራጊ-ፈጣሪ እንዲሆኑ የማድረግ ባሕርይ አለው፡፡ ይህም ኀላፊዎች ራሳቸው ሕግ (ከሕግ በላይ) እንዲሆኑ ስለሚያደርግ ተጠያቂነት እንዳይኖር፣ ይልቁንም በኀላፊዎችና በሠራተኞች መሀከል ያለው ግንኙነት የአለቃና ምንዝር ግንኙነት እንዲሆን በማድረግ የሠራተኞችን ፈጠራና የሥራ ተነሳሽነት ያዳክማል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለምን ከዚህ ችግር ወጥተን ዘመናዊ ሥርዓት መገንባት አልቻልንም? ዘመናዊ ሥርዓት ለመገንባት የተደረጉ ጥረቶችስ ልምን ከሸፉ? በእነዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ለበርካታ ዓመታት ያስተማሩ እና በርካታ የምርምር ሥራዎችን የጻፉ አንጋፋ ምሁር ናቸው፡፡
ሲራራ፡- እርስዎ በተለምዶ “ያ ትውልድ” እየተባለ የሚጠራው ትውልድ አካል ነዎት፡፡ “የእኛ ትውልድ” (የእኛ ዘመን) የሚሉት ነገር ሲነሳ የሚያድርብዎ ስሜት ምንድን ነው?
ፈቃደ (ዶ/ር)፡- “የእኛ ትውልድ” የሚለው ሐረግ ሲነሳ የሚፈራረቁብኝ ስሜቶች አሉ፡፡ በአንድ በኩል የልጅነትና የወጣትነት ዘመን ኑሮ፣ አፍላ ምኞትና ትግል ይታወሰኛል፡፡ ይህ እንግዲህ መልካሙ ነው፡፡ ሌላው ስሜት ዛሬ ላይ ቆሜ ወደኋላ ያንን ኑሮ፣ ያንን አፍላ ምኞትና ትግል ሳስብ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሆነውን እና እየሆነ ያለውን ሳሰላስል ውስጤ የሚገላበጠው፣ የትካዜ፣ የቁጭት፣ የሐዘን፣ የትዝብትና የፀፀት ስሜት ነው፡፡ ይኼ ብዙ ታሪክ የሚነካካ ነው፡፡
ሌላው “የእኛ ትውልድ” የሚለው ሐረግ የሚቀሰቅስብኝ ባጠቃላይ በአገራችን ውስጥ ያለውንና የነበረውን የትውልዶች ግንኙነት ወይም አለመገናኘት ነው፡፡ በየጊዜው የምንነጋገርበት አንዳንዴም ሥርዓት በሌለው መንገድ ቃላት የምንወራወርበት ጉዳይ ሁሉ ይታወሰኛል፡፡ እኔ ራሴ በፊት ስለነበረው ገናና ቡድን በልጅነትና በወጣትነቴ እና ዛሬ በጎልማሳነቴ የማስበውም ይመጣብኛል፡፡ ይህንን የማያውቁ የዛሬ ልጆችና ወጣቶች ደግሞ የእኔ ስለሚባለው ትውልድ በጉጉትም፣ በድፍረት የሚናገሩትም ይመጣብኛል፡፡ በዚህ ሁሉ መሀከል በዕውቀት መነጋገር ባለመኖሩ፣ የሚበዛው አተካሮና ስሞታ መሆኑ ሁሉ ይመጣብኛል፡፡ ይኼም ብዙ ጊዜ ያሳዝነኛል፡፡
እቅጫዊ ምክንያቱን ባላውቅም፣ “ትውልድ” የሚለው ቃል በተለያዩ የዕድሜዬ እርከኖች እኔ ራሴ የኖርኩትና የታዘብኩትን ሕይወት፣ በዕድሜ ከእኔ የበለጡ ሰዎች ስለኖሩትና ስለታዘቡት በተለያዩ ጊዜያት ካጫወቱኝ የማስታውሳቸውን ተርኮች (narratives) ኢትዮጵያ ውስጥ የዛሬ 80 እና 100 ዓመት ገደማ ስለነበረው የሕይወት ገጽታ በተለይ ከዱሮ ጋዜጦች የቃረምኳቸውን ያስታውሰኛል፡፡ ታዲያ ዛሬ አንድ ፋይዳ የለው የሕይወት ክስተት እንበል ሳስተምር ወይም ባጋጣሚ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ሬዲዮ ስሰማ ወይም ቴሌቪዥን ስመለከት ሲያጋጥመኝ፣ ራሱን ክስተቱን ብቻውን የመመልከት አቅም ብዙ ጊዜ የለኝም፡፡ ሳላውቀው ወይም ሆነ ብዬ ሳይሆን በቅፅበት፣ አእምሮና ስሜቴ ክስተቱን እውስጤ ከተከማቹ ክስተቶች ጋር ወደ ማነጻጸር በራሱ ይሄዳል፡፡ ብዙ ነገር ይጠራብኝና ያተራምሰኛል፡፡ አሁን ስለትውልድ ስትጠይቀኝ የሆነውም በጥቂቱም ቢሆን ይኸው ነው፡፡ ስለ አንዳንድ እሳቤዎች (concepts) ስጠየቅና ስመልስ፣ ብዙ ጊዜ አጭር መልስ የለኝም፡፡ በዚህ ላይ የዛሬ ወር ይህንኑ ጥያቄ ብጠየቅ እንዴት እንምመልሰው አላውቅም፡፡ በእሳቤዎች ላይ ተለጣጣቂነት ባለው መንገድ ባደባባይ እየተወያዩ ሐሳቦችን የማብሰልን ልምድ በአገራችን ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲዎች እና በብዙኃን መገናኛ ሥራዬ ብለን ስላላዳበርን ችግሩ የእኔ ብቻ አይደለም፡፡ የሁላችንም ይመስለኛል፡፡
ሲራራ፡- በትዝታ ተመልሰው የዛሬ 80 እና 100 ዓመት ገደማ ስላለው ትውልድ አኗኗር ከጋዜጦች ካገኙት አሁን ትዝ የሚልዎት ካለ ጥቂት ይንገሩን እስቲ….
ፈቃደ (ዶ/ር)፡- በደስታ! በተለይ ከጠላት በፊት (ከ1928 በፊት ማለቴ ነው)፣ በአድዋና በሁለተኛው የጣልያን ወረራ መሀከል ስላሉ ሰዎች ጥረት ብዙ መስማት እወዳለሁ፡፡ ታዲያ ማኅበራዊ ታሪኩ ነው በተለይ የሚስበኝ፡፡ ሰው ምን ሠራ? ምን በላ? ምን ጠጣ? ምን አሰበ? ምን ዘፈነ-አለቀሰ? ምን ለበሰ? እንዴት ተዳደረ? ምን ችግር ቀርቦለት ምን ፍርድ ሰጠ? ወዘተ… የመሳሰለው ነው የሚማርከኝ፡- መረጃው እንደልብ እና በቀላሉ ባይገኝም፡፡ ለማግኘት ብዙ ድካም አለበት፡፡ እኔ ዓመተ ምሕረት፣ የጦር መሪዎች ስም እና የቦታ ስም እየጠቀሰ እገሌ እገሌን ወጋ፣ እገሌ አሸነፈ፣ እገሌ ተሸነፈን ብቻ የሚያዘወትር ከኢዛና እስከ አሁን ድረስ ያለውን የሚደረደርና የሚያስብ፣ የማይተረጉም፣ ሕይወት ሕይወት የማይሸት ታሪክ እምብዛም አይከይፈኝም፡፡ ብቻ ይህንን ለጊዜው ትቼ ወደ ጥያቄህ ልመለስና፣ ጋዜጦቹን፣ በተለይ “ብርሃንና ሰላም” የተባለውን ጋዜጣ በማንበቤ ስለ ትውልዱ ያደረብኝን ስሜትና አጠቃላይ ሐሳብ እንደመጣልኝ ልግለጽ፡፡
ከጽሑፎቻቸው የተገነዘብኩት አንድ ትልቅ ቁምነገር ጥቂት የማይባሉ ግልጽና ቅን ሰዎች እንደነበሩባቸው ነው፡፡ በተለይ ስለ አገር ጉዳይ የሚጻፈውን ስመለከት ይገርመኛል፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ ሰዎች የሚጽፉት አገርን ስለማጠናከር፣ ስለመገንባት ነው፡፡ እርግጥ የአውሮፓን ፈለግ ተከትሎ ወይም ደግሞ ጃፓንን ተከትሎ የመልማት ሐሳብ ነበረ፡፡ ይበልጥ የሚማርከው ግን፣ በአገሪቱ ውስጥ የነበረውን የአኗኗር ስልት አስተዳደር ስልትና ባህሉን፣ የኢኮኖሚ ትዳሩን ላይ ላዩን በቁጥራ-ቁጥር ድርደራ ሳይሆን ከመሠረቱ የሚያውቁ ብዙዎቹ ነበሩ፡፡ እነሱ እና ሕዝቡ ነፍስ ለነፍስም ይባል ልብ ለልብ ይተዋወቁ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ዛሬ ስለ ዲሞክራሲ ብዙ የሚነገርበት ዘመን ስለሆነ ትዝ ያለኝን አንድ ምሳሌ ላጫውትህ፡፡
የእርሻ ሚኒስትር የነበሩት፣ ብላታ ዴሬሳ ይመስሉኛል፣ አንድ ሰው እርሳቸው ሚኒስቴር (መሥሪያ ቤት) የሠራውን፣ እርሱ ግን ስህተት የመሰለውን ጠቅሶ ትችት ይጽፋል፡፡ ያንን ወስዶ “ብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ ያትማል፡፡ በሳምንቱ ይሁን በ15ኛው ቀን እቅጩን አላስታውስም፣ ግን በሳምንቱ ይመስለኛል ብላታ ዴሬሳ በስማቸው መልስ ይጽፉለታል፡፡ ያም ታትሞ ይወጣል፡፡ ትዝ እንደሚለኝ፣ መልሳቸውን ሲደመድሙ ተቺያቸውን “አንቱ” እያሉ ይመስለኛል፣ የሚከተለውን የሚመስል ነገር ነበር ያሉት፡- “እርስዎ እርስዎ ከቆሙበት ሆነው የእኔን ሥራ እንዴት እንዳዩ ገልጸውልኛል፡፡ እኔ ደግሞ እኔ ተቆምኩበት ሆኜ የእኔን ሥራ እንዴት እንደማየው ገልጩልዎታለሁ፡፡ ይህንን ከተመለከቱ በኋላ አሳብዎን እንደሚገልፁልኝ ደግሞ እጠብቃለሁ” (ቃል በቃል እንዳልጠቅሳቸው ማስታወሻዬ በቀላሉ ስለማይገኝና ያነበብኩትም የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ስለሆነ ይቅርታ!)፡፡ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴም የማዘጋጃ ቤት ሹም በነበሩበት ጊዜ ስለመሥሪያ ቤታቸው ለተጻፈ ትችት በስማቸው መልስ የጻፉ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ዘመን በኋላ እስከዛሬ ድረስ የሆነውንና የሚሆነውን እያሰቡ ማመዛዘን የአንባብያን ፈንታ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ጋዜጣውን ሆነ ብሎ ለዚህ ጉዳይ ሲል ብቻ እንኳ የሚመረምር ትጉህና ብልህ ወጣት ተመራማሪ ቢገኝ ስለ ዘመኑ የአስተዳደርና የውይይት መንገድ (discourse) ብዙ ቁምነገር ሊነግረን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሲራራ፡- ታዲያ ይህንን ዓይነቱ አኪያሄድ እንዴት ሳያዳብር ቀረ ይላሉ?
ፈቃደ (ዶ/ር)፡- ይኼንን ጥያቄ ለመመለስ የብዙ ሙያ ተመራማሪዎች ጥረት ይጠይቅ ይመስለኛል፡፡ በቀላሉ የሚመለስም አይደለም፡፡ የእኔን የግል አስተያየት እየጠየቅኸኝ ነው በሚል ብቻ ሳሰላስላቸው ከቆየኋቸው ሐሳቦች አንዳንዶቹን ላካፍልህ… “ብርሃንና ሰላም” ውስጥ ይወጡ የነበሩት መልካም መጣጥፎች ቁጥር፣ ዓይነትና ለዛ ከ1923 ዓ.ም. በኋላ ዓይኔ እያየ “እንዴ!” እያልኩ እየተገረምኩ ነበር የተለወጡብኝ፡፡ እንግዲህ ንጉሡ ዘውድ ከጫኑ በኋላ ነገር ተለዋወጠ ማለት ነው፡፡ የእርሳቸው፣ የባለቤታቸው እና የልጆቻቸው ትልልቅ ፎተግራፎች በብዛት መታተም ይጀምራል፡፡ ፊቱኑ በጊዜው ለነበሩት የተማሩ ሰዎች ጋዜጣውን ለቅቀውላቸው የነበረው ከመሳፍንቱ ከመኳንንቱ ከታላላቆቹ ባላባቶችና የጦር መሪዎች ጋር ለነበራቸው የሥልጣን ትግል አጋር እንዲሆኗቸው ነበር ማለት ነው፡፡ ዘውድ ሲጭኑ የሥልጣኑ ነገር ስለተረጋገጠ፣ ጋዜጣው የእርሳቸውን ማንነት በየሳምንቱ ይበልጥ እምጉላት ላይ እንዲያተኩር የተደረገው በያዘው መንገድ ከቀጠለ የተማሩት ሰዎች ሌላ የሥልጣን ኀይል ወይም ተቀናቃኝ ይሆናሉ በሚል ስጋት ይመስላል፡፡ ለውጡ ግን የትኩረት ነው፡፡ ይኼ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ምክንያት ግን በ1928 የአገራችን በጠላት መወረር ካስከተላቸው ብዙ ጥፋቶች ጋር የተያያዘ ይስለኛል፡፡ የአገሩን ቁሳዊና መንፈሳዊ መልክዓምድርና የአኗኗር ሥርዓት ከእርሱ በኋላ ከመጡት ትውልዶች የተሻለ ያውቅ የነበረው፣ በመጠነኛ ትምህርቱና በዚህ አገራዊ ዕውቀቱና ልምዱ እያተወያየ ደህና መራመድ ጀምሮ የነበረው አረማመዱ ግን በጣሊያን ፖለቲከኞና መሪዎችም ያተወደደው ትውልድ በጣሊያን ወረራ ዘመን የተቀጨ ይመስለኛል፡፡ ከእርሱም ጋር ብዙ ነገር ተቀጭቶ ወደ ነጻነት ትግሉ ማተኮር አስፈለገ፡፡ የነጻነት ትግሉም ብዙ የራሱ ችግሮች ነበሩት፡፡ አርበኛ የውስጥ አርበኛ፣ ስደተኛ፣ ባንዳ ተብሎ የተከፋፈለ ሕዝብ ከነጻነት በኋላ በቀላሉ ወደመልሶ መቋቋምና ልማት ሊጓዝ ያልቻለ ይመስለኛል፡፡ በነገራች ላይ አርበኛ ባንዳ እና ስደተኛ የሚለው ክፍፍሎሽ በዘመነ ደርግና ዛሬም ጨርሶ ያልለቀቀን፣ ስሙን እየለዋወጠ እያሳመረና እያሰዋበ የነገሠ አንድ ብሔራዊ ሕመምና አደጋም ይመስለኛል፡፡
ሲራራ፡- ከዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ጋር የበቀለው ትውልድ እንዴት ለውጥ ማምጣት አልቻለም?
ፈቃደ (ዶ/ር)፡- ይብስ የሚከብድ ፕሮብሌም አመጣህ? ይኼም ብዙ ምርምር የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ የእኔ አስተያየት ግን የሚለተለው ነው፡፡ በትምህርቱ ዓይነት እንጀምር? ትምህርቱ ራሱ ምን ዓይነት ነበር? አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ በ1948 ያሳተሙትን መጽሐፍ ብታነብ ብዙ፣ እዚህ አንስተን የማንጨርሳቸው ጉዳዮች እንዳሉ ትረዳለህ፡፡ አገርኛውን ዕውቀት መሠረት አድርጎ ከእርሱ እና ከዘመናዊው ትምህርት ለአገሪቱ ጠቃሚ ጠቃሚውን እየጠቀሱ የማስተማርን አስፈላጊነት ተረድቶ በዚያ ላይ ያልተመሠረተ ስለነበር የትምህርት አኪያሄዱ ራሱ ተተችቷል፡፡ ትምህርቱ መሠረታዊ ፍልስፍና እምብዛም የነበረው አይመስልም፡፡ የአገሪቱ ሕዝብ የሚኖርበትን ሥርዓት፣ የአገሪቱን መንፈሳዊ ቁሳዊ መልክዓምድር ለተማሪው የሚያስተምረው ነበር ለማለት ያሰቸግራል፡፡ አጠገቡ ያለውን ወንዝና ተራራ ሳያውቅ ስለ ሂማሊያና ሚሲሲፒ ነበር የሚማር ማለት ነገር ማኳሸት አይሆንም፡፡ ታዲያ ምን ይዞ ነው አገር ሊለውጥ የሚችለው? ይህ እጅግ መሠረታዊ ነጥብ ነው፡፡ ዛሬም አልተመለሰም፡፡
ሌላው ችግር ከተማረው ሰው መሀከል መልካም ሐሳብ በየዘመኑ እንደየአቅማቸው የጻፉ ይኑሩ እንጂ ሐሳባቸው ተቀባይነት ያገኘበት ጊዜ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ በዚህ ላይ የአገራችን የተማረ ሰው፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ የመንግሥት ሠራተኛ ነበር፡፡ ስለዚህ ነጻነት አልነበረውም፡፡ በኢኮኖሚ ጥገኛ የሆነ ሰው ብዙ ጊዜ ሐሰቡም ጥገኛ እንዲሆን ይገፋፋል፣ ይገደዳልም ማለት ይቻላል፡፡ በኢኮኖሚ ነጻ የሆነ ሰው ደግሞ ብዙ ጊዜ ሐሳቡ ነጻ የሚሆንበት ዕድል ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው በነጻ ለማሰብ የሞከሩ፣ የኢኮኖሚ ነጻነት ኖሯቸው በሐሳባቸው ጥገኛ የነበሩና ዛሬም የሆኑ የሉም ማለት አይደለም፡፡ ይኼ ራሱ አንድ ችግር ነው ለማለት ብቻ ነው ያነሳሁት፡፡
በዚህ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተማረ ሰው አገርን በበላይነት የመራበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ሁልጊዜ ባለጠመንጃው ነው ሥልጣን የሚይዝ፡፡ እርሱ ደግሞ ከተማሩትና ተማሩ ከሚባሉት መሀከል አብረውት እንዲሠሩ የሚመርጣቸውን የሚመርጠው በራሱ መመዘኛ ነው፡፡ ከመረጣቸውም በኋለ ምክራቸውንና ዕውቀታቸውን ምን ያህል እንደሚቀበል አይታወቅም፡፡ ሥልጣን ላይ አንድ ሁለት ዓመት ከቆየ በኋላ ባለሥልጣኑ ራሱ ሁሉን ነገር አውቃለሁ የሚል ስሜት ስለሚያድርበት ብዙ ጊዜ በሁሉም መስክና ሙያ ከእነሱ ይልቅ ራሱን ያዳምጣል፤ ለእነርሱም እንዳስተማሪ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ብዙዎችም አደግድገው ይማራሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ታዲያ አንድም መሪዎች ከእነርሱ የተሻለ ዕውቀት እና ብርቱ ሰብዕና ያላቸውን በሌላ አነጋገር በራሰቸው ዕውቀትና ማንነት የሚተማመኑትን ከሚመርጡበት ጊዜ የማይመርጡበት ጊዜ በታሪካችን በዝቶ ስለሚገኝ ይመስላል፡፡ ሌላው ቀርቶ አንድ ዘበኛ አምስት ሌሎች ዘበኞችን የመቅጠር ሙሉ መብት ቢሰጠው በሁሉም ነገር ከእሱ የሚሻሉትን ከመምረጥ ይልቅ ከእርሱ የሚያንሱትን የሚመርጥ ይመስላል፡፡ ይህ በየደረጃው ከራስ ያነሰን ሰው የሚያስመርጥ ሥርዓት እጅግ በተንሰራፋበት ሁኔታ ውስጥ አዎንታዊ ለውጥን መመኘት ዘበት ይሆናል፡፡ አንዳንዴኮ በዚህም ወደኋላ ሄደናል የያስብላል፡፡ አስብ እስቲ፣ ምኒልክን እና ጎበናን ምኒልክን እና አሉላን፣ ምኒልክንና ባልቻን፣ ምኒልክን እና ሀብተጊዮርጊስን እንዲህ እያልክ ቀጥል፡፡ በምን-ምን ዓይነት ሰዎች ንጉሠ ነገሥቱ እንደተከበቡ ልብ በል፡፡ በዘመኑ መስፈርት ጠንካራ ቀጥተኛ ታማኝ ጀግና የሚባሉትን እኮ ነው ያስባሰቡት፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ጊዜው የተከተልነው ባብዛኛው የዚህን ተቃራኒ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሲራራ፡- የትውልድ የትምህርትና የአስተዳድር ተከታታይነት ወይም ቅብብሎሽ ከሌለ ያለው ምንድን ነው?
ፈቃደ (ዶ/ር) ያለውማ፣ ባብዛኛው ማንሳት መጣል ከዚያ ደግሞ ሀ ብሎ መጀመር፣ መያዝ መጣል ነው፡፡ በእኔ ዕድሜ ያየሁት ባብዛኛው ይህንን ነው፡፡ ለዚህም ነው ብዙ መራመድ ያልቻልነው፡፡ ጠንካራ ድልድይ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ክፍተቱ ይበዛል፡፡
አየህ፣ በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበሩት ልዩ ልዩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋዜጦች ውስጥ የታየ መልካም ነገር ነበር፡፡፡ አንዳንዱ አዝጋሚ ለውጥን ደግፎ አንዳንዱ ዛሬም የሚነሳውን የሊብራል ዲሞክራሲ ሐሳብ ደግፎ፣ ዓይናፋሩ ደግሞ አልፎ አልፎ ፊቱን ተሸፋፍኖ የጥንቱን ደግፎ፣ ሌላው ደግሞ “ሶሻሊዝም፣ ኮሚኒዝም፣ ማርክሲዝም” የተባሉትን ደግፎ ይፅፍ ነበር፡፡ ይኼ መልካም አዝማሚያ ነበር፡፡ በሁለት የተለያዩ ሐሳቦች መሀከልም፣ አልፎ አልፎ አንዳንድ ክርክርም ይታተም ነበር፡፡ ይህ ግን አልቀጠለም፡፡ እኔ “የመሬት ላራሹ ትውልድ” የምለው እና እርሱን የሚደግፉ የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ኀይሎች ሲያይሉ በ“ድርጅታዊ አሠራር” (በሕቡዕ፣ በስውር፣ በምስጢራዊ የቡድን አሠራር ማለቴ ነው) መጓዝ በግልጽና በዲሞክራሲያዊ ውይይት ለመጓዝ የተጀመረውን ሙከራ አጨናገፉት፡፡ በዚህ ብቻ እንኳን ክፍተት ተፈጥሯል ማለት ይቻላል፡፡ በእኔ ትውልድ እና ከእኔ በፊት በነበረው እና ከእኔ በኋላ በመጡት ትውልዶች መሀከል ያውን ለጊዜው ተወት አድርገን ማለቴ ነው፡፡ በትውልዶች መሀከል ግንኙነት መፍጠር እኮ በተቻለ መጠን እንደ ሪሌ ዱላ ቅብብሎሽ እንዲሆን መሥራት ያለብን፡፡ እርግጥ እንደሪሌው ቅብብሎሽ እርግጠኛና የተሳካ ሊሆን አይችልም፡፡ ብቻ ትውልድ ለትውልድ እያቀበለ፣ ተቀባይም የተቀበለውን ቢያንስ እንዳገኘው፣ ሲሆን-ሲሆን ደግሞ አዳብሮና ጉድፉን ነቅሶ ለተከታዩ ትውልድ ለመስጠት መትጋት አለብን፡፡ ይህ የባህል፣ የትምህርት፣ የአስተዳደር የእምነት የማኅበራዊ ኑሮ የፍልስፍና፣ የርእይ ወዘተ…፣ ቅብብሎሽ ከሌለ የተበጣጠሰውን ይዞም ሆነ በጭፍንና በድንቁርና በባነኑ ቁጥር ለመቀጣጠል እየናወዙ ትርጉም ያለው ኑሮ መኖር የሚቻል አይመስለኝም፡፡
ሲራራ፡- ብዙ ሰዎች የወጣቱ ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ ነው ይላሉ፡፡ ዕውን የወጣቱ ኢትዮጵያዊነት እንደሚባለው አደጋ ላይ ነው?
ፈቃደ ዶ/ር፡- ቁርጥ አድርጎ እንደመጠየቅ ቁርጥ ያለ መልስ መስጠት ይከብዳል፡፡ ብቻ ከፍ ብዬ የጠቀስኳቸውን የብዙኃን መገናኛዎች አኪያሄድ ስመለከት በተከማው ውስጥ ያሉትን የመሥሪያ ቤቶች፣ የሆቴሎች፣ የኬክ ቤቶች፣ የሱቆችና የልዩ ልዩ የንግድ ድርጅቶች ስሞች ስመለከት እኔም አሰጋለሁ፡፡ በዐፄው እና በደርግ ዘመን የነበሩን ስሞች ስመለከት ብዙዎቹ፣ እጅግ ብዙዎቹ ከአገራዊ እውነታ፣ አኗኗር፣ መልክአምድር ከኢትዮጵያነት ጋር የተያያዙ ይመስሉኛል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ከወጡት የአማርኛ ጋዜጦችና መጽሔቶች ብዙዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማገልገል በብሔርተኝነት ስሜት ጭምር መነሳሳታቸወን በየጊዜው የሚልፁ ናቸው፡፡ የአንዳንዶቹን ስም ስመለከት ግን ይገርመኛል፣ ያስቀኛ፣ ያናድደኛልም፡፡ እርጅና ይሆን? አይመስለኝም!
ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አንዳንድ ከተሞችም ስሞችን በሚመለከትም ተመሳሳይ ወረራዎች ተመልክቻለሁ፡፡ የገጠሩን ሁኔታ ግን በውል አላውቅም፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ከ27 ዓመቱ የአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሽኩቻ ጋርም የተያያዘ ድብብቆሽ እንዳለበት እገምታለሁ፡፡ ግን ወረራው ያስፈራል፡፡ በከተማ አፀደ ሕፃናትና በልዩ ልዩ ትምህርት ቤቶች በሚሰጡ ትምህርቶች ውስጥ ገቡ መሠረታዊ ጥቅም የሌላቸው የውጭ ባህሎችን ስመለከት አዝናለሁ፡፡ ከውጭው ባህል መልካም መልካሙን ቢወርሱኮ ከሚደሰተቱት አንዱ እኔ እሆን ነበር፡፡ ብዙ ገንዘብ አስከፍለው በጉሮሮና ባፍንጫ ብቻ የሚጊያጌጥ ብልጭልጭ እንግሊዝኛ ከሚያስተምሯቸው ጥሩ መጻፍና መናገርን፣ ድንቅ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን እያጣጣሙ ማንበብን ቢያስተምሯቸው ከሚከፈለው ገንዘብ ብዙውን ለቤተ መጻሕፍት ማዳበሪያ፣ በኮምፒውተር መሥራት ለማስተማሪያ እና በተለይ ደግሞ ለፊዚክስ፣ ለኬሚስትሪ፣ ለባዮሎጂና ለተግባራዊ ሳይንስ ላቦራቶሪዎች ሲያውሉ ባያቸው ስጋቴ ይቀንስ ነበር፡፡
ለዚህ ነው ስለወደፊቱ ሳሰብ የምሰጋው፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ በብሔረሰብ አስተሳሰብ የሚታመሰውን ወጣት ሳይጨምር ነው፡፡
ከዚህ በላይ የተናገረርኩት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ የዛሬውን የከተማ ውስጥ አኗኗራችንን ስመለከት የአገሬን ሕዘብ በጣም አደንቃለሁ፡፡ አከብራለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ድህነት ውስጥ ተዘፍቆ እንኳ ባንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የምናየውን ዓይነት የተመሰቃቀለ የሥነ ሥርዓት ጉድለት ሲደርስ አለማየቴ ይገርመኛል፡፡ ብዙው ተርታ ሕዝብ ድህነት ውስጥ የተዘፈቀውን ያህል እጅግ ጥቂቶች ደግሞ በድሎት ውስጥ ተዘፍቀው ይታያሉ፡፡ ይህንን እያየ በሰላም መኖሩን ባብዛኛው በሥነ ሥርዓት ውሎ መግባቱን ስመለከት ደግሞ ለዘመናት እንደልብ ተክፍለ አገር ወደ ክፍለ ሀገር፣ ተአውራጃ ወደ አውራጃ ከተማ ወደ ከተማ እንደልብ ተጓጉዞና ተቀባቅሎ በመኖር ያዳበረውን እኔ “ጋሩማ” የምለውን ባህል ማድነቄን እንድቀጥል እበረታታለሁ፡፡ አሁን አሁን ግን በየአካባቢው የሚታዩት ዓይተናቸው የማናውቃቸው አስፈሪም አሳፋሪም ሁኔታዎች ይህን “ጋሩማ”ን እንዳይነጥቁን እንዳያሳጡን በእጅ እሰጋለሁ፡፡
ሲራራ፡- “ጋሩማ” ማለት ምን ማለት ነው?
ፈቃደ (ዶ/ር) ባጭሩ “የጋራ” ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዘመናት የኖሩትን ዛሬም የምኖረውን ሰዎች ባንድነት የሚያቆየን ሐሳብ ነው፡፡ በእኔ አስተያየት ለረዥም ዘመናት በጦርነትና ሰላም፣ ለረዥም ዘመን በንግድ ጋብቻ፣ በመጋደልና በመዋለድ ስንኖር፣ እኛም ሆንን በታሪክ የተጠቀሱ ጠላቶችን ስላላጠናነው ይኸው በውጭ ኀይል ቅኝ ሳንገዛ በራሳችንም ኀይል ሳንለማ አለን፡፡ ልዩ ልዩ እኛን የማይጠቅሙ አዋጆችና ደንቦች ሳናውቅ በስህተት አውቀን በድፍረት ብናወጣም እንኳ ይህ የማናውቀው፣ ያላጠናነው “ጋሩማ” እስከዛሬ አብሮ አቆይቶናል ብዬ ማሰብ ከጀመርኩኝ ቆይቻለሁ፡፡ ሐሳቡ ረዘም ያለ ማብራሪያ ስለሚፈለገ፣ አንባብያን “ልሳነ ኢኮኖሚክስ” በተባለው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር በሚያሳትመው መጽሔት የወጣውን ጽሑፌን፣ ወይም ደግሞ “ሰሚ ያጡ ድምጾች” የተባለውን አንዳንድ የምርምር ጽሑፎቼ የታተሙበትን መጽሐፍ እንዲመለከቱ አጋብዛለሁ፡፡
ሲራራ፡- “የመሬት ላረሹ ትውልድ” የሚባለው ጠፍቶ ያጠፋው ግራ በመጋባቱ ነው በሚለው አስተያየት የስማማሉ?
ፈቃደ (ዶ/ር)፡- ግራ የተገባ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ነገር ግን፣ ለምን ግራ ተጋባ? እኔ፣ አንድ ለውጥ የሚፈልግ፣ ለውጥ ለማምጣት ባቅሙ ደፋ ቀና ስለሚል ጭቆናና በደልን በዝምታ አንገቱን አቀርቅሮ ለመቀበል የማይሻ ትውልድ ስለነበረ ይመስለኛል ግራ የተጋባው፡፡ በድህነት በተዘፈቀ ማኅበረሰብ ውስጥ ዳንስና ዘፈን ማብዛት ሐሺሽን እና ጆሊጃኪዝምን ማስፋፋት የቁንጅና ውድድር ማኪያሄድና የፋሽን ትርዒት ማሳየት አሳዛኝ ምግባራዊ ቅሌት ነው ብሎ ያሰብ የነበረ ትውልድ ስለነበረ ነው ግራ የተጋባው፡፡ ግራ የተጋባው ግን ለለውጥ ስለታገለ አይደለም፡፡ ግራ የተጋባው የአገሩን ቁሳዊና መንፈሳዊ መልክአምድራዊ ሁኔታ አበጥሮ ሳያጠናና ሳያውቅ ትግል በመጀመሩ ይመስለኛል፡፡ ልብ በል፣ ይኼ ሐሳብ መልሶ ወደ ትምህርት ሥርዓቱ ነው የሚወስደን፡፡ ያልተማረውን ከየት ያምጣው?
በተጨማሪ የተማሪን እንቅስቃሴ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንቅስቃሴ በመመልከቱም ይመስለኛል ግራ የተጋባው፡፡ በአገሪቱ ውስት የነበረ፣ የብዙውን ሰው ሐሳብ የሚያዳምጥ የፖለቲካ ልምድ ስላልነበረም በወጣትነቱና በመልካም ፍላጎቱ እየተገፋ ብዙ ነገሮን ፈፀመ፡፡ ከሁሉም የባሰው ደግሞ እርስ በርሱ መከፋፈሉ ያመጣው እልቂት ነው፡፡ ነገር ግን ግራ ተጋባ የሚባለው የመሬት ላራሹ ትውለድ ስለ መሬት ስለ አፍሪካ ነፃነት ስለ ኢምፔሪያሊዝም፣ ስለ ቬየትናም ወረራ፣ ስለ ‹ሮዴዥያ› (የዛሬይቱ ዚምባብዌ)፣ ስለአፓርታይድ እያነሳ ይጽፉ፣ ይናገር፣ ሰላማዊ ሰልፉ ይወጣ የነበረው ዕድሜያቸው ባብዛኛው ከ15 እስከ 25 የሆኑ የዩኒቨርስቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪችን እያሳተፈ እንደነበር መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህ የሠራቸውን መልካም ነገሮች እያስታወሱ ማድነቅም ግዴታ ይመስለኛል፡፡ በልምድና ዕውቀት ማጣትና በልዩ ልዩ የውስጥና የውጭ ኃይሎች በቀላሉ ተጠልፎ የፈፀማቸውንም ስህተቶች አጥንቶ ከዚያ መማር የሚገባ ይመስለኛል፡፡ የሥልጣን ሽሚውያም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በስደት ፖለቲካና እና በአገር ውስጥ ፖለቲካ መሀከል ተከስቶ የነበረውን ጠንቅም ማሰብ የስፈልጋል፡፡ የሆነ ሆኖ ስለትውልድ በጅምላ ከመነጋገር በምርምር እየተገዝን በፈርጅ በፈርጁ ብንወያይ ይሻላል፡፡
ደግሞ እኔ የመሬት ላራሹ ትውልዱ የምለው ግራ የገባው ትውልድ ከተባለ የዛሬው ትውልድ ምን የገባው ሊባል ነው ያሰበው? ነገ ጣታቸውን የሚቀስሩ እሱ ላይ ነው፡፡ ታዲያ ስለ መሬት ላራሹ ትውልድ ሊያወራቸው ነው? ወይስ ስለረሱ ምንም ሳያመነታና ሳያፍር የሚነግራቸው ነገር አለው? ከ1970ዎቹ ወዲህ የተወለደ አዲስ ትውልድ እኮ አለ፡፡ እርሱስ ምን የሚለው አለው? ዕድሜው 25 እና ከዚያ በላይ የሆነው እኮ ስለራሱም ነባራዊ ሁኔታ ነው ዛሬ በትምህርት ቤቶችና ባደባባይ በግልጽ በሰላማዊና በዕውቀታዊ መንገድ መወያየትና መከራከር ያለበት፡፡
ሲራራ፡- በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ፣ በድርግና አሁን ባለው የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ የነበረውንና ያለውን የትውዶች ግንኙነት እንዴት ይገመግሙታል?
ፈቃደ (ዶ/ር)፡- የዘረዘርካቸው እኮ መንግሥታት ናቸው፡፡ ስለዚህ ከፖለቲካ ሥልጣን ከኢኮኖሚ ከውስጣዊና ከውጫዊ ሰላም ጋር እያያዝኩ ነው ይህንን ጥያቄ መመለስ የምሻው፡፡ የዐፄው ትውልድ በርሳቸው ዘመን አገሪቱን ሲገዛ “የመሬት ላራሹ ትውልድ” እና ሌሎች ተቺዎች ነበርን፡፡ በተለይ ከ1966 በኋላ የመሬት ላራሹ ትውልድ ወደተለያዩ ቡድኖችና ፓርቲዎች በይፋ ተከፋፍለ፡፡ የተወሰነው ወገን ከደርግ ጋር እስከተለያዩ ደረጃዎች ተጓዘ፡፡ ከደርግ ጋር የዘለቀውም ዘለቀ፡፡ ጫካ ከገባው መሀከል ሁለቱ፣ ሁለት አገርና ሁለት መንግሥት በ1983 ‹ሀ› ብለን አቋቋምን አለ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ነገሩ ዛሬ ታለበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ስለዚህ ከዐፄው በኋላ፣ በደርግና በኢሕአዴግ የሥልጣን እርከኖች ውስጥ የነበረውና ያለው ባብዛኛው የ1960ዎቹ ወጣት ነው፡፡ በተቃዋሚነት ከተሰለፉት ውስጥም የዚሁ ትውልድ አባላት በብዛት አሉ፡፡ ሁሉም አሉበት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በሦስቱ መንግሥት በተኖረው ኑሮ ሦስቱን መንግሥታት ማነጻጸሩ ይሻላል፤ ትውልዶችን በቀጥታ ከማነጻጸር፡፡ ያንንም የማደርገው ያው በእኔ አመለካከት ነው፡፡
በመጀመሪያ ከቁሳዊው ነገር አንዳንዱን ላንሳ፡፡ ቁሳዊ የምለው ዳቦን ነው፡፡ ይህ ምሳሌ ተደጋገመ፡፡ ምን ይደረግ? ቁልፍ የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፡፡ በዓይን የሚታይ በእጅ የሚዳሰስ እሆድ ውስጥ መኖር አለመኖሩም በውል የሚታውቅ፡፡ እኔ በበኩሌ በዳቦ ዋጋ ብቻ ልዩነታቸውን እለካበታለሁ፡፡ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ፣ በአምስት ሳንቲም ሁለት ዳቦ ገዝቶ መብላት ይቻል ነበር፡፡ ያ ዳቦ ዛሬ በ20 ሳንቲም አንድ የሚገዛውን ዓይነት ገና ሲነኩት የሚፈረካከስ፣ ጡር ካልፈሩ ጠቅልለው እንደኪኒን በውኃ አርሰው የሚውጡት ዓይነት እንዳይመስልህ፡፡ እሱን በልተህ አንድ ጠርሙስ ውኃ ከሻይ ቤት ጠይቀህ፣ ያላንዳች ማመንታት ተሰጥቶህ፣ ያንን ጠጥተህ ትምህርት ቤት መሄድ ትችላለህ፡፡ ዛሬ ያንን ማድረግ ይቻላል? መሬት ጠበበ፣ ሕዝብ በዛ፣ ምርት ቀነሰ የሚል ምክንያት ይሰጣል፡፡ ሌላውም ብዙ ምክንያት፡፡ ነገር ግን፣ ከምኒልክ ዘመን ጋር ሲነጻጸር እኮ ያፄው ዘመን ሕዝብ ቁጥርም በዝቷል፡፡ እኔ ዋናው ጥያቄ ሌላ ይመስለኛል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት ዋናው ነው፡፡ ዕውቀትን እና የአስተዳደር ብቃትንና ኀላፊነትን ባለፉት 45 ዓመታት እያፋቱ ቀሽም ክድርናን እና ሥልጣንን እያጋቡ መጓዝ የዚሁ እጦት አንድ ገጽታ ነው፡ የመንግሥታትና የጭፍሮቻቸው ዋና ትኩረት የራሳቸውን የሥልጣንና የጥቅም ዘመን ለማራዘም ቀን ከሌት መባከን ላይ መሆኑም ሌላው የእጦቱ ገጽታ ይመስለኛል፡፡
ማኅበራት ያልኩህ ደግሞ ሽምግልናውን፣ እርቁን በቤተሰብ ውስጥ ያለውን ግንኙነት፣ ከጎረቤት ጋር ያለውን ኑሮ የሥነ ምግባርን ሁኔታ ወዘተ… መለኪያ ሳደርግ የማገኘውን ነው፡፡ እነዚህ ፍፀም ናቸው ማለቴ አይደለም፡፡ መሻሻል የሚገባቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ግን ለማኅበሩ መረጋጋትና ሰላም እስከዛሬ ከፍተኛውን አስተዋጽዖ እያደረጉ ያሉት እነርሱ ይመስሉኛል፡፡ አዲስ የተዘረጉት ዘመናዊ ሚባት መዋቅሮች ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል የሚል ጠንካራ እምነት የለኝም፡፡ በዚህ ላይ የምግባር ጉዳይ አለ፡፡ እኔ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ይባል በነበረው ውስጥ እማር በነበረበት ጊዜ፣ በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥም ሆነ በየመንገዱ ላይ ተማሪ ሲጃራ ደፍሮ አያጨስም ነበር የሚል ትዝታ ነው ያለኝ፡፡ ብናጨስ እንኳን ከትልልቅ ሰውና ከአስተማሪዎቻችን ተደብቀን ወይ ጫካ ሄደን ወይ ስውር ብለን ነበር፡፡ አስተማሪ እያየ ማጨስ አይታሰብም፡፡ ከአስተማሪ ጋር ጫት መቃም ሲጃራ ማጨስና መጠጥ መጠጣትማ እንኳን በውን በቅዠትም አይታሰብም፡፡
ዛሬ ብዙ ወጣት ጠጪ አለ፡፡ ዘመኑ “ገንዘብ! ገንዘብ!” የሚልና የሚያስኝም ስለሆነ ነው መሰለኝ፣ እርሱ ይጠይቅ፣ ገንዘብ ይዞ ይገኝ እንጂ ልጅን የሚመክርና የሚከለክል መጠጥ ሻጭ ቁጥር በጣም የቀነሰ ይመስላል፡፡ አንዳንዴማ በአንድ እጅ ጡጦ ይዞ ቢገባም የሚቀዳለት ይመስላል፡፡ እናስ? ስለ መንግሥት ስናወራ እንዲህ ዓይነቶቹን ያውም ገር ገሩን መመዘኛዎች ይዘን ከሆነ ለማወዳደር ብዙ የምንቸገር አይመስለኝም፡፡
ሲራራ፡- ምሁራን ከትውልዱ ጋር አብረው እንደወደቁ ሊቆጡሩ ይችላል?
ፈቃደ (ዶ/ር)፡- ወሰብሰብ ያለ ጥያቄ ነው፡፡ በእኔ አስተያየት፣ ይኼ “ምሁራን” የሚል ቃል በተለያየ ሙያ የሰለጠኑ፣ ወይ ዲግሪና ዲፕሎማ ያላቸው በሚል ቢተካ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ፣ “አካውንታንት፣ መሐንዲስ፣ ሐኪም፣ ኢኮኖሚስት ወዘተ… እያልን ብንነጋርስ?” እላለሁ፡፡ ሆኖም ጥቂት ስለእነርሱ ላውራ፡- በተለይ ስለ አንጋፋው ዩኒቨርስቲ፡፡
በእኔ አስተያየት ዋናው ተጠቂ በሦስቱም መንግሥታት እሱ ነበር፡፡ የጥቃቱ መጠን ያለጥርጥር ይለያያል፡፡ እየባሰ እየመረረ ነው የመጣ፡፡ በዐፄው ጊዜ መሬት ላራሹን ያነሳ ዞሮ ዞሮ ይኼው ግቢ ነበር፡፡ ነገር ግን አባላቱ አመጽ እየተባሉ ሲታሰሩ፣ ሲደበደቡ እና ሲገደሉ ድምፁን አጉልቶ ያሰማለት የማኅበረሰብ ክፍል እምብዛም አልነበረም፡፡ አብዮት በተፋፋመበት ዘመን፣ “አብዮቱ ዩኒቨርሲቲው በር ላይ ደርሶ አይቆምም!” እየተባለ ተፈክሮ በደርግ ዘመን የሆነው ሁሉ ሲሆን ደርግን “ተው!” ለማለት የደፈረ አልተገኘም፡፡ በኢሕአደግ ጊዜ፣ 42 መምህራን ከዩኒቨርስቲ ሲባረሩ በአገር ውስጥ የተቆጡ ዜጎች ደምጽ በአደባባይ አልተሰማም፡፡ ግን ደግሞ፣ ያኔም ዛሬም፣ አገሪቱ ውስጥ አንድ መጥፎ ነገር ሲከሰት ብዙ ጊዜ “ምነው ዩኒቨርሲቲው ዝም አለ?” ይባለል፡፡ ይኼ በጅምላ ስለ ዩኒቨርስቲው ሲነገር የሚነሳ ነው፡፡
የተማረ ሰው ግን በዩኒቨርስቲም ውስጥ ከዩኒቨርስቲም ውጭ አለ፡፡ አስተሳሰቡ አመለካከቱና አቋሙ እንደየማንነቱ የተለያየ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የነበሩ የተማሩ ሰዎች የአገርና የማኅበረሰብ ጉዳይ እያነሱ በአደባባይ ይናገሩ ስለነበር በእነርሱ ላይ ይተኮራል፡፡ ከተነጋገርን፣ መነጋገር ያለብን ስለተማረው ዜጋ ሚና ባጠቃላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዚህ ኢንተርቪው የሚደፈር ርእስ አይደለም፡፡ ሆኖም፣ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ላቅ ያለ ዕውቀትና ልምድ በየሙያው ያላቸው የተማሩ ሰዎች ባለፉት ዓመታት ካለፉባቸው ሁኔታዎች በመነሳት ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩ ይመስላል ማለት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በየልባቸው ለመንግሥት፣ “እናንተ ጉልበት፣ ማለትም የጠመንጃና የእስር ቤት ጉልበት አላቸሁ፡፡ እኔ ደግሞ የለኝ፡፡ እንኖረኝም አልፈልግም፡፡ ስለዚህ አንመጣጠንም!” ብለው ራሳቸውን አግልለው መኖርን የመረጡ ይመስላል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በይፋ በሰላማዊ ፖለቲካ ውስጥ እየታገሉ ያሉ አሉ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ በመንግሥት ሥልጣን ላይ በመንግሥት ቢሮክራሲ ውስጥ በግል ሥራ ውስጥ ወዘተ… ሁሉ ያንድ ትውልድ አባላት ስለሚገኙ ነገሩን ውስብስብ ያደረገዋል፡፡ ጥያቄህን በቀላሉ መመለስ ያልቻልኩም ለዚህ ይመስለኛል፡፡
ሲራራ፡- “የእኛ ትውልድ” ወይም “የእኛ ዘመን” የሚለው ሐሳብ በምን የሚወሰን ነው?
ፈቃደ (ዶ/ር)፡- “የእኔ ትውልድ” የምትለውን በቀላሉ መወሰን የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ባንድ ወቅት ተመሳሳይ ጥያቄ ስመልስ ያልኩት ነው ባጭሩ ብጠቅሰልህ የምወድ፡፡ ትውልድ የሚለው ቃል፣ በተወሰነ ጊዜና ቦታ የኖሩ ወይም በመኖር ላይ ያሉ፣ ከሞላ ጎደል የጋራ የሆነ አመለካከት፣ ተግባር፣ ምኞት፣ ሥነ ምግባር ወዘተ… ያላቸውን ወገኖች የሚገልጽ አድርጌ ነው የምመለከተው፡፡ በሻይና ቢራ ላይ በመበሻሸቅ መልክ የሚመጣ የመበላለጥ ጨዋታ አለ፡፡ ደግሞ የምር መበላለጥ አለ፡፡ እርሱን በምርምር ለይቶ ማወቅ ነው የሚሻል፡፡ ግን ደግሞ እንደ የመሬት ላራሹ ትውልድ በአገራችን ውስጥ የተንቀሳቀሰና ያነጋገረ ትውልድ አለ? ይህንን መመስከር ማድላት አይመስለኝም፡፡ ስላንድ ትውልድ ጥሩም መጥፎም መናገር የሚቻው አንድም በሆነ ምክንያት መንቀሳቀሱ፣ ደጋግሞ መጮሁ፣ የቻለውንም ያህል ለመተግበር መሞከሩ በተርታው ሕዝብ ዘንድ ጭምር ሲታወቅ ይመስለኛል፡፡
(ከአዘጋጁ፡- ይህ ከዶ/ር ፈቃደ ጋር የተደረገው ውይይት ከደም ሲል በየወሩ ትታተን በነበረው ‹ውይይት› ከተሰኘች መጽሔታችን ጋር የተደረገ ነው፡፡)
Leave a Reply