“በትግራይ ክልል ያለው የሚና መደበላለቅ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጠው አደገኛ ነው” | አቶ አታክልቲ ወልደሥላሴ
እንወያይ, እንግዳ

“በትግራይ ክልል ያለው የሚና መደበላለቅ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጠው አደገኛ ነው” | አቶ አታክልቲ ወልደሥላሴ

በትግራይ ክልል ከተካሄደው “የሕግ ማስከበር” እርምጃ በኋላ ክልሉ በጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመራ ተደርጓል፡፡ ኮማንድ ፖስትም ተመድቧል፡፡ ሆኖም ክልሉን እንዲያረጋጉ በተመደቡት አመራሮች መሀከል የሚና መደበላለቅ እንዳለ እና በዚህም ምክንያት ሕዝቡ እየተማረረ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች የተመደቡት አመራሮችም እየለቀቁ ነው፡፡ በቅርቡ ከኀላፊነታቸው የተነሱት የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አታክልቲ ወልደሥላሴ ከእነዚህ አመራሮች አንዱ ናቸው፡፡ በምስጉን አመራርነታቸው ብዙ ሲባልላቸው የነበሩት አቶ አታክልቲ እንዴትና ለምን ለቀቁ? የክልሉ ወቅታዊ ሁኔታሰስ ምን ይመስላል? በእነዚህና እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አወያይተናቸዋል፡፡ ውይይቱን እነሆ፡-

ሲራራ፡- በትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ መቀመጫውን በውጭ ያደረገው የትግራይ ሚዲያ ሐውስ (TMH) የመንግሥት ሚዲያዎች እና የውጭ ሚዲያዎች የሚያወጧቸው መረጃዎች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ከክልሉ ውጭ ያለው ማኅበረሰብ እውነተኛ መረጃ ማግኘት አልቻለም፡፡ በእርስዎ እይታ አሁን በትግራይ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ምን ይመስላል? ውይይታችን በዚህ እንጀምር፡፡

አቶ አታክልቲ፡- እውነት ነው ከፍተኛ የሆነ የሚዲያ ጦርነት ነው ያለው፡፡ አንዱ የሚለውና ሌላው የሚናገረው ፍፁም አይገናኝም፡፡ በዚህ ምክንያት እንኳን ከትግራይ ክልል ውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ እኛም መቀሌ ውስጥ እየኖርን በጣም የምንፈተንበት ጉዳይ ነው፡፡ በእኔ በኩል የተጠናከረ መረጃ መስጠት የምችለው በመቀሌ ከተማ ስላለው ሁኔታ ብቻ ነው፡፡ ስለ ሙሉ ትግራይ ያለኝ መረጃ እኔም ከአንተ የተሻለ አይደለም፡፡ የመቀሌ ከተማ አስተዳደር መቀሌ ከተማን ሲረከብ መብራት እና ውሃ ሙሉ በሙሉ በሌለበት፣ ከፍተኛ የጸጥታና የደህንነት ስጋት በነበረበት፣ ማንኛውም ዓይነት የግልም ይሁን የመንግሥት ተቋም አገልግሎት ባልጀመረበት ሁኔታ ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት በመቀሌ ከተማ ሁሉም ነገር ከሞላ ጎደል ተስተካክሎ ሥራ ጀምሯል፡፡ መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ባንክ እና ትራንስፖርት ወደ ቀድሞ ሥራቸው ተመልሰዋል፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎትም ለሚመለከታቸው ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደገ ነው፡፡ በመቀሌ ከተማ ሁሉም በሚባል ደረጀ መሠረተ ልማቶች ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ከመንግሥት አገልግሎት አንጻር የጤና፣ ገቢዎች፣ ግብርና፣ የጥቃቅን እና አነስተኛ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤቶች ሁሉም ዘርፎች አገልግሎት እየሰጡ  ይገኛሉ፡፡ አገልግሎት ያልጀመረው የትምህርት ዘርፍ ብቻ ነው፡፡

ከጸጥታ አንጻር ወደ መጀመሪያ አካባቢ ለሚዲያም ስንገልጽ እንደነበረው በከተማዋ የተደራጀ እና በትጥቅ የታገዘ ዝርፊያ ይፈጸም ነበር፡፡ ሕወሓት በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ፈትቶ በመልቀቁም ጭምር የነበረው ዝርፊያ በጣም የተደራጀ ነበር፡፡ የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ዩኒፎርም እየለበሱ እና በተሽከርካሪ እየታገዙ በጣም ከፍተኛ ዝርፊያ የሚፈጽሙ አካላት ነበሩ፡፡ ማን መቼ እንደሚመታህ፣ ማን ከየት መጥቶ እንደሚዘርፍህ አታውቅም ነበር፡፡ በጥቅሉ በከተማዋ የነበረው አስፈሪ የሆነ የፍርሃት ድባብ ነበር፡፡ አሁን በዚያ ደረጃ የሚገለጽ የጸጥታ ስጋት የለም፡፡ ሁሉም ገበያዎች፣ የንግድ ተቋማት ወደ ቀደሞ ሥራቸው ተመልሰዋል፡፡ ሰዓት እላፊው እስከ ማታ ሁለት ሰዓት ነው፡፡ ይህን ተጠቅመው አልፎ አልፎ የሞባይል ስርቆቶች በተለያዩ አካባቢዎች ይስተዋላሉ፡፡ ይህን ለመቅረፍ 1 ሺሕ 680 ወጣቶችን በማደራጀት በየሰፈራቸው ጸጥታ እንዲያስከብሩ እያደረግን ነው፡፡ በዚህም በግልጽ የሚታዩ ለውጦችን አምጥተናል፡፡

ከሰብአዊ ድጋፍ አንጻር ሕግን ለማስከበር በተደረገው ዘመቻ በርካታ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ከ120 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ወደ መቀሌ ከተማ ገብተዋል፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎም በከተማዋ በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ነበሩ፡፡ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ባለው የሴፍትኔት ፕሮግራም ከፍተኛ ቁጥር ድጋፍ የሚያገኘው የትግራይ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ቀደም ብሎም በክልሉ ከፍተኛ ችግር እንደ ነበረ ነው፡፡ ያን ታሳቢ በማድረግ የሰብአዊ ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን በመቀሌ ከተማ ብቻ ለ350 ሺሕ ሕዝብ  ድጋፍ አድርሰናል፡፡ ያም ሆኖ ድጋፉ በቂ እንዳልሆነ አይተናል፡፡ ድጋፍ የሚፈልገው ሕዝብ  እና እየቀረበ ያለው የድጋፍ መጠን የሚመጣጠን አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን በመቀሌ ከተማ የተሟሉት ነገሮች በሌሎች የትግራይ አካባቢዎችም ተሟልተዋል ማለት አይደለም፡፡

ሲራራ፡- በሌሎች አካባቢዎች ስላለው ሁኔታ ያለዎት መረጃ እምብዛም መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ ሆኖም የመቀሌን ያህልም ባይሆን በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎችም የመዘዋወር ዕድል ነበረዎት፡፡ ባዩት መጠን በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ አታክልቲ፡- እንዳልኩህ ነው፤ በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች ስላለው ጉዳይ ዝርዝር የተጠናከረ መረጃ የለኝም፡፡ ይህን መረጃ የሚያጠናክር ሌላ አካል አለ፡፡ ከእሱ ሙሉ መረጃውን መውሰድ ትችላለህ፡፡ እንዲሁ ከምታዘባቸው ሁኔታዎች አንጻር ግን በመቀሌ ልክ በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች መሠረተ ልማትን ወደ ቀድሞ ተግባር የመመለሱ ሥራ በፍጥነት እየሄደ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ችግርም አለ፡፡ በእኔ እምነት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ክልሉን ወደነበረበት ለመመለስ እየሠራ ያለው ሥራ አመርቂ አይደለም፡፡ በጣም ብዙ የአመራር ችግር ነው ያለው፡፡ ፌዴራል መንግሥት እያደረገ ያለው መጠነ-ሰፊ ድጋፍ እና ዓለም ዐቀፍ ግብረ-ሰናይ ደርጅቶች እያደረጉ ያሉት ድጋፍ እንዲሁ በግለሰቦችና በተደራጁ ቡድኖች እጅ እየገባ መልሶ ክልሉ የትርምስ ቀጠና እንዳይሆን ጉዳዩን በፍጥነት ገምግሞ የእርማት እርምጃዎችን መውሰድ አለበት ባይ ነኝ፡፡

ሲራራ፡- መሠረተ ልማቱ ወደ ቀደመ ይዞታው እንዳይመለስ ያደረገው መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? የድጋፉ ማነስ ነው ወይስ የሚቀርበውን ድጋፍ በአግባቡ የመጠቀም ችግር? ወይስ ሌላ ምክንያት አለ?

አቶ አታክልቲ፡- የመጀመሪያ እና መሠረታዊ ጉዳይ በአካባቢዎቹ አስተማማኝ ሰላም አለመኖሩ ነው፡፡ አሁንም አልፎ አልፎ የሚታዩ ግጭቶች አሉ፡፡ እዚህም እዚያም ግጭቶች የሚታዩባቸው 3 እና 4 ወረዳዎች አሉ፡፡ እንዳልኩት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ያለው የሥራ ተነሳሽነት፣ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለው ዝግጁነት እና የአቅም ችግሮች አሉ፡፡ በሁሉም የትግራይ አካባቢ የጸጥታ ችግር አለ ማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ለይቶ በእነሱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ እንዲማረርና ከመንግሥት እየተነጠለ እንዳይሄድ ማድረግ የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ አስፈሪ የሆነ ረኀብ እየመጣ ስለሆነ ለእሱም ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ መገምገም ይኖርበታል፡፡ ችግሮች ከአሁኑ ተገምግመው መልክ ካልያዙ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሊወጡ ይችላሉ፡፡

መሠረተ ልማቱን ለማሟላት ፍላጎት ቢኖርም እንኳ የአቅም እጥረት ይገጥማል፡፡ የተጎዱ የመሠረተ ልማቶችን መልሶ ማቋቋም እጅግ በርካታ አቅም ይጠይቃል፡፡ ወደ መሃል ትግራይ ሄደን ካየን የመብራት እና የስልክ ሁሉም የመሠረተ ልማቶች የወደሙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ግጭቱ በራሱ የመሠረተ ልማቶችን ለማውደም የተደረገ እስኪመስል ድረስ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ውድመት ደርሷል፡፡ ስለሆነም ጊዜያዊ አስተዳደሩም ከመቀሌም አለፍ ብሎ መላውን ትግራይ ማየት መቻል አለበት፡፡ መቀሌ በጣም የተሻለ ሁኔታ አለ፡፡ እሱን ለራሱ ለሚመለከተው አካል ትቶ በሌላው የትግራይ አካባቢ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ ከጊዜያዊ መስተዳደሩ ጋር ሆነን ስንገመግምም አሁን ያለው ነገር አግባብ እንዳልሆነ እና ትግራይ ማለት መቀሌ ብቻ ማለት እንዳልሆነ አይተናል፡፡ ከመቀሌ ውጭ ያለውም የትግራይ ማኅበረሰብ ንጹሕ ውሃ እና መብራት ማግኘት እንዳለበት ተነጋግረናል፡፡ በሌላው አካባቢ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት ያለው ችግር አንድ ከውስጥ የሚመነጭ ሲሆን ሌላው ደግሞ በአካባቢዎቹ ላይ አስተማማኝ ሰላም ካለመኖሩ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ሲራራ፡- በትግራይ ክልል በግጭቱ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ የሚሆን የዓይነትም ሆነ የገንዘብ ድጋፎች ሲደረጉ ይታያል፡፡ በሌላ መልኩ ድጋፍ በትክክል ለሚገባው ሰው እየደረሰ እንዳልሆነ ሲገለጽ ይደመጣል፡፡ በትክክል ያለው ሁኔታ ምንድን ነው?

አቶ አታክልቲ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ክልሎች፣ የውጭ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የተለያዩ ድጋፎችን ለክልሉ ጊዜያዊ መንግሥት እያደረጉ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ይህ የሚደረገው ድጋፍ በትክክል ለሚፈለገው አካል በትክክል እየደረሰ ነው እየደረሰ አይደለም የሚለው ጉዳይ በአግባቡ መታየት እና መፈተሽ ያለበት ነው፡፡ በጣም ብዙ ችግር አለ፡፡ በዚህ ሰዓት በጣም ብዙ የተራበ እና የተቸገረ ሰው አለ፡፡ ለዚህ ሕዝብ የሚደረገው ድጋፍ ከዘገየ የሚፈጠረው ነገር ከባድ ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት እየተለያዩ እና በሕዝቡ ዘንድ ምሬት እየሰፈነ እንዳይሄድ ችግሩን ከስር ከስሩ መፍታት ይገባል፡፡

ሲራራ፡– በጄነራል ዮሐንስ የሚመራው የኮምንድ ፖስት እና ጊዜያዊ እስተዳደሩ መካከል የተፈጠረ የሥልጣን (የሥራ ኀላፊነት) መደራረብ እንዳለ ይሰማል፡፡ ይህም በእርስዎ ላይ ቅሬታ ፈጥሯል የሚባል ነገር አለ፡፡ በተጨባጭ ያለው ሁኔታ ምንድን ነው?

አቶ አታክልቲ፡- በንድፈ ሐሳብ ደረጃ በሁለቱ ኀይሎች የሥራ ኀላፊነት ላይ የሚቀላቀል ነገር የለም፡፡ በተግባር ግን ሁለቱም እየሠሩ ያሉት የማስተዳደር ሥራ ነው፡፡ ሆኖም ኮማንድ ፖስቱ የሥራ ኀላፊነቱን በአግባቡ ያውቃል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሥራውን ረስቷል የሚል ሐሳብ ነው ያለኝ በእኔ በኩል፡፡ ከእሱ የሚጠበቁ ኀላፊነቶችንም ሲወጣ እምብዛም አላይም፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ሲቪል ሰርቫንቱን ወደ ማባረር መሬት ወደ መሸንሸን የገባበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደ መንግሥት የሚጠበቅበትን ተግባርና ኀላፊነት እንዳይወጣ እንቅፋት ሆኖበታል ብየ አምናለሁ፡፡ ራሱ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በችግር የተተበተበ መሆኑ ሳይዘነጋ ማለቴ ነው፡፡ ለማንኛውም ደጋግሜ እንዳልኩት ትግራይ ውስጥ ያለው ነገር ምን ያህል በተቀመጠለት አቅጣጫ እየሄደ ነው የሚለውን ጉዳይ ፌዴራል መንግሥቱ ራሱ ጊዜ ሳይሰጥ መገምገም ይገበዋል፡፡

ሲራራ፡– በምታደርጉት ግምገማ ላይ የኮማድ ፖስቱን የሥራ እንቅስቃሴ ምን ያህል ትገመግሙ ነበር?

አቶ አታክልቲ፡- የኮማንድ ፖስቱን የሥራ እንቅስቃሴ ገምግመን አናውቅም፡፡ የገመገምነው የመቀሌን (እንደ ዞን) የ100 ቀን የሥራ አፈጻጸምን ነው፡፡ መቀሌም የራሱ የሆነ ኮማንድ ፖስት አለው፡፡ ስንገመግም ግምገማችን ትኩረት የሚያደርገው የመሠረተ ልማት ሥራ ማስጀመር እና አዲስ አገልግሎትን መስጠት የሚሉ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ በግምገማችንም መሠረት ልማቱም እርዳታውም ለምን መቀሌ ከተማ ላይ ብቻ ይሆናል በሚል ግምገማ አድርገናል፡፡ ትግራይ ማለት መቀሌ ብቻ አይደለም፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋንንም ሆነ እንግዳ ሲመጣ እንዲያይ የሚደረገው ግን መቀሌን ብቻ ነው፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም በሚል ገምግመናል፡፡ አሁንም መታረም ያለበት ነገር ነው፡፡ ትግራይ መቀሌ ብቻ አይደለችም፡፡

ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመበት ጊዜ እስካሁን ድረስ ዕቅድ ከማቅረብ የዘለለ ሥራ የገመገመበት ጊዜ የለም፡፡ ነገር ግን የኮማንድ ፖስት ሰብሳቢው እስከታችኛው የወረዳ መዋቅር ድረስ የአስተዳደር ሥራዎችን ሲሠራ ነው የሚስተዋለው፡፡ ከሰላም ጸጥታ ጋር የሚያያዙ ከወታደራዊ ጉዳዮች ጋር የሚያያዙ በርካታ ሥራዎች ቢኖሩም በዚያ ሥራ ላይ ትኩረት አድርገው ሲሠሩ አይታይም፡፡

ሲራራ፡- ቀደም ሲል ኮማንድ ፖስቱ የመሬት ሽንሸና ውስጥ እየተሳተፈ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ጉዳዩን በዝርዝር ቢያስረዱን?

አቶ አታክልቲ፡- ከእኔ ጋርም ለተፈጠረው ግጭት ዋናው ምክንያት ይኸው ጉዳይ ነው፡፡  በከተማው ትምህርት ለማስጀመር እንቅስቃሴ እያደረግን ነበር፡፡ 16 ትምህርት ቤቶች በተፈናቃዮች ተሞልተዋል፡፡ ትምህርት ለማስጀመር ተፈናቃዮቹን ለማስወጣት ተቀያሪ ቦታ ማግኘት ነበረብን፡፡ እነዚህን ቦታዎች ለማየት ስንዘዋወር አንድ ቦታ ላይ ግንባታ ሲከናወን አገኘን፡፡ ሥራውን አስቁመን በማን ፈቃድ ነው የምትገነቡት? ስንል ኮማንድ ፖስቱ ነው የፈቀደልን የሚል ምላሽ አገኘን፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ቦታ የመሸንሸን፣ ቦታ የመስጠት፣ ግንባታ ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን የለውም ማቆም አለባችሁ ስንላቸው፣ ወደ ጀነራል ዮሐንስ ስልክ የመደወል፣ የሚመለከታቸውን የወረዳ እና የክፍለ ከተማ ባለድርሻ አካላትን የማሰር ሁኔታዎች  ታይተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የተፈጠረው ብዙ ዝርዝር ጉዳይ ስለሆነ ልተወው፡፡ ብቻ ይህንና ይህን የመሳሰሉ በከፍተኛ አመራሮችና በጥገኛ ባለሀብቶች መሀከል ያሉ አላስፈላጊ ግንኙነቶች እና ሌለችም በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ይህ እንግዲህ አንዱ ማሳያ ነው እንጂ ከዚህም በላይ ብዙ አስቀያሚ ነገሮች አሉ፡፡

ትግራይ ካለችበት ሁኔታ እና ሕዝቡ ከሚጠብቀው ጉዳይ አንጻር እንዲህ ዓይነቱን ነገር ማውራቱ ብዙም ጠቃሚ ነገር አይደለም፡፡ በጥቅሉ ግን ኮማንድ ፖስቱ ከእርሱ የሚጠበቀውን ነገር እየሠራ አይደለም የሚለውን ጉዳይ መያዝ ተገቢ ነው፡፡

ሲራራ፡- ቀደም ሲል ነክተውት  አልፈዋል፡፡ ለትግራይ ክልል ከተለያዩ አካላት የሚላከው ድጋፍ ለትክክለኛው አካል እየደረሰ አይደለም የሚሉ አስተያየቶች ከተለያዩ ወገኖች ይሰማል፡፡ በዚያ አካባቢ ያለው ሁኔታ ምንድን ነው?

አቶ አታክልቲ፡- ለ4.9 ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ ተደራሽ ተደርጓል ተብሏል፡፡ ድጋፉ እውነት ተሰጥቶ ከሆነ ለምን ሰው በረኀብ ይሞታል? ይኼን ያህል ኩንታል እያልኩኝ በቁጥር ማስቀመጥ ባልችልም፣ ይኼን ያህል ሰው ድጋፍ ያስፈልገዋል ተብሎ ተጠየቀ፤ በተጠየቀው መሠረት ከዓለም ዐቀፍ ተቋማት፣ ከተለያዩ ክልሎች ድጋፎች መጥተዋል፡፡ ችግሩ ድጋፍ ካለማግኘት ነው ወይስ ደጋፉን በትክክል ለሚፈለገው አካል ካለማዳረስ ነው? የሚለው በሚገባ መታየት አለበት፡፡ እኔ በግሌ በየቀኑ ድጋፎች እና ስጦታዎች እንደሚመጡ አውቃለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በሌላ በኩል ሰው በረኀብ ሊሞት ነው የሚለውን ነገር ስትሰማ ጥያቄ ማንሳት አለብህ፡፡ ይህን ለመጠየቅ የግድ አመራር መሆንን አይጠይቅም፡፡ ከድጋፉ ባለፈ እስካሁን ድረስ ሥራ ማስኬጃ ተብሎ አንድ በጀት አልተለቀቀም፡፡ ነገር ግን ከ200 ሚሊዮን በላይ ብር ከአንድ ክልል ብቻ መገኘቱን ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ እየተሰበሰበ ያለው ድጋፍ እና እርዳታ ወደ የት እየገባ ነው የሚለውን የሚመለከተው አካል በአግባቡ ማየት እና መመርመር እንዳለበት ይሰማኛል፡፡

ሲራራ፡- በእርስዎ እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል የተፈጠረው ነገር ምንድን ነው? ከሥራዎ ላይ እንዲነሱ ያደረገዎት ምክንያትስ ምንድን ነው?

አቶ አታክልቲ፡- ነገሩ የተፈጠረው የጀመረው የመቶ ቀናት ግምገማ ስናደርግ ነው፡፡ ከመቀሌ ውጪ ባለው አካባቢ እንብዛም ሥራዎች እየተሠሩ አለመሆናቸውን መቀሌ ላይ ያለው ሥራም የከተማው ካቢኔ፣  ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ባለው አካል ጥረት የመጣ እንጂ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አጋዥ እንዳልሆነ ገምግመናል፡፡ ለዚህም በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ በመመሪያዎች እና በአሠራር አለማገዝ ሁኔታዎች አሉ ለምሳሌ ትምህርት እንዳንጀምር ካሪኩለም ከክልሉ መውረድ አለበት፡፡ ትምህርት መቼ ይጀምራል መቼ ይጠናቀቃል የሚለው ነገር ተለይቶ መቀመጥ አለበት፡፡ የገቢዎች ሥራ ለማስጀመር ከጥቅምት እስከ ጥር ያለው ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችል መመሪያ የሚሰጠው ከክልሉ ነው፡፡ ምሕረት ተደርጓል ከተባለም፣ ያለ ቅጣት ነው የሚከፍሉት ከተባለ ውሳኔ የሚሰጠው ከክልሉ መንግሥት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ መመሪያዎች በፍጥነት መልስ እያገኙ አልነበረም፡፡ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት የበጀት ጥያቄ በፍጥነት ምላሽ እያገኘ አይደለም፡፡

ሌላው ከተማውን ስንረከብ ከባድ መኪኖችና ተሽከርካሪዎች ከከተማ እንዳይወጡ ሁሉም ኬላዎች እንዲዘጉ ወስነን ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ግለሰብ መውጫ እየሰጠ ማሽኖችን ከከተማ ሲያወጣ እንደነበር ተደርሶበታል፡፡ ይህ ግለሰብ የጠፉ ተሽከርካሪዎችን የሚያሰባስበው ግብረ ኀይል ኀላፊ እና ከውጪ የመጣ ደላላ ነው፡፡ ይህ ግለሰብ ለእያንዳንዱ ማሽነሪ 60 ሺሕ ብር እየተቀበለ መውጫ እንደሚሰጥ እና የሚያገኘውን ብር ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ጋር እንደሚካፈል ፌዴራል ፖሊስም በምርመራ የደረሰበት ጉዳይ ነው፡፡

በአንድ በኩል ሕዝብ ተርቧል፡፡ በሌላ በኩል ጊዜያዊ መንግሥቱን  ተጠቅሞ ሀብት የሚሰበስብ አካል ካለ ተጣርቶ በሕግ መጠየቅ አለበት የሚል አቋም ነበረን፡፡ ይህ ነገር ሁኔታው እንዲካረር አድርጎታል፡፡ የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢም ሆነ የጸጥታ ዘርፍ ኀላፊው ይህን ማድረግ  አልቻሉም፡፡ ነገር ግን ብር የሰጠውም የተቀበለውም ሰው ይታወቃል በአካልም አሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት አግባብ አይደለም፡፡

በመጨረሻ ቀደም ብዬ ያነሳሁትን የመሬት ጉዳይ ስናስቆም ካስቆሙት መካከል አቶ ከበደ አሰፋ  የሚባሉ ሰው ጄነራሉ ለምን ቦታ ሸንሽኖ ይሰጣል የሚሉ ቅሬታዎች በከፍተኛ ሁኔታ ያሰሙ ነበር፡፡ ይህን ሰው በኮማንድ ፖስት እንዲባረር ወስነናል የሚል ሐሳብ ሲመጣ ይህን አልቀበልም አልኩ፡፡ እኔ ነኝ የሾምኩት ይህ ሰው መባረርም ካለበት ችግሩ ታውቆ ተገምግሞ ነው መሆን ያለበት  ብያለሁ፡፡ እውነት ስላወጣ የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት አይዘረፍም ስላለ መባረር የለበትም ስል፣ የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች ይደርሱብኝ ጀመር፡፡ እኔም የሚያሠራ ሁኔታ ከሌለ እለቃለሁ ብልኩኝ ይህን ስል እንዳይቀድመን በሚል የእኔን መልቀቂያ ሳይቀበሉ ለቀሃል ለነበረህ ጊዜ እናመሰግናለን የሚል ደብዳቤ ሰጡኝ፡፡ በድምሩ ሥራዎችን የሚያሠራ ሁኔታ ስለሌለ ነው እኔ የለቀቀኩት፡፡

ሲራራ፡- ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በየዕለቱ ግጭት አለ፤ የሰው ሕይወትም ይጠፋል፡፡ ዘላቂ መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?

አቶ አታክልቲ፡- አንደኛውና ዋናው ነገር በመንግሥትና በሕዝቡ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ ሕዝቡ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ይህ መንግሥት የእኔ መንግሥት ነው፣ ያስብልኛል፣ ከጎኔ ይቆማል ማለት የሚችለው ሕዝቡ አገልግሎት ሲያገኝ ነው፡፡ ከፌዴራል መንግሥት የተመደበው እና በዓለም ዐቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በኩል የሚቀርበው ድጋፍ በአግባቡ ለሕዝብ ሊደርስ ይገባል፡፡ መንግሥትንና ሕዝብን የሚያቃቅር ተግባር መፈፀም የለበትም፡፡ ሁሉንም የክልሉን ሕዝብ በእኩል ዓይን ሀብታም ድሃ ሳይሉ፣ የዚህ አካባቢ ወይም የዚያ ሳይሉ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማገልገል ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ፌዴራል መንግሥትም በጣም የተጠናከረ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መሥራት ይገባዋል፡፡ ሕዝቡ ኑሮውን እየተወ ጫካ እንዲገባ በሚቀሰቅሱት ኀይሎች እንዳይታለልና ሰለባ እንዳይሆን በሕዝብ ላይ በደል የፈፀሙ የመከላከያም ይሁን ሌሎች አካላት ላይ ተጠያቂነትን ማስፈን ያስፈልጋል፡፡

ትግራይ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ስለደረሰባት ልዩ የሆነ ብሔራዊ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ መርሐ ግብር መዘርጋት ያስፈልጋልም ብዬ አምናለሁ፡፡ ትግራይ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ፣ በአጠቃላይም በአገር ደረጃ ሁከት የሚፈጥሩ ኀይሎች ዕድል እንዳያገኙ ማደረግ የሚቻለው አካባቢውንና ሕዝቡን መልሶ ማቋቋም ሲቻል ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ጦርነት አንገፍግፎታል፡፡ ብዙ መከራም አይቷል፡፡ ሊደገፍ የሚገባው ሕዝብ ነው፡፡

 

April 10, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *