“ለአማራና ትግራይ ሕዝቦች ዘላቂ ሰላም ሲባል የወልቃይትና አላማጣ ጉዳይ መፈታት አለበት” | ዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ
እንግዳ

“ለአማራና ትግራይ ሕዝቦች ዘላቂ ሰላም ሲባል የወልቃይትና አላማጣ ጉዳይ መፈታት አለበት” | ዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ

እንደሚያውቁት ኢትዮጵያ አሁን እየተከተለች ያለችው የብሔር ፌዴራሊዝም የክርክር አውድማ ነው፡፡ የኢሕአዴግ አመራሮች ጨምሮ አንዳንድ ምሁራንና ፖለቲከኞች በብሔሮችን መብት ለማስጠበቅና የአገሪቱን ህልውና ለማቆየት ከዚህ የተሻለ አማራጭ የለም ይላሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ይህ ፌዴራላዊ አወቃቀር በሕዝቦች መሀከል ልዩነትንና ጥርጣሬን የሚፈጥርና ውሎ አድሮ ኢትዮጵያን ህልውና የሚፈትን ነው ይላሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

መቼም እንደተባለው ይህ ጉዳይ በአገራችንም በሌሎች አገሮችም አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር የሚባለው መርህ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በተለይ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት  ማግስት ጀምሮ የገነነ አስተሳሰብ ነው፡፡ ብዙ ክርክር የተደረገበትና እየተደረገበትም ያለ፣ በጣም በርካታ መጻሕፍትና ጥናታዊ ጽሑፎችም የተጻፉበት ጉዳይ ነው፡፡ በሊብራል አገሮች አኳያ ያለውን ሁኔታ ያየን እንደሆነ፣ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ሲባል ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ ግለሰቦችም የራሳቸውን፣ ማለትም የመሰላቸውን አመከላከት የመያዝ፣ የሚፈልጉትን የአኗኗር ዘይቤ የመምረጥ፣ በመረጡት መሪ የመተዳደር ወዘተ… ሁኔታን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ግለሰቦች ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ የሚፈልጉትን መሪ የመምረጥ፣ የሚፈልጉትን የአኗኗር ዘይቤ፣ ማለትም ቢፈልጉ በትዳር፣ ባይፈልጉ ያለትዳር፤ ቢፈልጉ ልጅ መውለድ፣ ባይፈልጉ ያለመውለድ እና ውርጃንም ጨምሮ ብቻ የራሳቸውን ሁኔታ ራሳቸው ያለ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት ተጽዕኖ የሚመርጡበት አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ ማለት ጉዳዩ የቡድን መብትን አይመለከትም ማለት አይደለም፡፡ የቡድን መብትንም ይመለከታል፡፡ ቡድን ሲባል እንግዲህ የሴቶችን፣ የጥቁሮችን፣ የሙያ ማኅበራትን፣ የሠራተኞችን፣ የብሔሮችን፣ የሃይማኖት ተከታዮች ወይም የሃይማኖት ተቋማት መብትን ወዘተ… ሁሉ ያካትታል፡፡

እንግዲህ በእኛ አገር ያየነው እንደሆነ ከሌሎች የቡድን መብቶች በላይ የብሔረሰቦች መብት ነው ያለ ልክ ተለጥጦ ሲራገብ የምናየው፡፡ ይህም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ፖለቲከኞች የብሔረሰቦችን ጉዳይ እንደ ዓይነተኛ ማደራጀ መሣሪያ ስለሚጠቀሙበት ነው፡፡ ተጠቃህ፣ ተዋረድክ፣ ባህልህ፣ ቋንቋህና ማንነትህ እንዲህና እንዲያ ሆነብህ ብሎ ስሜት ኮርኳሪ ቃላትን እየተጠቀሙ በመቀስቀስ በቀላሉ ብዙ ደጋፊ ማግኘት ይቻላል፤ ሲቻልም አይተናል፡፡ በተለይ እንደኛ አገር ባለ የሚበዛው ሕዝብ ያልተማረ በሚሆንበት ሁኔታ ደግሞ የሰዎችን ስሜት  በቀላሉ ማግለብለብ ይቻላል፤ ተችሎም አይተነዋል፡፡ ሕወሓትን ጨምሮ ብዙዎቹ የብሔረሰብ ድርጅቶች ያደረጉት ይህንኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ቁምነገር የጎሳዎችና ብሔረሰቦች መብት መከበሩ በጣም አግባብ ያለው ነገር መሆኑ ነው፡፡ ትልቁ ፈተና እና ውሎ አድሮም የምንወዳትን አገራችንን ህልውና የሚፈታተነው ነገር ግን የጎሳና የብሔረሰብ አጀንዳ የፖለቲካ ማደራጃ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ የጎሳና የብሔረሰብ አጀንዳ ከፖለቲካ ወጥቶ በራሱ መንገድ መልክ ካልያዘ ግጭት አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ የመሬት መገፋፋት ይመጣል፣ በባህል አከባበር ረገድ ቅራኔ ይፈጠራል፣ አላስፈላጊ ሽኩቻና ውድድር ይነግሣል፣ በኢኮኖሚው መስክም ቢሆን ጤናማ ግንኙነት አይኖርም፡፡ ከዚህ መለስ እኔ መሬት ነው፤ ከዚያ መለስ የአንተ ነው ተብሎ አጥር ከተበጀ በኋላ በምን መልኩ ነው ኢንቨስትመንት የሚሰፋፋው? እንዴት ነው ኢንዱስትሪ ሊቋቋምና ሊገነባ የሚችለው? ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው፡፡

እርግጥ ነው እንዳልኩት የማናቸውም ጎሳዎችና ብሔረሰቦች ባህልና ቋንቋ መከበሩ በጎ ነው፡፡ የሚደገፍም ነው፡፡ እያንዳንዱ ጎሳና ብሔረሰብ የየራሱን በረት አጥሮ ይቀመጥ ማለት ግን እጅግ አደገኛ ነው፡፡ መቼም እንደዚህ ስንል “መቼ እንደሱ ተባለ” የሚሉ አይጠፉም፡፡ ለእኔ ግን አሁን በማየውና በምታዘበው መልኩ ከዚህ የተለየ አይታየኝም፡፡ የሚታየኝ አጥርና ክልል ነው፡፡ የክልሉ አጥር ወደ መሬት ከመውረዱም በፊት በብዙ ወገኖቻችን ጭንቅላት ውስጥ ይታየኛል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በክፉውም በደጉም አብረን ያሳለፍን፣ በመከራ ጊዜዎቻችን ሁሉ ውዲቱን አገራችንን ለመጠበቅ አብረን በጋራ ወጥተን አብረን በአንድ ጉድጓድ የተቀበርን ሕዝብ ነን፡፡ አንዳንዶች ይህን ውድ እና በምንም የማይተመን ነገር ሲያቃልሉት ባየሁ ጊዜ ሁሉ ልቤ ይደማል፡፡ እኔ አገራችን በጠላት ዘመን ምን እንደደረሰባት ከሚያውቁት ጥቂት ኢትዮጵያዊያን አንዱ ነኝ፡፡ በጠላት ቀንበር የነበረውን ግፍና መከራ አውቀዋለሁ፤ ቀምሸዋለሁ፡፡ ወገኖቻችን በገዛ አገራቸው ስደተኞች ሆነው መሄጃ ሲያጡና ሲቅበዘበዙ አስታውሳለሁ፡፡ በዚያ የግፍና የለቅሶ ዘመን ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ እርስ በርሱ እንዴት በስስትና በለቅሶ ይተያይ እንደነበር አልረሳውምና አሁን ያለንበትን ሁኔታ ሳይ እጅጉን ያሳዝነኛል፤ ያስለቅሰኛል፡፡

በጎሳ ወይም በብሔረሰባዊ ማንነት መደራጀት በሕግ መከልከል አለበት ብለው ያምናሉ?

በእውነቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጎሳና በብሔረሰብ ስም እንዲደራጁ መፍቀድ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ዛሬ ሁሉም ነገር ሰላም ሊመስለን ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም ውሎ አድሮ መዘዝ ይዞ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ እንደምታውቀው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀዳሚ ዓላማ ሥልጣን መያዝ ነው፡፡ ሥልጣን ለመያዝ ደግሞ ሕዝቡን ማሳመንና መቀስቀስ ያስፈልጋል፤ ይገባልም፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ በጎሳ የተደራጁ ፓርቲዎች የሕዝቡን ስሜት በቀላሉ ለመኮርኮርና ከጎናቸው ለማሰለፍ በአደባባይም በስውርም እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ተጠቃህ፣ ተዋረድክ፣ እነ እከሌ መሬትክን ወሰዱብህ፣ ማንነትህን ነጠቁህ ወዘተ… ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለ ኢኮኖሚ፣ ስለ ፖለቲካ እና ስለ ሶሻል ችግሮች እያወሱ እና እነሱን ለመፍታት ስላዘጋጇቸው መርሐ-ግብሮች የሚቀሰቅሱት እምብዛም ናቸው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ምልክት አይተነዋል፤ እያየነውም ነው፡፡ የፖለቲካ ክርክሮች በአመዛኙ ከሐሳብ ይልቅ በጎሳ ላይ እየተመሠረቱ ለዘመናት አብረው በኖሩ ኢትዮጵያዊያን መካከልም ልዩነትና ጥርጣሬ እየፈጠሩ ናቸው፡፡ በበኩሌ ይህ ነገር ከወዲሁ መፍትሔ ካልተበጀለት አደጋ ይዞ እንደሚመጣ ነው የሚታየኝ፡፡ ስጋቴ ስጋት ብቻ ሆኖ ቢቀር ደስ ይለኛል፡፡ ግን አይመስለኝም፡፡

እኔ እንደ አንድ አገር ወደድ ዜጋ፣ ይልቁንም እንደ አንድ ሰፊ ተሞክሮ እንዳለው ሽማግሌ ኢትዮጵያዊያን ወገኖችን የምመክረው በጎሳና በብሔረሰብ ስም የሚደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ከጥቅማች ይለቅ ጉዳታቸው የትየለሌ መሆኑን ነው፡፡ ልክ በሃይማኖት ስም የፖለቲካ ድርጅት ማደረጀት ክልክል እንደሆነው ሁሉ በጎሳና በብሔረሰብ ስምም የፖለቲካ ድርጅት ማደራጀት በሕግ መከልከል አለበት ባይ ነኝ፡፡ ይህ ማለት የጎሳዎችና የብሔረሰቦች ባህል፣ ቋንቋና ልዩ ልዩ ነገሮች አይከበሩም፣ አይበለጽጉም ማለት አይደለም፡፡ ማንም ሰው ወይም ጎሳ የራሱን ባህል እና ቋንቋ የማዳበርና የማሳደግ መብቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡ በእሱ ላይ ብዥታ የለም፡፡ እሳት ሆኖ የሚለበልበን የጎሳና ብሔረሰብ ማንነት ከፖለቲካ ጋር ሲያያዝ ነው፡፡ እሱንም እያየነው ነው፡፡ ውሎ አድሮም ውዲቱን አገራችንን አብዝቶ መፈተኑ አይቀሬ ነው፡፡

የብሔረሰብ ፖለቲካ አንድ ጊዜ ከተቀሰቀሰ ባለበት ሁኔታ በዴሞክራሲና በሕግ እየተገራ ይሄዳል እንጅ አይመለስም፤ አሁን ያለውን ፌዴራላዊ አወቃቀር መንካትም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፤ አንድ ጊዜ በብሔረሰብ ስም መደራጀት የሚሰጠውን ጥቅም የቀመሱ ልኂቃን ይህንን መሪ የማደራጃ መሣሪያ አሳልፈው ከሚሰጡ ቢሞቱ ይመርጣሉና የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እርስዎ አሁን ያለውን የብሔረሰብ ፌዴራላዊ ሥርዓት መቀየር አይከብድም ይላሉ?

ፈጽሞ ከባድ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ በእኔ አስተያየት የየራሳቸውን ጠባብ ጥቅም ለማስጠበቅ እንደ ዋነኛ መሣሪያ ከሚጠቀሙት ፖለቲከኞች ውጪ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ይህንን አስተሳሰብ አይፈልገውም፤ አይደግፈውምም፡፡ እኔ የተወለድኩት ጀልዱ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ውስጥ በልዩ ልዩ የኀላፊነት ቦታዎች አገልግያለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ እንደነበሩት አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቼና እህቶቼ እኔም በሚንቀለቀል አገራዊ ስሜት አገሬን አገልግያለሁ፤ ተዘዋውሬም አይቻታለሁ፡፡ ሕዝቡን አውቀዋለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ሥራየ ብየ ከሰሜን እስከ ደቡብ እሄዳለሁ፤ ከወገኖቼ ጋር እገናኛለሁ፤ እወያያለሁ፡፡ እንደሚገባኝ ይህን አጀንዳ የሞት የሽት ጉዳይ አድርገው የሚያራምዱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ አንዳንዶች እውነትም አገርንና ሕዝብን ይጠቅማል ብለው ከምር የሚያስቡ ተቆርቋሪዎች ናቸው፡፡ የሚበዙት ግን  ያው ጥሩ ማደራጃ ስለሚቆጥሩት አምርረው ሲጮሁ ይታያል፡፡

መታወቅ ያለበት ይህ የእኛ መሬት ነው፣ ያኛው የእናንተ መሬት ነው የሚለው በኢትዮጵያዊያን መካከል አጥር የሚያጥር አስተሳሰብ ጊዜ ከተሰጠው ግን አደገኛ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አንዱን ተወላጅና ባለርስት ሌላውን መጤና ሁለተኛ ዜጋ የሚያደርግ አስተሳሰብ እጅግ ሲበዛ አደገኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እንኳን ነጻነቷን በልጆቿ መስዋዕትነት አስከብራ በኖረችው ኢትዮጵያ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ስር በነበሩት አገሮችም አይታይም፡፡ በእውነቱ አሁን የገባንበት በኢትዮጵያዊያን መካከል አጥር የሚያስቀምጥ አስተሳሰብ እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ በተለይ ከሞት ለተረፍነው እንደኔ ላሉት ኢትዮጵያን በመከራዋ ጊዜ ለሚያውቋት ልጆቿማ ሲበዛ የሚያስለቅስና የሚያሳቅቅ ሁኔታ ነው፡፡ በአንዳንድ ረገድ የሞቱት ታድለዋልም እላለሁ፡፡

እንደ አንድ አገር ወዳድ እና ረዥም የመንግሥታዊ ሥራ ተሞክሮ እንዳለው ኢትዮጵያዊ የዕድሜ  ባለጽጋ የኢሕአዴግን ከፍተኛ አመራሮች ይህ ነገር አይበጅም ብለው መክረው ወይም ሐሳብ ሰጥተው ያውቃሉ?

ብዙ ጊዜ ስጋቴን ገልጫለሁ፡፡ በእውነቱ ያለኝን አስተያየትና ስጋት ሳልገልጽ የቦዘንኩበት ጊዜ የለም፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ እንዳጠና፤ ይልቁንም በልዩ ልዩ በከፍተኛ መንግሥታዊ ኀላፊነት ቦታዎች እንደሠራ እና የአገሩ ጉዳይ እንደሚያንገበግበው ኢትዮጵያዊ፤ ከዚያም አልፎ እንደ ዕድሜ ባለፀጋ ሁልጊዜም የሚሰማኝንና ለአገሬ ይጠቅማል የምለው ከመግለጽ ወደኋላ ብየ አላውቅም፡፡ ወደፊትም ቢሆን በአገሬ ጉዳይ ወደኋላ የምልበት ምክንያት የለም፡፡

በእውነቱ የሆነ እንደሆነ ለኢሕአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተው ይህ ነገር አይበጅም ሳልል የቀረሁበት ጊዜ የለም፡፡ ኤርትራና የትግራይ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው፡፡ ግን በፖለቲከኞች ጥፋት እንዲለያይ ተደርጓል፡፡ ሕዝቡ ግን አሁንም ፖለቲከኞችን ወደጎን ብሎ ይጋባል፣ ይጠያየቃል፣ በሰርጉም፣ በለቅሶውም፣ በበዓሉም ይገናኛል፡፡ ግን ፖለቲከኞች በሕዝብ መሃል አሁንም ግንብ ለመሥራት እየሠሩ ነው፡፡ ሌላው ወደፊት ሊፈነዳ የሚችለው የወልቃይት ጉዳይ ነው፡፡ ታዝበህ እንደሆነ አላውቅም፣ የሽሬ አካባቢ ሰዎች የሚናገሩት ጎንደሬዎች የሚናገሩትን አማርኛ ነው፡፡ ምንም ልዩነት አታይም፡፡ ጎንደር አካባቢም በብዛት ትግርኛ ሲነገር ትሰማለህ፡፡ ዋግና የጁም እንዲሁ ነው፡፡ የሕወሓት መሪዎች በእነዚህ የኢትዮጵያ መሠረት በሆኑ ሕዝቦች መካከል የተከሉት ክፉ ነቀርሳ አለ፡፡ የወልቃይት ጉዳይ እነዚህን ለሺሕ ዘመናት ተዋልደውና ተጋምደው የኖሩ ሕዝቦች የሚያለያይ ክፉ ነቀርሳ ነው፡፡ ወልቃይት ዕድሜውን ሙሉ በበጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ስር የኖረ ነው፡፡ እሱን ወደ ትግራይ ክልል በመከለል ለትግራይ ውለታ ዋሉለት መስሏቸው ከሆነ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ተሳስተዋል፡፡ ከወንድሙ ከጎንደር ሕዝብ የሚያቀያይመውና የሚያጋጨው አደገኛ የቤት ሥራ ነው የሰጡት፡፡ በራያ በተለይም በአለማጣ ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው፡፡ ራያ አዘቦ ከትግራይ ውጪ የሆነበትን ጊዜ አላስታውስም፤ አላውቅም፡፡ አለማጣ አካባቢ ግን ለዘመናት የየጁ አካል ሆኖ የኖረ አካባቢ ነው፡፡

ይህን ስል ጎንደር የጎንደሬዎቹ ብቻ ይሁን፤ ትግራይም የትግሬዎቹ ብቻ ይሁን እያልኩ አይደለም፡፡ አልነበረምም፡፡ አሁንም ቢሆን ጎንደር ላይ ብዙ የትግራይ ተወላጆች አሉ፡፡ ትግራይ ላይም ብዙ ጎንደሬዎች አሉ፡፡ በሌላው እንዲሁ ነው፡፡ የእኔ ስጋት በክልል አጥር ሲታጠር መሬቱ የእኔ ብቻ ነው የሚል ስሜት ይፈጥራል፤ በዚህ ሒሳብ ደግሞ ወልቃይት ትግራይ ነው የሚል ነገር እጅግ ሲበዛ አደገኛ ነው፤ ይልቁንም አደጋው ለትግራይ ሕዝብ ነው የሚል ነው፡፡ እንደሚገባኝ የትግራይ ሕዝብ ከጎንደር ወንድሙ ጋር እንደ ጥንቱ በሰላምና በፍቅር መኖር ይፈልጋል፡፡ አብሮ መኖር፣ አብሮ ማደግ ነው ፍላጎቱ፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ የችግር ምንጭ ሆነው የሚታዩት ፖለቲከኞች ናቸው እንጅ በሕዝብ መካከል ምንም ዓይነት ችግር የለም፡፡

እንደሚያውቁት ወልቃይት አካባቢ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ይኖራሉ፡፡ የትግራይ ክልል መንግሥስት ያሰፈራቸው በርካታ የቀድሞ ታጋዮችም አሉ፡፡ ወልቃይት ወደ ጎንደር ይመለስ ቢባል እነዚህ ሰዎች እሽ የሚሉ ይመስሉዎታል?

በእኔ በኩል የሚከብድ ነገር አይታየኝም፡፡ ከፍ ብየ እንደገለጽኩት በዚህ አካባቢ ትግርኛም አማርኛም በደንብ ይነገራል፡፡ እንዳልኩት በሽሬና አካባቢው የሚነገረው አማርኛ በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች ከሚነገረው አማርኛ በእጅጉ ይለያል፡፡ ጎንደር ውስጥ ከሚነገረው አማርኛ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህም ቅርበት የፈጠረው ነገር ነው፡፡ ከጎንደር ሽሬ እና ከሽሬ ጎንደር ያለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከጎንደር ደብረ ታቦርና ከደብረ ታቦር ጎንደር ወይም ከባሕር ዳር ጎንደርና ከጎንደር ባሕር ዳር ካለው እንቅስቃሴ ይልቃል፡፡ ይህን ሁሉ የምለው ቋንቋ ችግር አለመሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በሁለቱ ቋንቋዎች መግባባትም፣ መሥራትም፣ መማርም ይቻላል፡፡ እርግጥ ሁለት ቋንቋዎች የሚባሉም አይደሉም፡፡ ፊደላቸውም፣ የአጻጻፍ ሁኔታቸው አንድና እጅግ ተመሳሳይ የሆነ የአንድ የግዕዝ ቋንቋ ልጆች ናቸውና፡፡

ነገሩ “ከልብ ካዘኑ እምባ አይገድም” እንደሚባለው ነው፡፡ በእውነት ለጎንደርና ለትግራይ ሕዝብ፣ ከዚያም አልፎ ለትግራይና ለወሎ ሕዝብ አንድነትና ወንድማማችነት የምናስብ ከሆነ ነገሩ ከባድ አይደለም፡፡ እኔ በኩል ወልቃይትና አለማጣ ቀድሞ ወደ ነበሩበት ጠቅላይ ግዛቶች መመለሳቸው ወሳኝ ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ የትግራይ ሕዝብ ቢጠየቅ ከዚህ የተለየ ነገር አይልም፡፡ ችግር ላይ የጣለን ፖለቲከኞች ያመጡብን ጣጣ ነው፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራስ ሁኔታ? በቅርብ ጊዜ ግንኙነታቸው የሚሻሻልበት መንገድ ይታዩዎታል?

በእውነቱ አገራችን በዚያ አካባቢ የከፈለችው የሰብአዊና የማቴሪያል ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የውጭ ኀይሎች ከፍተኛ ተሳትፎ ያለበት መሆኑ ባይካድም ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ጀምሮ የእኛም ድክመት ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ስህተቶች ተሠርተዋል፡፡ በዝርዝር ጽፌዋለሁ፡፡ ወዳጀና ወንድሜ አምባሳደር ዘውዴ ረታም በሚያረካ ሁኔታ አስቀምጦታል፡፡ ብዙ ተዋናዮች ነበሩ፡፡ በእኛም በኩል ብዙ ስህተቶች ተሠርተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በወታደራዊው የአገዛዝ ሥርዓት የተፈፀመው በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ የሚያሳዝነው የኤርትራ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የራሳቸውን አገር ከመሠረቱም በኋላ ጦርነቱ አልቀረልንም፡፡ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙ ኢትዮጵያዊያንም ኤርትራዊያንም የሆኑ ወገኖቻችንን አጥተናል፡፡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ረግፈዋል፡፡ አዝናለሁ፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖም ግን እነዚህ ሁለት አገሮች ተለያይተው ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጥንካሬ ከአንድነታቸው የሚመነጭ ነው፡፡ ጥንካሬያቸው ኅብረታቸው ነው፡፡ ስለሆነም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንም ኤርትራዊያንም በሰላሙ ጥረት ላይ ተስፋ ሳይቆርጡ እንዲገፉበት ያስፈልጋል፡፡ የሰላም ጥረቶች ረዥም ጊዜ ሊፈጁ ቢችሉም ውጤታቸውና ፍሬያቸው ያማረ ነው፡፡

(ከአዘጋጁ፡- ባልደረባችን አቤል ዋበላ ይህን ቃለ ምልልስ ከዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ ጋር ያደረገው በ2000 ዓ.ም. ነው፡፡)

December 13, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *