‹ዴማጎግሪ›፡- የተበላሸ ዴሞክራሲ | ሹምዬ ጌጡ (ዶ/ር)
እንወያይ

‹ዴማጎግሪ›፡- የተበላሸ ዴሞክራሲ | ሹምዬ ጌጡ (ዶ/ር)

የጥንት ግሪካውያን እምርታዊ የሥልጣኔ ዕድገት የዴሞክራሲን እሳቤ እና አስተዳደርን በመፍጠርና ለተቀረው ዓለም በማስተዋወቅ ቢጠቀስም፣ ግሪኮቹ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይ የበዙ ጥርጣሬዎች ነበሯቸው፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ሶቅራጥስ እና ፕሌቶ ያሉ የፍልስፍና ሊቃውንት ዴሞክራሲን አብዝተው ይጠሉ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ እነዚህ በዴሞክራሲ ላይ የተሰነዘሩ ጥርጣሬዎች እና የሚታዩ ድክመቶች በሰፊው ሲንፀባረቁ  በገሐድ እየተመለከትን ያለበት ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡ ለመሆኑ ዴሞክራሲ እንዴት ይጠላል? እንዴትስ ሊበላሸ እና ሊነቅዝ ይችላል? ይህን ጥያቄ ስንመልስ በቀጥታ ስለ ‹ዴማጎግሪ› (demagoguery) እንድናወራ እንገደዳለን፡፡

‹ዴማጎግሪ› እንደ አንድ የፖለቲካ እሳቤ መሠረታዊ የሆነ የርዕዮተ ዓለም እና የክርክር ሐሳብ ሕፀፅ (ጉድለት) ያለበት አመክኖአዊ ስህተቱም ከጤነኛ የፖለቲካ አካሄድ ጋር የማይታረቅ ሲሆን በፖለቲካ እሳቤው እና አተገባበሩም ከሕዝብኝነት ጋር እጅግ የሚመሳሰል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህም አለ በዚያ ‹ዴማጎግሪ› ከትክክለኛ የዴሞክራሲ መርህ እና ከትክክለኛ አመክንዮ ጋር የተፋታ መሆኑ በሕፀፅ የተሞላ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲን ለመገንባት የሚደረግን ሂደት አስቸጋሪ በማድረግ ይታወቃል፡፡ ‹ዴማጎግሪ›ን ከዴሞክራሲ ጋር ለይቶ ያለማየት ችግር እና በዲሞክራሲ ስም በ‹ዴማጎግሪ› የሚጫዎቱ ልኂቃን መብዛት ዴሞክራሲን እንደገና ደግመን ደጋግመን እንድንመረምረው እና እንድንጠራጠረው መንገድ ከፍች ሆኗል፡፡ ይህ በዴሞክራሲ ላይ የሚደረግ ፍተሻ እና ጥርጣሬ በ‹ዲማጎግሪ› እና በዴሞክራሲ መካከል ያለው ድንበር በግልጽ እስከሚለይ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ሶቅራጥስ እና ፕሌቶም ዴሞክራሲን እንዲጠሉ እና እንዲጠራጠሩ ያደረገው ምክንያት ይህ ሆኖ አልፏል፡፡ በአጭሩ ለመግለጽ ‹ዴማጎግሪ› የተበላሸ ዴሞክራሲ ማለት ነው፡፡

‹ዴማጎግሪ› በተፈጥሮው ስሜታዊነትን (ኢ-አመክኖአዊነትን)፣ ጭፍን ፍረጃን እንዲሁም እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን ባይነትን ይፈልጋል፡፡ በተጨማሪም እውነትን በመሸሽ (በመደበቅ)፤ ርካሽ ተወዳጅነትን እና የፖለቲካ ሥልጣንን ያለአግባብ ለማግኘት ብዙሃንን በጥላቻ እና በውሸት በማነሳሳት ድጋፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው (demagoguery is a political leadership who seeks support by appealing to the desires and prejudices of ordinary people rather than by using rational argument) በመሆኑም “ዴማጎግሪ” በአንድ አገር (የፖለቲካ ማኅበረሰብ) ውስጥ ሊኖር የሚችለው ለምን ብሎ የማይጠይቅ እና የማይመረምር (parochial) ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ሲፈጠር እና በራሱ መቆም ሳይችል እንደተፈለገው የሚነዳ መንጋ እንዲሁም ይህን አጋጣሚ የሚጠቀም ልኂቅ እስካለ ድረስ ብቻ ነው፡፡

በእርግጥ ‹ዲማጎግሪ› በብዙ መንገድ መተርጎም የሚችል ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ አንደኛው ዓይነት አተረጓጎም እንደሚያስረዳው ‹ዴማጎግሪ› የሚታዎቀው ስሜታዊነትን ብቻ ያለ ምክንያታዊነት በማራመድ (በማጉላት) ነው፡፡ ልኂቃን የራሳቸው ብቻ የሆነ ዕውቀት ያላቸው በማስመሰል እነሱ ብቻ የሚያውቁት ጉዳይ እንዳለ አድርገው በእኔ አውቅልሃለው አጉል ፈሊጥ አብዛኛውን ሕዝብ ስሜታዊ የሚያደርግ (ስሜታዊነት ብቻ የሚንፀባረቅበት) ፍፁም ሐሰት የሆነ ንግግር በመናገር እና ሕዝቡ በሚያንፀባርቀው ከፍተኛ የስሜታዊነት ምላሽ እና ድርጊት እንደ የእነሱ ሐሳብ ትክክለኛነት ማረጋገጫ ሊወስዱት እና ሊያረጋግጡ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ተቀባይነት ያለው እና ግልጽ የሆነ ማስረጃ (ምክንያት) በማምጣት ብዙሃኑን ከማሳመን እና እንዲደግፋቸው (እንዲከተላቸው) ከማድረግ ይልቅ የእነዚህ ግለሰቦች ሐሳብ የሚለካው (የሚመዘነው) ብዙሃኑን ምን ያህል ስሜታዊ አድርገዋል ወይም አናድደዋል ወይም ደግሞ አነሳስተዋል የሚል በሚመስል ስሁት መነሻ ሐሳብ እንጅ በሚኖራቸው ተጠየቃዊ አሳማኝ ምክንያታዊ መነሻ አይደለም፡፡ ይህም ለሚፈጠሩ (“fabricate” ለሚደረጉ) ግለሰባዊ የጥቅም ፍላጎት እና የውሸት ቅስቀሳ አብዛኛውን ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጋልጥ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የእንደዚህ ዓይነት ፖለቲካዊ ክርክር ሥነ አመክኖአዊ የሕፀፅ መንገድ “Appeal to the People” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህም በጽሑፍ ወይም በንግግር አማካኝነት አብዛኛውን ሰው (crowd) ለማስደሰት ሲባል ብቻ ስሜትን ወይም ከመጠን ያለፈ ደስታን (emotions and enthusiasm) በማነሳሳት የእነዚህን ግለሰቦች የውሸት ሐሳብ እንዲደገፍ እና ተቀባይነት እንዲኖረው የሚደረግ የማሳሳት ሙከራ ነው፡፡

(Appeal to the People fallacy is committed when demagogues (arguers) tried to address a large group of people and tried to excite the emotions and enthusiasm of the crowd to win acceptance for his or her conclusion. The objective is to arouse a kind of mob mentality).

በተጨማሪም እነዚህ ሥልጣን እና ድጋፍ የተጠሙ ልኂቃን ይህን ሲያደርጉ እነሱ ብቻ የሚያውቁት መረጃ ወይም ዕውቀት እንዳለ በማስመሰል እና ስለዚህ የሚነግሩን ነገር ትክክል እንደሆነና ልናምናቸው እንደሚገባ ሊነግሩን እና ሊያሳስቱን የሚያደርጉትን ጥረትም  ያካትታል፡፡ ይህም መረጃ (ዕውቀት) የአንድ ወገን ብቻ ሃብት (ይዞታ) እንዳልሆነ እየታወቀ እነዚህ ሰዎች ግን መረጃን (ዕውቀትን) ብቻቸውን እንደያዙ በማስመሰል ለማደናገር ይሞክራሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው አንድም አለን የሚሉትን መረጃ ወይም እውቀት ቢያወጡት ውሸት እንደሚሆንና ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ስለሚያውቁ ሁለትም ይህን በማድረግ ግራ ለማጋባት እና ግራ የተጋባው አብዛኛው ሕዝብ “እውነትም እኮ ትክክለኛ መረጃ (ዕውቀት) ሊኖራቸው ይችላል“ በሚል ግምታዊ እና ጭፍን አመለካከት አሁንም የእነሱን ሐሳብ እንዲቀበል ለማድረግ ታስቦ ነው፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት አንድ መሠረታዊ ሐቅ ‹ዴማጎግሪ› የለየለት የውሸትና የስሜታዊነት መንገድ መሆኑን እና ዴሞክራሲ በሚባለው ሥርዓት ውስጥም በመደበቅ ዴሞክራሲን በእጅጉ እንድንጠራጠረው መንገድ ከፍቷል፡፡ ይህም በዴሞክራሲና በ‹ዲማጎግሪ› መካከል ያለው ልዩነት በጣም ቀጭንና የማይታይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ፕሌቶ ‹ሪፐብሊክ› በተባለው ዝነኛ ሥራው በስድስተኛው ክፍል ውሰጥ ያለው ጉዳይም ዴሞክራሲ ከ‹ዲማጎግሪ› ጋር በተፈጠረው መቀላቀል የተነሳ ሶቅራጠስ በዴሞክራሲ ላይ ያለውን ጨለምተኝነት እና ያነሳቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች በጥልቀት አብራርቷል፡፡ ዴሞክራሲ በመሠረቱ ዕውቀትንና ምክንያታዊነትን እንደ ግዴታዊ ቅድመ ሁኔታ የሚፈልግ ሥርዓት (ሂደት) ነው፡፡ ነገር ግን በዴሞክራሲያዊ መርሆች እንገዛለን እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቆመናል  በሚሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች ውስጥም ቢሆን ብዙውን ጊዜ ይኼን ማደናገሪያ (confusion) መቀላቀል የተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ፈላስፋዎቹ ሶቅራጠስ እና ፕሌቶ አስተምህሮ ዴሞክራሲ የቁጥር ጉዳይ ብቻ አይደለችም፡፡ ለዚህም ነው ፕሌቶ “መሪ መሆን ያለበት ማን ነው (who should rule)?” የሚለውን መሠረታዊ የዴሞክራሲ ጥያቄ የመለሰው ዕውቀትን እና ምክንያታዊነትን ብቻ ማእከል ባደረገው ትንተናው ነው፡፡ ስለዚህ ዴሞክራሲ ዕውቀትንና ብቃትን እንደቅድመ ሁኔታ የሚፈልግና ቁጥር ከዚያ በሁዋላ የሚመጣ ጉዳይ የሚሆነው፡፡

ቁጥርን ከምክንያታዊነትና ዕውቀት አስበልጠን ያስቀደምን ጊዜ ዴሞክራሲ ‹ዴማጎግሪ› ትሆናለች፡፡ አደገኛነቷም ያኔ ይጀምራል፡፡ ለዚህም ነው የምርጫ ወረቀት (Ballot Paper) ትርጓሜ፡- “Are you sure you are qualified to make this decision (vote)” የሚል የሆነው፡፡ ይህም በአፈ ቀላጤዎች እና በአታላዮች (ስሜትን የሚኮረኩር ንግግር እና መረጃ የሚያቀርቡ ነገር ግን እነርሱ ብቻ የሚውቁት መረጃ እና እውነት ያለ የሚያስመስሉት ውሸት በሆነ)  ግለሰቦች እና ቡድኖች ብቻ የተነዳ “መንጋ” (Crowd) አብዛኛ (አብላጫ) ድምጽን ለአንድ የፖለቲካ ቡድን (ግለሰብ) ቢሰጥ እና ድጋፍ ቢያገኝ ይህ ዴሞክራሲ ሳይሆን አደገኛ የሆነ የ‹ዴማጎግሪ› ሥርዓት ይፈጠራል፡፡ ለዚህም ነው በተለይ በእኛ አገር “ፖለቲከኞች” የምትዘወተር “ሕዝብ ሁልጊዜም ልክ ነው” የምትል ነጠላ ዜማ እጅግ አደገኛ የምትሆነው፡፡ ሕዝብ ልክ የሚሆነው ምክንያት እና ዕውቀት ኖሮት ብቁ (qualified) ሆኖ ለሚያቀርበው ጥያቄና በሚሰጠው ድምጽ (vote) ጊዜ እንጅ አብዛኛው ሕዝብ ባለማወቅ እና ባለመንቃት በአታላዮች እና በአስመሳዮች እንደ በግ በሚነዳ ጊዜ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛው ሕዝብ ባልተማረበት እና ባልነቃበት እንዲሁም ጥራዝ ነጠቆች በበዙበት ማኅበረሰብ ዴሞክራሲን መገንባት ፈተና ሆኖ የሚቀጥለው፡፡ ይህን መሠረታዊ እውነታ ለማስረዳት በዕውቀት፣ ዴሞክራሲ እና ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ የሶቅራጥስን አመለካከት በመጠቀም በሚከተለው መልኩ ማስረዳት ይቻላል፡-

“We have forgotten this distinction between an intellectual democracy and a democracy by birthright. We have given the vote to all without connecting it to that of wisdom. And Socrates knew exactly where that would lead: to a system the Greeks feared above all, demagoguery.”

በመጨረሻም፤ እዚህ ላይ ሳይነሳ መቅረት የሌለበት ሌላው ጉዳይ ሕዝበኝነት እና “ዴማጎግሪ” በጣም የሚመሳሰሉ ግን በስሱ ወይም ባልጎላ መንገድ (Subtly) የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች መሆናቸው ጭምር ነው፡፡ ሕዝበኝነት ከ‹ዲማጎግሪ› የበለጠ ርዕዮተ ዓለማዊ ሲሆን፣ ‹ዴማጎግሪ› ግን በዋናነት አንድን አመለካከት ተናጋሪው በፈለገው መንገድ ብቻ ለሕዝብ የማሰተላለፊያ ዘዴ ወይም ንግግር (rhetoric) ነው፡፡ ‹ዴማጎግሪ›ን የንግግር ዘዴ በደንብ ይገልጸዋል የሚባልበት ምክንያት የራሱ የሆነ የተለየ በስሜታዊነትና ፕሮፖጋንዳ  ተሞልቶ (በተናጋረውና በአድማጩ መካከል ያለ ግንኙነት) ሕዝብን የመድረስ መንገድ ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝበኝነት የግድ የራሱ የሆነ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እንዲኖረው አይጠበቅበትም፡፡ ይልቁንስ በንግግር ወይም በጽሑፍ መልክ ከተናጋሪው ወደ አድማጩ የሚተላለፍ ምክንያት (ማስረጃ) አለው ተብሎ የታሰበን መልዕክት ብቻ ያመላክታል፡፡ በተቃራኒው በሌላ ጊዜ ሕዝበኝነት በትክክል ግልጽ ባይሆንም እንኳ እንደ ፖለቲካ ፕሮግራም ሆኖ የሚያገለግል ርዕዮተ ዓለም ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕዝበኞች በዚህም ጊዜ ‹ዴማጎግሪ›ን እንደ አንድ የንግግር ዘዴ ወይም መንገድ ይጠቀሙበታል፡፡ በመሆኑም ‹ዴማጎግሪ› እና ሕዝበኝነት የማይነጣጠሉ ይልቁንም ብዙውን ጊዜ አንዱ ሌላኛውን ተከትሎ የሚመጣ ጉዳይ ይሆናል፡፡

 

 

October 21, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *