ወደ ሕዝብ የወረደው ልኂቃን ችግር | ታምራት ኀይሌ
እንወያይ

ወደ ሕዝብ የወረደው ልኂቃን ችግር | ታምራት ኀይሌ

“የፖለቲካ ሥልጣንን በአመጽ ከነጠቅህ በአመጽ ትገዛለህ፣ ልትወገድ የሚቻለውም በአመጽ ብቻ ነው።” – ፒክ ቦታ፣ የቀድሞው የአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

ባጭሩ ለመግለጽ፣ ዴሞክራሲ በሕዝብ ፈቃድ ላይ የሚመሠረት፣ ሕዝቡ ሰላማዊና ነጻ በሆነ የድምጽ አሰጣጥ ሥርዓት በየተወሰኑ ጊዜያት በሚመርጣቸው ተወካዮች እና በራሱ ሕዝበ ውሳኔ በተደነገገው ማኀበራዊ ውል (social contract) ወይም ሕገ መንግሥት መሠረት የሚተዳደርበት አስተዳደር ማለት ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሚሾመውና የሚሽረው ሕዝቡ ነው፡፡ የሕዝቡን ፈቃድና ፍላጎት የሚጻረር አንዳችም ቡድን ወይም ፓርቲ ተቀባይነት አይኖረውም፤ ሊኖረውም አይገባም። ባለሥልጣናቱ ተጠያቂነት ለመረጣቸውና ለሾማቸው ሕዝብ ነው። የሕግ የበላይነትና ነጻነት የሰፈነበት ሥርዓት ነው ዴሞክራሲ። የቀድሞ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት አብረሐም ሊንከን እንዳስቀመጡት፣ “ዴሞክራሲ የሕዝብ፣ ለሕዝብ፣ በሕዝብ የሆነ መንግሥት” ነው።

ምሁራን ስለ ኅብረ-ብሔራዊ አገረ-መንግሥታት

አንደኛ፣ በርካታ ብሔረሰቦች ባሉበት እና ጽኑ አንድነት በሌለበት አገር ሊብራል ዴሞክራሲን ለማስፈን አዳጋች እንደሆነ ነው (ጆን ስቲዋርት ሚል፣ ፍራንሲስ ፉኩያማ)።

ኹለተኛ፣ በቂ የኢኮኖሚ አቅም የሌለው፣ ዘመናዊ ትምህርት የቀሰመና የሚመርጠውን በሚገባ ለመረዳትና ለመወሰን አቅም የሌለው ደሃ ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ደንታ አይኖረውም የሚሉ ምዕራባውያን ደግሞ አሉ (ማርቲን ሊፕሴት)።

ሦስተኛ፣ የዴሞክራሲ እሴቶች የምዕራባውያን እሴቶች ስለሆኑ ሌሎች ኅብረተሰቦች በቀላሉ ሊማሩዋቸው አይችሉም የሚሉም አሉ (ቤርገር)።

አራተኛ፣ በርካታ ብሔረሰቦችና ቋንቋዎች ቢኖሩም እንደ ሕንድ የመሳሰሉት አገሮች በብሔር ማንነት ላይ ሳይሆን በዜግነት መብትና በሕንዳዊነት የጋራ መታወቂያና ብሔራዊ መለያ ላይ የተመሠረተ እሴት በማስቀደምና ክልላዊ ፌዴሬሽን (ethno-regional federation) በመዘርጋት እንዲሁም የአገሪቱ አንድነት የማይሸራረፍና የማይደፈር፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የመገንጠል መብት በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል አድርጎ በመደንገግ ሊብራል ዴሞክራሲን ለማስፈን ችሏል ብለው የሚከራከሩ ምሁራን ይገኛሉ (ማኖር 1996)።

አምስተኛ፣ የፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነትና የኢኮኖሚ ልማት ካለ በማንኛውም አገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማስፈን ይቻላል የሚሉ ታዋቂ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን አሉ በዚህ ረገድ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሐንትንግተንን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ስድስተኛ፣ ብዙ ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎችና ባህሎች ባሉበት አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን የሚቻለው ሁሉንም ብሔረሰቦች የሚያሳትፍ ሰፊ መሠረተ ያለው የጥምረት መንግሥት (coalition) በማደራጀት እንደሆነ አርተር ሊዊስ የተባሉ ምሁር ያስረዳሉ።

ሰባተኛ፣ የሩቅ ምሥራቅ እስያ አገሮች የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች፣ ደሃ አገሮች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስገኘትና የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ፣ የማኅበረሰቡን መስተጋብር በትምህርት ጭምር እመርታ እንዲያሳይ በማስቻል፣ የገጠር ሕይወት በወሳኝነት ወደ ከተሜነት በመለወጥ እና ኢንዱስትሪን በማሳደግ ወደ ሊብራል ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ይቻላል በማለት ይከራከራሉ (ኬኒቺ)።

ይህ ሁሉ አከራካሪ  አስተሳሰብ እንዳለ ቢሆንም፣ ሁሉም የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁራን እንደሚስማሙበት የፖለቲካ ሥልጣን ቁንጮ ላይ የወጡ ልኂቃን ዴሞክራሲን ለማስፈን የማያወላውል ቁርጠኝነት ካላቸው ዴሞክራሲ በአንድ አገር ውስጥ ሊያብብና ሊጎለብት እንደሚችል፤ እንዲሁም የዴሞክራሲ እሴት በትምህርት የምናገኘው እሴት እንጂ በውርስ የሚተላለፍ እሴት አለመሆኑን ነው፡፡ ከውስጥ የሚለመልምና የሚያድግ ማኅበራዊ እሴት እንጅ እንደሸቀጥ ከውጭ የምናስገባው አይደለም። ስለዚህም በትምህርት የምናገኘውን የዴሞክራሲ እሴት ወደ ተግባር ለመተርጎም ፍላጎትና ቁርጠኝነት ካለ ከጊዜ በኋላ እንደማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር ይህንን እሴት በመንግሥት ቅርፅነትም ሆነ በኑሮ/በሕይወት ዘይቤነት ተግባራዊ ለማድረግ እንደምንችል ነው። ይህንንም እውን ለማድረግ ረዥም፣ በጣም ረዥም ጊዜና ትዕግስት እንደሚያስፈልግ ሁሉም ምሁራን በአጽንዖት ያሳስባሉ።

ዴሞክራሲን እስከመቼ እንጠብቅ?

ሁላችንም መገንዘብ ያለብን፣ ከግለሰብ ችግሮች አንስቶ በማናቸውም ደረጃ የሚያጋጥሙንን የዴሞክራሲና የልማት ችግሮችና ፈተናዎች ለማሸነፍ የምንችለው በራሳችን ጥረት፣ ጥሪት፣ ዘዴና አቅም ነው – ምንም እንኳ ዕውቀትና የሌሎች ገንቢ እገዛ ከተገኙ የሚጠቅሙን ቢሆንም። ዛሬ የምናካሂደው መራራ ትግል በአንድ ወገን ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት በማምጣት ሕዝባችንን  ከከፋ ድህነት ማውጣትና ብቃት/አቅም ያለው ዜጋ እንዲፈጠር ማገዝ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ እውነተኛ ዴሞክራሲን በገዥው ፓርቲ የበላይነት ላይ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድና የበላይነት ላይ በማስፈን የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን በሚገባ መጠበቅ፣ ለነዚህም መከበር ዋስትና የሚሆኑ ተቋሞችን መዘርጋት ሲሆኑ ኹለቱም የትግል ፈርጆች የማይነጣጠሉ የኅልውናችን ምሰሶዎች ናቸው። አንዱን አስቀድሞ ሌላውን በይደር ለማቆየት መሞከር አደገኛ ውጤት ያስከትላል፣ ዴሞክራሲና ልማት ሊነጣጠሉ አይችሉም። ለዚህም ነው እኮ ልማታዊ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት (democratic-developmental state) መሆን የግድ ነው የሚባለው።

በተጨማሪ፣ ለእኛ በአፋኝ የአገዛዝ ሥርዓቶች ለበርካታ ዘመናት ለተሰቃየንና ላሳለፍን ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ1960ዎቹ ኮሪያ፣ ታይዋን እና ሲንጋፖር እኛም “ማንኛውንም ዋጋ ከፍለን የኢኮኖሚ ልማታችንን ማፋጠን አለብን” (economic growth at any cost) የሚለው አስተያየት ከሁሉም በላይ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችንና የሕግ የበላይነትን እንዲሁም የግለሰብና የማኅበረሰብ ነጻነቶችን የሚደፈጥጥ የልማት አማራጭ ከሆነ በአሁኑ ዘመን ተቀባይነት አይኖረውም።

ማናቸውንም ዋጋ ለዛሬውና ለነገው የልማት ትግሎችና ተስፋዎች የዛሬው ትውልድ የዕውቀት፣ የሀብትና የጉልበት መስዋዕትነት ከሚከፍል በስተቀር ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ጭምር እንዲሰዋ መጠየቅ ተቀባይነት የሌለው ጭፍን ፍርድ ነው። ዘላቂ ልማት ማለት (sustainable development) እኮ የዛሬውን ዜጎች መሠረታዊ ፍላጎቶች (ምግብ፣ መጠለያ፣ ልብስ፣ ሕክምና፣ የሥራ ዕድልና ወርሐዊ ገቢ፣ ነጻነት) እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና  ማኅበራዊ  ፍላጐቶች በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ አብዛኛው ሕዝብ ከፍርሐትና ከጭቆና ነጻ ወጥቶ በደስታና በሰላም እንዲኖር ማብቃት አልፎ ተርፎም መጪው ትውልድ ተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ እንዲኖር የሚያስችለው ሀብትና የሀብት ምንጭ መኖሩን ማረጋገጥ ነው። የዛሬውን  ትውልድ ለመጪው ትውልድ ስንል መቅጣት አይደለም።

በዴሞክራሲ ግንባታ፣ በሰብኣዊ መብቶች አከባበር፣ በተቋማት ግንባታ፣ በፖለቲካ ምኅዳር ወዘተ… ረገድ የእስከዛሬው ጉዟችን እጅግም አመርቂ አለመሆኑን እኛ ገዥዎች እና የእኛ ደጋፊዎች ለማመን ባንሻም ያለማቋረጥ  በአገር ውስጥና  ከአገር ውጭ አያሌ ወገኖቻችን የሚያሰሟቸው ጩኸቶችና ሮሮዎች ዓይነተኛ ምስክሮች ናቸውና ሊያሳስቡን ይገባል። ባለፉት የዐሥር ዓመታት ጊዜ ብቻ እጅግ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በአገሪቱ ቆዳ ስፋት የዘረጋና ዓለምን ያስደነቀ የባለ ሁለት አሐዝ (ከ10% እስከ 11%) የኢኮኖሚ ዕድገት (GDP growth) ያስመዘገበ ፓርቲና አገዛዝ በፖለቲካ ነጻነቶችና መብቶች እጦት ምክንያት ቀስ በቀስ ተሽመድምዶ ሲዳከም ለማየት የሚሻ ዜጋ በፍፁም አይኖርም። ገዢው ፓርቲ እና መንግሥት የሚነገሩትን ሕፀፆች አርሞና አስተካክሎ ለበለጡ ድሎች እንዲበቃ እንጂ።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ በሕገ መንግሥታችን መሠረት የብሔረሰቦችን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ በሕዝብ ተወካዮችና በፌደሬሽን ምክር ቤት ደረጃዎች እንዲሁም በክልልና በብሔር ደረጃ ለማረጋገጥና ለማዳበር  የተደረጉት ገንቢ ጥረቶች ሊካዱ አይቻልም። የፖለቲካ ፋይዳቸው አመርቂ ባይሆንም ቢያንስ ቢያንስ ከየብሔረሰቡ አንዳንድ ተወካይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሳተፉ ተደርጓልና። ከዚህ በተጨማሪ፣ በኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች አገዛዝ ክልሎች ሥር የሚገኙትን ሕዝቦች ሁሉ ከምን ጊዜውም በተሻለ ተቋማዊ ትስስር አንድነታቸውንና ኅብረታቸውን እንዲያጠናክሩ የተቀየሰው ሰፊ የኅብረት ግንባር (broad based coalition) እጅግ የሚደነቅ የፖለቲካ ብልሕነት ነበር። የኅብረቱ አባል ፓርቲዎች ነጻነትና ሥልጣን፣ ዕኩል ወይም ተመጣጣኝ ቢሆኑ ኖሮ እንዲሁም የክልላዊ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተግባራዊነት አጠያያቂ ሆኖ ባይቀር ደግሞ ትልቅ እመርታ ነበር።

ይህቺን የበርካታ ብሔረሰቦች፣ ባህሎችና እምነቶች አገር ባለፉት ዘመናት በጠብመንጃ ኀይልና በፖለቲካ ጋብቻ፣ በጥቅማ ጥቅሞችና በኀይል እርምጃዎች (carrot and stick) አንድነቷን ለማቆየት ሲደረግ የነበረው ውጣ ውረድ የዚህ ዓይነቱን አስተማማኝ ተቋማዊ ቅርጽ መያዙ ያለውን አገዛዝ የሚያስመሰግነው በጎ እርምጃ በሆነ ነበር፤ ቲዎሪውና አተገባበሩ ለየቅል ባይሆኑ ኖሮ።

ከሁሉም በላይ፣ ከሃያ ስምንት የአገዛዝ ዓመታት በኋላ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ የሕግ የበላይነት፣ የቡድን መብቶችን፣ የግለሰብ ዜጎችን ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማክበርና በማስከበር ረገድ አሁንም ከቀድሞው አፋኝ ሥርዓቶች እውነታዎች እምብዛም ፈቀቅ እንዳላልን እነዚህ ድምፆች እየጮሁብን ይገኛሉ። “ለምን አድሮ ቃሪያ እንሆናለን?” ነው የጩኸቶቹ መልዕክት። ወገኖቻችን በእኛ ዘገምተኛ እርምጃዎች ተስፋ ቆርጠው መፍትሔ ፍለጋ ወደ ውጭ መሪዎችና አገሮች አቤቱታ እንዲያቀርቡ ወይንም የስደትን አማራጭ ለመተግበር እንዲገደዱ ለምን እንገፋፋቸዋለን? ነው ጉዳዩ፡፡ ለምን ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ማድረግ ተሳነን? ለምን ከአንድ ጦርነት ወደ ጦርነት እየተላጋን ዘመናችንን እንገፋለን?

ዴሞክራሲ በሌሎች ድጋፍም ሆነ በአመጽ አይመጣም

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቢሆንም፣ ሌሎች የበለፀጉና ያደጉ የምዕራብም ሆነ የምሥራቅ አገሮች እና የዐረብም ሆኑ የላቲን አሜሪካ አገሮች በኢኮኖሚ ግንባታ ረገድ ሊያግዙን ይችላሉ። ነገር ግን ወሳኝ የሚሆነው የራሳችን የውስጥ ሀብትና ጉልበት እንዲሁም በቁርጠኝነትና  በኅብረት መነሳሳትና የርብርቦሽ ተጋድሎ ብቻ ነው። ልማትም ሆነ ዴሞክራሲ ከአሜሪካም ሆነ ከኮሪያ፣ ከጃፓንም ሆነ ከታይዋን  አይመጣልንም፤ በራሳችን ትግል ብቻ እንጅ። አዎን፣ በዚህ መንገድ ነው ዘላቂ ዴሞክራሲም ሆነ ልማት፣ ሰላምም ሆነ የፖለቲካ መረጋጋት ሊያብብና ሊሰፍን የሚችለው።

በተጨማሪም ዴሞክራሲና ልማት፣ ሰላምና የፖለቲካ መረጋጋት በአመጽ፣ በኹከትና በጦርነት መንገዶች ሊመጡ እንደማይችሉና እንዲያውም ከቀድሞ ሁኔታዎች የባሱና የከፉ ቀውሶችን እንዳስከተሉና ሊያስከትሉም እንደሚችሉ (The law of unintended consequences) እ.ኤ.አ. ከ2003 እስካሁን ድረስ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሶሪያ፣ በዩክሬይን የሚካሄዱት የሰሜን አትላንቲክ ባለቃልኪዳን አገሮች (NATO) የጣልቃ ገብነት ጦርነቶች እንዲሁም ከ2010/11 ዓመታት ወዲህ በመጀመሪያ በቱኒዚያ ቀጥሎ ደግሞ በሊቢያ፣ በግብፅ፣ በሶሪያ፣ ባህሬን ወዘተ… ከውስጥ በመነጩ ብሶቶችና በውጭ ኀይሎች በታገዙና በተቀነባበሩ ማኅበራዊ ንቅናቄዎች የተነሳ የተቀጣጠሉት የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው።

ከነዚህ እውነታዎች ተገቢውን ትምህርት በመውሰድ ከማናቸውም የአመጽና የሽብር መንገድ በመራቅ እንዲሁም የማንንም የውጭ ኀይል ጣልቃ ገብነትና ገንቢ ያልሆነ ተጽዕኖ ሳንጋብዝ በራሳችን ቁርጠኛ ውሳኔና በተባበረ የሕዝባችን ተጋድሎ እውነተኛና ሌሎቹ የበለፀጉት አገሮችና ሕዝቦች የሚደሰቱባቸውን የዴሞክራሲ፣ የብልጽግና፣ የሕግ የበላይነት፣ የሰላም፣ የደኅንነት ዋስትና፣ የነጻነት ሕይወት ለራሳችንም ሆነ ለሕዝቦቻችን ለማስገኘትና ለማጎናፀፍ የምንረባረብበት ወቅት አሁን ነው።

የሕዝብ ወሳኝነት

ዴሞክራሲ እንዲሰፍንለት ከመንግሥት የሚጠብቅበትን ጊዜ ማሳጠርም ሆነ ማዘግየት የሚችለው  ራሱ ሕዝቡ ነው። ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ ሥርዓተ መንግሥት ሥር ለመኖር አንፈቅድም የሚል ብርቱ  አቅም ሲያገኝ ወይም ሲያጣ ነው። አቅሙን ያዳበረለት ግን በእጁ  ያለውን የምርጫ ካርድ በምርጫ ሳጥን ውስጥ በመክተት ድጋፉን በመስጠት ወይም በመንፈግ ይወስናል። በሥልጣን ያለውን አገዛዝ ያወርዳል ወይም ተጨማሪ የአገልግሎት ጊዜ በኮንትራት መልክ ይሰጠዋል፤ ወይንም ደግሞ ሌላ አገዛዝ ያስቀምጣል። በተለያዩ ምክንያቶች ይህን  አቅምና ጉልበት ያጣ ሕዝብ ግን ዴሞክራሲን ከገዥዎቹ ሲጠብቅ ይኖራል። ወይንም ጫናውን መሸከም ሲያቅተዉ ያምፃል፤ ሌላ ምን አማራጭ አለው? ከሁሉም በላይ፣ አንድ ሕዝብ ዴሞክራሲን አገዛዙ እንዲያሰፍንለት መጠበቅ ሳይሆን ማስገደድ ነው ያለበት። ይህንን ማድረግ ካልቻለ ለዝንተዓለም በፍርሃት መገዛት ነው ዕጣ ፈንታው።

ከሁሉም በላይ መገንዘብ ያለብን ቁምነገር፣  ጊዜ ሲፈቅድ አገዛዝ ይነሳል፣ ጊዜ ሲከዳው ወይንም ሕዝብ ከጠላውና ድምፅ ከነፈገው ደግሞ ይለወጣል፤ ወይም ይወድቃል። የኀይል ሚዛን ተለዋዋጭ ነው። ትናንት ወዲያና ትናንትና እንደነበሩት አገዛዞች ሁሉ የጊዜ እንጅ የሰው ጀግና የለውም እንደተባለው። የፖለቲካ ሥልጣን ለሀብት ቁጥጥርና ዝርፊያ ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑ ባይካድም ይዋል ይደር እንጅ ያከማቹት ሀብትም ያልቃል። የፖለቲካ ሥልጣንም ጊዜያዊ ነው፡፡ መውጣት እንዳለ መውረድም አይቀሬ ነው። ጊዜው ቢረዝምም ቢያጥርም፣ በሰፈሩት ቁና መሰፈርም የማይቀር ዕዳ ነው። የነገውንና የመጪውን ጊዜ አርቆና አሻቅቦ መተንበይ ለሁላችንም ይበጃል እንጅ ጉዳት አያስከትልም። የዐፄ ኀይለ ሥላሴ፣ የደርግና የሕወሓት መሪዎች ማየት የተሳናቸው ይህ ነው፡፡ የአሁኖቹ ሰዎችም በዚህ ረገድ መሻሻል አይታይባቸውም፡፡

ሁልጊዜም ለሚኖረው አገራችንና ለማያልፈው ሕዝባችን የማያልፍ ዘላቂ የዴሞክራሲ እና የልማት ገንቢ ታሪክ ሠርተን ለማለፍ በቁርጠኝነት እንነሳ። የጋራ አገራችንና ዞሮ መግቢያችን፣ የጋራ ቤታችንና መከበሪያችን/መቀበሪያችን እንዳትዳከምና እንዳትፈራርስ ብርቱ ጥንቃቄዎችን የምናደርግበት ዘመን ላይ እንደምንገኝ ሁላችንም ልንዘናጋ አይገባም።

ጆን ኤፍ ኬኔዲ እንዳለው፣ “ሰላማዊ አብዮትን የሚከላከሉ ሁሉ አመጽ የተሞላበትን አብዮት  አይቀሬ ያደርጉታልና” የአገራችን እጣ-ፋንታ በሰላማዊ መንገድ የሚመጣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሆን የፖለቲካ ልኂቃንና መላው ሕዝባችን በቁርጠኝነት እንዲታገሉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። ሌላው አማራጭ ሁሉ የመጠፋፋትና የመበተታን ጎዳና ነውና።

ወደ ሕዝብ የወረደው የልኂቃን ችግር

እስካሁን የነበረው የኢትዮጵያ ችግር ከልኂቃኑ የሚመነጭ ወይም ልኂቃን ሠራሽ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ችግር ነበር፡፡ አንዱ ባላባት ወይም መሳፍንት ከሌላው ጋር፣ አንዱ ንጉሥ ከሌላው ንጉሥ ጋር፣ አንዱ ፓርቲ ከሌላው ፓርቲ ጋር ወዘተ… የሚያደርጉት ሽኩቻ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ መርገም ሆኖ የኖረው፡፡ በተለይ ከ1960ዎቹ ወዲህ ያለውን ሁኔታ ያየን እንደሆነ የፖለቲካ ልኂቃኑ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅር በማይባል ደረጃ በድለዋል፡፡ በፖለቲካ ልኂቃኑ የፖለቲካ ግንዛቤ እና ብስለት ችግር ምክንያት፣ ይልቁንም በእነሱ የሥልጣን ጥም እና ለውይይት ቦታ ያለመስጠት በሽታ ምክንያት ኢትዮጵያ ከበቂ በላይ ደምታለች፡፡

የፍልስፍና ምሁሩ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ “Ideology and Elite Conflics: Autopsy of the Ethiopian Revolution” በሚለው መጽሐፋቸው እንዳብራሩት የኢትዮጵያ ልኂቃን በአገራቸው ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ፈጽመዋል፡፡

እጅግ የሚያሳዝነው ይህ በልኂቃኑ መሀከል የነበረውና ያለው ችግር በጊዜ ሂደት ወደ ሕዝቡ መውረዱ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ችግር የልኂቃኑ ችግር ነው ብሎ ማለፍ የሚቻል አይመስልም፡፡ በተለይ ዘውጌ ብሔርተኛ የሆኑ ልኂቃን የሚያራምዱት አስተሳሰብ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ እንዳሸነፈውና ሕዝቡ ራሱ የዚህ አስተሳሰብ ተሸካሚ እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ክልሎች የሚንቀሳቀስ ማንም ሰው እንደሚገነዘበው አርሶ አደሩ ሳይቀር ስለ ብሔር ፖለቲካና ስለ ብሔር ልዩነት በስፋት ይወያያል፡፡ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለው አስተሳሰብ ከትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ፣ ከቤተ እምነት እስከ ባንክና ሆስፒታል ድረስ ዘልቆ ገብቷል፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በብሔር ልዩነት የተወጠሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ችግሮች የልኂቃን ችግሮች ናቸው ብሎ ማለፍ አይቻልም፡፡

February 7, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *