መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም. “በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚያራምዱ የጋራ የፖለቲካ አቋሞቻቸው ላይ ስምምነት ተፈራረሙ” የሚለውን ዜና ከተለያዩ ሚዲያዎች ዘገባ ሰምተናል። ይህ አካሄድ በአማራና በኦሮሚያ ፓርቲዎች መካከል በጋራ አቋሞች ላይ ስምምነት ከተፈጠረ፣ በሌሎቹ ክልሎቹ አልፎ ተርፎም በአገሪቱ ያሉ ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ (by default) የሚል አንድምታዊ ትርጓሜን የሚያስተላልፍ ይመስላል። የሚገርመው ደግሞ የሁለቱ ክልሎች ፓርቲዎች እንደተስማሙባቸው ከተነገሩ ዐሥር ስምምነቶች መካከል ወደ ስምንቱ ከሁለቱ ክልሎች ጋር የሚገናኙ ሳይሆኑ መላ አገሪቱን የሚመለከቱ ርእሰ ጉዳዮች ናቸው። ለምሳሌ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ መጠየቅ፣ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ሐሳብ መቅረቡ፣ በመላ አገሪቱ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥያቄ መቅረቡ፣ “የኢትዮጵያ የታሪክ አቀራረብ የታሪክ አንጓዎችን ተከትሎ ከሁሉም ብሔርና ብሔረሰቦች በተውጣጡ የታሪክ ምሁራን የአገሪቱን ሕዝቦች ግንኙነትና ታሪክ ጥናት እንዲካሄድ፤ የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም (Institute) ማቋቋም” ወዘተ… የሁለቱ ክልሎች ፓርቲዎች የጎንዮሽ ስምምነት ለማድረግ በተገናኙበት መድረክ የሌሎችን ስምንቱን ክልሎች ዕጣ ፋንታ በሚወስኑ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ የመስማማት ሥልጣንን ማን ሰጣቸው?
በእኔ እይታ አገራዊ የመፍትሔ አጀንዳዎች ከስምምነት ላይ መደረስ ያላባቸው በአገር ዐቀፍ አሳታፊ መድረኮች ላይ ነው። ክልሎች ግን በየራሳቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ከስምምነት ላይ መድረስ ይችላሉ፣ እንደዚህ ዓይነቱ የክልሎች የጎንዮሽ ስምምነቶች የፌዴራሊዝምን ሥርዓት በሚከተሉ በሌሎች አገሮችም የተለመደ ነው። ከዚህ ባሻገር በአገር ዐቀፍ አጀንዳ ላይ በሁለት ክልሎች ሐሳብ አመንጪነት የተደረገው ስምምነት ነገ ከነገ ወዲያ ተግባራዊ ሲሆን የውሳኔው የባለቤትነት ስሜት በሁለቱ ክልሎችና በቀሩት ስምንት ክልሎች መካከል የሚፈጥረው ድባብ ለየቅል ስለመሆኑ ከወዲሁ መገመት አያደግትም።
በእኔ እይታ በአገራዊ አጀንዳዎች የሁሉም ክልል ፓርቲዎች ከሐሳብ አመንጪነት እስከ ትግበራ መሳተፍ አለባቸው። የተወሰኑ ክልሎች በሐሳብ አመንጪነቱ ተስማምተውና ተፈራርመው ሌላው ለትግበረው መጠራት የለበትም። የሁለቱ ክልሎች የስምምነቱ የመጀመሪያ አካል የሆነው ማለትም፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ሁሉን አካታች የሆነ ቀጣይ አገራዊ ውይይትና ድርድር ማካሄድ የሚለው ጥሪም መተላለፍ ያለበት በአገር ዐቀፍ አጀንዳዎች ላይ ከስምምነት ሳይደረስ በፊት መሆን ነበረበት።
Leave a Reply