ስለ ፌዴራሊዝም እንወያይ | ዳንኤል ክንዴ (ዶ/ር)
እንወያይ

ስለ ፌዴራሊዝም እንወያይ | ዳንኤል ክንዴ (ዶ/ር)

በአንድ አገር ውስጥ ዘመናዊ አስተዳደርን ለመገንባትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ተመራጭነት ያለው አሕዳዊ ነው ወይስ ፌደራላዊ ሥርዓት? የሚለው ጥያቄ አሁንም አከራካሪነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ የትኛው አወቃቀር ይሻላል? ለምን? ለሚሉት ጥያቄዎች አንድ ያለቀለት ሁሉንም የሚያስማማ መልስ መስጠጥ አይቻልም፡፡

የሆነ ሆኖ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ክርክሩ ተጧጡፎ እንደቀጠለ ቢሆንም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፌደራላዊ ሥርዓት ነው በሚለው አጀንዳ ላይ ከሞላ ጎደል በሁሉም የአገራችን የፖለቲካ ኀይሎች ዘንድ መግባባት አለ፡፡ በአገራችን አሕዳዊ ሥርዓት እመሠርታለሁ ብሎ የሚታገል በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚንቀሳቀስ አንድም የፖለቲካ ድርጅት የለም፡፡

ይህም የሆነው በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በልዩ ልዩ ባሕሎችና ቋንቋዎች ባሸበረቁ እና በተነጻጻሪ ሰፋ ያለ መልከዓምድር ባላቸው አገሮች ዘንድ የተሻለ ተመራጭነት ያለው ፌደራላዊ ሥርዓት ነው፡፡ ፌደራላዊ ሥርዓት ለአስተዳደር ቀናነት፣ ለዕድገት አመችነት፣ እንዲሁም ባሕልንና ቋንቋን ለማሳደግ በሚሰጠው ዕድል ምክንያት ከፍ ያለ ተመራጭነት አለው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ከታሪካችን እንደምንረዳውም አሕዳዊ አስተዳደር ለአገራችን እንግዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዘመናዊ መልክ አይዋቀር እንጂ ጠቅላይ ግዛቶች በነገሥታት፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ ደግሞ በንጉሠ ነገሥት ወይም በንግሥተ ነገሥታት መተዳደራቸው የሚያመለክተው በማዕከላዊ መንግሥትና በጠቅላይ ግዛቶች መካከል የነበረውን የሥልጣን ክፍፍል ነው፤ ከጊዜ ጋር እየዘመነ መምጣት ባይችልም፡፡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ ያጠኑ ምሁራን እንደሚነግሩን አሕዳዊ ወይም የተማከለ አስተዳደር በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፣ በተለይም ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በኋላ የመጣ ክስተት ነው፡፡ ስለሆነም በታሪካዊም ሆነ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት እና የሚስማማት ፌደራላዊ ሥርዓት ነው መባሉ በጣም ትክክል ነው፡፡ እስከዚህ ድረስ ልዩነት የለም፡፡ ልዩነት የሚመጣው ምን ዓይነት ፌደራላዊ ሥርዓት? በሚለው ጥያቄ ላይ ነው፡፡

በሥራ ላይ ያለውን በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፌደራላዊ ሥርዓት ኢሕአዴግና ሌሎች ብሔርተኛ የፖለቲካ ኀይሎች በጥብቅ እንደሚደግፉት ይታወቃል፡፡ በሥራ ላይ ያለውን ሥርዓት በግንባር ቀደምትነት ተግባራዊ ያደረገው ኢሕአዴግ፣ ለምን ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌደራላዊ ሥርዓትን መከተል እንደሚያስፈልግ የሚያቀርባቸው የመከራከሪያ ነጥቦች አሉ፡፡ ገዥው ግንባር፣ በተለይም ሕወሓት ለትጥቅ ትግል ምክንያት ሆነኝ የሚለው በወቅቱ የነበረው የብሔረሰቦች ጭቆና በመሆኑ፣ ድርጅቱ የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ታገልኩለት የሚለውን አጀንዳ ተግባራዊ ማድረግ ነበረበት፡፡

የኢሕአዴግ ከፍተኛ መሪዎች በቋንቋ ላይ የተመሠረተው ፌደራላዊ ሥርዓት በሥራ ላይ መዋሉ ብሔረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዲወስኑ በማድረጉ ኢትዮጵያን ከብተናና ትርምስ ታድጓል፣ ሰላምና መረጋጋት አምጥቷል፣ ለብሔራዊ መግባባት መሠረት ሆኗል፤ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ወዘተ… እያሉ አበክረው ሲገልጹ ነበር፡፡ አሁንም የሕወሓት አመራሮች በዚኸው አቋማቸው እንደጸኑ ቀጥለዋል፡፡

የሕወሓት አመራሮች በተደጋጋሚ እንደሚናገሩት እና ከድርጅቱ ሰነዶች መረዳት እንደሚቻለው፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል ካስፈለገ ያለው አማራጭ አሁን በሥራ ላይ ያለው በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፌደራላዊ ሥርዓት ብቻ ነው፡፡ እነሱ እንደሚሉት በቋንቋ ላይ የተመሠረተውን ፌደራላዊ ሥርዓት መቀየር ኢትዮጵያን ወደማያባራ ግጭት ውስጥ መክተት ነው፡፡

ባለፉት 28 ዓመታት የተከሰተውና ከጊዜ ወደጊዜ እየባሰበት የመጣውን የዜጎች ሞትና መፈናቀል ከፌደራላዊ ሥርዓቱ ጋር አይገናኝም ባይ ናቸው የሕወሓት መሪዎች፡፡ በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች እምነት በሕዝቦች መካከል ግጭት ተከስቶ አያውቅም፤ ግጭት የሚቀሰቅሱት የየአካባቢው ኪራይ ሰብሳቢ አመራሮችና ጸረ ሰላም ኀይሎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በሥራ ላይ ያለውን አወቃቀር የሚደግፉት ወገኖች ቋንቋን መሠረት ያደረገው ፌደራላዊ ሥርዓት በጊዜ ሂደት እየተሻሻለና እየጎለበት ይሄዳል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ከፍ ሲል እንደተገለጸው ከሕወሓት በተጨማሪ በሥራ ላይ ያለውን ፌደራላዊ ሥርዓት አጥብቀው የሚደግፉ ሌሎች ብሔርተኛ የፖለቲካ ኀይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ኀይሎች ልክ እንደ ሕወሓት ሁሉ ለኢትዮጵያ መድህኗ በቋንቋ ላይ የተመሠረተው ፌደራላዊ ሥርዓት ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ በአገራችን በተደጋጋሚ የሚከሰቱት ግጭቶች፣ ማለቂያ የሌላቸው የድንበር ይገባኛል እና የልዩ ወረዳና ዞን ጥያቄዎች፣ የሕዝብ ሞትና መፈናቀል ወዘተ… ሁሉ ከፌደራላዊ አወቃቀሩ ጋር ግንኙነት የለውም፣ ዋናው ችግር ዴሞክራሲና የፌደራላዊ ሥርዓቱ በአግባቡ (ሕገ መንግሥቱ በሚደነግገው መሠረት) ተግባራዊ አለመሆኑ ነው ባይ ናቸው እነዚህ ኀይሎች፡፡

ሆኖም አሁን በሥራ ላይ ያለው ፌደራላዊ ሥርዓት በዜጎች መካከል ኅብረትና ትብብርን ሳይሆን አላስፈላጊ ውድድርን፣ ጥላቻን እና የእርስ በርስ ግጭትን እንደሚፈጥር በግልጽ እያየነው ነው፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት በግልጽ እንደታየውና ከጊዜ ወደጊዜ እየባሰበት እንደመጣው ይህ በቋንቋና ዘውጋዊ ማንነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት አንዳንዶችን ዋና ሌሎችን ሁለተኛ ዜጋ የሚያደርግ፣ “ሌሎችን” በማግለል ላይ ተመሠረተ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን እንደምናየው፣ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው እንደባይተዋርና ሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠሩ፣ “ክልላችሁ አይደለምና ‹ከክልሉ ባለቤቶች› ጋር እኩል መብት የላችሁም፣ እንዲያውም አካባቢያችሁ ስላልሆነ ለቃችሁ ውጡ …” ይባላሉ፡፡ በዚህ ሒደት የበርካታ ወገኖቻችንን ሕይወት አጥተናል፤ በርካቶች ከኖሩበትና ከሚያውቁት አካባቢ በግፍ ተባረዋል፤ በዚህም ምክንያት በሕዝቦች መካከል ቂምና ቁርሾ ተፈጥሯል፡፡

በመሠረቱ በቋንቋና ዘውጋዊ ማንነት ላይ የተመሠረተ ፌደራላዊ ሥርዓት፣ ውስብስብ ችግሮችን ያዘለ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በፖለቲካ ገጽታው በሕዝቦች መካከል ያሉትን ልዩነቶች የማቆየት፣ የማጉላትና የማስፋት ብሎም ወደውጭ ለሚስቡ (centrifugal) ኀይሎች አመቺ ሁኔታን የመፍጠር፣ የሕዝቦችን አንድነትና የውሕደት አዝማሚያዎች የመግታትና የማዳከም ባሕርይ አለው፡፡ በኢኮኖሚም ረገድ ለአገር ዐቀፍ ልማት፣ በዕቅድ መምራትና ለተመጣጠነ የአገር ዕድገት እንቅፋትን ሊፈጥርና የመንግሥትን ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወጪዎችን በማሳደግ ልማትን ሊያጓትት ይችላል፡፡ (አንዷለም አለባቸው፣ “የፌደራላዊነት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አንድምታዎች”፣ መድረክ መጽሔት፣ 1985 ዓ.ም.፣ ገጽ 9)

የብሔረሰብ ፖለቲካ ዋና የማደራጃ ርዕዮተ ዓለም በሆነበት የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ይህ የተለመደ ነው፡፡ ዜጎችን “ነባር-መጤ” ብሎ መከፋፈል፤ መሬታችን ተወሰደ፣ ድንበራችን ተጣሰ፣ ማንነታችን ተዋረደ ወዘተ… ብሎ ስሜታዊ ቅስቀሳ ማድረግና ሕዝብን በሕዝብ ላይ ማነሳሳትም የተለመደ ነገር ነው፡፡ በዚህ መልኩ ነው የዘር ማጥራት (ethnic-cleansing) እና የዘር ፍጅት (Genocide) እርምጃዎች እንደዘበት የሚከሰቱት፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው አገር ህልውና እንደዘበት አደጋ ላይ የሚወድቀው፡፡

የብሔረሰብ ጠበቃ ነን የሚሉ ሰዎች በውጭም በአገር ውስጥም የሚያካሂዱት ስሜታዊና አደገኛ ቅስቀሳ ፍሬ ማፍራት ጀምሯል፡፡ ጽንፈኛ ብሔርተኞች በቋንቋና ዘውጋዊ ማንነት ላይ የተመሠረተውን ፌደራላዊ ሥርዓት በመጠቀም ‹መጤ› የሚሏቸውን ዜጎች በውድም በግድም እያፈናቀሉና እያሳደዱ (ንጹሕ) የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ክልል ለመፍጠር ሌት ተቀን እየሠሩ ነው፡፡ ሁሉም የእኔ የሚለውን ሕዝብና መሬት አጥሮ ለመቀመጥ፣ ሁኔታዎች ሲያመቹም “የራስን ዕድል በራስ መወሰን” የሚለውን የተለመደ የብሔርተኛ ድርጅቶች ማደናገሪያ በማቅረብ አገርን ለማፍረስ ነው እየተንደረደረ ያለው፡፡ በአጠቃላይ በቋንቋ ላይ የተመሠረተውን ፌደራላዊ ሥርዓት አጥብቀው የሚተቹ ምሁራን እንደሚሉት የዚህ ዓይነቱ ሥርዓት “የአዳዲስ አገሮች መፈልፈያ ማዕከል ነው፡፡”

በዚህ አደገኛ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውስጥ የኢትዮጵያን መዳከም የሚፈልጉ ኀይሎች በመካከላችን እየገቡ ብሔርተኛ ድርጅቶችን እንደሚደግፉ በግልጽ ይታወቃል፡፡ ግብጽና ሌሎች አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ኢትዮጵያን ማየት የማይፈልጉ ኀይሎች በብሔርተኛ ድርጅቶች አንቀልባ ታዝለው በአገራችን ላይ ለመፈንጨት ነው የሚፈልጉት፡፡ እነ ግብጽ ኢትዮጵያን ለማዳከም እንደ ጀባሕና ሻዕብያ ያሉ ድርጅቶችን እንዴት ይደግፉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዛታ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የውስጥ ጉዳያችንን ራሳችን ልንፈታ ይገባል፡፡ የአገራችንን መጠናከር የማይፈልጉና ድብቅ ዓላማ ያላቸው ኀይሎች በውስጥ ጉዳያችን ገብተው እንዲፈተፍቱ ዕድል ልንሰጣቸው አይገባም፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በቋንቋና ዘውጋዊ ማንነት ላይ የተመሠረተው ሥርዓት የሕዝቦችን ኅብረትና አንድነት የሚበትን፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት እንቅፋት የሆነ እና ውሎ አድሮም በአገር ህልው ላይ አደጋ የሚደቅን ሥርዓት ነው፡፡ ስለሆነም ከቋንቋና ከዘውጋዊ ማንነት ይልቅ ሌሎች አግባብነት ያላቸው መሥፈርቶችን መጠቀሙ ለሕዝብ መብት መከበርም ሆነ ለብልጽግናና ለአገር ህልውና መጠበቅ እጅግ የተሻለ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ቋንቋና ዘውጋዊ ማንነነቶች ወደጎን ይባሉ ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የእያንዳንዱ የቋንቋና ባሕል ሉዓላዊነት የሚከበርባት (cultural sovereignty) እና ፖለቲካዊ አንደነቷ የሚጠበቅባት (political unity) ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በምትባለው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ወሰኗ በታወቀ ጆክራፊያዊ ክልል ውስጥ በመወለዱ ብቻ የዚህች አገር ዜጋ መሆኑን እና በዚህች ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች ቋንቋቸውንና ባሕላቸውን የመጠበቅና የማሳደግ ሙሉ መብት ያላቸው መሆኑን በደንብ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የእነዚህ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች መብት የሚጠበቀውና ዘላቂ ብልጽግና ሊገኝ የሚችለው የኢትዮጵያ አንድነት ሲከበር መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም መንግሥታዊ አደረጃጀታችን የዜጎቻችን መብት የሚጠበቅበትንና አገራዊ ብልጽግና የሚረጋገጥበትን ሁኔታ የሚያመቻች መሆን ይኖርበታል ማለት ነው፡፡

በመሠረቱ የመንግሥት አደረጃጀት የዜጎችን ሕይወት የበለጠ የተሟላ ለማድረግ የሚያስችል መሆን አለበት፡፡ የክፍለ አገሮች ወይም የፌደሬሽኑ አሐዶች (States) አከፋፈልና አሠራር ከፌደራላዊው መዋቅር ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ይህንን መሠረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ እንዳደረገችው አንድ አሐዳዊ የነበረ አገር ራሱን ወደ ፌደራላዊነት (holding together federalism) በሚለውጥበት ጊዜ ለቋንቋ፣ ለባሕልና ዘውጋዊ ልዩነቶች በተቻለ መጠን ትኩረት መስጠቱ አስፈላጊ ቢሆንም፣ የእነዚህ ሁኔታዎች በጊዜ ሂደትና በልዩ ልዩ ምክንያች ሊለወጡ የሚችሉ መሆኑ ተዘንግቶ ቋሚና ዘላቂ እንደሆኑ መታየትና መወሰድ አይገባቸውም፡፡

የክፍለ አገሮች ወይም የፌደሬሽኑ አባል አሐዶች አከፋፈልና አከላለል ከዘውጋዊ ማንነት ይልቅ የበለጠ አግባብነት ያላቸው መስፈርቶችን ቢከተል የተሻለ ይሆናል፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ አከፋፈሉ የአስተዳደር ቀናነትን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡ አከፋፈሉ አስተዳደራዊ ቀናነትን ለማስገኘት መሆን ይገባዋል፡፡ ሰዎችን በተለይም አምራቾችን የማያጉላላ፣ የማያዳክም፣ ጊዜንና ጉልበትን ለመቆጠብ የሚያስችል መሆኑ አስፈላጊ ነው፡፡ የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች፣ ለምሳሌ የልማት ሥራ ለመጀመር ፈቃድ የሚሰጡ፣ ግብር የሚቀበሉ፣ ደህንነትንና ፍትሕን የሚጠብቁትና የመሳሰሉት መሥሪያ ቤቶች ከሕዝብ ሩቅ መሆን አይገባቸውም፡፡ በአምራቹ አጠገብና አካባቢ ተገኝተው ጉዳዩን ያለብዙ ውጣ ውረድ ለመፈጸም መቻል ይኖርባቸዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ አከፋፈሉ ለአካባቢና ለአገር ዕድገት አመቺ መሆን ይኖርበታል፡፡ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ያለ ብዙ መሰናክል መራመድ መቻል ይገባቸዋል፡፡ መሰናክሎችን ለመቀነስና ከነጭራሹም ለማስወገድ የሚያግዙ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችሉ አከላለሎች ያስፈልጋሉ፡፡ ዕድገት የሥራ ውጤት እንደመሆኑ የሥራ ቅልጥፍናን የሚያስገኝ፣ ለሰዎችና ለዕቃዎች እንደልብ መንቀሳቀስና መዘዋወር የሚያመእ፣ ሰዎችን ለሥራ የሚያበረታታና የሚጋብዝ ዓይነት አደላደል ጠቀሜታ እንደሚኖረው አያጠራጥርም፡፡ የሥራ ክፍፍል፣ በተወሰኑ የችሎታ መስኮች ላይ ትኩረት ማድረግ ተደጋጋፊነት አንዱ የሌላውን ፍላጎት ማሟላት የመሳሰሉት ለሶሲዮ-ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስፈላጊነታቸው የተረጋገጠ ስለሆነ አከፋፈሉ እነዚህን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡፡

ሦስተኛ፣ የክፍለ አገሮች ወይም የፌደሬሽኑ አባል ክልሎች አከፋፈልና አከላለል የሕዝብና የሀብት መመጣጠን (symmetry) ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡ የፌደራላዊ መንግሥት የሚሠርቱት በሕግ የሆኑ አሃዶች ናቸው፡፡ ይህ በሕግ እኩልነት፣ በሀብትና በሕዝብ እኩልነት ወይም ተቀራራቢነት ካልተደገፈ ችግሮች ሊከተሉና ፌደሬሽኑ በትክክል ላይሠራ ይችላል፡፡ የፌደሬሽኑ አባል ክፈለ አገሮች (አሐዶች) በሀብትና በሕዝብ ብዛት የተመጣጠኑ ካልሆኑ ትልቁ ትንሹን ሊጨፈልቀውና የበላይነቱን ሊጭንበት ይችላል፡፡ ይህም በፈረንጆች አባባል የብዙሃኑ አፈና (majority tyranny) የሚሉት ነው፡፡

በአራተኛ ደረጃ የክፍለ አገሮች ወይም የፌደሬሽኑ አባል ክልሎች አከፋፈልና አከላለል የዜጎችን የአንድነትና መቀራረብ ሂደት የበለጠ የሚያጠናክር እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ አከፋፈሉ በሕዝቦች ልዩነት ላይ የሚያተኩር፣ ለአላስፈላጊ ጥርጣሬና ጥላቻ የሚጋብዝ ሳይሆን የየራሳቸውን ቋንቋ ባሕል የመጠበቅና የማሳደግ ሙሉ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሚጋሯቸው ዕሴቶች ላይ ሊያተኩር ይገባል፡፡ ለሁሉም ሕዝቦች መብት መከበርና የጋራ ብልጽግና የሚበጀው መነጣጠልና በመካከላቸው አጥር መገንባቱ ሳይሆን ኅብረትና አንድነት ነው፡፡ (ዝኒ ከማሁ፣ 10-11)

አምስተኛ፣ ሕዝቦች ቋንቋቸውንና ባሕላቸውን ለመንከባከብና ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ስለአገር አንድነትና ስለሕዝቦች ኅብረት ሲባል ልዩነቶች ይጥፉ ማለት አይቻልም፣ አይገባምም፡፡ ስለሆነም አከፋፈሉ እነዚህ በአንድ አገር ጥላ ሥር የሚኖሩ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩና የተለያየ ባሕል ያላቸው ሕዝቦች፣ ቋንቋቸውንና ባሕላቸውን የሚንከባከቡበትንና የሚያሳድጉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ዜጎችና ሕዝቦች መብት እንዲጠበቅና በአገራችን ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና እንዲመጣ ካስፈለገ፣ ከላይ የተጠቀሱትን አምስት እና ሌሎችንም መሠረታዊ መስፈርቶች ተጠቅሞ አሁን ያለውን በቋንቋ በዘውጋዊ ማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት እንደገና ማዋቀር (መከለስ) ያስፈልጋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች ተጠቅሞ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ፌደራላዊ ሥርዓት ለመከለስ ጥሩ መነሻ የሚሆነው በቀድሞው ሥርዓት የመጨረሻ ዓመታት በዘርፉ ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ባላቸው ምሁራን ተጠንቶ የቀረበው አስተዳደራዊ ክፍፍል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ያለፈው መንግሥት ይከተል የነበረው አሐዳዊ ሥርዓትን ስለነበረ እነዚያ ክፈለ አገሮች የፌዴራል መንግሥት አባል አሐድነት ቁመና (status) አልነበራቸውም፡፡ ስለሆነም ፌዴራላዊ አወቃቀሩ እንደገና የሚከለስ ከሆነ እነዚያን ክፍለ አገሮች ወደፌደራል መንግሥት አባል አሐድነት (ስቴት) ቀይሮ የየራሳቸው ሕገ መንግሥት፣ ምክር ቤት፣ የፍትሕና ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እንዲኖሯቸው ማድረግ ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት፣ ተደጋግሞ የሚቀርብ ምዕራብ ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ምሥራቅ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ ወዘተ… እየተባለ መከፈሉ ማኅበረሰቦች ቋንቋቸውንና ባሕላቸውን እንዳያሳድጉ ያደርጋል የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አስተያየት ውኃ የማይቋጥር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ሰሜን ወሎን ብንወስድ፣ ሰሜን ወሎ ውስጥ አማራ፣ ዋግ ኽምራ፣ አፋር፣ ትግራይ ወዘተ… ሕዝቦች ይኖራሉ፡፡ በዚህ ክፍለ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በምን ቋንቋ/ዎች እንደሚሠሩ፣ እንደሚማሩና እንደሚዳኙ የመወሰን እና የየራሳቸውን ቋንቋና ባሕል የማሳደግ ሙሉ ነጻነት አላቸው፡፡ ይህ ትግራይ ውስጥም ሆነ ሲዳማ፣ ምሥራቅ ሐረርጌም ሆነ ሰሜን ሸዋ ውስጥ ይሠራል፡፡ የሁላችንም የጋራ መዲና የሆነቸው አዲስ አበባም እንደ አንድ የፌደራል መንግሥት አባል አሐድ ሆና ራሷን ታስተዳድራለች፡፡

ናይጀሪያ እና እኛ

በቅርቡ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ፈርሶ በርከት ያሉ ክልሎች እንደገና እየተዋቀሩ ነው፡፡ ይህም የፌደሬሽኑን አሐዶች እንደገና የመከለስና የማዋቀር ዕድልን ፈጥሯል፡፡ ይህ መንገድ በጆግራፊያዊ መጠንም ሆነ በሕዝብ ብዛት ከሞላ ጎደል ተመጣጣኝነት ያላቸው ክፍለ አገሮችን ለመፍጠር እና የትልልቅ ክልሎችን ማን አህሎኝነት ለማረቅ፣ ወዲያውም የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ትልቅ በር የሚከፍት ነገር ነው፡፡ ለዚህ ትልቅ አብነት የሚሆነን የናይጀሪያ ፌደሬሽን የታሪክ ጉዞ ነው፡፡

ናይጀሪያ ገና በብሪታኒያ የቅኝ አገዛዝ ሥር እያለች፣ ማለትም በ1954 (እ.ኤ.አ) 3 ክፍለ አገሮችን (ስቴትስ) ይዛ በፌደሬሽን የተዋቀረች ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜያት የፌደሬሽኑን አሐዶች እንደገና እየከለሰች አደራጅታለች፡፡ በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ በ1963 ከሦስት ወደ አራት፣ በ1964 ከአራት ወደ ዐሥራ ሁለት፣ በ1976 ከዐሥራ ሁለት ወደ ዐሥራ ዘጠኝ፣ በ1987 ከዐሥራ ዘጠኝ ወደ ሃያ አንድ፣ በ1991 ከሃያ አንድ ወደ ሠላሳ እና በ1996 ከሠላሳ ወደ ሠላሳ ስድስት የፌደሬሽኑን አባል ክልሎች ወይም ክፍለ አገሮች ከፍ አድርጋለች፡፡ የናይጀሪያን ፖለቲካ ያጠኑ ምሁራን እንደሚገልጹት ይህ እርምጃ ለናይጀሪያ ህልውና መጠበቅና ለዚያች አገር ሁለንተናዊ ልማት ያደረገው አስተዋጽዖ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ናይጀሪያና ሕንድ ካሉ አገሮች የምትቀስማቸው በርካታ ትምህርቶች አሉ፡፡

 

 

October 21, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *