“ለተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥት አጥጋቢ ምላሽ እየሰጠ አይደለም” | ኢዜማ
እንወያይ

“ለተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥት አጥጋቢ ምላሽ እየሰጠ አይደለም” | ኢዜማ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ችግር ለተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥት አጥጋቢ ምላሽ እየሰጠ አይደለም አለ::

ኢዜማ መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ከመንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ገልጿል:: ፓርቲው ኮሚቴዎችን አዋቅሮ የደረሰውን ጉዳት እና ተጎጂዎች ያሉበትን ሁኔታ እንዲሁም በመንግሥት በኩል እተደረገ ያለውን እገዛ እና አሁን ያሉበትን የደህንነት ሁኔታ ገምግሞ ከተጎጂዎች ጋር ተወያይቶ መመለሱን አስታውሷል። በዚህም የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በሻሸመኔ እና በአርሲ ዞን ዴራ ከተማ የሚኖሩ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ዜጎች ጉዳት ከደረሰባቸው ከሁለት ወር በላይ ቢሆናቸውም፣ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ማድረግ እና በቋሚነት መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ባደረኩት ግምገማ አረጋግጫለሁ ብሏል::

በተለይ በዴራ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ 50 ቀን የሞላቸው ቢሆንም ከትኛውም የመንግሥት አካል ስለጉዳታቸው ያነጋገራቸው እንደሌለ እና ድጋፍም ከመንግሥት እንዳልተደረገላቸው አረጋግጫለሁ ሲል ፓርቲው በመግለጫው ጠቁሟል:: በዴራ ከተማ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስተያን ተጠልለው የሚገኙት ዜጎች ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭ በሆነ የአኗኗር ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ለአስቸኳይ ድጋፍ ተብለው ከቀረቡት ቁሳቁሶች መካከል የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ቁሳቁስ መኖሩ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንደነፈገው የሚያሳይ ሆኖ ማግኘቱን እና ይህም እንዳሳዘነው ኢዜማ ገልጿል።

ፓርቲው ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማገዝ እና መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንዲያሳውቅ በደብዳቤ የጠየቀ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በክልሉ መንግሥት በኩል የተሰጠው ምላሽ አለመኖሩን ጠቅሷል::

በተጨማሪም ጉዳት ውስጥ የሚገኙት ዜጎች የደረሰባቸው ጉዳት ሳያንስ አሁንም ድረስ ዛቻ እና ማስፈራርያ እየደረሰባቸው በመሆኑ ተረጋግተው ራሳቸውን ማቋቋም ቀርቶ መንግሥት የተለየ ጥበቃ ማድረግ ካልቻለ ለሕይወታቸው እንደሚያሰጋቸውም ለኢዜማ ከፍተኛ አመራሮች መግለጻቸውን ጠቁሞ፣ መንግሥት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሷ ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስቧል።

ነሐሴ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ አንዳንድ አካቢዎች በተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጾ መንግሥት ለዜጎች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ኮሚሽኑ ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም::

ኢዜማ ሐምሌ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የክልሉ ልዩ ኀይል እና መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ አልደረሰንም በሚል ምክንያት ንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ለማስቆም አለመቻላቸውን በመግለጽ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና ሰላም የማስከበር ኀላፊነት የነበረባቸው አካላት ሕዝቡን ከጉዳት መከላከል እየቻሉ ከለላ ባለመስጠታቸው በደረሰው ጥቃት ላይ ተቋማቱ በቂ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቆ፣ መንግሥት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ ወጥቶ ይቅርታ እንዲጠይቅ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው::

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በጎርፍ አደጋ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግም ኢዜማ ጠይቋል::

በአፋር ክልል በተልይ ደግሞ በዱፍቲ፣ አሳኢታ፣ አሚባራ፣ ግሎ፣ አፋምቦ እና ገዋኔ ወረዶች ቁጥራቸው ከ67‚000 በላይ በሆኑ ሰዎች የጎርፍ አደጋ ጉዳት ሲደርስባቸው፣ ከ40 ሺሕ በላይ የሆኑት ተፈናቅለዋል ያለው ፓርቲው በኦሮሚያ ክልል በአዋሽ ተፋሰስን ተከትሎ ባሉ ወረዶች እና ከተሞች በተልይ ደግሞ ወንጂ፣ ፈንታሌ እና የተወሰኑ የአዳማ ከተማ ሰፈሮች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ጠቁሟል::

በምሥራቅ ሸዋ ፈንታሌ ወረዳ ከ25 ሺሕ በላይ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ሳቢያ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል:: በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልል ጊሎ ወንዝ፣ ባሮ ወንዝ እና በንወር ዞን በሚገኙ የክረምት ደራሽ ወንዞች ሞልተው መስመር ጥሰው ስለፈሰሱ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ ሕዝብ ተፈናቅሏ፤ በአማራ ክልል የውሃ መጥለቅለቅ በመከሰቱ ከ10 ሺሕ ዜጎች ሲፈናቀሉ በሰብል እና በእንስሳት ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የገለጸው ኢዜማ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች አስቸካይ ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸው መንግሥት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል::

የክረምቱ ዝናብ አሁንም ጠንክሮ በመቀጠሉ በጎርፉ ሳቢያ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ላይ መጠኑ የተለያየ ጉዳት፣ እንዲሁም ከ400 ሺሕ ሰዎች በላይ ሊያፈናቅል እንደሚችል ግምት በመኖሩ መንግሥት አደጋ ይደርስባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ጋር በመነጋገር አደጋ ተከስቶ ሕዝቡን ችግር ውስጥ ከመክተቱ በፊት የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ አደጋውን ማስቀረት አለበት ብሎ እንዲያምን ኢዜማ በወጣው መግለጫ አሳስቧል::

 

 

 

 

 

October 4, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *