ጦርነቱ እና ኢኮኖሚው | ይዴድያ ዳዊት
ኢኮኖሚ

ጦርነቱ እና ኢኮኖሚው | ይዴድያ ዳዊት

ጦርነት በአንድ ውስን ቦታ ላይ የሚከናወን ቢሆንም ዳፋው ግን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለአጭር እና ለተራዘመ ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡ በአጭር ጊዜ እስከ አምስት ዓመት፣ ሲራዘም እስከ ዐሥር ዓመት የሚቆይ ውስብስብ ችግሮች ሊፈጥር ይችላል፡፡ ከፖለቲካው ባሻገር ኢኮኖሚያዊ እና ማኀበራዊ ችግሮችንም ይፈጥራል፡፡

በፌዴራል መንግሥት እና ትግራይን በሚመራው የሕወሓት አክራሪ አመራር መሀከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ከተጀመረ ሳምንት አልፎታል፡፡ መንግሥት ሕግ  ለመስከበር እና አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚወስደው እርምጃ የሚደገፍ ቢሆንም፣ ተገድዶ ወደ ጦርነት ውስጥ መግባቱ ግን በኢኮኖሚ ላይ የረጅም እና አጭር ጊዜ ችግር መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ በዛሬ ጽሑፌ ጦርነቱ በኢኮኖሚ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የአጭር እና የረጅም ጊዜ ተጽዕኖ  ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

ከአጭር ጊዜ  አኳያ በጦርነቱ  ምክንያት የምርት እንቅስቃሴ መታወኩ የማይቀር ነው፡፡ አገር እንዲህ ባለችግር ውስጥ ስትሆን ገበሬው ምርቱን አውጥቶ ለመሸጥ ድፍረት ያጣል፤ ነጋዴውም የገዛውን ምርት አንቀሳቅሶ ለመሸጥ ተነሳሽነቱ ይቀንሳል፡፡ ነጋዴ ምርት አንቀሳቅሶ መሸጥ ካልቻለ ደግሞ በአገሪቱ ገበያ ላይ የምርት እጥረት ሊገጥም የሚችለበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ይህም እስከ ጦርነቱ ማብቂያ ድረስ መለስተኛ የምርት ግሽበት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡

አሁን ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የሚመረተው ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የቅባት እህል ጦርነቱ ከተራዘመ በጊዜው ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ይህም ደግሞ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የራሱን የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ከመፍጠሩ ባሻገር የተመረተውን ምርት ገበያ አቅርቦ መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎችን የሚገዛው አምራች ገበሬ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡

በጦርነት ከሚፈተኑ ዘርፎች መካከል የጤናው ሴክተር በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በጦርነት ወቅት በሁሉም ወገን ተጎድቶ እና ቆስሎ የሚመጣው አካል ብዙ ከመሆኑ አኳያ ዘርፉ ሰፊ የሰው ኀይል እና የመድኃኒት ግዥ ወጪን የሚፈልግ ነው፡፡ አገሪቱ በኮሮና ወረርሽኝ ፈተና ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ እስከ ጦርነቱ ማብቂያ ድረስ በእጅጉ ሊፈተን እንደሚችል እርግጥ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ቀድሞ ከነበረው የጤና በጀት ተጨማሪ ማስፈለጉም ግድ ነው፡፡

በጦርነቱ ምክንያት የሚፈጠር መፈናቀል የሚኖር ከሆነ ይህን ማኅበረሰብ የእለት ደራሽ ምግብ እና መጠጥ ማቅረብ ከጦርነቱ ጎን ለጎን መንግሥት ደርቦ መሥራት ያለበት ድርብ ኀላፊነቱ ነው፡፡ ይህም ተጨማሪ በጀት እና አቅም የሚፈልግ አንድ እራሱን የቻለ ኢኮኖሚያዊ ጫና ነው፡፡

አሁን የፌዴራል መንግሥቱ የገባበት ጦርነት ወዶ እና ፈቅዶ ቀድሞ ዝግጅት ያላደረገበት እና በጀት ያልተቆረጠለት በመሆኑ ለዓመት ከያዘው በጀት ተጫማሪ የበጀት ድጎማ እንዲፈልግ ሊያደርገው ይችላል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የሠራዊት እና የመሣሪያ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ብቻ ሰፋ ያለ በጀት ይጠይቃል፡፡ ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚውለው ነዳጅ ከውጭ ተገዝቶ የሚገባ እንደመሆኑ መጠን ለዚህ ኦፕሬሽን ብቻ ለነዳጅ ፍጆታ ቀድሞ ከነበረው የውጭ ምንዛሪ መጠን ተጨማሪ ያስፈልገዋል፡፡ ይህም መንግሥትን ተጨማሪ ወጪን እንዲፈልግ ያደርገዋል፡፡ ይህን ወጪ ለመሸፈን መንግሥት ሳይወድ በግድ ለካፒታል በጀት ያሰበውን ገንዘብ ወደ ጦርነቱ እንዲያዞር ይገደዳል፡፡ ይህም አገሪቱ በያዘችው ዕቅድ መሠረት እንደትጎዝ ሰንኮፋ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡

በጦርነቱ አካባቢ ያሉ እንደ ባንክ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ዝግ ሆነው መቆየታቸው ተቀጥረው የሚሠሩ እና በርካታ ገንዘባቸውን በባንክ ያስቀመጡ ዜጎች የእለት ጉርሳቸውን መሸፈን ሊያቅታቸው ይችላል፡፡ ከአጭር ጊዜ አኳያ እነዚህንና እነዚህ የሚመስሉ ችግሮች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ከስር ከስር የመፍትሔ እርምጃዎችን መውሰድ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ጦርነቱ ከረጅም ጊዜ አንጻርም ችግር ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ማንም በሚረዳው መልኩ የጦርነት ቀጠና በሆኑ አካባቢዎች የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለረጅም ጊዜ መዳከሙ የማይቀር ነው፡፡ ቀደሞም ቢሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ላለፉት ስምንት እና ዘጠኝ ወራት የቱሪዝም ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ ነው የቆየው፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት ይህን ዘርፍ ጠብቆ ለማቆየት በጀት መድቦ ሲደጉመው ቆይቷል፡፡ ይህ ዘርፍ አሁን ለማንሰራራት እየሞከረ ባለበት ወቅት ይህ ጦርነት መከሰቱ የቱሪዝም ዘርፉ ዳግም ወደ ቆየበት ጉዳት እንዲመለስ ማድረጉ የማይቀር ነው፡፡ በዚህም ዘርፍ አገሪቱ  በጥቂቱም ቢሆን ታገኘው የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ ያደርጋታል፡፡

ጦርነት ከሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ባሻገር በማኅበራዊ ዘርፍ ላይ ዜጎች ባለው መንግሥት ላይ እምነት በማጣት ፈሪና ተጠራጣሪ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ዜጎች በመደንገጥና በመሸበር ስደትን አማራጭ ያደርጋሉ፡፡ ከሰሞኑ ባለው ጦርነትም ከስድስት ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን ማቅናታቸውን ከሱዳን የሚወጡ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡ ይህን ዜጋ ከጦርነቱ በኋላ ዳግም ወደ ቀየው ለማስፈር እና ለማቋቋም ከፍተኛ የሆነ በጀት ይፈልጋል፡፡

በጦርነት ከሚጠፋው የሰው ሕይወት ባሻገር በአካባቢው ቀድመው ተገንብተው የነበሩ የመሠረተ ልማቶችን ማውደሙ የማይቀር ነው፡፡ ይህን የመሠረተ ልማት ከጦርነት በኋላ ዳግም ለመገንባት ተጨማሪ የካፒታል በጀት መያዝ ግድ የሚል  ነው፡፡ ምናልባት የሚወድሙት ተቋማት እና የመሠረተ ልማቶች የተራዘመ ጊዜን የማይሰጡ ከሆነ በመንግሥት ቀጣይ ዓመት በጀት ላይ ከፍተኛ መጨናነቅን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡

ጦርነት በተደረገበት  አካባቢው ቀድሞ የነበረው የመዋዕለንዋይ ፈሰት ረዘም ላለጊዜ ይዳከማል፡፡ ባለሀብቶች በተራዘመ  ጊዜ አመኔታ ፈጥረው እስኪመጡ ድረስ በአካባቢው ያለው ወጣት ሥራ አጥ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ አሁን ላይ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ራስ ምታት ለሆነው  የሥራ አጥነት  ተጨማሪ ቁጥር የሚጨምር ነው፡፡ ይህም ለአካባቢው የተራዘመ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ እየተፈጠሩ ከነበሩ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ጋር ያሁኑ ጦርነት ተዳምሮ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለተራዘመ ጊዜ እንዳይጎዳው ትልቅ ስጋት አለኝ፡፡

ምን ይበጃል?

ቀደም ብዬ ለመጥቀስ የሞከርኮቸው ነጥቦች ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተቻለ ፍጥነት ጦርነቱን ማጠናቀቅ ይገባል፡፡ ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር የሚጠፈው የሰው ሕይውት እየጨመረ በኢኮኖሚው ላይ የሚደርሰውም ጉዳት ከፍ እያለ ይመጣል፡፡ በመሆኑም የጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉት ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ ይገባል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት በሚፈጠር ጉዳት ምክንያት እየጨመረ የሚሄደውን የደም ፍላጎት ለመደጎም አሁን የተጀመረው የደም ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

በቀጣይ በውጭ መዋዕለንዋይ ፍሰት ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ለመቀነስ መንግሥት ለተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጦርነቱ ሕግን የማስከበር ሥራ አንድ አካል መሆኑን እና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ በተደጋጋሚ መግለጽ ያስፈልጋል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ በሚል እየተሰበሰቡ ያሉ ድጋፎችንም ይበልጥ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሕዝብ የሚሰበሰብ ድጋፍ በተወሰ መልኩም ቢሆን መንግሥት ሊገጥመው የሚችለውን የበጀት እጥረት መድፈን ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የሕዝቡ የተነሳሽነት ስሜት ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ትልቅ አቅም በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በወሳኝ ተቋማት ላይ በተቻለ መጠን ጥብቅ የሆኑ ጥበቃዎችን ማድረግ ይገባል፡፡ ይህ በቀጣይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማቃለል ትልቅ አቅም አለው፡፡

 

 

November 16, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *