“ይህ መንግሥት ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደሚከተል ግልጽ አይደለም” | ካሱ ኀይሉ
ኢኮኖሚ

“ይህ መንግሥት ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደሚከተል ግልጽ አይደለም” | ካሱ ኀይሉ

እንግዳችን አቶ ካሱ ኀይሉ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክ ፖሊሲ ማኔጅመንት አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በእንጅባራ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ መምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ከሲራራ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሲራራ፡- ብዙ ሰዎች በሥልጣን ላይ ያለው ኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የለውም ይላሉ፡፡ እርስዎ እንደ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ባለሙያነትዎ መንግሥት የሚከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ካሱ፡- መንግሥት በሚከተለው ፖሊሲ ላይ በግልጽ ይህን የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም እንከተላለን፣  የፖሊሲያችን ግብ ይኼ ነው በሚል የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ርዕዮተ ዓለም ላይ አናተኩርም የሚል አቋም ነው በመንግሥት በኩል ያለው አቃም፡፡ መደመር የሚባለው “ፍልስፍና”ም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጥሩ ጥሩውን እንወስዳለን፣ የማያሠራንን እንተዋለን የሚል አቋም አለው፡፡  እኛ ካፒታሊስት ነን፣ የልማታዊ መንግሥት እሳቤን እንከተላለን የሚል ዓይነት አቋም በመንግሥት አምብዛም አይታይም፡፡ ምናልባት እንደ ርዕዮተ ዓለም ከተገለጸ ‹ፕራግማቲክ› ነን የሚሉ ይመስለኛል፡፡

በሌላ በኩል ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ በመንግሥት ሥር የነበሩ ተቋማትን ወደ ግል ለማዛወር የተጀመረ እንቅስቃሴ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ እንግዲህ ከነጻ ገበያ አስተሳሰብ ጋር የሚገናኝ ነገር ነው፡፡ የአክሲዮን ገበያ ለማቋቋም ተመሳሳይ ሥራዎች ተጀምረው ነበር፡፡ የውጭ ባንኮችን ለማስገባትም ጅማሮዎች ነበሩ፡፡ በእርግጥ እነዚህ ጅምር ሥራዎች ላይ መንግሥት እየቆየ ለዘብተኝነቱን አሳይቷል፡፡ ቀደም ተብሎ የተጀመሩት ሥራዎች አብዛኛዎቹ  ኢኮኖሚውን ‹ሊብራላይዝድ› ለማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ብዙው እንቅስቃሴ ተዳክሟል፡፡ ይህ መሆኑ የመንግሥትን የፖለሲ አቅጣጫ ግራ የሚያጋባ አድርጎታል፡፡  በእኔ በኩል እስካሁን ባየነው ሁኔታ ይህ መንግሥት ከቀድሞው የኢሕአዴግ መንግሥት የተለየ ሐሳብ አለው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ድሮም የነበረው በአመዛኙ ግራ የተጋባ ነገር ነው፣ አሁንም ያው ነው፡፡

በግልጽ የሚታወቅ የርዕዮተ ዓለም እና የፖሊሲ አቅጣጫ ቢኖር መልካም ነው፡፡ በእርግጥ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያለውን ሁኔታም ብናይ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ወዲህ ርዕዮተ ዓለም ያን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር አልሆነም፡፡ እንደሁኔታው የሚጠቅመውንና የሚያዋጣውን መጠቀም ነው የሚያዋጣው የሚል ነገር አለ፡፡ ሆኖም ከርዕዮተ ዓለም መለስ ባለ በመስመር ደረጃ መንግሥት የሚከተለው አቅጣጫ መታወቁ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ ላይ ትልቅ ጉድለት ይታያል፡፡

ሲራራ፡- መንግሥት አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የዐሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህንን እርስዎ እንዴት ነው የሚያዩት?

አቶ ካሱ፡- በተደጋጋሚ አገር በቀል ኢኮኖሚ ሥርዓት ሲባል እንሰማለን፡፡ ነገር ግን የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለው እስካሁን በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ ምናልባት የእኛን ውስጣዊ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚያዊ አቅማችንን፣ የሕዝብን አስተሳሰብን  ያገናዘበ የኢኮኖሚ መስመር የሚለው ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን አገር በቀል በሚል ስያሜ ይገለጻል ወይ? የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር በተገናኘ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ሲደርጉ ቆይተዋል፡፡ የብድር ሁኔታን ለማቃለል፣ የፋይናንስ ተቋማቱን ለማዘመን የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ መንግሥት በጎን ከተለያዩ የዐረብ አገሮች እና ከምዕራብ ዓለም የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ መጠን ያላቸው ብድሮችን ወስዷል፡፡ እነዚህ ብድሮች በምን መሠረት ላይ እንደተወሰዱ በግልጽ መቀመጥ ቢኖርበትም አልተደረገም፡፡ አገሪቱ የምትበደረው ብድሩን ለመክፈልም ጭምር ውል ገብታ ነው፡፡ ይህ እስከሆነ ድረስ  ለምን እንደምንበደር እና ከማን መበደር እንዳለብን ከብድር ሥርዓቱ አስቀድሞ ክርክር መደረግ አለበት፤ አልተደረገም፡፡ በየጊዜው ብድር ተበደርን እንጂ ብድሩ ምን ላይ ዋለ? ምን ውጤት አመጣ? የሚለው ሲገለጽ አይሰማም፡፡

ሲራራ፡- በዐሥር ዓመቱ መሪ ልማት ዕቅድ ላይ የሚያነሱት ችግር ወይም ጉድለት አለ?

አቶ ካሱ፡- ከአሳታፊነት አንጻር ዕቅዱ ሰፊ ክፍተት እንዳለበት አይተናል፡፡ በዚህ አገር ፖለቲካው እና ኢኮኖሚ በእጅጉ የተጋመደ ነው፡፡ ዕቅድን የአንድ ፓርቲ ሰዎች በር ዘርግተው ከሠሩት ዕቅዱ የዚያ የፖለቲካ ፓርቲ እንጂ የአገሪቱ አይሆንም፡፡ የዐሥር ዓመት ዕቅድ ሲባል የሁለት ምርጫ ጊዜን የያዘ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕቅድ የአንድ ድርጅት አባላትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አካላትን ያሳተፈ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪ ለሕዝቡ ቀርቦ በአግባቡ ውይይት መደረግ አለበት፡፡ ከዚያ አንጻር የዐሥር ዓመት ዕቅዱ ላይ ጉድለት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡

የረጅም ጊዜ ዕቅድ ሲዘጋጅ ሕዝቡን ማነቃቃት የሚችሉ የመዳረሻ ግቦች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ይህ መነሳሳት የሚመጣው ደግሞ ዕቅዱን ሕዝብ ሲያውቀው፣ ሲወያይበት እና የእኔ ብሎ ሲቀበለው ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የዕቅድ ዝግጅቱ አሳታፊ አልነበረም፡፡

ሲራራ፡- እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ትልቁ የዕድገት ማነቆ የፋይናንስ አቀርቦት ችግር ነው፤ ስለሆነም የባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት እየተበራከቱ መምጣት ኢኮኖሚው በጤናማ መስመር ላይ ለመሆኑ አመላካች ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እየተቋቋሙ ባሉት ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ላይ ያለዎ አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ካሱ፡- እውነትም የፋይናንስ አቅርቦት መሠረታዊ ነው፡፡ ብዙ ባንኮች እና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ያስፈልጋሉ የሚለውም ተገቢ አስተያየት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የፋይናንስ ዘርፍ አድጓል፣ ትልቅ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ካሉት ኢኮኖሚያዊ መለኪያዎች አንጻር ስንመለከተው በዘርፉ ላይ ዕድገቶች ቢኖሩም ዕድገቱ ግን ጨርሶ አጥጋቢ አይደለም፡፡ የዘርፉ መገለጫም ቢሆን ከሌላው ዓለም የተለየ ነው፡፡ ክፍት የሆነ ሥርዓት አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች፣ የማይክሮ ፋይናንስ ዘርፎች ናቸው ያሉት፡፡ እነዚህ ተቋማትም ቢሆን ሰፋ ባለ መልኩ ኢንቨስትመንትን (የመዋዕለንዋይ ፍሰትን) የማስፋፋት ኀላፊነታቸውን በአግባቡ እይተወጡ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ዋና ዓላማ ስለ ኢንቨስትመንቱ መረጃን በማሰራጨት የቢዝነሱን እንቅስቃሴ ቅርጽ ማሳያት ነው፡፡ በአጠቃላይ ዘርፉ እንደ ዘርፍ ብዙ ያላሟላቸው እና ሊያሟላቸውን የሚገቡ በርካታ የቤት ሥራዎች አሉ፡፡ ለአብነት የባንክ ዘርፉ ያለበትን ሁኔታ ብናይ የባንኮች ቅርንጫፍ ካለው ሕዝብ ቁጥር አንጻር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካልሆነ በስተቀር የአብዛኛው የግል ባንኮች ቅርንጫፍ መጠን  አነስተኛ ነው፡፡

ከእኛ አገር ባንኮች ብድር የማግኘት ዕድል በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ከአጠቃላይ ሕዝብ ቁጥር አንጻር የሚሰጠው የብድር መጠን በጣም ጥቂት ነው፡፡ አብዛኛው ባንክ ከ85 በመቶ በላይ ብድር  የሚሰጠው መያዣን ተጠቅሞ ነው፡፡ የሚጠየቀው መያዣም ቢሆን የብድሩን እጥፍ በላይ  ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በአገሪቱ ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ሕዝቡን ከድህነት ከማውጣት፣ አገሪቱን በሰፋፊ የመዋዕለንዋይ ፍሰት እና ዕድገት ከመመምራት አንፃር የሚጠበቅበትን አስተዋጽዖ ከመወጣት አንጻር  ብዙ ጉድለቶች እንዳሉበት፡፡  ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዘርፉ ላይ መሻሻሎች እንዳሉ አይካድም፡፡

ሲራራ፡-  በእርስዎ ግምገማ የፋይናንስ ዘርፉ ደካማ እንዲሆን ያደረገው መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ካሱ፡- ምዕራባውያኑ በፋይናስ ዘርፍ ላይ የራሳቸው የሆነ ዕይታ አላቸው፡፡ የባንክ ዘርፉን የሚመሩት ‹ሊብራላይዝድ› በሆነ መንገድ ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ለዓለም ዐቀፍ ገበያ እና ለዓለም ዐቀፉ ቢዝነስ እንቅስቃሴ ራሳቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው የሚል አቋም አላቸው፡፡ከኢሕአዴግ ቀደም ብሎ በሥልጣን ላይ የነበረው የደርግ ሥርዓት የሚከተለው የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም የዕዝ ኢኮኖሚን ነበር፡፡ ሥርዓቱ የግል ባንኮችን ሆነ የውጭ ባንኮችን በአገር  ውስጥ ገብተው እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ አልነበረም፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም  የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በባንክ ዘርፍ ላይ እንዲሳተፉ የፈቀደ ቢሆንም የውጭ ባንኮች ግን ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክል የፖሊሲ አቅጣጫን ይዞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡

በእኔ እምነት የፋይናንስ ዘርፉ ሙሉ በሙሉ ለውጭ ተቋማት ከመዝጋት ይልቅ የተወሰነ  መልኩ ከፈት ቢል የተሻለ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም ዘላለም ራሳችንን ከዓለም ዐቀፍ ገበያው ዝግ አድርገን አንቀጥልም፡፡ በተወሰ መልኩ በራችንን ገርበብ እያደረግን የውጭውን ዓለም መለማመድ መጀመር እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ ይህ ባለፉት 30 ዓመታት አልተሞከረም፡፡ አንደኛው ችግር ይህ ነው፡፡

የአክሲዮን ገበያ እስካሁን ድረስ በዚች አገር አለመጀመሩ ለአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፈ አለማደግ  ሌላው ምክንያት ነው፡፡ የድርሻ ገበያ ቢኖር አዳዲስ የመዋዕለንዋይ ፍሰት የሚፈጠርበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ የቢዝነስ እንቅስቃሴ ሲሰፋ ተወደደም ተጠላ የፋይናንስ ዘርፉ ማደጉ አይቀርም፡፡ አክሲዮን ገበያ በዚህ አገር ላለመቋቋሙ ደግሞ መሠረታዊ ምክንያት የፖሊሲ ድክመት ነው፡፡

የአገሪቱ አብዛኛው የፋይናንስ እንቅስቃሴ በመንግሥት ተቋም መያዙ ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ የአገሪቱን 60 በመቶ የፋይናንስ እንቅስቃሴ የተያዘው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ የሚያሳየው የግል የፋይናንስ ተቋማት ሊወዳደሩበት የሚችል ነጻ የውድድር ሜዳ እንደሌለ ነው፡፡ በዚህ አገር ትልቁ ሀብታም መንግሥት ነው፡፡ ይህ ትልቅ ሀብት እስካሁን ወደ ግል የፋይናንስ ተቋማት የሚሄድበት ዕድል አለተፈጠርም፡፡ የመንግሥት ሁሉም ዓይነት የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚደረገው በራሱ በየንግድ ባንክ በኩል መሆኑ ፍትሐዊ ውድድርን የሚያበረታታ አልነበረም፣ አሁንም አይደለም፡፡  የንግድ ባንክም ቢሆን ቅርንጫፍን ከማስፋፋት ውጪ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማምጣት፣ አዳዲስ የክፍያ ሥርዓትን ከመፍጠር፣ አዳዲስ የብድር አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ሰፊ ክፍተቶች ያሉበት ባንክ ነው፡፡

የባንኮች የብድር ሥርዓት በተያዥ የሚሰጥ መሆኑ አብዛኛው ሕዝብ በድህነት ውስጥ የሚኖር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙሃኑ የብድር ሥርዓቱ ተጠቃሚ መሆን አልቻለም፡፡ በኢትዮጵያ ከ23 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ነው፡፡ ድሃው ማኅበረሰብ ተበድሮ መሥራት ካልቻለ ድህነቱን ይዞ መሄድ ግዴታ ይሆንበታል፡፡ ከወራት በፊት አርብቶ አደሮች አንስሳቶቻቸውን አስይዘው መበደር እንደሚቻሉ የተገለጸ ቢሆንም እስካሁን ወደ ተግባር አልተቀየረም፡፡

ሲራራ፡- በአገራችን በኢኮኖሚስቶችና በፖለቲካ ሰዎች መሀከል “የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ወደ አገር ውስጥ መግባት አለባቸው፣ የለም መግባት የለባቸውም” የሚል ክርክር እንዳለ ይታወቃል፡፡ በእርስዎ አስተያየት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በሩ ክፍት መደረጉ ያለው ፋይዳና የሚያስከትለው ችግር ምንድን ነው?

አተ ካሱ፡- የውጭ አገር ባንኮች ከገቡ የአገር ውስጥ ባንኮችን ከሥራ ውጭ አድርገው ተቋማቱ በፈለጉት መንገድ እየሠሩ ኢኮኖሚውን በግዞት ውስጥ ይከታሉ የሚለውን ስጋት ትክክል ነው፡፡ እኔም ብሆን በተወሰነ መልኩ እጋራዋለሁ፡፡ ግን በአንድ ወገን ደግሞ ራሳችን ከዓለም ዐቀፉ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ለዘላለሙ አግለን መቆየት እንችላለን የሚል እምነት የለኝም፡፡ እስካሁን በመጣንበት ሁኔታ መቀጠል አንችልም፡፡ ውድድር መኖር አለበት፡፡ ሕዝቡም ከባንኮች ውድድር መጠቀም ይገባዋል፡፡ ባንኮችም ቢሆኑ በመንግሥት ጥበቃ ስር ሆነው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን አይችሉም፡፡ ራሳቸውን ችለው መወዳደርና በውድድሩ ውስጥ አሸናፊ ሆነው መውጣት ይገባቸዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ባንኮችን ከዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጋር ተወዳድረው ማሸነፍ የሚችሉበትን መደላድል መፍጠር ይገባል፡፡ ሙሉ በሙሉ ባይከፈት እንኳን የተወሰኑ መመሪያዎችን እና ደንቦችን እያስቀመጥን የውጭ ተቋማት የሚገቡበት ዕድል መፈጠር አለብን፡፡ እንደ አማራጭ የውጭ ተቋማት እና የአገር ውስጥ ተቋማት በጋራ ባንክ የሚያቋቁሙበትን ሁኔታ መፍጠር ቢቻል ለዘርፉ የተሻለ ዕድል ይሰጣል፡፡

ዛሬ ዓለም በፋይናንስ ዘረፉ ላይ ከፍተኛ እምርታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ባንኮች የኢንፎርሜሽን ኮምኒኬሽን ቴክኖሎጂውን በሚገባ በመጠቀም የሚሰጡት አገልግሎት በጣም አስደናቂ ሆኗል፡፡ ዓለም ከደረሰበት ደረጃ አንጻር ሲታይ እኛ ያለንበት ሁኔታ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የእኛን ባንኮች ከናይጀሪያ፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ባንኮች ስናወዳድራቸው እንኳ በጣም በሚያሳዝን ደረጃ ላይ ነው የምንገኘው፡፡

ስለሆነም ወደዚህ የቴክኖሎጂ ዓለም ወደፊት መግባታችን ግዴታ እስከሆነ ድረስ ልምምዱ አሁን መጀመር አለበት፡፡ እንደሚታወቀው ባንኮቻችን ለአስቀማጩ የሚሰጡት የወለድ መጠን በአገሪቱ ካለው የዋጋ ንረት መጠን አንጻር አክሳሪ ነው፡፡ ባንኮቻችን ከሚሰጡት ብድር፣ በኢኮኖሚ ውስጥ ሊወጡ ከሚገባቸው ሚና አንጻር፣ ዓለም ዐቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አንጻር የውጭ ተቋማትን በከፊል ወደ ገበያው መግባታቸው በጣም አንገብጋቢ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂ እንዲኖር ከተፈለገ ከዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በተወሰነ መልኩም ቢሆን ውድድር መጀመር አለበት፡፡ የግል ባንኮችን ለውድድር ተጋላጭ እያደረግናቸው በሄድን ቁጥር አሠራራቸውን ሳይወዱ በግድ እያዘመኑ ይሄዳሉ፡፡ የሚችለው ይዋኛል፣ የማይችለውና ቆሞ-የቀረው ይሰምጣል፡፡ እዚህ ላይ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት የውጭ ተቋማት ሲገቡ የአገር ውስጥ ተቋማትን ህልውና በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ለማደግና ለመወዳደር ጥረት የሚያደርጉትን ጭምር የውጭው ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም ሊደፈጥጣቸው አይገባም፡፡ በጥቅሉ ሚዛኑን ጠብቆ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፣ ይገባልም፡፡

ሲራራ፡- ቀደም ሲል ለባንኮቹ አለማደግ በምክንያትነት የጠቀሷቸው አብዛኛዎቹ ምክንያቶች በአገሪቱ ካለው የኢኮኖሚ ሥርዓት ድክመት ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ በባንኮቹ በራሳቸው በኩልስ መነሳት ያላባቸው ድክመቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ካሱ፡- ባንኮቻችን ብድር በመስጠት አብሮ በመሥራት በኩል የሚመርጡት ዘርፍ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ለሚችለውን አይደለም፡፡ ባንኮቻችን  በረጅም ጊዜ ትርፍ ለሚያመጡ ዘርፎች ማበደር የሚያስችል በራስ መተማመን አልፈጠሩም፡፡ ከአገሪቱ የባንክ ዘርፍ በግል ባንኮች የተያዘው ድርሻ 40 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ቀሪው 60 በመቶ የተያዘው በመንግሥት ባንክ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የግሉ ባንክ ጠንካራ መሠረት እንደሌለው ነው፡፡ ይህ መሆኑ ተቋማቱ ሰፊ አቅም እና ጊዜ ለሚፈልጉ የኢንዱስትሪው እና የግብርናው ዘርፍ  ብድር የመስጠት ፍላጎት እንዲያጡ አድርጎል፡፡ ይህ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ከዚያ ባለፈ ባንኮች ድረሻቸውን በመሸጥ አዳዲስ የካፒታል አቅም መፍጠር ላይ ከፍተኛ ችግር ይታይባቸዋል፡፡ ሰፊ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው አካላት የባንኩን ሰፊ ድርሻ በብቸኝነት የሙጥኝ የማለት ፍላጎት ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህ መሆኑ ባንኩ አዳዲስ የካፒታል አቅፍ በመፍጠር ዕድገት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ደረሰበትን ደረጃ አይተን እኛ የምንገኝበትን ሁኔታ ስንገመግም እጅግ በጣም ወደ ኋላ ቀርተናል፡፡

ሲራራ፡-  የፋይናንስ ዘርፉን በበላይነት እየመራው ያለው ብሔራዊ ባንክ የባንክ ዘርፉን ምን ያህል በአግባቡ እየመራው ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ ካሱ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕወሓት በሥልጣን ላይ  በነበረበት ጊዜ  በተለይ በውጭ ምንዛሪ ላይ ቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርገው ለራሱ ሰዎች ነበር፡፡ በብድር ሥርዓትም የነበረው ነገር ተመሳሳይ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የድርጅቱ ጠባብ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከየትኛውም የፖለቲካ አሻጥር ነጻ እና ገለልተኛ መሆን አለበት፡፡  ተቋሙ በነጻ ባለሙያዎች መመራት ቢኖርበትም ይህን ዕድል አላገኘም፡፡ ባንኮችን ሽባ ሲያደርግ፣ ባንኮች የሚያመጧቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ተግባር እንዳያወርዱ መሰናክል ሲሆን የቆየ ተቋም ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ያለው ችግር በአገሪቱ የወጪ ገቢ ንግድ ላይ የራሱን ጫና ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ባለሙያዎችን አካቶ፣ አገራዊ ርዕይ ይዞ ሲሠራ ነበር ለማለት ይከብደኛል፡፡

ለብሔራዊ ባንክ አመካሪ ተብለው የሚቀጠሩ በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የሚሠሩ ሰዎች አንብዛም ድምጽ አልነበራቸውም፡፡ አሁን ላይ በአገር ውስጥ እና በውጭ ተቋማት ውስጥ ያሉ  ሰፊ ልምድ እና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች የሚሳተፉበት  የኢኮኖሚ ምክር ቤት ተቋቁሟል ይህ ምክር ቤት ለውጦችን ያመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሲራራ፡-  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚቋቋሙ የግል ባንኮች ቁጥር ቢጨምርም አደረጃጀታቸው ግን ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት እያደረጉ መጥተዋል፡፡ ብዙ ሰዎች የፋይናንስ ተቋማቱ ብሔርና ሃይማትን መሠረት አድርገው መደራጀታቸው አግባብ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ካሱ፡- የግል ባንኮች መብዛት ዘርፉ ላይ ችግር አይፈጥርም፡፡ እንዲያውም ዘርፉን ይበልጥ ያነቃቃዋል፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ የባንክ ተጠቃሚ የሆነው ማኅበረሰብ ከጠቅላላው ሕዝብ አንጻር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ አሁንም ቢሆንም የባንክ ተደራሽነቱ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የአማራ ባንክ ከ9 ቢሊዮን  ብር በላይ ሀብት መሰብሰብ የቻለው በአገሪቱ ያልተነካ እምቅ አቅም በመኖሩ ነው፡፡ ሌላም ባንክ ሕዝባዊ መሠረት ይዞ ቢመጣ ከዚህ የተሻለ አቅም ሊያሳየን ይችላል፡፡ እንደ አዲስ ተቋቁመው ወደ ዘርፉ የሚገቡ ባንኮች ከምንም በላይ ለአዳዲስ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ለአዲስ የአሠራር ስርዓት ትኩረት አድርገው መሥራት ይገባቸዋል፡፡ የአዳዲስ ባንኮች መጨመር በዘርፉ ውስጥ ያለውን ውድድር ይጨምረዋል፡፡ በዚህም ለተገልጋዩ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ፡፡ አሁን ባላው ሁኔታ ያሉት የግል ባንኮች ተደምሮ ያላቸው የፋይናንስ ድረሻ 40 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የግል የፋይናንስ ዘርፉ እስካሁን አንዳልተነካ ነው፡፡

በቅርቡ የአማራ ባንክ ተቋቋሟል፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ የቁጠባ አቅም ከሚሰበስብባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ አማራ ክልል ቢሆንም ሕዝቡ ግን የብድር ተጠቃሚ እንዳይሆን ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ባንክ ይዞ የተቋቋመው የአማራ ባንክ ብዙ ነገሮችን ይቀይራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ ቀደም በግልጽ ባይነገርም አብዛኛው የቢዝነስ  እና የባንክ እንቅስቃሴ ሲከናወን የቆየው ብሔርን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ ኢሕአዴግ አገሪቱን በብሔር አደራጅቶ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ብዙው እንቅስቃሴ ብሔርን መሠረት የደረገ ነው፡፡ በአንዳንድ ተቋማት የሠራተኛ ቅጥር ለማድረግ፣ ብድር ለማግኘት ብሔር መሠረታዊ ጉዳይ  ሆኗል፡፡ በባንክ ዘርፉ ላይ የሚታየው ብሔርን መሠረት አድርጎ የመደራጀት ችግር የሚፈታው እንደ አገር የተዋቀርንበት መሠረት መሻሻል ሲችል ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ወደ ፊት ይህ ሁኔታ በሕገ መንግሥት ፣ በስርዓት እና በተቋም ሲሻሻል የብሔረሰብ ስም የያዘ የፋይናንስ ተቋም ማቋቋም አይቻልም የሚል ሕግ ሊፈጠር ይችላል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  በብሔር ስም የሚደራጀው የባንክ ተቋም የፖለቲካው ውጤት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በፖለቲካው ላይ ያለው የብሔር አደረጃጀት እስካልተቀየረ ድረስ የፋይናንስ ስርዓቱ ላይ ያለው የብሔር አደራጀትም አብሮ ይቀጥላል፡፡ በበኩሌ በመርህ ደረጃ ወደፊት ቢዝነስ ተቋማትም ሆኑ የፖለቲካ  እንቅስቃሴ ከብሔርና ሃይማኖት መሠረት ነጻ መሆን እንዳለባቸው በሕግ ተሰምሮ መቀመጥ እንዳለበት አምናለሁ፡፡ በአሁን ግን በተግባር ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው፣ ማኅበራዊ እንቅስቃሴው ሁሉ ብሔረሰባዊ መሠረትን ይዟል፡፡

ሲራራ፡- የባንኩ ዘርፍ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት መፍትሔው ምንድን ነው?

አቶ ካሱ፡- ከአመለካከት ነው የሚጀምረው፡፡ በቅድሚያ መንግሥትም ሆነ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች የአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሞተር መሆናቸውን መገንዘብ እና ለዘርፉ ዕድገት ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው፡፡ ባንኮችም ተቀማጭን ወደ ብድር እያገላበጡ ብቻ መቆየት የለባቸውም፡፡ ወደ ለአምራች ዘርፉ ለግብርናው፤ ለኢንዱስትሪውን መነቃቃት ትኩረት መስጠት  አለባቸው፡፡

የመንግሥት አብዛኛው የገንዘብ እንቅስቃሴ እየተከናወነ ያለው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ነው፡፡ የግል ባንኩ አቀም እንዲያገኝ ከተፈለገ መንግሥት የተወሰነውን የገንዘብ እንቅስቃሴ ውድድርን መሠረት ባደረገ መልኩ በተወሰነ መልኩ ወደ ግል ማዛወር ይኖርበታል፡፡ መንግሥት የግል ባንኩ የተሻለ መተማመን እንዲኖረው ለተመረጡ ዘርፎች ብድር ለሚሰጡ ባንኮች ማበረታቻ የሚሰጥበት ሁኔታ ቢኖር የተሻለ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በተጨማሪ የግል ባንኩ የማይደፍራቸውን መስኮች በራሱ ብድር በመስጠት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ማነቃቃት ይኖርበታል፡፡

በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይም መሻሻሎች እንዲኖሩ በተመጠነ መንገድ የውጭ ተቋማት ወደ ዘርፉ እንዲገቡ መፍቀድ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው፣ ከብድር አሰጣጥም ጋር በተገናኘ አሁን ያለው የመያዣ (ኮላተራል) አሠራር  የሚሻሻልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ ያለው ማኅበረሰብ ብድር አግኝቶ ሕይወቱን የሚቀይርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ባንኮች ከመንግሥት ጋር ጥምረት ፈጥረው የተበዳሪዎችን የቢዝነስ እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተሉ ያለ ተያዥ የሚያበድሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ በተለይ ለአነስተኛ ግብርና ለኢንዱስትሪዎች ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይገባቸዋል፡፡

 

 

 

March 26, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *