በ1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ በአገሪቱ የነበረው የግል ክፍለ ኢኮኖሚ በጣም ደካም ነበር፡፡ ለነገሩ አሁንም ደካማ ነው። ይህም በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ጉድለቱን ለመሙላት ደርግን አስወግዶ ወደ መንበረ ሥልጣኑን የጨበጠው ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ማለትም ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን እንደ ቅደም ተከተላቸው ትዕምት (ኤፈርት)፣ ጥረት፣ ዴንሾ፣ ወንዶ የመሳሰሉ የአደራ (የኢንዶውመንት) ድርጅቶችን መሠረቱ፡፡ እነዚህ የአደራ ድርጅቶችም በግለሰብ ደረጃ ሊሞከሩ የማይችሉ እንደ መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ጉና የንግድ ሥራዎች፣ አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግን፣ አምባሰል የንግድ ሥራዎች፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ሱር ኮንስትራክሽን ወዘተ… የመሳሰሉ ግዙፍ የቢዝነስ ተቋማትን በሥራቸው አቋቁመው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ከኅዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ግን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የ34 ድርጅቶችን በባንክ ያላቸውን ገንዘብ ጨምሮ [የድርጅቶችን] የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ማገዱን አስታውቋል፡፡
እነዚህ በአደራ (ኢንዶውመንት) ስም የተቋቋሙ ድርጅቶች ምንም እንኳን ለአገር ዕድገት እና ልማት የማይናቅ አስተዋጽዖ ቢኖራቸውም በኢኮኖሚው ላይ የፈጠሩት አደጋ ግን ከጥቅማቸው ጋር ፈጽሞ የሚመጣጠን አይደለም፡፡ እነዚህን ድርጅቶች የሚመሯቸው እና የሚጠቀሙባቸው ዜጎች ሳይሆኑ በጣም ጥቂት ባለሥልጣናትና የፖለቲካ ካድሬዎች ነበሩ፡፡ ለአብነት የኤፈርትን ሁኔታ ብንወስድ፣ የተቋሙን ሀብት ጥቂት ግለሰቦች እንደ ግል የባንክ ሒሳብ ተቀማጫቸው ሲያንቀሳቅሱት ነው የቆዩት፡፡ ድርጅቱ የትግራይ ሕዝብ ነው ይባል እንጅ ሰፊውና ድሃው የትግራይ ሕዝብ ግን እስካሁን በድርጅቱ ተጠቃሚ ሆኖ አያውቅም፤ ለሠራተኞች ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውጪ፡፡ ድርጅቶቹ በሕዝብ ስም እና ለሕዝብ የተቋቋሙ ናቸው፤ ሕዝቡን ከድህነት ለማውጣት እና ሁለንተናዊ ልማት ለማምጣት እንደተቋቋሙ በተደጋጋሚ ቢነገርም ለምሳሌ ትዕምት ሌላው ቀርቶ የመቀሌ ከተማን የውኃ ችግር የሚፈታ አንዳችም ሥራ አልሠራም፡፡ በዚህ ምክንያት ተቋሙ አለ የሚለውን ሕዝባዊ መሠረቱን አጥቶ የጥቂት ግለሰቦች እና አመራሮች መጠቀሚያ መሆኑ አንዱ እና ዋነኛው ድክመቱ ነው፡፡ የዚህ ድርጅት ሀብት እንዴት በጥቂት ሰዎች እንደሚዘወርና አንዳንዶችን ባንድ ሌሊት እንዴት ሚሊየነር እንዳደረገ የአቶ ገብሩ አሥራትና የኤርሚያስ ለገሠን መጻሕፍት ማንበብ ብቻ በቂ ነው፡፡ በእርግጥ በእነዚህ ድርጅቶች ላይ የተሠሩ በርካታ ጥናቶችም አሉ፡፡ በየመገናኛ ብዙሃኑም አገር ወዳድ ዜጎች ስለነዚህ ድርጅቶች አደጋነት አበክረው አሳስበዋል፤ የሚሰማቸው ባያገኙም፡፡
ሁለተኛው ድክመት በአደራ የሚተዳደሩት ተቋማት ከመንግሥት ጋር ልክ ያለፈ ጋብቻ መፈፀማቸው እና ሌላው የግልም ይሁን የፌዴራል መንግሥት ተወዳዳሪ ዘርፍ እንዳይላወስ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የተቋማቱ ባለቤቶች በሥልጣን ላይ ያሉ ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች መሆናቸው ነው፡፡ የተቋማቱ መሪዎች ለተራዘመ ጊዜ ከመንግሥት ሥርዓት ውስጥ አለመውጣታቸው፣ ከግል ዘርፉ ባሻገር የመንግሥት ድርጅቶችንም ሳይቀር ፍትሐዊ ባልሆነ ውድድር እንዲጎዱ በር ከፍቷል፡፡ ለአብነት ብናነሳ አቶ ስዩም መስፍን የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ የቦርድ አባል ነበሩ፡፡ እርሳቸው እዚያ ውስጥ በመኖራቸው ምክንያት የሙገርን ሲሚንቶ ምርት እንዲዳከም በማድረግ፣ ድርጅቱን ላላስፈላጊ ዕደሳ በመዝጋት፣ የሲሚንቶን ዋጋ በማስናር የመሶቦ ሲሚንቶ በገበያው ላይ በስፋት እንዲሸጥና ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዲይዝ (እስከ 40%) ይደረግ ነበር፡፡ ጅንአድና የመንግሥት ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችም በዚህ መንገድ ነው የተዳከሙት፤ እንዳንዶችም የጠፉት። እንዲህ ዓይነት አሻጥርና ኢፍትሐዊ ተወዳዳሪነት በመኖሩ ምክንያት መንግሥትም የግል ዘርፉም በገበያው ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ሲደረግ ነው የቆየው፡፡ ፓርቲውንና የፓርቲ ኀላፊዎችን ጡንቻም ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ አፈርጥሟል። ለዚህም ቁልፉ ነገር የተቋማቱ መሪዎች መንግሥት በመሆናቸው የሚወጡ ፖሊሲዎች ከሌላው በተሻለ እነሱን ብቻ መርጦ እንዲያስተናግዱ ይደርግ ስለነበረ ነው።፡
ከፖሊሲ ባሻገር የትዕምት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የሚወስዱትን ብድር የተበላሸ ብድር ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ወደ ልማት ባንክ ተዛውሮ ሳይከፈል እንቀረ ይታወቃል፡፡ ከ1996-1997 ዓ.ም. የውጡትን የሪፖርተር ጋዜጣ ተከታታይ ዘገባዎች ያነበበ ሰው ይህ ጉዳይ ፍንትው ብሎ ይታየዋል፡፡ በበኩሌ ተቋማቱ ቀረጥም በአግባቡ መክፈላቸውን እጠራጠራለሁ፤ በከፋይነታችን ተሸላሚ ነን ቢሉም ቅሉ። እነዚህ ተቋማት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚገዛው ሕግ ሳይወጣ ሕገ-ወጥ ሆነው መመሥረታቸውን ትተን፣ ከባንክ በተዘረፈና ለተራበ ከተስጠ እርዳታ ተነጥቀው የተጀመሩ መሆኑንም ወደ ጎን ብለን፣ በ1990ዎቹ ከነበራቸው መነሻ ካፒታል ከ70-80% የሚሆነው ከብሔራዊ ባንክ ሕግ ተጥሶ ያለመያዣ ከመንግሥት ባንክ በተወሰደና በኋላም በተበላሸ ብድር ስም ወደ ልማት ባንክ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ትዕዛዝ ተዛውሮ ሳይከፈል እንዲከስም የተደረገ ነው፡፡ በሕጉ መሠረት አንድ ጊዜ ብድር ያበላሸ ተቋም ድጋሚ ብድር እንዳይወስድ የሚከለከል ቢሆንም እነዚህ ተቋማት ግን በተደጋጋሚ ብድር እንዲወስዱ ይደረግ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይ ለመንግሥት ባንኮች እንደ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ያሉ ተቋማት ሳይቀሩ እስኪያስጨንቃቸው ድረስ የባንኮች ትልቅ ራስ ምታት ሆነው ቆይተዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው እነዚህ ተቋማት በጠቅላላው በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብና ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ከውጪ በእርዳታና በብድር በሚያገቸው ገንዘብ (በተለይ IDA በሚባለው የዓለም ባንክ አነስተኛ ወለድ የሚያስከፍል ብድር) ሕግን በጣሰ መልኩ የተቋቋሙና በሕገ-ወጥና አድሏዊ በሆነ መንገድ ይሠሩ የነበሩ መሆናቸውን ነው።
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህ በሕዝብ ስም በአደራ (ኢንዶውመንት) ድርጅትነት የተቋቋሙ ድርጅቶች የሙስና ምንጭ ሆነው ነው የቆዩት፡፡ በዚህ ውስጥ በሕወሓት ስር የነበረው ትዕምት ሌሎቹን ተቋማት በሚያስከነዳ መልኩ በሙስና እና ብልሹ አሠራር ውስጥ ተዘፍቆ የቆየ ተቋም ነው፡፡ ለአብነትም አቶ ገብሩ አሥራት በመጽሐፋቸው እንዳሳዩን እስከ 20 ሚሊዮን የሚያወጣ የትዕምት መርከብ ሙሉ ብረት የት እንደገባ አይታወቅም፤ ጉዳዩም ከድርጅቶቹ መዝገብ ላይ ጠፍቷል። አመራሮቹም ተጠያቂ አልሆኑም።
እነዚህ ተቋማት እስካሁን ሲሄዱ የቆዩበት መንገድ መቀየር እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ ተቋማቱ ከዚህ በኋላ እንዴት በገበያ ውስጥ መቆየት እንዳለባቸው ለመወሰን አዳዲስ አሠራር እና አዲስ መንገድ ሊቀየስላቸው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ይህ ደግሞ ከኢኮኖሚውም ባሻገር የመንግሥትን ትልቅ የፖለቲካ ውሳኔ እና ቁርጠኝነት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፤ ሕወሓት የአገር መከላከያ ሠራዊትን ማጥቃቱና ወደ ሽብርተኛነት መሽጋገሩ ነገሩን ቢያቀለውም። መንግሥት በቁርጠኝነት ከተንቀሳቀሰ ተቋማቱ በስኬት በገበያ ውስጥ የሚቀጥሉበት በርካታ አማራጮች አሉ። ለአብነት የተወሰኑትን ለማየት ብንሞክር፡-
1). ተቋማቱ በአብዛኛው የተቋቋሙት በትንሹ በጦርነት ወቅት በብዛት ግን ከላይ እንዳየነው በሰላም ጊዜ ከተዘረፈ የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ ይህ ሀብት የሕዝብ እስከሆነ ድረስ ለሕዝብ ተመልሶ እንዲያገለግል በፌደራል የልማት ድርጅቶች ውስጥ ማጠቃለል፡፡ ይህን ሐሳብ የሚያጠናክረው ፓርቲና ቢዝነስን የሚለየው ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድም ይሁን በሌላ በንግድ ሥራ ላይ አይሰማሩም ወይም የንግድ ድርጅት ባለቤት መሆን አይችሉም የሚለው ሕግ ነው። በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ መሠረት አንድ ፓርቲ የቢዝነስ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት እንደማይችል በሕግ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ ተቋማቱ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ወዘተ… ወደ ፌዴራል መንግሥቱ ገቢ ተደርገው ገለልተኛ የሆነ አካል የሚመራው ቦርድ በማቋቋም የሚተዳደሩበትን ዕድል መፈጠር ይቻላል።
2.) የፌዴራል መንግሥቱ የሕወሓትንም የብልጽግናንም ድርጅትቶች ሙሉን ወርሶ ከፍተኛውን ድርሻ መንግሥት እንዲያዝ በማድረግ የተቀረውን ድርሻ ለግል ባለሀብቱ ማዞር የሚሉትን በግሌ እንደ አማራጭ ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡
ተቋማቱ አሁን ባሉበት ሁኔታ ዝም ተብለው መተው አለባቸው የሚል እምነት ግን የለኝም፡፡ ለአብነት ከትዕምት ድርጅቶች መሀከል በርከት ያሉ ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት የፈሰሰባቸው ተቋማት አሉ፡፡ ይህን ተቋም አሁን ባለበት ሁኔታ ዝም ከተባለና የመላው ኢትዮጵያን ገበያ ካጣ፣ ምናልባትም የመንግሥትንም ድጋፍ ካጣ፣ ተፈረካክሶ መውደቁ የማይቀር ነው፡፡ እኔ በግሌ መሰቦ ፋብሪካ እንደ ፋብሪካ በገበያ ውስጥ እንዲቀጥል እፈልጋለሁ፡፡ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ እንደ ተቋም በገበያ ውስጥ እንዲቀጥል እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ተቋም ሆኖ መሆን አለበት። ሌሎችንም እንደዚያው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ተቋማት በአንድም በሌላም መንገድ የሕዝብ ሀብት የፈሰሰባቸው እና የሕዝብ ሀብት ናቸውና ነው፡፡ ይህ ሀብት እንዳይባክን በአፋጣኝ በጥናት ላይ የተመሠረተ አዲስ መንገድ ሊበጅለት ይገባል፡፡
በአደራ የሚተዳደሩት ተቋማት ያላቸው ዓመታዊ ገቢ እና ትርፍ በምስጢር የሚያዝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞና ሌብነቱ ታክሎበት የተቋማቱ ካፒታል አቅም ይህ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ያም ቢሆን ግን በኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸው አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደሆነ ከብድራቸው፣ ከታክስ ክፍያ፣ ከተቀጣሪ ሠራተኛ ብዛትና የገበያ ድርሻ በመነሳት ማንም ሰው ይረዳል ብዬ አስባለሁ፡፡
እንደሚታወቀው የግል የንግድ ድርጅት በአብዛኛው ትርፍ እንጂ ማኅበረሰባዊ ጥቅምን አስቦ አይቋቋምም፡፡ በግል ዘርፉ ድካማነት ምክንያት የሚፈጠረውን የኢኮኖሚ ስንጥቅ እና የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግር ክፍተቶችን በመሙላት ረገድ ወደ መንግሥት የሚዛወሩ እንደነዚህ ዓይነት ተቋማት (የኢንዶውመንት ተቋማት) ትልቅ ጥቅም አላቸው፡፡ ተቋማቱ በግልና በመንግሥት ሽርክናም ሊተዳደሩ ይችላሉ። በእስያ አገሮች ያለውም ተሞክሮ ይህን በደንብ የሚያሳይ ነው፡፡
ይህ ዓይነቱን አካሄድ ግን እንደ ዓለም ባንክ እና ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ጥሪት (IMF) ያሉ ተቋማት የሚፈልጉት አይደለም፡፡ እነሱ ሁሉም ተቋም ወደ ግል ዘርፉ እንዲዘዋወር ነው ፍላጎታቸው፡፡ በዚህ መልክ ወደ ኢንዱስትሪ ባንሸጋገርም ምርጫቸው ነው። ስለዚህ በዚህ ሂደት መሰናክል እንደሚፈጥሩ ከወዲሁ ማሰብ ጥሩ ነው። ነገር ግን የልማት ድርጅት ሳይኖረው ያደገ የዓለም አገር የለም፡፡ በየትኛውም አገር ዕድገት ውስጥ ልማት ባንክ እና የልማት ድርጅቶች ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፡፡ በእኔ አስተያየት እነዚህ የአደራ ተቋማት በልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ኤጀንሲ ታቅፈው እንቅስቃሴ ማድረግ መቻል አለባቸው፡፡ ከዚያ በፊት ግን በልማት ድርጅቶች ውስጥ ያለው ሌብነትና ብልሹ አሠራር በአግባቡ መታረም እና መስተካከል መቻል አለበት፡፡ ይህም ጠንካራ የሆነ ሥርዓት እና የተቋም ግንባታ ይፈልጋል። የልማት ድርጅቶቹን መምራት የሚችሉ ጠንካራ፣ ገለልተኛና የሞራል ልዕልና ያላቸው አካላትና ግለሰቦች የሚሳተፉበት፣ መንግሥትም ሚናውን የሚያሳርፍበት ቦርድ ተቋቁሞ የተቋማቱ የሥራ እንቅስቃሴ በዚያ የሚመራበት ዕድል መፈጠር መቻል አለበት፡፡ ቦርዱ ብቻ ተዓማኒና ተጠያቂ መሆኑ ሌብነትን ለማጥፋት በቂ አይደለም። መንግሥትም ራሱ ተጠያቂና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የዘረጋ መሆን ይገባዋል፡፡
Leave a Reply