የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ የአፈጻጸም ሪፖርት፤ አንዳንድ ነጥቦች | አብዱልመናን ሞሐመድ
ኢኮኖሚ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ የአፈጻጸም ሪፖርት፤ አንዳንድ ነጥቦች | አብዱልመናን ሞሐመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የመንግሥታቸውን የስምንት ወራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጥሩ አፈጻጸም እንዳለው የሚገልጽ ነው፡፡ ሪፖርቱ በአብዛኛው በጥሬ-ገንዘብ (ሞነተሪ) ልኬት ደረጃ የቀረበ ሲሆን፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አብዛኛው ማነጻጸሪያ ገንዘብ መሆኑ ግን ጥያቄ የሚጭር ነገር ነው፡፡

እንደኛ ባለ በዋጋ ንረት የሚታመስ አገር ውስጥ ገንዘብን እንደ ዕድገት መለኪያ አድርጎ መውሰድ ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ሦስት ዓመታት የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ መጠን ወድቋልና ነው፡፡ ለአብነት አንዱን የሪፖርታቸውን አካል እናንሳ፡፡ በ2010 ዓ.ም. የኢንቨስትመንት የብድር አቅርቦት 170 ቢሊዮን ብር ነበር፤ በ2011 ዓ.ም. 236 ቢሊዮን ብር ብድር ቀርቧል፤ በ2012 ዓ.ም. የቀረበው በድር  271 ቢሊዮን ብር ነው፤ በ2013 ዓ.ም.  በ6 ወር ውስጥ 155 ቢሊዮን ብድር ቀርቧል የሚል ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል፡፡ ለእኔ እንዲህ ዓይነት ሪፖርት ትርጉም የለውም፡፡ የብር አቅም እየወደቀ ባለበት ሁኔታ ብርን እንደ መለኪያ ተጠቅሞ ከአምናው የተሻለ አፈጻጸም አለ ብሎ መደምደም በጣም ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም የብር የመግዛት አቅም ከአምና ይልቅ ዘንድሮ በጣም ደካማ ነው፡፡

ሌላው የመንግሥት ያለፉት ወራት ገቢ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡ በአንድ አገር ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የዋጋ ንረት ካለ የመንግሥት ታክስ መጠን መጨመሩ የማይቀር ነው፡፡ የምርት ዋጋ  ሲጨምር ታክስ  ከዋጋው መጠን በበመቶኛ የሚሰላ ስለሆነ አብሮ ይጨምራል፡፡ የዋጋ ንረት ተለይቶ ያልወጣለት (ኖሚናል) ዕድገት እንደ ዕድገት መለኪያ ተደርጎ መቅረቡ አግባብ አይደለም፡፡ ዕድገትንም አያሳይም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ቢሆኑ “ለምን በዚህ መልክ ቀረበ?” ብለው ሊሞግቱ በተገባቸው ነበር፡፡

አንድ ሰው ከሦስት ዓመት በፊት በነበረው ደሞዝ ይገዛ የነበረውን ምርት ዛሬ መግዛት አይችልም፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በጥቅሉ ያለው የዋጋ ንረት ከ50 በመቶ በላይ ነው፡፡ አንድ ሰው ከዓመት በፊት የሁለት ሚሊዮን ብር ቤት ሠራሁ ቢል እና ሌላ ሰው ዘንድሮ የሦስት ሚሊዮን ብር ቤት ቢሠራ፣ ይህን ከብር አንጻር ስናወዳድረው የሦስት ሚሊዮኑ ቤት የተሻለ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን በተግባር በዋጋ ንረት ምክንያት የተሠራው የሦስት ሚሊዮኑ  ቤት  ከዓመት በፊት በሁለት ሚሊዮን ብር ከተሠራው ቤት የደከመ ሊሆን ይችላል፡፡ የብር መጠን መጨመር እውነተኛውን ዕድገት ሊያሳየን አይችልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  ከሪፖርታቸው ውስጥ የዋጋ ንረቱን አውጥተው እውነተኛውን ዕድገት ለምን ማቅርብ እንዳልፈለጉ ግልጽ አይደለም፡፡

መንግሥት ይህን ያህል ገቢ በብር አግኝቻለሁ፣ ገቢዬም ከአምናው የተሻለ ነው ማለት የሚችለው በገበያው ላይ የዋጋ ንረት ከሌለ ብቻ ነው፡፡ ከ20 በመቶ በላይ የዋጋ ንረት ባለበት አገር ብር እንደ ዕድገት መለኪያ መቅርብ አይችልም፡፡

ከውጭ ንግድ ገቢ ጋር በተገናኘ ባለፉት ስምንት ወራት ከፍተኛ ገቢ መመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ብለን ስናነሳ፣ የወርቅ ንግድ ገቢ በመጨመሩ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ወራት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስድስት ወራቱን የውጭ ንግድ አፈጻጸም ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ ከቡና እና አበባ በላይ ከፍተኛ ገቢ ያስገኘው የወርቅ ንግድ መሆኑን አይተናል፡፡ በስድስት ወራቱ የውጭ ንግድ ከወርቅ 335.54 ሚሊዮን ዶላር ሲገኝ፤ ከቡና 304.46 ሚሊዮን ዶላር፣ ከአበባ 213.37 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል፡፡  በእኔ እምነት የኢትዮጵያ የወርቅ ንግድ ገቢ ከፍ ያለው ከሁለት ዓመት በላይ ምርት አቁሞ የነበረው የሻኪሶ የወርቅ ማዕድን ልማት ወደ ሥራ በመግባቱ እና ብሔራዊ ባንክ የወርቅ መግዣ ዋጋን ከፍ በማድረጉ ነው እንጂ እንደሚባለው መንግሥት የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሥርዓት በመከተሉ (በፖሊሲ ለውጥ) የመጣ ዕድገት አይደለም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ባለፉት ዐሥር ዓመታት መንግሥት በከፍተኛ መጠን ከተፈተናበቸው ችግሮች መካከል አንዱ የዋጋ ንረት ነው፡፡ መንግሥት የዋጋ ንረትን መቆጣጠር አቅቶታል፡፡

መንግሥት የዋጋ ንረት ለመከላከል እንደ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ያሉ ተቋማትን ማቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡ ነገር ግን የሸገር ዳቦ ፋብሪካ በመጀመሪያው ስድስት ወር 70 ሚሊዮን ብር ከስሬያለሁ ሲለን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የዳባ መሸጫ ሱቆቹም ቢሆን ቡና መሸጫ እየሆኑ ነው፡፡  የዳቦ ፋብሪካ መከፈት ለተወሰኑ በድህነት ውስጥ ላሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጥቂቱ ዳቦ እንዲያገኙ ረድቷል እንጂ የዋጋ ንረትን አረጋግቷል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የአንድ ዳቦ ፋብሪካ መከፈት የኢትዮጵያን የዋጋ ንረት አያረጋጋም፡፡ የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት መንስኤው እና መሠረቱ በጣም ብዙ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ማረጋጋት የሚችለው የዳቦ ፋብሪካ መከፈት ሳይሆን የስንዴ ዓመታዊ ምርት ማደግ ነው፡፡

ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኮቪድ-19 ምክንያት ተጽዕኖ ደርሶበት 2 በመቶ ገደማ ዕድገት እንደሚያስመዘገብ ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት 6 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መመዝገቡን አንስቷል፡፡ የዚህ ዕድገት መሠረቱ አገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲው እንደ ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው አንስተዋል፡፡ በእኔ እይታ  ከበፊቱ የተቀየር የተጋነነ አዲስ ነገር አይታየኝም፡፡ በአገር በቀል ዕቅዶች ከተያዙት ግቦች መካከል አንዱ በመንግሥት እጅ ያሉ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወር የሚለው ይገኝበታል፡፡ እስከማውቀው ድረስ አንድም ተቋም ባለፉት ሦስት ዓመታት ወደ ግል ባለቤትነት አልተዛወረም፡፡ ትልቅ የሚባል የተጨበጠ የፖሊሲ ለውጥ እስካሁን ድረስ አላየንም፡፡ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ትንንሽ መመሪያዎችን ከማውጣት የተሻለ በሦስት ዓመት ወስጥ ትልቁ ተነካ የሚባለው ከዶላር አንጻር የብርን የመግዛት አቅም ማዳከሙ ነው፡፡ በአምራች ዘርፉ ላይ፣ በመንግሥት መዋቅር ላይ (የውስጥ አሠራር)፣ በግብርናው ዘርፍ ላይ የተደረገ መሠረታዊ ማሻሻያ የለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ ዘርፉን በዳሰሱበት ሪፖርታቸው፡፡ የገንዘብ አቅርቦት በ15 በመቶ ማደጉን የቁጠባ መጠን በ25 በመቶ  ማደጉን አንስተዋል፡፡ እኔ እስከምረዳው ደረስ ይህ ዓይነቱ ውጤት የመጣው ጉልበተኛ ፖሊሲ በማውጣት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ከባንክ ማውጣት አትችልም፣ አቤት ብታስቀምጥ ወንጀል ነው በሚል ማስፈራሪያ የመጣ ውጤት ነው፡፡  ሰው ገንዘቡን በባንክ ቤት ወዶ እና ፈቅዶ እንዲያስቀምጥ ማበረታቻዎችን በመስጠት፣ የወለድ መጠንን ከዋጋ ንረቱ ጋር በሚመጣጠን መልኩ በማስተካከል አይደለም፡፡ ሰው ወዶና ፈቅዶ ገንዘቡን በባንክ ቢያስቀምጥ ውጤቱ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ 6.2 ሚሊዮን አዳዲስ የባንክ አካውንት መከፈቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ 6.2 ሚሊዮን የሒሳብ ደብተር ምን ያህሉ ‹አክቲቭ› ነው? በኢትዮጵያ አሁን ባለው የፋይናንስ ሥርዓት አንድ ሰው 4 እና 5 የሒሳብ ደብተር ከተለያየ ባንክ እንዲያወጣ ተገድዷል፡፡ በምን ያህሉ የሒሳብ ደብተር ውስጥ ስንት ብር አለ? የሚለውን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚረዳው ነው፡፡ በዋናነት መረዳት ያለብን በአገሪቱ ውስጥ የሒሳብ ደብተር መብዛቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ስለመኖሩ የሚያመለክተው ነገር የለም፡፡

March 26, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *