የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና፤ ለኢትዮጵያ የሚፈጥራቸው ዕድሎችና ተግዳሮቶች | ጥላሁን እምሩ (ዶ/ር)
ኢኮኖሚ

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና፤ ለኢትዮጵያ የሚፈጥራቸው ዕድሎችና ተግዳሮቶች | ጥላሁን እምሩ (ዶ/ር)

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 2018 ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ ተፈርሞ 2021 መባቻ ላይ ወደ ተግባር የገባው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ታቃፊ ባደረጋቸው 55 አገሮች ቁጥር በአለም ላይ አንደኛ ነው። ይህ ቀጠና የአፍሪካን ከ1.3 ቢሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ የሚሸፍንም ነው። (ይህን ስምምነት ያልፈረመች ብቸኛ አገር ኤርትራ ናት።)

ይህ ስምምነት ከመፈረሙ አንስቶ ተግባር ላይ እስከመዋል የፈጀበት ጊዜ ሶስት አመት ብቻ ቢሆንም የቅድመ-ስምምነት ስራዎች ሲሰሩ ግን ብዙ ዓመታትን አሳልፏል። የሸቀጦች ንግድ ስምምነት፣ የአገልግሎቶች ንግድ ስምምነትና ክርክሮች በሚነሱ ጊዜ ክርክሮቹ የሚፈቱበትን መንገድ ለመስማማት ረጅም ጊዜ ፈጅቷል።

የአለም ባንክ ሀምሌ 2020 ላይ እንዳወጥው ሰፋ ያለ ጥናት ይህ የንግድ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባር ላይ ሲውል በተሳታፊ አገሮች ውስጥ ያሉ በክፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ከ30 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሰዎችን ከድህነት ያወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁሟል።

ለመሆኑ ነጻ የንግድ ቀጠና ጽንሰ ሐሳቡ ምንድን ነው? እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ምን ዓይነት ዕድልን ይዞ ይመጣል? ይዟቸው የሚመጣቸው ዋና ዋና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች ከዚህ በታች በሚገኘው መጣጥፍ ለመመለስ እንሞክራለን።

ነጻ የንግድ ቀጠና ከኢኮኖሚ ንድፈ ሐሳብ አንጻር

ነጻ የንግድ ቀጠና ማለት ሁለት ወይንም ከሁለት በላይ አገሮች በመካከላቸው የሚኖር ንግድ ላይ ቀረጥ ወይንም ሌሎች ንግድን የሚያደናቅፉ መሰናክሎችን ሳይጥሉ እንዲገበያዩ የሚደረግ ስምምነት ነው። የእነዚህ የንግድ መሰናክሎች መነሳት በአገሮች መካከል የሚኖር ንግድን በማቀላጠፍ ዕድገትን ይጨምራል። በተጨማሪም ለሰራተኞች ሰፊ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ገቢያቸው እንዲሻሽል ያደርጋል። ብዙዎች ከድህነት እንዲወጡ በማድረግ ግለሰቦች መካከል ያለ የኑሮ ደረጃ አለመመጣጠንን ይቀንሳል።

እንድ አባል አገር ውስጥ የተመረተን ሸቀጥ ሩቅ ቦታ ድረስ ወስዶ መሸጥ የማጓጓዣ ወጪውን ከፍተኛ ያደርገዋል (iceberg cost)። ሸቀጡ ቅርብ የሆኑ የቀጠናው አባል ጎረቤት አገሮች ውስጥ የሚሸጥ ከሆነ ግን የማጓጓዣ ወጪው ስለሚቀንስ የሸቀጡም ዋጋ በዚያው ልክ ይቀንሳል። ይህም የአምራቾችንና የተጠቃሚዎችን የኑሮ ሁኔታ ያሻሽላል።

እንደዚህ ዓይነት ነጻ የንግድ ቀጠና ሸቀጦችና አገልግሎቶች በዝቅተኛ ዋጋ የሚመረቱበት ቦታ ላይ እንዲመረቱ በማድረግ፣ አገሮች ንጽጽራዊ ብልጫ (comparative advantage) ያላቸው ምሮቶች ላይ እንዲወሰኑ በማድረግ ተሳታፊ አገሮች የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ላይ እንዲደርሱ ያደርጋል። የንግድ ትስስሩ እየተጠናከረ ሲሄድ አባል በሆኑ አገሮች ፖሊቲካዊና ማኅበራዊ ትስስሮችንም እንዲጠናከሩ ያደርጋል።

ምንም እንኳን በአባል አገሮች መካከል የሚኖሩን የንግድ መሰናክሎች ቢቀንስም፣ አባል ካልሆነ ሦስተኛ አገር ጋር በሚኖራቸው ንግድ ላይ ግን የየራሳቸውን ቀረጥ መጣል እንዲችሉ የነጻ ቀጠናው ስምምነት ይፈቅዳል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚከፍታቸው እድሎች

ነጻ የንግድ ቀጠና ለተሳታፊ አገሮች የሚሰጠው ዋና ጥቅም ሸማቾችና አምራቾች ሰፊ ገበያ እንዲያገኙ በማድረግ የሚፈልጉትን ሸቀጥ ወይንም አገልግሎት በዝቅተኛ ዋጋ እንዲገዙ በማስቻል ነው። ሰሞኑን ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ የሆኑት አቶ ማሞ ምሕረቱ ይህንን ጥቅም ሲያብራሩ ነጻ የንግድ ቀጠናው በተሳታፊ አገሮች መካከል ያለውን ንግድ በ2022 በ50 በመቶ ይጨመረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።

እንደዚህ ዓይነት የንግድ ቀጠና ውስጥ ስትሳተፍ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጊዜዋ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ማሞ ነጻ ቀጠናው የአህጉራችንን ውስጣዊ ትስስር በመጨመር ለተሳታፊ አገሮች ብዙ የማይዋዥቅ ገበያ እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ያላት የንግድ ትስስር ዝቅተኛ እንደሆነ ለማስረዳትም አገራችን ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የምታደርገው ኤክስፖርት ከአጠቃላይ ኤክስፖርታችን 18.5 በመቶ ብቻ እንደሆነ እንዲሁም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ወደ አገራችን የምናስገባው ንግድ የአጠቃላይ ኢምፖርታችን 4 በመቶ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ይህ ስምምነት ሙሉ ተግባራዊ ሲሆንም ከሌሎች የአፍሪካ አገራች ጋር የሚደረግ ንግድን በእጥፍ እንደሚጨምረው ጠቁመዋል።  ይህ የንግድ ቀጠና ሰፊ ገበያን ስለሚፈጥር ያደጉ አገሮች ኢንቨስተሮች እንደሚስብም ይታመናል። ለሠራተኞች የሚከፈለው ደሞዝ ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር ሲወዳደር አፍሪካ ውስጥ አናሳ መሆኑና በተጨማሪም ሰፊ የሆነ ወጣት የሰው ኀይል በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ስለሚገኝ አፍሪካን የኢንቨስተሮች ተመራጭ መዳረሻ ያደርጋታል።

የነጻ ገበያ ቀጠናው ተግዳሮቶች

የነጻ ገባያው ዋና ተግዳሮት ፖለቲካዊ ጸባይ ያለው ነው። ይህን ለመረዳት ከነጻ ገበያ ቀጠና ጋር የሚመሳሰለውን የቀረጥ ስምምነቶች (customs union) በአጭሩ እንመልከት።

የቀረጥ ስምምነት ተስማሚ አገሮች በመካከላቸው የሚኖርን ቀረጥ ከማስወገድ በተጨማሪ አባላት አገሮች ከስምምነቱ ውጪ ከሆኑ አገሮች ጋር በሚኖራቸው ንግድ ላይ የሚጥሉትን ቀረጥ ማቀናጀት ይጠይቃል። ለምሳሌ የአፍሪካ አገራች የቀረጥ ስምምነት ውስጥ ቢገቡ ከቻይና ጋር የሚኖራቸው ንግድ ላይ ተመሳሳይ ቀረጥ መጣል ይኖርባቸዋል ማለት ነው። አሁን ወደ ተግባር የወረደው የአህጉረ አፍሪካ ነጻ ገበያ ቀጠና እንደዚህ አይነት ስምምነት ስለሌለው ነጻ የንግድ ቀጠና እንጂ የቀረጥ ስምምነት አይደለም።

የንግድ ቀጠናው ተሳታፊ አገሮች ከአፍሪካ ውጪ የሚመጡ ቁሶች ላይ ተመሳሳይ ቀረጥ እንዲጥሉ አለማድረጉ አስቸጋሪ ተግዳሮት አለው። ይህን ተግዳሮት በምሳሌ እናስረዳ። አንድ 2020 ላይ የተመረተ ቶዮታ ኮሮላ ኬንያ ውስጥ ለማስገባት የሚያስፈልገው ቀረጥ ወደ 5 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ነው። ይህ ቀረጥ የመኪናውን ዋጋ 25 በመቶ ገደማ የሚሆን ነው። ተመሳሳይ መኪና ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ቢያንስ የመኪናውን ዋጋ የሚያህል ቀረጥ መክፈል ያስፈልጋል። ይህም ማለት አንድ ነጋዴ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ መኪናውን ከማስመጣት ይልቅ ኬንያ ውስጥ ሆኖ ማስመጣት ያዋጣዋል ማለት ነው። ኢትዮጵያና ኬንያ የነጻ ንግድ ቀጠና ተስማሚ አባላት ስለሆኑ በኬንያ በኩል የገባው ቶዮታ ኮሮላ ያለምንም ተጨማሪ ቀረጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ሊሸጥ ይችላል። (መኪናን እንደምሳሌ ያነሳሁት ሀሳቡን ለማስረዳት እንጂ ከሌሎች ጥቅሞች አንጻር አይደለም)

ይህ ከነጻ ቀጠናው ውጪ የተመረቱ ሸቀጦች በአንድ አገር በኩል ገብተው ሌሎች የቀተናው ተሳታፊ አገሮች ውስጥ መሸጥ መቻል በቀጠናው ተሳታፊ አገሮች መካከል ፍጥጫ ሊፈጥር ይችላል። እንደዚህ ዓይነት አላግባብ የሆኑ ተግባራትን ለመቀነስ በነጻ ገበያ ውስጥ ያሉ ሀገራት “rules of origin” የሚባሉ ስምምነቶችን ይፈራረማሉ። የ“rules of origin” ስምምነቶች አንድ ሸቀጥ ከተጨማሪ ምርቱ (value added) ምን ያህሉ በቀጠናው ውስጥ ሲመረት ከቀጠናው ውስጥ እንደተመረት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል የሚገልጹ ስምምነቶች ናቸው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነጻ ቀጠናው አባል አገሮች የ“rules of origin” ስምምነት ላይ አልደረሱም ነበር።

የነጻ ገበያዎች ሌላ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮትም አላቸው። በተሳታፊ አገሮች መካከል የተጣለ ቀረጥ ሲነሳ ሸቀጦችን ከቀጠናው ውጪ ከሆኑ አገሮች መግዛት የሚያዋጣ ሆኖ ቢገኝ እንኳ ቀጠናው ውስጥ ቀረጥ ስለሌለ ሙሉ ለሙሉ ከቀጠናው አባል አገሮች ወደ መግዛት መዞር አዋጭ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ይህ ማለት ግን ሸቀጡ ወይንም አገልግሎቱ ከሌላ ሦስተኛ አካል በዝቅተና ዋጋ አይገኝም ማለት አይደለም።

ከመጀመሪያው ተግዳርት ጋር የሚዛመድ ሌላ ተግዳሮትም አለ። በአሁኑ ወቅት መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ አንዲገቡ የማይፈልጋቸውና አገር ውስጥ እንዲመረቱ የሚፈልጋቸው ሸቀጦች ላይ ከባድ ቀረጥ በመጣል እንዳይገቡ ሊያድረግ ይችላል (import susbstituion)። የነጻ ገባያው አባል ከሆነ በኋላ ግን ይህንን ማድረግ ፈጽሞ አስቸጋሪ ይሆናል። ኢትዮጵያ አገር ውስጥ ማምረት የምትፈልጋቸውን ሸቀጦች ሌሎች ተሳታፊ አገሮች ከውጭ ማምጣት ሊፈልጉ ይችሉ ይሆናል። ሸቀጦቹ በአንደኛው አባል አገር በኩል አድርገው ወደ ቀጠናው ከገቡ ወደ ሌሎች የቀጠናው አገሮች የማይዘዋወሩበት ምንም ምክንያት የለም። ይህ ችግር በአባል አገሮች መካከል የኢኮኖሚ ዕቅድና ዓላማ ልዩነት እስካለ ድረስ የሚኖር ነው። እንደዚህ ዓይነት ተግዳሮቶችን ለማስቀረት ሌላ ሁለትና ሦስትዮሽ የሆኑ ውስብስብ ስምምነቶችን ማድረግ አስፈላጊ ሊሆንም ይችላል።

ሌላው የነጻ ቀጠናው ጥቅም ተደርጎ የተነሳው የውጭ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ውስጣዊ የሆነ የፖሊቲካና ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ከሌለ አገር ውስጥ የሚገኝና የውጭ ኢንቨስትመንት የቀጠናው አባላት ወደሆኑ ሌሎች አገሮች ሊወስድም ይችላል። ይህም ማለት ከኢንቨስትመንቱ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ጥቅሞች (ለምሳሌ ያህል የሥራ ዕድልና የውጭ ምንዛሪ ማስገባት) ውስጣዊ መረጋጋት ከሌለ ወደሌሎች አገሮች ሊዛወሩ ይችላሉ ማለት ነው።

ማጠቃለያ

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ብዞ ዕድሎችን እንደሚፈጥር እሙን ነው። ነገር ግን ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው ተያይዘው የሚመጡ ብዙ ተግዳሮቶችም አሉ። የተወሰኑት ተግዳሮቶችን አባል የሆኑ አገሮች ማሸነፍ እንዲችሉ ስምምነቱ የሚፈቅዳቸው ከፍተቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል በነጻ ቀጠናው ስምምነት የተደረሰው በአሁነ ወቅት ያሉትን ቀረጦች ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ሳይሆን 97 በመቶ የሚሆኑትን ቀረጦች ቀስ በቀስ ለማስወገድ ነው። ይህም ማለት ተሳታፊ አገሮች እንዳንድ ቀረጦችን ማስወገድ አይጠበቅባቸውም። እንደዚህ ዓይነት ክፍተቶችን ጥንቃቄ በተሞላ ዕቅድ ለአገር ዘላቂ ጥቅምን እንዲያስገኙ መጠቀም ይቻላል። ኢትዮጵያን ለወደፊት የበለጠ ተፎካካሪ ሊያደርጉ የሚችሉ ዘርፎችን በጥናት ላይቶ እነዚህ ዘርፎች ላይ የተጣሉ ቀረጦች ካሉ እንዲቆዩ በማድረግ ዘርፎቹ እንዲጠናከሩ ማገዝ ያሰፈልጋል። የአገራችንን የወደፊት ጥቅም ባገናዘበ መልኩ ወሳኝ ዘርፎችን ለይቶ በማውጣት እነዚህ ዘርፎች ተፎካካሪ እስኪሆኑ ድረስ የተፈቀደውን ክፍተት መጠቀም ያስፈልጋል። የ“rules of origin” ስምምነቱም የአገራችንን ዘላቂ ጥቅም የማይጎዳ እንዲሆን በባለሙያዎች በታገዘ ሁኔታ ድርድሩ ሊፈጸም ይገባል።

 

 

January 16, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *