እንግዳችን ሰውአለ አባተ (ዶ/ር) የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግና ፋይናንስ ያገኙ ሲሆን፣ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በፋይናንስ ከኢንድራ ጋንዲ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ የቡና ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርም ናቸው፡፡ በፋይናንስ እና በካፒታል ገበያ ላይ ሰፊ የማሰልጠን ልምድ ካላቸው ባለሙያ ጋር ባለደረባችን ይስሐቅ አበበ አጭር ቆይታ አድርገናል፡፡
ሲራራ፡- በአገራችን ስለ የአክሲዮን ገበያ (stock market) በስፋት እየተወራ ነው፡፡ አንዳንዶች ወቅታዊነቱ እምብዛም ነው ሲሉ፣ ሌሎች መጀመሩ መሠረታዊ ነው ይላሉ፡፡ እርስዎ እንደ ባለሙያ በእነዚህ ክርክሮች ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- እንግዲህ ከትርጉሙ ብንጀምር አክሲዮን ገበያ ማለት በሽርክና የሚቋቋሙ ተቋማት ተጨማሪ አቅም (የካፒታል) ሲፈልጉ ድርሻቸውን የሚሸጡበት ገበያ ነው፡፡ አንድ ተቋም ራሱን ለማንቀሳቀስ እና ለማሳደግ ሲፈልግ ተጨማሪ የገንዘብ አቅም (ካፒታል) ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም ድርሻውን በመሸጥ ተጨማሪ ካፒታል ማግኘት እንዲችል የሚያደርግ ገበያ ነው፡፡ ማኅበርም ቢሆን በአቅሙ ድርሻ ገዝቶ የተቋማት ባለቤት መሆን ሲፈልግ፣ ድርሻ በቀላሉ የሚገዛበት፣ የገዛውንም ድርሻ በኋላ መሸጥ በፈለገበት ሰዓት በቀላሉ ድርሻውን የሚሸጥበት ገበያ ነው፡፡
በአጠቃላይ የአክሲዮን ገበያ የተቋማት ድርሻ፣ የብድር ሰነዶችም (ቦንድ) የሚሸጥበት ገበያ ነው፡፡ ከግለሰብ እስከ ተቋማት ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ሀብቱን ኢንቨስት የሚያደርግበት ገበያ እና ኢንቨስት ያደረጉበትን ሀብት ወደ ገንዘብ መቀየር ሲፈልጉም በአፋጣኝ ወደ ገንዘብ የሚለውጡበት ገበያ ነው፡፡
በበኩሌ በአገራችን የአክሲዮን ገበያ መጀመሩ ወቅታዊና አስፈላጊ ነው ባይ ነኝ፡፡ የአክሲዮን ገበያ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና አለው፡፡ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የአክስዮን ገበያ በኢትዮጵያ ነበር፡፡ በወቅቱም በርካታ የውጪ እና የአገር ውስጥ ተቋማትን መፈጠር ተችሎ ነበር፡፡ ነገር ግን በቀጣይነት የመጣው የደርግ መንግሥት ወደ ሶሻሊዝም ርዕዮት ያዘመመ በመሆኑ በግለሰብ ዕጅ ስር የነበሩ ተቋማትን ሲወርስና ሲቀማ ነው የቆየው፡፡ በዚህ ወቅት የአክሲዮን ገበያ መኖሩ አስፈላጊነት ስላልነበረው ገበያው ተዘግቷል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት የአክሲዮን ገበያን ለማቋቋም ሐሳቦች የነበሩ ቢሆንም፣ ሐሳቡን ወደ ተግባር ለማውረድ ጥረቶች ግን የተጀመሩት ባለፉት ሦስት ዓመታት ነው፡፡
የአክሲዮን ገበያ መኖሩ እንደ አገር ቁጠባን ያበረታታል፣ ካፒታልን በቀላሉ የማንቀሳቀስ ዕድልንም ይፈጥራል፡፡ ሥራ ፈጣሪ የምንላቸው የሥራ ሐሳብ ኗሯቸው በገንዘብ እጦት ሐሳባቸውን ወደ መሬት ማውረድ ላልቻሉ ዜጎች ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ በተጨማሪም መንግሥት ከሥሩ ያሉ ተቋማትን ወደ ግል ዘርፍ ለማሸጋገር የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህን እንቅስቃሴ የአክሲዮን ገበያ መቋቋሙ በእጅጉ ይረዳል፡፡ ተቋማቱን ወደ ግል ለማዛወር የሚደረገውንም ጥረት እያፋጠነው ይሄዳል፡፡
ማንም እንደሚረዳው በኢትዮጵያ ያለው የባንክ ሥርዓት ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ከባንክ ውድር ለማግኘት ማስያዥ ማቅረብ ግዴታ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት በርካታ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን አላላውስ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የአክሲዮን ገበያ መጀመር በተለይ ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች አዲስ የፋይናንስ አማራጭን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ ሥራ ፈጣሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደላድል ይፈጥራል፡፡ እንዳልኩት እንደ አገርም የቁጠባ አቅም እንዲጨምር ያደርጋል፡፡
በኢትዮጵያ እንደ ባንክ ያሉ በአክሲዮን የተቋቋሙ ተቋማት የአክሲዮን ድርሻ የሚሸጡት መሥራች ባለ አክሲዮኖች በሚያወጡት ድልድል ብቻ ነው፡፡ አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ አክሲዮን ድርሻው የሚገቡበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው፡፡ ድረሻ ያላቸው አካለትም ድርሻቸውን ሸጠው የሚወጡበት ገበያ አልነበረም፡፡ የአክሲዮን ገበያ ካለ ግን አዳዲስ ተቋማት እንዲፈጠሩ እና ያሉትም አዳዲስ ሀብት የሚሰበስብበትን ዕድል ይፈጥራል፣ ለግለሰቦችም ሀብት የማፍራት ዕድልን ይፈጥርላቸዋል፡፡
በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች በላከው መመሪያ የባንች መነሻ ካፒታል ከ500 ሚሊዮን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል መመሪያ አጥቷል፡፡ ስለዚህ ባንኮች በቀጣይ ይህን መነሻ ካፒታል ለማመንጨት ድርሻ መሸጣቸው ግድ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የአክሲዮን ገበያው መቋቋም ለባንኮች ተጨማሪ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ወደፊት ውጭ ባንኮች ሲገቡ የአገር ውስጥ ባንኮች ተጠናክረው እንዲጠብቁም ያደርጋል፡፡ በኢትዮጵያ ከ10 ዓመት በላይ የቆዩ ባንኮች አብዛኞች ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የላቸውም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ይህን ሕግ በዚህ ሰዓት ያወጣው በቀጣይ የአክሲዮን ገበያን እንደሚከፈት እና ባንኮችም ገበያውን እንደሚቀላቀሉ አስቦ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ መመሪያ ካፒታላቸውን ብቻ ሳይሆን የባንኮች የቁጠባ መጠን ከፍ እንዲልም ያደርጋል፡፡ በዚህ የባንኮች አቅም መጠናከር የአክሲዮን ገበያው መፈጠር ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡
የአክሲዮን ገበያው ከተከፈተ እና ግለሰቦች ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ካላቸው የግድ በርካታ ሚሊዮን ዶላር እስኪኖራቸው መጠበቅ ላይኖርባቸው ይችላል፡፡ መቶ ብርም ሁለት መቶ ብርም ያለው ሰው ገንዘብ አውጥቶ ኢንቨስት የሚያደርግበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ በዚህም ኢንቨስትመንትን ያበረታታል፤ ጎን ለጎን ለኢንቨስትመንት የሚውል ገንዘብ ማግኘት የሚቻልበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ የገበያው መጀመር ለግለሰብ፣ ለተቋም፣ ለአገር ያለው ጠቀሜታ እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡
ሲራራ፡- እንደሚያውቁት በተለያዩ ጊዜያት የአክሲዮን ማኅበራትን ለማቋቋም በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ብዙ ሰዎች ገንዘባቸውን ተበልተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ዜጎች በአክሲዮን ማኅበራት ላይ እንዳይተማመኑ አድርጓቸዋል፡፡ የአክሲዮን ገበያ መቋቋሙ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመቅረፍ ያለው አስተዋጽዖ ምንድን ነው?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የነበረው የአክሲዮን ማኅበራት የአመሠራረት ሂደት በአግባቡ በሕግ የተመራ አልነበረም፡፡ በዋናነት የአክሲዮን ገበያን የሚያስተዳድር ተቋም በሌለበት ይደረግ የነበረ ግብይት ነው፡፡ በተበጣጠሰ መንገድ ሲሠራበት የነበረ ነው፡፡ እንደገለጽከው በርካታ ግለሰቦች ተቋማትን ለማቋቋም ገንዘባቸውን ኢንቨስት አድርገው ተቋማቱ ወደ ሥራ ሳይገቡ የቀሩበት እና የሰው ሀብት ሰብስበው የጠፉ ተቋማት እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
የአክሲዮን ገበያ እንዲቋቋም ሲደረግ ሕጋዊ ተቆጣጣሪ አካል እና ሥርዓት ተዘጋጅቶለት መሆኑ አክሲዮን ለሚገዙ አካላት ዋስትና ይሰጣል፡፡ አንድ ሰው በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ስላስነገረ ብቻ የአክሲዮን ድርሻ የሚሸጥበት ሁኔታ የለም፡፡ የአክሲዮን ድርሻ ሲሸጥ ማለፍ የሚጠበቅበት በርካታ ሕጋዊ ሂደቶች ይኖራሉ፡፡ በዋናነት መዋዕለንዋይ አፍሳሾች ጥቅማቸው እንዲከበር ይሠራል፡፡ አንድ ተቋም ተጨማሪ ካፒታል ፈልጎ ወደ ገበያው ሲመጣ ሊያሟላቸው የሚገቡ በርካት ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ተቋሙን ከመሠረቱት ባለሀብቶች ስብዕና እና ማንነት፣ ተቋሙን እያስተዳደሩ ያሉ ግለሰቦች ማንነት፣ የማስተዳደር አቅም፣ ተቋሙ በውስጡ ያለው የቁጥጥር ሥርዓት፣ ተቋሙ ከተቋቋመ ጀምሮ ያለፈበት ሂደት እና አትራፊነት በተቆጣጣሪ ተቋሙ ከተገመገመ በኋላ ነው ወደ ገበያ መውጣት የሚችለው፡፡ ይህ መሆኑ ገዥው አካል ዋስትና እንዲኖረው ያደርጋል፡፡
ሌላው እና ትልቁ ነገር አንድ ሰው አንድ ጊዜ ኢንቨስት ያደረገውን ገንዘብ ቢፈልግ ድርሻውን ለመሸጥ የተቋሙን የበላይ ኀላፊዎች ፈቃድ ማግኘት አይጠበቅበትም፡፡ ለማንኛውም ሰው በማንኛውም ሰዓት ድረሻውን በሽያጭ የማስተላለፍ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ የአክሲዮን ገበያ አስካሁን ድረስ ባለመኖሩ ምክንያት ይህ ግልሰቦች የገዙትን ድርሻ መሸጥ ተስኗቸው እንዲቆዩ አድርጓል፡፡ ተቋማት እስካልፈቀዱ ድረስ ድርሻን ሸጦ መውጣት የሚቻልበት ሥርዓት አልነበረም፡፡ ባለሀብቶችም ተመሳሳይ ችግር ሲገጥማቸው የሚያመለክቱበት ቦታ ባለመኖሩ ብዙ ውጣ ውረዶችን ሲያዩ እንመለከታለን፡፡ ልሸጥም ቢሉ ገበያውን ገምቶ ዋጋ የሚያወጣ አካል አልነበረም፡፡ ስለዚህ ሽያጩ የሚከናወነው በድርድር ነው፡፡ ይህ ደግሙ ግለሰቦች ዋጋ ተቀባይ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የአክሲዮን ገበያ መመሥረቱ ግን እንደነዚህ ያሉ ችግሮችን መፍታት ያስችላል፡፡
ሲራራ፡- የግሉ ዘርፍ ባለደገበት ሁኔታ የሚቋቋም የአክሲዮን ገበያ ጠቀሜታው እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም የሚሉ አስተያየቶች ይቀርባሉ፡፡ እውነትም የግሉ ዘርፍ ገና እንጭጭ በሆነበት ሁኔታ የአክሲዮን ገበያ መቋቋሙ የሚጨምረው ነገር ምንድን ነው?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- እውነት ነው ኢትዮጵያ የግል ዘርፍ ገና ዳዴ እያለ የሚገኝ ዘርፍ ነው፡፡ እዚህ ላይ መመለስ ያለበት ጥያቄ የግል ዘርፉ ለምን አላደገም? የሚለው ነው፡፡ የግል ዘርፉ ስላላደገ ነው ይህ ገበያ ያስፈለገው፡፡ የግል ዘርፉ ያላደገው የፍላጎት ችግር ገጥሞት ሳይሆን የአቅም ችግር ስላለበት ነው፡፡ አምራቾች ምርታቸውን በብዛት አምርተው ገበያ ላይ የማይሸጡት ፍላጎት ስለሌላቸው ሳይሆን የፋይናንስ አቅም ስለሚያጥራቸው ነው፡፡ የአክሲዮን ገበያ መቋቋሙ የተቋማት የካፒታል ችግር እንዲፈታ በማድረግ ተቋማት ምርታቸውን በስፋት ለተጠቃሚዎች የሚያደርሱበት ዕድል ይፈጥራል፡፡ የተቋማት አቅም ሲያድግ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን የሥራ አጥነትና የምርት እጥረት ሸክም ማቃለል ይችላል፡፡
በብዙ አገር የሚታየውም ሆነ በፋይናንስ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት በአንድ አገር የአክሲዮን ገበያን መቀላቀል የሚችሉ 20 ተቋማት ካሉ የአክሲዮን ገበያን ማቋቋም ይችላል፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ሌላውን ትተን ከ20 በላይ ባንኮች፣ ከ20 በላይ ኢንሹራንሶች አሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ገበያውን እንደሚቀላቀሉ በርግጠኝነት መውሰድ ይቻላል፡፡ ወደፊት ገበያው እየሰፋ ባንኮች የተሻለ ካፒታል ሲያመነጩ፣ የግል ዘርፉም ገበያውን ለመቀላቀል እየተበረታታ ይሄዳል፡፡
አሁን ላይ የባንኮች ብቸኛው የሀብት መሰብሰቢያ መንገድ የደንበኞቻቸው ቁጠባ ነው፡፡ የአክስዮን ገበያ ሲቋቋም ግን ድርሻቸውን በቀላሉ ለገበያ እያቀረቡ ተጨማሪ ካፒታል የሚፈጥሩበት ዕድል አለ፡፡ የኑሮ ውድነት ሲከሰት የቁጠባ መጠን ይቀንሳል ቁጠባ ሲቀንስ ደግሞ ባንኮች የሚሰጡት ብድር ይቀንሳል፡፡ ብድር ሲቀንስ የመዋዕለንዋይ ፍሰት ይቀንሳል፡፡ የገበያው መቋቋም ግን የባንኮችን አቅም በማጠናከር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ ችግሮች መፍታት ያስችላል፡፡
ሲራራ፡- ዓለም ዐቀፋዊውን ተሞክሮ ስናየው፣ የአክሲዮን ገበያ በኢኮኖሚያቸው ላይ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከተላቸው አገራት እንዳሉ ሁሉ የገበያው መፈጠር የጎላ ተጽዕኖ ያልፈጠረላቸው አገራትም አሉ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ መውሰድ ያለባት ትምህርቶች ምንድን ናቸው?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- በመሠረቱ ኢትዮጵያ ለአክሲዮን ገበያ እንግዳ አይደለችም፡፡ ከ40 ዓመት በፊት የአክሲዮን ገበያ የነበራት አገር ናት፡፡ ስለሆነም የአክሲዮን ገበያን በሚመለከት ቀላል ያልሆነ ልምድም አለን፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሁልጊዜ ዘግይተው የሚመጡ አገራት ከመጀመሪያዎች የተሻለ የሚያገኙት ጥቅም አለ፡፡ በአክሲዮን ገበያ ስኬታማ የሆኑ አገራት የስኬታማነት ምክንያት አላቸው፡፡ ውድቀት ያጋጠማቸውም አገራት የውድቀት ምክንያት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ዘግይታ ወደ ገበያው የምትገባ በመሆኑ የምታገኘው የተሞክሮ ዕውቀት አለ፡፡ መንግሥት የሌሎች አገራትን ልምድ እና ተሞክሮ በአግባቡ የፈተሸ እና የቃኘ ፖሊሲ እስካወጣ ድረስ ችግር ይገጥመናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እርግጥ ችግር አይኖርም አይባልም፤ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የሚገጥሙትን ችግሮች የምንፈታበት የሕግ ማሕቀፍ እና ተቋማዊ አደረጃጀት እስከተፈጠረ ድረስ ኢትዮጵያ ስኬታማ የሆኑ አገራትን ልምድ በመውሰድ ዕድሉን ልትጠቀም ትችላለች፡፡
መንግሥት በዚህ ላይ የተለያዩ ጥረቶችን እንዳደረገ እረዳለሁ፡፡ በተለያዩ አገራት የተለያየ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች አሉ፡፡ መንግሥት እነዚህን ባለሙያዎች መጠቀም ከቻለ፣ አስቀድሞ በስልጠና የክህሎት ግንባታ ሥራዎችን መሥራት ከቻለ አገሪቱ ኢኮኖሚዋ በማደግ ላይ እና በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ያላት አገር በመሆኗ በአክሲዮን ገበያ ከፍተኛ ውጤት ማግኘት ትችላለች፡፡ መንግሥትም በገበያው የመጀመሪያ ምዕራፍ ማበረታቻዎችን በመስጠት ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ገበያው እየተጠናከረ ከሄደ በኋላ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ዘርፉን ለቆ መውጣት አለበት፡፡
ሲራራ፡– የአክሲዮን ገበያ መልካም ነገሮች እንዳሉት ሁሉ ስጋት የሚፈጥሩም ጉዳዮች አሉት፡፡ ከዚህ አንጻር መንግሥት በቀጣይ ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- እንደ ስጋት ከሚወሰዱ ነገሮች አንዱ ስለ አክሲዮን ገበያ ማኅበረሰቡ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡ ገበያው አንደተጀመረ ማኅበረሰቡ ቶሎ ወደዚህ ዘርፍ ገብቶ ተጠቃሚ ለመሆን ብዙ ርቀት ላይጎዝ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ በዚህ ላይ መንግሥት አስቀድሞ መሥራት አለበት፡፡ የመጀመሪያ ረቂቅ የአክሲዮን ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅ ወጥቷል፡፡ ከአዋጁ ዝግጅት በተጓዳኝ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል፡፡
የአክሲዮን ገበያ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ ከመቆየቱ አንጻር በቂ የሆነ የሰለጠነ የሰው ኀይል አለ ማለት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም በዚያ ላይ በደንብ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የተቋማትን አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሌላው፣ አላስፈላጊ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነቶችን ማስወገድ፣ አስፈለጊው የመሠረተ ልማቶች ከተሟሉ ከስጋቱ ይልቅ ያሉት መልካም ነገሮች እየጎሉ ይመጣሉ፡፡
ሲራራ፡- በኢትዮጵያ ያለው የባንክ ዘርፍ ዕድገት እያሳየ ነው ቢባልም በሥራ ላይ እንደቆየበት የጊዜ ርዝማኔ ፈጣን ዕድገት አላሳየም የሚሉ አስተያየቶች አሉ፡፡ በዘርፉ ላይ እንደሚሠራ ባለሙያ በእርስዎ ግምገማ ባንኮች ደካማ የሆኑበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- የኢትዮጵያ ባንክ ዘርፍ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ የቆየ ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ በቀዳማዊ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የመስፋት እና የማደግ ዕድል ያገኘ ቢሆንም በደርግ ሥርዓት ወደ አፈና የገባበት ጊዜ ተፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ ተቋቁመው የነበሩ የግል ተቋማት ወደ መንግሥት የተጠቀለሉበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር፡፡ከደርግ ዘመነ መንግሥት መውደቅ በኋላ የመጣው የኢሕአዴግ መንግሥት ለባንክ ዘርፉ በትንሹም ቢሆን በሩን ገርበብ ያደረገበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ዘርፉ የመጣበት መንገድ በራሱ ላለማደጉ አንድ ምክንያት ነው፡፡
ሌላው ለባንክ ዘርፉ ዕድገት ደካማ መሆን ዋናው ምክንያት እንደ አገር የሕዝባችን የቁጠባ ባህል አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ የባንኮች ዕድገት መሠረት ሲቋቋሙ የሚሸጡት የአክሲዮን ድርሻ አይደለም፡፡ የትርፋቸው ሆነ የዕድገታቸው መሠረት ከኅብረተሰቡ በተለያየ መንገድ የሚሰበስቡት የቁጣባ ገንዘብ ነው፡፡ በዚህ አገር ጠንካራ የቁጠባ ባህል አለመኖር፣ ብሎም ማኅበረሰቡ ባንክን እንደመቆጠቢያ መንገድ አድርጎ የመጠቀም ልምዱ አነስተኛ መሆኑ ለዘርፉ ዕድገት አዝጋሚ መሆን ምክንያት ሆኗል፡፡ ለአንድ አገር ማኅበረሰብ የቁጠባ ባህል መሻሻል በመንግሥት የሚወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች፣ እንዲሁም የባንክ ተቋማት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ከዚህ አንጻር የመንግሥትም ይሁን የተቋማቱ ሚና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
በተቋማት መካከል ጠንካራ የሚባል ፉክክር አለመፈጠሩም ሌላው መጠቀስ ያለበት ምክንያት ነው፡፡ በተግባር እንደምንመለከተው ሁሉም ባንኮች አትራፊዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ተቋማቱ አትራፊ ቢሆኑም የማኅበረሰቡን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ እና ተጨማሪ የቁጠባ መጠን ለማግኘት የሚያደርጉት ፉክክር ግን ደካማ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ባንኮች አዳዲስ አባላትን ለማፍራት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም በቂ አይደለም፡፡ የሚወጡ አዳዲስ ፖሊሲዎችና እንደ አገር ያለንበት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሁኔታ ለዘርፉ ዕድገት ተጽዕኖ ሲፈጥር ቆይቷል፡፡
ስለ ባንክ ተቋም ማኅበረሰቡ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ሌላ ችግር ነው፡፡ የባንክ አክሲዮን ያላቸው ሰዎች በእጃቸው ላይ ያለው የተቋም ድረሻ እንጂ የተቋሙ ሙሉ የባለቤትነት መብት አለመሆኑን አይረዱም፡፡ ጥቂት ባለ ሀብቶች ከመንግሥት ባልተናነሰ በባንክ ዘርፉ ላይ የበዛ ጣልቃ ገብነትን ሲያሳዩ ይስተዋላል፡፡ በገዙት የባንክ አክሲዮን ድርሻ መጠን ልክ በተቋሙ ላይ የፈላጭ ቆራጭነት ሚና የሚይዙ ባለ ሀብቶች አሉ፡፡ ይህ በአንዳንድ ባንኮች እንቅስቀሴ ላይ ተግዳሮት ሲፈጥር እንመለከታለን፡፡
ሲራራ፡- “የባንክ ዘርፉን የሚመራው የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ ዘርፉን በአግባቡ እየመራው አይደለም፤ ተቋማት በዘርፉ ውስጥ አዳዲስ የአሠራር ሥርዓት እንዳይፈጥሩ አስሮ የያዛቸው ይኸው ተቋጣጣሪ አካል ነው” በሚሉ ወቀሳዎች ይቀርባሉ፡፡ እርስዎ የብሔራዊ ባንክን የሥራ እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- በየትኛው ዓለም አገራት ባለው ተሞክሮ የፋይናንስ ተቋማትን በበላይነት የሚያስተዳርሩት የብሔራዊ ባንክ፣ ማዕከላዊ ባንክ (Central Bank) የሚባሉት ናቸው፡፡ በእኛ አገር ያለው የብሔራዊ ባንክ የዕውቀት እና የልምድ ችግር ያለበት ተቋም ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን በዚህ አገር ተቋማት ነጻ ሆነው የሚሠሩበት ዕድል ያልተፈጠረ መሆኑ በተቋሙ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንደፈጠረ እረዳለሁ፡፡ ብሔራዊ ባንክ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ያለበት ተቋም ነው፡፡ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነቱ ምክንያትም በዘርፉ በሚወጡ ጥብቅ መመሪያዎች ላይ የራሳቸውን አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድሩ ቆይተዋል፡፡
ለምሳሌ እያንዳንዱ ባንክ ከሚያበድረው ብድር በ27 መቶው ከመንግሥት የልማት ባንክ ቦንድ እንዲገዛበት ይገደድ ነበር፡፡ ያ ገንዘብ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ብድር መዋል የሚገባው ገንዘብ ነበር፡፡ በዚህ ሂደት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከግል ባንኮች ወጪ እየተደረገ ወደ መንግሥት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ይህ መሆኑ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እንዳያድግ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል፡፡
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ይህን አስገዳጅ የ27 ከመቶ ቦንድ ግዥ እንዲቆም ማድረጉ አንዱ ተጠቃሽ እርምጃ ነው፡፡ ይህ ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽዖ ነው፡፡ ባንኮች ተገደው ለሚገዙት የልማት ባንክ ቦንድ የሚታሰብላቸው ወለድ እነሱ ለቁጠባ ከሚከፍሉት ወለድ በታች ነው፡፡ በዚህ ትክክል ባልሆነ አሠራር የአገሪቱ ባንኮች የመንግሥት ኪስ ሲደጉሙ ቆይተዋል፡፡ ይህ በዘርፉ ዕደገት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
የፖለቲካ አጀንዳን ማስፈፀሚያ የሆኑ እንደነዚህ ዓይነት ሕጎች በዘርፉ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ማነቆ ፈጥረው ቆይተዋል፡፡ የሕግ ማዕቀፉቹ ከባንክ ዘርፉ በተጨማሪ ባንኮች በአገሪቱ የግል ዘርፍ ዕድገት የሚኖራቸው እገዛ አነስተኛ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ ቢንቀሳቀስ የባንክ ዘርፉ ከፍተኛ ግስጋሴ ያሳይ እንደነበር የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡
ሲራራ፡- በቁጥር በርከት ያሉ ባንኮች ገበያውን ለመቀላቀል ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ በእርስዎ እይታ የእነዚህ ባንኮች ወደ ገበያ መግባት በባንክ ዘርፉ ላይ ምን አዲስ ነገር ይፈጥራል?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- እውነት እንነጋገር ከተባለ በኢትዮጵያ ያለው የባንክ ብዛት ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ጋር ሲነጻጸር ይኼ ነው የሚባል አይደለም፡፡ የአብዛኛዎቹን ባንኮች ቅርንጫፍ ካየን የሁሉም በሚባል ደረጃ 60 በመቶ ቅርንጫፋቸው ያለው አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ አብዛኛው ሰው እንደሚረዳው በኢትዮጵያ ትልቁ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚኖረው በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ያለው ባንክ በቂ እና ጠንካራ እንዳልሆነ ነው፡፡
አሁን በርካታ ባንኮች ገበያውን ለመቀላቀል ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ ባንኮቹ ተመሥርተው ወደ ሥራ ሲገቡ በርግጠኝነት በዘርፉ ላይ ያለው ውድድር ከፍ ይላል፡፡ ውድድር ሲኖር ደግሞ እያንዳንዱ ባንክ በየሰው ቤት እያንኳኳ ማኅበረሰቡ እንዲቆጥብ የማድረግ ሥራ መሥራት ይጀምራል፡፡ ሌሎችን አገልግሎቶችን ለማቅረብም መወዳደር አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተሞች አካባቢ የሚታዩ መሰል እንቅስቀሴዎች አሉ፡፡ በተቋማቱ መካከል ያለው ውድድር ከዚህም በላይ ከፍ እያለ ሲመጣ ባንኮች አገልግሎታቸውን ወደ ገጠሩ አካባቢ እያስፋፋ መሄዳቸው አይቀርም፡፡ ይኼ በጎ ነገር ነው፡፡
ሁልጊዜ ወድድር ባለበት ኢኮኖሚ ጠንካራ እና የተሻለ አገልግሎት ይኖራል፡፡ ውድድር ሲኖር ባንኮች የሚያበድሩበትን የወለድ ምጣኔ እያስተካከሉ ይሄዳሉ፡፡ ዛሬ ላይ ባንኮች የሚጠይቁትን የብድር ወለድ መክፈል የሚችለው የማኅበረሰብ ክፍል ጥቂት ነው፡፡ ውድድሩ እየጠነከረ ሲሄድ ባንኮች የወለድ ምጣኔያቸውን በማስተካከል በርካታ ማኅበረሰብ የባንክ ብድር ተጠቃሚ ያደርጋሉ፤ እግረ መንገዱንም የግል ዘርፉ እያደገ የሚሄድበት ዕድል ይፈጠራል፡፡
በሌላ መልኩ በሥራ ላይ ያሉት ባንኮች አዳዲሰ እየተቋቋሙ ያሉ ባንኮችን ጨምሮ ረጅም ጊዜ ይሠራሉ ብዬ አላስብም፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚለው ኢኮኖሚው ለውጭ አልሚዎች ክፍት ካደረገ፡፡ የአገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ ከሚገቡት ጋር ተወዳዳሪ ሆነው ለመቀጠል በአንድም ይሆነ በሌላ መንገድ ወደ አንድ ባንክነት መዋሐዳቸው መሰባሰባቸው አይቀርም፡፡
ባንኮች የካፒታል አቅማቸውን፣ የደንበኛ መሠረታቸውን ለማስፋት አሁን ባለው ትንንሽ የባንክ አደረጃጀት ይቀጥላሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ባንኮች ወደ መዋሐድ ሲሄዱ ቁጥራቸው አሁንም ካለው በላይ ሊቀንስ ይችላል፡፡ እነዚህ ባንኮች የሚዋሐዱ ከሆነ ቀድሞም በአገሪቱ ካለው የሕዝብ ቁጥር አንጻር ቁጥራቸው ትንሽ ነበር ሲዋሐዱ የበለጠ በቁጥር ደረጃ እያነሱ ይሄዳሉ፡፡ ተቋማቱ ጥቂት ቢሆኑም ጠንካራ የሚሆኑበት ዕድልም ሰፊ ነው፡፡
ሲራራ፡- እንደገለጹት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ተቋማት ክፍት ለማድረግ የተያዘ ውጥን አለ፡፡ በዚህ ላይ በርካታ ባለሙያዎች መግባት አለባቸው የለም መግባት የለባቸውም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ በእርስዎ እይታ የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ወደ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ገበያ መቀላቀላቸው ያለው ጥቅም እና ጉዳት ምንድን ነው ይላሉ?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- ትልቁ ስጋት ከውጭ የሚመጡ የባንክ ተቋማት ባለቸው አቅም፣ የሰው ኀይል እና ቴክኖሎጂ አቅም አገር ውስጥ ካሉ ባንኮች ጋር ማወዳደር ከባድ ይሆናል የሚል ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባንኮች አቅማቸውን፣ የሚሠሩበትን የአሠራር ሥርዓት እንኪያሻሽሉ የተወሰነ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ ምክንያት በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘርፉ ለውጭ ተቋማት ክፍት መሆን የለበትም፡፡ ግን ደግሞ የባንክ ዘርፉ በአገር ውስጥ የባንክ ዘርፍ ብቻ ተዘግቶ መቀመጥ አለበት የሚል እምነትም የለኝም፡፡ ባንኮች በሰው ኀይል በአዳዲስ ቴክኖሎጂ አቅማቸውን ማጎልበት ከቻሉ እና ሁለት እና ሦስት ባንኮች ወደ አንድ ባንክነት መጥተው አቅማቸውን ማሳደግ ከቻሉ ከውጭ ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ፡፡ ውድድር ሲኖር አሸናፊ እና ተሸናፊ ይኖራል፡፡ በዚህ ምክንያት የተቋማቱ መግባት በአጭር ጊዜ የራሱን ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በረጅም ጊዜ ግን በኢኮኖሚው ላይም ሆነ በማኅበረሰቡ ላይ የሚፈጥረው አውንታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን የሌሎች አገራት ልምድም በሚገባ የሚያሳየው ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች ሳይጠናከሩ የውጭ ባንኮችን ማስገባት አደጋ አለው፡፡
መንግሥት የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን ጊዜ እና ሁኔታ አስቀድሞ ግልጽ ማድረግ አለበት፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ ባንኮች ያሉበት አቅም ለይቶ መቼ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ የሚለውን በጥናት ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ተቋማቱ ባልተጠና መንገድ በድንገት ዘው ብለው የሚገቡ ከሆነ ዘርፉ ትልቅ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ የባንክ ዘርፉ ውድቀት ደግሞ የአገር ኢኮኖሚ ውድቀት ነው፡፡
ሲራራ፡- አገሪቱ የገንዘብ ለውጥ ካደረገች በኋላ ብሔራዊ ባንክ ከጥሬ ገንዘብ ዝውውር ጋር በተያያዘ በርከት ያሉ መመሪያዎችን ሲያወጣ ይታያል፡፡ እነዚህ መመሪያዎች ባንኮቻችን ካላቸው የቴክኖሎጂ አቅም የሚናበቡ አይደሉም የሚሉ ትችቶች ሲሰነዘሩ ይሰማ፡፡ በዚህ ላይ ምን አሳብ አለዎት?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- እኔ በግሌ እንደዚህ ዓይነት አመለካከቶች የሚፈጠሩት ከግንዛቤ እጥረት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ቀደም ብሎም የንግድ ተቋማት የንግድ ሥራን የሚከውኑት በባንኮች አማካይነት ነው፡፡ ሚሊዮን ብሮችን በጥሬ ይዞ የሚንቃሳቀስ ነጋዴ በዚህ ሰዓት አለ ብሎ ለመቀበል ይከብደኛል፡፡ ቢኖር እንኳን በጣም ጥቂት ነው፡፡ በሕገ-ወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ካልሆኑ በቀር አብዛኛዎቹ ክፍያ የሚከፍሉት በቼክ ነው ክፍያ የሚቀበሉትም በቼክ ነው፡፡
ነጋዴዎች የፈለጉትን መጠን ያለው ገንዘብ በቼክ እንዲያንቀሳቅሱ መብት አላቸው፡፡ ብሔራዊ ባንክ በመመሪያዎች ገደብ የጣለው ከአንድ ሒሳብ ደብተር ወደ ሌላ ሒሳብ ደብተር የሚደረግ የጥሬ ግንዘብ ፍሰት በቀን ከአምስት እንዳይበልጥ ነው፡፡ የንግድ ማኅበረሰቡ ቼክን እስከ ተጠቀመ ድረስ በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው ጫና ያን ያህል ከባድ የሚባል አይደለም፡፡ ነጋዴው በቼክ መጠቀሙ የተቋማትን የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት ያሳድገዋለድ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ተቋማት ገቢ እና ወጪያቸውን በአግባቡ እንዲያዙ ያደርጋቸዋል፡፡ ባንኮች ይህን መመሪያ መፈፀም ይሳናቸዋል የሚል ጥናት እስካሁን የለም፡፡ ባንኮችም ያለችግር መመሪያውን ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡
የጥሬ ገንዘብ ዝውውሩ ላይ የሚደረጉ ገደቦች በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው ገንዘብ ኖት ያለ ወቅቱ እንዳያረጅ ዕድል ይሰጣል፡፡ ሁሉም እንደሚረዳው መንግሥት በከፍተኛ ወጪ ነው የገንዘብ ኖት ለውጥ ያደረገው፡፡ ይህ የጥሬ ገንዘብ ኖት በተደጋጋሚ በገበያ ውስጥ በተዘዋወረ ቁጥር የመበላሸት ዕድሉ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ገና ካሁኑም የተቀደዱ እና የቆሸሹ የብር ኖቶችን በገበያው ላይ እየተመለከትን ነው፡፡
ሌላው ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ ነው በጥቁር ገበያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ገንዘብ በባንክ ውስጥ ሲንቀሳቀስ እንደ አገር እንጠቀማለን፣ ለባንክ ይጠቅማል፣ ግብር ሰብሳቢ አካላት የተቋማትን ወጪ እና ገቢ በአግባቡ የሚቆጣጠሩበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ በግለሰብ ደራጃ አንድ ሰው በቀን 50 ሺሕ ብር ድረስ በጥሬ የማውጣት መብት አለው፡፡ ካዛ ባለፈ የፈለገውን መጠን ያህል ገንዘብ ወደ ፈለገው ሒሳብ ማዘዋወር ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ዕድል እያለ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ በኢኮኖሚው ላይ ችግር ይፈጥራል የሚል እምነት የለኝም፡፡
በእኛ አገር ውስጥ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ አለ፡፡ ይህ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ በቀን በእጁ ዐሥር ሺሕ ብር ቢይዝ እና ከባንክ ሥርዓት ውጪ ይሁን ተብሎ ቢታሰብ ከባንክ ውጪ የሚሆነው ገንዘብ መገመት ከሚቻለው በላይ በጣም ብዙ ነው፡፡ ገንዘብ ከባንክ ውጭ በሆነ ቁጥር የባንኮች የጥሬ ገንዘብ ፍሰት እና የመክፈል አቅም እየተዳከመ ይመጣል፡፡ ባለፈው ዓመት ሰዎች በተለያየ ምክንያት ገንዘባቸውን ከባንክ በማውጣታቸው ባንኮች የሚጻፉ ቼኮችን መክፈል እስከሚያቅታቸው ድረስ ችግር ውስጥ ገብተው እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ አሁን ላይ ገንዘብ ለማውጣትም ሆነ ለማንቀሳቀስ ‹ፖስ ማሽን›፣ ‹ኤ.ቲ.ኤ.ም›፣ ‹ሞባይል ባንኪንግ› ወዘተ… የመሳሳሉ አማራጮች አሉ፡፡ በዚህ ሁሉ አማራጭ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ኢኮኖሚውን ይጎዳል ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም፡፡
መንግሥት አሁን ካለው በላይ ባንኮች የቴክኖሎጂ ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ ጥሬ ገንዘብ የማይጠቀም ማኅበረሰብ መፍጠር ላይ ከዚህም በላይ መሥራት ይገባዋል፡፡ በያዝኩት ሞባይል ክፍያ መፈፀም እየቻልኩ፣ አልያም በ‹ኤ.ቲ.ኤም› ካርድ ገንዘብ በፈለኩበት ቦታ ማውጣት እየቻልኩ ለምን እቃ ለመግዛት ጥሬ ገንዘብ ተሸክሜ እዞራለሁ? ብዙ ሰው ከኖረበት ልማድ ውጪ አዲስ ባሕርይ ልመድ ሲባል ምቾት አይሰጠውም፡፡ አሁን የሚነሱት ቅሬታዎች መነሻቸው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ሲራራ፡- የፋይናንስ ዘርፉ በአግባቡ መነቃቃት እንዲችል ከመንግሥት ሆነ ከፋይናንስ ተቋማቱ ምን ይጠበቃል?
ሰውአለ (ዶ/ር)፡- በዋናነት የኤስያን አገሮች የዕድገት መሠረቱ ቁጠባ ነው፡፡ የሰዎች ቁጠባ በጨመረ ቁጥር አልሚዎች የሚያገኙት ብድር እያደገ ይሄዳል፡፡ የአልሚዎች እንቅስቃሴ መነቃቃት የምርት ዕድገት እንዲኖር፣ የአገሪቱ ጥቅል ምርት ዕድገት እንዲኖር ያደርጋል፣ አዳዲስ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ አዳዲስ ገቢ ያላቸው ዜጎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል፡፡ ከዚህ አንጻር መንግሥትም ሆነ ባንኮች በቀጣይ የቁጠባ መጠን እንዲያድግ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡
መንግሥት የቁጠባ አቅም እንዲጨምር የሚያደረጉ የፖሊሲ ማሕቀፎችን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ በተጨማሪ ሰዎች የሚያገኙት ገቢ ከሚያወጡት ወጪ እያነሰ ሲሄድ የቁጠባ መጠን እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ከዚያ ባለፈ ሰዎች ወደ ብድር የሚገቡበትም ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ አሁን የሚታየው የዋጋ ንረት የሚቀንስበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የባንኮችን ሥራ በሚያዘምን ሁኔታ ተቋማቱን በመደጎምም ሆነ ግዴታዎችን በማስቀመጥ ጫና ማድረግ ይገባል፡፡
Leave a Reply