የብር ቅያሪው ለኢትዮጵያ ምን ይዞ ይመጣል? | ጌታቸው አስፋው
ኢኮኖሚ

የብር ቅያሪው ለኢትዮጵያ ምን ይዞ ይመጣል? | ጌታቸው አስፋው

ብሔራዊ ባንክ የሚያሰራጨውን መገበያያ መሣሪያ ብር መቀየሩን ይፋ ሲያደርግ ምክንያቴ ነው ብሎ የነገረን ሕገ-ወጥ ብሮች በሰዎች ዘንድ ስለተከማቹ azበአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት አገሮችም ነው በማለት የብሔራዊ ባንክ ገዥው ማብራሪያ ሰጥተዋል:: ብሔራዊ ባንክ የወሰደው እርምጃ በቀዳማዊ ኀይለሥላሴም በደርግም ዘመን እንደተደረገው ማንኛውም ከብር ዓይነትና ቀለም ለውጥ ያልተለየ እና የፖሊሲ ለውጥም እንዳልሆነ እየታወቀ፣ የዋጋ ንረትን ያረግባል በማለት በመንግሥት ባለሥልጣናት የውጤት ትንበያም ተደርጎበታል::

በኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ሙያዊ የውጭ ቋንቋ ቃላት የአማርኛ ትርጉም ሰጥቶ መናገር እንዲቻል የቋንቋ አካዳሚ ተቋቁሞ ባለሙያዎች ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የጋራ መግባቢያ የቃላት ትርጓሜ መፍጠር ቢያስፈልግም፣ በዚህ ረገድ የተሠራ ሥራ ባለመኖሩ እያንዳንዱ ባለሙያ የራሱን ጥረት እያደረገ ዕውቀቱን ለወገኖቹ ለማስተላለፍ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል:: በአዋጅ ተቋቁመው ለብዙ ዓመታት አገርን ሲያገለግሉ የነበሩ ተቋማት ግን ሪፖርቶቻቸውና መግለጫዎቻቸው ከቃላት አጠቃቀም አንስቶ ለተመራማሪዎች ግልጽ አይደሉም::

የገንዘብ ሚኒስቴር ራሱ መጠሪያ ስሙን በእንግሊዘኛ ትርጉም “Ministry of Finance” ብሎ በራፉ ላይ ቢሰቅልም፣ ገንዘብን እና ፋይናንስን እኩል አድርጎ ላለመጥራት ገንዘብን በጥሬ ገንዘብ፣ ፋይናንስን በገንዘብ ትርጉሞች ተክቶ ለመጥራት አንዳንድ ባለሥልጣናት ሲሞክሩ አድምጬአለሁ:: እንግሊዘኛውን እናለማምዳለን ከሚሉ ንዋይ የሚባለው የአማርኛ ቃልም ነበረላቸው:: በቋንቋ አካዳሚ ተተርጉሞ በሕግ ዕውቅና ቢሰጠውና በራፋቸው ላይም ተምታቶ ባይጻፍ፣ ባለሙያዎች ለመቀበል ግድ ይለናል:: ነገር ግን ይህ ካልተደረገ የግላችንን ስያሜ ሰጥተን መጻፍ እንገደዳለን:: ለምሳሌ እኔ ዶላርን፣ ዩሮን፣ ፍራንክን፣ ፓውንድን የውጭ ምንዛሪ (Foreign Currency) ከሚለው ወስጄ ብርን “የአገር ውስጥ ምንዛሪ” ነው የምለው::

ፈረንጆች ለገንዘብ ኢኮኖሚያቸው ስም ለመስጠት ምንም እንደማይቸገሩ በአንድ ምሳሌ መመልከት እንችላለን:: በብሔራዊ ባንክ ተሰራጭቶ በገበያ ውስጥ በዝውውር ላይ እና በባንኮች ካዝና ውስጥ ያለውን በንግድ ባንኮች አራት ጊዜ እጥፍ ረብቶ ጠቅላላውን በኢኮኖሚው ውስጥ የተሰራጨውን ጥሬ ገንዘብ መጠን የሚያሳክለውን እኔ በራሴ መንገድ ተርጉሜ “እርሾ ጥሬ ገንዘብ” ብዬ የሰየምኩትን፣ ፈረንጆቹ በሦስት ዓይነት ስያሜዎች (Reserve Money/ High Powered Money/Base Money) ብለው ይጠራሉ:: በጊዜ ብዛት ስለተለመዱ እንጂ በየዕለት ተለት የቋንቋ ንግግር ግራ አጋቢ ናቸው:: እኛም ሕዝብ የሚያውቀው ገንዘብ የሚለው የወል ስሙ እንዳለ ሆኖ በጥሬነት ደረጃ (Liquidity) ለሚለያዩ የገንዘብ ዓይነቶቻችን ለእያንንዱ ልዩ ስያሜዎች ብንሰጥ ለተወሰኑ ወራት ቢያደናግሩ እንጂ መለመዳቸው አይቀርም:: በገዛ ገንዘቤ ምን አገባህ? ብለን ቁሳዊ ንብረትንም እንደ ገንዘብ የምንጠቀምበት ጊዜም አለ:: ይህን ሳናደርግ ወደ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ብንሄድ ሕዝቡን አደናግረን ጥቂት በዘርፉ ዕውቀት ያላቸውን ሰዎች ብቻ ተጠቃሚ እንደምናደርግ ሳላሳስብም አላልፍም:: ምክንያቱም የያንዳንዱ ገንዘብ ገበያ የሰነድ ዓይነት ትርፍና ወለድ ጥቅም የሚለካው ጥሬነትን ከማጣት ዋጋ ጋር ተነጻጽሮ ነው::

በበኩሌ በጋዜጦችና በመጻሕፍት ከምጠቃቅሳቸው ገንዘብ ነክ ጉዳዮች በተጨማሪ በኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. ራሱን የቻለ መጽሐፍ “ምንዛሪ፣ ጥሬ ገንዘብ፣ ገንዘብ እና የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ” በሚል ርእስ በአገሪቱ ውስጥ የሚታየውን የገንዘብ ሁኔታ የዳሰሰ መጽሐፍ አሳትሜ ለሽያጭ አቅርቤ ያሳተምኩትንም ሽጬ ጨርሼአለሁ:: የብር ቅያሪው የፖሊሲ ለውጥ እንዳልሆነ ከማብራራቴ በፊት ከመጽሐፌ አንድ ክፍል በገጽ 20 ያሰፈርኩትን ዋቢ አድርጌ ወስጄ አመለክታለሁ፡-

“እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2000 በብሔራዊ ባንክ የተሰራጨው ምንዛሪ ዐሥራ ስምንት ቢልዮን ብር ሆኖ ስልሳ ስምንት ቢልዮን ብር ከነበረው ጠቅላላው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ውስጥ ሃያ ስድስት በመቶ ድርሻ ነበረው:: ቀሪው ከጠቅላላው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ውስጥ ሰባ አራት በመቶ ድርሻ የነበረው ሐምሳ ቢልዮን ብር ንግድ ባንኮች የፈጠሩት የብድር ጥሬ ገንዘብ (Credit Money) ነበር:: በ2008 ጠቅላላው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ወደ አራት መቶ አርባ አምስት ቢልዮን ብር ሲያድግ በብሔራዊ ባንክ ተሰራጭቶ በገበያ ውስጥ የተዘዋወረው ምንዛሪ በመጠን በሦስት ነጥብ ሰባት እጥፍ አድጎ ስልሳ ሰባት ቢልዮን ብር ቢደርስም ከጠቅላላው ጥሬ ገንዘብ ድርሻው ግን ወደ ዐሥራ አምስት በመቶ ዝቅ ብሏል::

በ2008 ዓ.ም. ከተሰራጨው አራት መቶ አርባ አምስት ቢልዮን ብር ጠቅላላ ጥሬ ገንዘብ ውስጥ ሦስት መቶ ሰባ ስምንት ቢልዮን ብር ንግድ ባንኮች የፈጠሩት የብድር ጥሬ ገንዘብ ሆኖ ከጠቅላላው ጥሬ ገንዘብ ድርሻውም ወደ ሰማንያ አምስት በመቶ አድጓል:: ይህ የሚያመለክተው የእጅ በእጅ ክፍያ ግብይይት መጠን ቀንሶ በባንክ በኩል የሚደረግ የግብይይት ክፍያ እንደጨመረ ነው:: በዚያው መጠንም ለጥሬ ገንዘብ አቅርቦትና ለዋጋ ንረት ከፍተኛውን ድርሻ እየያዙ የመጡት የንግድ ባንኮች ተቀማጮች ወይም ንግድ ባንኮች የሚፈጥሯቸው የብድር ጥሬ ገንዘቦች ናቸው::

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ጎልቶ የሚታየው የዋጋ ንረትና የውጭ ምንዛሪ መጣኝ መውደቅ ምክንያቶቹ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ የምንዛሪ ስርጭቱ ኢኮኖሚው በሚያስፈልገው ልክ ባለመመጠኑ ብቻ ሳይሆን፣ ንግድ ባንኮች በሚፈጥሩት የብድር ጥሬ ገንዘብም ጭምር እንደሆነ እነኚህ መረጃዎች ያመለክታሉ::”

እንደ አንድ ተመራማሪ የብሔራዊ ባንኩን መረጃዎች አዘውትሬ ተጠቃሚ ነኝ:: ከቅርብ ወራት በፊት ጀምሮ ግን የንግድ ባንኮች አመራር አባላት ጭምር ባንኮች የማያውቁት አንድ መቶ ዐሥራ ሁለት ብልዮን ብር በግለሰቦች እጅ አለ ሲሉ ሰምቼ ግርምት ፈጥሮብኝ ሰንብቷል::

ብሔራዊ ባንኩ ሰሞኑን የብር ቅያሪ አደርኩኝ በማለት የሰጠው ምክንያትም የንግድ ባንኮች አመራር አባላትን አባባል የሚያጠናክር ሆኖብኛል:: በብሔራዊ ባንክ የ2010 ዓ.ም. ሪፖርት መሠረት ንግድ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ በመጠባበቂያ ተቀማጭነት እንዲይዙ ከሚፈለግባቸው አርባ አራት ቢልዮን ብር በላይ ሌላ ተጨማሪ አርባ አራት ቢልዮን ብር በድምሩ 88 ቢልዮን ብር መጠባበቂየ ተቀማጭ እንደነበራቸው ሪፖርት እየተደረገ እንደዚሁም ደግሞ ንግድ ባንኮቹ የምንዛሪ እጥረት ስለሌለባቸው የባንክ ለባንክ ብድር ተሰጣጥተው እንደማያውቁ እየተነገረ በድንገት ተነስቶ ባንኮች የሚያበድሩት ጥሬ ገንዘብ እጥረት ገጠማቸው ሲባል ለባለሙያ እንቆቅልሽ ነው የሚሆነው::

ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የቅርብ ጊዜ የ2010 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት በገበያ ውስጥ ራሱ ያሰራጨውን የምንዛሪ (ብሮች/Cur­rency Issued) መጠን ምን ያህል እንደሆነ ሳይገልጽ በጥሬገንዘብ አካሎች (Components of Broad Money) ሰንጠረዥ 4.1 ውስጥ ከጠቅላላው በባንክ ሥርዓቱ (Banking Sys­tem) ከተሰራጨው ስምንት መቶ ሰማንያ ሰባት ቢልዮን ብር ጠቅላላ ጥሬ ገንዘብ (Broad Money) ውስጥ ከባንክ ውጪ በገበያ ውስጥ ያለው ምንዛሪ/ብሮች/ ዘጠና ሁለት ቢልዮን ብር እንደሆነ ተመልክቷል:: ከጥቂት ገጾች በኋላ በመጠባበቂያ ተቀማጭ ጥሬ ገንዘብና የገንዘብ መጣኞች (Reserve Money and Monetary Ratios) ሰንጠረዥ 4.3 በዝውውር ላይ ያለ ምንዛሪ (ብሮች) ደግሞ አንድ መቶ ሃያ ሁለት ቢልዮን ብር ተብሎ ተመልክቷል:: ከባንክ ውጪ ያሉ ብሮች የሚለው የሰንጠረዥ 4.1 መረጃ እና በዝውውር ላይ ያሉ ብሮች የሰንጠረዥ 4.3 ልዩነት ምን እንደሆነም ግልጽ አይደለም:: ብሔራዊ ባንኩ በሪፖርቶቹ በሰንጠረዥ 4.1 እና በሠንጠረዥ 4.2 የሚያመለክተው የባንክ ሥርዓቱን (Bank­ing System) የሀብት እና የዕዳ መረጃዎች እንጂ የራሱን ሀብትና ዕዳ መረጃ ስለማያሰራጭ በየዓመቱ የሚያሰራጨውን የምንዛሪ (ብሮች) መጠን አያመለክትም፤ ምስጢርም እንደሆነ አላውቅም:: ብሔራዊ ባንኩ ከመንግሥትና ከንግድ ባንኮች ጋር የሚያደርገውን የማበደር መስተጋብር እና በዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማት ያለውን የውጭ ምንዛሪ መጠንም ለሁለት ወር ኢምፖርት የሚበቃ ከማለት በቀር በግልጽ በመጠን አያመለክትም::

ብሔራዊ ባንኩ ያሳተመውን የመጨረሻ በእጄ ያለ የ2010 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት ዘጠና ሁለት ቢልዮን ብር ከባንክ ውጪ የሚዘዋወሩ የምንዛሪዎች (ብሮች) እና ስምንት መቶ ሰማንያ ሰባት ቢልዮን ጠቅላላ ጥሬ ገንዘብ (Broad Money) ጥምርታ በ2008 ዓ.ም. ከነበረበት 15 በመቶ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ብሏል:: ይህም ማለት ለእጅ በእጅ ክፍያ በገበያ ውስጥ የሚዘዋወረው ብር መጠን እየቀነሰ በባንክ ብድር ዓማካኝነት የሚካሄደው ግብይይት ጨምሯል ማለት ነው:: ከብሔራዊ ባንኩ የቅርብ ጊዜ ሪፖርቶች ይህንን ማረጋገጥ እንችላለን:: እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠሮች የምንዛሪዎች እና የጠቅላላው ጥሬ ገንዘብ መጣኝ (Currency to Broad Mon­ey Ratio) በ2014/15—16.28፤ በ2015/16— 14.98፤ በ2016/17—12.89፤ በ2017/18—11.6 (በእኔ የተስተካከለ) በ18/19—10.37 ስለነበር፤ በገበያ ውስጥ የሚዘዋወረው ምንዛሪ (ብር) ድርሻ በራሱም እየቀነሰ እንደነበር የሚያመለክት ነው:: በአንጻሩ ንግድ ባንኮች በብሔራዊ ባንኩ የተሰራጩትን እርሾ ጥሬ ገንዘቦች በ2014/15- -በ3.62፣ በ2015/16–በ3.74፣ በ2016/17– በ3.92፣ በ2017/18–በ4.25፣ በ2018/19–በ4.42 እጅ አርብተዋል:: ይህ የሚያመለክተው ገና የኤሌክትሮኒክስ ግብይይቱ ከግምት ሳይገባም የእጅ በእጅ (Cash) ሽያጭ እየቀነሰ በባንክ በኩል የሚደረግ ግብይይት እየጨመረ እንደመጣ ነው::

ሕዝቡን አሳምኖ ወይም አስገድዶ የባንክ ተጠቃሚ ለማድረግ መሞከሩ በራሱ ችግር ባይሆንም ንግድ ባንኮች በብሔራዊ ባንኩ የሚሰራጨውን እርሾ ጥሬ ገንዘብ የማርባት አቅማቸው ስለሚጨምር የጥሬ ገንዘብ አቅርቦቱ እንዳይጨምር መጠባበቂያ ተቀማጫቸውን መጣኝ ከፍ በማድረግም ሊሆን ይችላል ወይንም በሌላ መንገድ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦቱ ሉጋም ካልተበጀለት የዋጋ ንረትን ማባባሱ አይቀርም::

 

 

October 4, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *