ኢትዮጵያ በዋናነት የውጭ ምንዛሪ የምታገኘው ከውጭ ንግድ እና ኑሯቸውን በውጭ አገሮች ያደረጉ ዜጎች ወደ አገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ (ሬሚታንስ) ነው፡፡ ከተለያዩ አገሮች እና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የምታገኘው ብድር እና እርዳታም ሌላው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ነው፡፡
አገሪቱ ከሚያስፈልጋት የውጭ ምንዛሪ መጠን አንጻር የምታገኘው በቂ አይደለም፡፡ ይህም አገሪቱን ለረጅም ዓመታት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ እንድትቆይ አድርጓታል፡፡ በእጥረቱ ሳቢያም በርካታ የኢኮኖሚ ዘርፎች ችግር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይህን እጥረት ለመሙላት እና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን መፍታት ቀላል አልሆነም፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ መጠቀም ያስችላሉ፣ሕገወጥነቱን ያስቀራሉ ያላቸውን የመመሪያ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን የሕገ-ወጥነቱ ቀዳዳዎች በርካታ በመሆናቸው በአንድ በኩል ሲደፈን በሌላ በኩል ማፍሰሳቸውን እየተለመከትን ነው፡፡ ለሕገ-ወጥነቱ መሠረት ለሆነው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንድ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አይቻልም፡፡ ያ እስኪሆን ድረስ ግን ብሔራዊ ባንክ ጊዜያዊ የማስታመሚያ እርምጃዎችን እየወሰደ ለመቆየት ተገዷል፡፡
በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ በሳምንት ውስጥ ገንዘብ ማዘዋወሪያ መጠንን የሚገድብ ደብዳቤ ለሁሉም ባንክ ቤቶች ልኳል፡፡ ደብዳቤው በአንድ ሳምንት ውስጥ ከአንድ የባንክ ሒሳብ ደብተር ወደ ሌላ ሒሳብ ደብተሮች የሚደረገው ዝውውር ከአምስት በላይ እንዳይሆን የሚከለክል ነው፡፡ይህ መመሪያ በሕገ-ወጥ የሐዋላ አስተላላፊዎች አማካይነት ወደ ትይዩ (ጥቁር) ገበያው የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሕጋዊ መንገድ እንዲገባ ያግዛል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡ መመሪያው በዋናነት አገሪቱ ከሬሚታንስ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ያሳደጋል ተብሎ ታምኗል፡፡
እስካሁን በነበረው አሠራር ሕገ-ወጥ የሐዋላ አስተላላፊዎች በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት የሚልኩትን ዶላር እዚያው በማስቀረት አገር ውስጥ በከፈቱት የሒሳብ ደብተር አማካይነት ለተቀባዩች በኢትዮጵያ ብር ይከፍላሉ፡፡ አገሪቱ በቅርቡ ያደረገችውን የብር ኖት ለውጥ ተከትሎ ከባንክ የገንዘብ ወጪ ጣሪያ 50 ሺሕ ብር መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ይህን ተከትሎ ሕገ-ወጥ የሐዋላ አንቀሳቃሾች ለአገር ውስጥ ተቀባዮች ክፍያዎችን በባንክ በኩል ማዘዋወር መጀመራቸውን ተደርሶበታል፡፡ ይህን እንቅስቃሴ ለማገድ ሲባል ብሔራዊ ባንክ የሳምንት የሚደረገውን የገንዘብ ዝውውር ላይ ጣሪያ አስቀጧል፡፡
የሕገ-ወጥ የሐዋላ ዋናው መሠረቱ በውጭ አገር ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በዚህ መመሪያ መሠረት ገንዘቡን ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ አካላት የገንዘብ ዝውውር መጠናቸው የሚገደብ ከሆነ ዲያስፖራው ማኅበረሰብ ባንክ ቤቶች አማራጭ ማድረግ የግድ ይሆንበታል የሚል እምነት አለ፡፡ በውጭ አገሮች ይህ ዓይነቱ ሥራ የሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር (money laundering) የሚባል ሲሆን፣ ቀደም ባሉት ዓመታት በሶማሊ ክልል ጠረፍ አካባቢዎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ይከናወን ነበር፡፡ በቅርቡ አገሪቱ ባደረገችው የብር ኖት ለውጥ አማካይነት በድንበር በኩል ያለው የዶላር ንግድ አሁን ላይ ተቀዛቅዟል፡፡
ሕገ-ወጥ የሐዋላ እንቅስቃሴ አገሪቱን ለበርካታ ዓመታት በሬሜታንስ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንዳታገኝ ሲያደርጋት ቆይቷል፡፡ በሬሜታንስ አማካይነት ወደ አገር ውስጥ ከሚገባው የውጭ ምንዛሪ ይልቅ በውጭ አገሮች የሚቀረው የውጭ ምንዛሪ በርካታ መጠን ያለው መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
ብሔራዊ ባንክ አሁን አዲስ ባወጣው መመሪያ ከአንድ አካውንት ወደ ተለያዩ ብዙ አካውንቶች የሚደረገውን የገንዘብ ዝውውር በሳምንት ውስጥ ያለውን መጠን ገድብ አበጅቶለታል፡፡ ይህ ማለት አንድ ሕገ-ወጥ ሐዋላ አገልግሎት የሚሠራ አካል ከአካውንቱ ወደ ተለያዩ ሰዎች ገንዘብ ማዘዋወር ካልቻለ ለተቀባዮች ገንዘቡን ማድረስ አይችልም፡፡ በዚህ ምክንያት ቀድሞ ሲሠራ ነበረው ሕገ-ወጥ ሥራ በግዴታ ለመተው ይገደዳል፡፡
ያም ሆኖ መመሪያው በተወሰነ መልኩም ቢሆን በንግድ እንቅስቃሴው ላይ የተሰማሩት ነጋዴዎች ለጉዳት መዳረጉ ማንንም የማያጠራጥር ጉዳይ ነው፡፡ መመሪያው በሁሉም የሒሳብ ደብተሮች ተፈጻሚ አለመሆኑ እና የድርጅቶች የሒሳብ ደብተር ይህ አሠራር የማይመለከታቸው መሆኑ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ሊያቃልል ይችላል፤ ተቋማት ለሠራተኞቻቸው የሚከፍሉት ደሞዝ መመሪያው አይመለከተውም፡፡ በንግድ እንቅስቀሴ ላይ የተሰማሩ ዜጎች መመሪያው የሥራ እንቅስቃሴያቸውን የሚጎዳው ከሆነ፣ ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት ለማቃለል የባንክ ፕሬዝዳንቶች ልዩ ፈቃድ እንዲሰጡ መብት እና ኀላፊነትን ሰጥቷቸዋል፡፡ ምናልባት እያንዳንዱ የንግድ ተዋናይ የባንክ ፕሬዝዳንት ጋር ደርሶ እልባት ማግኘቱ የራሱ የሆኑ አድካሚ ሁኔታ ነው፡፡
ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ያለው መመሪያ ለማውጣት የተገደደው በባንክ ቤት እና በትይዩ ገበያው ላይ ያለው የምንዛሪ ተመን ልዩነቱ እጅግ በጣም እየሰፋ በመምጣቱ ምክንያት ነው፡፡ ምናልባት ብሔራዊ ባንክ በሕገ-ወጥ መልኩ በሐዋላ በኩል ወደ ጥቁር ገበያው የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ መንገድ ሲዘጋው ዶላሩ በሌላ ሕገ ወጥ መስመር ሊመጣ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሐዋላ የሚላከው የውጭ ምንዛሪ ገንዘብ በዋናነት የትይዩ ገበያው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከ2 እስከ 3 ቢሊዮን የሚደርስ ዶላር ወደ አገር ውስጥ ይገባል፡፡
በግሌ ይህ ዓይነቱ መመሪያ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ይፈታዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ሊፈታ የሚችለው የውጭ ምንዛሪ ተመኑ ትክክለኛን ዋጋ እንዲያገኝ ማደረግ ሲቻል እና በበቂ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ግኝት አቅምን ማሳደግ ሲቻል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መመሪያ ቁንጽል ነገርን እንጂ ትልቁን ነገር ይቀይረዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡
Leave a Reply