የመደመር ፍልስፍና እና የኢኮኖሚ ሳይንስ | ጌታቸው አስፋው
ኢኮኖሚ

የመደመር ፍልስፍና እና የኢኮኖሚ ሳይንስ | ጌታቸው አስፋው

እግዚአብሔር ሰላሙን ቶሎ ይስጠን እንጂ በኢኮኖሚ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ሥርዓቶቻችን ሥር ነቀል ለውጦች ማድረግ የኢትዮጵያ ቀዳሚ ተግባሮች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይበጀናል ያሉትን የለውጥ ፍልስፍና ባሳተሙት የመደመር መጽሐፍ አስቀምጠዋል፡፡ ለየት ያለ አማራጭ ማቅረብ ወይም በቀረበው ላይ ማሻሻያ ወይም ማጠናከሪያ ወይም መቃወሚያ ሐሳብ መሰነንዘር ከምሁራን ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳ ምሁራን በቴሌቪዥን ፍልስፍናን በፍለስፍና የድጋፍ ማብራሪያና መግለጫ ሲሰጡ የተመለከትሁ ቢሆንም፣ በኢኮኖሚው በማኅበራዊው በፖለቲካው ተለይቶ በየሙያቸው ከፍተኛ ምርምር ያደረጉ ምሁራን ፍልስፍናውን በየሙያቸው ጠንከር ያለ ሌላ አማራጭ ወይም መቃወሚያ ለማቅረብ የሞከረ ወይም ማሻሻያና ማጠናከሪያ እስከዛሬ ቀርቦ አላየሁም፡፡  በየሙያቸው ምርምር ለሚያደርጉ ምሁራን ፋና-ወጊ ለመሆን ምንም እንኳ በዚህ የጦርነት ወቅት ስለ ኢኮኖሚ ቢጻፍና ቢነገር፣ የሚያነብ ዓይን እና የሚሰማ ጆሮ ማግኘት የሚቻል ባይመስልም፣ ኢኮኖሚው ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማሰብ ሐሳቡን በአእምሮ ይዞ ሰላም ሲመጣ እንደ አዲስ ማንሳትም እንደሚቻል በመገመትም ያለኝን ለመሰንዘር ይህችን አጭር ጽሑፍ ለማቅረብ ወሰንኩ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ኢሕአዴግ ይከተላቸው ከነበሩት የሊብራል እና የልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ አስተዳደር (የነጻ ገበያና የመንግሥታዊ ዕቅድ ጥምረቶች የተለያየ ቅንብር) ፍልስፍናዎች የትኛውን እንደሚከተል ማወቅ አቅቷቸው ግራ እንደተጋቡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችንም ጨምሮ ብዙ ሰዎች ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን የብልጽግና ፖለቲካል ኢኮኖሚማ መደመር ነው ብለው ይናገራሉ፡፡ ኢኮኖሚውን በሚመሩት የፖሊሲ መሥሪያ ቤቶች ግን በሚያቅዷቸው ዕቅዶች እና በሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች የመደመር ፍልስፍናን መመሪያቸው ስለማድረግ አለማድረጋቸው በግልጽ ያመላከቱት ነገር የለም ፖሊሲን የተመለከቱ ጽሑፎቻቸውንም ከመንግሥት ውጪ ያሉ ሰዎች እንዲያውቁ አሳትመው ለሕዝብና ለአገር ውስጥ ምሁራን ስለማያቀርቡ ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

ኢኮኖሚክስ የፍልስፍና አንድ አካል ከመሆን ወጥቶ ራሱን የቻለ ሳይንስ የሆነበትን ጊዜና ሁኔታ በምጽፋቸው የጋዜጣ ላይ ጽሑፎች ከአንድም ሁለት ጊዜ ከመጥቀሴም በላይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡት የኢኮኖሚክስ ምስክር ወረቀቶችም አርትም ሳይንስም ተብለው እንደሚጠሩም እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ ለእኔ የተሰጠኝ የምስክር ወረቀት በብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ዝግጅት ኢኮኖሚክስ የሳይንስ ማስትሬት ዲግሪ (MSC) የሚል ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ የአርት (ጥበብ) ዲግሪ ያገኛሉ፡፡ አውሮፓውያን ከፍልስፍና ወደ ሳይንስ ከተሸጋገሩ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ቢሆንም ታዳጊ አገሮች ዛሬም ፍልስፍናው ላይ እንደመዥገር እንደተጣበቁ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያማ ፍልስፍናው ጸጉር ስንጠቃ ያህል ቅጥ ያጣ ሆኗል፡፡

በደርግ ዘመን ጌታቸው ቦሎዲያ የተባሉ ዕውቅ ኢትዮጵያዊ የባዮኬሚስትሪ ሊቅ ከሐረር ወደ ዓለማያ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር ሲሄዱ መንገድ ላይ ያሳፈሯትን ኮረዳ ምንድን ነው የምታጠኚው? ብለው ጠይቀዋት ፖለቲካል ሳይንስ ነው ስላለቻቸው ዩነቨርሲቲው እንደደረሱ፤ “በይ ሳይንሱን ለእኔ ትተሽ ፖለቲካውን ይዘሽ ውረጂ” አሏት ተብሎ አንድ ሰሞን ይወራ ነበር፡፡ በዚህ ዘመንም ሳይንሱን በተማሩበትና ባስተማሩበት  ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አውልቀው የጣሉና ፖለቲካውን ብቻ ይዘው ከግቢው የወጡ ምሁራን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ካላጠናቀቁ ሰዎች እኩል በፖለቲካው ኢትዮጵያን ያምሷታል፤ እንደ ጤዛ ለሚረግፍ ዝናና ታዋቂነት ሲሉ እናትና ሕፃናትን በገጀራና በጦር ያስገድላሉ፡፡

ኢኮኖሚክስ የፍልስፍና አካል በነበረበት ጊዜ ጥንት የአሪስቶትል መምህር የነበረው ፕሌቶ ሀብት በመንግሥት እጅ ቢሆን በፍትሐዊነት ለመከፋፈል ይጠቅማል ብሎ ከማሰብም በላይ በፖለቲካውም በዘር የሚወረስ ዘውዳዊና መሳፍንታዊ ሥርዓትን ሲመርጥ ተማሪው አሪስቶትል ግን የሀብት ይዞታ በመንግሥት እጅና በግለሰብ እጅ ሊያዙ የሚገባቸው ተብለው ቢለዩ ንግድ ግን በሥነ ምግባር ቢመራና በሕግ ቢከበር እንደሚጠቅም ያስብ ነበር፡፡ በመካከለኛው ዘመን የኖረው ኢጣሊያዊው የሃይማኖት ሰውና የኢኮኖሚክስ ጸሐፊ ቶማስ አኳይነስም ነጋዴ ከማምረቻ ወጪ ጋር የተገናዘበ ትክክለኛውን የሸቀጥ ዋጋ ብቻ የመጠየቅ ግብረገባዊ ኀላፊነት አንዳለበት ያሳስብ ነበር፡፡ በየዘመናቱ ሌሎች የፍልስፍና የሃይማኖት እና የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪና ጸሐፊዎችም ስለ ኢኮኖሚ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፤ ጽፈዋል፡፡ ኢኮኖሚክስ ከፍልስፍናና ግብረገባዊ ሥነ ምግባር አስተሳሰብ ቀስ በቀስ ራሱን እያላቀቀ ወደ የማኅበራዊ ጥናት ሳይንስነት የተጓዘበት ሂደት ረጅም ነው፡፡

ከክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ቀደም ብሎ በዐሥራ ሰባተኛውና ዐሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የኒውተንን የእንቅስቃሴና የተፈጥሮ ስበት (ግራቪቲ) ሕግ ተውሶ በማመሳሰል ሪቻርድ ካንቲሎን የተባለ አይሪሽ ነጋዴና ኢኮኖሚስት ሌላውን ሳያታልሉ በሐቅ የግል ጥቅምን መሻት በውድድር መሳሳብና መጓተት ሕግ ራሱን በራሱ የሚያስተካክል የገበያ ዋጋ አወሳሰን ሥርዓትን ይፈጥራል በማለት አስገንዝቧል፡፡ በተፈጥሮ ሳይንስ ከሚያምኑት ፊዝዮክራትስ ተብለው ከሚጠሩት አንዱ በዚህ በእኛ ዘመን የብሔራዊ ኢኮኖሚ ገቢ ፍሰት ዙር (Circular Flow of Income) በመባል ለሚታወቀው የሐሳብ ጽንስ የሆነውን የኢኮኖሚ ሠንጠረዥ (Tableau Economic) የፈለሰፈው ፈረንሳዊው ፍራንሷ ኩዌስኒም ሳይንሱን ያመሳሰለው በሰው ደም ሥር ውስጥ ከሚዘዋወረው ደም የተፈጥሮ ሳይንስ ጋር ነው፡፡ ከነዚህ ከጥንት ጀምሮ ሲወርዱ ሲዋረዱ ከመጡ አስተሳሰቦች በኋላ ነው እንግዲህ በአዳም ስሚዝና በኢንዱስትሪው አብዮት ኢኮኖሚክስ ሙሉ በሙሉ ከፍልስፍና ውስጥ ወጥቶ ራሱን ችሎ የማኅበራዊ ጥናት ሳይንስ የሆነው፡፡

አዳም ሰሚዝ እያንዳንዱ ሰው ሰነፍና አልምጥም እንኳ ቢሆን ለራሱ ለመጠቀም ብሎ በሚያመርተው ምርት ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ምርት ስለሚያመርት የተፈጥሮ ነጻነቱን በመንግሥትም ሆነ በማንም መነጠቅ የለበትም ይላል፡፡ የአዳም ስሚዝን ነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ወደፊት ያራመደው ተከታዩ የሆነው ፈረንሳዊው ኢኮኖሚስት ጂን ባፕቲስት ሴይ አመለካከቱን የገለጸው፣ “የሴይ ሕግ” ተብሎ በሚታወቀው ሰው የሚያመርተውን መጠን የሚወስነው ምርቱን ሽጦ ለመሸመት በሚፈልገው የሌላ ሰው ምርት ልክ ስለሆነ ምንጊዜም አቅርቦት የራሱን ፍላጎት ይፈጥራል፤ ስለሆነም ማምረት የአቅርቦት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የፍላጎት ምልክትም ስለሆነ አቅርቦትና ፍላጎት እኩል ይሆናሉ በሚል የሒሳብ መልክ ስሌት ደረጃ ነው፡፡ በሴይ እምነት ከቤተሰቦች ገቢ ውስጥ ከፊሉ ለፍጆታ ሳይወጣ ቢቆጠብም ዘግይቶም ቢሆን ቁጠባ በመዋዕለንዋይ መልክ ወጪ ይደረጋል፡፡ ፍጆታና መዋዕለንዋይ ሁለቱ የፍላጎት ዓይነቶች ናቸውና ምርት አቅርቦት ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም በመሆኑ ፍላጎትና አቅርቦት እኩል የማይሆኑበት ጊዜ የለም፡፡ በርግጥ ሁለቱን እኩል የሚያደርጋቸው የገበያ ማጣሪያ ዋጋ (Market Clearing Price) የሚወሰነው በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር በገበያ ውስጥ ነው፡፡ ባለንበት ዘመን የኢኮኖሚ ትንታኔ ዕድገት ደረጃም በብሔራዊ ኢኮኖሚ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በገቢ መንገድ በወጪ መንገድ እና በምርት ቆጥራ መንገድ ተለክቶ በሦስቱም መንገዶች እኩል በመሆኑም የፍላጎትና የአቅርቦት እኩልነት የተረጋገጠ ነው፡፡

በሥራ አጥነት ምክንያት የፍጆታ ከአቅርቦት ማነስ ጽንሰ ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀነቀነው ስለ ሕዝብ ቁጥር ዕድገትና የምርት እጥረት ተንትኖ በጻፈው በሌላው የክላሲካል ኢኮኖሚስት በቶማስ ማልተስ ሲሆን፣ ይህም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተከሰተው ታላቁ የኢኮኖሚ ዝቅጠት ተነስቶ ኢኮኖሚክስን ከዋጋ አወሳሰን የማይክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት በተለየ መንገድ የጥቅል አገራዊ ገቢ ማክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት አድርጎ በፍላጎት አስተዳደር ኢኮኖሚክስ (Demand Management Economics) ለተነተነው ለጆን ሜናርድ ኬንስ ጥናት መሠረት ሆኗል፡፡ ጆን ሜናርድ ኬንስ አገር የማምረት ሙሉ አቅሟን ባለመጠቀም ያልተፈለገ ሥራ አጥነት ወይም ሥራ ለመሥራት ፈልጎ አለማግኘት (Involuntary Unemployment) ሲፈጠር የታቀደ የምርት ፍላጎት ከታቀደ የምርት አቅርቦት እንደሚያንስና መንግሥት በበጀት ወይንም በጥሬ ገንዘብ ፖሊሲው ተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጥሮ የጎደለውን የታቀደ ፍላጎት መሙላት እንዳለበት አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ሥራ አጥነት መሆኑን የሚቀበሉ አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች ግን ኬንስ የተነተነው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓና በአሜሪካ ስለነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ስለሆነ የአቅርቦት እንጂ የፍላጎት ችግር ከሌለበት ከእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አይመሳሰልም ይላሉ፡፡ እነዚህ ኢኮኖሚስቶች ያልገባቸው ነገር ያልተፈለገ ሥራ አጥነት እስካለ ድረስ የአገሪቱን የማምረት ሙሉ አቅም አሟጦ በመጠቀም በፍላጎት ጎን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተጨማሪ የምርት ፍላጎትን በመፍጠር አቅርቦትንም ማሳደግ ይቻላል የሚለው የኬንስ ማክሮ ኢኮኖሚክስ ትንታኔ ለአውሮፓና ለአሜሪካ እንደሠራው ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምደን ብንተገብረው ለእኛም እንደሚሠራ ነው፡፡

ኒዮ-ክላሲካል የሚባሉ እንደ አልፍሬድ ማርሻል፣ ካርል መንገር፣ ልዮን ዎልራስ ፍሬድሪክ ቮን ዋይዘር እና ሰታንሌ ጄቨንስን የመሳሰሉ የዐሥራ ስምንተኛውና ዐሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ኢኮኖሚስቶችም ቀጣይ ጠቀሜታን (Marginal Utility) እና ቀጣይ ትርፋማነትን (Marginal Productivity) በመለካት የዋጋ አወሳሰን መሠረቶችም በማድረግ የሸቀጥ ፍላጎትና የሸቀጥ አቅርቦት ምንጮችን በሒሳብ ስሌት ለመለካት ሞክረዋል፡፡ ኖርዌያዊው ጃን ቲንበርገን ኢኮኖሜትሪክስን በመጀመር፣ ሩስያዊ አሜሪካዊው ቫሲሊ ሊዮንቲፍ የግብዓተምርትና የምርት ተዛምዶ ሠንጠረዥን በማስተዋወቅ፣ ሩስያዊው ሊዮኒድ ካንቶሮቪች ሊንየር ፐሮግራሚንግ የተባለውን የሒሳብ ስሌት ዓይነት በማስተዋወቅ፣ እንግሊዛዊው ጆን ሂክስ በኬንስ መንገድ ቁጠባና መዋዕለንዋይን እኩል የሚያደርጋቸውን የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት (የጥሬ ገንዘብ ገበያ እኩልነት) እና በገቢ መጠን (የምርት ገበያ እኩልነትን) ጥምረት (IS-LM Equilibrium Model) በመተንተን፣ ሩስያዊ አሜሪካዊው ሲሞን ኩዝኔትስ በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ስሌት፣ ኢጣሊያዊው ቪልፈርዶ ፓሬቶ በላቀ የሀብት ድልድል ሒሳብ (Pareto Efficiency)፣ አሜሪካዊው ኢኮኖሚስት አርተር ላፈር የግብር መጣኝ ከተወሰነ መጠን በላይ ቢሆን በግብር የሚሰበሰበውን ገንዘብ መጠን እንደሚቀንሰው በስሌት በማረጋገጥ፣ የልማት ኢኮኖሚስቱ የአማርተያሴን ሥራዎች ብዙዎቹን የተባበሩት መንግሥታትን የሰዋዊ ልማት አመልካቾችን (Human Development Index) ለመለካት በመርዳት ኢኮኖሚክስን የሒሳብ ሳይንስ እንዲሆን ካደረጉ ኢኮኖሚስቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ይህ ሁሉ የሒሳብ ጋጋታ ለእኛ በስድ ንባብ ጽሑፍ ከመፈላሰፍ በቀር አራቱ መደብ ሒሳቦች መደመርና መቀነስ ማባዛትና ማካፈል ለሚከብደን ሰዎች ምን ይሠራልናል? የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሒሳብ ምንጊዜም ወደ እርግጠኝነት ለመቃረብ የሚያገለግል መሣሪያ ይሁን እንጂ አቅጣጫን ተመልክቶ ለመገንዘብም ይረዳል፡፡ ቁጥሩ ላይ እርግጠኛ ሳይሆኑም አቅጣጫውን ብቻ በማየትም ላይ ይወጣል ታች ይወርዳል ወደ ግራ ቀኝ ይጠባል ይሰፋል በማለት መግለጽም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ዋጋ ሲጨምር ፍላጎት መቀነሱን ዋጋ ሲቀንስ ፍላጎት መጨመሩን በአቅጣጫ አመልካችም ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እርግጠኛ ለመሆን መለካት ስንችል እንለካለን እስከዚያው ግን አቅጣጫን በመመልከት ብቻ ውሳኔ መስጠት እንችላለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በመደመር መጽሐፋቸው (ገጽ 52) አጭር፣ ረጅም፣ ትንሽ፣ ትልቅ ከማለት ይልቅ በቁጥር የመለካትን ጥቅም ጽፈዋል:: ዶ/ር ዐቢይ ሆይ ሁሉም ነገርኮ የሚሆነው ሲያስፈልግና ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰውን ለመግለጽ አጭር ረጅም ወፍራም ቀጭን ከማለት የቅቡል ደረጃ (Standard) መለኪያ በቀር ሜትርና ሚዛን ይዞ በየደረሱበት  ያገኙትን ሁሉ ወዲህ ና ልለካህ ማለት አይቻልም፡፡

ኢኮኖሚክስ የፍልስፍና አካል ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሳይንስነት የመጣበትን ጊዜያትና ሁኔታዎች ተመልክቶ የመደመር ፍልስፍና በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ሳይተነተን በፊት የአንድ አገረ መንግሥት መመሪያ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍልስፍና መሆን ቀርቶ የአንድ መካከለኛና መለስተኛ ግብ የፖሊሲ ጽንሰ ሐሳብም መሆን እንደማይችል ማስረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን ዶ/ር ዐቢይ ራሳቸው ፍልስፍናውን በሳይንሳዊ ኢኮኖሚክስ ይተንትኑት ማለት አይደለም፡፡ ኢኮኖሜትሪክስ (ኢኮኖሚ ልኬት) የተባለው ኢኮኖሚክስን በሒሳብ ስሌት ማመልከት ባልተጀመረበት ጊዜ አመለካከታቸውን በጽንሰ ሐሳብ የገለጹ ብዙ የኢኮኖሚክስ ሊቃውንት ከነርሱ በኋላ የመጡ ተከታዮቻቸው ጽንሰ ሐሳቦቹን በስሌት ማረጋገጥ እንደቻሉ ይታወቃል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ በጥቅል አመለካከት ስለ መደመር ሲፈላሰፉ የጋራ አካፋይ ስለሌላቸው በግና ጤፍ አንድ ላይ መደመር እንደማይቻል ያውቃሉ፡፡ ሆኖም ግን ጊዜያቸውን ጠብቀው በጉ ስጋ ወጥ ሆኖ ጤፉም እንጀራ ሆኖ በንጥረ-ነገራቸው ተደምረው ለሰውነታችን ገንቢ ምግብ እንደሚሆኑም ያውቃሉ፡፡ መጠናቸውና ቅንብራቸው የሚለካው ግን በዶ/ር ዐቢይ ሳይሆን በሥርዓተ-ምግብ ባለሙያ ነው፡፡ የውጭ ጠላት ሲመጣ ሀብታሙና ድሃው በፍላጎት ይደመራሉ፤ በሰላም ጊዜ ግን በአስገዳጅ ሁኔታ ብቻ ነው የሚደመሩት፡፡ በኢኮኖሚውም ምንና ምን መቼና እንዴት እንደሚደመሩ መመራመርና ማጥናት የኢኮኖሚስቱ ሥራ እንጂ የዶ/ር ዐቢይ አይደለም፡፡ በኢኮኖሚክስ ተመራማሪው ይህ እስከሚሆን ድረስ መደመር ፍልስፍና ብቻ እንጂ የኢኮኖሚ ሳይንስ ሊሆን አይችልም፡፡ ለመደመርም ለመቀነስም ጊዜና ቦታ አለው፡፡ ያን ጊዜና ቦታ ፈልጎ ማግኘት  የስፔሻሊስት ባለሙያው ሥራ ነው፡፡

ዓለም እስከዛሬ የሚያውቀው ሁለት ጫፍና ጫፍ ላይ ያሉ ካፒታሊዝምን እና መደብ አልባ ኮሙኒዝም የኢኮኖሚ ሥርዓቶችን ቢሆንም ወደ አንዱ ወይም ወደ ሌላው በማጋደል የሁለቱ ጥምረት እንጂ ጫፍ የረገጠ አገር የለም፡፡ በካፒታሊዝም የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት በጽንሰ ሐሳብም ሆነ በስሌት ፍላጎት፣ አቅርቦት፣ የፍላጎትና የአቅርቦት እኩልነት፣ የፍላጎት ለውጥ፣ የአቅርቦት ለውጥ፣ የገቢና የፍጆታ ተዛምዶ፣ የወለድ መጣኝ እና የመዋዕለንዋይ ተዛምዶ ወዘተ… በማለት በሳይንሳዊ መንገድ ለመተነተን ኢኮኖሚስቶች ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሆኖም ሸማቹም አምራቹም ጥቅማቸውን እና ትርፋቸውን የላቀ ለማድረግ ይፈልጋሉ የሚለው የክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ኢኮኖሚክስ ታሳቢዎች (Assumptions) የዚህን ዘመን ሰው ኢኮኖሚያዊ ባሕርይና ተግባር ስላላንጸባረቁ እንደ ሮበርት ሉቃስን፣ ኤድዋርድ ፕሬስኮትን፣ ቶማስ ሳርጀንትን፣ ፊን ኪድላንድን የመሳሰሉ የኖቤል ተሸላሚ የክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ደጋፊዎች በማይክሮ ደረጃም ሆነ በማክሮ ደረጃ ሳይንሱን እንደገና ለመመርመር ተገደዋል፡፡ እነ ጆሴፍ ስቲግሊዝ ደግሞ ችግሩ የመረጃ አለመዳረስ ነው ይላሉ፡፡ በአገራችን የምናየውን ሸማቹ ጠቀሜታውን ሳይለካ ከአገኘበት ቦታ መግዛቱንና አምራቹ ለራቱ ካገኘ በቃኝ ብሎ ድርጅቱን ለወደፊት ለማስፋፋት አለመፈለጉን አዲሶቹን ለክላሲካል ኢኮኖሚስቶችን ግራ ያጋባው ጠቀሜታን እና ትርፋማነትን በአመክንዮ ለመለካት አለመቻል (Irrationality) እምነት ተምሳሌት ነው ልንል እንችል ይሆን? ወይስ የመረጃ እንደልብ አለመዳረስ ነው? የእኛ ኢኮኖሚስቶችስ ስለዚህ ዓይነቱ የገበያ ውጥንቅጥ ምን ይላሉ? የሕዝባችንን ኢኮኖሚያዊ ባሕርይና ተግባር ማጥናት የእኛ ፋንታ ነው እንጂ ፈረንጅ አጥንቶ እስከሚነግረን የምንጠብቀው ጉዳይ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል የፈረንሳይ አብዮት የተካሄደበትን ሐሳባዊ ሶሻሊዝም (Utopian socialisem) የዋህነት ነው በማለት ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን በመደብ ትግል የተነተነው በካፒታሊስት ሥርዓት ዕሴት የሚፈጠርበትን የእነ ሪካርዶ ጽንሰ ሐሳብ ተውሶ ካፒታሊስቱ ወዛደሩን የሚበዘብዝበት ሥርዓተ አድርጎ በሳይንሳዊ ዘዴ የተነተነው ካርል ማርክስ በሶሻሊዝም አድርጎ ወደ ኮሙኒዝም የሚኬድበትን መንገድ ከመፈላሰፍ ሌላ በሳይንሳዊ ዘዴ ስላልተነተነ ይህም አልበቃ ብሎ እነ ሌኒን በኋላ ቀር አገር ውስጥ በአቋራጭ ሶሻሊስት ማኅበረሰብ ለመፍጠር ስለሞከሩ ከሰባ ዓመት አጭር ጉዞ በኋላ ፍልስፍናው ተቀጨ፡፡ ሆኖም እስካሁንም ድረስ ዓለም የኋላ ኋላ ወደዚያው እንደምትሄድ በካፒታሊዝም ውስጥ እያደገ የመጣው የብዝበዛ ዓይነት ያመለክታል ብለው የሚያምኑና እየተገነባ ያለውን የካፒታሊዝም ዓይነት እየኮነኑ ያሉ ዕውቅ ኢኮኖሚስቶች አሉ፡፡ የበለጸገች አገር በምትባለዋ አሜሪካ እንኳ እኛ ዘጠና ዘጠኝ በመቶዎቹ ለፍቶ አዳሪዎች እና አንድ በመቶዎቹ በዝባዝ ቅምጥሎች በመባል ማኅበረሰቡ በመደብ ተከፋፍሏል፡፡ በካፒታሊስት ሥርዓተ-ኢኮኖሚ ውስጥ ሆኖ ፈጣን ዕድገት ለማምጣት ይበጃል የተባለው የታዳጊ አገሮች የልማታዊ መንግሥት ፖለቲካል ኢኮኖሚም ቢሆን በአንዳንድ የእስያ አገሮች በተግባር ስለመረጋገጡ እንጂ ወጥ የሆነ ዓለም ዐቀፋዊ (Universal) የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ ተነድፎለት እንደ አቻው ሊብራል ካፒታሊዝም በሒሳብ ሳይንስ ታግዞ የሚጓዝ ስላልሆነ እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ በአምባገነናዊም በዴሞክራሲያዊም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት ስለሚተገበር ሳይንሳዊነቱ በትክክል የተረጋገጠ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ፍልስፍና ብቻውን የአገር ኢኮኖሚ ለማስተዳደር በቂ እንዳልሆነ ያልተረዱ የመንግሥት ሹማምንትና ዋናው ችግራችን የመዋዕለንዋይ እጥረት ነው የሚሉ የኢኮኖሚ ባለሟሎች በጽሑፍ ባላይም በቃለ መጠይቅ የኢኮኖሚ ፍልስፍናችን መደመር ነው ሙሉ አቅማችንን የምናውለውም ለአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚክስ (Supply Side Economics) ነው ኬንስ ማክሮ ኢኮኖሚን ሲተነትን በአውሮፓና በአሜሪካ የነበረው ሁኔታ አሁን እኛ ካለንበት ሁኔታ ጋር አይመሳሰልም፤ መንግሥታዊ ዕቅዶቻችንንም በውጭ ኮንሰልታንቶችም ጭምር አስጠንተናል ወዘተ… ይላሉ፡፡ ለመሆኑ የትኛው የውጭ ኮንሰልታንት ነው የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የሕዝቡን ኑሮ ደረጃ የሚያውቀው? ኧረ ለመሆኑ በውጭ ኮንሰልታንቶች ታግዞ የታቀደው የዐሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ በመነሻው ዓመት በ2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ያህል እንደሚያድግ ታቀደ በዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ስለተተነበየው የባዶ ኢኮኖሚ ዕድገትስ ምን ማለት ይቻላል? የመጀመሪያው ዓመት በትክክል ሳይታቀድ የመጨረሻው ዓመት እንዴት በትክክል ይታቀዳል?

እነኚህን የመሳሰሉ የአገራችን ወሳኝ ጉዳዮች የሚፈቱት በሳይንሳዊ መንገድ ቢቻል ደግሞ በስሌት ሳይንሳዊ መንገድ እንጂ በፍልስፍና ወሬ አይደለም፡፡ በተለይ ሒሳብን በፍጥነት የሚቀበል አእምሮ ያላችሁ ወጣት ኢኮኖሚስቶችና ሌሎች ምሁራን ከፍልስፍናው ቀነስ አድርጋችሁ የስሌት ሳይንሱንም ሞክሩት፡፡ ይህ ካልሆነ አገሮችን ከድህነት አዙሪት ውስጥ ልትወጣ እንደማትችል አበክሬ ላስገበዝባችሁ እወዳለሁ፡፡

November 25, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *