የመደመር ፍልስፍና እና የኢኮኖሚ ሳይንስ | ጌታቸው አስፋው
ኢኮኖሚ

የመደመር ፍልስፍና እና የኢኮኖሚ ሳይንስ | ጌታቸው አስፋው

እግዚአብሔር ሰላሙን ቶሎ ይስጠን እንጂ በኢኮኖሚ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ሥርዓቶቻችን ሥር ነቀል ለውጦች ማድረግ የኢትዮጵያ ቀዳሚ ተግባሮች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይበጀናል ያሉትን የለውጥ ፍልስፍና ባሳተሙት የመደመር መጽሐፍ አስቀምጠዋል፡፡ ለየት ያለ አማራጭ ማቅረብ ወይም በቀረበው ላይ ማሻሻያ ወይም ማጠናከሪያ ወይም መቃወሚያ ሐሳብ መሰነንዘር ከምሁራን ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳ ምሁራን በቴሌቪዥን ፍልስፍናን በፍለስፍና የድጋፍ ማብራሪያና መግለጫ ሲሰጡ የተመለከትሁ ቢሆንም፣ በኢኮኖሚው በማኅበራዊው በፖለቲካው ተለይቶ በየሙያቸው ከፍተኛ ምርምር ያደረጉ ምሁራን ፍልስፍናውን በየሙያቸው ጠንከር ያለ ሌላ አማራጭ ወይም መቃወሚያ ለማቅረብ የሞከረ ወይም ማሻሻያና ማጠናከሪያ እስከዛሬ ቀርቦ አላየሁም፡፡  በየሙያቸው ምርምር ለሚያደርጉ ምሁራን ፋና-ወጊ ለመሆን ምንም እንኳ በዚህ የጦርነት ወቅት ስለ ኢኮኖሚ ቢጻፍና ቢነገር፣ የሚያነብ ዓይን እና የሚሰማ ጆሮ ማግኘት የሚቻል ባይመስልም፣ ኢኮኖሚው ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማሰብ ሐሳቡን በአእምሮ ይዞ ሰላም ሲመጣ እንደ አዲስ ማንሳትም እንደሚቻል በመገመትም ያለኝን ለመሰንዘር ይህችን አጭር ጽሑፍ ለማቅረብ ወሰንኩ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ኢሕአዴግ ይከተላቸው ከነበሩት የሊብራል እና የልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ አስተዳደር (የነጻ ገበያና የመንግሥታዊ ዕቅድ ጥምረቶች የተለያየ ቅንብር) ፍልስፍናዎች የትኛውን እንደሚከተል ማወቅ አቅቷቸው ግራ እንደተጋቡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችንም ጨምሮ ብዙ ሰዎች ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን የብልጽግና ፖለቲካል ኢኮኖሚማ መደመር ነው ብለው ይናገራሉ፡፡ ኢኮኖሚውን በሚመሩት የፖሊሲ መሥሪያ ቤቶች ግን በሚያቅዷቸው ዕቅዶች እና በሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች የመደመር ፍልስፍናን መመሪያቸው ስለማድረግ አለማድረጋቸው በግልጽ ያመላከቱት ነገር የለም ፖሊሲን የተመለከቱ ጽሑፎቻቸውንም ከመንግሥት ውጪ ያሉ ሰዎች እንዲያውቁ አሳትመው ለሕዝብና ለአገር ውስጥ ምሁራን ስለማያቀርቡ ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

ኢኮኖሚክስ የፍልስፍና አንድ አካል ከመሆን ወጥቶ ራሱን የቻለ ሳይንስ የሆነበትን ጊዜና ሁኔታ በምጽፋቸው የጋዜጣ ላይ ጽሑፎች ከአንድም ሁለት ጊዜ ከመጥቀሴም በላይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡት የኢኮኖሚክስ ምስክር ወረቀቶችም አርትም ሳይንስም ተብለው እንደሚጠሩም እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ ለእኔ የተሰጠኝ የምስክር ወረቀት በብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ዝግጅት ኢኮኖሚክስ የሳይንስ ማስትሬት ዲግሪ (MSC) የሚል ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ የአርት (ጥበብ) ዲግሪ ያገኛሉ፡፡ አውሮፓውያን ከፍልስፍና ወደ ሳይንስ ከተሸጋገሩ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ቢሆንም ታዳጊ አገሮች ዛሬም ፍልስፍናው ላይ እንደመዥገር እንደተጣበቁ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያማ ፍልስፍናው ጸጉር ስንጠቃ ያህል ቅጥ ያጣ ሆኗል፡፡

በደርግ ዘመን ጌታቸው ቦሎዲያ የተባሉ ዕውቅ ኢትዮጵያዊ የባዮኬሚስትሪ ሊቅ ከሐረር ወደ ዓለማያ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር ሲሄዱ መንገድ ላይ ያሳፈሯትን ኮረዳ ምንድን ነው የምታጠኚው? ብለው ጠይቀዋት ፖለቲካል ሳይንስ ነው ስላለቻቸው ዩነቨርሲቲው እንደደረሱ፤ “በይ ሳይንሱን ለእኔ ትተሽ ፖለቲካውን ይዘሽ ውረጂ” አሏት ተብሎ አንድ ሰሞን ይወራ ነበር፡፡ በዚህ ዘመንም ሳይንሱን በተማሩበትና ባስተማሩበት  ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አውልቀው የጣሉና ፖለቲካውን ብቻ ይዘው ከግቢው የወጡ ምሁራን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ካላጠናቀቁ ሰዎች እኩል በፖለቲካው ኢትዮጵያን ያምሷታል፤ እንደ ጤዛ ለሚረግፍ ዝናና ታዋቂነት ሲሉ እናትና ሕፃናትን በገጀራና በጦር ያስገድላሉ፡፡

ኢኮኖሚክስ የፍልስፍና አካል በነበረበት ጊዜ ጥንት የአሪስቶትል መምህር የነበረው ፕሌቶ ሀብት በመንግሥት እጅ ቢሆን በፍትሐዊነት ለመከፋፈል ይጠቅማል ብሎ ከማሰብም በላይ በፖለቲካውም በዘር የሚወረስ ዘውዳዊና መሳፍንታዊ ሥርዓትን ሲመርጥ ተማሪው አሪስቶትል ግን የሀብት ይዞታ በመንግሥት እጅና በግለሰብ እጅ ሊያዙ የሚገባቸው ተብለው ቢለዩ ንግድ ግን በሥነ ምግባር ቢመራና በሕግ ቢከበር እንደሚጠቅም ያስብ ነበር፡፡ በመካከለኛው ዘመን የኖረው ኢጣሊያዊው የሃይማኖት ሰውና የኢኮኖሚክስ ጸሐፊ ቶማስ አኳይነስም ነጋዴ ከማምረቻ ወጪ ጋር የተገናዘበ ትክክለኛውን የሸቀጥ ዋጋ ብቻ የመጠየቅ ግብረገባዊ ኀላፊነት አንዳለበት ያሳስብ ነበር፡፡ በየዘመናቱ ሌሎች የፍልስፍና የሃይማኖት እና የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪና ጸሐፊዎችም ስለ ኢኮኖሚ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፤ ጽፈዋል፡፡ ኢኮኖሚክስ ከፍልስፍናና ግብረገባዊ ሥነ ምግባር አስተሳሰብ ቀስ በቀስ ራሱን እያላቀቀ ወደ የማኅበራዊ ጥናት ሳይንስነት የተጓዘበት ሂደት ረጅም ነው፡፡

ከክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ቀደም ብሎ በዐሥራ ሰባተኛውና ዐሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የኒውተንን የእንቅስቃሴና የተፈጥሮ ስበት (ግራቪቲ) ሕግ ተውሶ በማመሳሰል ሪቻርድ ካንቲሎን የተባለ አይሪሽ ነጋዴና ኢኮኖሚስት ሌላውን ሳያታልሉ በሐቅ የግል ጥቅምን መሻት በውድድር መሳሳብና መጓተት ሕግ ራሱን በራሱ የሚያስተካክል የገበያ ዋጋ አወሳሰን ሥርዓትን ይፈጥራል በማለት አስገንዝቧል፡፡ በተፈጥሮ ሳይንስ ከሚያምኑት ፊዝዮክራትስ ተብለው ከሚጠሩት አንዱ በዚህ በእኛ ዘመን የብሔራዊ ኢኮኖሚ ገቢ ፍሰት ዙር (Circular Flow of Income) በመባል ለሚታወቀው የሐሳብ ጽንስ የሆነውን የኢኮኖሚ ሠንጠረዥ (Tableau Economic) የፈለሰፈው ፈረንሳዊው ፍራንሷ ኩዌስኒም ሳይንሱን ያመሳሰለው በሰው ደም ሥር ውስጥ ከሚዘዋወረው ደም የተፈጥሮ ሳይንስ ጋር ነው፡፡ ከነዚህ ከጥንት ጀምሮ ሲወርዱ ሲዋረዱ ከመጡ አስተሳሰቦች በኋላ ነው እንግዲህ በአዳም ስሚዝና በኢንዱስትሪው አብዮት ኢኮኖሚክስ ሙሉ በሙሉ ከፍልስፍና ውስጥ ወጥቶ ራሱን ችሎ የማኅበራዊ ጥናት ሳይንስ የሆነው፡፡

አዳም ሰሚዝ እያንዳንዱ ሰው ሰነፍና አልምጥም እንኳ ቢሆን ለራሱ ለመጠቀም ብሎ በሚያመርተው ምርት ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ምርት ስለሚያመርት የተፈጥሮ ነጻነቱን በመንግሥትም ሆነ በማንም መነጠቅ የለበትም ይላል፡፡ የአዳም ስሚዝን ነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ወደፊት ያራመደው ተከታዩ የሆነው ፈረንሳዊው ኢኮኖሚስት ጂን ባፕቲስት ሴይ አመለካከቱን የገለጸው፣ “የሴይ ሕግ” ተብሎ በሚታወቀው ሰው የሚያመርተውን መጠን የሚወስነው ምርቱን ሽጦ ለመሸመት በሚፈልገው የሌላ ሰው ምርት ልክ ስለሆነ ምንጊዜም አቅርቦት የራሱን ፍላጎት ይፈጥራል፤ ስለሆነም ማምረት የአቅርቦት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የፍላጎት ምልክትም ስለሆነ አቅርቦትና ፍላጎት እኩል ይሆናሉ በሚል የሒሳብ መልክ ስሌት ደረጃ ነው፡፡ በሴይ እምነት ከቤተሰቦች ገቢ ውስጥ ከፊሉ ለፍጆታ ሳይወጣ ቢቆጠብም ዘግይቶም ቢሆን ቁጠባ በመዋዕለንዋይ መልክ ወጪ ይደረጋል፡፡ ፍጆታና መዋዕለንዋይ ሁለቱ የፍላጎት ዓይነቶች ናቸውና ምርት አቅርቦት ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም በመሆኑ ፍላጎትና አቅርቦት እኩል የማይሆኑበት ጊዜ የለም፡፡ በርግጥ ሁለቱን እኩል የሚያደርጋቸው የገበያ ማጣሪያ ዋጋ (Market Clearing Price) የሚወሰነው በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር በገበያ ውስጥ ነው፡፡ ባለንበት ዘመን የኢኮኖሚ ትንታኔ ዕድገት ደረጃም በብሔራዊ ኢኮኖሚ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት በገቢ መንገድ በወጪ መንገድ እና በምርት ቆጥራ መንገድ ተለክቶ በሦስቱም መንገዶች እኩል በመሆኑም የፍላጎትና የአቅርቦት እኩልነት የተረጋገጠ ነው፡፡

በሥራ አጥነት ምክንያት የፍጆታ ከአቅርቦት ማነስ ጽንሰ ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀነቀነው ስለ ሕዝብ ቁጥር ዕድገትና የምርት እጥረት ተንትኖ በጻፈው በሌላው የክላሲካል ኢኮኖሚስት በቶማስ ማልተስ ሲሆን፣ ይህም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተከሰተው ታላቁ የኢኮኖሚ ዝቅጠት ተነስቶ ኢኮኖሚክስን ከዋጋ አወሳሰን የማይክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት በተለየ መንገድ የጥቅል አገራዊ ገቢ ማክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት አድርጎ በፍላጎት አስተዳደር ኢኮኖሚክስ (Demand Management Economics) ለተነተነው ለጆን ሜናርድ ኬንስ ጥናት መሠረት ሆኗል፡፡ ጆን ሜናርድ ኬንስ አገር የማምረት ሙሉ አቅሟን ባለመጠቀም ያልተፈለገ ሥራ አጥነት ወይም ሥራ ለመሥራት ፈልጎ አለማግኘት (Involuntary Unemployment) ሲፈጠር የታቀደ የምርት ፍላጎት ከታቀደ የምርት አቅርቦት እንደሚያንስና መንግሥት በበጀት ወይንም በጥሬ ገንዘብ ፖሊሲው ተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጥሮ የጎደለውን የታቀደ ፍላጎት መሙላት እንዳለበት አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ሥራ አጥነት መሆኑን የሚቀበሉ አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች ግን ኬንስ የተነተነው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓና በአሜሪካ ስለነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ስለሆነ የአቅርቦት እንጂ የፍላጎት ችግር ከሌለበት ከእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አይመሳሰልም ይላሉ፡፡ እነዚህ ኢኮኖሚስቶች ያልገባቸው ነገር ያልተፈለገ ሥራ አጥነት እስካለ ድረስ የአገሪቱን የማምረት ሙሉ አቅም አሟጦ በመጠቀም በፍላጎት ጎን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተጨማሪ የምርት ፍላጎትን በመፍጠር አቅርቦትንም ማሳደግ ይቻላል የሚለው የኬንስ ማክሮ ኢኮኖሚክስ ትንታኔ ለአውሮፓና ለአሜሪካ እንደሠራው ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምደን ብንተገብረው ለእኛም እንደሚሠራ ነው፡፡

ኒዮ-ክላሲካል የሚባሉ እንደ አልፍሬድ ማርሻል፣ ካርል መንገር፣ ልዮን ዎልራስ ፍሬድሪክ ቮን ዋይዘር እና ሰታንሌ ጄቨንስን የመሳሰሉ የዐሥራ ስምንተኛውና ዐሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ኢኮኖሚስቶችም ቀጣይ ጠቀሜታን (Marginal Utility) እና ቀጣይ ትርፋማነትን (Marginal Productivity) በመለካት የዋጋ አወሳሰን መሠረቶችም በማድረግ የሸቀጥ ፍላጎትና የሸቀጥ አቅርቦት ምንጮችን በሒሳብ ስሌት ለመለካት ሞክረዋል፡፡ ኖርዌያዊው ጃን ቲንበርገን ኢኮኖሜትሪክስን በመጀመር፣ ሩስያዊ አሜሪካዊው ቫሲሊ ሊዮንቲፍ የግብዓተምርትና የምርት ተዛምዶ ሠንጠረዥን በማስተዋወቅ፣ ሩስያዊው ሊዮኒድ ካንቶሮቪች ሊንየር ፐሮግራሚንግ የተባለውን የሒሳብ ስሌት ዓይነት በማስተዋወቅ፣ እንግሊዛዊው ጆን ሂክስ በኬንስ መንገድ ቁጠባና መዋዕለንዋይን እኩል የሚያደርጋቸውን የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት (የጥሬ ገንዘብ ገበያ እኩልነት) እና በገቢ መጠን (የምርት ገበያ እኩልነትን) ጥምረት (IS-LM Equilibrium Model) በመተንተን፣ ሩስያዊ አሜሪካዊው ሲሞን ኩዝኔትስ በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ስሌት፣ ኢጣሊያዊው ቪልፈርዶ ፓሬቶ በላቀ የሀብት ድልድል ሒሳብ (Pareto Efficiency)፣ አሜሪካዊው ኢኮኖሚስት አርተር ላፈር የግብር መጣኝ ከተወሰነ መጠን በላይ ቢሆን በግብር የሚሰበሰበውን ገንዘብ መጠን እንደሚቀንሰው በስሌት በማረጋገጥ፣ የልማት ኢኮኖሚስቱ የአማርተያሴን ሥራዎች ብዙዎቹን የተባበሩት መንግሥታትን የሰዋዊ ልማት አመልካቾችን (Human Development Index) ለመለካት በመርዳት ኢኮኖሚክስን የሒሳብ ሳይንስ እንዲሆን ካደረጉ ኢኮኖሚስቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ይህ ሁሉ የሒሳብ ጋጋታ ለእኛ በስድ ንባብ ጽሑፍ ከመፈላሰፍ በቀር አራቱ መደብ ሒሳቦች መደመርና መቀነስ ማባዛትና ማካፈል ለሚከብደን ሰዎች ምን ይሠራልናል? የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሒሳብ ምንጊዜም ወደ እርግጠኝነት ለመቃረብ የሚያገለግል መሣሪያ ይሁን እንጂ አቅጣጫን ተመልክቶ ለመገንዘብም ይረዳል፡፡ ቁጥሩ ላይ እርግጠኛ ሳይሆኑም አቅጣጫውን ብቻ በማየትም ላይ ይወጣል ታች ይወርዳል ወደ ግራ ቀኝ ይጠባል ይሰፋል በማለት መግለጽም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ዋጋ ሲጨምር ፍላጎት መቀነሱን ዋጋ ሲቀንስ ፍላጎት መጨመሩን በአቅጣጫ አመልካችም ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እርግጠኛ ለመሆን መለካት ስንችል እንለካለን እስከዚያው ግን አቅጣጫን በመመልከት ብቻ ውሳኔ መስጠት እንችላለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በመደመር መጽሐፋቸው (ገጽ 52) አጭር፣ ረጅም፣ ትንሽ፣ ትልቅ ከማለት ይልቅ በቁጥር የመለካትን ጥቅም ጽፈዋል:: ዶ/ር ዐቢይ ሆይ ሁሉም ነገርኮ የሚሆነው ሲያስፈልግና ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰውን ለመግለጽ አጭር ረጅም ወፍራም ቀጭን ከማለት የቅቡል ደረጃ (Standard) መለኪያ በቀር ሜትርና ሚዛን ይዞ በየደረሱበት  ያገኙትን ሁሉ ወዲህ ና ልለካህ ማለት አይቻልም፡፡

ኢኮኖሚክስ የፍልስፍና አካል ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ሳይንስነት የመጣበትን ጊዜያትና ሁኔታዎች ተመልክቶ የመደመር ፍልስፍና በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ሳይተነተን በፊት የአንድ አገረ መንግሥት መመሪያ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍልስፍና መሆን ቀርቶ የአንድ መካከለኛና መለስተኛ ግብ የፖሊሲ ጽንሰ ሐሳብም መሆን እንደማይችል ማስረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን ዶ/ር ዐቢይ ራሳቸው ፍልስፍናውን በሳይንሳዊ ኢኮኖሚክስ ይተንትኑት ማለት አይደለም፡፡ ኢኮኖሜትሪክስ (ኢኮኖሚ ልኬት) የተባለው ኢኮኖሚክስን በሒሳብ ስሌት ማመልከት ባልተጀመረበት ጊዜ አመለካከታቸውን በጽንሰ ሐሳብ የገለጹ ብዙ የኢኮኖሚክስ ሊቃውንት ከነርሱ በኋላ የመጡ ተከታዮቻቸው ጽንሰ ሐሳቦቹን በስሌት ማረጋገጥ እንደቻሉ ይታወቃል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ በጥቅል አመለካከት ስለ መደመር ሲፈላሰፉ የጋራ አካፋይ ስለሌላቸው በግና ጤፍ አንድ ላይ መደመር እንደማይቻል ያውቃሉ፡፡ ሆኖም ግን ጊዜያቸውን ጠብቀው በጉ ስጋ ወጥ ሆኖ ጤፉም እንጀራ ሆኖ በንጥረ-ነገራቸው ተደምረው ለሰውነታችን ገንቢ ምግብ እንደሚሆኑም ያውቃሉ፡፡ መጠናቸውና ቅንብራቸው የሚለካው ግን በዶ/ር ዐቢይ ሳይሆን በሥርዓተ-ምግብ ባለሙያ ነው፡፡ የውጭ ጠላት ሲመጣ ሀብታሙና ድሃው በፍላጎት ይደመራሉ፤ በሰላም ጊዜ ግን በአስገዳጅ ሁኔታ ብቻ ነው የሚደመሩት፡፡ በኢኮኖሚውም ምንና ምን መቼና እንዴት እንደሚደመሩ መመራመርና ማጥናት የኢኮኖሚስቱ ሥራ እንጂ የዶ/ር ዐቢይ አይደለም፡፡ በኢኮኖሚክስ ተመራማሪው ይህ እስከሚሆን ድረስ መደመር ፍልስፍና ብቻ እንጂ የኢኮኖሚ ሳይንስ ሊሆን አይችልም፡፡ ለመደመርም ለመቀነስም ጊዜና ቦታ አለው፡፡ ያን ጊዜና ቦታ ፈልጎ ማግኘት  የስፔሻሊስት ባለሙያው ሥራ ነው፡፡

ዓለም እስከዛሬ የሚያውቀው ሁለት ጫፍና ጫፍ ላይ ያሉ ካፒታሊዝምን እና መደብ አልባ ኮሙኒዝም የኢኮኖሚ ሥርዓቶችን ቢሆንም ወደ አንዱ ወይም ወደ ሌላው በማጋደል የሁለቱ ጥምረት እንጂ ጫፍ የረገጠ አገር የለም፡፡ በካፒታሊዝም የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት በጽንሰ ሐሳብም ሆነ በስሌት ፍላጎት፣ አቅርቦት፣ የፍላጎትና የአቅርቦት እኩልነት፣ የፍላጎት ለውጥ፣ የአቅርቦት ለውጥ፣ የገቢና የፍጆታ ተዛምዶ፣ የወለድ መጣኝ እና የመዋዕለንዋይ ተዛምዶ ወዘተ… በማለት በሳይንሳዊ መንገድ ለመተነተን ኢኮኖሚስቶች ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሆኖም ሸማቹም አምራቹም ጥቅማቸውን እና ትርፋቸውን የላቀ ለማድረግ ይፈልጋሉ የሚለው የክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ኢኮኖሚክስ ታሳቢዎች (Assumptions) የዚህን ዘመን ሰው ኢኮኖሚያዊ ባሕርይና ተግባር ስላላንጸባረቁ እንደ ሮበርት ሉቃስን፣ ኤድዋርድ ፕሬስኮትን፣ ቶማስ ሳርጀንትን፣ ፊን ኪድላንድን የመሳሰሉ የኖቤል ተሸላሚ የክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ደጋፊዎች በማይክሮ ደረጃም ሆነ በማክሮ ደረጃ ሳይንሱን እንደገና ለመመርመር ተገደዋል፡፡ እነ ጆሴፍ ስቲግሊዝ ደግሞ ችግሩ የመረጃ አለመዳረስ ነው ይላሉ፡፡ በአገራችን የምናየውን ሸማቹ ጠቀሜታውን ሳይለካ ከአገኘበት ቦታ መግዛቱንና አምራቹ ለራቱ ካገኘ በቃኝ ብሎ ድርጅቱን ለወደፊት ለማስፋፋት አለመፈለጉን አዲሶቹን ለክላሲካል ኢኮኖሚስቶችን ግራ ያጋባው ጠቀሜታን እና ትርፋማነትን በአመክንዮ ለመለካት አለመቻል (Irrationality) እምነት ተምሳሌት ነው ልንል እንችል ይሆን? ወይስ የመረጃ እንደልብ አለመዳረስ ነው? የእኛ ኢኮኖሚስቶችስ ስለዚህ ዓይነቱ የገበያ ውጥንቅጥ ምን ይላሉ? የሕዝባችንን ኢኮኖሚያዊ ባሕርይና ተግባር ማጥናት የእኛ ፋንታ ነው እንጂ ፈረንጅ አጥንቶ እስከሚነግረን የምንጠብቀው ጉዳይ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል የፈረንሳይ አብዮት የተካሄደበትን ሐሳባዊ ሶሻሊዝም (Utopian socialisem) የዋህነት ነው በማለት ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን በመደብ ትግል የተነተነው በካፒታሊስት ሥርዓት ዕሴት የሚፈጠርበትን የእነ ሪካርዶ ጽንሰ ሐሳብ ተውሶ ካፒታሊስቱ ወዛደሩን የሚበዘብዝበት ሥርዓተ አድርጎ በሳይንሳዊ ዘዴ የተነተነው ካርል ማርክስ በሶሻሊዝም አድርጎ ወደ ኮሙኒዝም የሚኬድበትን መንገድ ከመፈላሰፍ ሌላ በሳይንሳዊ ዘዴ ስላልተነተነ ይህም አልበቃ ብሎ እነ ሌኒን በኋላ ቀር አገር ውስጥ በአቋራጭ ሶሻሊስት ማኅበረሰብ ለመፍጠር ስለሞከሩ ከሰባ ዓመት አጭር ጉዞ በኋላ ፍልስፍናው ተቀጨ፡፡ ሆኖም እስካሁንም ድረስ ዓለም የኋላ ኋላ ወደዚያው እንደምትሄድ በካፒታሊዝም ውስጥ እያደገ የመጣው የብዝበዛ ዓይነት ያመለክታል ብለው የሚያምኑና እየተገነባ ያለውን የካፒታሊዝም ዓይነት እየኮነኑ ያሉ ዕውቅ ኢኮኖሚስቶች አሉ፡፡ የበለጸገች አገር በምትባለዋ አሜሪካ እንኳ እኛ ዘጠና ዘጠኝ በመቶዎቹ ለፍቶ አዳሪዎች እና አንድ በመቶዎቹ በዝባዝ ቅምጥሎች በመባል ማኅበረሰቡ በመደብ ተከፋፍሏል፡፡ በካፒታሊስት ሥርዓተ-ኢኮኖሚ ውስጥ ሆኖ ፈጣን ዕድገት ለማምጣት ይበጃል የተባለው የታዳጊ አገሮች የልማታዊ መንግሥት ፖለቲካል ኢኮኖሚም ቢሆን በአንዳንድ የእስያ አገሮች በተግባር ስለመረጋገጡ እንጂ ወጥ የሆነ ዓለም ዐቀፋዊ (Universal) የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ ተነድፎለት እንደ አቻው ሊብራል ካፒታሊዝም በሒሳብ ሳይንስ ታግዞ የሚጓዝ ስላልሆነ እንደየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ በአምባገነናዊም በዴሞክራሲያዊም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት ስለሚተገበር ሳይንሳዊነቱ በትክክል የተረጋገጠ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ፍልስፍና ብቻውን የአገር ኢኮኖሚ ለማስተዳደር በቂ እንዳልሆነ ያልተረዱ የመንግሥት ሹማምንትና ዋናው ችግራችን የመዋዕለንዋይ እጥረት ነው የሚሉ የኢኮኖሚ ባለሟሎች በጽሑፍ ባላይም በቃለ መጠይቅ የኢኮኖሚ ፍልስፍናችን መደመር ነው ሙሉ አቅማችንን የምናውለውም ለአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚክስ (Supply Side Economics) ነው ኬንስ ማክሮ ኢኮኖሚን ሲተነትን በአውሮፓና በአሜሪካ የነበረው ሁኔታ አሁን እኛ ካለንበት ሁኔታ ጋር አይመሳሰልም፤ መንግሥታዊ ዕቅዶቻችንንም በውጭ ኮንሰልታንቶችም ጭምር አስጠንተናል ወዘተ… ይላሉ፡፡ ለመሆኑ የትኛው የውጭ ኮንሰልታንት ነው የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የሕዝቡን ኑሮ ደረጃ የሚያውቀው? ኧረ ለመሆኑ በውጭ ኮንሰልታንቶች ታግዞ የታቀደው የዐሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ በመነሻው ዓመት በ2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ያህል እንደሚያድግ ታቀደ በዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ስለተተነበየው የባዶ ኢኮኖሚ ዕድገትስ ምን ማለት ይቻላል? የመጀመሪያው ዓመት በትክክል ሳይታቀድ የመጨረሻው ዓመት እንዴት በትክክል ይታቀዳል?

እነኚህን የመሳሰሉ የአገራችን ወሳኝ ጉዳዮች የሚፈቱት በሳይንሳዊ መንገድ ቢቻል ደግሞ በስሌት ሳይንሳዊ መንገድ እንጂ በፍልስፍና ወሬ አይደለም፡፡ በተለይ ሒሳብን በፍጥነት የሚቀበል አእምሮ ያላችሁ ወጣት ኢኮኖሚስቶችና ሌሎች ምሁራን ከፍልስፍናው ቀነስ አድርጋችሁ የስሌት ሳይንሱንም ሞክሩት፡፡ ይህ ካልሆነ አገሮችን ከድህነት አዙሪት ውስጥ ልትወጣ እንደማትችል አበክሬ ላስገበዝባችሁ እወዳለሁ፡፡

ፍልስፍና ነባራዊ እውነትን ማየት ማወቅ መረዳት ማመንና መተርጎም (static situation) እንጂ ሁኔታን መለወጥ አይደለም፡፡ በፍልስፍና የሚለወጥ ነገር ቢኖር እንኳ በመረጃ ስህተት ምክንያት በትክክል ያልተመረመረ የአስተሳሰብና የሐሳብ ለውጥ እንጂ የተግባር ለውጥ አይደለም፡፡ በመረጃ ጥራት አዲስ እውነት ሲገለጽ ቀድሞ እውነት የመሰለው ውሸት ሆኖ በአዲስ እውነት ይተካል፡፡ ሁኔታዎችን የመለወጥና በሚፈለገው መልክ እንዲሆን የማድረግ ቴክኒክ የሙያ ሳይንስ ብቻ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ሙያ ሳይንስ የለውጥ ሳይንስ ስለሆነ ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ውስጥ (Dynamic Situation) ነው፡፡ ሆኖም ግን በፍልስፍና ጥበብ እውነታውን ማወቅና ማመንም ወደ መለወጥ ቴክኒኩ ለመሸጋገር የለውጥ ግብዓት ነው፡፡ ለዚህም ነው በንባብ የታወቀው የዶ/ር ዐቢይ የመደመር ፍልስፍና መጽሐፍ በሙያ ሳይንስ ካልተተነተነ ከንባብ አልፎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር አይሸጋገርም የምለው፡፡

 

በመደመር መጽሐፍ ምዕራፍ 3 የመደመር ብያኔ ርእስ ንዑስ ርእስ 3.1፤ መደመር ከብቸኝነት ጉድለት ወደ ክሡትነት ገጾች 38 እና 39 የቀረቡትን ሐሳቦች አልፎ አልፎ በመውሰድ ቋሚ ሕግ በሆነው በዶ/ር ዐቢይ የፍልስፍና ጥበብ እይታና በለውጥ ላይ በሆነው በሙያ ሳይንስ ትንታኔ መካከል ያለውን ልዩነት ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡ ከመጽሐፉ የተወሰደው የፍልስፍና አመለካከት እንደሚከተለው ነው፡፡

“… ዋናው የብቸኝነት ምንጭ ግን በፉክክርና በትብብር መካከል የሚከሰት የሚዛን መዛባት ነው፡፡ በአንድ በኩል ብቸኝነት የሚከሰተው በፉክክርና በትብብር መካከል ሚዛን ሲዛባ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከብቸኝነት መውጣት የሚቻለው ፉክክርና ትብብርን ለመፍጠር ሲቻል ነው፡፡ … ፍቱኑ መድኃኒት ፉክክር ትብብርን ሳያጠፋው፤ ትብብርም ፉክክርን ሳይደመስሰው በተዐቅቦና በሚዛን መኖር ነው፡፡ … ፉክክርና ትብብር አንዳቸው በአንዳቸው ላይ እያየሉ ሲመጡ የብቸኝነት ጉድለት የሚለኩሰውን ከከባቢ ጋር የመገናኘት ሂደት ይገቱታል፡፡ … የብቸኝነት ጉድለት በፉክክርና ትብብር ሚዛን ማጣት ምክንያት ራሳችንን ከትብብርም ከፉክክርም የምንነጥልበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህም ማለት ፉክክር ሲያይል ወይም ትብብር ሲያይል ሰዎች ከከባቢያቸው ጋር የሚያደርጉት መስተጋብር ይቋረጣል፡፡…”

ነገሮችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመመርመር ከዝርዝር ወደ ጥቅል (Induction) ብቻ ሳይሆን ከጥቅል ወደ ዝርዝርም (Deduction) ማየት ይቻላል፤ ይገባልም፡፡ ሰው ከከባቢው ጋር ያለውን ግንኙነት ስንመረምር ከዝርዝር ወደ ጥቅል እየተመራመርን ነው፡፡ ከባቢው ከሰውየው ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት ስንመረምር ግን ከጥቅል ወደ ዝርዝር እየተመራመርን ነው፡፡ ፉክክርና ትብብር በሰውየው ላይ የሚያመጡትን ውጤት ብቻ ሳይሆን ፉክክርና ትብብር በከባቢው ላይ የሚመጡትንም ውጤት መመልከት አለብን፡፡ ስለሰውየው ካሰብነው እኩል ስለከባቢውም ማሰብ ሰውየውንም ከባቢውንም ከጎንዮሽ ጉዳት ማዳን ነው፡፡ በኢኮኖሚ ሙያ ትንታኔ ሰውየው ከከባቢው የሚፈልገውና የሚወስደው ከባቢውም ከሰውየው የሚፈልገውና የሚወስደው ወጪም ገቢም ስላለው ወጪውና ገቢው ሊለካና ጥቅሙ ከጉዳቱ ካመዘነ ሊወሰድ ጉዳቱ ከጥቅሙ ካመዘነ ሊተው ይቻላል፡፡ ስለሆነም በፉክክርም ሆነ በትብብር ይህ የሰውና የከባቢ መስተጋብር እንድምታ ምን ሊሆን እንደሚችል እንመርምር፡፡

ዶ/ር ዐቢይ በፍልስፍና እይታ ፉክክርና ትብብር ተቃራኒ ጫፍና ጫፍ ዋልታ የረገጡ በፍጭት (Dialectics) አንዱ ሌላውን ሊጎዳ የሚችልበት ሁኔታዎች እንዳሉ አድርገው ነው የተመለከቱት፡፡  በኢኮኖሚ ሳይንሳዊ የሙያ ምልከታ ግን ትብብር ለፉክክር ቲፎዞ የማዘጋጀት ግብዓት የሚሆንበት እና ፉክክርም የትብብር ግብዓት ሊሆን የሚችልበት፤ አንዱ ሌላውን የሚፈጥር እና የሚያፋፋበት ሁኔታዎችም እንዳሉ እንጂ ሁሌም የተቃራኒ ጫፍ ዋልታ ረገጥ ሁኔታዎች ብቻ እንደሆኑ አይደሉም፡፡

በማኅበራዊ ሳይንሱ ሰዎች በዕድር ትብብር ኅብረት የሚመሠርቱት እከሌን ስንት ሰው ቀበረው በሚል ለቀብራቸው ከሌላው ሰው በላይ የሰው ቁጥር እንዲመጣ በሚያደርጉት ፉክክር ላይ ተመሥርተው ነው፣ በፖለቲካው ሰዎች በትብብር የፓርቲ ኅብረት የሚመሠርቱት ፓርቲው የመንግሥት ሥልጣን ሲጨብጥ ምን ሥልጣን ይሰጠኛል ምን የትምህርት ዕድል ይሰጠኛል፣ ምን ሀብት አገኛለሁ ብለው ፉክክር ውስጥ በመግባት ነው፡፡ ፉክክርና ትብብር እርስ በርስ የሚጋጩ ሳይሆኑ ተጋግዘው ሰነፎችን የሚሰቅሉና ጎበዞችን የሚያወርዱ አቋራጭ የመማሪያ፣ አቋራጭ ሥልጣን ማግኛ፣ አቋራጭ ሀብት ማፍሪያ፣ መንገዶች ናቸው፡፡ በተማሩበት ሙያ ዕውቀቱ ያላቸው ጎበዞች ገሸሽ ተደርገው ተፎካካሪም ተባባሪም ሆነው አገሪቱን የሰነፎች አገር ያደረጓት በስንፍናቸው የሚታወቁ ቲፎዞዎች እንደሆኑ በድህነታችን የተረጋገጠና በዓይናችን ያየነው በትንሹ ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ታሪካችን ነው፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት ፉክክር ለትብብር ግብዓት እና ትብብርም ለፉክክር ግብዓት ሊሆኑ ቢችሉም፣ ለዛሬ በተለይ ላተኩር የፈለግሁት ትብብር ለፉክክር የሚገዛ ሸቀጥና የፉክክር ግብዓት ስለመሆን ነው፡፡ በጽሑፌ እንደ ዝርዝር አካሎች የቆጠርኩት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በፉክክር የሚሳተፉ ሰውን የሚወክሉ ተቋማት ሁሉ ሲሆኑ እንደ ጥቅል አካሎች የቆጠርኩት ተባባሪና የድምር ውጤት ከባቢዎች ናቸው ስለሆነም የጽሑፍ አቀራረቤ ከዝርዝር ወደ ጥቅል ወይም ከጥቅል ወደ ዝርዝር ሊሆን ይችላል፡፡ ኢኮኖሚክስ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሰውን ጉልበትና ዕውቀት አክሎ ተጨማሪ ዕሴት በመፍጠር ሀብትን አዳብሮ መከፋፈል ሲሆን፣ አዲሱ ሀብት ወይም ምርት የሚሰላው ግብዓተምርትን ለማግኘት የሚወጣ ወጪን እና ከምርቱ የሚገኝ ጥቅምን በማነጻጸር በመሆኑ አንዱ ለሌላው ምን ያህል ያስፈልገዋል የሚለውን ይመረምራል፡፡ የተመረተው ምርትም ሸቀጥ ሆኖ ለፈላጊ የሚሸጠው በማምረቻ ወጪው ላይና በሚያስገኘው የገቢ ጥቅም ንጽጽር ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡

ሸቀጥ ለሚለው ቃል ካርል ማርክስ ሰያሜ እንደሰጠና ትርጉሙን ግን በሚገባ እንዳላብራራው የኢኮኖሚ ሥነ ጽሑፎች ይናገራሉ፡፡ ዕቃዎች ሁሉ የራሳቸው ስያሜ አላቸው ለምሳሌ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ ሳህን፣ ብርጭቆ ወዘተ… ሆኖም ግን እነኚህ ዕቃዎች በሰው እጅ ተጨማሪ ዕሴት ታክሎባቸው ለሽያጭ ሲቀርቡ ሸቀጥ (Commodity) ይባላሉ፡፡ በእኛም ቋንቋ ሸቀጥ የምንለው በማምረት ወይም በማጓጓዝ ወይም በንግድ የሰው እጅ የነካውን ስለተነካም ዋጋ ያወጣውን ወይም ዋጋው የጨመረውን ዕቃ ነው፡፡ ስለዚህም የሰው እጅ (ጉልበት) ወይም የሰው ዕውቀትና አስተሳሰብ የታከለበት ዕቃም ሆነ ሐሳብ ለሽያጭ ሲቀርብ ሸቀጥ ይሆናል፡፡ ትብብር እንደ ለፉክክር አስፈላጊ ሸቀጥ በቁሳዊ ስጦታ መልክ የሚቀርብም ሊሆን ይችላል አለበለዚያም በፉክክር ለማሸነፍና ለማሳካት በሐሳብ መስማማት ሊሆንም ይችላል በሁለቱም ሁኔታ ትብብሩን ላገኘው ተፎካካሪ ወገን በገንዘብ ግዢ ወይም በውለታ ዋጋ የሚገኝ ቁሳዊ ወይም የሐሳብ ሸቀጥም ሊሆን ይችላል፡፡ ሁኔታውን በማስረጃ አስረግጦ ለማሳየት ምሳሌዎችን እንጠቀም፡፡

ሕወሓቶች ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለመገዳደርና ለመፎካከር ትብብርን ለመግዛት ያፈሰሱትን የገንዘብ መጠን ብቻ በማየት ትብብር ለፉክክር ሲባል በገንዘብ የሚገዛ ሸቀጥ እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ ሕወሓት የኦነግን ትብብር እንደ ሸቀጥ ገዝታዋለች፤ የስንቱን ፕሮፌሰር ትብብር እንደ ሸቀጥ እየገዛች በየሚዲያው አስለፍልፋዋለች፡፡ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲዊ ትብብር የሚሸጥ ሸቀጥ ሆኖ የበለጸጉት አገሮች ስትራቴጂክ በሆኑት አገሮች ወዳጅነትን እንደ ሸቀጥ በገንዘብ ለመግዛት ይፎካከራሉ፡፡ ቤተሰቦች በሀብት ሽሚያ ኅብረት ፈጥረው ከሌላ ቤተሰብ ጋር ይጋጫሉ፡፡ ብሔረሰቦች በሀብት ሽሚያ ኅብረት ፈጥረው ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ግጭት ይፈጥራሉ፡፡ አገሮች በሀብት ሽሚያ ኅብረት ፈጥረው ከሌሎች አገሮች ጋር ግጭት ይፈጥራሉ፡፡ ስለሆነም ትብብር ወይም ኅብረት ለፉክክር የሚገዛ ሸቀጥ ነው፡፡

በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሜሪካ እንግሊዝና ሩስያ ትብብር ወይም ኅብረት የፈጠሩት ከጀርመንና ተባባሪዎቿ ጣሊያንና ጃፓን ጋር ለመፎካከር ነው፡፡ የሰሜን ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ምዕራባውያን ቃል ኪዳን አገሮች እና የቀድሞዎቹ የዋርሶ ምሥራቃውያን ስምምነት አገሮች ትብብርና ኅብረት ዓላማ እርስ በርሳቸው ለመፎካከር ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የአውሮፓ ኅብረት የተባበሩት የአሜሪካ ኅብረት አገሮች ዓላማ ከሌሎች ጋር ለመፎካከር ነው፡፡ እዚህም ትብብር ወይም ኅብረት ለፉክክር የሚገዛ ሸቀጥ ነው፡፡

 

እነኚህ ትብብሮች ወይም ኅብረቶች የሚያመለክቱት ትብብር የፉክክር መሣሪያ እንደሆነና ትብብር ሲያድግ ፉክክርም አብሮ እንደሚያድግና በተቃራኒ አቅጣጫ የሚጓዙ ሳይሆኑ እንዲያውም አንዱ የሌላው ምክንያትም ጥንካሬም እንደሆነ በመካከላቸው ያለው መቀራረብ (Convergence) እንጂ መራራቅ (Divergence) እንዳልሆነ ነው፡፡ በትብብርና በፉክክር መካከል ያለ ግንኙነት ወደ ውስጥ ስበት እንጂ ወደ ውጪ ግፊት ስላልሆነ ለአስታራቂ መሃል ቤት የሚወሰድ እርምጃና የሚጠበቅ ሚዛን የለም፡፡

በአጠቃላይ በሙያዊ ሳይንሶች ፉክክርና ትብብር የሚገለጹበትን ሁኔታ እርስ በርሳቸው የሚጋጩና ሚዛን ካልተጠበቀ አንዱ ሌላውን የሚያጠፋው እንደሆነ ተደርጎ መታየት የለበትም የሚለውን አቋም ወስጄ በተለይ በኢኮኖሚ ሙያ ሰፋ አድርጌ እንደሚከተለው አብራረራለሁ፡፡

የዝርዝሩና የጥቅሉ ለየብቻና የሁለቱን መስተጋብር እንደ የጥናትና የምርምር ዘዴ መውሰድን አስፈላጊነት ያነሳሁት በከንቱ አይደለም፡፡ የመደመር ፍልስፍናን ፉክክረና ትብብርን በሁለቱ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ዘርፎች በንዑስ ኢኮኖሚክስ (Microeconomics) እና በዐቢይ ኢኮኖሚክስ (Macroeconomics) መስሎ በመካከላቸው ያለውን መስተጋብር ለመመርመር ነው፡፡

ዶ/ር ዐቢይ በመደመር ፍልስፍናቸው የጠቀሷቸውን ፉክክርና ትብብርን በሙያ ቋንቋ ኢኮኖሚያዊ ሳይንሳዊ መልክ ለመስጠት ሁለቱም ለሰው ልጆች ምሉዕነት አስፈላጊነትን ወስደን ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር አገናዝበን ብንመለከት ጠቃሚ ነገሮችን እናገኝበታለን፡፡ እኔ እሳቤውን ወድጄዋለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ፉክክርን የግል ዋጋ አወሳሰን ንዑስ ኢኮኖሚክስን (Microeconomics) በመግለጽ እንደዚሁም ትብብርን የብሔራዊ ገቢ ለክፍላተ-ኢኮኖሚዎች ድልድል ሳይንስ ዐቢይ ኢኮኖሚክስን (Macroeconomics) በመግለጽ ዓይነተኛ መገለጫዎች አድርገን ብንተነትን ስለ ሁለቱ መስተጋብራዊ ውህደትና የዕድገት መሠረት መሆን ብዙ ልንናገርና ልንጽፍ እንችላለን፡፡

የዚህ ዘመን ኢኮኖሚ ሊቃውንት ዋና የጥናት መስክ የንዑስ ኢኮኖሚው መሠረታውያን ለዐቢይ ኢኮኖሚው ወይም የዐቢይ ኢኮኖሚው መሠረታውያን ለንዑስ ኢኮኖሚው ነው (Miceoeconomic foundations of the Macroeconomy or Macroeconomic foundations of the Microeconomy) ነው፡፡ ይህም ማለት ፉክክር ለትብብር እና ትብብር ለፉክክርም  እንዴት እንደሚጠቅሙ ሳይንሳዊ አላባዎቻቸውን ወስዶ መመርመርና የዕድገት መሠረት አድርጎ ማጥናት ማለት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት በሙያ ሳይንሳዊ መንገድ ከተፈጠረ ትብብር የፉክክር ግብዓት ብቻ መሆኑ ቀርቶ እርስ በራሳቸው ተመጋጋቢ ይሆናሉ፡፡ ፍልስፍና ይህንን ተመጋጋቢነት አያመጣም ምክንያቱም ፍልስፍና የሆነውንና እውነትን የመመርመር ጥናት እንጂ እንዲሆን የማድረግ ጥናት ስላይደለ ነው፡፡ የንዑስ ኢኮኖሚም ሆነ የዐቢይ ኢኮኖሚ ሙያዊ ጽንሰ ሐሳቦች መሠረታውያን ምን እንደሆኑ ባለፉት ስድስት ዓመታት በመገናኛ ብዙሃን ስጽፍና ለሕዝብ ሳስተዋውቅ ኖሬአለሁ፡፡

በክፍል አንዱ ጽሑፍ እንደገለጽኩት ለፍላጎት መሠረት የሆነው የሸማቹ ጥቅሙን የላቀ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል ባሕርይ በዚህ ዘመን ከሸማች ወደ ሸማች ተለዋዋጭ ከመሆኑ የተነሳ በኢኮኖሚክስ ተጠቃሎ የቀረበው የሸማቾች ባሕርይ ኢኮኖሚያዊ ሕግ የዚህን ዘመን ሰው አልገለጸውም፡፡ ለአቅርቦት መሠረት የሆነው የአምራቹ ትርፉን የላቀ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል ባሕርይም በዚህ ዘመን ከአምራች ወደ አምራች ተለዋዋጭ ከመሆኑ የተነሳ በኢኮኖሚክስ ተጠቃሎ የቀረበውን የአምራቾች ባሕርይ ኢኮኖሚያዊ ሕግም የዚህን ዘመን ሰው አልገለጸውም፡፡ እነኚህ ሁኔታዎችም የኢኮኖሚ ሳይንስን ተፈታትነውታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በፍልስፍናው የፉክክርና የትብብር ሰዋዊ ባሕርያት ናቸው የሚባሉትን የፍልስፍና እውነቶችንም አሜን ብሎ ከመቀበል በፊት በሥነ ባሕርይ (Psychology) ጥናትና ምርምር መረጋገጥ ሳይኖርበት አይቀርም ብዬ አምናለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጨዋታውን ሕግ ጠብቀው የሚሠሩ ፉክክሮች (የንዑስ ኢኮኖሚው ተቋማት፡- ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ድርጅቶች) አሉ ወይ? የሀብት በክፍለ ኢኮኖሚዎች ድልድል  (የዐቢይ ኢኮኖሚው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች) ትብብሮቹስ የፉክክሩ ግብዓት ሆነው እያገለገሉ ነው ወይ? ጉድለት ካለ የት ነው ያለው? ወይም የቱ ጋር ይበዛል? የሚሉ ጥያቄዎች በሳይንሳዊ መንገድ ተተንትነው መፍትሔ ቢፈለግላቸው በኑሯችን የዓለም ጭራ ከሆንበት ሁኔታ ያስጥሉን ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በመደመር መጽሐፍ ፉክክርና ትብብር እንደ የሰው ባሕርያት ቢገለጹም፣ ባቀረብኳቸው ምሳሌዎች ግለሰቦችን፣ ቤተሰቦችን ተቋማትን ሰዎችን ስለሚወክሉ እንደ ተፎካካሪዎች የዝርዝር ጥናት እና የሙሉውን ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን እንደ ትብብር የጥቅል ጥናት ከባቢ ሁኔታ አድርጌ ቆጥሬአለሁ፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት አገሪቱ በፉክክሩም በትብብሩም የሰነፎቹ አገር ስለሆነች ፉክክሩንና ትብብሩን ግለሰቦችንም ሆነ አገሪቱን በሚጠቅም መንገድ ሊመሩት አልቻሉም ጎበዞቹም የዳር ተመልካች ሆነው የሚደረገውን እና የሚሆነውን በትዝብት እያዩ ነው፡፡ በፉክክሩ የንዑስ ኢኮኖሚው መሠረታውያን እና ሕግጋት ምን እንደሆኑ ተዋንያን አውቀው እንዲንቀሳቀሱ በትብብሩም የአገር ሀብት ለክፍለ ኢኮኖሚዎች የሚከፋፈለው ሁሉንም በሚጠቅም መልኩ እንዲሆን አድርጎ የሚመራ አካልና ተቋም እስከአሁን የለም፡፡

ዶ/ር ዐቢይ በግል መጽሐፉን ለመጻፍ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ይሰማኛል:: አንድ ሚልዮን ኮፒም ሸጠዋል፡፡ አንድ ሚልዮን ሰነፎች እጅ የገባ መጽሐፍ የመደርደሪያ አድማቂ ብቻ ከመሆን አልፎ ተርፎ ሰውንም አገርንም እንዲጠቅም ዶ/ር ዐቢይ የመንግሥትን በጀት ሳይጠቀሙ ብዙ መሥራት እንደሚገባቸው ይሰማኛል፡፡ አለበለዚያ እርሳቸውም አላተረፉም፡፡ እኛ መጽሐፉን የገዛነውም ተጠቅመን ሊሆን ይችላል፡፡ ግን አላተረፍንም፡፡ አገሪቱም ወይም ከባቢውም አላተረፉም፡፡

 

March 13, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *