ዕውን ኢትዮጵያ የ7 በመቶ ዕድገት አስመዝግባለች?  የገንዘብ ሚኒስትሩ ሪፖርት ሲገመገም | ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ
ኢኮኖሚ

ዕውን ኢትዮጵያ የ7 በመቶ ዕድገት አስመዝግባለች? የገንዘብ ሚኒስትሩ ሪፖርት ሲገመገም | ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ

ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ መግለጫው በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት ስለነበረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና ለመሸጥ በታሰቡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እጣ ፋንታ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ በዚህች አጭር ጽሑፍ የገንዘብ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ የተወሰኑትን የራሴንም እይታዎች እያከልኩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

አቶ አሕመድ በመግለጫቸው በ2012 ዓ.ም. አገሪቱ በ7 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧን ገልጸዋል፡፡ ይህን ስሰማ አግራሞት ጭሮብኛል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም በየወቅቱ ሲነሱ በነበሩ አለመግባባቶች እና ብሔር ወለድ ግጭቶች ሲደቆስ እንደመቆየቱ መጠን ይህን ያህል ምጣኔ ዕድገት ይመዘገባል ብሎ ያሰበ አካል አልነበረም፡፡

የዓለም ባንክ ቀድሞ በሠራው ጥናት አገሪቱ 3.2 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ልታስመዘገብ እንደምትችል መላምት አስቀምጦ ነበር፡፡ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋም (IMF) በበኩሉ ባደረገው ተመሳሳይ ጥናት ዕድገቱ 3.2 በመቶ አካባቢ ሊሆን ይችላል የሚል ትንበያ አስቀምጦ ነበር፡፡ እኔም ቀደም ባሉት ጊዜያት ባደረኩት ጥናት የአገሪቱ ዕድገት በ2.8 በመቶ ገደማ ሊሆን እንደሚችል ግምታዊ ስሌቴን አስቀምጬ ነበር፡፡ አሁን ከመንግሥት የሰማነው ሪፖርት ግን ከእነዚህ ትንበያዎች በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ በበኩሌ በሚኒስትሩ የቀረበውን ሪፖርት ግነት የተቀላቀለበት ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

ይህ ዓይነት ሪፖርት የሚዘጋጀው እንደ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዓይነት ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ መሆን ሲያቅታቸው ነው፡፡ እንደ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኢጀንሲ ዓይነት ተቋማት በተቻለ መጠን ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ገለልተኛ ሆነው የሚሠሩበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ላለማስከፋት ሪፖርቶች የሚጋነኑበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በእኔ እምነት የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ቀጥተኛ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆን አለበት፡፡ ይህ ቢሆን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ከፖለቲካ ፓርቲ ጣልቃ ገብነት መዳን ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

መስከረም ከወራቱ ሁሉ ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበት ወር ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የአብዛኛው እቃ ዋጋ ይጨምራል፡፡ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በኩል ግን የባለፈው መስከረም ወር ላይ የዋጋ ግሽበት መጠን እንደቀነሰ ተደርጎ ነው የቀረበው፡፡ ሌላውን ትተን ከሰሞኑ በገንዘብ ለውጡ ምክንያት የምርቶች ዋጋ እየጨመረ ነው ያለው፡፡ ይህ ሁኔታ  በቀጣይም ኤጀንሲው በሚያወጣው መረጃ ላይ እምነት እንዳይጥሉ ያደረጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሌላው የገንዘብ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ያነሱት ነጥብ ለበርካታ ኢትዮጵያውያንን እፎይታ የሚሰጥ ጉዳይ ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን አየር መንገድ በከፊል ለመሸጥ የተጀመረው እንቅስቃሴ እንዲቆም መደረጉን በዚሁ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እኔን ጨምሮ በርካታ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን አየር መንገዱ እንዳይሸጥ ሰፊ የሐሳብ ትግል ባገኘነው መድረክ ሁሉ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ አሁን ላይ የመንግሥትን ሐሳብ ምን እንዳስቀየረው በትክክል ባይታወቅም በውሳኔው ግን ደስ ከተሰኙ ባለሙያዎች መካከል አንዱ እኔ ነኝ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓይነት ተቋም ሲሸጥ የሚቀመጡ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም አንደኛው ምክንያት የአቅም ችግር ሲገጥመው እና ችግሩን  የግል ተቋማት ቢገቡበት ይፈቱታል ተብሎ ሲታሰብ ነው፡፡ በእኔ እይታ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስከ ሽያጭ የሚያደርስ ጉድለት አለበት የሚል ግምት የለኝም፡፡ ምክንያቱም አየር መንገዱ ከአህጉር አልፎ በዓለም ዐቀፍ መድረኮችም ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም ነውና፡፡ ከትርፍም አንጻር ብንመለከተው በዓለም ላይ ካሉ አትራፊ አየር መንገዶች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም አንጻር አየር መንገዱ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ያለ ተቋም እንጅ ድጎማ የሚደረግለት ዓይነት ድርጅት አይደለም፡፡

ሁለተኛው ምክንያት የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማግኘት የሚደረግ ሽያጭ ነው፡፡ እስከምረዳው ድረስ አየር መንገዱ ዓለም ዐቀፍ አየር መንገዶች የሚጠቀሙትን ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም አየር መንገድ ነው፡፡ ዘመናዊ የሚባሉ ቦይንግ አውሮፕላኖችን ቀድሞ ገዝቶ የሚያስገባ እና በራሱ አቅም ጥገና የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በረራዎች በመስተጓጎላቸው ምክንያት በርካታ አገሮች አውሮፕላኖቻቸውን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና አገልግሎት ሲያገኙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህም አየር መንገዱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንደማይታማ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ወደብ የሌላት አገር ናት፡፡ በዚህ ምክንያት አየር መንገዱ እንደ ወደብ ሆኖ እያገለገለ ያለ ተቋም ነው፡፡ እንኳን ለእኛ ለአፍሪካ ደቡብ አሜሪካ አገሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ግብዓትን ለማቅረን ተመራጭ ወደባቸው ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ እኔ አየር መንገዱን መሸጥን እንደወደብ መሸጥ ነው የምቆጥረው፡፡ ኮሮናም ይህ ጥቅሙ ጎልቶ እንዲታይ ማድረጉ በጎ ተጽዕኖ ሳያሳድር አይቀርም እላለሁ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዚህች አገር እንደ አርማ ሆኖ እያገለገለ ያለ ተቋም ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ዐቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንደምትችል አንድ ማሳያ ሆኖ እያገለገለ ያለው ተቋም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ በመዳረሻ ብዛትም ከዓለም ሦስተኛው አየር መንገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ለአገሪቱ የገጽታ ግንባታ ትልቅ ማስታወቂያ ሆኖ እያገለገለ ያለ ተቋም ነው፡፡ ይህ አርማነት ለውጭ ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥ ላለነውም ዜጎች በዘር እና በጎጥ ከምንከፋፈል አንድ ብንሆን እንዲህ ዓይነት ተቋምን መመሥረት እንደምንችል የሚያሳይ ነው፡፡

ይህ ማለት ግን አየር መንገዱ ምንም ዓይነት ስህተት ወይም ችግር የለበትም ማለት  አይደለም፡፡ ከአስተዳደር ጋር በተገናኘ፣ ከሰው ኀይል ቅጥር፣ ሙስናና የሠራተኞች አያያዝ አንጻር የሚነሱ እንዳንድ ችግርች እንዳሉ ማየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ችግሮች በቦርድ እና በአስተዳደር መታረም ያለባቸው እንጅ ተቋሙን በመሸጥ የሚፈቱ ችግሮች አይደሉም፡፡

የእኛ አየር መንገድ ለራሱ ትርፍ ከማስገባት ባለፈ የሌሎች አየር መንገዶችን ድርሻ እየገዛ ገንዘቡን ኢንቨስት እያደገ ያለ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም እንዳይሸጥ በርካታ ባለሙያዎች ስንጮህ ቆይተናል፡፡ መንግሥትም ጩኸታችንን ሰምቶ አሁን የተቋሙን የሽያጭ ሁኔታ ለጊዜውም ቢሆን ቆም አድርጎታል፡፡ ይህም ለእኛ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ውሳኔ ነው፡፡ የመንግሥት ውሳኔ ዘላቂ እንዲሆን እንመኛለን። መንግሥት በአየር መንገዱ ላይ ያሳየውን ትዕግስት እና ብስለት እንደ ቴሌ ባሉ ተቋማትም ላይ ይ

October 21, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *