እየደኸዩ ከማደግ … | ጌታቸው አስፋው
ኢኮኖሚ

እየደኸዩ ከማደግ … | ጌታቸው አስፋው

በኢትዮጵያ በቂ የፍጆታ ሸቀጦች ተመርተው መሠረታዊ ሁኔታዎች ተሟልተውለት ለመኖር የሚፈልገው ሕዝብ እና መሠረተልማቶች ተስፋፍተው ማምረቻ መሣሪያዎች በብዛት ተመርተው ኢኮኖሚው በፍጥነት እንዲያድግ የሚፈልጉት የመንግሥት ባለሥልጣናት በምርት ዓይነት ምርጫ ላይ አልተስማሙም፡፡ ፍጆታ ለዛሬ ነው ማምረቻ መሣሪያ ግን ለነገ ነው፡፡ የዛሬ ኑሮ ሁኔታ የሚገለጸው በፍጆታ መልክ ነው ዕድገት የሚገለጸው ግን በመዋዕለንዋይ መልክ ነው፡፡ ፍጆታና መዋዕለንዋይ ሀብት የሚሻሙ ተጻራሪ ሁኔታዎችም አይደሉም፡፡ ይልቁንም የሚደጋገፉ ሂደቶች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግር ከቁጥር ይበልጣል ያንሳል ትንታኔ ተወጥቶ የፍጆታን እና መዋዕለንዋይን መደጋገፍ መፍጠር ባለመቻሉ ምክንያት፣ እየበለፀጉ ማደግ ሲቻል እየደኸዩ ማደግ እንደ አማራጭ መወሰዱ ነው፡፡ ቁጠባ የዕድገት መሠረት ነው፡፡ ለነገው ሳይቆጥብ ዛሬ ያመረተውን ዛሬ ተጠቅሞ የሚጨርስ ሰው አያድግም፡፡ ቁጠባ ወደ መዋዕለንዋይነት ሲቀየርና የማምረቻ መሣሪያ ሲሆን የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ይሆናል፡፡ የመዋዕለንዋይ የጀርባ አጥንት የሆነው ቁጠባ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ትርጉሙ በዚህ ዓመት ከተመረተው ውስጥ ለዚህ ዓመት ፍጆታ በልክ አውጥቶ የተረፈውን ለተሻለና የተራዘመ የምርት ሂደት ወደሚቀጥለው ዓመት ማሸጋገር ማለት ነው፡፡

በዚህ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ትርጉሙ ኢትዮጵያውያን እንደ ማንኛውም ታዳጊ አገር ራሳችን ከምናመርተው ውስጥ ለቁጠባና መዋዕለንዋይ የሚተርፈው በጣም ጥቂቱ ብቻ ነው፡፡ በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ ግን ብዙሃኑ ሕዝብ ከዓመታዊ ምርቱ ሳይሆን ከጠቅላላ ሀብቱ በመቆጠብ በዓለም ላይ የሚያክለንም የለም ማለት እንችላለን፡፡ ስለሆነም የእኛ አገር ፍጆታና ቁጠባ ሊለካ የሚገባው ከዓመታዊ ምርትና ገቢ ጋር ብቻ በማነጻጸር ሳይሆን በዘመናት ዕድሜ ከተፈራ የሀብትና የጥሪት ክምችት ጋር ተነጻጽሮ ነው፡፡

ምንም እንኳ ኑሯችን ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም ነገ ስለሚያስፈራን እንደ እኛ የሚቆጥብ የለም፡፡ ግማሹ በጥሬ ገንዘብ መልክ ይቆጥባል ግማሹ በዕቃ መልክ ይቆጥባል፤ ግማሹ በቤት እንስሳት መልክ ይቆጥባል፡፡ ገበሬው ጎተራው ለከርሞ እንዳይጎድልበት አንጀቱን አስሮ ይራባል፤ ያለመጫሚያ ይሄዳል የተቀደደ ይለብሳል፤ ይህ ሁሉ ለቁጠባ ሲል የሚያደርገው ነው፡፡ ሁሌም ስለማትገኝ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር አምረን ለመታየት ቆጥበን ሳጥን ውስጥ ለብዙ ዓመታት የምናስቀምጣትን እጀጠባብ ሱሪና ኮት ወይም ባለጥበብ ቀሚስ የክት ልብስ እንላታለን፤ ስሟን አሳምረን እሷም ቁጠባ ነች፡፡ ከጥቂት የከተማ ኗሪዎች በቀር አብዛኛው ሕዝብ የሚመገበው በባህላዊ ሰፌድ ነው፡፡ የሚጠጣው በጣሳ ነው የሚለብሰው አቡጀዲ ነው፡፡ የሚጫመው ጎማ ጫማ ነው፡፡ ከመቀመጫው ከመኝታው አንስቶ ብዙ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ገና የሉትም፡፡ ብዙ ያልረካ የፍጆታ ሸቀጥ ፍላጎት እያለ በባህላዊ ዕቃዎች እየኖሩ ይቆጠባል፡፡

እንደ እኛ ለዓመት በዓል ብሎ ከዓመት ዓመት ልብስ በሳጥን ውስጥ ቆጥቦ የሚያስቀምጥ ይኖር ይሆን? ጌጣጌጥንም እንደ ቁጠባ አድርገን እንይዛለን፤ ለክፉ ቀን ሽጠን ለመጠቀም፡፡ ዶሮ ወይም በግ ወይም ወይፈን ስጋ እያማረንም ቢሆን ለዓመት በዓል ብለን ቆጥበን እናስቀምጣለን፡፡ እንደ እኛ ለሆዱ የዓመት ቀጠሮ የሚይዝ ቆጣቢ ሌላ ሕዝብ በዓለም ላይ ይኖር ይሆን? ቆጥበን እድር እንገባለን፤ ቆጥበን እቁብ እንጥላለን፤ ቆጥበን ማኅበር እንገባለን፤ በአዲሱ የቁጠባ ሥርዓት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በቁሳዊ ንብረት መልክ ወይም በቤት እንስሳት መልክ ይይዝ የነበረውን እና በዕድር በዕቁብና በማኅበር መልክ ይቆጥብ የነበረውን ወደ ዘመናዊ የባንክ ቁጠባ ቀይሮ በባንክ አማካኝነት ከተማውን ሊያሳምር ወደ ከተማ ይሻገራል፡፡ አዲስ አበባን ያሳመሯት ፎቅ የገነቡ ጥቂት ባለሀብት ሰዎች ይመስለን ይሆናል ግን አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ወይም ከአዲስ አበባ ከተማ ጥቂት መንደሮች በውብ ፎቆችና በሽንጣም መንገዶች ያማሩት በመቶ ዐሥር ሚልዮን ሕዝብ ቁጠባ ነው፡፡

ከበርቴዎች የገበሬውን ቁጠባ ከእጁ ፈልቅቀው ወደ አዲስ አበባ በማምጣት አዲስ አበባን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ውብ ከተማ አደረጓት፡፡ ለኢትዮጵያ የገበሬው ቁጠባ እዚያው ገጠር ቀርቶ ገጠሩን ቢያለማ ይሻል ነበር ወይስ ከተማ መጥቶ አዲስ አበባን ቢያሳምር ገና ወደፊት በኢኮኖሚስቶች ጥናት ተደርጎ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ሊባል የሚችለው ገበሬው ገቢውን በባንክ ቁጠባ መልክ ይዞ ብልጦች ወደ ከተማ አዛወሩት እንጂ በዚያው በገጠሩ ወደ መዋዕለንዋይነት ስላለወጠው ድርቅ በመጣ ቁጥር ለረኀብ መጋለጡን ነው፡፡

የመዋዕለንዋይ ገንዘብ ምንጭ ቁጠባ በመሆኑና ቆጣቢዎችም ቁጠባቸውን በባንኮች አማካይነት ለመዋዕለንዋይ አፍሳሽ ስለሚያበድሩ የገጠሩ ቁጠባ በጥሬ ገንዘብና በባንኮች አማካይነት በቅስቀሳና ንግድ ባንኮች እስከ ገጠሩ ዘልቀው በመግባታቸው ብዙ ሰው በርካታ ጥሬ ገንዘብ ቆጥቦ በ2002 የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዝግጅት ወቅት ከአገር ውስጥ ጥቅል ምርት 9.5 በመቶ ብቻ የነበረው ቁጠባ በዕቅዱ መጨረሻ ዓመት 2007 በዕቅድ ከተያዘው 15 በመቶም በልጦ 21.8 በመቶ ሆኗል፡፡ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን መጨረሻ ዓመት 2012 ቁጠባ የአገር ውስጥ ጥቅል ምርትን ሲሶ ወይም 29.6 እንዲሆንም ታቅዷል፡፡ በደርግ ዘመን ቁጠባው ከሦስት በመቶ በልጦ አያውቅም ነበር፡፡ ከገቢው ውስጥ ሰባና ሰማንያ በመቶውን ለምግብ የሚያወጣ ድርቅ በመጣ ቁጥር በድህነት ለሚሰቃይና ለእርዳታ የሚዳረግ ሕዝብ ከገቢው ውስጥ ሃያ ሁለት በመቶ መቆጠብና ቁጠባውንም ባንኮች ለከተማ ፎቅ መሥሪያ እንዲያበድሩ ያደረገው በገበያው ውስጥ የሚዘዋወረው ጥሬ ገንዘብ በዝቶ ገበሬው ምርቱን ለከተሜው በውድ ዋጋ እንዲሸጥ በተደረገው የመንግሥት ጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ፖሊሲ ነው፡፡

የ‹ቁምራ› ዘመን በኢትዮጵያ ወጣቶች የተፈጠረ ስያሜ ሲሆን ትርጉሙ ከቁርስ ምሳና ራት በቀን ሦስት ጊዜ መብላት ወደ ‹ቁምራ› (ቁርስን ምሳን ራትን) አጠቃሎ በቀን አንድ ጊዜ መብላት የተሸጋገርንበት ዘመን ነው፡፡ ዘመድ ናፍቆን ለመጠየቅ የሄድን መስለን ሰው ቤት በመቀላወጥ ቁምራውንም መልሰን ለነገ እንቆጥባለን፡፡ የማናውቀው ሰው ሲሞት ሳንጠራ ቀብረን የእዝን በመብላት እንጀራና ወጥ ቢጠፋም ንፍሮውን በእጃችን ሙሉ ዘግነን ቁምራውን መልሰን ለነገ እንቆጥባለን፡፡ ድግስ ቤት ስንጠራ በአንድ ሳህን ለሦስት ቀን የሚበቃ ምግብ አንስተን ቁንጣን እስከሚይዘን በልተን እንቆጥባለን፤ የቁጠባ ቁጠባ መሆኑ ነው፡፡ የቅባት እህሎች አምሮታችንን የምንወጣው እንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎችን ጠብቀን ነው፡፡

እኛ ኑሯችን በሙሉ ቁጠባ ነው በዕድርና በዕቁብ አማካይነት ገንዘብ እንቆጥባለን፡፡ ራስጌ ሥር ለክፉ ጊዜ ብለን ብሮችን እንቆጥባለን፡፡ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ተመግበን ምግባችንን እንቆጥባለን፡፡ አንድ ካናቴራ ሸሚዝ ሱሪ ኮት ወይም ጫማ ለስድስትና ሰባት ዓመታት ለብሰንና ተጫምተን፣ የቤት እቃዎቻችን ለብዙ ዐሥርት ዓመታት ተጠቅመን፣ ዛኒጋባ ቤቶቻችን ሁለትና ሦስት ትውልድ አሳልፈው ቁሳቁሶች እንቆጥባለን፡፡

ቁጠባ አላሳለፈልንም እንጅ እንደኛ የሚቆጥብ የለም ኑሯችን ሁሉ ቁጠባ ነው፡፡ እንኳንስ እኛ ሰዎቹ የቤት እንሰሶቻችንም ይቆጥባሉ፡፡ የቤት ውሾችና ድመቶቻችን ከተሰጣቸው ምግብ ግማሹን በልተው ግማሹን መሬት ቆፍረው ይቀብራሉ፡፡ ከእኛው ነው የተማሩት ወይም የእኛን አቅም ስለሚያውቁ በፈለጉት ጊዜ ልንሰጣቸው እንደማንችል ገብቷቸው ነው፡፡

መንግሥት ብዙ የአገር ውስጥ ምንዛሪዎችን (ብርና ሳንቲሞችን) ገበያ ውስጥ አፍስሶ ሸቀጥህን በፈለግኸው ውድ ዋጋ ሸጠህ ከምታገኘው ትርፍ ለእኔም ግብሬን ክፈለኝ ለአንተም ባንክ አስቀምጥ ከበርቴው ለሕንጻ መሥሪያ ይፈልገዋል ብሎ ሳያስተምረን በፊትም ቆጣቢ ነበርን፡፡ ቁጠባና ፍጆታ ከጽንሰ ሐሳባዊ ትርጉም ባሻገር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን እንደሚመስል መሠረታዊ ጥናት የሚሻ ነው፡፡ ምክንያቱም በብሔራዊ ኢኮኖሚ ትርጉሙ ቁጠባ ማለት ትናንትና ዛሬ ከተመረተው ምርት ውስጥ ለነገና ለተነገወዲያ ማቆየት ማለት እንጅ ጥሬ ገንዘብ ወይም ብር ባንክ ውስጥ ማከማቸት ስላልሆነ ነው፡፡ ገበሬዎችን በማስጨነቅና በመስበክ በጥሬ ገንዘብ መልክ የተቆጠበው ከአንድ ሰው እጅ ወደ ሌላ ሰው ተዘዋወረ እንጅ ያው ድሮ በዕቃ መልክ ወይም በቤት እንስሳት መልክ ይቆጠብ የነበረው ነው አዲስ ቁጠባ የመሰለው፡፡

ለአንድ አገር ብሔራዊ ኢኮኖሚ ባንክ ውስጥ የሚቀመጥ ጥሬ ገንዘብ በባንኩ ደላላነት ከገጠር ድሃ ገበሬው ወደ ከተሜው ከበርቴ ዞረ እንጅ ኢኮኖሚያዊ ድምር ውጤቱ ባዶ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ለአገር ቁጠባ የሚባለው ከፍጆታ ተርፎ የተላለፈው ቁሳዊ እቃ እንጂ ጥሬ ገንዘብ አይደለም፡፡ ገጠሩን እያራቆቱ የገበሬውን ቁጠባ ወደ ጥሬ ገንዘብ ቀይሮ ከተማ ማምጣት ለግለሰቦች እንጅ ለአገር እንደ ቁጠባ አይቆጠርም፡፡

የገጠሩ ቁጠባ ወደ ከተማ ቢመጣ የተሻለ ነው ሊባል የሚቻለው በኢንዱስትሪ ሥራ ተሰማርቶ በትራንስፎርሜሽን የገጠሩን ኑሮ ወደ ከተማ ኑሮ ቀይሮ ቢሆን ነበር፡፡ የገጠሩ ቁጠባ ወደ ከተማ መጥቶ ሕንጻ ሠርቶ አገሪቱ በቱሪስት ፍሰት ተጠቅማለች እንዳይባል ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ በጣም አነስተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ቁጠባ መዋዕለንዋይና የእነርሱ ወሳኝ የሆነው የወለድ መጣኝ ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ሚና ስለሚጫወቱ የኢኮኖሚ ሊቃውንትን ቀልብ ስበው ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ሲያስቡና ሲናገሩ ከቁጠባና መዋዕለንዋይ ውጪ አይደለም፡፡ ቁጠባና መዋዕለንዋይ ሁሌም የዕድገት ማዕከላዊ ነጥቦች ናቸው፡፡ የቁጠባና የመዋዕለንዋይ መጠኖች እንዳይወለጋገዱም ሰፊ ትንታኔ ይሰጣሉ፡፡

ብዙ ሰዎች ዋጋን በማናር ግብር (Inflationary Taxing) መንግሥት ሕዝቡን አስገድዶ እንደሚያስቆጥብ ላይገነዘቡ ይችላሉ፡፡ ሆኖም በኢኮኖሚክስ በዋጋ ውድነት አማካኝነት መንግሥት እና ከበርቴ ነጋዴው ከድሃው ሕዝብ አስገድደው በማስቆጠብ ለመዋዕለንዋይ ወጪ የሚያውሉበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ለአጠቃላይ ሸቀጦች ዋጋ መናር እንደ ዋና ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው መንግሥት ዋጋን በማናር ግብር የመሠረተልማት ወጪውን መሸፈኑ ነው፡፡ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትና ሥርጭት ጭማሪ ከጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ጭማሪ በላይ ሆነ ማለት በምሳሌያዊ አነጋገር ወተትን በውኃ አቅጥኖ ወይም የጥሬ ገንዘብን የመግዛት አቅም ዋጋ ቢስ አድርጎ መንግሥት ሊገዛ የሚችለውን ቁሳዊ ሀብት መጨመር ማለት ነው፡፡

የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን በማሳደግ የዋጋ ንረት ግብር እንዴት እንደሚፈጠር በምሳሌ እንመልከት፡፡ አንድ ኩንታል ጤፍ በአንድ ሺሕ ብር ይገዙ ከነበረና ዋጋው ተወዶ ሁለት ሺሕ ብር በመግባቱ እርሶ በአንድ ሺሕ ብርዎ ግማሽ ኩንታል ጤፍ ብቻ የሚገዙት ብቸኛ የብር ማተም ሥልጣን ያለው መንግሥት አንድ ሺሕ ብሯን አትሞ በብሯ ግማሿን ኩንታል ጤፍ ወደ ጎተራው ስላስገበ ነው፡፡ ገበሬው ቀድሞ በአንድ ሺሕ ብር ይሸጥ የነበረውን አንዷን ኩንታል ጤፍ ለእርሶና ለመንግሥት ለየአንዳንዳችሁ ሐምሳ ኪሎ ጤፍ በአንድ አንድ ሺሕ ብር ሒሳብ በሁለት ሺሕ ብር ሽጦ ድሃ ገበሬው ድሃ ከተሜውን በጥሬ ገንዘብ መብዛት አማካይነት በዝብዞ እርሱም በተራው እህሉን የሸጠበትን ጥሬ ገንዘብ በኪሳራ ወለድ ሒሳብ በንግድ ባንክ አስቀምጦ ለሀብታሙ ከተሜ በማበደር ራሱም እንደገና ይበዘብዛል፡፡

ይህ ዓይነት የዋጋ ንረት ግብር የሚከፈለው በአምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሳይሆን ዋጋ የተወደደበት ማንኛውም ሸማች ሰው ሕጻን አዋቂ ሳይል በየአንዳንዱ ሸማች ስለሆነ ገቢው ለመንግሥት ቀላል አይደለም፡፡ ግብር ሰብሳቢ ተጨማሪ ሰው መቅጠር ስለማያስፈልገውም ወጪ የሌለበት ገቢም ነው፡፡ የገቢው ተጋሪ በአጋጣሚው ተጠቃሚና መረቡ ውስጥ የገቡ ከበርቴ ነጋዴዎችም ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት ያየነው የኢኮኖሚ ዕድገትና የብሔራዊ ሀብት መጨመር እያንዳንዱ ሰው የዋጋውን ንረትና የኑሮውን ውድነት አሜን ብሎ ተቀብሎ አንጀቱን አስሮ ያመጣው ለውጥ ነው፡፡ የመንግሥት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴና ለሀብታሙ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለውጭ ኢንቬስተሩ መሠረተልማቶቻችን በፍጥነት ያደጉት በዚህ ፎርሙላ ነው፡፡

በኢሕአዴግ ዘመን አዲስ አበባችን በመንገዶችና በሕንጻ ብዛት እንደበለጸገች ማንም ሊክደው አይችልም፡፡ ይህ ሁሉ ብልጽግና ግን ከባዶ የመጣ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ በዐሥራ አምስት ሳንቲም በደርግ ጊዜ በአንድ ብር ከሐምሳ ይበላ ለነበረው ሽሮ ምሳ አርባና ሐምሳ ብር በመክፈል መስዋዕት አድርጎ ነው አዲስ አበባ የበለጸገችው፡፡ ባለሀብቶች ከድሃው ወስደው ሠሯት እንጅ ከራሳቸው ላባቸውን አፍስሰው ያመጡት ለውጥ አይደለም፡፡ ጥሪቱን ከድሃው በምን መልክ እንደወሰዱት ራሱን የቻለ ትንታኔ ስላለው ወደፊት እገልጸዋለሁ፡፡

አንድ ሰው ለምሳው ሽሮ ወጥ እንጀራ አርባ ብር ለሆቴል ቤት ሲከፍል አንድ ብር ከሐምሳው የቀድሞው የሽሮው ዋጋ ሲሆን ሠላሳ ስምንት ብር ከሐምሳው ግን በዋጋ ንረት አማካይነት ለመንግሥት መንገድና ሕንጻ ግንባታ ወይም የጥቅም መረብ ውስጥ ለገባ ለማያውቀው የመንግሥት ወዳጅ ከበርቴ ሰው ሕንጻ ግንባታ በዋጋ ንረት ግብር አስገዳጅነት ለብሔራዊ ኢኮኖሚ ቁጠባ የተከፈለ ነው፡፡

የአንድ ብር ከሐምሳ ሳንቲም ሽሯችን ላይ ሠላሳ ስምንት ብር ከሐምሳ ሳንቲም ጨምረን እየከፈልን ነው የአዲስ አበባችንን የውጭ ዜጎችና ሀብታሞች የሚመላለሱባቸው የተወሰኑ ቦታዎች በአሳንሰር ፎቅ ለሚወጡ ለሚወርዱና በአውቶሞቢል ብቻ ለሚጓዙ ሰዎች ያሳመርንላቸው፡፡ ሽሮው ለድሆች የዛሬ ፍጆታ ሲሆን፣ ለመንገዱና ለሕንጻው በዋጋ ጭማሪ አማካኝነት የተከፈለው የድሃው ገንዘብ በመንግሥትም ይሠራ በግለሰብ ለአገር ከዛሬው ለነገ፣ ከዘንድሮው ለከርሞ ለብልጽግና የዋለ ቁጠባና መዋዕለንዋይ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ የቆዳ ስፋት የተወሰነው ክፍል በሕንጻዎችና በመንገዶች ማጌጥ እንደዚሁም ውብና ምቹ የቤትና የቢሮ ፍጆታ ሸቀጦች ሱቆች መከፈት በብዙ ሚልዮኖች ኢትዮጵያውያን በዋጋ ንረት አማካይነት ለመንግስት የዋጋ ንረት ግብር በመክፈል ቁጠባ የመራብ የመጠማት የመራቆት የመታረዝና የሕይወት ዋጋ የተከፈለበት ነው፡፡ የብልጽግናችን ጉዞ የመቶ ዐሥር ሚልዮን ሕዝብን ኑሮ የሚያሻሽል ነው ወይስ የጥቂት ከተሜዎችን ብቻ ነው? በድኅረ-ኮሮና ይህ በብልጽግና ወስጥ ያለ ድህነት ተቀልብሶ ሁሉም ሰው በጋራ እንዲበለጽግ እንሥራ፡፡

March 18, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *