መግቢያ
በሙያዊ የቋንቋ ትርጉም ትራንስፎርሜሽን ወደ ማኅበራዊ ጥናት ሲያደላ ልማት ወደ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ያደላል፤ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ቃል ነው፡፡ ሦስቱ በአንድነት በአንድ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ብሔራዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ወይም በአገረ መንግሥት ግንባታ ተጋምደው የተሳሰሩ ቃላት ናቸው፡፡ አንዱ ከጎደለ ሁሉም ይጎድላሉ፡፡ ልማት የሚለው ቃል አማርኛ ሲሆን፣ ትራንስፎርሜሽን እና ዲሞክራሲ የእንግሊዝኛ ቃላት ናቸው፡፡ ዲሞክራሲ በአማርኛ የከረመና የተለመደ ቃል ሲሆን፣ ትራንስፎርሜሽን በአማርኛ ለመነገር የዐሥር ዓመት ዕድሜ ብቻ ያለው አዲስ ቃል ነው፡፡ ሦስቱ የተጋመዱ የማኅበራዊ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ቃላቶች የአንድ አገረ መንግሥት ተቀዳሚ ዕሴቶች እንደሆኑ ለማመላከት ሊቃውንት ስለ ሦስቱ የተናገሩትን አገናኝተን እንመልከት፡፡
የካርል ፖላኒ ትራንስፎርሜሽን ምልከታ
ካርል ፖላኒ የተባሉ የሐንጋሪ ተወላጅ የሆኑ አሜሪካዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚስት እ.ኤ.አ. በ1944 “ታላቁ ትራንስፎርሜሽን” (The Great Transformation) በሚል ርእስ የጻፉት መጽሐፍ በእንግሊዝ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት በጀመረበት ወቅት የተካሄደውን ለውጥ ያትታል፡፡ እንደ ጸሐፊው አመለካከት የገበያ ኢኮኖሚና የአውሮፓ ብሔራዊ መንግሥታት ከከተማ አስተዳደርነት (City States) ወደ አሁኑ የአገሮች ቅርጽ የተቀየሩበት ብሔራዊ አገረ መንግሥት ምሥረታ (Nation Building) ተለያይተው የሚታዩ ነገሮች ሳይሆኑ በካፒታሊዝም ሥርዓተ ኢኮኖሚ የገበያ ማኅበረሰብ (Market Society) አፈጣጠር ውስጥ የተገነቡ ተያያዥ ክስተቶች ናቸው፡፡
በገበያ ማኅበረሰብ መፈጠር ምክንያት የሰው ልጆች የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ተለውጧል፡፡ ቀድሞ የነበረው በወል የማምረት ማኅበረሰባዊ አደረጃጀትና በደም ትስስር ቡድናዊ ተጠቃሚነት አመለካከት ተቀይሮ በገበያ ማኅበረሰባዊ አደረጃጀትና በዜግነት በግል ተጠቃሚነት አመለካከት ተተክቷል፡፡ ከገበያ ማኅበረሰብ በፊት መሬትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች እንደዚሁም ምርት የማምረትና የመከፋፈል ኢኮኖሚያዊ ይዞታና እንቅስቃሴ በጎሳ መሪዎች ወይም በባላባቶች የደም ትስስርና በልደት በሚገኝ ሥልጣን የሚከናወን ቡድናዊ ኮንትራታዊ ውል የኑሮ ሥርዓት ሲሆን፣ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ መፈጠር፣ የኢንዱስትሪ አብዮት መፈንዳት፣ የብሔራዊ አገረ መንግሥታት መመስረት፣ በአጠቃላይ አነጋገር የገበያ ማኅበረሰብ መፈጠር የትራንስፎርሜሽን ለውጥ የበፊቱን እንዳለ ቀይሮታል፡፡ ወገኔ ያስተዳድረኝ ከሚል ጠባብ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ወደ ኑሮዬን የሚያሻሽልልኝ ችሎታ ያለውና በገበያ ተወዳድሮ አሸንፎ የተመረጠ ሰው ያስተዳድረኝ የሚል ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ ተለውጧል፡፡
ካርል ፖላኒ በገበያ ማኅበረሰብ መፈጠር ወቅት የተካሄደውን የእንግሊዙን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የጻፉት ዘመናዊ የገበያ ኢኮኖሚ ምስረታ እና ዘመናዊ አገረ መንግሥት ግንባታ ተነጣጥለው የሚታዩ አለመሆናቸውንና እርሳቸው የገበያ ማኅበረሰብ (Market Society) ብለው የሚጠሩት የሰው ልጆች የዕድገት ደረጃ መሆኑን ነው፡፡ የገበያ ማኅበረሰብ መለያ መገለጫም የቁሳዊ ሸቀጥ ልውውጥ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ መለወጥም ጭምር ነው፡፡ በተለይ በኢኮኖሚስቶች የግብይይትና የዋጋ አወሳሰን መሠረት የሆነው የሸቀጥ ጠቀሜታ ልኬት የሰው ልጅ ከቡድን ተጠቃሚነት ይልቅ ለግል ተጠቃሚነት ዋጋ እንደሚሰጥ የሚገልጽ የሰውን ልጅ ልብ የሚገዛውም በደም የመተሳሰር ዝምድና ስሜት ሳይሆን የገበያ መስተጋብር መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ገበያ አሜሪካዊና ጀርመናዊውን፣ ኢትዮጵያዊና ግብጻዊውን፣ ቻይናውና ብራሊዛዊውን የቦታው መራራቅ ሳይገድበው አቀራርቧል፡፡
ከታላቁ ትራንስፎርሜሽን በፊት የሰው ልጆች ኢኮኖሚ የተመሠረተው አንድም በውሰትና ውለታ መላሽነት (Reciprocity)፤ ‹ሙቀጫ አውሱኝ ቡና ወቅጬ እመልሳለሁ፣ ብረት ምጣድ አውሱኝ አሻሮ ቆልቼ እመልሳለሁ› በሚል፣ የጎረቤት ለጎረቤትና የዘመድ አዝማድ ውሰትና ውለታ መላሽነት ሁለትም በጎሳ መሪ ክፍፍል አድራጊነት (Redistribution)፤ የእርሻ መሬትና የታረሰው በሙሉ የጎሳ መሪው ጎተራ ከገባ በኋላ የጎሳ መሪው እንደፈለገው ለጎሳው አባላት የሚያከፋፍልበት ሥርዓት፣ ሦስትም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ጎልቶ እንደሚታየው በቤተሰባዊ አንድነት ሥርዓት ምርትና ንግድ በቤተሰባዊ የጋራ ተጠቃሚነት ስለነበር፣ እያንዳንዱ ሰው በገበያ ኢኮኖሚ መርህ የራሱን የግል ተጠቃሚነት የላቀ ለማድረግ የሸቀጥ ሸመታ ምርጫ ማድረግና የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት አመክንዮ አልነበረም፡፡ ከታላቁ ትራንስፎርሜሽን በኋላ ግን ሰዎች በግል በሚያገኙት ተጠቃሚነት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ለመያዝ ምክንያታዊ ውሳኔ መወሰን ጀመሩ፡፡ የካፒታሊስት ተቋማትና ሥርዓት መዘርጋት የለወጠው የማኅበራዊ ኑሮ ሕግጋትን ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆችን የግብይይት ኢኮኖሚያዊ አመለካከትንም ሆነ፡፡ ስለሆነም ፖላኒ ጎሳዊ ማንነትን (Ethnography) ከውጫዊ ቅርጽ ዓይነታዊ ማንነት (Formalism) በውስጣዊ ይዘት ግብራዊ ምንነት (Substantivism) ቀይሮ ተንትኗል፡፡
እንደ ፖላኒ እምነት ነጻ ገበያ አልፋና ኦሜጋ የሆነ ዓለም ዐቀፋዊ የተፈጥሮ ሕግና ግዴታ ሳይሆን በታሪክ በአንድ ወቅት የተከሰተ ሁኔታና የተሻለ ከመጣም ሊቀየር የሚችል ነው፡፡ ከነጻ ገበያ በፊት መሬትና የተፈጥሮ ሀብት በገበያ ውስጥ የሚሸጡ ሸቀጦች ሳይሆኑ በሥነ ምግባር መርህ በሃይማኖታዊ እምነት እና በፖለቲካ አስተዳደር ማኅበራዊ ግንኙነት የሚገኙ ነገሮች እንደነበሩ ከፕሌቶና አሪሰቶትል ቅድመ ክርስትና ኢኮኖሚ አመለካከትና የመካከለኛው ዘመን የቶማስ አኳይነስ ግብረገባዊ የንግድ ሥነምግባር የኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች ያመለክታሉ፡፡ ስለሆነም ታላቁ ትራንስፎርሜሽን የለወጠው ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ አወቃቀርን እና የሰዎችን ኑሮ ወደ ካፒታሊዝም ለመቀየር ግፊት በሚያደርግ አገረ መንግሥት ምሥረታ ሲሆን፣ ለውጡ ከተቋማት አደረጀጃጀት ለውጥ ጋር አብሮ የሰው አስተሳሰብንም ቀይሯል፡፡
ፖላኒ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የገበያ ማኅበረሰብ የሰውን አስተሳሰብና የተገነባበትን ማኅበራዊ ሥርዓት ሥር መሠረት አናግቶ ስግብግብ እንስሳ ስለሚያደርግም፣ ዘላቂ አለመሆኑንና የኋላ ኋላ ራሱን በራሱ በልቶ የላቀ ብሔራዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ሥርዓት ነው ተብሎ በሚታሰበው በሶሻሊስት አብዮት እንደሚተካ አልሸሸገም፡፡ ምንም እንኳ ነጻ ገበያ የተትረፈረፈ ቁሳዊ ሀብት ቢያመጣም የማኅበረሰብን ህልውና በገበያ ሕግጋት መተካት ስለማይቻል ነጻ ገበያ ራሱን ከማኅበረሰቡ የመተሳሰብ የመደጋገፍና አንዱ ለሌላው አሳቢነት አፈጣጠር ውጪ በልዩነት ላይ የተመሠረተ ሰፊ ማኅበራዊ መፈናቀል ሲፈጥር ማኅበረሰብ ራሱን ለመጠበቅ የመደብ ትግልን የመሰለ ውስጣዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ሶሻሊስት ማኅበረሰብ እንደሚፈጥር ያምናል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ካርል ማርክስ እንደተነተነው የካፒታሊዝም ብዝበዛ የራሱን መቃብር ራሱ እስከሚቆፍር ገርጅፎ እንጂ እንደ ኢትዮጵያ የገበያ ኢኮኖሚ ጀማሪ በሆኑ አገሮች ውስጥ አይደለም፡፡ ሶቭየት ኅብረትና ሌሎች ቀድሞ ሶሻሊስት አገሮችም ሊፀኑ ያልቻሉት ጊዜውን ያልጠበቀ ሶሻሊስት አብዮት ስላላካሄዱም ነው፡፡ ይህን ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የኢኮኖሚ ደረጃ የቴክኖሎጂ ዕድገት እና ማኅበራዊ አስተሳሰብ ተጨባጭ ሁኔታ መመኘት ይፍጠንም ይዘግይ የሶቭየት ኅብረትን ዓይነት መፈራረስ መድገም ነው፡፡
የጆሴፍ ስቲግሊዝ ልማት ምልከታ
የአቶ መለስ የልብ ወዳጅ እንደነበሩ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተነገረላቸው የኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚና የቀድሞው የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ስቲግሊዝ ጥቅምት 10 ቀን 1990 ዓ.ም. በሄልሲንኪ ለተካሄደው የልማት ኢኮኖሚክስ ምርምር ተቋም መድረክ ለአዲስ የልማት ተምሳሌትነት (New Development Paradigm) ስትራቴጂዎች ፖሊሲዎችና ሂደቶች በሚል ርእስ ባቀረቡት ጽሑፍ ልማት ከልማዳዊ ማኅበረሰባዊ ግንኙነቶች ወደ ዘመናዊ ግንኙነቶች፣ ከለልማዳዊ አስተሳሰብ ወደ ዘመናዊ አስተሳሰብ፣ ከልማዳዊ የትምህርትና የጤና ተግባራት ወደ ዘመናዊ ተግባራት፣ ከልማዳዊ የአምራረት ዘይቤ ወደ ዘመናዊ የአመራረት ዘይቤ እንደ መሸጋገር የማኅበረሰብ ትራንስፎርሜሽን ነው በማለት በልማትና በማኅበረሰብ ትራንስፎርሜሽን መካከል ያለውን ጥብቅ ትስስር አትተዋል፡፡ ትራንስፎርሜሽን እንደ ጥንታዊ ማኅበረሰብ ነባራዊ ሁኔታዎችን እንዳለ ከመቀበል ይልቅ ሁኔታዎችን መለወጥ እንደሚቻል ያምናል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ አገሮች ሁሉም ማኅበረሰቦች ድብልቅ ናቸው፤ ልማዳዊውና ዘመናዊው ጎን ለጎን አብረው ይኖራሉ፤ ሆኖም ግን በአደጉት አገሮች ውስጥ ዘመናዊው ክፍል ሲበዛ በታዳጊ አገሮች ውስጥ ግን ልማዳዊው ይበዛል፡፡ ልማት በዚህ መልክ ከትራንስፎርሜሽን ጋር ተነጻጽሮ ከተተረጎመ የልማት ስትራቴጂ የለውጥ እንቅፋቶችን እና የለውጥ አራማጆችን ለይቶ እርምጃ በመውሰድ የማኅበረሰብን ትራንስፎርሜሽን የሚያሳካ መሆን አለበት፡፡
ይህ አመለካከታቸው ካርል ፖላኒ ስለ ታላቁ የእንግሊዝ ትራንስፎርሜሽን ከጻፈው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ለእኔ ጥያቄም እንቆቅልሽም የሆነብኝ አቶ መለስ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ማኅበረሰብ ወደ ኋላ ጎትተው ልማዳዊ ባላባታዊ የራስን በራስ አስተዳደር የጎሳ ሥርዓት እየመለሱ፣ በሌላ በኩል በቁሳዊ ሀብት ብልጽግና ከግብርና ምርት ወደ ኢንዱስትሪ ምርት መሸጋገርን የካፒታሊዝም ሥርዓተ ማኅበር አፈጣጠር ለውጥ አመለካከት የተቃረኑ አካሄዶች ሲጠነስሱ የልብ ወዳጃቸው ጆሴፍ ስቲግሊዝ እንዴት አላረሟቸውም ነው፡፡ ስቲግሊዝ መለስን አርመዋቸው ቢሆን ኖሮ የዛሬዎቹ የብሔሮቻቸውን አለመልማት በሌሎች ብሔረሰቦች ላይ የሚያሳብቡ ፖለቲከኞች አደብ በገዙ ነበር፡፡
ስቲግሊዝ በጽሑፋቸው ልማትን ሲገልጹ የማኅበረሰብ ትራንስፎርሜሽን ነው በማለት ከባህላዊና ልማዳዊ ግንኙነት፣ ከባህላዊና ልማዳዊ አስተሳሰብ፣ ከባህላዊና ልማዳዊ የጤናና ትምህርት አመለካከት፣ ከባህላዊና ልማዳዊ የአመራረት ዘይቤ ወደ ዘመናዊና ሳይንሳዊ መንገድ መቀየር ነው ይላሉ፡፡ በበለጸጉትም ሆነ ባልበለጸጉት አገሮች ባህላዊና ዘመናዊ ሁኔታዎች በጥምረት ቢኖሩም በበለጸጉት አገሮች ውስጥ ዘመናዊው አስተሳሰብ ልቆና ጎልቶ ሲታይ ባልበለጸጉት አገሮች ውስጥ ግን ባህላዊው ልቆና ጎልቶ ይታያል፡፡ ያልበለጸጉት አገሮች ዋና ባሕርይ ዘመናዊ አስተሳሰብ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰርጾ ስላልገባ በገጠርና በከተማ ኗሪዎች መካከል በቴክኖሎጂም በአመለካከትም ኋላ ቀርና ዘመናዊ መንታ (Dual) ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሁኔታ በጣት የሚቆጠሩ ጠማማ አስተሳሰብ ያላቸው በውጭ አገርና በአገር ውስጥ በከተማ የሚኖሩ የትራንስፎርሜሽን ልማት ተጠቃሚ የሆኑ ፖለቲከኞች በሺሕ የሚቆጠሩ ጠማማ አስተሳሰባቸውን ባለማወቅ ደግፈው የሚሞቱላቸው የትራንስፎርሜሽን ልማት ተጠቃሚ ያልሆኑ ወጣት የገጠር ኗሪዎች ማፍራታቸው ማኅበረሰባዊ መንትያ የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃችንን የሚያመለክት ነው፡፡
ስቲግሊዝ ሲናገሩ ልማት የግለሰቦችን ሕይወት የሚያቀለው የአመለካከት አድማሳቸውን በማስፋትና ማኅበረሰባዊ የመገለል ስሜታቸውን በመቀነስ ነው፡፡ ብዙ ቀደምት የልማት ስትራቴጂዎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ አትኩረዋል፤ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ አንዱ ቢሆንም ሁሉንም ግን አይደለም፡፡ በኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ላይ ብቻ ማትኮር ማኅበረሰባዊ የዘመናዊነት ለውጥ ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያትም ውጤትም ሊሆን እንደሚችል አልተጤነም ነበር ይላሉ፡፡
ስቲግሊዝ እንደሚሉት ልማት ዘላቂነት እንዲኖረውና ከኢኮኖሚ ዕድገት ባሻገር የአካባቢ ጥበቃና ማኅበረሰባዊ ትራንስፎረሜሽን ውጤት እንዲኖረው የልማቱ ማዕከል ከውሱን አካባቢዎችና ፕሮጀክቶች አጥር ወጥቶ ማኅበረሰብ ዐቀፍ እንዲሆንና የለሙና ያልለሙ አካባቢዎች መንታ ኢኮኖሚ እንዳይፈጠር ከቴክኖሎጂ ሽግግር ባሻገር ማኅበረሰባዊ ትራንስፎርሜሽንም መታሰብ አለበት አለበለዚያ ብቻቸውን የለሙ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ውሱን አካባቢዎች ሌሎችን የሚስቡ የዕድገት ማዕከል መሆን ይሳናቸዋል፡፡
የልማት ስትራቴጂው የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ፣ መንግሥትን፣ ማኅበረሰብን፣ ቤተሰብን እና ግለሰብን ያቀፈ መሆን አለበት፡፡ የልማት ስትራቴጂው ልዩ ልዩ ክፍሎች በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የግለሰብ ልማት ማዕከል ትምህርት ሲሆን ክህሎትን ማዳበር ምርታማ ሠራተኛን በመፍጠር ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት ማዕከል ይሆናል፤ በትምህርት አማካይነት የሴቶች ደሞዝ መጨመር ለቤተሰብ ልማት ማዕከል ነው፡፡ በዚህ መልክም አንዱ ከሌላው ጋር የተያያዙና የተሳሰሩ ናቸው፡፡ የልማት ለውጥ የአስተሳሰብ ለውጥ እንደመሆኑ ከውስጥ ይመነጫል እንጂ ከውጪ አይጫንም፡፡ ሰዎች በግድ እንዲናገሩ ወይንም በግድ እንዲሠሩ ሊደረጉ ይችላሉ፤ ልባቸውን እና አመለካከታቸውን በግድ መቀየር ግን አይቻልም፡፡ ለስኬታማ ማኅበረሰባዊ ትራንስፎርሜሽን የልማት ባለቤትነትና ባለድርሻ አካልነትም አስፈላጊ ነው፡፡ ቀደምት የልማት ኢኮኖሚስቶችም ልማትን ሲተረጉሙ የሌላ ሰው ስሜት ገላጭ አቀንቃኝ ወይም ባለሥልጣን የተናገረውን ደግመው የሚናገሩ አፈቀላጤና የገደል ማሚቱ ከመሆን ይልቅ ራስን እንደሙሉ ሰው ቆጥሮ በተረዱት ልክ የውስጥን አውጥቶ መናገር እንደመቻል ራስ አክባሪነት ሲመለከቱ ሌላው የቅርብ ጊዜ የልማት ኢኮኖሚ ኖቤል ተሸላሚው አማርተያሴንም ልማት ማለት ሰው ሕጋዊ የሆነን ማንኛውም ነገር በራሱ ለመሥራት አቅምና ነጻነት ማግኘቱ ነው ይላሉ፡፡
ዲሞክራሲ በሕዝባዊ መንግሥት የሚተረጎም የግሪካውያን ቃል
ዲሞክራሲ በሕዝባዊ መንግሥትነት የሚተረጎም የግሪክ ቋንቋ ቃል ሲሆን፣ በአንድ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ውስጥ የሁሉንም ሰው በእኩልነት መወከል የሚመለክት ሆኖ ከትራንስፎርሜሽን እና ከልማት ጋር የሚወራረስና የተሳሰረ ቃል ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊነት በውርስ ሳይሆን በምርጫና በድምጽ ብልጫ የፖለቲካ ሥልጣንን መጨበት ማለት ነው፡፡ ካለ ዲሞክራሲ ትራንስፎርሜሽን እና ልማትን ማምጣት አስቸጋሪ እንደሆነው ሁሉ ትራንስፎርሜሽን እና ልማት ባልገባበት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ከዚያ ይቀድማል ወይንም ያ ይህን ይከተላል የሚባልበት አይደለም፡፡ ዲሞክራሲን ሶሻል ዲሞክራሲ እና ሊብራል ዲሞክራሲ በማለት የቡድን ነጻነትና የግል ነጻነት አድርገው የሚተረጉሙ ቢኖሩም የግል ዲሞክራሲው በድምጽ ምርጫው ቡድንንም ከማቀፉም በላይ የቡድን ዲሞክራሲው የማኅበረሰቡ የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃና የሀብት ብልጽግና እንደ ስካንዲኔቪያን አገሮች ከገበያ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብነትም ልቆና መጥቆ ቡድናዊ ጥቅምንም ለማስጠበቅ በሚችልበት አስተማማኝ የብልጽግና ሁኔታ ላይ ካልደረሰ በቀር ከላይ እንደተመለከትነው የልደትና የውርስ ሥልጣን በመስጠት በገበያ ማኅበረሰብ ከሚፈጠር ትራንስፎርሜሽን ጋር ሊጋጭ ይችላል፡፡ በቡድን ስም ለራስ ብልጽግና መሻትና ሙስና መስፋፋትን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት የመጋት ያህል ውጦ ያቅለሸለሸው ስለሆነ እንደ አዲስ ነገር መናገሩ ለቀባሪው እንደ ማርዳት ይሆናል፡፡
ሆኖም ግን በዚህች ዓለም ላይ ሁሉም ነገር ተነጻጻሪ እንጂ ፍፁማዊ ነገር ስለሌለ ጫፍና ጫፍ የረገጡ አመለካከት ያላቸው ሰዎችን ወደ አስታራቂ መሃል ቤት ለማምጣት የቡድን ዲሞክራሲን እንደ የመፍትሔ አማራጭ የሚመለከቱበት ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዲሞክራሲ እና ፖለቲካዊ ዲሞክራሲ ሊለያዩም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በእንግሊዝ ወግ-ጠባቂዎች (‹ኮንሰርቫቲቮች›) እና በአሜሪካ ሪፐብሊካኖች በኢኮኖሚው ወደ ነጻ ገበያ ሊብራል ኢኮኖሚ ወይም ግላዊ የሀብት ይዞታ ነጻነት ዲሞክራሲ ሲያዘነብሉ በፖለቲካው ግን አክራሪ ቡድናዊና ብሔርተኞች ዘረኞችም ናቸው፡፡ በተቃራኒው በእንግሊዝ የሌበር ፓርቲ እና በአሜሪካ ዲሞክራቶች በኢኮኖሚው የጋራ ተጠቃሚነት ቡድናዊ ስሜትን ሲያንጸባርቁ በፖለቲካው ግን ነጻና ግላዊ ስሜትን ያንጸባርቃሉ፡፡ ዲሞክራቱ ኦባማ ጤና በጋራ ለሁሉም ‹ኦባማ ኬር› ቡድናዊ ፖሊሲን ሲከተሉ ሪፐብሊካኖቹ የቻለ ከፍሎ እንዲታከም ቢደረግ ሁሉም ለመቻል የራሱን ጥረት ያደርጋል የሚል ግላዊ ፖሊሲን ያራምዳሉ፡፡ ዲሞክራቶቹ ከሀብታሞች ከፍተኛ ታክስ ሰብስቦ የድሆችን ማኅበራዊ አገልግሎቶች ማስፋፋት ፖሊሲ ሲያምኑ ሪፐብሊካኖች ግን ለሀብታሞች ታክስን መቀነስ አገርን ያሳድጋል ይላሉ፡፡
ማጠቃለያ
2013 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ እንደ አንድ ብሔራዊ አገረ መንግሥት የመጠንከር ወይም የመላላት ምርጫ ዓመት ነው፡፡ አገሪቱን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን የወደፊቱ እጣ ፋንታዋ መንገድ ጠራጊ የፖለቲካ ፓርቲዋን የምትመርጥበት ዓመት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹም ቢያንስ የ1997ቱን ያህል ፕሮግራማቸውን እና ሐሳባቸውን የሚገልጹበት የውድድር መድረክና የሚድያ ሽፋን ያገኛሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች በባዶና አስጎምጂ ቃላት ብቻ ሕዝቡን እንዳይደልሉ ከምሁራን ብዙ የሚጠበቅ ነገር አለ፡፡ በየትኛውመም ዘርፍ ያሉ ምሁራን በመጻፍም በመናገርም የእያንዳንዱን የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም እና ዕቅድ ከጽንሰ ሐሳባዊ ትንታኔ ጋር በማገናዘብና የማስፈጸም አቅምን በመፈተሸ ፈትገው አበጥረው አንገዋለው የሕዝብ ድምጽ መስጫ ሳጥን ላይ የሚያስቀምጡበት ዓመት ነው፡፡ በአምስት ዓመት ውስጥ አንዴ ብቻ የሚያጋጥም ዕድል ስለሆነ ካመለጠ በኋላ እንዳይቆጨን ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
Leave a Reply