በጥናት ላይ ያልተመሠረተው የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ | ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር)
ኢኮኖሚ

በጥናት ላይ ያልተመሠረተው የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ | ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀን ከባንክ ወጪ ማድረግ የሚቻለውን የገንዘብ መጠን አስመልክቶ ክለሳ አድርጓል፡፡ ቀደም ሲል በግለሰብ በቀን ከባንክ ወጪ ማድረግ የሚቻለው የብር መጠን እስከ 200 ሺሕ ብር የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ መመሪያ ወደ 50 ሺሕ ብር ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ገደቡን ወደ 50 ሺሕ ብር ዝቅ ለማድረግ ካስቀመጠቻው ምክንያቶች አንዱ የገበያን ለማረጋጋት የሚል ይገኝበታል፡፡ ይሁን እንጅ ውሳኔው በየትኛውም መለኪያ ትክክለኛ እና ምክንያታዊ አይደለም፡፡ ባንኩ በገበያ ውስጥ ያለውን ገንዘብ መሰብሰብ ወደ ባንክ እያስገባ ነው፡፡ ገንዘብ በተሰበሰበ ቁጥር እና በገበያ ውስጥ የገንዘብ እጥረት በተፈጠረ ቁጥር የምርቶች ዋጋ ይጨምራል እንጅ ይቀንሳል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ በገበያው እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ የብር ለውጡን ተከትሎ ያልጨመረ ነገር የለም፡፡  የእኛ አገር ነጋዴ ዋጋ ለመጨመር ምክንያት ነው የሚፈልገው፡፡

አሁን መንግሥት ወደ ባንክ መግባት አለበት እያለን ያለው ገንዘብ ቀድሞም ቢሆን በገበያ ውስጥ የነበረ ገንዘብ አልነበረም፡፡ ከዚህ ቀደም የባንኮች ማኅበር ከባንክ ውጪ ነው ያለው 113 ቢሊዮን ብር ተቀምጦ ያለው በግለሰቦች አልጋ ስር አልያም ከአገር ውጭ ነው፤ ይህ ማለት ገንዘቡ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ አልነበረም ማለት ነው፡፡

የገንዘብ ለውጡ ከተጀመረ በኋላ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ባንክ መግባቱን የብሔራዊ ባንክ ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ ይህ ገንዘብ በገበያ ውስጥ የነበረ ገንዘብ እንጅ በግለሰቦች እጅ ተከማችቶ የነበረ ገንዘብ ነው ብሎ ማስበ ለእኔ ከባድ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ላይ መንግሥት በገበያ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ጠራርጎ ወደ ባንክ እያስገባ ነው፡፡ ይህም በገበያው ላይ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እየፈጠረ  ይገኛል፡፡  ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ በገበያው ላይ ጥሬ ገንዘብ ለማግኘት በሚደረግ ፍላጎት የምርቶች ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በዚህ ውስጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዜጋ ለጉዳት እየተዳረገ ይሄዳል፡፡ ይህን ሕዝብ ቀደም ብሎ ኮሮና አዳክሞታል፤ አሁን ደግሞ የመንግሥት ወቅቱን ያላገናዘበ ውሳኔ ይበልጥ እያዳከመው ነው፡፡

አሁን ላይ እየተወሰነው የባንክ ጥሬ ገንዘብ የማውጫ ጣሪያ 50 ሺሕ ብር መሆኑ ወቅትን እና የአገሪቱ [ወቅታዊ] አቋም ያላገናዘብ እንደሆነ ነው የምረዳው፡፡ የገንዘብ ወጪ ጣሪያው ቢቀመጥም ዛሬም ገንዘብ በባንክ ውስጥ ማሰተላለፍ የሚቻል በመሆኑ እና ግብይትንም በዚያው መንገድ ማድረግ ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ገበያን በምን መልኩ ይረጋጋል ብለው እንዳሰቡ ግልጽ አይደለም፡፡ የግብይት መንገዱ ተቀየረ እንጅ በፊት የሚደረገው ግብይት አሁን ይፈፀማል፡፡ በበኩሌ ውሳኔው ከንግድ መንገድ ጋር እንጅ ከምርት ዋጋ ጋር የሚገናኝበት መንገድ አለ ብዬ አላስብም፡፡  በዚህ አገር ካለው የቦንክ ሥርዓት አለመዘመን ጋር ተያይዞ የግብይት ሥርዓቱን ወደ ውስብውብ እና አስቸጋሪ መንገድ እንደ ከተቱት ነው የሚሰማኝ፡፡

አሁን የተወሰነው ውሳኔ አብዛኛውን ሕዝብ የሚነካ ውሳኔ ነው፡፡ ዛሬ መርካቶ ላይ ያለው አብዛኛው ንግድ የሚከናወነው እጅ በእጅ የገንዘብ ልውውጥ ነው፡፡ ጥቂት ሰዎች ገንዘብ ይዘዋል በሚል ምክንያት አገር ዐቀፍ  ገበያውን የሚያውክ እርምጃ መውሰድ ትክክለኛው መንገድ ነው፡፡ የዚህ አገር ሰው ገንዘብን የሚገበያየው በጥሬ ገንዘብ አማካይነት ነው፡፡ አሁን ሁሉን ነገር በባንክ አድርግ ተብሎ የገንዘብ ማውጫውን 50 ሺሕ ብር ማድረግ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸው አልቀረም፤ አሁንም እየተስተጓጎለ ነው ያለው፡፡

የዚህ አገር የዋጋ ውድነት/ንረት የመጣው በቅንጦት እቃዎች ላይ አይደለም፡፡ የመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች  ዋጋ ነው ከእለት ወደ እለት እየጨመረ  ያለው፡፡  እንደዚህ ዓይነት የዋጋ ውድነት ገንዘብ እጅ ላይ ቢቀመጥም በባንክ ቢቀመጥም ያወጣውን ዋጋ አውጥተን ሰዎች ይገዛሉ፡፡ ምክንያቱም ውድነቱ ያለው በመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ስለሆነ፡፡  የገንዘብ ወጪ ተመን ሲቀመጡ በምን መልኩ የዋጋ ውድነት ያረጋጋል ተብሎ እንደታሰበ በግልጽ ቢቀመጥ ጥሩ ነበር፡፡

በአሁኑ ሰዓት በ50 ሺሕ ብር ምንም መግዛት እንደማይችል ይታወቃል፡፡ የቤት እቃ ለማሟላት፣ ቤት ለመከራየት 50 ሺሕ ብር ዛሬ ብቻውን አቅም የለውም፡፡ መርካቶ ገብቶ እቃ ወደ ክፍለ አገር የሚጭነው ሰው የስንት ብር እቃ ነው የሚገዛው? ዛሬ በ50 ሺሕ ብር የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ  የለም፡፡ ያንን መሸከም የሚችል የባንኮች አገልግሎች በአገራችን ገና አልተገነባም፡፡ በዚህ ሰዓት የቢዝነስ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ ነው ያለው፡፡ መንግሥት የቢዝነስ እንቅስቃሴው እስኪያንሰራራ ጊዜ መስጠት ነበረበት፡፡ ዛሬ የቢዝነስ እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተቀዛቅዟል፡፡ በዚህ ምክንያት ቢዝነሱ ጭንቀት የሚፈጥርበትን ነገር አይፈልግል፡፡ በዚህ ሰዓት በገበያው ላይ የጥሬ ገንዘብ እጥረት መፍጠር በፍፁም ሊታሰብ የማይገባው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አካሄድ ከቀጠለ ሰው በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት እያጣ ነው የሚሄደው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ይህን ዓይነት ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት በዚህ ሰዓት የአገሪቱ የግዥ ሥርዓት የት ደርሷል? የሚለውን ነገር በጥናት ማየት ነበረበት፡፡

ዛሬ ልጅ ቢታመም ለአልጋ ከ50 ሺሕ ብር በላይ ነው የሚጠየቀው፡፡ ስንቱ ሆስፒታል ነው የሞይል ባንኪንግ ተጠቃሚ የሆነው? ስንቱ ሆስፒታል ፓስ ማሽን አለው? ይህ ሥርዓት ገና ባልተዘረጋበት ሁኔታ ነው ብሔራዊ ባንክ አገሪቱን የማይመስል መመሪያ እያወጣ ሕዝብን ውዝግብ ውስጥ እየከተተ የሚገኘው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ በፍጥነት ካልታረመ አደገኛ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ለሚያወጣቸው መመሪያዎች ዝርዝር ጥናቶች ቢያደርግ መልካም ነው፡፡

October 21, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *