ለዓለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ተጋላጭነታችን
ኢኮኖሚ

ለዓለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ተጋላጭነታችን

ማንም ሰው አዋቂ የገበያ ኢኮኖሚ ሰው ሳይሆን የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሰውነትን መስፈርት አያሟላም:: የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሰው ያልሆነም ከሌሎች አገሮች ሰዎች ጋር ተወዳድሮና ተገበያይቶ መኖር አይችልም:: በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የገበያ ኢኮኖሚ ዳብሮ የገበያ ኢኮኖሚ ሰው ባሕርይን ተላብሰን ፍላጎትና አቅርቦት ተመጣጥነው ትክክለኛው የሸቀጦች ዋጋ በገበያ ውስጥ ተተምኖ ገበያዎቻችን ይስተካከላሉ ይሆን? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል:: በቅርብ ካልተስተካከሉ መቼ ይስተካከላሉ? ከሐምሳ ዓመት በኋላ ወይስ ከመቶ ዓመት በኋላ? ወደዚያ እየሄድን ነው ወይስ ከዚያ እየራቅን ነው? ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል:: መቼ የገበያ ኢኮኖሚ ሰዎች ልንሆን እንደምንችል ሲታሰብ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው:: ምናልባትም ከማንኛውም የሰው ልማት መለኪያ ይበልጥ የወደፊቱን የኢትዮጵያውያን እጣ ፋንታ የሚያመለክተው በዓመት ስንት ሰው የገበያ ኢኮኖሚ ሰው ይሆናል? የሚለው መለኪያ ሊሆን ይችላል:: ወደ የገበያ ሰውነት የማይጓዝ ሁሉ ወደ ሽሚያ እየተጓዘ ነው:: በሽሚያ መርከብ የተሳፈረ ሁሉ ቀስ በቀስ መርከቧ እየሰጠመችበት ነው::

ከዚህ ቀደም በተመለከትናቸው የሊብራል ኢኮኖሚና የልማታዊ መንግሥት መለያ መገለጫዎችና የሁለቱ ልዩነቶች እንዲሁም ንጽጽሮች የአገሮችን ተሞክሮ እና የኢትዮጵያን ፈለግ ተመልክተናል በዚህ ክፍል ታዳጊ አገሮችን እና ያደጉ አገሮችን ከሸቀጥ በነጻ ገበያ እንደልብ ዝውውር ባሻገር በኢኮኖሚ ያስተሳሰራቸው የካፒታል ከአደጉ አገሮች ወደ ታዳጊ አገሮች እና ሠራተኛ ከታዳጊ አገሮች ወደ አደጉ አገሮች ዝውውርን በመጠኑም ቢሆን የፈቀደው የግሎባላይዜሽን ፍልስፍና ከኮቪድ-19 መከሰትም በፊት በአንዳንድ የአደጉ አገራት ብሔርተኛ መንግሥታት ወደ ሥልጣን መምጣት እየላላ መምጣቱን ያየንባቸው በርካታ ሁኔታዎች እና ጊዜያት ነበሩ:: የዓለም ኢኮኖሚ ጉዞ ፍልስፍናና መንገድን ታሪክ ማጤን የራሳችንን መንገድ ለመቀየስ ጥንቃቄ ለማድረግም ስለሚረዳን ምንም ማድረግ ባንችልም እንኳ አውቆ መገኘቱ ይጠቅማል::

በዚህ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የልማታዊ መንግሥት አገሮች የራሳቸውን የኢኮኖሚ አስተዳደር ከገበያ መር የሊብራል ኢኮኖሚ የተሻለ አድርገው ይመለከቱ ነበር:: የገበያ መር ሊብራል ኢኮኖሚ አገራትም የራሳቸውን የኢኮኖሚ አስተዳደር ከልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚ የተሻለ አድርገው ይመለከቱ ነበር:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በግሎባላይዜሽን ፍልስፍና ዓለም የአንድ ገበያ መንደር ትሁን ሲሉ ኖረው በገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ባሻቸው አገር ሄደው መዋዕለንዋይ አፍስሰው ብዙ ሀብት ከያዙ በኋላ ሁሉም በየአገሩ ሠርቶ ይብላ፤ ወደ ውጭ የሄዳችሁ ተመልሳችሁ ወደ አገራችሁ እንድትመጡ ስደተኞችም እዚያው በአገራችሁ ኑሩ ወደ እኛ አትምጡ አሉ:: ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ይዘረዝራሉ:: ደህንነታችንና ጸጥታችን በአሸባሪዎች ተናጋ ከሚለው ፖለቲካዊ ጉዳይ ጀምሮ እስከ የራሳችንን ሰው እያደኸየን የሌላ አገር ሰው አናከብርም የሚል ኢኮኖሚያዊ ጉዳይም ያነሳሉ::

በዐሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ቀድሞ የነበረውን የዓለም ዐቀፍ ንግድ ኢኮኖሚ (Mercan­talism) ተክቶ በምዕራባውያን አገሮች የሰረጸው የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር 1930ዎቹ በምርት እጥረት፣ በገቢ መቀነስ፣ በሥራ አጥነት መስፋፋት፣ ምክንያት የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ የመጀመሪያ ምዕራፍ ቀውስ ውስጥ ገብቶ ኢኮኖሚስት ሎርድ ኬንስ በሰጠው ትንታኔ መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በሚመራበት ሁለተኛው ምዕራፍ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ተሸጋገረ:: እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ የምዕራባውያን መንግሥታት ብሔራዊ ኢኮኖሚውን በፖሊሲ መምራት ስለአቃታቸው እንግሊዝ፣ አሜሪካ እና ጀርመን በርእሳነ መንግሥታቱ በዓለም ባንክና በዓለም የጥሬ ገንዘብ ጥሪት (IMF) ጠንሳሽነት ከሁለተኛው ምዕራፍ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አመራር ወደ የቀድሞው የነጻ ገበያ ሊብራል ኢኮኖሚ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተመለሱ፣ የቀድሞው ተመልሶ በመምጣቱም የኒዮ-ሊብራል ኢኮኖሚ ተባለ:: እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2008 በተከሰተው የገንዘብና የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ምራባውያን አገሮች በተለይም አንግሎ-ሳክሶን በመባል የሚታወቁት አሜሪካንን እና እንግሊዝን የመሳሰሉ አክራሪ የገበያ አገሮች እንደገና ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ የገበያ ኢኮኖሚ መንግሥታዊ የፖሊሲ አመራር ተመልሰው ጽንፍም ሳይዙ በመጀመሪያውና በሁለተኛው የገበያ ኢኮኖሚ ምዕራፎች ቅይጥ የገበያ ኢኮኖሚ እየተዳደሩ ይገኛሉ::

እ.ኤ.አ. በ2016 በታየው ፍንጭ የእንግሊዝን ከአውሮፓ ኅብረት አባልነት መውጣት እና አዲስ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መመረጥን ተከትሎ ያልተጠበቁ ርቆ ወደ ኋላ የመሄድ አዳዲስ ለውጦችን ተመልክተናል:: የነጻ ገበያ ሊብራል ኢኮኖሚን የሚተካ የለም ሲሉ የነበሩት ምዕራባውያን የአገራችሁን ግዙ የአገራችሁን ሰው ቅጠሩ ብሎ ከመስበክም አልፈው ቅድሚያ ለዜጋው በሚል መፈክር በውጭ መዋዕለንዋይ ያፈሰሳችሁ ወደ አገራችሁ ብትመለሱ ድጋፍ ይደረግላችኋል፤ ከግሎባላይዜሽን ፍልስፍናና ከሊብራል ነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ሥርዓት ያፈነገጠ ወደ ጥንቱ የብሔርተኛ ንግድ ኢኮኖሚ ሥርዓት የተመለሰ አመለካከት በተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና በሌሎች አገሮች ለምርጫ በቀረቡ ተወዳዳሪዎች ተንጸባረቀ::

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር በ2017 በዳቮስ ስዊዘርላንድ ለዓለም የኢኮኖሚ መድረክ ባቀረቡት ሪፖርት እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣቷ ከግሎባላይዜሽን ማፈንገጥ ሳይሆን ገበያችንን ከአንድ አሕጉር ወደ ዓለም ዐቀፋዊነት ማስፋት ነው ቢሉም ምስጢሩ ግን ከሊብራል ነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት በፊት ወደ ነበረው የብሔርተኛ ንግድ ኢኮኖሚ ሥርዓት መመለስ ነው:: በሌሎች የሊብራል ነጻ ገበያ ኢኮኖሚ አውሮፓና አሜሪካ አገሮችም የብሔርተኛነት ስሜት እያደገ ስለሆነ ታዳጊ አገሮች የኢኮኖሚ ሥርዓታቸውን በጥንቃቄ መምረጥ አለባቸው:: የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታትና ሕዝቦች የግሎባላይዜሽን ንግድን ከሚደግፉ ተወዳዳሪዎች ይልቅ ለብሔርተኛ ኢኮኖሚ ሥርዓት አቀንቃኝ የሥልጣን ተወዳዳሪዎች ድምጻቸውን በመስጠት የውስጥ ስሜታቸው ምን እንደሆነ አስመስክረዋል::

ይህ የራሳቸው በቂ ካፒታል አጥተው በውጭ ቀጥታ መዋዕለንዋይ ማደግ ተስፋ ላደረጉና በግሎባላይዜሽን እምነት ለጣሉ ታዳጊ አገሮች የጥንቃቄ ደወል ነው:: የውጭ ቀጥታ መዋዕለንዋዩ ታዳጊ አገርን ጠቅሞ ሳይሆን ርካሽ ጉልበት በዝብዞ መሬቷን አራቁቶ አደህይቶ ሱሶችን አስለምዶ ራስን ለመቻል እንኳ በቂ ጊዜ ሳይሰጥ ይሄዳል:: የሊብራል ነጻ ገበያ ኢኮኖሚ በግሎባላይዜሽን ፍልስፍና ዓለምን እንደ አንድ መንደር በመቁጠር ሠርቶና ነግዶ ማደር በአገር ድንበር አይታጠር፣ ሰውና ካፒታል በመረጡት አገር ተዘዋውረው ይሥሩ፣ ሰው ሁሉ ከብሔርተኝነት ስስት ይላቀቅ፣ የሚል ይመስል ነበር:: ምንም እንኳ በኢሚግሬሽን ሕጎች አማካኝነት ሰው እንደልቡ ከአገር አገር ተዘዋውሮ የመሥራት ዕድሉ ሙሉ በሙሉ ባይለቀቅለትም ካፒታል ግን ርካሽ ጉልበትና ድንግል መሬት ፍለጋ ወደ ድሃ አገሮች እንደልቡ ገብቶ እየበዘበዘም ቢሆን ሠርቶ ያሠራም ነበር::

የቀድሞው የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ባርልስኮኒ ፓርቲያቸው እንደገና ከተመረጠ መቶ ሺሕ ስደተኞችን ከአገር እንደሚያባርሩ ለመራጮች ቃል ገቡ:: አፍሪካውያንን ከአውሮፓ ማባረር የምርጫ ቅስቀሳ መሣሪያ ሆኗል፣ አገሮቻቸውን ማልማት ትተው አውሮፓና አሜሪካንን በሎሌነት የሚያገለግሉ ስደተኞች የወደፊት እጣ ፋንታ ምንድን ነው? የሩሲያው ፕሬዚዳንት የጥንቱን የሶቭየት ኅብረትን ኀያልነትና ገናናነት ናፋቂ ተብለው በአንድ ወቅት በሌሎች አገሮች መሪዎች ቢብጠለጠሉም በአገራቸው ሰዎች ግን አገር ወዳድ ብሔርተኛ ተብለው ተወድሰዋል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም አወድሰዋቸዋል::

ግሎባላይዜሽንን መጀመሪያ ያቀነቀኑት እንግሊዝና አሜሪካ ብሔርተኝነትን ለማቀንቀንም የመጀመሪዎቹ ሆኑ:: በሰው አገር ሄዶ የሌሎችን የተፈጥሮ ሀብትና ማዕድናት ተጠቅሞ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የዓለምን ኢኮኖሚ በእጥፍ ያሳደገው ካፒታላቸው ወደኛው ይመለስ አሉ:: እንደ ካፒታሉ ሙሉ የመዘዋወር ነጻነት ባይሰጠውም ከመጣ እንቀበለው በሚል ላላ ተደርጎ ተይዞ የነበረው የስደተኞች ጉዳይም ከፊሎቹ የምዕራብ አገሮች ሕዝቦች መንገድ ጠርገው ጽዳት አጽድተው ዝቅተኛ ሥራዎችን በሠሩ ለምን እንዳይመጡ እንከለክላቸዋለን ቢሉም በአንዳንዶች ግን ስደተኞች ወደ አገራችን እንዳይመጡ ግንብ እንገነባለን በሚል የመጥበብ ስሜት ተተካ::

ሰዎች ሰልጥነናል ሥልጣኔም ስሜታዊነትንና ጠባብነትን ያስወግዳል የሰው ዘር አንድ ነው ቀለምና ቅርጽ አይለያየንም ካሉ ከዓመታት በኋላ እንደገና ጠባብ ሲሆኑ፣ ገና አለመሰልጠናቸውን እየተረዳን እውነተኛው ውስጣዊ ማንነታቸውን እያየንም ነው:: ወትሮውንም የኢኮኖሚ አስተዳደር አቋም በመቀያየር ድብቅ ዓላማቸው የድሃ አገሮችን የተፈጥሮ ሀብትና ርካሽ ጉልበት መበዝበዝ ኖሮ ግሎባላይዜሽንን የሚያቀነቅነው የነጻ ገበያ ኢኮኖሚም ጠባብነትን የሚያቀነቅነው ብሔርተኛ የንግድ ኢኮኖሚም እነርሱኑ እንደሚጠቅሙ ተደርገው የተነደፉ ናቸው:: በግሎባላይዜሽኑ ሀብታሞቹ የምዕራቡ ዓለም ካፒታሊስቶች ይበልጥ ከከበሩ ድሆቹ የታዳጊ አገሮች ሕዝቦች ይባስ ከደኸዩ በኋላ የእነርሱ ስምንት ሀብታም ሰዎች ሀብት የዓለምን ግማሽ ሦስት ተኩል ቢልዮን ድሃ ሕዝቦችን ሀብት ካከለ በኋላ የከበሩት ወደ የአገሮቻችን እንሰባሰብ ተባባሉ:: የታዳጊ አገር ሰው በግሎባላይዜሽኑ ዓለምን እንደ አንድ መንደር ቆጥሮ አብሮ ለመኖር ጉጉት፣ የሀብታሙ መዋዕለንዋይ ይዞ መጥቶ መመዝበር እና የወጣቱ ትውልድ በባሕርና በበረሃ ወደ ከበርቴዎቹ ለሎሌነት መሰደድ፣ ያላቻ ጋብቻ ስምምነት መጎዳትን ብቻ ነው ያተረፈው::

በ1950ዎቹና 1960ዎቹ ታዳጊ አገሮች በቀጥታ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ሊገቡ ስለማይችሉ በቅድሚያ በኢኮኖሚ ልማት ራሳቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለው ያማከሩት በገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ያደጉ ምዕራባውያን ናቸው፤ ከጊዜ በኋላ ሐሳባቸውን ቀይረው የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ነድፈው ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ግቡ ያሉትም እነሱው ናቸው:: ከቅኝ ግዛት ማብቃት ጀምሮ እስከ ግሎባላይዜሽን በነበረው ጊዜ የእያንዳንዱ አገር ኢኮኖሚ ግንኙነት የተመሠረተው በሁለትዮሽ የአገሮች ንግድ ስምምነት ላይ ስለነበረ ታዳጊ አገሮች ራሳቸውን ችለው በኢኮኖሚ ልማት ፍልስፍና ለአገራቸው የሚበጅ የውስጥና የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ቢያድጉ ምዕራባውያንን የሚጎዳቸው ነገር ስለሌለ አልተቃወሟቸውም:: በግሎባላይዜሽን ዘመን ግን በሌላ አገር ጥሬ የተፈጥሮ ሀብት ለማደግ የንግድ ትስስር መፍጠርና በሌላ አገር ርካሽ ጉልበት ለመጠቀም በውጭ አገር መዋዕለንዋይ ማፍሰስ ተፈልጎ ምዕራባውያን መንግሥታት በዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ተጽዕኖ ታዳጊ አገሮች የገበያ ኢኮኖሚን እንዲከተሉ ግፊት አደረጉ:: የውስጥና የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ፖሊሲያቸው የዓለም ዐቀፍ ንግድን እንዳያደናቅፍ ብለው ከለከሏቸው:: ለአገራቸው ከማሰብ ይልቅ ለዓለም እንዲያስቡ መከሯቸው::

የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራሙ በልማት ኢኮኖሚ አመለካከት ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ታዳጊ አገሮችን ወደ ገበያ ኢኮኖሚ እንዲቀየሩ አድርገዋቸዋል:: አንዳንድ ታዳጊ አገሮች ግን በእርዳታ አሰጣጥና በሌሎች ምክንያቶች ተጽዕኖው ቢያይልባቸውም ከገበያ ኢኮኖሚው ይልቅ በልማት ኢኮኖሚ ፍልስፍናቸው ጸንተው መቆየትን መርጠዋል:: የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራሙን ላለመቀበል የምርጫቸውን ትክክለኛነት ለሕዝባቸው ለማስረዳት ምሳሌ አድርገው የሚያቀርቡትም በሰፊ የመንግሥት መር የልማት ኢኮኖሚ ፍልስፍና የደቡብ ምሥራቅና ደቡብ እስያ አገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ አድገው የሕዝባቸውን የኑሮ ደረጃ ማሻሻላቸውን ነው::

ሆኖም ቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃቸው ዝቅተኛ በሆነበትና በፍጥነት ወደ ኢንዱስትሪ ምርት ሊገቡ ባልቻሉ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ውስጥ የልማት ኢኮኖሚና የገበያ ኢኮኖሚ ካልተደጋገፉ አንዱ የወሰደውን ሀብት ሌላው ስለሚያጣው በሀብት ሽሚያ ይጋጫሉ:: ይህ ግጭትም ከተመጣጣኝ የመንግሥትና የግል

ሀብት ይዞታ ድርሻ በራቀና በቀረበ ቁጥር ግጭቱ የሰፋና የጠበበ ይሆናል:: ስለዚህም የእነዚህ አገሮች የመጨረሻው ዕድላቸው የኑሮ ደረጃው ዝቅተኛ በሆነ ግብር ከፋይ ሕዝባቸው ወጪና መስዋዕትነት መሠረተልማት ገንብተው ምዕራባውያኑንም ምሥራቅያውያኑንም ርካሽ ጉልበትና ድንግል መሬት ተጠቅመው መዋዕለንዋይ አፍስሰው ለውጭ ገበያ ሸቀጥ አምርተው እንዲሸጡ ለምኖ ከሚገኘው ትርፍራፊ መጠቀም መሆኑን እያየን ነው::

ደርግ በኢሕአዴግ ሲተካ የበለጸጉት አገሮች እና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ታዳጊ አገሮችን ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ለማስገባት የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ቀርጸው የተንቀሳቀሱበት ጊዜ ስለ ነበር ኢትዮጵያም ይህንን የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ስትተገብርና በደርግ መንግሥት ተወርሰው የጋራ ሀብት የነበሩትን ድርጅቶች የማስተዳደር ልምድ ለሌላቸው ግለሰቦች ስትቸበችብ ከኖርች በኋላ ከኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር 1990ዎቹ ጀምሮ ፊቷን ወደ ቻይና በማዞር የልማታዊ ኢኮኖሚ ተከታይ አገር ነኝ አለች::

ሶቭየት ኅብረት በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎቹ ዓመታት የሶሻሊስት ኢኮኖሚን መገንባት እንደጀመረች ለመሠረተልማትና ትላልቅ ኢንዱስትሪ ግንባታ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት መላውን አገር በኤሌክትሪክ አጥለቀለቀች የባቡር ትራንስፖርት ተስፋፋ የብረት ማቅለጥና ማሺነሪ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎችም ገነባች፣ በጦር ኀይልም ከአውሮፓ የሚወዳደራት አልተገኘም ከአሜሪካ የምትፎካከር ሁለተኛ ኀያል አገር ሆነች:: ለሕዝቦቿ የፍጆታ ሸቀጦችን በማቅረብ ግን ከውጭ ሸምተው የሚኖሩት ታዳጊ አገሮች ሳይቀሩ ይበልጧት ነበር:: የሶቭየት ኅብረት ውድቀት ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው:: እስከዛሬም ድረስ ምንም እንኳ የተፈጥሮ ሀብት በመታደል ከዓለም ቀዳሚ አገሮች አንዷ ብትሆንም በነፍስ ወከፍ ገቢ መጠን ብዙ ትናንሽ አገሮች ይበልጧታል:: በቅርቡ በኢኮኖሚ ቀውስ ስትናወጥ የነበረችው ግሪክ በነበራት ሃያ ስምንት ሺሕ ዶላር ነፍስ ወከፍ ገቢ የሩስያን ሰባት ሺሕ ዶላር ነፍስ ወከፍ ገቢ በአራት እጥፍ ትበልጥ ነበር:: ኢትዮጵያ በያዘችው የልማታዊ መንግሥት አካሄድ የወደፊት እጣ ፋንታዋ ከእስያ ልማታዊ አገሮች ጋር የሚመሳሰል ሳይሆን ከቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ጋር የሚመሳሰል ሊሆን ይችላል:: የገበያ ኢኮኖሚውን እና የልማት ኢኮኖሚውን ባለማመጣጠን የሕዝቦቿን የቁሳዊ ሀብት ፍላጎት፣ እንደ ተቀረው ዓለም ለመኖር መንፈሳዊ ጥማት ልታረካ ሳትችል ትቀራለች:: ምናልባት ለውጭ መዋዕለንዋይ አፍሳሾች የሰውን ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብትን በርካሽ ዋጋ በመሸጥ የግሎባላይዜሽን ፍልስፍና መሠረት ኢትዮጵያ ከሶቭየት ኅብረት የተለየ ሁኔታ ሊገጥማት ይችል ይሆናል፤ ይህ ግን ምናልባት ብቻ ነው::

ለምሥራቅ እስያውያኑና ለደቡብ ምሥራቅ እስያውያኑ ልማታዊ መንግሥታት ፈጣን ዕድገት የምዕራባውያን ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎችና ግሎባላይዜሽኑ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳደረጉ ይነገራል:: ዛሬም አፍሪካውያን ካለ የውጭ መዋዕለንዋይ ሊያድጉ እንደማይችሉ እምነታቸው ጽኑ ነው:: ጥንት በቅኝ ግዛትና በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ኋላም በግሎባላይዜሽን መርህ የአፍሪካን ከርሰ- ምድርና ገጸ-ምድር ሲግጡ የነበሩ ምዕራባውያን ጠግበው በቃን ሲሉ በቦታቸው ለመተካትና በቀጥታ መዋዕለንዋይ ማፍሰስ ስም የአፍሪካን ሕዝብ ርካሽ ጉልበት እና የተፈጥሮ ሀብቷን ለመበዝበዝ ደፋ ቀና የሚሉት ደግሞ ራሳቸውም ገና ለማደግ ደፋ ቀና እያሉ ያሉና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየበለጸጉ ያሉ የልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና ተከታይ ነን ያሉ ሕንድ፣ ቱርክ፣ ቻይና፣ የዐረብ አገሮች ናቸው፡

ዐረቦች፣ ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉ ልማታዊ አገሮች የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በሚያስብል ደረጃ በውጭ ቀጥታ መዋዕለንዋይ ስም በታዳጊ አገሮች ውስጥ እግራቸውን እየተከሉ ነው:: መሬታቸው ምንም የማያበቅል አሸዋ የሆነባቸው ዐረብ አገሮች በነዳጅ ሀብታቸው ለወደፊት የልጅ ልጆቻቸው ርስት በአፍሪካ ውስጥ እየገዙ ነው፤ ቻይናና ሕንድ የዓለም ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት የሕዝብ ብዛትን ይዘው፣ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብትና አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላት አፍሪካ ውስጥ ምን የረጅም ዘመን ዕቅድ እንደሚኖራቸው ማን ያውቃል:: ታዳጊ አገሮችን በፍጥነት አሳድገው ይጠቅሟቸው ይሆን ወይስ ምዕራባውያን በቀድሞ ዘመናት እንዳደረጉት ጥሬ ሀብታቸውን እና ማዕድናቶቻቸውን በዝብዘው ዞር ለማለት ነው ወይስ ወደ ፊት ዓለም አንድ መንደር ስትሆን ለማንም የእኔ የሚለው አገር ስለማይኖር ሕዝባቸው በሰው አገር ውስጥ ገብቶ እግሩን እንዲተክል ሀብት እንዲያፈራ ባለ አገር እንዲሆን ከወዲሁ እያመቻቹ ነው? የደቡብ አፍሪካ ነጮችና ጥቁሮች ከጥቂት መቶ ዓመታት በፊት በገነቡት እኩል ያልሆነ ኅብረተሰብ ሰፊ የሀብት ይዞታ ልዩነት አድጎ ዛሬ በጥቁሮች ላይ የተፈጠረው የበታችነት ነገ በእኛ ልጆች ላይ እንዲደገም እየሠራን ላለመሆናችን ምን መተማመኛ አለን::

“ስትሄድ የመታህ እንቅፋት ስትመለስም ከመታህ እንቅፋቱ አንተ ነህ” ይባላልና እስካሁን በምዕራባውያን በተመቱት ድንጋይ አሁን ደግሞ በእስያና በዐረብ አገሮች መልሶ እንዳይመቱ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ የታዳጊ አገር ሕዝቦች ሊጠነቀቁ ይገባቸዋል:: ምዕራባውያን በዝብዘው ሄደዋል ምሥራቃውያኑ ግን በዝብዘው አይሄዱም፤ ግሎባላይዜሽኑ ተጠናክሮ በድንበር መካለልና መነጣጠል ሲቀር የአገሬውን ሰው ሎሌ አሽከር አድርጎ ለብዙ ዘመናት የመግዛት ዓላማ ነው ያላቸው:: በግሎባላይዜሽን የነጻ ገበያ ወግ ግለሰብ የውጭ ባለሀብት በሌላ አገር ውስጥ ገበያውን አጥንቶ፣ ለምርቱ ጥሬ ዕቃ እንደማይጎድለው አውቆ፣ የሕዝቡን የመግዛት አቅም ገምቶ፣ መዋዕለንዋይ ማፍሰስ ሲገባው ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ውጭ ተጉዘው ከመንግሥታት ጋር ተዋውለው በፖሊሲ ጉዳይ ላይ ተደራድረው ርካሽ የሰው ጉልበት እንዳላቸው ማስታወቂያ አስነግረው መንግሥት ለመንግሥት በመግባባት ተለምነውም ስለሚመጡ ግባቸው ሩቅ ጡንቻቸው የፈረጠመም ናቸው::

ካሪቱሪ የተባለው በጋምቤላ እርሻ ጀምሮ የነበረ ሕንዳዊ የውጭ ኢንቬስተር ባለመስማማት ሥራውን ሲያቋርጥ የሕንድን ኀያልነት አታውቁም መሰለኝ ብሎ እስከመዛት ደርሶ ነበር:: ከቻይና ለፕሮጀክት ሥራ ተቀጥረው የመጡ ቻይናውያን ለውጭ ዜጎች በተከለከለ የንግድ ሥራ መሰማራታቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፤ ከአገሬው ወግና ባህል ወጪ የአህያ ቄራ ኢንዱስትሪ ከፍተዋል:: ግሎባላይዜሽን የዓለምን ኢኮኖሚ እንደሚያበለጸገው ግልጽ ነው የዓለም ኢኮኖሚ ሲያድግ ለአንዳንድ ከተሜዎችና ምሁራን በትርፍራፊ መልክ የሚደርስ ንፋስ አመጣሽ ሀብት እንደሚኖርም ግልጽ ነው:: የዐረቦች ኢኮኖሚ በማደጉ ብዙ ኢትዮጵያውያን ዐረብ አገር ሄደው አብዛኛው በሎሌነት ለመሥራት በቅተዋል፤ አውሮፓና አሜሪካ ዛሬ ላሉበት የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ በግድ ታስረው የተወሰዱ የጥንት አፍሪካውያን ርካሽ ጉልበትና የአፍሪካ ጥሬዕቃ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳበረከቱ እያወቅንም ዛሬ እኛ በግድ ሳንታሰር በሕይወታችን ቆርጠን በረሃና አሸዋ አቋርጠን እነርሱ ሳያስገድዱን እኛ አስገድደናቸው ሳንጠራ በግድ ወደ አገራቸው ተሰደን ሎሌ ሆኖ ማገልገልን ወደናል::

እኛ ዛሬ ለምዕራቡም ለምሥራቁም በነጻና በርካሽ ዋጋ የምንሰጠው የተፈጥሮ ሀብታችን እና የሕዝባችን ጉልበት እነርሱን አክብሮ እኛን የሚያደኸይ ነው:: የምንሠራው እኛ ዛሬን ለመኖር ለለት ፍጆታችን ሲሆን እነርሱ ግን ለወደፊት ለልጆቻቸው ካፒታላቸውን ለማሳደግ ነው:: ሳንወድ በግድ ከትውልድ ትውልድ የተላለፉልንን ማምረቻና አገልግሎት መስጫ ተቋሞቻችንን ጭምር እየቸበቸብን ጊዜያዊ ችግሮቻችንን እናቃልላለን::

ብዙ ዓለም ዐቀፍ ጥናቶችና መረጃዎች የበለፀጉት ሰሜኖችና የደኸዩት ደቡቦች አብረው በኖሩበት የግሎባላይዜሽን ሦስትና አራት ዐሥርት ዓመታት የሀብት ክፍተቱ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እንደሾረ አመልክተዋል:: እኛ ወልደን ተዋልደን ለእለት ጉርሱ የሚንከራተት ሕዝብ እንጨምራለን እነርሱ ልጆቻቸው ባለብዙ ሎሌ ጌታ የሚሆኑበትን ካፒታል በየአገሩ ያከማቻሉ:: ኢትዮጵያ ውስጥም ተተከለ ወይም ኬንያ የነርሱ ፋብሪካና የነርሱ ካፒታል የነርሱ ነው ወደ አገራቸው ተመለሰም እዚሁ ቀረም ወራሾቹ የነርሱ ልጆች ናቸው፤ ልጆቻቸው የካፒታላቸውም የመጪው ትውልድ ጉልበትም ወራሾች ናቸው::

 

 

October 4, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *