ለውድድር ክፍት መሆን ያለበት የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ | ሁሴን ዓሊ
ኢኮኖሚ

ለውድድር ክፍት መሆን ያለበት የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ | ሁሴን ዓሊ

በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ከጀመረ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ያስቆጠረውን ዕድሜ ያህል ግን ማደግ አልቻለም፡፡ በአገራችን ያለው የባንክ አገልግሎት እንደ ዘርፍ ገና ጨቅላ ከሚባሉት ዘርፎች መካከል  የሚመደብ ነው፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ተቋማት ቁጥር እየጨመረ ቢሄድም ይህን ነው የሚባል የተቋማት ውድድርን ሲያመጡ ግን አይስተዋልም፡፡

ለዚህ አገር የባንክ አገልግሎት አለማደግ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም መንግሥት ለዘርፉ ከለላ የሰጠበት መንገድ ለአገልግሎቱ አለማደግ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል የሚል እምነት አለኝ፡፡ መንግሥት ለአገር ውስጥ ባንኮች በሰጠው ከለላ ምክንያት ዘርፉ ወደ ሞኖፖል ሥርዓት ዘርፍ ተቀይሯል፡፡ የአገር ውስጥ ባንኮች እስካሁን ድረስ የውድድር ሜዳ ተሰጥቷቸው ከውጭ አገር ባንኮች ጋር የመፎካከር ዕድል አልገጠማቸውም፡፡ በአንድ ውስን አጥር ውስጥ ነው ሲሮጡ የሚታዩት፡፡ ባንኮች ከዚያች አጥር መውጣት አይፈልጉም፤ ሌላውም እንዲገባባቸው አያደርጉም፡፡

በተቋማቱ መካከል የሚደረገው ውድድር እዚህ ግባ የሚባል ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ  የሚሰጡትም አገልግሎት አንዱ ተቋም ከሌላው የሚለየው አይደለም፡፡  በባንኮች መሃል ይህ ነው የሚባል የወለድ መጠን ልዩነት የለም፤ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልዩነት የለም፤ በተለየ መልኩ ከተያዥ ነጻ የሆነ የብድር አገልግሎት የላቸውም፡፡ ይህ ሁኔታ የሕዝብን የተሻለ አገልግሎት የማግኘት መብት የሚጋፋ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህም በባሰ  አንዳንድ ባንኮች በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውንም በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን መንግሥት ለእነዚህ ተቋማት ድጋፍ እና ጥበቃ ያረግላቸዋል፡፡ አንድ ዘርፍ እንዲያድግ ከተፈለገ ለውድድር ክፍት መሆን አለበት፡፡ በየትኛውም የዓለም ተሞክሮ ጤናማ ውድድር የቢዝነስን ዕድገት ሲያፋጥን እንጅ ሲገድል አልታየም፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች ዛሬም በመንግሥት እቅፍ ውስጥ ሆነው ጥበቃ እየተደረገላቸው የሚቀጥሉ ከሆነ ያለ ምንም ጥርጥር የአገልግሎት ዕድገት ሳይኖራቸው ምዕተ ዓመት ያልፋል፡፡ ይህ ዘርፍ ከዘመኑ ጋር እንዲዘምን ከተፈለገ የግድ ለውድድር ክፍት መሆን መቻል አለበት፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ያለ ምንም ውድድር እና ፉክክር ትርፍ በቀላሉ የሚያገኙ መሆናቸው ተመቻችተው እንዲተኙ ሆነዋል፡፡ ሳይለፉና ሳይወዳደሩ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማጋበስ ለምደዋል፡፡ ይህ ትርፍ የሚገኘው በተጋነነ የወለድ መጠን በሚሰጡት ብድር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ግን የአገሪቱን የመዋዕለንዋይ ፍሰት እያደቀቀ መሆኑን ማንም ልብ ብሎ የተመለከተው አይመስለኝም፡፡

ከመንግሥት ውሳኔ ይልቅ የገበያ ውሳኔ የተሻለ ነው፡፡ መንግሥት የባንኮችን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል የዜጎችን ደህንነት አደጋ ውስጥ እየከተተ እስከመቼ መቀጠል እንዳሰበ አይገባኝም፡፡ የጥቂት የባንክ ባለድረሻ ባለሀብቶችን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደርግ ጥረት 100 ሚሊዮን ዜጎች ጥቅም እና መብት እየተነፈገ ነው፡፡ መንግሥት ላለፉት ዓመታት የአገር ውስጥ ባንኮችን ለመጠበቅ ሲል የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዳይሠሩ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህም ባንኮች ለተሻለ ውድድር እና አገልግሎት እንዳይነሱ አድርጓል፡፡

አብዛኛው ማኅበረሰብ  የሚማረርበት የኤ.ቲ.ኤም መቆራረጥ፣ የባንክ ቤት ወረፋ፣ የፓስ ማሽን በየቦታው አለመኖር፣ የባንኮች እርስ በርስ ግንኙነት ደካማ መሆን የሚመጣው ጠንካራ ውድድር በባንኮች መሃል ባለመኖሩ ምክንያት ነው፡፡ ጠንካራ ተቋም ከውጭ ገብቶ ውድድሩን ቢያፈጥነው ያለ ጥርጥር ባንኮች በዓመት የሚያጋብሱትን ትርፍ ወደ ሥራ ቀይረው የተሻለ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ፡፡

በእኛ አገር አንድ ሰው ቤት እና መኪና ለመግዛት ለረጅም ዓመታት መቆጠብ አለበት፡፡ በሌላው ዓለም ቤት የፈለገ ሰው ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት ደብዳቤ አስጽፎ በቀላሉ ከወር ደሞዙ የሚቆረጥ የቤት እና መኪና መግዣ ብድር ማግኘት ይችላል፡፡ ለዚህ ዓይነት አገልግሎት የእኛ አገር ዜጋ አልታደለም፡፡ በኢትዮጵያ አንድ ሰው በረጅም ጊዜ ክፍያ ቤት ላግኝ እንኳ ቢል ጠቀም ያለ ክፍያ ቀድሞ መክፈል ይኖርበታል፡፡ ከቅድመ ክፍያው ውድነት የተነሳ ብዙው ዜጋ የማይደፍረው በሩቅ የተሰቀለ አገልግሎት ነው፡፡

በውጭ ዓለም አንድ የሥራ ዕቅድ ያለው ሰው የሐሳቡን ንድፍ  ለባንክ አሳይቶ ብድር ማግኘት ይችላል፡፡ በዚህ አገር በርካታ ሥራ ፈጣሪዎች ጠቃሚ እና ቢሊዮን ብር የሚታፈስበት የሥራ ዕቅድ ኖሯቸው ለባንክ የሚያስይዙት ንብረት አጥተው በፋይናንስ እጥረት ከግባቸው ተሰናክለዋል፡፡ ከዚህ በላይ አገር እና ሕዝብን  በምን ይጎዳ?  ባንኮቻችን ለሆቴል እና ለግንባታው ዘርፈ  ካልሆነ በቀር  ብድር መስጠት አይፈልጉም፡፡

በአንደኛውም ሆነ በሁለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመንግሥት ሐሳብ ከግብርናው ዘርፍ ወደ አምራች ዘርፍ ሽግግር ማድረግ ቢሆንም በተግባር ሽግግሩ እየሆነ ያለው ከግብርናው ወደ አገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ ለዚህም አንደኛው ምክንያት የአገር ውስጥ ባንኮች ደካማ መሆን ነው፡፡

ለአምራች ዘረፍ ዕድገትም ሆነ መዘመን የፋይናንስ አቅርቦት በጣም ወሳኝ ሚና  አለው፡፡ የዚህ አገር ባንኮች ከሆቴል እና ግንባታ ውጪ ለእርሻ ማዘመኛ  እና ለአምራች ዘርፍ ማስፋፊያ የማበደር ፍላጎት የላቸውም፡፡ ዛሬ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት በረካታ ፋብሪካዎች ዕውን ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ግብርናውንም በተፈለገው መጠን ማዘመን አልተቻለም፡፡ ባንኮች ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው አገርም ሕዝብ ተጎጂ እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መንግሥት እስከ መቼ ነው የአገር ውስጥ ባንክ እሹሩሩ እያለ የሚኖረው? ተፍጨርጭሮ ለማያድግ ልጅ ጡጦ እያጠባ የሚቀጥለውስ እስከመቼ ነው? መንግሥት እንደ ዘርፍ ብቻ  ሳይሆን እንደ አገር እና ሕዝብ ጥቅም ማሰብ መጀመር አለበት፡፡

የአገር ውስጥ ባንኮች 28 ዓመት ሙሉ በመንግሥት ጥበቃ እየተደረገላቸው ቴክኖሎጂን እንኳ በአግባቡ መጠቀም እና ማዳረስ አልቻሉም፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ ሰው በኤ.ቲ.ኤም ብር ሲያወጣ የአገልግሎት ክፍያ በሳንቲም ደረጃ ይቆረጥበታል፡፡ በደብተር ሲያወጣ ግን ቆረጣ የለውም፡፡ ይህ ባንኮቻችን ለዘመናዊነት እና ለቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ምን ያህል ክፍት ልብ እንደ ሌላቸው  የሚያሳይ ነው፡፡

መንግሥት አሁን ላይ የተሻለውን ጥቅም ወደ ሚሰጠው አካል ፊቱን ማዞር እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ የአገር ውስጥ አቅም መገንባት አስፈላጊ ቢሆንም የአገር ውስጥ አቅም ግን የሚገነባው ሕዝብ እየተጎዳ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ የአገር ውስጥ ባንኮች እንዲጎዱ አልፈልግም ካለ የውጭ ባንኮችን አስገብቶ  ለአገር ውስጥ ባንኮች ድጋፍ የተለየ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል፡፡ የአገር ውስጥ ባንኮችም የውጭ ባንኮች ከገቡ እንጎዳለን የሚል ፍርሃት ካላቸው ውሕደት ይፍጠሩ፡፡ አሁን ላይ ቁም ነገሩ የባንኮች ቁጥር መብዛት ሳይሆን ጥራት ያለው አግልግሎት መስጠት ነው መሆን ያለበት፡፡

October 21, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *