ከውጭ ወራሪ የተከላከልናትን አገር ከውስጥ ጭቆና ማላቀቅ ለምን ተሳነን?
ርእሰ አንቀጽ

ከውጭ ወራሪ የተከላከልናትን አገር ከውስጥ ጭቆና ማላቀቅ ለምን ተሳነን?

የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. 84ኛው የየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ታስቦ ውሏል፡፡ 125ኛውን የዓድዋ ድል በዓልም በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል፡፡ ይህችን አገር ከውጭ ወረራ ጠብቆ ለማቆት የተከፈለው መስዋዕትነት እጅግ የሚያኮራ ነው፡፡ ሆኖም  ኢትዮጵያዊያን አገራችንን ከውጭ ወራሪ ጠብቆ በማቆየት ረገድ ደማቅ ታሪክ ያለን ብንሆንም ከውጭ ወራሪ የተከላከልናትን አገር ከውስጥ ጭቆና ማላቀቅ እና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማት ማረጋገጥ አለመቻላችን ግን ትልቅ እንቆቅልሽ ነው፡፡ እንደ ሕዝብ ይህ ለምን ሊሆን እንደቻለ የማያቋርጥ ውይይትና ክርክር ማደረግ ይገባናል፡፡ ራሷን ከወራሪ በመከላከልና ነጸነቷን ጠብቃ በማቆየት ረገድ ከማርከስ ጋርቬይ እስከ ንኩሩማ፣ ከማንዴላ እስከ ጃዋሕራል ኔሕሩ ምሳሌ ያደረጓት ኢትዮጵያ ለምን በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም መስክ በዚህ ደረጃ ወደኋላ ቀረች?

ለዚህ የበቃንበት አንዱ ምክንያት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል “ሁሉንም ወይም ምንም” በሚል መንፈስ የተቃኘ ለዴሞክራሲ ግንባታ እጅግ አደገኛ የሆነ ባህል መሆኑ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ወይም ሁሉንም ነገር ማጣት የተለመደ የፖለቲካ ታሪካችን አካል ነው፡፡ አሁንም ከዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ፈቀቅ አላልንም፡፡

በእርግጥ ይህ ባህል የእኛ ብቻ ባህል አልነበረም፡፡ ዛሬ ዴሞክራሲያዊ ናቸው የምንላቸው ብዙዎቹ የዓለማችን አገሮች እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብና አሠራር ነበራቸውና፡፡ አገረ-መንግሥቱን የተቆጣጠረው ቡድን ከሚያስበው ውጪ ያሰበ አካል፣ እሱ ካስቀመጠው ውጪ የተለየ ነገር ያደረገ አካል ከባድ ቅጣት የሚቀበልበት ባህል በብዙ አገሮች የነበረ ነው፡፡ አውሮፓ ውስጥ ምን ያህል አፈና እንደነበር፣ የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱ ሰዎች እንዴት ያለ ቅጣት ይደርስባቸው እንደነበር፣ የነበረውን ጥብቅ ሳንሱር ወዘተ… ታሪክ የመዘገበው ሐቅ ነው፡፡ ሁሉንም መጠቅለል የተለመደ ነገር ነበር፡፡ በጊዜ ሒደት በብዙ ትግልና መስዋዕትነት ነው ሁሉንም የመጠቅለል ባህልና አሠራር እንዲቀር የተደረገው፡፡ ከብዙ ትግልና መስዋዕትነት በኋላ ነው ሥልጣን ልጓም የተበጀለት፡፡ ይህ አገረ-መንግሥቱን እና አገረ መንግሥቱን የሚመራውን አካል (መንግሥትን) የማዘመን (Civilizing the State) ሒደት ምዕራባዊያን ለዓለም ያበረከቱት ትልቅ አበርክቶ ነው፡፡

የአገራችን ፖለቲካ ግን አሁንም ኋላቀር ነው፡፡ አልተሻሻለም፣ አልዘመነም፡፡ የፖለቲካ ተፎካካሪዎችን በጠላትነት መፈረጅ፣ በጠላትነት ከመፈረጅም አልፎ ስትራቴጂ ነድፎ ተፎካካሪዎች እንዲጠፉ መሥራት የተለመደ ያልተሻገርነው የፖለቲካችን ነቀርሳ ነው፡፡ ሌሎች አገሮች የፖለቲካ ፉክክር የሚደረግበትን ሜዳ እና የጨዋታውን ሕግ ሥርዓት ባለው መልኩ ሲያዘምኑት እኛ አሁንም በጨዋታው ሕግም በመጫወቻ ሜዳው ሁኔታም እንደነበርን አለን፤ ፈቀቅ አላልንም፡፡

ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ መውሰድ ከጊዜ በኋላ ሁሉንም ነገር ማጣትን እንደሚያስከትል ከቀዳማዊ ኀይለሥላሴ መንግሥት አልተማርንም፡፡ ቀዳሚ ኀይለ ሥላሴ ለተቀናቃኞቻቸው ቦታ ቢተው ወይም ከጊዜ ጋር አብረው ቢሄዱ ኖሮ ለበርካታ ዓመታት ደክመው የገነቡት ሥርዓትም፣ የእሳቸው ክብርና ስምም፣ እሳቸው፣ ልጆቻቸና ያገለገሏቸው ባለሥልጣኖቻቸውም በዚያ ደረጃ መከራ ባላዩ ነበር፡፡ ሁሉንም መጠቅለል ሁሉንም ማጣትን አስከተለ፡፡

ዐፄ ኀይለ ሥላሴን በፈላጭ ቆራጭነት ፈርጆ ብዙ ሲዘምር የከረመው የደርግ እጣ-ፈንታም ተመሳሳይ ነው፡፡ ደርጋዊያኑም ሁሉንም ተፎካካሪያቸውን በኀይል ፀጥ አሰኝተው አገሪቱን በብቸኝነት ለመግዛት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ ለውይይት ቦታ አልነበረም፡፡ ለልዩነትና ለሰጥቶ መቀበል ቦታ አልነበረም፡፡ ሁሉንም እኛ ብቻ እንያዘው፤ እንጠቅልለው ተባለ፡፡ ሆኖም ይህ ስግብግብ አስተሳሰብ ሄዶ ሆዶ ሁሉንም ማጣትን አስከተለ፡፡ አይነኬ ይመስሉ የነበሩት የደርግ መሪዎች እየተለቀሙ ወህኒ ቤት ወረዱ፣ የሥርዓቱ ቁንጮና አንዳንድ ዕድል የገጠማቸው ተከታዮቻቸው ደግሞ አገር ጥለው ተሰደዱ፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለመዘመኑ ምክንያት ኢሕአዴግም በዚያው በተለመደው የሁሉንም ልጠቅልለው አባዜ ተለክፎ ተፎካካሪዎቹን ሁሉ በሽብርተኝነት እየፈረጀ ሲያስር፣ በንጹሐን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈፅም፣ ለሥልጣኔ አስጊ ናቸው ያላቸውን ሁሉ ሲያሳድድ ከረመ፡፡ ሁሉንም እኛ ብቻ እንብላው አሉ፡፡ ሆኖም እንዲያ ልክ በሌለው እብሪት ተወጥረው በአገርና በሕዝብ ላይ ተነግሮ የማያልቅ በደል ያደረሱ ሰዎች ዛሬ የት እንዳሉ እያየን ነው፡፡ የውይይት ባህል ስር እንዲሰድ ሁኔታዎችን ቢያመቻቹ ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲዘምን የበኩላችን ገንቢ ሚና ተጫውተው ቢሆን ኖሮ ዛሬ በዚህ ደረጃ የገነቡት ሁሉ የእምቧይ ካብ ባልሆነም ነበር፡፡

ኢትዮጵያዊያን አሁንም ከዚህ አደገኛ በሽታ አልተፈወስንም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የያዘውም በተቃራኒ ጎራ የተሰለፈውም ሁሉም የዚህ የመጠቅለል በሽታ ሰለባ ነው፡፡ የለውጡ ብቸኛ ባለቤት እኔ ነኝ እየተባለ የሚዘመረው፣ እከሌ የተባለውን ቡድን ያደራጀነው እኛ ነን፤ ተነስ ስንለው የሚነሳ ቁጭ በል ስንለው የሚቀመጥ በእኛ ትዕዛዝ ነው እየተባለ የሚነገረው ሁሉ የዚህ በሽታ ምልክት ነው፡፡ ፈውስ ያስፈልገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዚህ የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ካልተፈወሰ እና ካልዘመነ ማናችንም ነጻ እንወጣም፡፡ ለልዩነት ቦታ መስጠት፣ ኢትዮጵያ የሁሉንም ልጆቿን አስተዋጽዖ እንደምትፈልግ ከምር መቀበል፣ ይብዛም ይነስም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ አስተዋጽዖ ሊያደርግ እንደሚችል ማመን ያስፈልጋል፡፡ እብሪትና መታበይ የውድቀት መሠረት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ በብዙ ብሔር፣ ሃይማኖትና የፖለቲካ አመለካከት ባሸበረቀ አገር ውስጥ አንድ ድርጅት ወይም አንድ ቡድን ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለበት እና የአገሪቱን ችግሮች ሊፈታ የሚችልበት ምንም ዓይነት ዕድል የለም፡፡ ይህን መሠረታዊ ሐቅ መቀበል ያስፈልጋል፡፡

የውጭ ወረራን በሚያኮራ ሁኔታ ተከላክለን አገራችንን የምናስከብረውን ያህል፣ ውስጣዊ ልዩነታችንን በሰለጠነ መልኩ ለመፍታት የሚያስችል ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ይገባናል፡፡

 

February 23, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *