አሁንም ሥርዓት አልባነት እየነገሠ አገር እየተበደለ ነው!
ርእሰ አንቀጽ

አሁንም ሥርዓት አልባነት እየነገሠ አገር እየተበደለ ነው!

በኢትዮጵያ ከዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ከዚያም አልፎ እስከዛሬ ድረስ የሕዝባችን መሪ ጥያቄ የሥርዓት (institution) ጥያቄ ነው:: ዳግማዊ ቴዎድሮስ የአገራቸው ሕዝብ ሥርዓት አልገባ ብሎ ቢያስቸግራቸው፡- “ሥርዓት ግባ ብለው እምቢ አለኝ” ሲሉ በጽኑ አማርረዋል፤ ኮንነዋል:: ዘመናዊ ሥርዓትን ለመዘርጋት ያደረጉት ጥረት ከሥርዓት አልቦነት
የሚጠቀሙ ኀይሎች ዘንድ ፈተና ገጥሞት ጥረታቸው ሳይሰምር ባተሌ ሆነው አልፈዋል:: በዐፄ ቴዎድሮስ ጥረት በእጅጉ የተማረኩት ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝም ስለ ሥርዓት አስፈላጊነት አበክረው መክረዋል::

የሥርዓታት መኖርና መጠናከር ለአንዲት አገር ሁለንተናዊ ልማትና ግስጋሴ ምን ያህል ዓይነተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው የኢኮኖሚከስ የኖቤል ሎሬቱን ፕሮፌሰር ዳግላስ ኖርዝን ጨምሮ በርካታ የዘመናችን ምሁራን በስፋት ጽፈዋል፤ መክረዋል:: ቅቡልነት ያላቸው፣ ጠንካራ/ዘመናዊ፣ ዝርዝር እና ተፈጻሚነት ያላቸው ሕጎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው:: በኅብረተሰቡ ውስጥ የእርስ በርስ መተማመን እንዲኖር፤ ማንኛውም ሰው በነጻነት ተንቀሳቅሶ መሥራት፣ ንብረት ማፍራት እና መኖር እንዲችል፤ ተግባሩን በንቃት፣ በብቃት እና በኀላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ የሚወጣ የፍትሕ ሥርዓት ያስፈልጋል:: ተገልጋዩን ያለ አድልዎ እና ያለ ምንም ዓይነት የእጅ መንሻ በፍትሐዊነት መንፈስ የሚያስተናግድ ሲቪል ሰርቪስ ያስፈልጋል:: ተገማች፣ ተዓማኒነት ያለው እና ከየትኛውም ዓይነት አድልዎ የጸዳ ዘመናዊ የመንግሥት ተቋም እንዲኖር ያስፈልጋል:: ጥራት ያላቸው ሕጎች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች ሲኖሩ፤ ይልቁንም ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ያለ አድልዎ ሲፈፀሙ በኅብረተሰቡ መሀከል ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰቡ እና በመንግሥት መሀከል ጠንካራ መተማመን ይፈጠራል:: ጠንካራ መተማመን ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ ደግሞ የፈጠራ ሥራ (innovation) ይጎለምሳል፤ ኢንቨስትመንት ይስፋፋል፤ ሁለንተናዊ ልማት ዕውን ይሆናል::

ከትናንት እስከ ዛሬ የዚህች አገር መሪ ጥያቄ የሥርዓት ጥያቄ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከዓይነተኛው አገራዊ አጀንዳ እያፈነገጥን እና በጭፍጫፊ ጉዳዮች ላይ እየተጠመድን፤ በዚህም አገርና ሕዝብ በእጅጉ እየተበደሉ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከድጡ ወደ ምጡ እየሆነ መጥቷል:: ከሁለት ዓመት በፊት በመጣው አገራዊ ለውጥ ማግስት “አንዱ ትውልድ በሠራው ላይ ሌለው እየጨመረበት፣ መሻሻል ያለበት በጥበብና በዕውቀት እየተስተካከለና እየዘመነ ይሄዳል እንጂ ሁልጊዜም ‹ሀ› ብለን አንጀምርም” ተብሎ ቢነገረንም ከሥርዓት ግንባታ አንጻር ያለንበት ሁኔታ የቁልቁለት ጉዞ ነው ለማለት ይቻላል::

በአገራችን ግለሰቦች ከሕግ በላይ ብቻ ሳይሆን ሕግ እየሆኑ፣ ጭፍሮቻቸውም ገዥዎች የሚናገሩትን ከአፋቸው እየለቀሙ እንደበቀቀን እያስተጋቡ፣ በአገሪቱ ሥርዓት አልባነት እየነገሠ እና ሕዝብ እየተበደለ በኪነ ጥበቡ እዚህ ደርሰናል:: ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴን ሲያመልክ የነበረ ሕዝብ ተመልሶ ንጉሠ ነገሥቱን የሚረግም እና “ቆራጡን አብዮታዊ መሪ” በጭፍራነት የሚከተል ሆነ:: ኮሎኔል መንግሥቱን ሕግ አድርጎ የኖረ አገርና ሕዝብ ተመልሶ “አምባገነኑና ሰው በላው መንግሥቱ ኀይለ ማርያም አገር ጥሎ ፈረጠጠ” እያለ ትናንትና በጭፍራነት እና በተላላኪነት አድሮለት የነበረውን ግለሰብ ክዶ የተጋዳላዮች ተከታይ፣ ኩሽክ ለባሽና ሸበጥ ጫማ አድናቂ (አርቲስቶች ሳይቀሩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምን ሲያደርጉ እንደነበር ልብ ይሏል) ሆነ:: ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን “ታላቁ መሪ” የሚል ማዕረግ ያጎናጸፋቸው ጠበቃና ታዋቂ አርቲስት ዛሬ ተመልሶ “ከዘረኛ ሥርዓት ነጻ ወጣን” እያለ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግንባር ቀደም አድናቂ ሆነ፤ ሌሎችም ሚሊዮኖች በጭፍራነት ተሰለፉ:: “በሕግ አምላክ!” የሚል ትልቅ ዕሴት የነበረው ሕዝብ ከሕግ ይልቅ ለግለሰቦች ጭፍራ መሆንን ባህል አደረገ:: ሕግና ሥርዓት ሳይሆን ጭፍራነት ግብር ሆነ!

እንዲህ ዓይነቱ ግለሰቦችን ሕግ የማድረግ ክፉ ልማድ የሥርዓት ግንባታ ጸር ነው:: ለዘላቂ ሥርዓት ግንባታ ሳይሆን ለግለሰብ እና ለአገዛዝ የማደግደግ ባህል መልክ ካልያዘ፤ የአገዛዝ መሣሪያ ሆኖ እና በየመስኩ በትናንሽ ንጉሥነት ተሰይሞ የአገርን አንጡራ ሀብት የመዝረፍ ባህል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካልተወገደ ኢትዮጵያ ከገባችበት መከራ ልትፈውስ አትችልም:: ኢትዮጵያዊያን ራሳችንን ኂስ ማድረግ ይገባናል:: ያለ ጥርጥር በሥርዓት ግንባታ ረገድ ወድቀናል:: አንድን አገዛዝ በሌላ ከመተካት ውጪ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ እና በጊዜ ሒደት እየዳበሩ የሚሄዱ ዘመናዊ ሥርዓታትን (institutions) መገንባት አልቻልንም:: በዚህ ምክንያት ዝመና ሲያልፍም አልነካንም::

በአገራችን ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ሕዝብ በነጻና ፍትሐዊ ምርጫ በመረጣቸው ተወካዮቹ አማካይነት ወይም በቀጥታ ተሳታፊነት መክሮ ዘክሮ የሚያወጣቸው መተዳደሪያዎች ሳይሆኑ፣ በሥልጣን ላይ ያሉ አካላትን ለመጥቀም የሚዘጋጁና ጥቅም ላይ የሚውሉ የመግዣ መሣሪያዎች ናቸው:: ሁሉም አገዛዞች ስለ ሕገ መንግሥት እና ስለ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አስፈላጊነት እስኪበቃን ሰብከውናል:: ሆኖም ሕግን በደንገጡርነት የሚገለገሉባት እነሱ ራሳቸው አገዛዞቹ እንደሆኑ ደግሞ ደጋግመናል አይተናል፤ ታዝበናል:: ስለ ሕግ የበላይነት ይነገራል፤ ያየነውና የምናየው ግን በሕግ መግዛትን ነው:: ስለ ፍትሕ ይነገራል፤ ያየነውና የሚታየው ግን ኢፍትሐዊነት ነው::

በአገራችን ሥርዓታት ባለመገንባታቸው ምክንያት በየዘመኑ አዳዲስ ተረኛ በላተኞች ይቀያየራሉ እንጅ የሕዝቡ ኑሮ ጨርሶ አልተሻሻለም፤ እንዲያውም ከድጡ ወደማጡ እየሆነ ነው:: የጠገበ በላተኛ ሲሄድ የራበው እየመጣ አገሪቱ ተግጣ ተግጣ አጥንቷ ቀርቷል:: በየደረጃው ባሉ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ትንንሽ ፈላጭ ቆራጭ በላተኞች ተቀምጠው ትናንትና በአብዮቱና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዛሬ ደግሞ በመደመር ስም እየማሉ ሕዝብ እየበደሉ ነው:: መንግሥታዊ ተቋማት ሕዝብ የሚገለገልባቸው አልሆኑም:: አገልግሎት በገንዘብ የሚሸጥ ሸቀጥ ሆኗል:: ሕዝብ በእጅጉ እየተማረረ ነው:: ዛሬም እንደትናንቱ ተጠያቂነት ባለመኖሩ ሕዝብን ያማረረ አመራር ጭፍራነቱን እስካስመሰከረ ድረስ በሕግ ከመጠየቅ ይልቅ ከቦታ ቦታ እየተቀያየረ የሚበላበት ተቋም እንደሚመቻችለት እየታየ ነው:: ጭፍራነት አሁንም ያስሾማል፤ ያስሸልማል:: ኂስ ማቅረብና መቃወም አሁንም ያሳስራል፤ ያንገላታል፤ ከሥራ ገበታ ያባርራል::

ለኢትዮጵያም ለኢትዮጵያዊያንም ዘላቂ ጥቅም ሲባል እንዲህ ዓይነቱ የጥፋት አካሄድ መቆም ይገባዋል:: በሥልጣን ላይ ያሉትም ነገ ሥልጣን ሲለቁ እንዳይሳደዱና ተከብረው እንዲኖሩ፣ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚታገሉትም ከበቀል ስሜት የወጣ የሰለጠነ መንገድ እንዲመርጡ፣ ሕዝቡም በሰላም ወጥቶ ገብቶ ሠርቶ እንዲበላ እና ኑሮውን በነጻነት እንዲገፋ ጠንካራና ዘመናዊ ሥርዓታትን መገንባት ይገባናል:: ሥርዓታት ሲገነቡ በኅብረተሰቡ ውስጥ፣ በመንግሥት እና በኅብረተሰቡ መሀከል እንዲሁም በመንግሥትና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መሀከል ጤናም ግንኙነት ይኖራል፤ መተማመን ይሰፍናል:: ሕግ የመተማመን መሠረት ነው:: መተማመን ደግሞ የሁለንተናዊ ልማት እናት ናት::

 

October 2, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *