አንጋፋው የፖለቲካ ሰው አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክተው በቅርቡ ያሳተሙት መጽሐፍ ርእስ “ቅን ፍላጎት እስካለ መንገድ አለ” ይላል፡፡ እውነትም ቅን ፍላጎት እስካለ ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍቻ የሚሆን መንገድ አይጠፋም፡፡ ከትናንት እስከዛሬ የዚህች አገር ችግር ቡድኖችና ግለሰቦች በየትኛውም መንገድ ሥልጣን እየያዙ ሌሎችን የሚያገልሉበት ሁኔታ ነው፡፡ ጠቅልሉ መውሰድ፣ ለሌሎች ቦታ አለመተው፣ ልዩነትን እንደ ፀጋ አለመቀበል በሽታችን ነው፡፡ ስለ ዴሞክራሲ ይነገራል፤ ግን ዴሞክራሲን የሚቀብር ሥራ ይሠራል፡፡ ስለ ፍትሕ አስፈላጊነት ይዘመራል፤ ግን ፍትሕን ገደል የሚከትት ተግባር ይፈጸማል፡፡ ልዩነትን ስለማክበር ይነገራል፤ ግን ልዩነትን የሚደፈጥጥ ሥራ ይሠራል፡፡ ቅን ፍላጎት ቢኖር በቀላሉ የሚፈቱት የኢትዮጵያ ችግሮች በዘመናት መሀከል እየተንከባለሉ እና ሌላ ችግር እየወለዱ እዚህ ደርሰናል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የፖለቲካ ልማት በሌለባቸው አገሮች ውስጥ የገዥ ፓርቲዎች እና የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ዕውን እንዲሆን የሁሉም ዜጋና የፖለቲካ ኀይሎች ተሳትፎ አስፈላጊ ቢሆንም የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ቁርጠኝነት ግን ከምንም በላይ ወሳኝ ነው፡፡ በአህጉራችን የዴሞክራሲ ሽግግር አብነት ተደርገው የሚጠቀሱት እነ ደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና፣ ሞሪሸስ፣ ጋና፣ ናይጀሪያ ወዘተ… ተሞክሮ በግልጽ እንደሚያሳየን ገዥ ፓርቲዎች/መሪዎች ለዴሞክራሲ ሽግግር የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ በኢትዮጵያም ዴሞክራሲ ዕውን እንዲሆን ካስፈለገ ትልቁን ድርሻ መውሰድ ያለበት ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የዴሞክራሲ ሽግግር ተስፋው እንዲጨነግፍም የገዥው ፓርቲ አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡
በብዙ አገሮች፣ በተለይም መሠረታዊ የፖለቲካ ለውጥ በተካሄባቸው አገሮች ውስጥ ከዴሞክራሲ ይልቅ ሕግና ሥርዓት ይስፈን የሚለው የኅብረተሰብ ጥያቄ አንድ የአፈና አገዛዝ በሌላ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ እንዲተካ ምክንያት ይሆናል፡፡ ቅድሚያ ለኅብረተሰብ ሰላምና መረጋጋት፣ ቅድሚያ ለአገር ህልውና ይባልና ዴሞክራሲ ሁለተኛ ቦታ እንድትይዝ ይደረጋል፡፡ አገዛዝ ደግሞ ሕግና ሥርዓት በማስከበር ስም አንድ ጊዜ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብት መደፍጠጥ ከጀመረ አይመለስም፡፡ ትልቁ አደጋ ይህ ነው፡፡
በኢትዮጵያችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያስፈልጋል፡፡ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱት ግጭቶች፣ የዜጎች ሞትና መፈናቀል ሊቆም ይገባል፡፡ የአገራችን ህልውናም ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይገባም፡፡ ሆኖም ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ ነጻነቶችና መብቶች ሰለባ ይሁኑ ማለት ትልቅ ውድቀት ነው፤ እጅግ አደገኛ ውድቀት፡፡
ለኢትዮጵያ ህልውና ትልቁ መድኀኗ ፍትሕና እኩልነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሚበዙት የአፍሪካ አገዛዞች ሕግና ሥርዓትን በማስፈን እና የአገር ህልውናን በማስጠበቅ ስም የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አፍነው ነው የሚኖሩት፡፡ ሆኖም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሰላምና መረጋጋትም አይሰፍንም፤ የአገር ህልውናም አይጠበቅም፤ ዴሞክራሲም አይታሰብም፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ አምባገነናዊ አገዛዝን ልትሸከም የምትችልበት ትከሻ የላትም፡፡ ብዙ ቋንቋና ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በጣም በርካታና የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ያሉባት ኢትዮጵያ በአንድ የአፈና አገዛዝ ሥር ልትቀጥል አይቻላትም፡፡ ይህ መንገድ ተሞክሮ የከሸፈ የጥፋት መንገድ ነው፡፡ የአፈና አገዛዝን ኮትኩተን ስናበቃ ሁላችንም የጭቆና ሰለባ መሆን፣ ጭቆናውን ለማስወገድ ስንታገል መሞት፣ እንደገና አንዱን የአፈና አገዛዝ ጥለን ሌላ ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት ማንገሥ የኖርንበትና እስኪበቃን ያየነው የጥፋት መንገድ ነው፡፡ ከዚህ አዙሪት የሚያወጣን ዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ለአገራችን ከዴሞክራሲ ውጪ ምርጫ የለም፡፡
ስለሆነም ኢትዮጵያ አንድነቷን አስከብራ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስዳትን ሽግግር (democratization) በሙሉ ልብ መጀመር አለባት፤ አሁንኑ! ለዚህ ደግሞ የኅብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ሕዝባችን የራሱን ሰላም ራሱ የሚጠብቅና የዴሞክራሲ ተስፋውን በመረጋጋት ስም ለአገዛዝ የማያስረክብ መሆን ይገባዋል፡፡
መንግሥት በአገራችን ሰላምና መረጋጋትን እንዲያሰፍን መጠየቅና መርዳት፣ እዚያው በዚያው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግሥታቸው ዴሞክራሲን ለመገንባት የገቡትን ቃላቸውን እንዲያከብሩ መጠየቅና ከሥር ከሥር እየተከታተሉ መወትወት፤ ከኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ መግባት እናተርፋለን ብለው በየቦታው እሳት የሚለኩሱ የጥፋት ኀይሎችንም አምርሮ መታገል ይገባል፡፡ ስለ አገራችን ሰላምና ደኅንነት እየሠራን እዚያው በዚያው ሌሎች ለዲሞክራሲ እንቅፋት የሆኑ ኀይሎች ከአፍራሽ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ መታገል ይኖርብናል፡፡ የንቁ ዜጋ መሠረታዊ መርኹ ይህ ነው፡፡
ዴሞክራሲን በሰላምና መረጋጋት ስም መስዋዕት ማድረግ ውድ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ሕግና ሥርዓት ባልተከበረበት ሁኔታም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊገነባ አይችልም፡፡ ሁለቱም ጎን ለጎን አብረው መሄድ ይገባቸዋል፤ ይቻላልም፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር ግን፣ ዴሞክራሲ ዴሞክራቶችን የሚፈልግ መሆኑን ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያጎናጽፈውን መብት እንዲሁም የሚያሸክመውን ኀላፊነትና ግዴታ ጠንቅቆ ማወቅ ይገባል፡፡ የጨዋታው ሕግ በደንብ እንዲሰርጸን ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ እኛው ራሳችን ዴሞክራቶችና የዴሞክራሲ ጠበቃዎች መሆን ይገባናል፡፡
ከሥርዓት ግንባታ ይልቅ በግለሰብ ተክለ ሰብዕና ግንባታ ላይ ማተኮር፣ ለገለልተኛ ተቋማት ግንባታ ከመታገል ይለቅ በግለሰብ ዙሪያ መኮልኮልና ማደግደግ የዴሞክራሲ ሾተላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወደፊት ልትራምድ የምትችለው ሁሉንም ሕዝቦቿንና ዜጎቿን በእኩልነት እና በፍትሐዊነት ሊያስተናግድ የሚችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ይሁንታ ላይ የቆመ የአገዛዝ ሥርዓት አጥፊ ነው፡፡ በአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ላይ የተፈፀመ ኢፍትሐዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ቆጥረን አላግባብ ከሚገፉት ጎን መቆም፣ ኢፍትሐዊነትን መታገል፣ ለዴሞክራሲ ዘብ መቆም ይገባናል፡፡
የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችም በታሪክ ውስጥ ያገኙትን ዕድል ሊያባክኑት አይገባም፡፡ በዚህች አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን እንዲሆን፤ እነሱም ተከብረው እንዲኖሩ ማድረግ እየቻለ ወደነበርንበት የጨለማ ዓለም ሊወስዱን አይገባም፤ ለእነሱም አይበጃቸውም፡፡ አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ እንዳሉት ቅን ፍላጎት እስካለ መንገድ አለና ቅን ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡
Leave a Reply