«ዳኛው ማነው?» – ክረምት አውጪው የብዕር ድግስ | ግርማ ይ. ጌታኹን
መጻሕፍት

«ዳኛው ማነው?» – ክረምት አውጪው የብዕር ድግስ | ግርማ ይ. ጌታኹን

«ዳኛው ማነው?» – ክረምት አውጪው የብዕር ድግስ

ቋንቋተኰር የመጽሐፍ ዳሰሳ

ግርማ . ጌታኹን

መጽሐፉ፤ «ዳኛው ማነው?»

ደራሲ፤ ታደለች ኃ/ሚካኤል

አርታዒ፤ ማንይንገረው ሸንቍጥ

አታሚ፤ ኤክሊፕስ ማተሚያ ቤት

የታተመው፤ 2012 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ደምላላ ያስተውሎ ነጥቦች

በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለንባብ የበቃውን «ዳኛው ማነው?» በከፍተኛ ጕጕት እና ተመስጦ አነበብኩ። መጽሐፉ እንደ መልካም ድግስ የሰጠኝን ደስታ እና ርካታ፣ እንደ ፎቶ ማኅደር (album) የቀሰቀሰብኝን ትውስታ፣ ኀዘን እና ቍጭት በሚገባ መግለጽ ያዳግተኛል። ደራሲዋ ታደለች ኀይለ-ሚካኤል በቀላል እና ግልጽ ቋንቋ፣ በምሁራዊ ትሕትና እና ቍጥብነት ላቀረቡልን ማለፊያ-ዐለፍ (extraordinary) መጽሐፍ ወሰንየለሽ ምስጋናዬን ላቅርብላቸው ወደድኩ። እንዲያ ለማድረግ ደግሞ ለኔ-ብጤው ሰው ሒሳዊ ተማግቦ ከማቅረብ፣ በስፋት እንዲነበብ እና መወያያ ቁስ እንዲኾን ከመርዳት የተሻለ መላ ያለ አይመስለኝም። ደራሲዋም በገፍ የደገሱለትን የበላ፣ በጋን የሰየሙለትን የጠጣ የኔ-ብጤ፣ “ዝ ጠላ ከመወይን ጣዕሙ፤ እስኩ ድግሙ ድግሙ” እያለ በወረብ የማወደስ ወግ ባይኖረው እንኳ “የታሪክ ቅርስ ያወረሰን እጅዎ ይባረክ!” ማለት አይገድደውም። እርሳቸውም ወሸን እንደሚሉት እገምታለኹ።

«ዳኛው ማነው?» በዋናነት የደራሲዋ እና የባልቤታቸው ብርሃነ-መስቀል ረዳ የሕይወት ታሪክ ነው። (ከዚህ በኋላ ታደለች እና ብርሃነ እያልኩ አነሣሣቸዋለኹ፤ ለተዋሥኦ ቅልጥፍና ስል)። የኹለቱም ሕይወት፣ በተለይም የብርሃነ ከተማሪዎች ትግል እና ከየካቲቱ አብዮት ታሪክ ጋር እጅግ የተሳሰረ በመኾኑ መጽሐፉ የአብዮቱ ታሪክ አንድ ተጋማጅ (strand) ነው ማለት ይቻላል። በመሪ ተዋንያኑ ኑረት፣ ደግሞም በተፌ ተሳትፏቸው ገለጻ የአብዮቱ ታሪክ ሲከሠት እናያለንና። መጽሐፉ ለመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዘመናዊ እና ሀገር-ዐቀፍ የለውጥ ንቅናቄ ታሪክ ከፍተኛ ተዋፅኦ ያደርጋል። በመካያውም ዕውቅ ታጋይ ስለነበሩ ሌሎች ጥቂት ሰዎች – ተስፋዬ ደበሳይ፣ አክሊሉ ኅሩይ፣ ዘርዑ ክሕሸን – ጐላ ያሉ ምስሎች በማቅረብ አንባቢ የነርሱን ሚና በቅርበት እና በጥልቀት የሚመለከትበት መስኮት ይሰጣል።

የመጽሐፉ አንድ ትልቅ ርባና የግል ሕይወት ታሪክ ከመኾኑ ይመነጫል። ስለ ኹለቱ የመጽሐፉ ገድለኞች ልጅነት፣ አስተዳደግ፣ የንሕሰት ዘመኖቻቸውን (formative years) ለመቅረጽ ተጽእኖ ስለነበራቸው ከባቢ ነገሮች እና ገጠመኞች ይበልጥ ስናውቅ ሰለነርሱ የነበረን ግንዛቤ በአእምሯችን ጥልቀት እና ግዝፈት ሲነሣ ይሰባናል። የብርሃነ እና ታደለች ፖለቲካዊ ሰብእናዎች በሥጋ እና ደም፣ በሐሳብ እና ተግባር፣ በፍቅር እና ሥነ- ምግባር ደግሞም በማኅበረሰባዊ ተሳትፎ ሙሉ ትስብእት ተቀዳጅተው እናያለን። ብርሃነን ያለፍርድ የገደሉት የደርግ ባለሥልጣኖችም ኾኑ ሊገድሉት ያልተሳኩ ሙከራዎች ያደረጉት የራሱ ድርጅት የቀድሞ ጓዶቹ ያወረዱበት ክስ፣ ውግዘት እና ስም ማጕደፍ ኹሉ ሕይወቱን ለመቅጠፍ ለነበራቸው ጽኑ ፍላጎት ማጠየቂያ ይመስላሉ። በተለይ የደርጉ ኵነና “የገደልነው ርኵስ ምናምንቴ እንጂ ክቡር ሰው አይደለም” ለማለት እንዲመች የቀረቡ ነበሩ። ታደለችንም ከሞት ያተረፈው ርግዝናቸው ነበር። ደም-ጠማሹ የደርግ አገዛዝ የፍጅት ዘመኑ ካበቃ በኋላ እንኳ ሊገድላቸው በተደጋጋሚ ሞክሯል፤ ሐራራውን ሊወጣባቸው።

በሕይወት ያሉ በርካታ የቀድሞ የ-ኢሕአፓ አባሎች የትግል ዘመን ትውስቶቻቸውን እና የሕይወት ታሪኮቻቸውን እየዘገቡልን መኾኑ ደስ ያሰኛል። በደረቅ ትንተና እና ትርክት እንዲሁም በዐፅማዊ ቁመና ለቀረቡልን ሥራዎች ማጎልበቻ እና ማሟያ፣ ማረሚያ እና መየከሻ፣ መወገጫ እና መቃወሚያ እያቀረቡልን ነው። በራስ ተመክሮ እና ትውስት ላይ ከተመረኰዙ ኢ-ልቦለዳዊ ሥራዎች ውስጥ በቅብጥርጥር እና ሴራ-ጠቀስ ኀልዮ (conspiracy theory) የተሞሉ የሚመስሉትን ችላ ብል፣ የሕይወት ተፈራ፣ የካሕሳይ አብርሃ፣ የመላኩ ተገኝ እና የዐቢዩ ብርሌ (የጌራ) ጐልተው ይታዩኛል። በቅርብ የወጡ እና ያላነበብኳቸው ሌሎች እንዳሉም አምናለኹ። ሌሎችም የነርሱን አብነት ተከትለው ታሪካቸውን ጀባ እንደሚሉን ተስፋ አደርጋለኹ።

ሕይወት ተፈራ በ Tower in the Sky ስለራሳቸው እና ስለ ፍቅረኛቸው ጌታቸው ማሩ፣ እግረመንገዱንም ስለ ፓርቲው የወጣት ክንፍ ድርጅት (ኢሕአወሊ)፣ እጅግ አማላይ እና መዜንው ታሪክ አቅርበውልን ነበር። እነሆ የታደለች መጽሐፍ ደግሞ በብዙ ረገድ የዚያን ትርክት ሌላ ገጽ በማሳየት የተሟላ ሥዕል እና አረዳድ እንዲኖረን ያደርጋል። ታደለች እና ሕይወት “አንጀኞች” የተባሉት የድርጅቱ መሥራቾች እና መሪዎች አስተሳሰብ እና አቋም ምን እንደነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ከራሳቸው ከተወጋዦች አንደበት የሰሙትን እንድንሰማ አስችለውናል። እስከ ቅርብ ጊዜ የሰማነው/ያነበብነው ገዳዮቻቸው እና አሳዳጆቻቸው ስለነርሱ ያሉትን ብቻ ነበር። ብርሃነ እና ጌታቸው በቃልም ኾነ በጽሑፍ ያቀረቧቸውን መከራከሪያዎች የፓርቲው አመራር ለአባላት ያለምንም ለውጥ አቅርበው ሳያወያዩ ነበር ርምጃ የወሰዱባቸው። ታደለች እና ሕይወት ከሞት ተረፉና ይኸው የኹለቱን በአስተሳሰብም ኾነ በብስለት፣ በምድንም (discipline) ኾነ በቍርጠኛነት፣ በድርጅት ምሥረታም ኾነ በንቁ ተሳትፎ ከጓዶቻቸው ቢልቅ እንጂ በምንም የማያንስ ሚና ስለነበራቸው እኒያ ብሩህ አእምሮዎች አሳዛኝ ፍጻሜ ሊያሳውቁን በቃን።

የታደለች ከጥላቻ እና በቀል የራቀ ትርክት ያለው ርባና ከላይ ተጠቍሟል። በደራሲዋ ትርክት ውስጥ ምሬት፣ ኵነና እና ዘለፋ አይነበብም። ባለቤታቸውን እና ወንድማቸውን ለገደሉ፣ የጓዶቻቸው ሕይወት እንዲቀጠፉ ላበቁ፣ ራሳቸውንም ከ12 ዓመታት በላይ ላሰሩ ባለሥልጣናትም ኾኑ የቀድሞ ጓዶቻቸው እንኳን ውግዘት፣ ክፉ ቃል ከመጻፍ ተቈጥበዋል። የራሳቸውን ሐቅ እና አተያይ በሚመስጥ ቀላል ቋንቋ አቅርበው የአረዳድ እና የዳኝነት ድርሻውን ለአንባቢ፣ ደግሞም ለታሪክ ተመራማሪ ትተዋል። እንዲያውም በመጽሐፋቸው የመጨረሻ ክፍል ውስጥ በዚህ ርእሰ-ነገር ላይ የሚሉት አላቸው። በማንም ላይ ቂም እንደሌላቸው፣ ለራሳቸው ጤና እና የኅሊና ነጻነት ሲሉ ከበቀል እና ጥላቻ እንደሚርቁ ይገልጻሉ። ደግሞም ለዚያ ክፉ ዘመን ገዳዮች እና አስገዳዮች ተገቢ ጥያቄ ያቀርባሉ፤ በየትኛው ሕጋዊ፣ ተፈጥሯዊ ወይም መለኮታዊ ሥልጣናቸው እንዲያ እንዳደረጉ? በዐሥር ሺሕዎች የሚቈጠሩ ወጣቶች እና ባለሙያዎች በየትኛው የፍትሕ ኺደት፣ መቼ እና የት ተከስሰው፣ በየትኛው ችሎት ራሳቸውን ተከላክለው ነው የተገደሉት? የትኛው የእምነት ቃላቸው ነበር ያለምንም ሥቃይ እና እንግልት፣ ያለ ማስፈራሪያ እና ጫና ተሰጥቶ ለእስራትም ኾነ ለግድያ ያበቃቸው? በዚያ አሳዛኝ የዕልቂት ዘመን ዳኛው ማን ነበር? በመጽሐፉ ርእስ እንደተጠቈመው ዛሬስ የዚያ ዘመን ታሪክ “ዳኛው ማነው?”

መጽሐፉ ስለ ታደለች እና ብርሃነ ብቻ ነው ማለት ርባናውን ማኰሰሰ ይኾናል። ለኔ መጽሐፉ ከሚያነሣሣቸው የፓርቲው ዕንቍዎች ውስጥ ተስፋዬ ደበሳይ እና አክሊሉ ኅሩይ ይገኙበታል። ሌሎችም አሉ፤ ዘርአብሩክ፣ ኤርሚያስ፣ ዐቢዩ፣ በክሪ፣ መልእክተ ዮሐንስ፣ ደምሴ …። ከኋለኞቹ ብዙዎቹ በገዛ ራሳቸው ፓርቲ እየታደኑ የተገደሉ ናቸው፤ በታችኛ የድርጅት እርከኖች ውስጥ የነበሩ ተከታዮቻቸው ለደርግ እጅ ሰጥተው የብቀላ ርምጃ ከመውሰዳቸው አስቀድሞ። ፍጹም ጭቁን እና ምዝብር ከነበሩ ዐርሶ-ዐደሮችም እንደ አያ ሙሄ፣ በልኹ ወልዴ እና እሸት መኵሪያ ያሉት ይታወሳሉ፤ የቅድመ-አብዮት ኢትዮጵያ ጕልተኛ ሥርዐት እልፍ አእላፍ ሰለባዎችን የሚወክሉ ኾነው። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ዘርዑ ክሕሸን ያሉ አመራሮችን የባሕሪ እና የሥነ-ምግባር ሕጸጾች ከተንኰል ሥራዎቻቸው እንድንረዳ የሚያስችሉ ኹነቶች እና ገጠመኞች ተመዝግበዋል። ብርሃነ ስለ ዘርዑ የነበረው አተያይ በቸልታ የሚታለፍ ነገር አይመስልም። የፓርቲውን ስኬት እና ውድቀት (በተለይም በከተማ የኾነውን) በጥልቀት ለማወቅ፣ ደግሞም በመጽሐፉ የሚጠቀሱትን የዋና ተዋንያን ድርሻ ለመረዳት፣ የደራሲዋን ሐቆች እና ትዝብቶች ስሌት ውስጥ ማስገባት ግድ ነው።

ተስፋዬ እና አክሊሉ በቅድመ-አብዮት ዓመታት በስዊትዘርላንድ ያሳላፉት ሕይወት ምን እንደሚመስል የማየት ዕድል ደራሲዋ ይሰጡናል፤ ኹለቱ ሰዎች የርሳቸው ጓደኞች፣ አስጠኚዎች እና መካሮች (mentors) ስለነበሩ። 3ኛ ገጽ ከ7 ኅሩይ አንጀት የሚበላ ጀግና ነው፤ ሕይወቱን ለትግሉ እና ለድርጅቱ የሰጠ፤ ለጓዶቹ ልዩ ፍቅር የነበረው፤ የሚከተለው መርሕ እና ኀልዮታዊ ግንዛቤ ድርጅቱ አላግባብ ከነደፈው ዐዲስ የትግል መስመር ጋር ሲጋጩበት እንኳ መሪዎቹን በፍጹም ታማኝነት የተከተለ። የኔ የሚለው ምንም ነገር ስላልነበረው ምስኪንነቱ በአንባቢ ልብ ላይ በጋለ ብረት ይተኰሳል (is cauterised)። የርሱ ሰብእና እና ዕጣ ፈንታ የ-ኢሕአወሊ-ን ያሳስበኛል። ሊጉን ከወንድሙ ከቲቶ ኅሩይ ጋር ኾኖ ያደራጀው እርሱ ስለነበር እንዲህ እላለኹ፤ ወጣት ክንፉን በራሱ አምሳል ቀርጾት ነበርን?

የተስፋዬ ደበሳይም በቅንነት እና ልዝብነት የተሞላ ባሕሪ ተለባሚ ነው። ዝግታው ገንኖ፣ ለጓዶቹ ያለው ፍቅር እና አክብሮት ጐልቶ ይታያል። የተማሪው ትግል ባህል ግርፍ ስላልነበር በፓርቲው አመራር ውስጥ በተነሡ ሽኵቻዎች እና የተንኰል አካኼዶች ከትክክለኛ እምነቱ እና አቋሙ ሊያፈነግጥ እንደቻለ ደራሲዋ ይገምታሉ።(1) በስተመጨረሻም “በሠራው ስሕተት” የተጸጸተ ሰው ይመስላል። ለታደለች የተናገረውን ቃል-በ-ቃል ማመን የሚያዳግተው አንባቢ፣ በዐሠሣው ጊዜ ተስፋዬ በተቻለው መጠን ጓዶቹን ለማትረፍ ሲባትል የራሱን ሕይወት በራሱ ለማጥፋት የሚገደድበት ኹኔታ ውስጥ መግባቱን አይክድም። ይህን አቶ ክፍሉም በተደጋጋሚ ይመሰክራሉ፤ (ይመ. «ያ ትውልድ፣ ቅጽ 3፣ ኢትዮጵያ ሆይ ቅጽ 1)። ተስፋዬ የቀደምት ኢየሱሳውያንን አብነት በመከተል ምሁር መነኵሴ መኾን የሚችል ሰው ነበር። ታዲያ የርሱን ሃይማኖታዊ እና ፍልስፍናዊ ዳራ ያልዘነጋ ሰው በአእምሮው እንዲህ የሚል ጥያቄ ይመላለስበታል፤ ንስሓውን በደሙ ለመከፈል ይኾን ሕይወቱን ያጠፋው?

በታደለች የብርሃነ ምሰላ (portrayal) ውስጥ ልበ-ሰፊነቱ ይስተዋላል። ይህን ለመለበም “ሽማግሌው” ስለ ተስፋዬ እና ኀይሌ ፊዳ የነበረው ዕይታ እና አረዳድ በቂ ምሳሌዎች ናቸው። ተስፋዬ የከተማ ትጥቅ ትግልን በመደገፉ፣ በሌሎችም “ጥፋቶቹ” የተነሣ ብርሃነ የተሰማው ቍጣ እና በቀል ሳይኾን ዐዘኔታ እና ይቅርባይነት ይመስላል።(2) ኀይሌንም እንደ ተስፋዬ ይረዳው እንደነበር እንገነዘባለን፤ የእርሱንም ቅንነት እና ደንሴ መኾን (docility) ለእኩይ አጀንዳቸው የሚጠቀሙ ሰዎች ከበስተጀርባው መኖራቸውን ያምን ነበርና። ኀይሌም ተስፋዬም አንጋፋ ናቸው፤ በዕድሜ፣ በትምህርት፣ በመምህርነት ሙያ። በሀገር ቤቱ የተማሪው ንቅናቄ ውስጥ ተካፍለው ለባህሉ (ለደጉም ለክፉውም) አልተጋለጡም። ብቅለታቸውም ገጠር ወይም ገጠር-ቀመስ ከነበሩ የዳርጌ ማኅበረሰቦች (peripheral communities) በመኾኑ ለከተሜ ልሂቃን የሻጥር ፖለቲካ ባይተዋርነታቸውን መገመት ይቻላል። በሚሲዮናውያን ትምህርት እና ሥነ-ምግባር ተኰትኵተው ማደጋቸውንም ተሰሊ ማድረግ (consider as a factor) ተገቢ ይመስላል፤ በተለይ ሻጥርን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ወይም እንደ ትግል ስልት የተቀበሉ ሰዎች ባለመኾናቸው። ብርሃነ ስለኹለቱ ሰዎች ያለው አረዳድ ኹለንተናዊ (holistic) እንደነበር መገመት አያዳግትም፤ በትግል ስልት እና በወቅታዊ ፖለቲካዊ አተያይ ከርሱ የተለየ አቋም ቢይዙም የሰብእናቸውን ክቡርነት፣ የሥነምግባራቸውን ከፍታ፣ የባሕሪያቸውን በጐነት ለአፍታም አልዘነጋም። የትግል ታክቲክ ቢያለያየንም ግባችን በአንድ ጐራ ያቆመናልና በደመኛነት መፈላለግ የለብንም ባይ ነበር፤ አርቆ-ዐሳቢነቱን፣ ከአድማስ ባሻገር ተመልካችነቱን በሚጠቍም ደረጃ።

ሌላው ልበ-ሰፊ የመኾኑ ማስረጃ ከበቀለኛነት የራቀ መኾኑ ነው። የገዛ ጓዶቹ ሊገድሉት እንደሚፈልጉ ከጥርጣሬ ያለፈ ግንዛቤ የነበረው ጊዜ እንኳ የመረጠው ሽሽት እንጂ እጁን ለደርግ ሰጥቶ አሳዳጆቹን መበቀል አልነበረም። ጌታቸው ማሩም አደጋ ላይ መኾኑን ዐውቆ ዐብሮት እንዲሸሽ ሞክሮ ነበር፤ ሊያሳምነው አልቻለም እንጂ። ጌታቸው ከአመራር ያገለሉት ጓዶቹ በቀጠሩት ቦታ እየተገኘ እስረኛቸው ኾነ። እያወገዙትም እንኳ ያምናቸው በነበሩ ጓዶቹ ተገደለ። ብርሃነ በቀድሞ ጓዶቹ ላይ በቀለኛ አለመኾኑን ደርግም ይመሰክርለታል። እርሱን ለመግደያ ከተጠቀመባቸው ዐበይት መወንጀያዎች አንዱ ከፓርቲው አመራር ሲገለል እጁን ለመንግሥት ሰጥቶ የቀድሞ ጓዶቹን አላጋለጠም የሚል ነውና።

ለኔ ከመጽሐፉ ትልቅ ርባናዎች አንዱ በሰሜን ሸዋ ስለተደረገው የእርማት ንቅናቄ የሚያቀርበው ዝርዝር ታሪክ ነው። በርግጥ ስለዚህ ንቅናቄ እና ስለ ታ/አ/አ/ቡ በኅዳግ ማስታወሻ ቍጥር 2 የተጠቀሰው የደርግ መርማሪዎች ዘገባ ዝርዝር መረጃ ይሰጣል። ዘገባው ግን የታተመ ባለመኾኑ እምብዛ አይታወቅም፤ ለብዙ ዓመታት በ-ፖዶፎ (PDF) የተሰራጨ ቢኾንም። ስለዚህ ታደለች በገዛ ራሳቸው ትውስቶች ላይ ተመርኵዘው ያቀረቡት የታ/አ/አ/ቡ ታሪክ ታትሞ አንባቢ ዘንድ መድረሱ ትልቅ ቁምነገር ነው። ትርክታቸው በዘገባው የቀረበውን የሚመሰክር እና የሚያሟላ ነው።(3)

በጭብጥ ረገድ ስሕተቶች እና አጠያያቂ ነገሮች የምላቸው ጥቂት ናቸው፤ ጕልሕም አይደሉም። በገጽ 228 ላይ ከሮባ (አብዲሳ አያና) በቀር ሌሎቹ አውሮፕላን ጠላፊዎች የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደነበሩ የሚገልጽ ፍሬ ቃል አለ። ይህ ግን ትክክል አይደለም። አብዲሳ በጠለፋው ጊዜ ዩኒቨርስቲ ተዘግቶ ጊዜያዊ ሠራተኛ ለመኾን ከመገደዱ በቀር የዚያ ተቋም ተማሪ ነበር። ማኅበራዊ ግንኙነቱም ከዩኒቨርስቲ ጓደኞቹ ጋር እንደነበር እሙን ነው። እንዲያውም ከርሱ ይልቅ ተማሪነታቸው የሚያጠራጥር ደረጃ ላይ የደረሰው የብርሃነ እና አማኑኤል ገብረ-ኢየሱስ እንደነበር እገምታለኹ፤ ቢያንስ ረዘም ላለ ጊዜ ከትምህርት እና ከዩኒቨርስቲው ርቀው ነበርና። በዚያው ገጽ ላይ ጠላፊዎቹ ወደ ስምንት ወር በወታደራዊ ካምፕ መታሰራቸው ይጠቀሳል። ይህም በፖሊስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ ስድስት ወራት ያኽል ተጠብቀው መቈየታቸውን በሚገልጽ ዐረፍተነገር ቢገለጽ የሱዳን ቈይታቸውን ይበልጥ በትክክሉ እንደሚገልጽ ዐስባለኹ።

አንድ ኹለት አጠራጣሪ የዕለት መጥቀሻዎችም አጋጥመውኛል። የመጀመሪያው በገጽ 3 ላይ የተጠቀሰው 1962 ዓመት ምሕረት ነው። ይህ የከተባ ስሕተት ይመስለኛል፤ 1963 ዓ.ም ለማለት። ምክንያቱ በሚቀጥሉት ገጾች ተገልጿል። ጥላኹን ግዛው ተገድሎ ከፍተኛ የተማሪዎች ተቃውሞ ዩኒቨርስቲውን ሲያናውጥ ታደለች የተቋሙ ተማሪ ነበሩ፤ የዐይን ምስክርም ለመኾን በቅተዋል። ወደ አውሮፓ የተጓዙት በዓመቱ ነበር። ኹለተኛው በምዕራፍ 15 ውስጥ ጌታቸው እና ብርሃነን ከማ.ኮ ስላስወገደው ስብሰባ የተጠቀሱ ኹለት ዕለቶችን ይመለከታል፤ ጥር 17 እና ጥር 18 (ገገ. 217፣ 274 ላይ)። ይህ የኾነው የማ.ኮ ስብሰባው ኹለት ቀኖች በመፍጀቱ ይኾን? ካልኾነ የትኛው ነው ትክክል?

በመጨረሻ መጽሐፉ መጠቍም ያለው በመኾኑ መደሰቴን መጥቀስ እወድዳለኹ። መጠቍሙ የተሟላ ነው ሊባል የሚችል ባይኾንም ዐበይት በኾኑ ሰዎች እና አርእስተ-ነገር ላይ የተሰጡ ፍሬ ቃሎችን የሚያመላክቱ የገጽ ማጣቀሻዎች አሉት። ኹለተኛ ዝግጅት ቢታተም የጐደሉትን በቀላሉ ለማሟላት የሚያስችል መሠረት ጥሏል።

ቋንቋነክ ተማግቦ

«ዳኛው ማነው?» በጽሑፋዊ ቋንቋ ረገድ ግሩም ነው። ዐጠር-ዐጠር ባሉ ዐረፍተነገሮች፣ ቅልጥፍ ባሉ ግልጸቶች የተደራጀ ትርክት ስለሚያቀርብ ለንባብ ቀላል ኾኖ አግኝቼዋለኹ። እንከን-የለሽ ባይባልም ባለንበት ዘመን ከሚታተሙ እጅግ ብዙ ኅተመቶች ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም የተሻለ ነው። ለዚህም ከደራሲዋ በተጨማሪ አርታዒያቸው፣ ማንይንገረው ሸንቍጥ፣ ሊመሰገኑ ይገባል።

መጽሐፉ ትኵረቴን የሳቡ በርካታ ቀበልኛዎች እና ከዚህ ቀደም የማላውቃቸው ቃላት አሉት። አያ ሙሄ – ያ የብርሃነን አእምሮ እንዳይረሳ አድርጎ የደሰመው ሢሶ ዐራሽ – “ለጌቶች የተነየትውማ አይቀርም” ብሎ (ገ. 201) እኔን ዐዲስ ከኾነ ጠቃሚ ቃል ጋር ያስተዋውቀኛል። ቃሉ በግሱም ኾነ በውልድ ግሱ፣ (ነየተ፣ ተነየተ)፣ በመዛግብተ-ቃላትም ውስጥ ተካትቶ አላገኘኹትም። በሌላ ቦታ ደራሲዋ “በጀበርና ታጥቀን” (ገ. 315) ብለው በከተሜ ዐማርኛ ውስጥ እምብዛ እማይደመጥ ቃል ይዘግቡልናል። በሰሜን ሸዋ እና ወሎ የገጠሩ ሕዝብ ኢሕአፓ-ን ሙሃባ ወይም ሙሃቦች እንደሚል ቀደም ሲል ባውቅም መጽሐፉ ላይ እንደገና ሲያጋጥመኝ የስሙን ጥዋሬያዊ ኺደት (process of adaptation) እንድጠይቅ አድርጎኛል። ኢሕአፓ ወደ ሙሃባ የተቀየረበት ባህላዊ እና ሥነ-ልሳናዊ ኺደት ምን ይኾን ብያለኹ። አጓጊ ሚስጥር (intriguing) ነው። መጽሐፉ በርካታ ሌሎች ተለባሚዎች አሉት፤ እንደ ጣይ ስትቀድ (293)፣ ሙጥቁላን (ገ.320)፣ ብብቻ (319) ያሉ።

ከላይ የተባለው እንዳለ ኾኖ በቋንቋ ረገድ የታዩኝን እንከኖች እና አስተውሎዎች ማንጠብ ተገቢ ነው። የነዚህ ዝርዝር ለደራሲዋ ከተማራጭ ሐሳቦች ጋር በዐባሪ ሰነድ መልክ በመቅረባቸው፣ ይህ ዳሰሳ ለአስረጅነት በሚበቁ ናሙናዎች ብቻ ያተኵራል። የከተባ ስሕተቶች ብዙ አይደሉም። ከስሕተቶቹ ውስጥ ደግሞ ጥቂቱ “ኳ” እና “ጓ” ለመክተብ ካለመቻል የተከተሉ ይመስላል፤ በተደጋጋሚ በ“ኴ” እና “ጔ” ተተክተው ይታያሉና። በተመሳሳይ ኹኔታ በ “ጵ” ቦታ “ዽ” ይታያል።

ዐጕል እና ዝንኵር አጠቃቀሞችም ጥቂት ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ አንድ-ኹለቱ በዚህ መጽሐፍ ብቻ የማይወሰን ቅቡልነት ስላላቸው በዚህ አጋጣሚ መጠነኛ ማብራሪያ ቢሰጥባቸው እንደሚበጅ ዐስባለኹ። የመጀመሪያው የወቅት ስሞችን የሚመለከት ነው። ስለ ወቅቶች ስያሜ ዘመናዊ ትምህርት በቀሰመው ዐማርኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብ ውስጥ የአጠቃቀም ውዥንብሮች በስፋት እና በተደጋጋሚ ይስተዋላሉ። ልጆች ሳለን የተማርናቸው ስሕተተኛ የወቅት ስሞች አፈታት ለዚህ መነሻ ይመስለኛል። መዛግበተ ቃላት እና መማሪያ መጻሕፍት ክረምትን winter፣ በጋን (መኸርን) summer፣ ጸደይን spring፣ በልግን autumn እያሉ በመፍታት አስተምረውን ነበር። የወቅቶችን ፍቺ ከምድር ዑደት እና ከዋልታዎቿ ዝማሜ ይልቅ ከአየር ጠባይ እና ከዕፀዋት ኹኔታ ጋር ማያያዛቸው ነበር የአፈታቱ ችግር መንሥኤ። እኒህን ዐጕል ፍቺዎች የተማርን ኹሉ ተደጋጋሚ ስሕተቶች እየሠራን እንኖራለን። ኢትዮጵያ በሰሜን ንፍቀ-ክብ (hemisphere) እንደመገኘቷ የክረምቷ ወቅት የሚጐዳኘው ከአውሮፓውያን ሰመር እንጂ ከክረምታቸው ጋር አይደለም። በተመሳሳይ የሀገራችን መከ(ኸ)ር (የአዝመራ መሰብሰቢያው ወቅት) የሚጐዳኘው ከአውሮፓውያን ዊንተር ጋር ነው። ጸደይ እና በልግ ኹለት ወቅቶች አይደሉም፣ ከአውሮፓውያኑ ስፕሪንግ ጋር የሚገጥሙ እንጂ። በልግ በጸደይ ወቅት (መጋቢት – ግንቦት) የሚከሠት መለስተኛ የዝናብ ወቅትን ይገልጻል። በተቀር ከአውሮፓውያኑ ኦተም ጋር የሚጐዳኘው የሀገራችን የአበባ ወቅት (መስከረም – ኅዳር) የሚታወቅበት ስም መፀው ነው፤ በጥቢ እና ጽጌ ሊከፈል የሚችል። እናም ደራሲዋ ዐደይ አበባ የሚፈካበትን ወቅት “ፀደይ” ሲሉ (ገ. 5) በልማድ የተማርነውን ሲደግሙ ነው። በርግጥ በኢትዮጵያ ከክረምት እና በጋ በቀር መፀው እና በልግ ጐልተው እና ረዘም ላሉ ጊዜያት ቈይተው አይታዩም፤ በተለይ ለከተሜዎች እና በቈላማ ቦታዎች ለሚኖሩ ሰዎች። በደጋ እና ወይናደጋ ገጠሮች ግን መፀው እና በልግም ይታወቃሉ፤ የመጀመሪያው የእሸት መብሊያ፣ የአበባ እኽል መዝሪያ በመኾኑ፤ ኹለተኛው ደግሞ በቂ ዝናብ እስከጣለ ኹለተኛ ምርት የሚያስገኝ የዕርሻ ሥራ ስለሚከወንበት።

በተጨማሪ ጥቂት ቦታዎች ላይ “በይነ ፓርቲ” ዐጕል ጥቅም ላይ ውሎ እናያለን (ገገ. 269፣ 277፣ 423)፤ ውስጠ-ፓርቲ መኾን ሲገባው። ‹በይነ› በቁሙ ኹለት ወይም ከኹለት በላይ አሐዶችን (units) አሊያም ራስ- ገዝ አካሎችን (autonomous entities) የማካተት ፍቺ ያዘለ ቃል ነው። በአንድ ድርጅት ወይም ተቋም ውስጥ የሚኾንን ነገር አይጠቍምም።

በመጽሐፉ ውስጥ በአገባብ እና አገላለጽ አለመሰብቀል የሚታይባቸው ፍሬቃሎች ጥቂት በመኾናቸው በተለየ ፈርጅ መታየታቸውን አላስፈላጊ ሊያስመስል ይችላል። ጕዳዩ ግን የብዛት ሳይኾን የዐይነት ነውና ለብቻ መቅረባቸው አግባብ አለው። ለምሳሌ የሚከተሉትን እንመልከት። በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት በጥቍር ቀለም ከገጽ መጠቈሚያዎቻቸው ጋር ተጠቅሰዋል፤ ከነርሱ ቀጥሎ ደግሞ በሰማያዊ ቀለም የተመለከቱ ተማራጮች አሉ።

1ሀ. … ሲሆን፣ ለራስ መሸፈኛ ቆብ ከኮቱ ጋር የተያያዘ ሙቀት የሚሰጥ፣ ሳያስፈልግ ሲቀር ደግሞ ወደ ትከሻ የሚመለስ ነው። (ገ. 60)

1ለ. … ነው። ደግሞም ራዎት (hood) ስላለው፣ ሲያስፈለግ ራስን ሸፍኖ ያሞቃል፤ ሳያስፈለግ ደግሞ በስተጀርባ ታጥፎ ይቈያል።

2ሀ. የፀረ ኢምፔሪያሊስት በተለይም በነአሜሪካ ላይ ተቃውሞው እየበረታ (ገ. 219)

2ለ. በፀረ ኢምፔሪያሊስት [ኀይሎች]፣ በተለይም በአሜሪካ፣ ላይ ተቃውሞ እየበረታ 2መ. የፀረ ኢምፔሪያሊዝም ተቃውሞው፣ በተለይ በአሜሪካ ላይ እየበረታ

3ሀ. ብርሃነመስቀል ከማውቃቸው ጥቂት ሰዎች ውስጥ larger than life በሚለው መገለጫ ከሚታወቁ ሰዎች አንዱ ነው። (ገ. 368)

3ለ. ብርሃነመስቀል ከማውቃቸው እና larger than life መባል ከሚገባቸው ጥቂት ሰዎች አንዱ ነው።

በገጽ 66 የኅዳግ ማስታወሻ ላይ የፋርሶች ባህላዊ ዐጭር የቈዳ ካፖርት ይገለጻል (1ሀ.)። ግልጸቱ ግን በቃላት አሰካክ ችግር የተነሣ የተሰናከለ ነው። በ1ለ. የተሰጠው ተማራጭ ከኮት ኮሌታ/ክሳድ ጋር ተያይዞ ያለ የራስ ልብስን በተገቢ ስሙ ‹ራዎት› ብሎ፣ የርሱን ግልጋሎቱም ዕጥር ምጥን አድርጎ ይገልጻል። በ2ሀ. የተሰጠው ሐረግ መሙያ (complement)፣ የመስተዋድድ ማረሚያ እና የቅደም-ተከተል ማስተካከያ ያስፈልጉታል። በ2ለ. እና በ2መ. የተሰጡት ተማራጮች እኒህን ያረታሉ። 3ሀ. ከቃላት ድግግሞሹ (“ከማዋቃቸው”፣ “ከሚታወቁ”፣ “ሰዎች”፣ “ሰዎች”) በተጨማሪ ያልቆፈጠነ ነው። የ3ለ. ተማራጭ ድግግሞሹን ብቻ ሳይኾን ሰባራ ግልጸቱንም እንደሚያቀና ዐስባለኹ።

ከላይ የተመለከቱት እና ሌሎቹም በመጽሐፉ ውስጥ ዐልፎ-ዐልፎ የሚገኙ ያልሰበቀሉ ፍሬቃሎች ያንባቢን የመረዳት ዐቅም የሚፈታተኑ አይደሉም። እንዲያውም ብዙ አንባቢዎች እንከኖቻቸውን ልብ የሚሉ አይመስለኝም። ቢስተካከሉ ግን ለመጽሐፉ ቋንቋ-ነክ ፍጽምና ርባና ይኖራቸዋል።

መቋጫ አስተያየቶች

መጽሐፉ የአእምሮዬ ጓዳ-ጐድጓድዎች ውስጥ በተጐዘጐዙ ቋያዎች ላይ እሳት የሚጭር ክብሪት ኾኖ አግኝቸዋለኹ። ታደለች ስለቤተሰባቸው እና ሰለ አባታቸው የሚሉት ኹሉ ያደግኩበትን ቤተሰብ የሚያሳስብ ነው። አባታቸው አቶ ኅይለሚካኤል ለትምህርት የሚሰጡት ትኵረት፣ እናታቸው በቀይ ሽብሩ ጊዜ ልጆቻቸውን ለማዳን ያዩት መከራ፣ በቤታቸው የሚኖሩ ወይም ለጥየቃ መጥተው የሚሰነባብቱ የዘመድ-አዝማድ ብዛት ኹሉ ካሳዳጊዎቼ ቤተሰብ ጋር ያለው ተመሳሳይነት በግርመት ሞልቶኛል። ወንድሜ ተሻለ ፈርሻ ሲገደል፣ ብዙ ወንድሞቼ እና እኅቶቼ ሲታሰሩ፣ እኔን ገጠር ደብቆ ለማትረፍ አሳዳጊዎቼ፣ ሌሎች ዘመዶቼ እና የእኅቴ ወዳጆች ኹሉ ያዩት መከራ ወለል ብሎ እንዲታየኝ አድርጓል።

«ዳኛው ማነው?» ትልቅ የታሪክ ቅርስ ነው። ለደራሲዋ እና ለብርሃነ፣ ለተስፋዬ እና አክሊሉ ሐውልቶች ያቆማል። የሌሎች የ-ኢሕአፓ ጀግኖችንም ስሞች እያነሣሣ እንዳይረሱ ያደርጋል። ለዚህ ቅድጅቱ፣ ደግሞም ይህ ውሱን ተማግቦ ላነጠባቸው አስተውሎዎች (ላልዳሰሳቸውም እጅግ ብዙ የመጽሐፉ ዕሴቶች) ደራሲዋ ወሰንየለሽ ምስጋናዬ ይድረሳቸው።

ታሪካቸውን ያልተናገሩ አያሌ የፓርቲው እና የወጣት ክንፉ ጀግኖች የደራሲዋን አብነት እንደሚከተሉ ተስፋ አደርጋለኹ። “የኔ ለመጽሐፍ ወግ አይበቃም” በሚል ሰበብ ዳተኛ ለኾኑት ኹሉ በየራሳቸው ታሪክ ውስጥ ጓዶቻቸውም እንደሚታወሱ ታደለች አሳይተዋቸዋል። የራሳቸውን ታሪክ ከቍብ ባይቈጥሩ፣ ሰማዕታት ጓዶቻቸው ተረስተው እንዳይቀሩ የማድረግን ዐደራ መዘንጋት አይችሉም።

ይህ ዳሰሳ በራሴ ውሱን አረዳድ የተነሣ በምላት እና በስፋት የቀረበ ሥነ-ጽሑፋዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ ዳሰሳ አይደለም። ይልቁን ኹለት ቀዳማዎችን አንግቦ ተዘጋጅቷል። አንደኛው ስለ መጽሐፉ ያለኝን እኳቴ (appreciation) መግለጽ ሲኾን፤ ኹለተኛው በስፋት እንዲነበብ፣ በጥልቀት እንዲገመገም ይረዳ ዘንድ የውይይት መንደርደሪያ ይኾናሉ ያልኳቸውን አንዳንድ አስተውሎዎች ማንጠብ ነው። የተሳካልኝ መኾኑን እንጃ፤ በእጄ ያለውን ግን ወርውሬያለኹ።

……………………………………………………….

1) ለምሳሌ በገጽ 170 ላይ ታደለች ቅሬታ/ተቃውሞ ያቀረቡበትን ኮምዩኒኬ እንመልከት። ተስፋዬ ከዘርዑ ጋር በፓርቲው ስም ኮምዩኒኬውን መፈረሙ ስሕተት ነበር። ግን ደራሲዋ ልክ እንደ ብርሃነ በዘርዑ ተንኰል እና በሻዕቢያ ጫና ተስፋዬ እንደተሳሳተ አምነው የጓደኛ ወገንተኛነት ያሳያሉ። ኾኖም ጕዳዩ በአንባቢ አእምሮ የሚያስነሣው ጥያቄ አለ፤ “ተስፋዬ በምሁራዊ ዕውቀት እንጂ በእውኑ ፖለቲካ (realpolitik) ስሑል አልነበረምን?”

2) በርግጥ የብርሃነ “የእምነት ቃል” እየተባለ በሚጠቀስ አንድ የደርግ መርማሪዎች ዘገባ ውስጥ ስለ ተስፋዬ የተባሉት ነገሮች ሲደመሩ ያልተዋበ ምስል (unflattering picture) የሚከሥቱ ናቸው። እንዲያውም ብርሃነ “ክሊክ” በሚለው የአመራር ስብስብ ውስጥ እንደ ቀንደኛ ተዋናይ ይገለጻል። የዘገባው ተአማኒነት ግን በብዙ ረገድ ያጠያይቃል። የደርግ እስረኛ በኾነ ሰው የተሰጠ ቃል በገዛ ራሱ የማያስተማምን ከመኾኑ በተጨማሪ፣ ዘገባው ብርሃነ የተናገረውን/የጻፈውን ቃል-በ-ቃል የሚሰጥ አይደለም፤ በመርማሪዎች ለግድያ እንዲያበቃ ተደርጎ የተጠናቀረ መወንጀያ እንጂ። (ይመ. በሠኔ 1971 ዓ.ም ለአገር አስተዳደር ሚኒስቴር አ/መ/ማ/ማ/ኮ የቀረበውን ዘገባ።)

3) ከዚህ ጋር በተያያዘ የደርጉን ዘገባ ካነበቡ ሰዎች አንዳንዶቹ በብርሃነ ላይ ተጨማሪ ወቀሳ እና ውግዘት ማንሣታቸው ይታሰበኛል። ከሰነዱ ተአሚኒነት/ኢ-ተአማኒነት ባሻገር ብርሃነ እጁን ለደርግ መስጠት አልነበርበትም፣ በደርግ ወታደሮች የተከበበ ጊዜ ተታኩሶ መሞት ወይም ራሱን እንደ ዐፄ ተዎድሮስ መግደል ነበረበት፣ ወዘተ. በሚሉ አስተያየቶች ላይ የተመረኰዙ ውግዘቶች ናቸው። በበኩሌ እንኳን እጁን ሰጠ፤ እንኳንም የራሱን ሕይወት ለማቈየት መረጠ፤ ደርግ እስከገደለው ዕለት። ሕይወቱን ያላጠፋው ድፍረት አንሶት፣ ሞት አስፈርቶት አይመስለኝም። የራስ ግድያን ከሚነቅፍ አቋሙ በተጨማሪ፣ ከቀድሞ ጓዶቹ የተለየበት የትግል መስመር ምን እንደነበር፣ በሰሜን ሸዋም የመራው ንቅናቄ ምን እንደሚመስል ለታሪክ የራሱን ሐቅ ሳያስመዘግብ መሞት ባለመፈልጉ ይመስለኛል። እንደ ጌታቸው ማሩ ድምፁ ታፍኖ መሞት አልወደደም። ቀደም ሲልም “የብዙኃን መስመር”ን በመቅረፀ-ድምፅ የዘገበው በዚህ ምክንያት እንደኾነ መገመት ይቻላል። ታሪኩን እና አተያዩን ማስታወቅ፣ ለወደፊት ትውልድም ቅርስ አድርጎ ማቈየት እጅግ ሳያሳሰበው እንዳልቀረ እገምታለኹ። ያ ዝግብ ድምፅ ቢገኝ ኖሮ የደርጉ ሰነድ እምብዛ ዋጋ አይኖረውም ነበር።

October 23, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *