የዶክተር ዓለማየሁ አረዳ “ምሁሩ” | ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)
መጻሕፍት

የዶክተር ዓለማየሁ አረዳ “ምሁሩ” | ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)

“ምሁሩ” የተሰኘው የዶ/ር ዓለማየሁ አረዳ መጽሐፍ፣ ከዚህ በፊት ይህንን ርዕሰ ጉዳይ መሠረት አድርጎ የቀረበ ወጥ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራ ስላልነበረን፤ ስለ ኢትዮጵያ ምሁር ሰፊ ዘገባና ትንተና ያቀረበ የመጀመሪያ ሥራ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የምርምሩ ጭብጥ አትኩረቶች፤ ምሁርነት ምንድን ነው? ተግባሩስ እንደምን ይገለጻል? ብሎ ይጀምርና፤ የምሁሩን ጠባይ፣ የምሁሩን ምንንት፣ የምሁሩን ርዕይ እና አመለካከት ለማተት ይሞክራል፡፡ በሌላው ዓለም ስለ ምሁሩ፣ ራሱን የቻለ ሐቲት በተደጋጋሚ ቀርቧል፡፡ በኢትዮጵያ ግን ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ ርዕሰ ጉዳዩ በመጽሐፍ መልክ አንድ ወጥ ኾኖ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ መጽሐፍ ያነሳ እና ፈር ቀዳጅ የኾነ ሥራ ነው የሚል ዕምነት አለኝ፡፡

የዶ/ር ዓለማየሁን መጽሐፍ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ያተኮረ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራ እንደመኾኑ በብዙ ፈርጅ ማየት የሚቻል ቢኾንም፤ ለጊዜው በሚከተሉት ሦስት ነጥቦች ላይ አተኩሬ አልፋለሁ፡-

አንደኛ፡- ከምሁሩ ጥናት ባሻገር እንደ ተጓዳኝ ነጥብ በየጊዜው የፖለቲካ ውይይት ስናደርግ የምንጠቀምባቸውን ቃላት እና ስያሜዎች ደግመን እንድንፈትሻቸው ይጋብዘናል፡፡ ለምሳሌ፡- መንግሥት፣ ብሔር፣ ነገድ፣ ብሔርተኝነት፣ ዜጋዊ ብሔተኝነት ወዘተ… የሚሉትን ቃላት ፈትሾ ለውይይታችን መስመር የሚያስይዝ የመግባቢያ ፈለግ ሰጥቶናል፡፡

ኹለተኛ፡- ስለ ኢትዮጵያ የሚጻፉ መጻሕፍት ላይ በተደጋጋሚ በሚቀርበው ትችት፣ የታሪክ ጸሐፊዎቹን በውክልና (የሃይማኖት፣ የብሔር እና የማንነት) ኩለንተናዊነት ይጎድለዋል እና አግላይም ነው የሚሉ ክሶች ሲቀርብባቸው ይስተዋላል፡፡ የዶ/ር ዓለማየሁ አቀራረብ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ባደረገው ጥረት፤ በመጽሐፉ ቀዳሚ ቃል ላይ እንደገጽኩት፣ በመጀመሪያ፡- ከአክሱም ሥልጣኔ ተነስቶ፣ በዛጉዌ ተሸጋግሮ፣ ወደ ሸዋ እና ጎንደር ሥርወ መንግሥት የሚያቀናውን፣ [በአብዛኛው] የክርስትና ሃይማኖት ታሪክን አጣምሮ የያዘውን “የታሪክ አተራረክ” ሲኾን፣ ሁለተኛው፡- ከ7ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ የእስልምና ሃይማኖት ያደረገውን ትልቅ መስፋፋት፤ የባህል፣ የወግ እና የመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ትረካ ይዞ፣ በሦስተኛ ደረጃ፤ የኦሮሞን ሕዝብ ፍልሰት እና በመላው ኢትዮጵያ የመዋሐድ ተግባር አያይዞ በማቅረቡ ነው፡፡

በመሆኑም እነኚህ ሦስት የታሪክ ካስማዎች፣ አሁን በተለያየ መንገድ አገሪቱ ላይ ያለውን የብሔረ ኢትዮጵያ መልክ፣ እንደፈጠሩ ከተረከልን በኋላ፤ ወደ ደቡብ ሕዝቦች ታሪክ ስንመጣ፣ ከላይ ባዋቀራቸው የታሪክ ዕይታዎች ልክ ተገቢ ቦታ ያገኘለት አይመስልም፡፡

የተማሪውን እንቅስቃሴ ለየት ባለ መንገድ ከማስቀመጡም ባሻገር፣ አሁን የበላይነት የያዘውን የነገዳዊ ፖለቲካ እንዴት እንደተጠነሰሰ እና አሁን የያዘውን መልክ እንዴት ሊፈጥር እንደቻለ፣ ብሎም እንዴት የበላይነትን ሊቆናጸፍ እንደቻለ በጥሩ አቀራረብ አሳይቶናል፡፡

ለዶ/ር ዓለማየሁ፣ ታሪክ ቀላል ነገር አይደለም፤ ውስብስብነት ቀላል መቋጫ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ታሪክ ለመጻፍ ዕውቀት፣ ክሕሎት፣ ሚዛናዊ ዕይታ እና አንድምታውን መረዳት ወዘተ፣ በጥቂቱ ይህን ሁሉ የሚጠይቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ እንዴት ተመሠረተች? ብለን ብንጠይቅ፤ አብዛኛውን ጊዜ የሚሰጠን መልስ፣ በጦርነት እና በኃይል ነው የተመሠረተችው፤ የሚል መልስ ይሰጠና፡፡ በዶ/ር ዓለማየሁ ጽሑፍ ላይ ጦርነትና ኃይል ብቻ ብለን ከምናቆም፤ ኢትዮጵያ በመፈቃቀድ እና በመደበላለቅም ጭምር የተፈጠረች አገር ኾኗን ባንረሳ ምሉዕ የኾነ የታሪክ ዘገባ ሊኖረን ይችላል፡፡

ስንጀምር በጠብ ጀምረን ሊኾን ይችላል፡፡ የመጨረሻ ግባችን ግን በፀብ ተጠናቋል ማለት ላይቻል ይችላል፡፡ አነሳስ እና አጨራረስ የየቅል ናቸውና፡፡ ትልቁ የጀርመን የ20ኛው ክፍል ዘመን ፈላስፋ ካርል ያስፐርስ በአንድ ወቅት ይህን ጉዳይ አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “አንድ አገር በጉልበት ተመሥርቶ ይኾን ይኾናል፣ ሆኖም ግን፣ ያ- የጉልበት እና የኃይል ግንኙነት ዘላለማዊ ስላልኾነ፣ ወደ ፍላጎት እና ወደ መፈቃቀድ ሊለወጥ ይችላል፡፡”

ኢትዮጵያውያንም፤ ታሪካቸው የጀመረበትን ብቻ ሳይኾን፤ በሒደት የደረሰበትንም ሁኔታ በማጤን፣ ወደ አብሮነት እና ወደ ጋራ ማንነታችን ማለትም፤ እንደ ዜግነታችን በዴሞክራሲ ተሳስረን ወደፊት እንደ አገር መቀጠል ይኖርብናል፡፡

ምሁሩ ማን ነው?

ምሁሩን በጥቅሉ አጠር ያለ ትርጉም ብንሰጠው፤ መደበኛ ትምህርት የተማረ (አገር በቀላዊውን ወይም የምዕራቡን) ወይም ራሱን ያስተማረ፣ በአእምሮው የሚመራ፣ አእምሯዊ ምርት የሚያቀርብ፣ እንደ ዶ/ር ዓለማየሁ አቀራረብ፣ “በሐሳብ ደረጃ፤ ‘ምሁር’፣ ለሚናው ባለው መታመን፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ባለው ቅቡልነት፣ ዕውቀቱን ይፋ በሚያደርግበት የሞራል ድፍረት የሚገለጽ፣ ኅብረተሰቡ ያለበትን ዕውነታ የሚያንፀባርቁ ሐሳቦች የሚያቀርብ፣ ጠቅለል ባለ መልክ፣ በዓይነተኛ ሚናው ለእውነት የቆመ መሆን አለበት፡፡  ይሁን እንጂ፤ የምሁሩ ሚና፣ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በሚኖረው ጥሪ፣ ከቦታ ቦታ የተለያየ እንደኾነ ልንገነዘብ ይገባናል፡፡ ለምሳሌ፡- የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የላቲን አሜሪካ ምሁራን የተለያየ ሚና እና ጥሪ ይጠብቃቸዋል፡፡ የኢትዮጵያም ምሁራን የራሳቸው የኃላፊነት ድርሻ እንዳላቸው ያቀርብና፤ ሆኖም ግን፤ ትልቁ ችግር በተወሰነ ርዕሰ ጉዳይ አቋም ይዘው ሐሳባቸውን ከማራመድ ይልቅ፣ “እኔን አይመለከተኝም” በሚል እሳቤ፣ የድርሻቸውን ሳይወጡ መቅረታቸው ነው፡፡

እዚህ ላይ፣ ቀዳሚው የኤግዚሽቴንሽያሊስት ፈላስፋ ዣን ፖል ሳርተ እና የሥነ-ጽሑፉ መምህር እና ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ ያሉትን እንደማሳያ መጥቀሱ የተገባ ይኾናል፡፡

ሀ- እንደ ዣንፖል ሳርተ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ምሁሩ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሳትፎ ያለው (engagement) እና ይህንን ተሳትፎውን በፍልስፍናው ወይም በሥነ-ጽሑፉ ሊያንፀባርቅ ይገባዋል፤ ብሎ ያምናል፡፡ እንዲያውም ለሳርተ፣ “አያገባኝም” ብሎ ከኃላፊነት መሸሽ፣ አይቻልም፡፡ ምክንያም፣ ማኅበረሰብ ውስጥ እስከኖርክ ድረስ፣ አንተ ብታምንበትም ወይም ባታምንበትም፣ አያገባኝም ብለህ ተሸሽገህ የምታመልጠው ነገር የለም፡፡ የማኅበረሰቡ አካል ነህና፡፡

እንዲያውም፤ “እኔን አይመለከተኝም” ብሎ ማሰብ በራሱ፣ ለሳርተ በተዘዋዋሪ መልኩ ሥርዓቱ እንዲቀጥል አስተዋጽዖ የማድረግ ዝምታዊ ድጋፍ ነው፡፡ በመሆኑም፤ “አይመለከተኝም” የሚለው አቋም፣ ይፋ ያልወጣ የሥርዓቱ ድጋፍ እና ወገናዊነትም ነው፡፡ ምሁራን “አይመለከተንም” የሚለውን ሰበብ ተሻግረው፣ የድርሻቸውን ኃላፊነት በነቃ መልኩ በመሳተፍ፣ ለሰው ልጅ መብት እና ነጻነት ተሟጋች መኾን አለባቸው፡፡

ለ- ባለቅኔውና የሥነ-ጽሑፍ መምህሩ ደበበ ሰይፉም፤ ከዣንፖል ሳርተ ባልተናነሰ፣ ስለ ምሁሩ ዝምታ እና “አይገባኝም” ባይነት፣ አንዲት የማትረሳ ግጥም “ጥሬ ጨው በሚል ርዕስ” ጽፏል፡፡

መስለውኝ ነበረ፣

የበቁ የነቁ፣

ያወቁ የረቀቁ፣

የሰው ፍጥረቶች፣

ለካ እነሱ ናቸው፣

ጥሬ ጨው…ጥሬ ጨው፣

ጥሬ ጨዋዎች፣

መፈጨት- መሰለቅ- መደለዝ- መወቀጥ-

መታሸት- መቀየጥ

ገና እሚቀራቸው፣

“እኔ የለሁበት!

ዘወትር ቋንቋቸው፡፡

ምሁሩ፤ ምንጊዜም በሚነሳ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሁሉ መናገር ወይም መጻፍ ይገባዋል፤ የሚል አቋም የለኝም፡፡ ነገር ግን፤ ከሙያው ጋር በተያያዘ ጉዳይ፣ በቀጥታ የሚመለከተው ርዕስ ሲመጣ፣ ለምሳሌ፡- አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር፣ የትምህርት ጥያቄ ቤቱ ድረስ ሲመጣ፣ እንደ መምህርነቱ የራሱን አስተያየት፣ ጥያቄ ወይም ሒስ ማቅረብ ይኖርበታል እንጂ፣ እንዴት አይመለከተኝም ብሎ አርምሞን ሊመርጥ ይችላል፡፡

የአንቶኒዮ ግራምሺ ዕይታ፡- “ምሁር እና መንግሥት”

ዶ/ር ዓለማየሁ በመጽሐፉ አንቶኒዮ ግራምሺ ስለ ምሁሩ ያለውን አመለካከት በጥቂቱ ገልጾልናል፡፡ ከዶ/ር ዓለማየሁ ሰፋ ባለ፤ የአንቶኒዮ ግራምሺን የምሁራን ዕይታ በተመለከተ ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ በጥሩ ሁኔታ እንዳተተው፡-

“ግራምሺ ‘Traditional’ ወይም ‘Oppressive intellectual’ እና ‘organic intellectual’ በማለት በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ ‘oppressive’ የሚላቸው ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው የሚሠሩትን ነው፡፡ እነዚህ ምሁራን ከጥንት ጀምሮ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ምሁራን ተብለው የሚጠሩና፣ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ፈላስፎች፣ አስተማሪዎች፣ አርቲስቶች፣ ሐኪሞች፣ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች፣ የሕግ ሊቃውንት፣ የጦር መሪዎች፣ የእምነት አባቶችና ሊቃውንትን ያካትታል።”

“እነዚህ ኃይሎች፣ ልሒቃን በመሆናቸው ከሰፊው ሕዝብ የቀን ተቀን ሕይወት ራቅ ያለ ግንኙነት ይኖራቸዋል። ‘ትራዲሺናል’ ምሁራን የሕዝቡን አስተሳሰብና ዓለማዊ ዕይታ በመቅረጽና ሕዝቡን በመወከል፣ ፖለቲካዊ ሥርዓቱንና ገዢውን ኃይል በመደገፍ፣ መንግሥታዊ ቢሮክራሲውንም ሆነ ሲቪል ማኅበረሰቡን በማጠናከር የአገሪቱን እርምጃ በመወሰን ሥርዓቱ ክትያ እንዲኖረው ብሎም ህልውናው ተጠብቆ እንዲኖር ተግተው ይሠራሉ።”

“‘ኦርጋኒክ’ ምሁራን በአንጻሩ ወደ ሥልጣን ከሚመጣ ቡድን ወይም ኃይል ጋር አብረው የሚመጡ ሲኾኑ፤ የዚያን ቡድን አካሔድ የሚተልሙና፣ ርዕዮተ-ዓለም የሚቀርፁ ናቸው። በተለያዩ ፖለቲካዊ ኃይሎች መካከል በሚደረገው የሐሳብ የበላይነት (Hegemony) ትግል ውስጥ፣ የራሳቸው ‘ስፔሻላይዝድ’ ሥልጠና ያላቸውና የፖለቲካዊ መሪነት ሚና የሚጫወቱ “ኦርጋኒክ ምሁራን” ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል። ማንኛውም ለሐሳብ የበላይነት የሚታገል ቡድን፣ የራሱን ‘ኦርጋኒክ’ ምሁራን በማሳደግ፣ በ‘ትራዲሺናል’ ምሁራን ላይ የበላይነቱን መጨበጥ ካልቻለ፣ የመሪነት ሚናውን አሳልፎ መስጠቱ የማይቀር ነው።”

“‘ኦርጋኒክ’ ምሁራን፤ በሕዝቡ የቀን ተቀን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በስፋት በመሳተፍ፣ የማኅበራዊ መሠረቶቻቸውና፣ የድርጅታቸው አስተሳሰብ፣ በሕዝቡ ውስጥ እንዲሠርፅና ተቀባይነት እንዲያገኝ ይሠራሉ። ምሁራኑ በተለያየ የትምህርት መስክ ቢሰለጥኑም፣ ፖለቲካዊ እምነታቸው ግን ተመሳሳይና ወጥ ነው።”

“በሐሳብ የበላይነት ትግል ውስጥ፣ በቅርብ ጊዜ ሥልጣን የያዘ ኃይልና፣ ከእርሱ ቀድሞ ሥልጣን ላይ የነበረው ገዢ ኃይል፣ የሚታገሉት [በአንድ መልኩ] ምሁራዊ የበላይነትን ለመጨበጥም ጭምር ነው። ፖለቲካዊ ሥልጣንንና የመንግሥትነት ኃይል መቆጣጠር ብቻ የበላይነትን ዘላቂ ስለማያደርግ፣ በተቃራኒ ጎራዎች የቆሙ ምሁራን የሐሳብ ፍጭት በማድረግ፣ ተቋማትንና መዋቅሮችን በመቆጣጠርና፣ አቅጣጫ በመስጠት፣ የአስተሳሰብ ትግሉን ሥጋ ለብሶ እንዲታይ የሚያደርጉ አካላት (“Agent”) ናቸው።”

“ወደ ሥልጣን የሚመጣ አዲስ ኃይል፣ በመጀመሪያ የሚያጋጥመውም ቅራኔ ከ“ትራዲሺናል” ምሁራን ወይንም፣ ከቀደመው ሥርዓት “ኦርጋኒክ” ምሁራን አካባቢ ነው። እነዚህ ምሁራን በስፋት በተንሰራፉባቸው የሲቪልና ወታደራዊ ቢሮክራሲ፣ የትምህርት፣ የፕሮፖጋንዳና ባሕል ተቋማት ውስጥ ደግሞ፣ ተቃውሞው ጠንከር ብሎ ሊታይ ይችላል። ከዚህ አንጻር፤ አዲሱ ኃይል ሊከተለው የሚችለው ስትራቴጂ፣ የራሱን “ኦርጋኒክ” ኃይል በመፍጠር፣ ከ“ትራዲሺናል” ምሁራን መካከል የተቻለውን ያህል ወደ ራሱ በመሳብና በማዋሐድ፣ ቀሪውን ደግሞ በማንኛውም መንገድ የሐሳብ የበላይነት እንዳይኖረው መጫን ነው።”

(ማሰታዎሻ፡- ይህ ጽሑፍ ከዚህ ቀደም “ውይይት” በተሰኘችው መጽሔታችን ላይ ወጥቶ ከነበርው ጽሑፍ ተቀንጭቦ የቀረበ ነው)

October 21, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *