ከምርጫ ወደ አመጽ ወይስ በምርጫ ወደ ዴሞክራሲ?
ሕግ

ከምርጫ ወደ አመጽ ወይስ በምርጫ ወደ ዴሞክራሲ?

ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት ያራዘመችውን ስድስተኛውን አገር ዐቀፍ ምርጫ በተያዘው ዓመት ላይ ለማድረግ ዝግጅት ጀምራለች፡፡ በዘንድሮ ዓመት ለማድረግ የታሰበውን ምርጫ እስካሁን በአገሪቱ ከተደረጉ አምስት ምርጫዎች በተሻለ መልኩ ነጻ እና ፍትሐዊ ለማድረግ በሚል ቀድሞ የነበሩ የምርጫ ማስፈጸሚያ ደንቦች እና መመሪያዎች በአዲስ መልክ እንዲሻሻሉ ተደርገዋል፡፡ ምርጫ ቦርድም በአዲስ መልክ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መንግሥት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ በማድረግ ምርጫውን ቢያራዝምም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መከናወን አለበት የሚል አቋም ይዞ ክልላዊ ምርጫ አካሂዶ መንግሥት አዋቅሯል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው እንዳልተደረገ ይቆጠራል የሚል ውሳኔ ማሳለፉ አይዘነጋም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እየተከላከሉ ምርጫ ማድረግ ይቻላል የሚል ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥቱ በተያዘው ዓመት ስድስተኛውን አገር ዐቀፍ ምርጫ ለማድረግ አቋም ቢይዝም፣ አገሪቱ ካለችበት አንጻራዊ ሁኔታ ምርጫውን በዚህ ጊዜ ማድረግ ይቻላል በሚለው ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬም የጋራ አቋም ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶችን እና ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀምጣሉ፡፡
“ምርጫ ማድረግ የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡ ሆኖም የሚደረገው ምርጫ ምን ዓይነት ምርጫ ነው? የሚለው በሚገባ ሊጤን ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም ሲደረጉ እንደነበሩት ወይም በቅርቡ በትግራይ እንደተደረገው ዓይነት ምርጫ ከሆነ በአገር ህልውና ላይ መቀለድ ነው፡፡ ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር የሚደረግበትን መንገድ የሚጠርግ በዓይነቱ አዲስ የሆነ ምርጫ ለማድረግ ቁርጠኝነቱ ካለ ግን ከወዲሁ ሰፊ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በእኔ አስተያየት ችግሩ የጊዜ እጥረት ሊሆን አይችልም፡፡ ችግሩ የገዥው ፓርቲ ቁርጠኝነት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁርጠኝነቱ ካለው ሁሉም ነገር ይቻላል፡፡ ገዥው ፓርቲ ለዴሞክራሲ ቁርጠኛ መሆኑን ካስመሰከረ ጽንፈኛ የሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅድመ ምርጫና ድኅረ ምርጫ ግጭት ሊፈጥሩ ቢሞክሩ እንኳ ተከታይ አይኖራቸውም፡፡ ሕዝቡ ራሱ ነው የሚቀጣቸው እና ለፍትሕ አካል አሳልፎ የሚሰጣቸው፡፡” ይላሉ ካሳሁን ብርሃን (ዶ/ር)፡፡
ካሳሁን (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፡- “ዛሬም እንደተናንቱ ኳሷ ያለችው በገዥው ፓርቲ ሜዳ ላይ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ለዴሞክራሲ ግንባታ ቁርጠኝነት ካለው የጊዜ ጉዳይ እምብዛም አሳሳቢ አይደለም፡፡ ለዴሞክራሲ ዝግጁ የሆነ ዝም የተሰኘ ብዙሃን (silent majority) አለ፡፡”
ከሲራራ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኅብር ኢትዮጵያ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው ለምርጫው እንዲሟሉ የጠየቋቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሁንም ስላልተሟሉ ምርጫው መራዘም አለበት የሚል አቋም እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ “ከዚህ ቀደም ለጋራ ምክር ቤቱ ለውይይት የቀረቡ ሰባት አጀንዳዎች ውይይት ሳይደረግባቸው እና ውሳኔ ሳያገኙ ወደ ምርጫ መግባቱ ምርጫውን ኢፍትሐዊ ያደርገዋል፡፡ ውጤቱም ተመልሰን ወደ አመጽ አዙሪት እንድንገባ የሚያደርግ ነው” ይላሉ፡፡
በአጀንዳዎቹ ውስጥ የምርጫ ቦርድን ዝግጁነት እና የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን በተመለከተ እንዲሁም የአዲስ አባባ የባለቤትነት ጥያቄን የሚመለከቱ ጉዳዮች መኖራቸውን የሚያነሱት አቶ ግርማ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ሳይያዝ የሚደረግ ምርጫ ቀድሞ ከነበሩት 5 ምርጫዎች እምብዛም የሚለይ አይሆንም ይላሉ፡፡
“ከምርጫ በፊት ክፍፍል በፈጠሩ ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመርህ ደረጃ መግባባት ሊኖር ይገባል፡፡ ካልሆነ እነዚህ ጉዳዮች በምርጫው ማግስት የልዩነትና የግጭት መሆናቸው አይቀርም” ይላሉ አቶ ግርማ፡፡ ምርጫ ከመደረጉ በፊት ውይይት ሊደረግባቸውና መፍትሔ ሊበጅላቸው የሚገቡ አንኳር አገራዊ ጉዳዮች መኖራቸውን አበክረው የሚናገሩት አቶ ግርማ ሁሉም ሆደ ሰፊና አርቆ አሳቢ ሆኖ ራሱን ለሰጥቶ መቀበል ዝግጁ ሊያደርግ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
“የምርጫ ቦርድ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ባልተደራጀበት እና የዴሞክራሲ ተቋማት በገለልተኝነት ባልታነጹበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ረብ የለሽ ነው” የሚሉት አቶ ግርማ ተቋማቱ በአግባቡ እስኪደራጁ እና በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ አለመረጋጋቶች እና ግጭቶች እልባት እስኪያገኙ ስድስተኛው አገር ዐቀፍ ምርጫ እንዲራዘም ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱ ሰላም ሳይመለስ እና የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሳይፈቱ የሚደረግ ምርጫ አገሪቱን ወደባሰ ምስቅልቅል ሊከታት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም አቶ ግርማ ጨምረው አብራርተዋል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ ቀደም ብሎም ምርጫው ለአንድ ዓመት እንዲራዘም የሚጠይቅ ሰነድ ለመንግሥት ማስገባቱን የሚያስታውሱት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ በሰነዱ ላይ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ባለበት ሆኖ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በመበተን፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪክ ማኅበራት የተዋቀረ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚውን እየተቆጣጠረ የሚሄድበትን ምክረ ሐሳብ ለመንግሥት ቢያቀርቡም መንግሥት ተገቢውን ምላሽ እንዳልሰጠ ይናገራሉ፡፡
በተያዘው ዓመት ላይ ምርጫ ለማድረግ መታሰቡ ላይ ቅራኔ እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ ቀጀላ ከምርጫው በፊት የታሰሩ የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮች ሊፈቱ እንደሚገባ ገልጸው፣ የፖለቲካ አመራሮች ባላቸው የፖለቲካ እይታ ምክንያት በእስር ቤት ሆነው የሚደረግ ምርጫ ነጻ እና ፍትሐዊ ይሆናል የሚል እምነት በፓርቲያቸው በኩል እንደሌለ አብራርተዋል፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች መፍትሔ ካላገኙ ለምርጫው ትልቅ መሰናክል ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳለባቸው የሚያነሱት አቶ ቀጀላ፣ ፓርቲዎች እርስ በርስ በሚያደርጉት ውይይት የችግሮቹን ስፋት ማጥበብ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
“ፓርቲዎች የቱንም ያህል የፖለቲካ ልዩነት ቢኖራቸውም የአገር ጉዳይ ነውና ለመነጋገርና አብረው ለመሥራት ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ አለባቸው፡፡ ምርጫ ከመደረጉ በፊት በርከት ያሉ የውይይት መድረኮች እየተዘጋጁ ወሳኝ የፖለቲካ ጉዳዮች ክርክርና ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ኦነግም ለአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል” ያሉት አቶ ቀጀላ፣ ፓርቲያቸው የአማራን ሕዝብ ወክለው ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርጎ መግባባት ላይ በደረሱባቸው ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት አቋም መያዙን በአብነት ያነሳሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልል እና አማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መካከል ስምምነት ላይ ለመድረስ ላለፉት ወራት ተደጋጋሚ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ ቀጀላ፡- “በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ለሚነሱ ግጭቶች ምክንያቶቹ እኛ ፓርቲዎቹ እንዳንሆን በማሰብ በፓርቲዎቹ መካከል ውይይቶችን ስናደርግ ቆይተናል፤ በውይይታችን መግባባት በቻልንባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ስምምነት ተፈራርመናል” ብለዋል፡፡
ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ ጣሂር ሙሐመድ ውይይቱ በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሰፋ የሐሳብ እና የታሪክ ትርክት በመኖሩ ምክንያት ፓርቲዎቹ ተቀራርበው እንዲሠሩ ለማስቻል ታስቦ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና አብን ከሌሎች ፓርቲዎችም ጋር ውይይቶችን እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
“በፓርቲዎች መካከል የተደረገው ስምምነት ፖለቲካዊ ስምምነት ነው፤ የሕግ አስገዳጅነትም ያለው አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ልኂቃን መካከል ያለውን ችግር ለማረቅና ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ የማያቋርጥ ውይይትና ንግግር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እኛም በቅርቡ ከኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር በሕገ መንግሥት ጉዳይ፣ በሕዝብ ቆጠራ ጉዳይ ላይ በጋር ለመሥራት ተስማምተናል በቀጣይ አፈጻጸሞችን እየገመገምን አብረን እንሠራለን፡፡ ፓርቲያችንም በዚህ ላይ ጠንካራ አቋም አለው” ብለዋል፡፡
“ውይይቱ በሁለቱ ትልልቅ ብሔሮች መካከል ብቻ የሆነው በሁለቱ ብሔሮች መካከል፣ በተለይም በልኂቃኑ ዘንድ ተደጋጋሚ ግጭቶች በመኖራቸው እና በምሁራኖቻቸው መሃል ያለው የተራራቀ የሚመስለውን ልዩነት ለማጥበብ በማሰብ ነው” ያሉት አቶ ጣሂር በቀጣይ የሌሎች ፓርቲዎች ተሳትፎ ታክሎበት ውይይቱ ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በተናጠል የሚደረጉ ስምምነቶች እና ውይይቶች ክፋት ይኖራቸዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው ያነሱት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው በኦሮሚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በአማራ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለውን የታሪክ ትርክት ልዩነት ለማጥበብ የሚደረጉ ውይይቶች ዓላማቸው በጎ እስከሆነ ድረስ መበረታታት እንዳለባቸው አቶ ጣሂር ጨምረው ገልጸዋል፡፡
“የጥላቻ ፖለቲካን እና የተሳሳተ የታሪክ ትርክትን ከሌሎች የብሔረሰብ ወካይ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ለማረም እና አብሮ ለመሥራት አብን ጠንካራ አቋም አለው” ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ያሉት ጽንፍ ረገጥ አስተሳሰቦች እና ግጭቶችን ለማስቀረት የሲቪክ ማኅበራቱ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፍትሕ አካላት የሚሳተፉበት ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባም አቶ ጣሂር ይናገራሉ፡፡
አብን በማንኛውም ሰዓት ምርጫ ይደረግ ቢባል ምርጫውን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት አቶ ጣሂር፣ ከሁሉ አስቀድሞ ለምርጫው ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ የሰላም ችግሮች በሚመለከታቸው አካላት ሊፈቱ ይገባል ብለዋል፡፡
በአማራ እና በኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ አቋም ስምምነት ማግስት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በስምምነቱ ላይ አለመሳተፉን እና ስምምነት አለመፈረሙን አሳውቋል፡፡ ፓርቲው ለመገናኛ ብዙሃን መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሰራጨው ደብዳቤ “ኦሮ-ማራ የተባለው ስብስብ ላይ ቀደም ባሉት ጊዜያት ብንሳተፍም ስብስቡ የኅብረተሰባችንን ጥቅም የሚያስጠብቅ እና ለፊርማ የሚያበቃ ባለመሆኑ ፊርማው ላይ አልተሳተፍኩም” ብሏል፡፡
ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ የነበራቸው የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፡- “አብሮ ለመሥራት በውይይት ላይ ብንቆይም በተለይ ከሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት በኋላ በውይይት ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ጭምር በመገናኛ ብዙሃን ላይ ወጥተው ግንኙነታችንን የሚያበላሽ ንግግሮችን ሲያደርጉ ተመልክተናል፡፡ በውይይት ውስጥ ሆነን ይህንን ማድረጉ ውጤት አያመጣም በሚል ስምምነቱን ሳንፈርም አቋርጠን ወጥናል” ብለዋል፡፡
ከሲራራ ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢዜማው የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተክሌ በቀለ በበኩላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ራሳቸው በመከባበር ላይ የተመሠረተ የሰለጠነ ውይይት ማድረግ እንደሚገባቸው ይመክራሉ፡፡ “እንዲህ ዓይነት ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸው በመሀከላችን መተማመንን ይፈጥራል፡፡ ዋና ዋና የፖለቲካ ችግሮቻችን ነጥረው እንዲወጡና መፍትሔ እንዲፈለግላቸው በር ይከፍታል፡፡ ምርጫውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚያዋልድ ይሆናል” ይላሉ አቶ ተክሌ፡፡
የተሻለ መደማመጥ እና ሁሉን አካታች የሆኑ መድረኮች ሲፈጠሩ ወደ ውይይት እንመለሳለን በሚል ምክንያት የአቋም ስምምነቱ ላይ ሳይፈራረሙ ቀድሞ ፓርቲያቸው ከውይይቱ ራሱን ማግለሉን ተናግረዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ ያናገርናቸው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ኦፌኮ ከስምምነቱ ለምን ራሱን እንዳገለለ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸው ፓርቲው እስከ መጨረሻው የአቋም ስምምነት ድረስ ተሳታፊ እንደነበር እና ወደፊት ወደ መድረኩ ይመለሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ከምርጫ ወደ አመጽ ሳይሆን በምርጫ ወደ ዴሞክራሲ እንድትሸጋገር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ብልጽግናም፣ ሕወሓትም፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ዜጎችም ኀላፊነት አለባቸው” ይላሉ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ካሳሁን ብርሃን (ዶ/ር)፡፡
2013፤ ሌላ የውዝግብ ዓመት?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ምክር ቤቱ 6ተኛው አገራዊ ምርጫ በትግራይ ክልልም እንዲካሄድ መወሰኑን ለመገናኛ ብዙሃን መግለጻቸውን ተከትሎ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ “ትግራይ ምርጫ አድርጋለች፡፡ የትግራይ ሕዝብም ይወክለኛል የሚለውን ፓርቲ መርጧል፡፡ ከዚህ በኋላ በትግራይ ምርጫ ሊካሄድ የሚችለው ከአምስት ዓመት በኋላ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ምርጫ ይደረጋል ማለቱ ቀልድ ነው” ብለዋል፡፡ በትግራይ ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ክልላዊ ምርጫ መካሄዱ እና መስከረም 14 ቀን 2013 ቀን የክልል መንግሥት መመሥረቱ አይዘነጋም፡፡ አዲሱ የክልል ምክር ቤት ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤልን (ዶ/ር) የክልሉ ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል፡፡
ይህን የትግራይ ክልል እና የፌዴራል መንግሥቱን የቀጠለ እሰጥ አገባ ተከትሎ በርካቶች ይህ ዓመት የግጭት ዓመት እንዳይሆን ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ካሳሁን (ዶ/ር)፡- “በትግራይ ክልል በዚህ ዓመት ምርጫ ይደረጋል የሚለው ውሳኔ የማይመስልና ለግጭት በር የሚከፍት ነው፡፡ በመሠረቱ የትግራይ ክልል መንግሥት በክልል ደረጃ ምርጫ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ምንም እንኳ ምርጫውን ያደረጉበት ዓላማ የሕወሓትን ተቀባይነት ከፍ ለማድረግ ቢሆንም ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመውበታል” ይላሉ፡፡
“የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትና የትግራይ ክልል አመራሮች አንዱ ለሌላው ዕውቅና መስጠት ይገባቸዋል፡፡ ችግሩ አንዱ ለሌላው ዕውቅና አልሰጥም ማለቱ ነው፡፡ ትናንትና በአንድ ደርጅት ስር ሆነው ሕዝብ ሲበድሉ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ደግሞ መነጋገር አቅቷቸው ወደ ሌላ ግጭት ገብተው አገር ሊበድሉ አይገባም” የሚሉት ደግሞ የኢዜማው አቶ ተክሌ በቀለ ናቸው፡፡
በፌዴራል መንግሥት በኩል ትልቅ የብስለት ጉድለት መኖሩን የሚገልጹት የፖለቲካል ሳይንስና የአንትሮፖሎጂ ምሁሯ ኬት ማንከስ በበኩላቸው፡- “በማያጠራጥር ሁኔታ ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ከዚህ በኋላ ያለው ብቸኛ አማራጭ ከትግራይ ክልል መንግሥት ጋር መሥራት ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ጥበብ በተሞላበት መንገድ ጉዳዩን ከያዘው በጊዜ ሂደት የሕወሓት ድጋፍ እየተዳከመ መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ ሕወሓትን ይበልጥ የሚያጠናክረው ከፌዴራል መንግሥቱ የሚነሳው ግጭት ነው፡፡ ስለሆነም የፌዴራል መንግሥት ሕወሓትን ከማጠናከር መቆጠብ፣ የሕወሓት አመራሮች በአገር ዐቀፍ ደረጃ ሊያደርጉ የሚችሉትን የጥፋት ተግባር በንቃት መከታተል እና የራሳቸውን ክልል እንዲያስተዳድሩ መፍቀድ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው” ይላሉ።
(ይስሐቅ አበበ እና ዳዊት ዋበላ)

 

 

October 4, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *