በወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተሰጠ አስተያየት | በላይነው አሻግሬ
ሕግ

በወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተሰጠ አስተያየት | በላይነው አሻግሬ

በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ እየተሠራበት ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ በ1954 ዓ.ም የታወጀው ነው፡፡ ይህ ሕግ ዋና የወንጀል ሥነ-ሥርዓ ሕግ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ዋና ዓላማው በመሠረታዊ ሕግጋት ውስጥ የተረጋገጡት የዜጎች መብቶችና ግዴታዎች በፍትሕ ሂደት ውስጥ የሚመሩበት ሥርዓት ነው፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ብዙ ጊዜ በአገዛዞች ሲጠመዘዝ እንደነበር እና አገዛዞቹ በሚፈልጉበት መንገድ የወንጀል ጉዳይ አልሄድ ሲላቸው ልዩ ልዩ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግን ሲያወጡ ብዙ ጊዜ ታዝበናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢሕአዴግን የሚስተካከል የለም፡፡

ኢሕአዴግ ያወጃቸው የፀረ-ሙስና አዋጅ እና የፀረ-ሽብር አዋጅ በተለይ የራሱን ሥልጣን ለማራዘም እና አገዛዙን ለማጥበቅ ሲል በመሠረታዊ ሕግጋት የተረጋገጡ የዜጎችን መብቶች የሚያጣብቡ የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎችን ማስቀመጡ  አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህ ሕግጋት በተጨማሪ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር እና የፋይናንስ ሥርዓትን ሽብርን በገንዘብ መደገፍን ለመቆጣጠር የወጡ አዋጆች አንዳንድ የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎችን ማካተታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ እነዚህ አዋጆች የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎች እንዲበታተኑ አድርጓል፤ የዜጎች መብቶችንም ማጣበባቸው ይጠቀሳል፡፡

ባለፈው ሳምንት ከሰማናቸው ዐበይት ዜናዎች መካከል ደግሞ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ረቂቅ በሕዝብ ተወካዮች ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ ከሃያ ሦስት ዓመታት ወዲህ በረቂቅነት ሲንከባለል ቆይቶ አሁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሊጸድቅ ትንሽ ቀናት የቀረው ይመስላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የረቂቁን አዋጅ የተወሰኑ ድንጋጌዎችን እንፈትሻለን፡፡

ረቂቁ ብዙ ጊዜ ሲወጣ ስለነበር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው በመቼ ዓመተ ምሕረት የተረቀቀው እንደሆነ የቅርብ ምንጭ አላገኘሁም፡፡ እኔ በበኩሌ በ2002 እና በ2009 ዓ.ም የተረቀቀው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ረቂቅ አዋጅ በእጄ ይገኛል፡፡ ይህ ጽሑፍ በ2009 ዓ.ም. በወጣው ረቂቅ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡

1) የተፈጻሚነት ወሰን፡-  የ2009 ዓ.ም. ረቂቅ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና ማስረጃ ሕግ አንቀጽ 1 መሠረት የአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕግ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጉዳዮች ሁሉ ነው በማለት አስቀምጦታል፡፡ የ1996 ዓ.ም የወንጀል ሕግ ምንም እንኳ እናት ሕግ ቢሆንም ነገር ግን ሁሉንም ዓይነት የወንጀል ይዘቶች ይዟል ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በርካታ አዋጆች የወንጀል ድንጋጌዎችን እንዲያካትቱ የተደረገው፡፡ ስለዚህ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ተፈጻሚ ሊሆን የሚገባው በሁሉም የወንጀል ድንጋጌዎችን በያዙ ሕግጋት ላይ እንጅ በ1996 ዓ.ም የወንጀል ሕግ ብቻ ሊሆን አይገባውም፡፡ ረቂቁ “የተፈጻሚነት ወሰን” የሚለው ግልጽነትም ይጎድለዋል፤ ምክንያቱም ወሰኑ የወንጀል ዓይነቶችን ብቻ ለማመለክት ይሁን ወይም ሕጉ ተፈጻሚ የሚሆንበት መልክአ ምድራዊ ወሰን (በሕግ ቋንቋ “የሥልጣን ክልል”) ለመረዳት ያዳግታል፡፡ ስለዚህ ረቂቁ የተፈጻሚነት ወሰኑን ዘርዘር ቢያደርገው መልካም ነው፡፡

2) ዓላማ፡- የረቂቁ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (1) የሕጉን ዓላማ ሲዘረዝር “…በሕገ-መንግሥቱ የተረጋገጡትን የግለሰብ መብቶችን በማስከበር…” የሚል ሐረግ ይዟል፡፡ ከዚህ ላይ የግለሰብ መብቶችን የያዙ ሕግጋት ሕገ-መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶችና ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸው የተለያዩ ስምምነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሕግጋት የአገሪቱ የሕግ አካል እንደሆኑ ሕገ-መንግሥቱ በግልጽ ስላስቀመጠ፣ ረቂቁ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ እነዚህን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች እና ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸውን ስምምነቶች በግልጽ ማካተት አለበት፡፡

3) የፍትሕ ተቋማት፡- የረቂቁ አንቀጽ 18(3) የፍትሕ ተቋማት ብሎ የዘረዘራቸው ፍርድ ቤት፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ ተከላካይ ጠበቆች እና ማረሚያ ቤቶችን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ በዐቃቤ ሕግ ሥር እንደሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ተከላካይ ጠበቃ በፍርድ ቤት ሥር ነው፡፡ ከዚህ ላይ አንድ ትልቅ ጉዳይ አሁንም ተዘንግቷል፡፡ ጠበቆች የፍትሕ አካላት መሆናቸው እንዴት እውቅና ሊነፈገው ይገባል? ጠበቆች በፍትሕ ሥርዓቱ ያላቸው ሚና እንዲህ አቅልለን የምንመለከተው ጉዳይ አይደለም፡፡ በጠበቃ ያልተወከለ የፍርድ ቤት ባለጉዳይ መብቱን በፍ/ቤት እንዴት ማስከበር እንደሚቸገር ለማወቅ ፍርድ ቤት ሄዶ ማየትን አይጠይቅም፡፡ ጠበቆችን የሚመለከት ሕግ የወጣው፣ አንዳንድ የወንጅል ጉዳዮች እንኳ ያለ ጠበቃ እንደማይታዩ በግልጽ የተደነገገው ጠበቆች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ከፍ ያለ ሚና ስላላቸው ነው፡፡ እንዲያውም በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዐቃቤ ሕጎችን እና ጠበቆችን በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ሰብስበው በነበረበት ወቅት፣ “ጠበቆች የፍትሕ ሥርዓቱ አካል ናችሁ” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ይህ በአንደበት የተነገረ ነገር የሕግ መሠረት ካልያዘ ከፌዝነት አያልፍም፡፡ ስለዚህ ጠበቆች የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት እንደሆኑ በሕግ ዕውቅና ተሰጥቷቸው ሚናቸውም መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ የጥብቅናው ሙያ ተገቢው ክብር ካልተሰጠው አሁንም ቢሆን ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓትና ተጠያቂ መንግሥት እንዲኖር ማድረግ አይቻልም፡፡ በመሆኑም ጠበቆች የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት እንደሆኑ በሕግ መደነገግ አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በአንደበታቸው የተናገሩትን በተግባር ላይ የሚያውሉበት ጊዜው አሁን ነው፡፡

4) አማራጭ የፍርድ ሂደት? /አንቀጽ 20/፡- ይህ የረቂቁ ድንጋጌ የዐቃቤ ሕግን ሥልጣንና ተግባር የሚደነግገው ክፍል ነው፡፡ በንዑስ አንቀጽ (3) ሥር ዐቃቤ ሕግ፣ “…የወንጀል ድርጊት ከመደበኛው የፍርድ ሂደት ውጭ ያለ አማራጭ የሚታይበትን ሥርዓት ያደራጃል” የሚል ተቀምጧል፡፡ ታዲያ ይህ በሆነበት የፍርድ ሂደቱን በምን አግባብ ወደ አማራጭ ዘዴዎች መውሰድ ይቻላል፡፡ የወንጀል ጉዳዮች በእርቅ ወይም በሽምግልና ወይም በሌላ ድርድር መፍታት የሚቻል አይደለም – በአቤቱታ የሚቀርብ የወንጀል ክስ ካልሆነ በስተቀር፡፡ በአቤቱታ የሚቀርብ ወንጀልም ቢሆን የተበደለው ሰው ራሱ ካልተወው በስተቀር ፍርድ ቤት ቀርቦ ከሆነ የሚቀር አይደለም፡፡ ስለዚህ የወንጀል ጉዳዮችን ከፍርድ ቤት ውጭ ለመጨረስ የሚደረገው ነገር የሚደገፍ አሠራር አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህ ድንጋጌ የወንጀል ጉዳዮችን ከፍርድ ቤቶች ለመንጠቅ የሚያስችል ሰፊ ቀዳዳ መስሎ ይታየኛል፡፡ በመሆኑም ይህ የረቂቁ ክፍል ተገቢ መስሎ ስለማይታይ መውጣት አለበት እላለሁ፡፡

5) በግልጽ ያልተደነገገ ወንጀል፡- የፍርድ ቤቶን የሥረ ነገር ሥልጣን በሚደነግገው ክፍል በአንቀጽ 39 ሥር፣ “በግልጽ ያልተደነገገ ወንጀል የሥረ ነገር ሥልጣን የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ነው” ይላል፡፡ እንዴት ያለ ድንጋጌ ነው? ይህ እኮ ግልጽ የሆነውን “የሕጋዊነት” መርህ ሙሉ በሙሉ አፈር ድሜ የሚያላ ነው፡፡ በወንጀል ሕግ እንደሚታወቀው አንድ ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ በወንጀል የሚያስቀጣ ነው ተብሎ በግልጽ ሕግ እስካልተደነገገ ድረስ ወንጀል ሆኖ አይቆጠርም፡፡ አንድ ድርጊት ወንጀል ነው ለማለት ድርጊቱን ወንጀል ነው ብሎ የሚደነግግ ሕግ መኖር አለበት፤ አለዚያ ግን ወንጀል ተብሎ ሊያስቀጣ አይችልም፡፡ አንድ ድርጊት በግልጽ ወንጀል ነው ተብሎ ካልተደነገገ ፍርድ ቤት ሊቀርብ አይችልም፤ ስለ ፍርድ ቤት የሥረ ነገር ሥልጣን ማውራት አያስፈልግም፡፡ ይህ ረቂቅ ድንጋጌ ግን ወንጀል ያልሆነን ድርጊት ከሕጋዊነት መርህ ውጭ በፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲታይ የሚያመቻች በመሆኑ ፍጹም መወገድ ያለበት አደገኛ ድንጋጌ ነው፡፡ ይህ ማለት እኮ ዛሬ አንድ ድርጊት ፈጽመህ በዚያ ድርጊት መንግሥት ቂም ቢይዝብህ ነገ ወንጀል ሆኖ ሊያስጠይቅህ ነው ማለት ነው፡፡ እስካሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች የተለመዱ በመሆናቸው ነው ይህን ቀላል ምሳሌ ለማስቀመጥ የተገደድኩት፡፡ ይህ ፍጹም ሕገ ወጥ እና የሰዎችን ነጻነት የሚገፍፍ፣ ለሰው ልጅ እረፍት እንዳይኖር የሚያደርግ ድንጋጌ ነው፤ መውጣት አለበት፡፡

6) ዳኛ ከችሎት እንዲነሳ የቀረበ አቤቱታ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ፡- በሕጉ ላይ የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች ከተከሰቱ ተከሳሹ ዳኛው ከችሎት እንዲነሳ ማመልከት ይችላል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 25/88 ይህ ጉዳይ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ዳኛ ከችሎት እንዲነሳ የሚቀርብ ማመልከቻ ቀርቦ በፍጥነት ውሳኔ ማግኘት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ረቂቁ አንቀጽ 62/4/ እንዳስቀመጠው ዳኛ ከችሎት የመነሳት ውሳኔ ይግባኝ የማይባልበት ነው በማለት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ አዋጅ ቁጥር 25/88 እንዲሁ ይግባኝ አይባልበትም ብሏል፡፡ ግን ለምን? ዳኛ ከችሎት እንዲነሳ መጠየቅ መብት ከሆነ በዚህ መብት ላይ የሚሰጥ ውሳኔ ይግባኝ የማይጠቀበት ውሳኔ ከሆነ በመብትነት መቀመጡ ምን ትርጉም አለው? ከችሎት እንዲነሳ በተጠቀው ዳኛ እና በተከሳሹ መካከል እስከ መጨረሻ ውሳኔ ድረስ የሚደርስ በመሆኑ በተለይ ከችሎት እንዲነሳ የተጠየቀው ዳኛ በተከሳሹ ላይ ገለልተኛ የሆነ እይታ ላይኖር ይችላል፤ ይህ ደግሞ ዳኛው በነጻነት እንዳይሠራ ሊያደርገው ስለሚችል አመዛዛኝ የዳኛ ኅሊና የሚዛባበት ጊዜ ይሆናል፡፡ ይህን ኅሊናዊ ግምት ብንተወው እንኳ ዳኛ ከችሎት እንዲነሳ መጠየቅ መብት ከሆነ በዚህ መብት ላይ የሚሰጥ ውሳኔ ይግባኝ መንፈግ ትክክለኛ የሕግ አቀራረጽ መስሎ አይታይም፡፡ ባይሆን የተቀላጠፈ ፍትሕ ያስተጓጉላል ተብሎ ከሆነ ይግባኙ በአፋጣኝ የሚታይበትን መንገድ ማበጀት እንጅ የይግባኝ መብትን ማስቀረት ተገቢ መስሎ አይታይም፡፡

7) የሞተ ሰው አካልን መመርመር፡- የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 99/1/፣ “መርማሪ ፖሊስ በተፈጸመ ወንጀል የሞተ ሰው ሲኖር ወይም አካሉ የተደበቀ ወይም የተቀበረ ወይም በሌላ ሁኔታ የተበላሸ የተረዳ እንደሆነ በጥንቃቄ እንዲነሳ ወይም እንዲወጣ … ማድረግ አለበት” በማለት ደንግጓል፡፡ ከዚህ ላይ ደንብ ቁጥር 299/2005 መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ደንብ አንቀጽ 38(2) መሠረት “በፍርድ ቤት ትአዛዝ ወይም አግባብ ባለው ሕግ መሠረት የመቃብሩ ቦታ ለሕዝብ ጥቅም ሲፈለግ ካልሆነ በስተቀር አስከሬንን ከተቀበረበት ጊዜ ጀምሮ ሰባት ዓመት ሳይቆይ ከተቀበረበት ሊወጣ አይችልም” በማት በግልጽ ደንግጓል፡፡ ረቂቁ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ከደንብ ቁጥር 299 ጋር ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ነው፡፡ ስለዚህ መርማሪ ፖሊስ የግድ የተቀበረን አስከሬን ለምርመራ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው አስከሬኑ ከተቀበረ ከሰባት ዓመት በፊት ለማውጣት የፍርድ ቤት ትእዛዝ ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ አስከሬንን ከተቀበረበት ማውጣት ልዩ ሁኔታ በመሆኑ ይህ ድንጋጌ በጠባቡ መደንገግ እና አፈጻጸሙም በጠባቡ እንዲሆን ተደርጎ ሕጉ መቀረጽ አለበት፡፡ አለዚያ ፖሊስ ሙታንን እንኳ እረፍት የለሽ ማድረጉ አይቀርም፡፡

8) ጊዜ ቀጠሮ ከተጠናቀቀ በኋላ ክስ አለመቅረብ፡- የጊዜ ቀጠሮ ክርክር ወይም ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ ዐቃቤ ሕግ ወዲያውኑ መደበኛ ክስ ማቅረብ አለበት፡፡ ረቂቁ ሕግ ግን ዐቃቤ ሕጉ ክስ እስኪመሠርት ድረስ ተጠርጣሪው ለ15 ቀናት ማረፊያ ቤት እንዲቆይ “ፍርድ ቤቱ ሊወስን ይችላል” ይላል፡፡ (ረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 124/5/) ከዚህ ላይ ተጠርጣሪው ለ15 ቀናት በማረፊያ ቤት ሊቆይ ይችላል አለ እንጅ የግድ 15 ቀናት በማረፊያ ቤት ይቆያል ማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ ፍርድ ቤቶች ለዜጎች ነጻነት የሚቆሙ ከሆነ የተጠርጣሪዎችን ነጻ ሆኖ መገመት ቅድሚያ ሰጥተው ተጠርጣሪ በዋስትና እንዲወጣ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በዘልማድ እንደሚታየው ጊዜ ቀጠሮ ከተጠናቀቀ በኋላ “የክስ መመሥረቻ” ተብሎ ለዐቃቤ ሕጉ 15 ቀናት ይሰጡትና በእነዚህ ቀናት ውስጥ መደበኛ ክስ እንዲመሠርት ይደረጋል፡፡ ነገር ግን በዚህ የ15 ቀናት ልዩነት ውስጥ ተጠርጣሪው በዋስትና መውጣትን የማይከለክለው እንደሆነ ፍርድ ቤቶች ዋስትናውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ ተጠርጣሪው በማረፊያ ቤት ሆኖ ዐቃቤ ሕጉ በ15 ቀናት ውስጥ መደበኛ ክስ ሳይመሠርት ቢቀር ውጤቱ ምን ይሆናል የሚለው በግልጽ አለመቀመጡ ነው፡፡ የአገራችን ፍርድ ቤቶች ዝምተኛ እና ዘገምተኛ እንደመሆናቸው አንድ ሰው ያለ ምንም ክስ ማረፊያ ቤት መቆየት እንደሌለበት ቢታወቅም ነገር ግን አቤቱታው ለፍርድ ቤቶች ቢቀርብላቸው ይህ ነው የሚባል መፍትሔ ሲሰጡ አይታዩም፡፡ ስለዚህ የምርመራ መዝገቡ ከተጠናቀቀ በኋላ በ15 ቀናት ውስጥ መደበኛ ክስ ያልቀረበበት ተጠርጣሪ ወዲያውኑ መለቀቅ እንዳለበት ረቂቁ አዋጅ በግልጽ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ዳተኛውን ዐቃቤ ሕግ በፍጥነት ክስ እንዲመሠርት እና ተጠርጣሪው ያለ አግባብ ማረፊያ ቤት እንዳይቆይ ሊታደገው ይችላል፡፡

9) ዋስትና፡- ዋስትና ሕገ-መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ ዋስትና “አንድ የተያዘ ወይም የተከሰሰ ነው ነጻ ሆኖ የመገመት” መብቱ የሚረጋገጥበት መብት ነው፡፡ ዋስትና መብት ሲሆን በዋስትና አለመውጣት (ዋስትና መከልከል) ደግሞ ልዩ ሁኔታ ነው፡፡ ረቂቁ አዋጅ ዋስትና የሚያስከለክሉ ወንጀሎች በማለት በአንቀጽ 154 ሥር ዘርዝሯቸዋል፡፡ እነዚህ ዋስትናን የሚያስከለክሉ ድንግጌዎች በዝተዋል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ዋስትና የሚያስከለክልበት ሁኔታ ጠባብ ነው፤ ምንም እንኳ በኋላ ዘመን የፀረ-ሙስና አዋጁ የዋስትናን ጉዳይ ቢያጠበውም፡፡

ረቂቁ የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ደግሞ ዋስትና የሚያስከለክሉ የወንጀል ዓይነቶችን ዝርዝር ጨምሯል፡፡ ይህ ማለት በዋስትና የመውጣት መብት እየተጣበበ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተከሳሾች መብት በጣም የሚያጠብ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ በዋስትና መውጣት የሚከለክለው ድንጋጌ ሰፊ መሠረት ካለት ልዩ ሁኔታ መሆኑ ቀርቶ መርህ ሊሆን እየተንደረደረ ነው ማለት ነው፡፡ መሆን ያለበት ግን መርሁ (በዋስትና መውጣት) ሰፊ ሆኖ ልዩ ሁኔታው (ዋስትና መከልከል) ጠባብ እንዲሆን ነው፡፡ በመሆነኑም ረቂቁ አዋጅ ዋስትና ማጥበብ የለበትም የሚል እምነት አለኝ፡፡

ይቆየን፡፡

(አቶ በላይነው አሻግሬ ጠበቃና የሕግ አማካሪ ናቸው፡፡ በኢሜል አድራሻቸው belyub@gmail.com ላይ ይገኛሉ፡፡)

October 21, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *