ገንዘባችሁን በባንክ አስቀምጣችሁ [ብራችሁን] የዋጋ ንረት ይብላው ተብሎ ተፈርዶብናል
ሐተታ, ሕግ

ገንዘባችሁን በባንክ አስቀምጣችሁ [ብራችሁን] የዋጋ ንረት ይብላው ተብሎ ተፈርዶብናል

የኢትዮጵያ መንግሥት ባሳለፍነው ሳምንት በአገሪቱን የመገበያያ ገንዘብ ኖት ላይ ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል ለዚህ እርምጃው ምክንያት ናቸው ያላቸውንም ጉዳዮች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የሕገ-ወጥ ገንዘብን መቆጣጠር የሚለው ይገኝበታል፡፡ ሙስናንን ለመዋጋት የሚል ሐሳብም ቀርቧል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የመገበያያ ገንዘብ ቅያሪ ማድረግ ምን ያህል ያግዛል? የሚለውን ጉዳይ በሂደት አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሕገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር ዛሬ የተጀመረ ባይሆንም በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን ተስፋፍቶ መቀጠሉን እያየን ነበር፡፡ በእነዚህ ዓመታት ከባንኮች ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መጠን ሲሸሽ እና ሲኮበልል ቆይቷል፡፡ ይህ ገንዘብ የአገሪቱን ሰላም እያወከ ኢኮኖሚውንም ሲፈታተን ነው የቆየው፡፡
በበኩሌ መንግሥት የብር ኖት ለመቀየር ማሰቡ ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታ ይችላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለውጡ ምናልባት በሕገ-ወጥ መንገድ የተከማቸውን ገንዘብ ወደ ባንክ ሥርዓት ዳግም ተመልሶ እንዲገባ እና በውጭ አገሮች የተቀመጡትን ገንዘቦች ለማምከን ዕድል ይሰጥ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሁለት ዓመት ሙሉ ገንዘቡን እንደፈለጉ ሲያሽከረክሩት የነበሩ ሰዎች ገንዘቡ እጃቸው ላይ በአትዮጵያ ጥሬ ገንዘብ (በብር) ይይዙታል ወይ? የሚለውም ጉዳይ በአግባቡ መታየት ያለበት ነው፡፡ ይህን ገንዘብ ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ አካላት የብር ቅያሪው ሊመጣ እንደሚችል አስቀድመው መተንበይ የሚችሉ ከመሆናቸው አኳያ ገንዘቡን ወደ ንብረት እንደሚቀይሩት ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡
ሌላው አሁን አገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የገንዘብ ለውጡ በዚህ ጊዜ መሆኑም እንዲሁ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የገንዘብ ቅያሪ ዕቅድ፣ የሰው ኀይል፣ የተቋማት ርብርብን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አሁን አገሪቱ ካለችበት አለመረጋጋት አንጻር እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ አንጻር እውነት በዚህ ጊዜ መሆን ነበረበት ወይ? የሚለው ቀድሞ ታስቦበት ቢሆን በጣም ጠቃሚ ነበር፡፡
ይህ የብር ኖት ቅያሪ አንደኛው ዓላማው ያደረገው ሙስናን እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ሙስና ደግሞ አብዛኛውን ያለው በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ነው፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚደረገው በእነዚሁ አካባቢዎች ነውና፡፡ ሙስና ወረቀት ሰጥቶ ወረቀት በመቀበል ብቻ የሚከናወን ጉዳይ ባለመሆኑ፣ ቅያሪው ሙስናን ለመዋጋት ይረዳል የሚለው አካሄድ እምብዛም አያስሄድም፡፡ ሌባ ሁልጊዜ በአንድ መንገድ ይሰርቃል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ገንዘብ በማዳበሪያ፣ በጀሪካን አጠራቅመው ለሚይዙት ሰዎች ግን ይህ ውሳኔ በጣም የሚያስደነግጣቸው ነው፡፡
ለገንዘብ ለውጡ ሌላኛው ምክንያት ተደርጎ የተቀመጠው የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የሚል ነው፡፡ እዚህ ላይ ቀድመን ማየት ያለብን ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ንረት ምን ዓይነት የዋጋ ንረት ነው? በምን ዓይነት ምርቶች ላይ ንረቱ የጠነከረ ነው? የሚለውን በደንብ ማየት ይፈልጋል፡፡ በዚህ አገር ያለው የዋጋ ንረት አብዛኛው በመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ ያለ ነው፡፡ ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ ስንዴ፣ ሽንኩርት በመሳሰሉ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረቱ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ እነዚህ ምርቶች በአብዛኛው ከውጭ አገር ነው የሚገቡት፡፡ ከውጭ ሲገቡ ደግሞ በውጭ ምንዛሪ ነው ተገዝተው የሚገቡት፡፡ ስለዚህ ለዚህ አገር የዋጋ ንረት መሠረታዊ ምክንያቱ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ የአገር ውስጥ የገንዘብ ኖት መቀየር የዋጋ ንረት ላይ ውስን ለውጥ ሊያመጣ ይችል ይሆናል እንጂ በታሰበው ልክ በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡
የዋጋ ንረቱ ክፍ እያለ የመጣው የሰዎች የመግዛት ፍላጎት ከፍ እየለ በመምጣቱ፣ የሰዎች ገቢ እያደገ በመምጣቱ እና የምርት እጥረት በመኖሩ ብቻ አይደለም፡፡ የዚህ አገር ብር የውጭ ምንዛሪን የመግዛት አቅሙ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ያለ እረፍት እንዲዳከም በመደረጉም ጭምር ነው፡፡ ሰው የሚገዛውን ምርት አይደለም ያጣው፤ ምርቱ እያለ ዋጋው ነው የተወደደበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ አሁን ያለው የዋጋ ንረት መንስኤው በፍላጎት ጎን ሳይሆን በአቅርቦት ጎን የሚነሳ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ የሚመረቱ ምርቶች አብዛኛው ግብዓታቸውን የሚያገኙት ከውጭ አገራት ነው፡፡ የማምረቻ ወጪያቸው በጨመረ ቁጥር ለገበያ የሚያቀርቡትም ምርት ዋጋ አብሮ ይጨምራል፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ የገንዘብ ለውጥ ማድረግ በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ያለውን የዋጋ ንረት ይቀይራል ማለት የዋህነት ነው፡፡
አንድ ሰው 1 ሚሊዮን ብር ወደ ባንክ አስገብቶ መልሶ እስኪያወጣው ድረስ ጊዜ ሊወስድበት ይችል ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ገበያው ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሊረጋጋ ይችላል፡፡ ይህ ገንዘብ ተመልሶ ወደ ገበያው ሲገባ ግን የሸሸነው የዋጋ ንረት ዳግም ተመልሶ እንደማይመጣ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ የለንም፡፡ ጋና፣ ዙምባብዌ፣ ቱርክ ተመሳሳይ እርምጃዎችን ወስደው አመርቂ ውጤትን ማምጣት አልተቻላቸውም ነበር፡፡
ሌላው ኮሮና ባለበት፣ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅም እየሠሩ ባልሆነበት፣ ሆቴሎች ሥራ አተው ባለበት፣ የሰላም ችግር ባለበት እና ምርት እንደፈለገ በማይንቀሳቀስበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን የብር ኖትን በመቀየር ዋጋን ማረጋጋት ይቻላል ብሎ ማሰብ እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡
ከዋጋ ንረቱ ባሻገር መንግሥት የገንዘብ ለውጥ ያደረገበት አንኳር ምክንያት ገንዘብ ወደ ባንክ ቤት ገብቷ ሰዎች ግብይታቸውን በኤሌክትሮኒክስ እንዲፈጽሙ ለማስቻል ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ዕቅዶች መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያለገናዘቡ እና በጨበጣ የተወሰኑ ውሳኔዎች እንደሆኑ ነው የምረዳው፡፡ በአገራችን 85 በመቶ የሚሆነው ማኅበረሰብ ኑሮውን ያደረገው በገጠር ነው፡፡ ባንክ ለማግኘት እና ወደ ባንክ ሥርዓት ለመግባት በጥቂቱ ግማሽ ቀን በላይ መጓዝ መቻል አለበት፡፡ ይህ ሰው የሞባይል ባንክ ተጠቃሚ ለማድረግ ገጠር ድረስ የገባ ኤሌክትሪክ ኀይል ይፈልጋል፤ ኔትዎርክ ይፈልጋል፡፡ ይህ ምን ያህል በመላ አገሪቱ ተዳርሷል? እንኳን ገጠር ላይ ከተማ ላይ ባንኮች በሲስተም መቆራረጥ መከራ ሲያዩ አይደለም ወይ የሚውሉት፡፡ መንግሥት ቅዠት የሚመስል ዕቅዱን ለጊዜው ያዝ አድርጎት መሠረተ ልማቱ ላይ ቢያተኩር ተመራጭ ነው፡፡ አገር አዲስ አበባ ብቻ አይደለም፡፡ ፖሊሲዎች እንደ አገር ሲወጡ ሰፊውን የገጠር ማኅበረሰብንም ታሳቢ ማድረግ መቻል አለባቸው፡፡
ባንኮችስ እርስ በርሳቸው ምን ያህል ተናበው እየሠሩ ነው? ከንግድ ባንክ ወደ አዋሽ ባንክ ገንዘብ ለማዘዋወር ሦስት ቀን በሚፈጅበት ገንዘብህን ወደ ባንክ አስገብተህ በባንክ ብቻ ገንዘብህን አዘዋውር የሚል ነገር፤ ሐሳቡ ጥሩ ቢሆንም መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ግን አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡
የኮሮና ወረርሽን ኢኮኖሚውን እያደቀቀ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ዓለም እየመከረ ያለው ገንዘባችሁን በባንክ አታስቀምጡ አውጡና ኢንቨስት አድርጉበት ነው፡፡ አገሮች በዜሮ የወለድ መጠን ብድር እንሰጣለን ገንዘባችሁን ወደ ሥራ አስገቡ በሚባሉበት ጊዜ የእኛ መንግሥት ገንዘባችሁን ወደ ባንክ አምጥታችሁ አጉሩ ማለቱ የትም የሚያደርሰው ጉዳይ አይደለም፡፡
መንግሥት በዚህ ሰዓት ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ ገበያው ላይ ተሯሩጦ ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቃ ነው መሥራት መታገል ያለበት፡፡ በአነስተኛ ሥራ የተሰማሩ ድርጅቶች ኢኮኖሚውን እንዲያነቃቁ ማበረታቻ መስጠት አለበት፡፡ ሌላው ዓለም ይህን ነው እያደረገ ያለው፡፡ በዚህ ሰዓት መንግሥት ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲገባ ሳይሆን መሥራት ያለበት ግብይቶች እንዲስፋፉ፣ ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ ነው፡፡ ዛሬም እኮ በኮሮና ምክንያት ንግዳቸው የተቀዛቀዘባቸው በርካታ ነጋዴዎች፣ አምራቾች አሉ፡፡ እነሱን በዚህ ሰዓት መደገፍ ዛሬ ላይ መሠረት ያለበት ሥራ ነው፡፡
መንግሥት አሁን ላይ እያለን ያለው ገንዘባችሁን በባንክ አስቀምጣችሁ ብራችሁን የዋጋ ንረት ይብላው ነው፡፡ ባንክ ገንዘብ ስናስቀምጥ የወለድ መጠኑ 7 በመቶ ነው፡፡ የዋጋ ንረቱ 26 በመቶ ነው፡፡ መንግሥት ለዚህ ምን አስቦ ነው ገንዘብን በባንክ አስቀምጡ የሚል አስገዳጅ ሕግ የሚያወጣው? ገንዘብ አስቀማጩ ለሚደርስበት ኪሳራ ማንን ነው የሚጠይቀው? ለኪሳራውስ ካሳ የሚከፍለው ማን ነው? መንግሥት እንዲ ዓይነት መመሪያ ሲያወጣ እታች መሬት ላይ ወርዶ ችግሮቹን ማየት መቻል አለበት፡፡ የዓለም ዐቀፍ ተቋማት ይህን አድርግ ሲሉት ቅድሚያ የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን ማማከር መቻል አለበት፡፡ የሚገለበጥ ነገር ችግሩ ይህ ነው፡፡ መደማመጥ የለም፤ የአገር ውስጥ ምሁራንን ማማከር የለም፤ መገልበጥ ብቻ ነው የተያዘው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ አደገኛ በሽታ ፈጥና ካልተፈወሰች አደገኛ ነው፡፡
(ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር))

 

 

October 4, 2020

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *