የዘር ፍጅትን ለማስቀረት | ብላታ ታከለ
ሐተታ

የዘር ፍጅትን ለማስቀረት | ብላታ ታከለ

ከሃያ ሰባት ዓመት በፊት ሩዋንዳ ወደለየለት አመጽ ገብታ በመቶ ቀናት ውስጥ ከስምንት መቶ ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች እጅግ ዘግናኝ በሆነ መልኩ ተገደሉ፡፡ በወቅቱ ያንን አሰቃቂ የዘር ፍጅት አሳፋሪ በሆነ ዝምታ የተመለከተው ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ጭፍጨፈው ከተፈፀመ ጊዜ ጀምሮ ግን በየዓመቱ በተለያዩ መርሐ ግብሮች  ይዘክረዋል፡፡ በኢትዮጵያም ስለ ሩዋንዳ የዘር ፍጅት ብዙ ይጻፋል፣ ይዘከራል፡፡ ነገር ግን ከዚያ አሰቃቂ ክስተት ጨርሶ የተማርን አይመስልም፡፡ እንዲያውም እጅግ አስፈሪ በሆነ መልኩ ወደዚያው እያመራን ይመስላል፡፡

በብሔረሰብና በእምነት ላይ ተመርኩዘው ከሚደረጉ ጥቃቶች መካከል እጅግ አሰቃቂ የሆነውና “የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል “ተብሎ የሚታወቀው የዘር ፍጅት ወይም ‹ጄኖሳይድ› ነው፡፡ ‹ጄኖሳይድ› የሚለውን ቃል የጅምላ ዘር ማጥፋት ተግባርን እንዲገልጽ በ1936 ዓ.ም. የፈጠረውና በዓለም ዐቀፍ ሕግጋት ውስጥ እንዲካተት ከፍተኛ ጥረት ያደረገው ራፋኤል ለምኪን የተባለ አይሁዳዊ ምሁር ነበር፡፡ ወቅቱም ናዚ ጀርመን ለአይሁዳውያን “የማያዳግም መፍትሔ” ያለችውንና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ወደር ያልተገኘለትን ጭፍጨፋ የምትፈጽምበት ነበር፡፡ ይህንን ድርጊት ከሰብአዊ ጥቃቶች በልዩ ወንጀልነት ለመፈረጅ በመጀመሪያ የዘር ማጥፋትን ትርጉም መወሰን አስፈላጊ ነበር፡፡

ስለሆነም የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ  በታኅሣሥ 1939 ዓ.ም. ያሳለፈው ውሳኔ ቁጥር A/Res/96(I) የጄኖሳይድ ጥቃት ክልል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቡድኖችን እንዲያካትት ተስማማ፡፡ ነገር ግን ከሁለት ዓመታት በኋላ በታኅሣሥ 1941 የጸደቀው A/RES/260A (III) ደንብ ጠባቡን በዘርና በእምነት ማንነት ላይ ያተኮረውን ትርጉም እንዲይዝ በመደረጉ፣ ‹‹የዘር ማጥፋት ወንጀልን ስለመከላከልና መቅጣት ስምምነት›› አንቀጽ 2 መሠረት፣ ጄኖሳይድ የሚባለው አንድን ብሔረሰብ፣ ዘውግ፣ ጎሣ ወይም ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ በጠቅላላው ወይም በከፊል ለማውደም በማሰብ የሚከተሉት አምስት ተግባራት ሲፈጸሙ ነው፡-

1/ የቡድኑን አባላት መግደል፤ 2/ በቡድኑ አባላት ላይ ጽኑ አካላዊ ወይም አዕምሯዊ ጉዳት ማድረስ፤ 3/ በማኅበረሰቡ አኗኗር ላይ በሙሉ ወይም በከፊል አካላዊ ጥፋት ለማስከተል የተሰላ እርምጃ መውሰድ፤ 4/ በማኅበረሰቡ ውስጥ ወሊድ እንዳይደረግ ወይም እንዳይኖር የታለመ እርምጃ መውሰድ፤ 5/ የማኅበረሰቡን ሕጻናት በግድ ወደሌላ ማኅበረሰብ ማዛወር፡፡

ከዘር ማጥፋት ጋር ተቀራራቢ ትርጓሜ ያለውና ብዙ ጊዜም በተለዋጭነት የሚውለው “ዘር ማጽዳት” (ethnic cleansing) የተባለው ሲሆን፣ ይህ ድርጊት ደግሞ አንድን ማኅበረሰብ ከኖረበት አካባቢ በኀይል ማፈናቀልን ይወክላል፡፡ ምንም እንኳን ስቃይን፣ ስደትንና ግድያን ቢያካትትም የዘር ማጽዳት ዓላማው ተጠቂውን ማኅበረሰብ በሙሉ ወይም በከፊል ማጥፋት አይደለም ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ የዘር ማጽዳት እርምጃ በጊዜ ካልተገታ ወደ ዘር ማጥፋት መሸጋገሪያ መሆኑን በመገንዘብ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤው በ1984 ዓ.ም. ዘር ማጽዳት የዘር ማጥፋት ዓይነት አንደሆነ ወስኗል፡፡ ሌላውና ሰብአዊ ወንጀሎች የሚለው እሳቤም በሠላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ መጠነ ሰፊና የተቀናጁ ጥቃቶችን የሚመለከተው ሲሆን፣ በተመሳሳይ በአንድ ዘር፣  ብሔረሰባዊ ወይም ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ ላይ ብቻ የተነጣጠረ አይደለም፡፡ ዘር ማጥፋት ከሰብአዊ መብቶች ጥሰት እጅግ የላቀ ተግባር ነው፡፡ ዘር ማጥፋት  ሌላ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ሌላ የጎሳ ግጭት ወይም የከሸፈ ወይም የመከነ መንግሥት ተምሳሌት ብቻም አይደለም፡፡ በሰው ለጆች ላይ ከሚያደርሰው እኩይ መቅሰፍት የተነሳ፣ ዘር ማጥፋት በራሱ በሥልጣኔ ላይ የተቃጣ አረመኔያዊ ጥቃት ተደርጎም ይቆጠራል፡፡

በዚህም መሠረት በሶማሊያ መንግሥት ውድቀት የተነሳ የተፈጠረው ነውጥና ፍጅት በቦስኒያ፣ በሩዋንዳ፣ በኮሶቮና በዳርፉር ከታዩት ድርጊቶች የተለየ ነው፡፡ ጄኖሳይድ እንደፊተኛው ግብታዊ ወንጀል ሳይሆን፣ በአደገኛና መሰሪ የፖለቲካ ልኂቃን ታስቦና ታቅዶ በስልት የሚፈጸም አረመኔያዊ የጅምላ ጭፍጨፋ ዘመቻ ነው፡፡ እነዚህ ልዩነቶች የጸጉር ስንጠቃ ጉዳይ አይደሉም፡፡ የዘር ማጥፋትን በተመለከተ በርካታ የተራራቁ ምሁራዊ አስተያየቶች ቢኖሩም፣ አጠቃላይ ተቀባይነት ያገኘውና ወንጀሉን ለመከላከል፣ ለማስቆምም ሆነ ለመቅጣት አመቺው ብቸኛው ሕጋዊ ትርጓሜ ከላይ የተቀመጠው ነው፡፡ እንደ ዊሊያም ሻባስ ያሉ የሕግ ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት የዘር ማጥፋትን ለመዳኘት የሚያገለግል የሕግ ማዕቀፍ ሰባት አንቀጾችን ካካተተው ከኑረምበርግ መርሆችና ከጄኖሳይድ ስምምነት ጀምሮ ለግማሽ ምዕተ ዓመት የኖረ በመሆኑ አዲስ መቅረጽ አስፈላጊ አይሆንም፡፡

የዘር ጥቃት ተዋናዮች

ጭካኔና አረመኔያዊነት ቀለም፣ዘውግ/ብሔረሰብ፣ ጎሣ፣ ሃይማኖት፣ መደብ፣ ርዕዮተ ዓለም ወዘተ… አይለይም፡፡ በሁሉም ክፍለ ዓለማት፣ በሁሉም ዘመናት፣ በሁሉም ሥርዓታት ተከስቷል፡፡ ኮሚኒስቶቹ እነ ስታሊን፣ ማኦ ሴቱንግ፣ ቺያንግ ካይሼክና ፖልፖት በጨፍጫፊነታቸው ሂትለርን የሚያስከነዱ ነበሩ፡፡ የሰው ልጆች በጃፓን፣ በካምቦዲያ፣ በኮንጎ፣ በቡሩንዲ፣ እንዲሁም በቅርቡ በመካከለኛው አፍሪካና በሶሪያ ተቃዋሚዎች መካከል እንደተከሰተው የጠላትን ስጋ እስከመብላት ድረስ ወደ አውሬነት እንደሚወርዱ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡

ሥልጣኔ የሰው ልጅን ባሕርይ ያሻሽለዋል የሚሉ የዋሆች ተስፋ ይቁረጡ፡፡ እንዲያውም ራሱ የሰው ልጅ የመጠፋፋት አቅም በኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ ብቻ የሚወሰን አለመሆኑ ገሃድ ሆኗል፡፡ የሩዋንዳው የዘር ፍጅት ከናዚዎች ሳይንሳዊ የጥፋት ዘዴዎች በአምስት እጥፍ ስሉጥና አውዳሚ ነበር፡፡ በ100 ቀናት ብቻ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉትን የቀጠፈ ሲሆን፣ ሰማንያ በመቶውን ቱትሲዎች የጥቃቱ ሰለባ አድርጓል፡፡ ስመጥሩ የፖለቲካ ሳይንቲስትና በፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ሥር የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የነበሩት ዝቢግኒው ብርዚንስኪ እንዳሉት “ቀደም ባሉት ጊዜያት አንድ ሚሊዮን ሕዝብን ከመግደል ይልቅ መቆጣጠር የቀለለ ነበር፡፡ ዛሬ ግን አንድ ሚሊዮኖችን መግደል ከመቆጣጠር በአጅጉ የቀለለ ሆኗል፡፡” (Hagan, Johna and Wenona Rymond-Richmond. 2009. Darfur and the Crime of Genocide.  2009)

የዘር ማጥፋት በዘፈቀደና በድንገት የሚቀሰቀስ ሳይሆን ታስቦና ታቅዶ የሚከወንና የራሱ  ተዋናዮችና ውስጣዊ ሂደቶች ያሉት ብቻ ሳይሆን በቡድን የሚከወን ድርጊትም ነው፡፡  የዘር ማጥፋት ወንጀል ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሥነ-ልቦናዊ መልኮችን ያካተተ ሰፊ ሂደት ውጤት ነው፡፡ እስከዛሬ እንደታየው የዘር ማጥፋት በዋነኝነት የሚቀነባበረውና የሚፈጸመው መንግሥታዊ ሥልጣን በጨበጡ የፖለቲካ ልኂቃንና ደጋፊዎቻቸው በመሆኑ ወንጀሉን ለመከላከል፣ ለማስቆምም ሆነ ጥፋተኞችን ለፍርድ ለማቅረብ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሥልጣን የጨበጡ ቡድኖች በዘር ጥቃት ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ቀጥተኛ ወይም ተዘዋዋሪ ሊሆን ይችላል፡፡

በጀርመን የናዚ ፓርቲው ግልጽ የሆነ ፀረ-ሴማዊ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ገና ሂትለር ሥልጣን ከመያዙ በፊት ጀምሮ ለ15 ዓመታት የተካሄደ ነበር፡፡ ሂትለር መንግሥት እንደመሠረተ በቀጥታ ሕልሙን ተግባራዊ ማደረግ ጀመረ፡፡ በአይሁዳውያን ላይ የተከተለው ፖሊሲ በጦርነቱ ዋዜማ በ1931 ዓ.ም.  ሙሉ በሙሉ ከጀርመን ሕይወት ውስጥ አገለላቸው፡፡ ለውድመት ተመቻቹ፡፡ በኮሶቮና በቀሪው ዩጎዝላቪያ የተፈጸመው የዘር ማጽዳት ዕቅድ የተነደፈውና መስከረም 1979 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው በሰርቢያ የሳይንስና ሥነ-ጥበብ አካዳሚ አማካይነት ነበር፡፡ ይህም ሰነድ ሚሎሶቪች ሥልጣን እንዲቆናጠጥና ዓላማውን በተግባር እንዲያውል ረድቶታል፡፡

በሩዋንዳም ከጥላቻ ዘመቻው እስከ ግድያ ትዕዛዙ ድረስ ሂደቱ የተመራው በመንግሥት ፖለቲከኞች አማካይነት ነበር፡፡ ሁቱ መራሹ አገዛዝ የጥላቻ ፖለቲካ ሲያካሂድ የነበረው ቢያንስ ለአርባ ዓመታት ገደማ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ቱትሲዎች በጦር ኀይሉ ውስጥ ያላቸውን ቦታ እንዲያጡ መደረግ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ግልጽ መድልዎና በደል ይደርስባቸው ነበር፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ ጸረ-ቱትሲ ፕሮፓጋንዳዎችን ያሰራጩ ነበር፡፡ በ1995 ዓ.ም. የፈነዳው የዳርፉር ጭፍጨፋም የሱዳን መንግሥት የሃያ ዓመታት ፀረ-ጥቁር/አፍሪካውያን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻና ፖሊሲ ፍሬ ነበር፡፡  ከደቡብ ሱዳን ነጻነት በኋላ ደግሞ ፕሬዘዳንት አልበሽር በንቀት ‹ዙርጋ› እያለ የሚጠራቸውን ሦስት የዳርፉር ብሔረሰቦች ማለትም ዳር፣ ማሳሊትና ዛግዋን መሬት የጃንጃዊድ ዐረብ ሚሊሻዎች ከመደበኛው የመንግሥት ሠራዊት በማበር እንዲነጥቁ፣ ነዋሪዎቹን እንዲያሰቃዩ፣ እንዲገድሉና እንዲደፍሩ፣ መንደሮችን በጠቅላላ እንዲያወድሙና ከብቶችንም እንዲወርሱ አድርጓል፡፡

በሥልጣን ያለው አገዛዝ ዋና ተዋናይ ይሁን እንጂ፣ የዘር ጥላቻን በማራገብና ሕዝቦችን ለመጠፋፋት በማዘጋጀት በኩል መንግሥትን የሚቃወሙ ብሔረሰባዊ ወይም ፖለቲካዊ ቡድኖችም ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖች አቅማቸው እስከፈቀደ ድረሰ በጠመንጃም ሆነ ያለጠመንጃ የሚፋለሙትን መንግሥት ከአንድ ወይም ከሌላ ብሔረሰብ ጋር በማዛመድ የዘር ጥላቻና ተቃውሞ ይቀሰቅሱበታል፡፡ አገዛዙ ለፖለቲካቸው የሚመች ከሆነም ደግሞ በዴሞክራሲ፣ በፍትሕና በእኩልነት ስም በሕዝቦች ውስጥ የሚነፈርቅ ጠላትነት ይዘራሉ፡፡ ነገር ግን በሰላምም ይሁን በአመጽ ሥልጣን ካልያዙ፣ ወይም ከፍተኛ ማኅበራዊ ነውጥ ካልተፈጠረላቸው በስተቀር ዕኩይ ዓላማቸውን  በተግባር የማዋል ዕድል የላቸውም፡፡

ከሥነ ልቦና አንጻር ስናየው ደግሞ ሰፊ የዘር ጥቃቶች አመንጪዎችና አንቀሳቃሶች በበታችነት ስሜት የሚሰቃዩ የፖለቲካ ልኂቃን ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ምሁራን በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ላይ ርዕዮተ ዓለሙን በመንደፍና በማስፋፋት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የጥላቻው ደረጃ ወደ እብደት ደረጃ ሲሻገር ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የዘረፋ ቡድን ካፖዎች፣ የለየላቸው ንኮችም ሳይቀር በብሔረሰብ ወይም በሃይማኖት ተቆርቋሪነት ስም ብቅ ብቅ ይላሉ፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ዶብሪካ ኮሲክ (ሰርቢያ)፣ ፈርዲናንድ ኒህማና (ሩዋንዳ)፣ ዶ/ር ጎብልስና (ጀርመን) ዶ/ር ሊዎን ሙገሴራ (ሩዋንዳ)፣ አረመኔው ሳይካትሪስት ራዶቫን ካራዲችን የመሳሰሉ ምሁራንን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የዘር ጥቃት በሰፊው ሲተገበር ቢያንስ በተርታው ሕዝብ ውስጥ የተወሰነ ተቀባይነትና ተባባሪነት ማግኘት የግድ ነው፡፡ በጥላቻ የተዋጠና የማያመነታ የካድሬ ቡድን እስካለ ድረስ ደግሞ ሰፊውን ሕዝብ በውድም በግድም ወደ ጥፋቱ ማኅበር ማስገባት ይቻላል፡፡ ማባበል፣ መደለል፣ ማስፈራራት፣ ማግለል፣ መቅጣት፣ መሳቂያ ማድረግ፣ ቀስ በቀስ ተግባር ላይ የሚውሉና በአረመኔያዊ ተግባሮች ላይ ለመሳተፍ የሚያመነቱን ለመቀላቀል የሚውሉ ስልቶች ናቸው፡፡ በጀርመንና በሩዋንዳ ታይተዋል፡፡ ተመራማሪዎች እንደሚሉት አመጽ አንድ ጊዜ ከተጫረ በተዋናዮቹ ውስጥ እመርታዊ ለውጥ ያስከትላል፡፡ በግለሰቦች ማንነት፣ በማኅበራዊ ደንቦች፣ በተቋማት፣ እንዲሁም በወግ ልማዶች ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ድርጊቱ የተለመደና ተራ እንዲመስል ያደርገዋል፡፡ ክፉ አትዋል የሚለው ብሂል “ከፍ ባሉ” የቡድኑን ንጽሕና፣ መልካምነትና ደህንነት በመጠበቅና ጠላቶችና አጥፍቶ የተሻለ ማኅበረሰብ መፍጠር በሚሉ የሞራል መርሆዎች ይተካል፡፡

ለመሆኑ የዘር ማጥፋትን የመሰሉ ዘግናኝ ድርጊቶች መሠረታዊ መንሥኤዎች ምንድናቸው? የባህል፣ ቋንቋና እምነት ልዩነቶች፣ የሀብት ክፍፍል ችግሮች፣ የፖለቲካ ሥልጣንና ውክልና፣ የዘመናዊነት ተጽዕኖዎች፣ የሰው ልጅ እኩይ ተፈጥሮ ወይስ ውስብስብ የሥነ-ልቦና ችግሮች? የሚገርመው ነገር የዘር ጥቃቶች በዓላማም ሆነ በግብ በዘርና በእምነት ማንነት ላይ የተመሠረቱ ይሁን እንጂ፣ ለምሳሌ እንደ ሩዋንዳ ባሉት አገሮች የብሔረሰብ ድንበሮች፣ ቋንቋ፣ ባህል ወይም እምነት ቀዳሚ የግጭት ምክንያቶች አልነበሩም፡፡ የዘር ጥቃትን በተለያየ ደረጃ የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ ቡድኖች ቢያንስ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ይኖራቸዋል፡፡ አንደኛው ፖለቲካዊ ምክንያት ሲሆን የጥቃቱ ዒላማ የሥልጣን ተቀናቃኝ ሊሆን፣ አገዛዙን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ተብሎ የሚገመትን ብሔረሰባዊና ሃይማኖታዊ ቡድን በተቻለ መጠን ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ከምድረ ገጽ ጠራርጎ ለማጥፋት የሚፈጸም ድርጊት ነው፡፡

ሁለተኛው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሲሆን በተለይም በአንድ ብሔረሰብ ውስጥ ተሰባጥረው የሚኖሩና በኢኮኖሚው የተለያየ ዘርፍ እጅግ በተሳካላቸው ቡድኖች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በእነዚህ ስኬታማ ማኅበረሰቦች የቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይ አሉባልታዎች ከመንዛት፣ ከማሻጠርና አድማ ከማድረግ ጀምሮ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣልና በመውረስም ጭምር እስከማክሰር ይሄዳል፡፡ በገጠርማ አካባቢዎችም ከመሬታቸው የማፈናቀልና የመቀማት እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ በተለይ በአገራችን በበርካታ ቦታዎች በጉራ ፈርዳ፣ በአሶሳ፣ ወዘተ የተደረጉ “በመጤነት” የተፈረጁ ማኅበረሰቦችን በማስፈራራትና በማስገደድ ማባረር እነዚህን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መልኮች ያቀላቀለ ከመሆንም አልፎ፣ የጥቃቱ አበጋዞች ወደፊት ለሚመኙት “ንጹሕ” ክልልና አገር መንገድ የሚያዘጋጅ ሂደት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው ማኅበረሰቦችን በኃይል በማስገደድ ከመኖሪያቸው የማፈናቀል ዓለም ዐቀፍ ወንጀል “ዘር ማጽዳት” ተብሎ ይታወቃል፡፡

በዘር ጥቃት መንስኤነት የሚታወቀውና ረቀቅ ያለው ምክንያት ሥነ-ልቦናዊ ሲሆን በተለይም ደግሞ ዋነኞቹን አሉታዊ ስሜቶች በቀል፣ ቅናትና ስጋትን ይጨምራል፡፡ የዚህ አጠቃላይ መንፈስ መንስኤዎች ታሪካዊም ነባራዊም፣ እውነታም ምናባዊም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በቀል ጥቂትም ቢሆን ታሪካዊ ይዘት ያለውና ላለፉ ጉዳቶች መካሻ የሚፈልግ ስሜት ሲሆን፣ አቀራረቡም በፍትህና ርትዕ ስም ይሆናል፡፡ ቅናት ደግሞ በተቃራኒው ቡድን ነባራዊም ሆነ ምናባዊ ሀብት፣ ተሰጥኦ ወይም ዕሴት ላይ የተመሠረተ፣ ነገር ግን ማኅበራዊ ተቀባይነት የሌለው መንፈስ በመሆኑ ራሱን እንደ እኩልነት፣ አገር ወዳድነት፣ ተቆርቋሪነት፣ ወዘተ ባሉ መልኮች የሚገልጥ ነው፡፡ ስጋት ታሪካዊውንም፣ ነባራዊውንም፣ መጻኢውንም አቅጣጫዎች የሚዳስስ በራስ ያለመተማመን ስሜት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ስሜቶች የተቀላቀሉበት የበታችነት መንፈስ ደግሞ የፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ የበላይነት የማያጠፋው መሆኑ አንዱ አወሳሳቢ ችግር ነው፡፡

ኒኮላስ ሮቢንስና አዳም ጆንስ “Genocide by the Oppressed (2009)” በሚል ርእስ በሳተሙት መጽሐፍ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ህዳጣን ኀይሎች የሚካሄዱ ጭፍጨፋዎችን በማጥናት ረገድ ከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ግንባር ቀደሙ በነባራዊው እውነታና በሕሊናዊ ግንዛቤ መካከል የሚስተዋለው ተገላቢጦሽ/ተቃርኖ ነው፡፡ ሩዋንዳን ለአብነት ብንወስድ የሁቱዎች ብሔራዊ የበላይነት ከ1952 ዓ.ም. ጀምሮ በይፋ ቢመሠረትም፣ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ግን የተዋረድ ግንዛቤው ሊለወጥ አልቻለም ነበር፡፡ የቱትሲዎች ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ቁሳዊና አካላዊ የበላይነት ላይ የተመረኮዙ ፍረጃዎች በሰፊው የሁቱ ማኅበረሰብ ውስጥ የቅናት፣ የበቀልና የስጋት ምንጮች ነበሩ፡፡ ሁቱዎች ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ እነዚህን ስሜቶች ከማጥፋት ይልቅ ቅኝ ገዥዎች በፈጠሯቸው የሐሰት እምነቶች ራሳቸውን ኮድኩደው ቀጠሉ፡፡

ከላይ እንደጠቀስነውም ሁቱ መራሹ መንግሥት ቱትሲዎች ላይ ይህ ቀረሽ የማይባል የበቀል ጭቆና ሲያደርግባቸው ቆይቷል፡፡ በርካታ ቱትሲዎች ተገድለዋል፣ አገራቸውንም ጥለው ተሰድደዋል፡፡ በኋላም በ1950ዎቹ  የተሰደዱት ቱትሲዎች ልጆች በ1980ዎቹ መጀመሪያ ወደ አገራቸው በኀይል ለመመለስ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር የተሰኘ ጦር በዩጋንዳ መሥርተው ትግል ሲቀጥሉ በርካታ ቱትሲዎች ይህን ወታደራዊ ዘመቻ የሚደግፉ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን ይህ እንቅስቃሴ የሁቱዎችን የማይሞት ስጋት እንዲያንሰራራ አደረገው፡፡ ቱትሲዎች አሁንም ሥልጣናችንን ቀምተው የጥንቱን አገዛዝ ሊጭኑብን እያሴሩ ነው የሚል ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ ተቀሰቀሰ፡፡ አንዳንድ ወቅታዊ አቀጣጣይ ጉዳዮች ሲጨመሩበትማ ሁኔታው ወደ ዘር ማጥፋት ሥነ-ልቦና አደገ፡፡ ለምሳሌ ሁቱዎች በነሐሴ ወር 1985 ዓ.ም. የተደረገው የአሩሻ ሥምምነት ለቱትሲዎች ያደላ ነው የሚል ቁጭት አድሮባቸው ነበር፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ለሁቱ ጽንፈኞች ተአማኒነት መጨመር የቡሩንዲው ሁቱ ፕሬዚዳንት ሜልኮር ንዳዳየ በቱትሲ ጄኔራሎች ጥቅምት 1986 ዓ.ም. መገደሉ ዋነኛው ነበር፡፡ ይህን የስጋት ጡዘት ለመደምደም ሀቢሪማናም በሚያዝያ 1986 ዓ.ም. በአውሮፕላን አደጋ ሕይወቱ አለፈች፡፡ ይህም አገሪቱን ወደ ደም ምድርነት ቀየራት፡፡ በዘመናችን ከፍተኛ የዘር እልቂት በተፈጸመባቸው አገራት በጀርመን፣ በሰርቢያና ኮሶቮ፣ በዳርፉርና በሌሎችም አካባቢዎች የታዩት ተመሳሳይ ሂደቶች ናቸው፡፡

እዚህ ላይ ትኩረታችንን የዘር ጥቃት ርዕዮተ ዓለም ምንድነው፣ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ይህን ዘግናኝ ወንጀል ለመከላከልም ሆነ ለማስቆም ያልቻለው በምን የተነሳ ነው፣ የዘር ጥቃትን አስቀድሞ ለማወቅና ለመጠንቀቅ ምን መደረግ አለበት? ወደሚሉት ጉዳዮች እንመልስ፡፡ የዘር ጥቃት የሚገለጥባቸውን መልኮችና ደረጃዎች፣ ችግሩን ለመቅረፍ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ያጋጠመውን ፈተና፣ እንዲሁም በየፈርጁ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የመከላከል እርምጃዎች እንዳስሳለን፡፡

ምድራችን ሰብአዊ ፍጡራን ለመጠፋፋት የተፋጠጡባት አውድማ የመሆኗ ነገር በእጅጉ የሚያሳስብ ነው፡፡ ችግሩን የበለጠ አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ የሰው ልጅ ዘር ማንዘሩን ከናካቴው ለማውደም የሚያስችል አቅም ማበጀቱ ነው፡፡ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ከባተ በኋላም አመክንዮና መርህ በጠቋሮቹ የስሜትና ጥላቻ መናፍስት እንደተዋጡ የቀሩ ይመስላል፡፡ በያቅጣጫው ሕይወት እየረገፈ ደም እየጎረፈ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ፍዳ ደራሲ የሆነው የማንነት ፖለቲካ አሁንም ከመንበሩ አልወረደም፡፡ ታዲያስ ምን ይበጃል?

የጥላቻ ፖለቲካ የማንነት አስተሳሰብን ተጣብቶ የሚኖርና በሂደትም ጭራሽ ፖለቲካ የተባለን ነገር የሚያጠፋ መንፈስ ነው፡፡ አደገኛነቱም በከፊል የመደብ፣ የርዕዮተ ዓለምና የእምነት ድንበሮችን ተሻግሮ ከማስተባበር ባሕርይው ይመነጫል፡፡ የዘር ጥቃት አቅጣጫውን የሳተ ጽንፈኛ ብሔርተኝነት ወይም ጎሰኝነት ውጤት ሲሆን፣ ብሔርተኝነት ደግሞ ድሩም ማጉም ታሪክ ነው፡፡ ለጽንፈኞች “ሌላው ማኅበረሰብ” ብሔራዊ ባላንጣም ታሪካዊ ጠላትም ነው፡፡ ይህን ጠላት ለማጥቃት በሚነድፉት መርሐ-ግብር ውስጥም ታሪክ ነክ ፖለቲካ ዋነኛ የብሶት አስታዋሽና አንቀሳቃሽ ኀይል ሆኖ ያገለግላል፡፡ ታሪክ ለጠባብ፣ አጭርና አፍራሽ ግብ እንዲውል እንዳመችነቱ ይፈበረካል፣ ይቃናል፣ ይወላገዳል፣ ይበረዛል ወዘተ…

ዘውጌ ብሔርተኞች የታሪክ እስረኞች እንደመሆናቸው መጠን ለአብሮነትና አዎንታዊ መስተጋብሮች የከረረ ጥላቻ አላቸው፡፡ ካሰመሩት ጠባብ ቅጥር ውጭ ያሉትን ታሪኮች በሙሉ የጭቆናና የጨቋኝ ብሔረሰብ ገድሎች በማለት ያጣጥላሉ፡፡ ቆምንለት የሚሉትን ማኅበረሰብ ራስ-በቅ፣ ፍጹምና ያልተነካካ አድርገው ይስላሉ፡፡ ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ “ያለመቻቻል ፖለቲካ ሰማዕታት” በሚለው መጽሐፍ ላይ በወጣ ጽሑፋቸው (1998፣78) ላይ እንዳስገነዘቡት “አክራሪ ጎሰኞች የማንነት መጋራትን፤ እንደድልድይ የሚያገለግሉ የብዝሃ-ማንነት ባለቤት የሆኑ ሰዎች መኖር ለሚያራምዱት አጀንዳ አመች አለመሆን በሚገባ ስለሚረዱት ይክዱታል፤ ያጥላሉታል፤ ያወግዙታል፡፡ ጎሣቸውን ወይም ብሔረሰባቸውን በጠባቡ የሚያጥር ትርጉም ያስቀምጡታል፡፡ ንጹሕነቱን መጠበቅንም ዋነኛ ጉዳይ ያደርጉታል፡፡”

እነዚህ ኀይሎች ታሪካዊ ቁስሎችን በመሞዠቅ፣ የግጭት ገድሎችን ነጥሎ በማጋነን የቁጭት መንፈስን ለማፍላት አበክረው ይሠራሉ፡፡ የትናንቱ ግፍ ሳይበቃን፣ ዛሬም ለጥቃት ተጋልጠናል የሚል ፍርሃት ይዘራሉ፡፡ በነጻነት፣ በፍትሕና ርትዕ ስም ለታሪካዊ በቀል ያነሳሳሉ፡፡

የጥላቻ ፖለቲካ ‹መሰሪ ጠላታችን ሳይቀድመን እንቅደመው› በሚል የአልሞት ባይ ተጋዳይነት አቋም ለማስፈን የሚታለም/የሚታቀድ ሲሆን፣ ቁልፍ አስተሳሰቡም “አፈር ማስጋጥ፣ አንገት ማስደፋት፣ ቅስም መስበር” በሚሉ ሐረጎች ይገለጣል፡፡ በባሕርይው ይህ የደመኝነት አስተምህሮ በነተበ የታሪክ እውነታ ወይም በለየለት ፈጠራ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለምሳሌ የሰርቦች ቁጭት ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት በ1381 ዓ.ም. በተደረገው የኮሶቮ ጦርነት ከደረሰባቸው ሽንፈት ይነሳና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፋሽስታዊው የክሮሽያ ኡስታሻ አገዛዝ እስከተፈፀመባቸው ግፍ ድረስ በቀጭን ክር ያስተሳስራል፡፡ ይባስ ብሎም ቱርኮች በ14ኛው ክፍለ ዘመን፣ ክሮአቶች ደግሞ በ1940ዎቹ ለፈፀሙት በደል በ1990ዎቹ የቦሲኒያ ሙስሊሞችን ጭዳ አድርጓል፡፡

በአጠቃላይ ዘውጌ ብሔረተኞችና ጎሰኞች ከዛሬውና ከመጭው ተስፋ ይልቅ ባለፉ ታሪኮች በመኮድኮዳቸው፣ ጠላቶቻቸው የቅድመ አያት ናቸው፡፡ ምኒልክ ሲነሳ ደማቸው ይሞቃል፤ የሚያባንናቸው “የነፍጠኞች ሴራ ከትናንት እስከዛሬ” ነው፡፡ ነገር ግን ይኸው የተወላገደ የተጠቂነት ቅርስ የዛሬን እውነታም በቅጡ እንዳይገነዘቡ ይከልላቸዋል፡፡ ዓለምን ቢጨብጡም ሕሊናቸው ዓይተኛም፡፡ ተመራማሪዎች እንደሚጠቁሙት “ተጨቆንኩ” የሚለው ቡድን ሥነ-ልቦና ጨቋኝ የተባለውን በተመለከተ ካሳደረው ያለመተማመንና የቅናት ስሜት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ እሮሮውም በውኑም ሆነ በሕልሙ ባለጋራውን እያሰበ እንጂ በተጨባጭ ባለበት ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ አይደለም፡፡ ስለዚህም ናዚዎች፣ ሰርቦችና ሁቱዎች ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊው ሥልጣን በእጃቸው ተጠቅልሎ እያለ “ጠላቶቻችን ሊያጠፉን ወይም ሊውጡን ነው” የሚለው ደመነፍሳዊ ቅዠት ይረብሻቸው ነበር፡፡

ልብ ሊባል የሚገባው የጥላቻ ታሪክ አበጋዞች የአገም-ጠቀም ደራሲያን ሳይሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑና በየትምህርት ተቋማቱ ውስጥ የተሰገሰጉ “ምሁራን” ናቸው፡፡ እነዚህም ለጄኖሳይድ ከሚደረጉ የሥነ-ልቦና ዝግጅቶች መካከል ዋነኞቹ በሆኑት ብሔረተኛ/ጎሰኛ ስሜቶችን የሚያጠናክሩ አስተሳሰቦችና ተቋማትን በማስፋፋት፣ አንዲሁም የጀግንነት ወኔን በመቀስቀስ ረገድ በቀደምትነት ይሳተፋሉ፡፡ “ያልተበረዘ ያልተከለሰ” ታሪካችንን ለመጻፍ ከእኛ በላይ ላሳር ይላሉ፡፡ ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ እስከሆነ ድረስ በጥናትና ምርምር የተለወሱ ውሸቶችን ለማራመድ ቅንጣት አያመነቱም፡፡ አቅማቸው በፈቀደ መጠን የሚወጥኑት የአስተሳሰብ ጽዳት ከታሪክ አሻራዎች ጽዳት ይጀምራል፡፡ ቤተ-መጻሕፍት፣ ቤተ-መዛግብት፣ የታሪክና ቅርስ መዘክሮች ዋነኛዎቹ ዒላማዎች ይሆናሉ፡፡  የትምህርት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎችም ማኅበራዊ መድረኮች በጽንፈኛ አስተምህሮዎች ይቃኛሉ፡፡ የቦታዎች፣ መንገዶች፣ ተቋማት፣ አልፎም የግለሰብ ስሞች ሳይቀሩ ይለወጣሉ፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎች የኢትዮጵያ ታሪክና ኢትዮጵያን የሚመለከቱ መልካም ነገሮች እነሱ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እንደጀመሩ ሊያስገነዝቡን የሚታትሩት ከዚህ አንጻር ነው፡፡ የቀደሙት የኢትዮጵያ መሪዎች የሠሩት ሥራ ወይ ከነጭራሹ አይነሳም፤ ከተነሳም በአሉታዊ ጎኑ ብቻ ነው፡፡

የሁቱ “የታሪክ ምሁራን” ልክ በአገራችን እንደተደረገው ቱትሲዎች በሩዋንዳ የሠፈሩበትን ሂደት “የውስጥ ቅኝ አገዛዝ” (internal colonialism) በማለት ፕሮፓጋንዳ ሲሰሩበት ኖረዋል፡፡ የሰርብና የሁቱ ጽንፈኞች በ1980ዎቹ ባካሄዱት የሕሊና ብዝበዛ፣ በሕዝባቸው መካከል ጥላቻና ፍርሃትን በማንገስ ለዓላማቸው አመቻችተውታል፡፡ ኒል ክረሰል (2002፣ 97) እንደጠቆመው የዘር ጥቃት አስከፊነት የጋራ ማንነት መገለጫዎች በተንሰራሩበት፣ በተጋነኑበትና ለፖለቲካ ጥቅም በተበጃጁበት መጠን የተወሰነ ይሆናል፡፡ በአጭሩ ታሪክ የዘር ማጥፋት ርዕዮት ምሰሶ ነው፡፡

ከጥላቻ ወደለየለት እብደት

የዘር ጥቃት ከመቅጽበት ዱብዳ ሳይሆን፣ በዕቅድና በስልት ከፍረጃ እስከ ደም መፋሰስ የሚሸጋገር ሂደት ነው፡፡ የመጀመሪያው ደረጃም የጥቃቱ ዒላማ የሆነውን ማኅበረሰብ እኩይነት በሚያጎሉ ቃላትና ትእምርቶች ለይቶ መግለጽ ነው፡፡ ለምሳሌ ደገኛ፣ መጤ፣ ሰፋሪ፣ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ፣ ተስፋፊ፣ ቀማኛ፣ ወዘተ… የተለመዱ ቅጽሎች ናቸው፡፡ ይህ ውግዘት ላቅ ሲልም በሚታይና በሚዳሰስ ቁሳቁስ ይገለጻል፡፡ የጥላቻው መሐንዲሶች በአንድ አገር ዜጎች መካከል የማይፋቅ የደመኝነት ሐውልት ይቀርጻሉ፡፡ እንደምሁራን እምነት የፖለቲካ መሪዎች በአደባባይ ዲስኩሮቻቸው፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን፣ በፓርቲ ልሳናት ወዘተ… እንዲህ ያሉ መንፈሶችን ማራገብ ሲጀምሩ የዘር ማጥፋት ሊከሰት እንደሚችል ከሚጠቁሙ ቅድመ ማስጠንቀቂያዎች አንዱ ነው፡፡

በተለይ ተጠቂዎችን ከመፈረጅ በተለጣጣቂ ኅሊናዊና ማኅበራዊ ክልላቸውን ማጥበብና መዝጋት ዓይነተኛ ስልት ነው፡፡ በንግድ፣ በእንቅስቃሴ፣ በሥራና በትምህርት ዕድል፣ በፖለቲካ ውክልና፣ በፍትሕ፣ በሰብአዊና ዜግነታዊ መብቶችም ጭምር  መድልኦዎችና አግልሎዎች ማድረግ፣ ንብረቶቻቸውን መውረስ፣ ከቀያቸው ማፈናቀል፣ ማሳደድና በማጎሪያዎች ማሰባሰብ ይፈጸማሉ፡፡ ናዚዎች ከሞት ቀጠናዎች በፊት በአይሁዳውያን ላይ ተከታታይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ግድያ ማድረግ ነበረባቸው፡፡ በሰርቢያ የዘር ማጽዳቱ የጀመረው ተወላጅ ላልሆኑ የሥራ ዕድሎችን በመገደብ፣ በነጻነት የመሰብሰብ፣ የመንቀሳቀስና የመገናኘት መብቶቻቸውን በመሸርሸር ነበር፡፡

ከዚህ ሁሉ ቅድመ-ዝግጅት በኋላ የዘር ጥቃቱ ራሱን የቻለና የማይቀለበስ እብደት ይሆናል፡፡ ሰዎች በተነሳሽነትም ሆነ ከፍርሃት ይሳተፉበታል፡፡ ትክክለኛና ተገቢ፣ ወይም ሊያመልጡት የማይቻልና አይቀሬ አድርገው ይቀበሉታል፡፡ ነገር ግን ድርጊቱን ሊቃወሙ የሚፈልጉ፣ በማባበያና የማስፈራሪያ ስልቶች ሰልፍ የማይገቡ ካሉ ደግሞ በባንዳነት፣ በመናፍቅነትና በከሃዲነት መክሰስ ይከተላል፡፡ የናዚ ጀርመን ሁለተኛው ሰው የነበረው ኸርማን ጎሪንግ በ1938 የኑረምበርግ ችሎት ላይ እንደተናገረው “ድምጽ ኖራቸውም አልኖራቸው ሕዝቦች ሁሉጊዜም ለመሪዎቻቸው እንዲታዘዙ ማድረግ ቀላል ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ነገር እየተጠቁ መሆናቸውን መንገር ነው፡፡ ከዚያም ሠላም ፈላጊዎቹን አገር ወዳድነት ስለሚጎድላቸው ለአደጋ እያጋለጡን ናቸው ብለህ ማውገዝ ነው፡፡” (Dutton, Donald. 2007. The Psychology of Genocide, Massacres and Extreme, p. 109)

ለጥላቻ ፖለቲካ ነጋዴዎች ተጠቂ ቡድኖችን ማግለል በቂ አይደለም፡፡ ከምድረ-ገጽ መወገድ አለባቸው፡፡ ለዚህም ነው በማሕጸን ያሉ ሽሎችን ዘንጥሎ በማውጣት ግንዱን ከነሥሩና ከነአበባው ለማጥፋት መሞከራቸው፡፡ በሌላም በኩል የዘር ማጽዳት ረቂቅ ዓላማው የራስንም የበታችነት ስሜት ጠራርጎ መገላገል ይመስላል፡፡ እንደ ማኅበራዊ ሥነ-ልቦና ተመራማሪዎች ግምት ይህ የማይሞት የውርደት ስሜት ለሚታየው ቅጥ ያለፈ ጭካኔ ከፊል ምክንያት ይሆናል፡፡ ቁም ነገሩ መግደሉ ብቻ አይደለም፡፡ እንደውም ግድያው የማዋረዱ አካል በመሆኑ የአምልኮ ዓይነት ሥርዓት ይታይበታል፡፡ በአስከሬኖች ላይ ሳይቀር ዘግናኝ ድርጊቶችን ከመፈጸም ያደርሳል፡፡ ሆኖም ይህ እብደት እንደ በጎ ተግባር እንዲቆጠር ወይም ሕሊናን እንዳይወጋ የአክብሮት መጠሪያ ይደለደልለታል፡፡ ሰርቦች አረመኔያዊ ድርጊታቸውን ‹‹ማጽዳት›› በማለት ሲያቆላምጡት፤ “መጠራረግ፣ ማስወገድ፣ ማባረር” በካምቦዲያ የተለመዱ አገላለጾች ነበሩ፡፡ ሁቱዎች ጭፍጨፋውን “ሥራው”፣ ናዚዎች ደግሞ “ማግለል እና ልዩ እርምጃ” በማለት ይጠሩት ነበር፡፡ በተለይም “ልዩና ነጻ እርምጃ” በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ያለፍርድ ደም የማፍሰሻ ዘይቤ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

ዶ/ር የራስወርቅ በተጠቀሰው መጽሐፍ (74-75) ግሪጎሪ ስታንተን የተባሉት ምሁር ያስቀመጧቸውን ስምንት የዘር ማጥፋት ፍጅት ደረጃዎች ጠቅሰው እንደሚከተለው ዘርዝረዋቸዋል፡-

  • የመጀመሪያ ደረጃ “እነሱና-እኛ” ብሎ ለመከፋፈል በሚረዳ መልኩ ልዩነትን በማስረገጥ የሚደረግበት ምደባ ወይም classification፤
  • ሁለተኛው እንደልዩ አልባሳት፣ ተንጠልጣይ ምልክቶችና ከዚያም አልፎ በመታወቂያ ካርድ ላይ በሚሰፍር ቃል ወይም ምልክትና እነዚህን በመሳሰሉ መለያዎች አማካይነት “ዒላማዎችን ለይቶ ማተም” ወይም symbolization፤
  • ሦስተኛው አንዱ ቡድን የሌላውን ቡድን ሰብዓዊ መሆን የሚክድበትና ከእንስሳት፣ ተባይና በሽታ ጋር የሚያይዝበት “ከሰብአዊነት ማስወገድ” ወይም የdehumanization ደረጃ፤
  • አራተኛው ደረጃ የዘር ማጥፋትን ፍጅት ለማስፈጸም አስፈላጊው ዕቅድ የሚዘጋጅበት፤ አስፈጻሚው ኀይል የሚሰናዳበትና የሚታጠቅበት የማደራጀት ወይም የorganization፤
  • አምስተኛው ለይቶ ለመምታት አመች የሆነው የመለያየት ሂደት የሚከናወንበት በተለይም መሐል ላይ ያለው ሕዝብ ወደ አንዱ ወይም ወደሌላው እንዲከት የሚደረግበት የpolarization ደረጃ፤
  • ስደስተኛው የፍጅት ሰለባዎች የሚለዩበትና ለዕርድ የሚዘጋጁበት የpreparation ደረጃ፤
  • ሰባተኛው ራሱ ግድያው የሚጀመርበትና ወደ መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋ የሚዛመትበት የextermination ደረጃ እንዲሁም
  • ስምንተኛው አስገራሚውና አይቀሬው ድርጊቱን የመካድ ወይም የdenial ደረጃ ናቸው፡፡

የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ሚና

እስካሁኑ የዓለም ተሞክሮ እንደሚያሳየው ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የዘር ፍጅትን በመከላከል ረገድ እምብዛም አመርቂ ሪከርድ የለውም፡፡ የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በቦስኒያ፣ በሩዋንዳና በኮሶቮ የተደረጉትን የዘር ማጥፋት ፍጅቶች በቁርጠኝነት ለመከላከልና ለመግታት አልቻለም፡፡ ይህ የሆነው ስለ ወንጀለኞቹ ወቅታዊ መረጃና በቂ ወታደራዊ አቅም ሳይኖር ቀርቶ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ አሜሪካኖች የሩዋንዳውን እልቂት የዝሆን ጆሮ ይስጠን ብለው ያለፉት በሶማሊያ ከአምስት ወራት በፊት ባጋጠማቸው ውርደት በመሸማቀቃቸው ምክንያት ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ነገር ግን ማንም የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ በጨረፍታ የታዘበ እንደሚመሰክረው ለአሜሪካውያን ሰብአዊ ጉዳዮች ከአፍአዊነት ያለፉ አጀንዳዎች ሆነው አያውቁም፡፡ ቢል ክሊንተን የአይሁዳውያን ፍጅት (holocoust) መዘክርን ከሩዋንዳው እልቂት ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ሲመርቁ ባደረጉት ንግግር፣ “የታሪኩን ከሃዲዎች እንታገላለን፤ ይህ ጉዳይ በፍጹም እንዳይደገምም ቃል እንገባለን” ብለው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሌላው  ቀርቶ በዚያ የሩዋንዳ ምድር ቁና በሆነችበት ሰዓት፣ የኋይት ሀውስ ፖለቲከኞች ‹ጄኖሳይድ› የምትለዋን ቃል እንኳን በጥንቃቄ ከአደባባይ አስወግደዋት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በተደጋጋሚ እንደታየው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላቅ ያሉ ታሪካዊ ኃላፊነቶቹን ለመወጣት ብቃቱም ተነሳሽነቱም ኖሮት አያውቅም፡፡ ከ1984 እስከ 1987 ዓ.ም. በቦሲኒያና በሰረብረንካ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለቁት የተመድ የታጠቁ ወኪሎች አፍንጫ ሥር ነበር፡፡ ምህረት የለሾቹ የሁቱ አራጆች አሜሪካ መራሹ ማኅበረሰብ የቦስኒያን ጭፍጨፋ ለማስቆም ያለመቻሉንና ሶማሊያንም እንደፍጥርጥሯ አራግፏት መሄዱን በጥንቃቄ ታዝበዋል፤ በቂ ተመክሮ ቀስመዋል፡፡ የጥፋት ዕቅዳቸውን በተግባር ለማዋል ከከንፈር መጠጣ ያለፈ ተቃውሞ እንደማይገጥማቸውም ተረድተው ነበር፡፡ የተመድ የሰብአዊ መብቶቸ ኮሚሽንም ሆነ ዓለም ዐቀፋዊና አሕጉራዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሩዋንዳ ጄኖሳይድ እየተፈጸመ መሆኑን ያሳወቁት ገና ከአንድ ዓመት በፊት ቢሆንም፣ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ 1986 ዓ.ም.  የኢንተርሐምዌና የኢምፑጋሙጋምቢ ሚሊሻዎች የደም አበላ ሲያጎርፉ ‹ሃይ!› ያላቸው አልነበረም፡፡ በወቅቱ የመንግሥታቱ የሰላም ኀይሎች የፈጸሙት ቅሌት የጥቂት ምዕራባውያንን ነፍስ ይዞ መፈርጠጥ ነበር፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ፈረንሣይና አሜሪካ በጉዳዩ ጣልቃ ለመግባት ሲገደዱም ቢሆን ያደረጉት ተጠቂዎቹን ከመታደግ ይልቅ ግፈኞቹ ወደ ዛየር እንዲያመልጡ መርዳት ነበር፡፡

ማድሊን ኦልብራይት ለመጀመሪያ ጊዜ ዘር ማጥፋቱን በአደባባይ ያመኑት በ1989 ዓ.ም. ሲሆን፣ በ1990 ዓ.ም. ደግሞ ክሊንተን በይፋ ለስህተቱ “ይቅርታ” ጠይቀዋል፡፡ ልብ ብሎ ለተመለከተው ነገሩ ተጨማሪ ለበጣ ይመስላል፡፡ በሩዋንዳ ፍጅት ወቅት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት አፍሪካዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ አንዳችም አዎንታዊ አስተዋጽኦ አላደረጉም፡፡ በወቅቱ የድርጅቱ ፀጥታ ማስከበር ኀላፊና በኋላም የተመድ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሌላው አፍሪካዊ ኮፊ አናንም ቢሆኑ እያንገራገሩ ጄኖሳይድ መፈጸሙን የተቀበሉት በ1991 ዓ.ም. ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ ዘግናኝ ስህተት ትምህርት የቀሰመ ወገን አልነበረም፡፡ በዳርፉር አሜሪካ አለወትሮዋ ቀድማ በ1996 ዓ.ም. “የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል” በማለት ስትጮህ፣ ኮፊ አናን ከማንገራገር አልፈው በ1997 ዓ.ም. ጭራሽ ድርጊቱ አለመፈጸሙን ገለጹ፡፡ የአውሮፓ ኅብረትም (ኋላ ቢቀበለውም) ሆነ የሰብአዊ መብቶች ጠባቂ ድርጅት ለቡሽ አስተዳደር ድጋፍ አልቸሩትም፡፡ በክፍለ ዓለሙ ደም እንደጅረት ሲፈስስ “የወሬ መደብር” ወይም “የአምባገነኖች ክበብ” ተብሎ የሚተቸው የአፍሪካ ሕብረት እንደ ልማዱ ከሕዝብ ግንኙነት ተውኔቶችና ከጣት ቅሰራ የዘለለ ኀላፊነቱን አልተወጣም፡፡ እንዲያውም በዳርፉር ጉዳይማ ዓለም ዐቀፉ ፍርድ ቤት በአልበሽር ላይ ያስተላለፈውን የእስር ትዕዛዝ በጣልቃ ገብነትና “በቀለም ትምክህተኝነት” ስም በማላከክ ድርጊቱን እስከማውገዝ ደርሷል፡፡ አሳፋሪ የበታችነት መገለጫ ሆኖ በታሪክ መዘከሩ አይቀርም፡፡

ከቅድመ መከላከሉና ጥቃት ከማስቆሙ ውድቀት ባልተናነሰ የድህረ ጭፍጨፋው የፍርድ ሂደትም ተስፋ አሰቆራጭ ነው፡፡ አንዱ ተግዳሮት ወንጀለኞቹ በሥልጣን ያሉ ወይም በተከታዩ መንግሥት ከለላ ያገኙ መሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አሮጌው የዌስትፋሊያ ግንዛቤ (1641 ዓ.ም.) ወይም የመንግሥታዊ ሉዓላዊነት መርህ መደበቂያ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ ለምሳሌ ከ1907-8 ዓ.ም. በመሐመድ ታላት የሚመራው የወጣት ቱርኮች አገዛዝ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ አርመኖችንና የተወሰኑ ግሪኮችንም አጥፍቷል፡፡ ይህን ወንጀል እስከዛሬም ድረስ ቱርክ ያልተቀበለችው ሲሆን፣ በምዕራቡ ዓለምም ቢሆን ይፋ ዕውቅና የተሰጠው ገና በቅርቡ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የፈረንሣይ ፓርላማ ድርጊቱ የዘር ማጥፋት ፍጅት መሆኑን እውቅና ሲሰጥ የፕሬዚዳንት (ያኔ ጠ/ሚኒስትር) ኤርዶዋን መንግሥት ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምቶ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

እውነትም ሂትለር በ1931 ዓ.ም ንግግሩ “አርመኖችን ማን ያስታውሳቸዋልና” ሲል ተንብዮ ነበር፡፡ ነገሩ “እኛም ለምንፈጽመው አይሁዳውያንን የማስወገድ እርምጃ ስጋት አይግባችሁ” ይመስላል፡፡ በ1951 እና በ1962 ዓ.ም. መካከል ወደ 1 ሺሕ ገደማ ናዚዎች በጦር ወንጀለኝነት ቢከሰሱም፣ ዕድሜ ይፍታህ የተፈረደባቸው ከመቶ ያነሱ ናቸው፡፡ በተከታዮቹ ዓመታትም ለፍርድ ከቀረቡ ወደ 6 ሺሕ ናዚዎች ውስጥ ተመሳሳይ ቅጣት የተፈረደባቸው 157 ብቻ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የናዚ ዳኞች በዘመናቸው “ፀረ ናዚ ቀልድ ቀልደሃል” በመሳሰሉ ቀላል ምክንያቶች ጭምር ወደ 26ሺህ ሰዎች በሞት የቀጡ ቢሆንም፣ አንዳቸውም ጥፋተኛ ሆነው አልተገኙም፡፡ በ1931 ዓ.ም. ለተፈጸመው “የናንኪንግ መደፈር” ለተሰኘውና የ300 ሺሕ ቻይናውያንን ሕይወት ለቀጠፈው ግፍ በሕግ ተፈርዶባቸው የተሰቀሉት ሰባት የጃፓን ወታደራዊ ባለሥልጣናት ብቻ ነበሩ፡፡

በተመሳሳይ የቦስኒያው ጭፍጨፋ መሪና አስተናባሪ ስሎቮዳን ሚሎሶቪች (በኋላ በኮሶቮ ጉዳይ እስኪጋለጥ) በ1987 የዴይተን ስምምነት በሠላም ሐዋሪያነት መወደሱ ታላቁ የዘመናችን ምፀት ነው፡፡ ሚሎሶቪች በሄግ ችሎት የተከሰሰው ‹‹በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ወንጀል በመፈጸም››  እንጂ በዘር ማጥፋት ፍጅት አልነበረም፡፡  በእስር ቤት ሕይወቱ እስኪያልፍ ድረስ በጄኖሳይድ ወንጀል ለመክሰስ የሚያስችል ማስረጃ ተሰብስቦ አላለቀም ነበር፡፡ የሌሎቹ የጥቂት ሰርብና ክሮአት ጄኔራሎች ጉዳይም በፍትሕ የመቀለድ ያህል ነበር፡፡ የሩዋንዳውም የፍርድ ሂደት ከፍተኛ ንትርክና መሰናክል የበዛበት በመሆኑ የተፈለገውን ያክል አልሄደም፡፡ ከነጆሴፍ ኮኒ የማይሻሉት እንደነ አልበሽር ያሉ ወንጀለኞች በዚሁ በመዲናችን ሳይቀር ደግሞ አሁንም በቀይ ስጋጃ አቀባበል እየተደረገላቸው ነው፡፡ ይህ የተስፈኛ ዘር አጥፊዎችን ልብ የሚያደነድንና አጥፍቶ ያለመጠየቅ ባህልን የሚፈጥር  ድርጊት በእጅጉ መወገዝ ይገባዋል፡፡ ኬኔት ካምፕቤል (2001፣ 2) እንደሚለው ዛሬም ቢሆን ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የዘር ማጥፋት ፍጅት ችግርን ለመፍታት እምብዛም ከቀድሞው የተሻለ ፖለቲካዊም ሆነ ድርጅታዊ መሰናዶና ቁርጠኝነት የለውም፡፡

ምን ይሻላል?

ታዲያ ዓለም ዐቀፍ አካላት ቁርጠኝነት የሚጎድላቸውና የየአገሩ ፖለቲከኞችም የዘር ማጥፋት ዝንባሌ ያላቸው ከሆነ ምን ሊደረግ ይችላል? ይህ የመጨረሻው አስቀያሚ ምስል ነው፡፡ ከዚህ በመለስ  የዘር ጥቃት ጉዳይ ተመራማሪዎች ከላይ በዘረዘርናቸው ባሕርያቱ ላይ የተመረኮዙ የአጭር ጊዜና ዘላቂ መፍትሔዎችን ይሰነዝራሉ፡፡ ይህም የችግሩ ምንጭም ሆነ የመፍትሔው ኀይል ውስጣዊ መሆኑን ከመገንዘብ ይጀምራል፡፡ ሰፊ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳዮችን እንደሚያቅፍ መረዳት ያሻል፡፡ እንደ ስስት፣ ፍርሃት፣ ምኞት፣ ጥላቻ፣ ስህተት የመሳሰሉ ሰብአዊ ባህርያት ለብዝበዛ የተጋለጡ መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ግጭቶች ከትናንሽ አካባቢያዊ ክስተትነት ወደ ሙሉ አቅም የጥፋት ዘመቻነት የሚያደርጉትን ሽግግርም በቅጡ መገንዘብ ይገባል፡፡

የዘር ጥቃትን የመከላከሉ አንዱና ቀዳሚው መንገድ ባለሙያዎች “የዘር ማጥፋት ሰንሰለት” (ጄኖሳይዳል ኮንቲነም) የሚሉት ሲሆን፣ ይህም ተራና ጤናማ በሚመስሉ ባሕርያትና ተቋማት የሚንጸባረቁ ታዳጊ በደሎችን ይመለከታል፡፡ በትምህርት ሥርዓትና በመገናኛ ብዙሃን የሚራገቡ ግልጽና ረቂቅ ቅስቀሳዎች፣ በፍትሕና ማኅበራዊ አገልግሎት፣ በሌሎችም መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት የሚፈጸሙ ክብረ-ነክ አስተምህሮዎችና ድርጊቶች የጥፋት መንስኤዎች መሆናቸውን መረዳት፣ እነዚህን ዝንባሌዎች በመለየት የሚያስተሳስራቸውን ሐረግ ለማወቅና ሕዝብንም ለማስተማር ነቅቶ መጠበቅ ያሻል፡፡

የሕዝብ ቁርሾንና ጥላቻን ለማስቀረት ጠንካራ ሥርዓትን ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም አክራሪ የሆነ የማንነት ፖለቲካን በእውነተኛና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተካት አማራጭ የማይገኝለት መፍትሔ ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት ለዘብተኞችና ሰላማዊ ፖለቲከኞች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው ጥረት ማድረግ ከዝነኛ/ጉልበተኛ መሪዎች የአደገኝነት ዝንባሌ ለመጠንቀቅ፣ አክራሪ ፖለቲከኞችና የጥቅም ስብስቦች በተቻለ መጠን ወደ ሥልጣን እንዳይወጡ ለመከላከል ወዘተ… ይረዳል፡፡

የብሔረሰብ ታሪከኞች እንደሚሉት በአገራችን የሚታዩት ትናንሽ ማኅበራዊ ግጭቶች የማይታረቅ  “ታሪካዊ ጠላትነት” ውጤቶች ሳይሆኑ፣ ነባራዊ ምክንያቶች ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ማስጨበጥ፣ ገንቢ መፍትሔዎችንም ማቅረብ ያሻል፡፡ ማኅበረሰቦች የጋራ ሠላም ለምርጫ የሚያቀርቡት ሳይሆን የህልውናቸው መሠረት መሆኑን ማስገንዘብ፣ ችግሮቻቸውን በጋራ የሚፈቱበትን መንገዶች ማዳበር፣ የጭካኔን ኢሰብአዊ ገጽታዎች ማሳየት፣ ንጹሐን ዜጎች በጥላቻ ቸርቻሪዎች ለጥፋት እንዳይጋበዙ ማንቃት  ያስፈልጋል፡፡  በዚህም አለ በዚያ ዘር ማጥፋት የዜሮ ድምር ርዕዮት፣ ለቆስቋሾቹም አትራፊ ሳይሆን የራስ-ተሸናፊነት ስልት ነው፡፡ ስለዚህም ሽብር ፈጣሪዎችና የአርማጌዶን ናፋቂዎች በፍትህ፣ በዴሞክራሲና በነጻነት ስም የሚያደሩትን የብጥብጥ ድር ነቅቶ መጠባበቅ፣ በምሁራዊ ምርምር ሽፋን የሚያሰራጩትን የፈጠራ ታሪካቸውን እየተከታተሉ እጅ በጅ ማፍረስ የእያንዳንዱ ቅን አሳቢ ዜጋ ግዴታ ነው፡፡

 

April 13, 2021

About Author

admin


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *