“ምሁር” የሚለው ቃል ትርጉሙ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ሁሉንም የሚያስማማ ትርጉም ማግኘትም ያስቸግራል፡፡ ብዙ ሰዎች የጻፉበት ርእሰ ጉዳይም ነው፡፡ ለምሳሌ በእኛ አገር ምሁርነት በተለምዶ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ዲፕሎማ ዲግሪ ከማግኘት ጋር ይያያዛል፡፡ ይህ አመለካከት ግን ብዙ ርቀት አያስኬድም፡፡
አንቶኒዮ ግራምሺ (Antonio Gramsci) የተባለው ጣሊያናዊ ፈላስፋ ‹‹ምሁር ማት ልክ እንደ መደብ ራሱን ችሎ የቆመ ሳይሆን ወደ ሥልጣን ከሚመጣ ማኅበራዊ ቡድን/መደብ (Social group) ጋር አብሮ የሚመጣ ሆኖ የሚመጣውን ቡድን ርዕዮት የሚያቀናብርለት ነው›› ይለዋል፡፡ ‹‹ሁሉም ሰው ምሁር ነው›› ይላል ግራምሺ፡፡ ሁሉም ሰው እምነት አለው፤ ሁሉም ሰው ባህል አለው፤ እያንዳንዱ ሰው የዓለም አተያይ፣ ፍልስፍና ወዘተ. አለው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ምሁር ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው የምሁር ሥራ አይሠራም፡፡ የምሁር ሥራ የሚሠሩት ግራምሺ ‹‹ኦርጋኒክ ምሁራን›› (Organic Intellectuals) የሚላቸውና በቁጥርም ትንሽ የሆኑትን ነው፡፡
ከላይ እንደጠቀስነው እነኝህ ምሁራን ሥርዓቱን ምንነት የሚቀርጹ፣ የሥርዓቱን ጠቅላላ አካሄድ (በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ ወዘተ. መስክ) የሚተልሙና አቅጣጫ የሚያስቀምጡ ናቸው፡፡ እንግዲህ ምሁርነት በከፍተኛ ደረጃ ከመማር ጋር ሳይሆን ከምትሠራው ሥራ ጋር ነው የሚያያዘው፡፡ ለምሳሌ፣ የፖለቲካ ፓርቲን ሥራ የወሰድን እንደሆነ ምሁራኑ የፓርቲውን ርዕዮተዓለም፣ አደረጃጀት ወዘተ. የመቅረጽ ሥራ ነው የሚሠሩት፡፡
እንዳልኩት ጉዳዩ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ወደ አፍሪካም የመጣን እንደሆነ በርካታ ምሁራን በተለይ እንደ ‹‹ኮደስሪያ›› (CODESRIA) ባሉ ድርጅቶች አማካይነት፤ ፕሮፌሰር ዓሊ ማዙሪ፣ መሐሙድ ማምዳኒና ታንዲካ ማከንዋሬን የመሳሰሉ አፍሪካዊ ምሁራን ብዙ የጻፉበት ጉዳይ ነው፡፡ ዓሊ ማዙሪ ለምሳሌ፣ ‹‹ምሁር ማለት በሐሳብ ‹‹ኢንስፓየርድ›› የሚሆን፣ ሐሳብ የሚያፈልቅና ከዚያ ሐሳብ ተነስቶ ለመወያየትና ለመከራከር ዝግጁ የሆነ፣ የኅብረተሰብ ጥያቄዎችን አንስቶ ለመወያየትና ለመከራከር የተዘጋጀ ነው›› ይላል፡፡ ምናአልባት ከዚህ ጋር አያይዘን ልናነሳው የሚገባው ‹‹የአደባባይ ምሁር›› (Public Intellectual) የሚባለውን ነው፡፡ የአደባባይ ምሁር በዩኒቨርሲቲ ወይ በሌላ የጥናትና ምርምር ተቋም እንደሚሠራው ምሁር በከፍተኛ ደረጃ የተማረ ነገር ግን ደግሞ ከዚያም አልፎ የእውነት ጉዳዮችን፣ የፍትሕ ጉዳዮችን፣ የዕሴት ጉዳዮችን፣ የሞራል ጉዳዮችን አንስቶ ‹‹ትክክል ነው›› ብሎ ያመነበትን ነገር ወደ አደባባይ ይዞ የሚወጣ ነው፡፡ ጉዳዩ መቆርቆርን ይጠይቃል፡፡ የአደባባይ ምሁር በኅብረተሰቡ ወስጥ የሚያያቸውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የፍትሕ ወዘተ. ችግሮች ዝም ብሎ ማለፍ አይችልም፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ‹‹ይኼ ነገር ትክክል አይደለም፤ እንደዚህ ነው መሆን ያለበት›› እያለ የኅብረተሰቡ ዓይንና ጆሮ ሆኖ የሚመክርና ጥብቅና የሚቆም ነው፡፡
የምሁራን ኀላፊነት
***
ትምህርት መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ ትምህርት ደግሞ ሰውን እንዲጠይቅና እንዲመረምር ማስቻል አለበት፡፡ ‹‹ያለንበት ሁኔታ ምክንያታዊ ነው ወይ? ያለንበት ሁኔታ ተቀባይነት አለው ወይ? ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎችንና አስተሳሰቦችን የማመንጨት ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ኅብረተሰቡን ለማገልገል ተቋማት የተቋቋሙለትን ዓላማ እየፈጸሙና እያስፈጸሙ ነው ወይ? አኗኗራችን ለእኛ ተቀባይነት ያለው ነው ወይስ ከላይ ነው የተጫነበን?›› የሚሉትን ጥያቄዎች የመጠየቅ ጉዳይ ነው፡፡
እንግዲህ ይህ ጉዳይ እኛ ብዙ ጊዜ የምንወቀስበት ነገር ነው፡፡ በእኔ ግምት ወቀሳውም አግባብነት አለው፡፡ በዩኒቨርሲቲ አካባቢ ያለነውም ሆነ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ዝምታን ነው የምንመርጠው፡፡ ዝምታው ደግሞ ከፍራቻ የተወለደ ነው፡፡ መንግሥት ዜጎች በነጻነት የሚሠሩበትን ሁኔታ ስለማይፈጥር ኅብረተሰባችን በፍራቻ የታጠረ ነው፡፡ ዝምታውና ፍራቻው ግን ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን ከምሁራን የማይጠበቅም ነው፡፡ በእርግጥ በምሁራኑ ላይ መፍረድ ትንሽ ያስቸግራል፡፡ በአንድ በኩል የመኖርና የመሥራት ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን አካሄዱ ማንኛውንም ዓይነት ችግር ተቀብሎ የመኖርን ሁኔታ ስለሚፈጥር በጣም አደገኛ ነው፡፡ በመሠረቱ ዝምታ ብልህነትም አይደለም፤ ደፋርነትም አይደለም፡፡ ለአገርም ሆነ ለራሱ ለምሁሩ የሚበጀው አይደለም፡፡
በዚህ ረገድ በአፍሪካም ደረጃ ያየን እንደሆነ ብዙ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ከቅኝ አገዛዝ ማብቃት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ተስፋና መነቃቃት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በብዙ የአፍሪካ አገራት የተከሰተው መንሸራተት በምሁራኑ ላይ ከፍተኛ በትር ነው ያሳረፈው፡፡ በአገራችንም ብናይ ለምሳሌ ይህን ዩኒቨርሲቲ ያየን እንደሆነ በንጉሡ ጊዜ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ውይይት፣ ክርክርና ንቅናቄ የሚካሄድበት ቦታ ነበር፡፡ የውይይት መድረኮች ነበሩ፡፡ ልዩ ልዩ ማኅበራት፣ ጋዜጦችና መጽሔቶችም ነበሩ፡፡ የንጉሡን አገዛዝ ለመቃወምም ብዙ ንቅናቄዎችና እንቅስቃሴዎች ይደረጉ ነበር፡፡ ሆኖም ከአብዮት በኋላ በተለይ የደርግ አገዛዝ ባሳረፈው በትር ብዙ ሰው ሞተ፤ ብዙ ሰው ተሰደደ፤ የተረፈው ደግሞ ዝምታን እንዲመርጥ ተገደደ፡፡ ከደርግ መውደቅ በኋላም የተሻለ ሁኔታ ይመጣል የሚለው ተስፋ በተለይ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን መባረር ጋር ተያይዞ መሸማቀቅና ፍራቻን አባባሰ፡፡
በአጠቃላይ ያለፉትም ሆነ ያሉት ሁኔታዎች ምሁሩ ከፍተኛ በሆነ መቀዛቀዝ እና ፍርሃት ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል፡፡ እንዳልኩት ያለፉትም ሁኑ ያሉት ሁኔታዎች ከባድ ትምህርት ስለሰጡት ሰው ይፈራል፡፡ ነገር ግን ዝምታ ለትንሽ ጊዜ ስትራቴጂ ሊሆን ይችል እንደሆነ ነው እንጂ ለዘላለሙ በፍራቻና በዝምታ መቀመጡ መፍትሔ አይመጣም፡፡ የምሁር ግዴታና መብት መሆን ያለበት ሚናውን መጫዎት ነው፡፡ ‹‹ያለንበት ሁኔታ ምክንያታዊ ነው ወይ? የሚገባን ነው ወይ?›› እያሉ መጠየቅ ግዴታም መብትም ነው፡፡ ምሁራን በተገኘው መድረክ ሁሉ ‹‹መኖር ያለብን በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው ወይ?›› ብለው መጠየቅ አለባቸው፡፡
ለነገሩ መታወስ ያለበት የአፍሪካውያን ምሁራን ከውስጥ ከአገዛዝ ጋር ብቻ አይደለም ተጽዕኖ የሚደርስባቸው፡፡ ዓለም ዐቀፋዊ ሁኔታውም ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በአገር ውስጥ ነጻነት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ለጥናትና ምርምር የሚመደበው በጀት ውሱን ስለሚሆን፣ ምሁራን ወደ ውጭ እንዲመለከቱ ይገደዳሉ፡፡ የውጭ አካላት (መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች) ደግሞ ምሁራኑን ወሳኝ በሆነው የጥናትና ምርምር ዘርፍ ማለትም በ‹‹ቤዚክ ሪሰርች›› አያሳትፏቸውም፡፡ ከዚያ ይልቅ በኮንሰልታንሲ ሥራዎች ይጠምዷቸዋል፡፡ የምሁር ሥራ በቤዚክ ጥናትና ምርምር ዕውቀት ማመንጨት መሆኑ ቀርቶ በኮንሰልታንሲ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ጥቅማ ጥቅሞችን መሰብሰብ እየሆነ ነው፡፡
ምሁራን ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የተለየ ኃላፊነት አለባቸው?
***
በእኔ አስተያየት ምሁራን የተለየ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ ከማወቃቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የአገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ብናይ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች ናቸው የመሬት ላራሹንና ሌሎችን የፍትሕ ጥያቄዎች በተደራጀ መልኩ አንስተው የታገሉት፡፡ በአርግጥ አርሶ አደሩም በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች ሲታገል ቆይቷል፡፡ ሆኖም ትግሉን በሥነ ሥርዓት ያቀናበረውና ወደአደባባይ እንዲወጣ ያደረገው ምሁሩ ነው፡፡ ስለዚህ ምሁሩ ያስተማረውን ኅብረተሰብ ችግሮች የማንሳት ኃላፊነትም የሞራል ግዴታም አለበት፡፡
ኅብረተሰብንና አገርን የሚጎዱ ነገሮችን አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ምሁራዊ ግዴታንና ኃላፊነትን አለመወጣት ነው፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ፍርሃትና ዝምታን የሚጋብዙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ፍራቻ የትም አያደርስም፡፡ ለሕዝብም ለመንግሥትም ለአገርም አይጠቅምም፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት የመንግሥትና የዩኒቨርሲቲዎች ግንኙነት ነው፡፡ እንግዲህ ቀደም ብየ እንደጠቀስኩት በዩኒቨርሲቲዎች በተለይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው ከፍተኛ እንቅስቃሴዎቸ የነበሩት፡፡ ከንጉሣዊ አገዛዙ መውደቅ ጋር ተያይዞ በመንግሥትና በዩኒቨርሲቲው መካከል ያለው ግንኙነት በጥርጣሬና አለመተማመን የተመሠረተ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመካከላችን ጥርጣሬና አለማመን አለ፡፡አንዱ በአንዱ ላይ ጣት የመጠቆም ሁኔታዎች አሉ፡፡ የሆነ ሆኖ መንግሥትም ዩኒቨርሲቲዎች የሚገነባውና ትምህርት የሚያፋፋው ለአገር ነው፡፡ ምሁሩም የሚያስተምረው፣ በልዩ ልዩ ዘርፎች ጥናትና ምርምር የሚያደርገውና ዕውቀት የሚያመነጨው ለዚህች አገር ነው፡፡ ስለዚህ በእኔ እምነት ግንኙነቱ ጣት ከመጠቋቆም ማለፍ መቻል አለበት፡፡ መንግሥት በኅብረተሰቡ ሀብት ተጠቅሞ መልሶ ለኅብረተሰቡ የሚያገለግሉ የትምህርት መስጫ ድርጀቶችን ይገነባል፤ የትምህርት ሥርጭትን ያስፋፋል ወዘተ. ምሁሩ በበኩሉ ዕውቀት በማመንጨት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማሳደግ ወዘተ. ከፍተኛ ሚና ይጫዎታል፡፡ ከዚያም በላይ ምሁሩ የኅብረተሰቡ ኅሊና (Moral Consciense) ስለሆነ ነገሮችን ቀድሞ በመመርመር መንገዱን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ግን ነጻነት ያስፈልገዋል፡፡
ስለሆነም ምሁሩ በነጻነት የሚያስብበትን ከባቢ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ምሁር ስለመሠረታዊ ፍላጎቶቹ – ስለሚበላው፣ ስለሚጠጣው ወዘተ. መጨነቅ የለበትም፡፡ ከዚህ በላይ ግን ለምሁሩ የሚያስፈልገው በነጻነት የሚያስብበትን ሁኔታ መፍጠር ወይም ማመቻቸት ነው፡፡
በእርግጥ ነጻነት ሲባል ደግሞ ከኃላፊነት ጋር ነው፡፡ የኅብረተሰቡን ዕሴቶች፣ የኅብረተሰቡን ወግ፣ ባህል ወዘተ. አክብሮና ጠብቆ በሚሠራው ምርምርና በሚያመነጨው ሐሳብ ደግሞ ይህ ይደርስብኛል ብሎ ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ የሚያስብበትን ከባቢ መፍጠር በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ምን ልብላ? ምን ልጠጣ? ምን ልልበስ? ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይ ምን ብጽፍ ምን ችግር ይደርስብኝ ይሆን? እያለ እየፈራና እየተሸማቀቀ የሚኖር ምሁር ለአገር የሚጠቅም ዕውቀት ያመነጫል ማለት ያስቸግራል፡፡ ነጻነት በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡
ምሁራንና መንግሥታት በኢትዮጵያ
***
በምሁራኑና በአገዛዞች ብቻ ሳይሆን በምሁራኑ በራሳቸው መካከልም ክፍፍል እንዳለ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም አገዛዞች ምሁራኑን ይይዛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በአገራችን እንኳን ብናይ ደርግም የራሱ ምሁራን ነበሩት፤ ኢሕአዴግም የራሱ ምሁራን አሉት፡፡ የአገዛዝ መሣሪያ የሚሆኑ በየትኛውም ሥርዓት ይኖራሉ፡፡ የሚያማክሩ፣ ሕጉን የሚጽፉ ወዘተ. ነበሩ፤ አሁንም አሉ፡፡ የአገዛዙ አካል ሆነው አገዛዙ ችግር ሲፈጥር ወይም ወደተሳሳተ ጎዳና ሲሄድ ምን ያህል በነጻነት ደፍረው ሐሳብ ይሰጣሉ? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ለማንኛውም እኔ ያነሳሁት በመንግሥትና በዩኒቨርሲቲ አካባቢ በሚሠሩት ምሁራን መካከል ያለውን ግንኙነት ነው፡፡
ከፓርቲ ተግባራት ርቀውና ነጻነታቸውን ጠብቀው በዩኒቨርሲቲም ይሁን በሌላ የጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ የሚሠሩትንና አገዛዙን ጠንከር ባለ መልኩ (ክሪቲካሊ) የሚመለከቱትን ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ ያለመግባባት ምንጩ ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ የፖለቲካ ሥርዓቱን ብናነሳ፣ ዴሞክራሲ በየአገሩ እንዴት እንደሚሠራ እናውቃለን፡፡ ምን ያህል ከባህሉና ከእውነታው ጋር እንዳልተዛመደም እናውቃለን፡፡ መንግሥታት እንግዲህ ዕቅዶች ያወጣሉ፡፡ ያወጧቸውን ዕቅዶች ደግሞ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ምሁሩ ደግሞ እንደ ኅብረተሰብ ኅሊናነቱ ‹‹ይህ ነገር ትክክል አይደለም፤ ወይም እንዲህ ነው መሆን ያለበት›› ይላል፡፡ ያን ጊዜ ግጭት ይፈጠራል፡፡
እንዳልኩት ከ1960ዎቹ ጀምሮ የዩኒቨርሲቲዎችና የአገዛዞች ግንኙነት በጥርጣሬና አለመተማመን የተመሠረተ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችን የአመጽ ምንጭና የተቃውሞ ማዕከል አድርጎ የማቅረብ ሁኔታ አለ፡፡ መሆን ያለበት ግን ለምሁራን የሚያስተምሩበት፣ የሚመራመሩበትና ሐሳብ የሚያፈልቁበት ነጻ የሆነ ከባቢ መፍጥር ነው፡፡ ሐሳብ አምንጭተው የሚያሰራጩበት ዴሞክራቲክ የሆነ ሁኔታ ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡
ዕውቀት ሊመነጭ የሚችለው በነጻ ከባቢ ውስጥ ነው፡፡ ምሁራን ምርምር እንዲያደርጉ ነጻነት መስጠት፣ የምርምር ውጤታቸውን የፖሊሲ ግብዓት ማድረግ እና ለምርምሩ ደግሞ አስፈላጊውን (የሚቻለውን) ገንዘብ መመደብ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ጥናታዊ ሥራዎች የማይጠቅሙ ሆነው ሳይሆን ባለው የግንኙነት ችግር ምክንያት ጥቅም ላይ ሳይውሉ እየቀሩ ነው፡፡ ምሁራን አገር ሀብቶች ስለሆኑ ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡
Leave a Reply